የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ስንሞት ምን እንሆናለን?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

      ስንሞት ምን እንሆናለን?

      መካነ መቃብር ውስጥ ሬሳ ሣጥን አጠገብ የቆሙ አዋቂዎችና ልጆች

      “ሰው ሲሞት ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል አሊያም ወደ መንጽሔ ይሄዳል ብዬ አስብ ነበር። እርግጥ ወደ ሰማይ የሚያስገባ ጥሩ ነገር እንዳልሠራሁ አሊያም ለሲኦል የሚያበቃ ክፉ ነገር እንዳልሠራሁ አውቃለሁ። በሌላ በኩል መንጽሔ ውስጥ ምን እንዳለ በትክክል የማውቀው ነገር አልነበረም። ሰዎች ሲያወሩ ከሰማሁት ውጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጽ ሐሳብ አንብቤ አላውቅም።”—ላየነል

      “ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለውን ትምህርት አውቃለሁ፤ ሆኖም አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ እንደሆነ አድርጌ ስለማስብ ሙታን ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ይሰማኝ ነበር።”—ፈርናንዶ

      ‘ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች የሆነ ቦታ ሄደው እየተሠቃዩ ይሆን? ዳግመኛ እናያቸው ይሆን? ከሆነስ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች አስበህባቸው ታውቃለህ? እባክህ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ጉዳይ ምን ብለው እንደሚያስተምሩ ለማስተዋል ሞክር። እስቲ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል እንመልከት። ከዚያም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ እንመረምራለን።

      የሞቱ ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም፤ ከእንግዲህም የሚያገኙት ብድራት የለም፤ ምክንያቱም የሚታወሱበት ነገር ሁሉ ተረስቷል። እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን፤ አንተ በምትሄድበት በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።”a—መክብብ 9:5, 10

      በአጭር አነጋገር፣ መቃብር ሰዎች ሲሞቱ የሚያርፉበት ቦታ ሲሆን ቃሉ ምሳሌያዊ ቦታን ወይም ሁኔታን ያመለክታል፤ መቃብር ውስጥ ማሰብም ሆነ መሥራት አይቻልም። ታማኙ ኢዮብ መቃብርን እንዴት ይመለከተው ነበር? ኢዮብ በአንድ ቀን ንብረቱንና ልጆቹን በሙሉ አጣ፤ ከዚያም ክፉኛ የሚያሠቃይ እባጭ መላ ሰውነቱን ወረሰው። አምላክን “ምነው በመቃብር [“በሲኦል፣” የ1954 ትርጉም] ውስጥ በሰወርከኝ” በማለት ተማጽኖ ነበር። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7፤ 14:13) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢዮብ ሲኦልን የማቃጠያ ቦታ አድርጎ አልተመለከተውም፤ ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ወደሚሠቃይበት ቦታ ለመሄድ አይመኝም ነበር። ከዚህ ይልቅ እፎይታ የሚያገኝበት ቦታ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።

      የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ከሞት ስለተነሱ ስምንት ሰዎች የሚናገረውን ታሪክ መመርመር እንችላለን።—“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      ከስምንቱ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከሞት ሲነሱ ተድላ ወይም ሥቃይ ወዳለበት ቦታ ሄደው እንደነበር አልተናገሩም። እነዚህ ሰዎች ሲሞቱ እንዲህ ወዳለ ቦታ ሄደው ቢሆን ኖሮ ስለዚህ ጉዳይ ለሰዎች አያወሩም ነበር? ደግሞስ ተናግረው ቢሆን ኖሮ ሁላችንም እንድናነበው በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይካተትም ነበር? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የትም ቦታ ላይ እንዲህ ያለ ሐሳብ ተመዝግቦ አናገኝም። እነዚህ ስምንት ሰዎች ይህን በተመለከተ ሊናገሩ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ስለነበር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ለመግለጽ እንቅልፍን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ ዳዊትም ሆነ እስጢፋኖስ ‘በሞት እንዳንቀላፉ’ ተገልጿል።—የሐዋርያት ሥራ 7:60፤ 13:36

      ታዲያ የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? ከዚህ እንቅልፍ መንቃት ይችላሉ?

      a በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “መቃብር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የዕብራይስጡን “ሲኦል” እና የግሪክኛውን “ሐዲስ” ያመለክታል። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሲኦል የሚለው ቃል የሞቱ ሰዎች እየተቃጠሉ የሚሠቃዩበት ቦታ እንደሆነ ያስባሉ፤ ይሁንና ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም።

      በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎችb

      የአንዲት መበለት ልጅ፦ ነቢዩ ኤልያስ፣ በሰሜናዊ እስራኤል በሰራፕታ የምትኖር አንዲት መበለት ልጇ በሞተ ጊዜ አስነስቶላታል።—1 ነገሥት 17:17-24

      የሹነማዊቷ ልጅ፦ የኤልያስ ተተኪ የሆነው ኤልሳዕ በሹነም ከተማ አንድን ልጅ ከሞት አስነስቶ ለወላጆቹ ሰጥቷቸዋል።—2 ነገሥት 4:32-37

      መቃብር ውስጥ የተጣለው በድን፦ ሰዎች የአንድን ሰው አስከሬን፣ የኤልሳዕ አፅም አርፎበት በነበረው ቦታ ላይ በጥድፊያ ወርውረውት ሄዱ። የሰውየው በድን የነቢዩ ኤልሳዕን አፅም በነካ ጊዜ ሰውየው ከሞት ተነሳ።—2 ነገሥት 13:20, 21

      በናይን የምትኖረው መበለት ልጅ፦ ኢየሱስ ከናይን ከተማ ውጭ ወደ ቀብር እየሄዱ ከነበሩ ሰዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ሞቶ የነበረውን ልጅ አስነስቶ እያለቀሰች ለነበረችው እናቱ ሰጣት።—ሉቃስ 7:11-15

      የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፦ ኢያኢሮስ የሚባል አንድ የምኩራብ አለቃ ታማ የነበረችውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ተማጽኖት ነበር። ኢየሱስም ልጅቷ ከሞተች በኋላ ብዙም ሳትቆይ አስነስቷታል።—ሉቃስ 8:41, 42, 49-56

      የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር፦ ኢየሱስ አልዓዛርን በብዙ ሰዎች ፊት ከሞት ያስነሳው በሞተ በአራተኛው ቀን ነበር።—ዮሐንስ 11:38-44

      ዶርቃ፦ ሐዋርያው ጴጥሮስ በደግነቷ የምትታወቀውን ይህችን ተወዳጅ ሴት ከሞት አስነስቷታል።—የሐዋርያት ሥራ 9:36-42

      አውጤኪስ፦ አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት ከፎቅ ላይ ወድቆ ሕይወቱ ባለፈበት ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ አስነስቶታል።—የሐዋርያት ሥራ 20:7-12

      b ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚይዘው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ ከእነዚህ ስምንት ትንሣኤዎች ፈጽሞ የተለየ ነው፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን እንመለከታለን።

  • የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

      የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

      ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላሉ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።’—ዮሐንስ 5:28, 29

      ኢየሱስ ከላይ የተናገረው ሐሳብ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር መቃብሮች ባዶ የሚሆኑበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ፈርናንዶ “ለመጀመሪያ ጊዜ ዮሐንስ 5:28, 29⁠ን ሳነብ በጣም ተደንቄ ነበር። ጥቅሱ እውነተኛ ተስፋ የሰጠኝ ሲሆን ስለወደፊቱ ጊዜም ብሩህ አመለካከት እንዲኖረኝ አስችሎኛል” በማለት ተናግሯል።

      በጥንት ዘመን የኖረው ታማኙ ኢዮብ፣ አምላክ ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል እምነት ነበረው። ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም በሙሉ ልብ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል፦ “እፎይታ የማገኝበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ፣ የግዳጅ አገልግሎት በምፈጽምበት ዘመን [በመቃብር የሚያሳልፈውን ጊዜ ያመለክታል] ሁሉ በትዕግሥት እጠብቃለሁ። አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ።”—ኢዮብ 14:14, 15

      ከሞት የተነሳው አልዓዛር እህቱን አቅፎ

      የአልዓዛር ትንሣኤ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ እንድንጠባበቅ ያስችለናል

      የአልዓዛር እህት ማርታ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ታውቅ ነበር። አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። በዚህ ጊዜ ማርታ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” አላት። (ዮሐንስ 11:23-25) ከዚያም ኢየሱስ ወዲያውኑ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው! ይህ አስደሳች ታሪክ ወደፊት ለሚፈጸመው ታላቅ ክንውን እንደ ቅምሻ ነው። በዚያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትንሣኤ ሲከናወን ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ይታይህ!

      ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ይኖራሉ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የአምላክ ቃል የኢየሱስ ትንሣኤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ስምንት ትንሣኤዎች እንደሚለይ ይጠቁማል። እነዚያ ስምንት ሰዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ የኖሩት እዚሁ ምድር ላይ ነው። ሆኖም የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ እንዲህ የሚል ዘገባ እናነባለን፦ “ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል።” (1 ጴጥሮስ 3:21, 22) ከኢየሱስ ሌላ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሚሄድ ይኖራል? ኢየሱስ ቀደም ብሎ ለሐዋርያቱ “ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 14:3

      ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ በዚያ ለደቀ መዛሙርቱ ቦታ አዘጋጅቶላቸዋል። ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 144,000 ነው። (ራእይ 14:1, 3) ሆኖም እነዚህ የኢየሱስ ተከታዮች እዚያ ሄደው ምን ያደርጋሉ?

      ብዙ የሚሠሩት ሥራ ይኖራቸዋል! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሆኑ ሁሉ ደስተኞችና ቅዱሳን ናቸው፤ ሁለተኛው ሞት በእነዚህ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእሱም ጋር ለ1,000 ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእይ 20:6) ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙት እነዚህ ሰዎች ነገሥታትና ካህናት በመሆን ከክርስቶስ ጋር ምድርን ይገዛሉ።

      ቀጥሎስ እነማን ይነሳሉ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የአምላክ ቃል ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:15

      ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ አንዲት ሴት ከሞት የተነሳችን ትንሽ ልጅ አቅፋ

      የአምላክ ቃል በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ዳግም ሕያው እንደሚሆኑ ማረጋገጫ ይሰጠናል

      ጳውሎስ “ጻድቃን” በማለት ከጠራቸው ሰዎች ውስጥ እነማን ይገኙበታል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ታማኙ ዳንኤል በሕይወቱ መገባደጃ ላይ “ታርፋለህ፤ ሆኖም በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ” በማለት ተነግሮት ነበር። (ዳንኤል 12:13) ዳንኤል ከሞት ሲነሳ የሚኖረው የት ነው? “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ኢየሱስም ቢሆን “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5) ዳንኤልም ሆነ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ዳግም ሕያው ይሆናሉ።

      ጳውሎስ “ዓመፀኞች” በማለት ከጠራቸው ሰዎች መካከል እነማን ይገኙበታል? የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማርና ተግባራዊ ለማድረግ አጋጣሚ ያላገኙ እዚህ ምድር ላይ ኖረው ያለፉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። ከሞት ከተነሱ በኋላ ስለ ይሖዋa እና ስለ ኢየሱስ የመማር እንዲሁም ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኝነታቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ዮሐንስ 17:3) አምላክን ለማገልገል የሚመርጡ ሰዎች ሁሉ እንደ ይሖዋ እነሱም ለዘላለም ይኖራሉ።

      አምላክን ለማገልገል የሚመርጡ ሁሉ የተሟላ ደስታና ጤንነት አግኝተው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል

      በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? አምላክ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) በተጨማሪም “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።”—ኢሳይያስ 65:21

      ከሞት ከሚነሱ ወዳጅ ዘመዶችህ ጋር እንዲህ ባለ ሁኔታ ስትኖር ይታይህ! ሆኖም መልስ የሚያሻው አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፦ ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

      a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

  • የሞቱ ሰዎች ያላቸው ተስፋ—እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ነሐሴ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

      የሞቱ ሰዎች ያላቸው ተስፋ—እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

      የሞቱ ሰዎች ዳግመኛ ሕያው ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ አላሰበም። በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ይሁንና ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል።” (1 ቆሮንቶስ 15:19, 20) ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋ እርግጠኛ መሆኑን ያምን ነበር። ኢየሱስ ራሱ ከሞት መነሳቱ ለዚህ ዋስትና ይሆናል።a (የሐዋርያት ሥራ 17:31) ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ረገድ የመጀመሪያው ሰው ስለነበር ጳውሎስ “በኩራት” ሲል ጠርቶታል። ኢየሱስ የመጀመሪያ ከሆነ ሌሎች ሰዎችም ይኖራሉ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

      አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ በእጇ ይዛ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት አሻግራ ስትመለከት

      ኢዮብ አምላክን “የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሎታል። —ኢዮብ 14:14, 15

      የትንሣኤ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንድትሆን የሚያስችልህን ሌላ ማስረጃ እንመልከት። ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው። ደግሞም ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ዋሽቶ አያውቅም፤ ወደፊትም ቢሆን አይዋሽም። የትንሣኤን ተስፋ ከሰጠና ሊፈጽመው እንደሚችል ካሳየም በኋላ ተስፋው ውሸት ሆኖ እንዲቀር ያደርጋል? እንዲህ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!

      ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ የሰጠው ለምንድን ነው? አፍቃሪ ስለሆነ ነው። ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” በማለት ጠይቆ ነበር። ከዚያም “አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሏል። (ኢዮብ 14:14, 15) ኢዮብ አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባቱ ከሞት ሊያስነሳው እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር። አምላክ ተለውጧል? “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም” በማለት ተናግሯል። (ሚልክያስ 3:6) አምላክ አሁንም ቢሆን የሞቱ ሰዎች ዳግም ሕያው ሆነው የተሟላ ጤና እንዲሁም ደስታ አግኝተው ሲኖሩ ለማየት ይጓጓል። ይህ ደግሞ ማንኛውም አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ልጁን በሞት ሲያጣ የሚያድርበት ምኞት ነው። ልዩነቱ ግን አምላክ ምኞት ብቻ ሳይሆን የተመኘውን ነገር መፈጸም የሚያስችል ኃይልም አለው።—መዝሙር 135:6

      ሞት አስከፊ ችግር ነው፤ አምላክ ግን ለዚህ ችግር መፍትሔ አዘጋጅቷል

      ይሖዋ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ቅስማቸው ለተሰበረ ሰዎች ወደር የሌለው ደስታ ማጎናጸፍ እንዲችል ለልጁ ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት የአልዓዛር እህቶችና ወዳጆች የደረሰባቸው ከባድ ሐዘን ተሰምቶት ነበር፤ እንዲያውም ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ አንድ ልጇን በሞት ያጣችውን በናይን የምትኖር መበለት ሲያይ “በጣም አዘነላትና ‘በቃ፣ አታልቅሺ’ አላት።” ከዚያም ልጇን ወዲያውኑ አስነሳላት። (ሉቃስ 7:13) በመሆኑም ኢየሱስ ሐዘንና ሞት የሰዎችን ስሜት በጥልቅ እንደሚጎዳ ይገነዘባል። ወደፊት በመላው ምድር ላይ ሐዘን ተወግዶ በደስታ እንዲተካ ሲያደርግ ደግሞ ምን ያህል በሐሴት ይሞላ ይሆን!

      ትንሽ ልጁን ያቀፈ ሰው

      ሐዘን ደርሶብህ ያውቃል? ሞት መፍትሔ የሌለው ችግር እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም መፍትሔ አለው፤ ይህም አምላክ በልጁ አማካኝነት ወደፊት የሚያከናውነው ትንሣኤ ነው። አምላክ ይህ ችግር መፍትሔ ሲያገኝ በገዛ ዓይንህ እንድታይ ይፈልጋል። በዚያ ተገኝተህ የምትወዳቸውን ሰዎች እቅፍ አድርገህ እንድትቀበል ይመኝልሃል። የዘላለም ሕይወት አግኝታችሁ የረጅም ጊዜ እቅድ ስታወጡ ይታይህ፤ በዚያን ጊዜ መለያየት የሚባል ነገር አይኖርም!

      ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ላየነል እንዲህ ብሏል፦ “ከጊዜ በኋላ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሰማሁ። መጀመሪያ ላይ መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር፤ እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ የነገረኝን ሰው አላመንኩትም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ስመረምር ይህ ተስፋ እውነት መሆኑን ተረዳሁ! አያቴን ዳግመኛ ለማየት በጣም እጓጓለሁ።”

      ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት ከራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማሳየት ፈቃደኞች ናቸው።b

      a ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ለማየት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 78-86 ተመልከት።

      b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ