-
“መጨረሻው” ምን ማለት ነው?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ግንቦት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጨረሻው ቀርቧል?
“መጨረሻው” ምን ማለት ነው?
“መጨረሻው ቀርቧል” የሚሉትን ቃላት ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ ይዞ መድረክ ላይ እየተወራጨ የሚደነፋ ሰባኪ ነው? ወይስ የመዓት ቀን ቀርቧል የሚል ምልክት ይዞ በመንገድ ማዕዘን ላይ የቆመ ረጅም ቀሚስ የለበሰና ወገቡን የታጠቀ ጢማም አረጋዊ ሰው? አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ሲያስቡ ጭንቀት ይለቅባቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ጥርጣሬ ያድርባቸዋል አሊያም ያሾፋሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ “መጨረሻው ይመጣል” በማለት ይናገራል። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ጊዜ “[የአምላክ] ታላቅ ቀን” እና “አርማጌዶን” ተብሎም ተጠርቷል። (ራእይ 16:14, 16) እውነት ነው፣ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የሚሰጡት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሰዎችን ግራ ያጋባሉ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለማመን የሚከብዱና ብሩህ ተስፋ የማይሰጡ አስተሳሰቦችም ተስፋፍተዋል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻውን ቀን በተመለከተ የሚናገረው ነገር ግልጽ ነው፤ መጨረሻው ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ምን ማለት እንዳልሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም የአምላክ ቃል መጨረሻው ቅርብ መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል። ከሁሉ በላይ ግን መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው ሲመጣ በሕይወት መትረፍ የሚቻልበትን መንገድ ያስተምረናል! እስቲ መጀመሪያ ግን መጨረሻውን በተመለከተ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለይተን ለማወቅና ትርጉሙን ለመረዳት እንሞክር። ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር “መጨረሻው” ሲባል ምን ማለት ነው?
መጨረሻው ሲባል ምን ማለት አይደለም?
መጨረሻው ምድር ተቃጥላ የምትጠፋበት ታላቅ የጥፋት ቀን አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 104:5) ይህንን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥቅሶች አምላክ ምድርን እንደማያጠፋት፣ እንድትጠፋም እንደማይፈቅድ ያረጋግጡልናል!—መክብብ 1:4፤ ኢሳይያስ 45:18
መጨረሻው የተወሰነለት ጊዜ የሌለው በአጋጣሚ የሚከሰት ነገር አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው አምላክ ጊዜ የወሰነለት ነገር እንደሆነ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማርቆስ 13:32, 33) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ (“አብ”) መጨረሻው እንዲጀምር የሚያደርግበትን ‘የተወሰነ ጊዜ’ ቀጥሯል።
መጨረሻው በሰዎች ወይም ከጠፈር በሚወረወሩ ናዳዎች ምክንያት የሚቀሰቀስ አይደለም።
መጨረሻው እንዲጀምር የሚያደርገው ምንድን ነው? ራእይ 19:11 “እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር። በእሱም ላይ የተቀመጠው ‘ታማኝና እውነተኛ’ ተብሎ ይጠራል” ይላል። በመቀጠልም ቁጥር 19 እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።” (ራእይ 19:11-21) እዚህ ጥቅስ ላይ ያሉት አብዛኞቹ አገላለጾች ምሳሌያዊ ቢሆኑም አምላክ ጠላቶቹን ለመደምሰስ የመላእክትን ሠራዊት እንደሚልክ መረዳት እንችላለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው የሚናገረው ነገር ምሥራች እንጂ መጥፎ ዜና አይደለም
መጨረሻው ሲባል ምን ማለት ነው?
የሰብዓዊ መንግሥታት መጨረሻ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” (ዳንኤል 2:44) ቀደም ብሎ በሦስተኛው ተራ ቁጥር ላይ እንደተገለጸው “በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት” የተሰበሰቡት “የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው” ይጠፋሉ።—ራእይ 19:19
የጦርነት፣ የዓመፅና የፍትሕ መዛባት መጨረሻ ይሆናል።
አምላክ “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (መዝሙር 46:9) “በምድር ላይ የሚኖሩት ቅኖች ብቻ ናቸውና፤ በእሷም ላይ የሚቀሩት ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። ክፉዎች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፤ ከዳተኞችም ከእሷ ይወገዳሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ።”—ራእይ 21:4, 5
አምላክንም ሆነ ሰዎችን ማስደሰት ያልቻሉ ሃይማኖቶች መጨረሻ ይሆናል።
“ነቢያቱ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ ካህናቱም በራሳቸው ሥልጣን በኃይል ይገዛሉ። . . . ይሁንና መጨረሻው ሲመጣ ምን ታደርጉ ይሆን?” (ኤርምያስ 5:31) “በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23
የዚህን ሥርዓት አመለካከት የሚያራምዱና የሚደግፉ ሰዎች መጨረሻ ይሆናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ።” (ዮሐንስ 3:19) መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ሰው በነበረው በኖኅ ዘመን ስለተከሰተው ዓለም አቀፍ ጥፋት ይገልጻል። “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም . . . ጠፍቷል። ይህም የሆነው መላዋ ምድር በውኃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ነው። ሆኖም በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።”—2 ጴጥሮስ 3:5-7
መጪው “የፍርድ ቀን” እና ‘ጥፋት’ በኖኅ ዘመን ከደረሰው “የዓለም” ጥፋት ጋር እንደተመሳሰለ ልብ በል። በኖኅ ዘመን የጠፋው የትኛው ዓለም ነበር? ፕላኔቷ ምድራችን አልጠፋችም፤ የጠፉት የአምላክ ጠላቶች ይኸውም “ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች” ነበሩ። በተመሳሳይም በመጪው የአምላክ “የፍርድ ቀን” የሚጠፉት የአምላክ ጠላቶች ለመሆን የመረጡ ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የአምላክ ወዳጆች ልክ እንደ ኖኅና እንደ ቤተሰቡ ከጥፋቱ ይተርፋሉ።—ማቴዎስ 24:37-42
አምላክ ክፉዎችን ሁሉ ካስወገደ በኋላ ይህች ምድር እንዴት ያማረች እንደምትሆን አስብ! በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው የሚናገረው ነገር ምሥራች እንጂ መጥፎ ዜና አይደለም። ያም ሆኖ ‘መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ይነግረናል? በቅርቡ ይመጣ ይሆን? ከመጨረሻው ቀን በሕይወት መትረፍ የምችለውስ እንዴት ነው?’ እያልክ ታስብ ይሆናል።
-
-
መጨረሻው ቀርቧል?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ግንቦት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
መጨረሻው ቀርቧል?
አምላክ፣ ሰዎች አንዳቸው ሌላውን እየገዙና የሰውን ዘር ሕልውና ስጋት ላይ እየጣሉ እንዲቀጥሉ ይፈቅድላቸዋል? አይፈቅድላቸውም፤ ምክንያቱም እስካሁን እንዳየነው ለብዙ መቶ ዘመናት የቆየውን መከራና ጭቆና ወደ ፍጻሜ ለማምጣት እርምጃ ይወስዳል። የሰዎችና የምድር ፈጣሪ ይህን እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን አንተም እንድታውቅ ይፈልጋል። ታዲያ ይህን እንድታውቅ የሚያደርገው እንዴት ነው?
እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ ከዚህ ቀደም ሄደህ ወደማታውቅበት ቦታ በመኪና ከመጓዝህ በፊት ኢንተርኔት ላይ የምታገኛቸውን የመረጃ ምንጮች፣ ካርታዎችንና በጽሑፍ የተዘጋጁ አቅጣጫ ጠቋሚዎችን ትመለከት ይሆናል። ከዚያም አቅጣጫ ጠቋሚዎቹ ላይ የተገለጹትን ምልክቶችና መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች ስታይ ወዳሰብክበት ቦታ እየተቃረብክ እንደሆነ ይሰማሃል። በተመሳሳይም አምላክ ጉልህ ስለሆኑ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሚገልጸውን ቃሉን ሰጥቶናል። ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸውን እነዚህን ክስተቶች በምናይበት ጊዜ ወደ መጨረሻው በጣም እንደቀረብን እርግጠኞች እንሆናለን።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሁኔታ እንደሚከሰትና ይህም በመጨረሻው ቀን እንደሚደመደም ይናገራል። በዚህ ወቅት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይተው የማያውቁ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችና ሁኔታዎች ይታያሉ። እስቲ በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱትን አንዳንድ የመጨረሻው ቀን ገጽታዎች እንመልከት።
1. ዓለም አቀፍ ብጥብጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የተመዘገበው ትንቢት በምድር ላይ የሚፈጸሙ ክስተቶችን ይዘረዝራል፤ እነዚህ ክስተቶች የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ምልክት ክፍል ናቸው። ይህ ምልክት “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሆነውን ጊዜ ለይቶ የሚያመለክት ሲሆን ወደ “መጨረሻው” የሚመራ ይሆናል። (ቁጥር 3, 14) እነዚህ የምልክቱ ገጽታዎች ጦርነቶችን፣ የምግብ እጥረትን፣ በተለያየ ስፍራ የሚከሰት የምድር ነውጥን፣ የክፋት መብዛትን፣ የፍቅር መጥፋትንና የሃይማኖት መሪዎች ሰዎችን ለማሳሳት የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ያካትታሉ። (ቁጥር 6-26) እርግጥ ነው፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች ባለፉት መቶ ዘመናት ሲፈጸሙ የነበሩ ናቸው። ይሁን እንጂ መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ እነዚህ ክስተቶች በሙሉ በአንድ ዘመን ውስጥ ይፈጸማሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ሦስት ምልክቶች በዚያ ዘመን ውስጥ ይፈጸማሉ።
2. የሰዎች ባሕርይ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፍጻሜው የሚመሩትን ‘የመጨረሻ ቀናት’ ለይተው ከሚያሳውቋቸው ነገሮች አንዱ የሰዎች ባሕርይ መበላሸቱ እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) እርግጥ ነው፣ በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች አክብሮት የሚባል ነገር የሌላቸው መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም፤ ይሁንና የሰዎች ባሕርይ ከላይ የተዘረዘረው ዓይነት ሁኔታ ላይ የሚደርሰው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ዘመን “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ” ብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው። ታዲያ የሰዎች ባሕርይ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን አስተውለሃል?
3. ምድር እየተበላሸች ነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን የሚያጠፋበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ራእይ 11:18) ሰዎች ምድርን እያበላሹ ያሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ኖኅ የኖረበት ዘመን ከዚህ ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ተገልጿል፦ “ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር።” በመሆኑም አምላክ ያንን ብልሹ ኅብረተሰብ አስመልክቶ ሲናገር ‘አጠፋቸዋለሁ’ ብሏል። (ዘፍጥረት 6:11-13) አንተስ ምድር በዓመፅ እየተሞላች እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን አስተውለሃል? በተጨማሪም ሰዎች በታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጊዜ ላይ ይኸውም በምድር ላይ ያለውን ሰብዓዊ ሕይወት በሙሉ ቃል በቃል ጠራርገው ማጥፋት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህን ማድረግ የሚያስችል መሣሪያ አላቸው። ምድር በሌላም መንገድ እየተበላሸች ነው። የሰው ልጆች ምድርን በአግባቡ ባለመያዛቸው ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ማለትም የምንተነፍሰው አየር፣ የእንስሳትና የዕፀዋት ሥነ ምህዳር እንዲሁም ውቅያኖሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሹ ነው።
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ከመቶ ዓመት በፊት የሰው ልጅ ራሱን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የሚያስችል ኃይል ነበረው?’ አሁን ግን ሰዎች በጣም የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን በማከማቸትና ከባቢ አየርን በማበላሸት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው እያሳዩ ነው። በቴክኖሎጂ መስክ እየታየ ያለው ፈጣን እድገት የሚያስከትለው መዘዝ ከሰዎች የመረዳት ችሎታ በላይ ወይም ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆነ ይመስላል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የምድርን የወደፊት ዕጣ መወሰንም ሆነ መቆጣጠር አይችልም። በዚህ ምድር ላይ ያለው ሕይወት በሙሉ ከመጥፋቱ በፊት አምላክ ምድርን እያጠፉ ያሉትን ለማጥፋት ጣልቃ ይገባል። አምላክ እንዲህ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል!
4. ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አንድ ሥራ እንደሚከናወን በትንቢት ተነግሯል፤ ይህ ደግሞ የመጨረሻው ቀን ምልክት ሌላው ገጽታ ነው፤ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ የስብከት ዘመቻ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ካደረጉት ጥረት የተለየ ነው። በመጨረሻዎቹ ቀናት “የመንግሥቱ ምሥራች” ይሰበካል። ይህን መልእክት የሚያሳውቅ ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ የምታውቀው ሃይማኖታዊ ቡድን አለ? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚሰብኩ ይመስላሉ፤ ይሁንና እነዚህ ሰዎች የስብከት እንቅስቃሴያቸው በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ነው? ወይስ ይህን ምሥራች “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” ያውጃሉ?
የአምላክ መንግሥት በመላው ዓለም በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው
www.pr2711.com የተባለው ድረ ገጻችን ‘በመንግሥቱ ምሥራች’ ላይ ያተኮረ ነው። በድረ ገጹ ላይ ይህን መልእክት የያዙ ጽሑፎችን ከ700 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል። ከይሖዋ ምሥክሮች ሌላ እንዲህ ባለ ዓለም አቀፍ ደረጃ የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ ተነሳሽነት ያለው ሌላ ቡድን ታውቃለህ? ኢንተርኔት ሥራ ላይ ከመዋሉ ከረጅም ጊዜ በፊትም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለማሰራጨት በሚያደርጉት ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተው ነበር። ከ1939 አንስቶ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሽፋን ላይ “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉት ቃላት ሲወጡ ቆይቷል። ስለ ሃይማኖቶች የሚናገር አንድ መጽሐፍ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ “በፍጥነቱም ሆነ በስፋቱ ተወዳዳሪ የሌለው” እንደሆነ ገልጿል። የስብከቱ ሥራ ትኩረት የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት በሚወስደው እርምጃ አማካኝነት በቅርቡ ‘መጨረሻው እንደሚመጣ’ በሚገልጸው ምሥራች ላይ ነው።
በዓለም ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሆነው ጊዜ
በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹት አራት የምልክቱ ገጽታዎች በአንተ የሕይወት ዘመን ውስጥ ሲፈጸሙ ተመልክተሃል? ይህ መጽሔት ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ለአንባቢዎቹ፣ የምንኖረው መጨረሻው በቀረበበት ጊዜ ላይ እንደሆነ ራሳቸው ማረጋገጥ እንዲችሉ ለመርዳት የዓለምን ክስተቶች በተመለከተ መረጃዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ተጠራጣሪዎች የቀረቡት እውነታዎችና አኃዛዊ መረጃዎች በግል ስሜት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑና እንደግለሰቡ አመለካከት ሊተረጎሙ እንደሚችሉ በመናገር ማስረጃውን አይቀበሉም። በተጨማሪም የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ የሄዱ የሚመስሉት ዓለም አቀፍ የመገናኛ መንገዶች እየተስፋፉ ስለመጡ እንደሆነ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አንድ ልዩ ዘመን በሚደመደምበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።
አንዳንድ ባለሙያዎች በዚህች ምድር ላይ ከፍተኛ ለውጦች ወደሚካሄዱበት ጊዜ እየተቃረብን እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2014 ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው ጋዜጣ ላይ የሳይንስና ደህንነት ቦርድ ያወጣው ጽሑፍ የተባበሩት መንግሥታትን የፀጥታ ምክር ቤት በሰው ዘር ሕልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደተጋረጠበት አስጠንቅቆ ነበር። እነዚህ የሳይንስ ሊቃውንት እንዲህ ብለዋል፦ “በሰው ዘር ሕልውና ላይ የተጋረጡ ስጋቶችን አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ሥልጣኔን ስጋት ላይ የሚጥሉ ቴክኖሎጂያዊ አደጋዎች እየጨመሩ ሄደዋል ብለን እንድንደመድም አድርጎናል።” ብዙ ሰዎች በዓለም ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሆንን ይናገራሉ። የዚህ መጽሔት አዘጋጆችና አንባቢዎች ይህ ልዩ ወቅት በእርግጥም የመጨረሻው ቀን እንደሆነና መጨረሻውም ቅርብ እንደሆነ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የላቸውም። የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራት ይልቅ የመጨረሻው ቀን በሚያመጣው ውጤት ልትደሰት ትችላለህ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከመጨረሻው ቀን በሕይወት መትረፍ ትችላለህ!
-
-
ብዙዎች ከመጨረሻው ቀን በሕይወት ይተርፋሉ—አንተም መትረፍ ትችላለህመጠበቂያ ግንብ—2015 | ግንቦት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጨረሻው ቀርቧል?
ብዙዎች ከመጨረሻው ቀን በሕይወት ይተርፋሉ—አንተም መትረፍ ትችላለህ
መጽሐፍ ቅዱስ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ . . . ታላቅ መከራ ይከሰታል። እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልዳነ ነበር” በማለት በመጨረሻው ቀን ጥፋትም እንደሚኖር ይነግረናል። (ማቴዎስ 24:21, 22) ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከጥፋት እንደሚተርፉ አምላክ ቃል ገብቷል፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17
አንተስ ይህ ዓለም ሲያልፍ በሕይወት ተርፈህ ‘ለዘላለም መኖር’ የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለክፉ ቀን መጠባበቂያ የሚሆን እህልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማከማቸት ወይም ሌሎች አካላዊ ዝግጅቶችን ማድረግ መጀመር ይኖርብህ ይሆን? እንዲህ ማድረግ አያስፈልግህም። መጽሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለእነዚህ ነገሮች እንዳልሆነ ይነግረናል። እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!” (2 ጴጥሮስ 3:10-12) በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው እንደሚቀልጡ የተገለጹት “እነዚህ ሁሉ ነገሮች” የዚህን ብልሹ ዓለም አገዛዞችና ከአምላክ አገዛዝ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ብልሹ አገዛዝ የሚመርጡ ሰዎችን ሁሉ ያካትታሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቁሳዊ ነገሮችን ማከማቸት ከመጪው ጥፋት ለመዳን አይረዳንም።
በእርግጥም ከጥፋቱ መትረፋችን የተመካው ለይሖዋ አምላክ ያደርን በመሆናችን ላይ ነው፤ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ብሎም ምን ዓይነት ተግባር መፈጸም እንዳለብን መማር ያስፈልገናል። (ሶፎንያስ 2:3) ስለዚህ ከፍተኛ ትኩረት በሚያሻው ጊዜ ውስጥ እየኖርን መሆናችንን የሚያሳዩትን ግልጽ ምልክቶች ችላ በማለት ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት መጠበቅና በአእምሯችን አቅርበን መመልከት’ ይኖርብናል። የይሖዋ ምሥክሮች ከመጪው የጥፋት ቀን እንዴት በሕይወት መትረፍ እንደምትችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳዩህ ይችላሉ።
-