-
ጭንቀት የሌለበት ቦታ የለም!መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሐምሌ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ጭንቀት የሌለበት ቦታ የለም!
“ምግብ ለመግዛት ስሄድ ያገኘሁት ብስኩት ብቻ ነበር፤ ያውም ከተለመደው ዋጋ በ10,000 እጥፍ ጨምሮ ነበር! በቀጣዩ ቀን በየትኛውም ሱቅ ውስጥ ምንም የሚሸጥ ምግብ አልነበረም።”—ፖል፣ ዚምባብዌ
“ባለቤቴ ትቶን እንደሚሄድ ቁጭ አድርጎ ነገረኝ። እንዲህ ዓይነቱን ክህደት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው? ልጆቼስ ምን ይሆናሉ?”—ጃኔት፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደወሉ ሲጮኽና ሮኬቶች ሲተኮሱ ከአደጋው የምሸሸግበት ቦታ ለማግኘት ሮጬ በመሄድ ወለሉ ላይ ተኛሁ። ሰዓታት ካለፉ በኋላም እንኳ እጆቼ ይንቀጠቀጡ ነበር።”—አሎና፣ እስራኤል
የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ’ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙዎች በኢኮኖሚ ቀውስ፣ በቤተሰብ መፍረስ፣ በጦርነት፣ ገዳይ በሆኑ በሽታዎችና በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተነሳ ይጨነቃሉ። ይህ አልበቃ ብሎ ‘በሰውነቴ ላይ የወጣብኝ እብጠት ወደ ካንሰርነት ይቀየርብኝ ይሆን?’ ‘የልጅ ልጆቼ ወደፊት ምን ዓይነት ዓለም ይጠብቃቸው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ በግለሰብ ደረጃ የሚያስጨንቁ ነገሮች ያጋጥሙናል።
ጭንቀት ሁሉ መጥፎ አይደለም። ፈተና ልንፈተን ስንል፣ አንድ ልዩ ችሎታ የሚጠይቅ ትዕይንት እንድናሳይ ስንጠየቅ ወይም ሥራ ለመቀጠር ለቃለ መጠይቅ ስንቀርብ ትንሽ መረበሻችን አይቀርም። በተጨማሪም አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን በተመለከተ ተገቢውን ፍርሃት ማሳየታችን ከጉዳት ይጠብቀናል። ይሁን እንጂ ከመጠን ያለፈ ወይም የማያባራ ጭንቀት ጎጂ ነው። በቅርቡ ከ68,000 በላይ በሆኑ አዋቂዎች ላይ የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች መጠነኛ የሚባለው ጭንቀትም እንኳ ዕድሜን ሊያሳጥር እንደሚችል አረጋግጠዋል። እንግዲያውስ ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?” ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። በእርግጥም ጭንቀት የማንንም ዕድሜ አያስረዝምም። በመሆኑም ኢየሱስ “መጨነቃችሁን ተዉ” በማለት መክሯል። (ማቴዎስ 6:25, 27 የግርጌ ማስታወሻ) ይሁንና መጨነቃችንን መተው የምንችለው እንዴት ነው?
ይህን ማድረግ የምንችለው ጥበብን በሥራ ላይ በማዋል፣ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት በማዳበርና ስለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ በመገንባት ነው። አሁን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ባያጋጥሙንም እንኳ ወደፊት ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በመሆኑም ፖል፣ ጃኔትና አሎና እነዚህን እርምጃዎች መውሰዳቸው ጭንቀትን እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
-
-
ስለ ገንዘብ መጨነቅመጠበቂያ ግንብ—2015 | ሐምሌ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ስለ ገንዘብ መጨነቅ
“አገራችን በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በተመታች ጊዜ ምግብ እጅግ ከመወደዱም በላይ እንደ ልብ አይገኝም ነበር” በማለት ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፖል ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኛውን ጊዜ ለሰዓታት ተሰልፈን ከቆምን በኋላ ወረፋችን ከመድረሱ በፊት ምግቡ ያልቃል። ሰዎች ከረሃቡ የተነሳ በጣም ከስተው እንዲሁም አንዳንዶች መንገድ ላይ ተዝለፍልፈው ወድቀው ይታዩ ነበር። መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለመግዛት በሚሊዮን አልፎ ተርፎም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልግ ነበር። በመጨረሻም የአገሪቱ ገንዘብ ዋጋ አጣ። እኔም በባንክ ያጠራቀምኩትንም ሆነ ለኢንሹራንስና ለጡረታ ብዬ ያስቀመጥኩትን ገንዘብ አጣሁ።”
ፖል
ፖል ቤተሰቡን በሕይወት ለማቆየት ‘የጥበብ’ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተገነዘበ። (ምሳሌ 3:21) እንዲህ ብሏል፦ “የኤሌክትሪክ ሥራ ተቋራጭ ሆኜ እሠራ የነበረ ቢሆንም የማገኘውን ማንኛውንም ሥራ በዝቅተኛ ክፍያም እንኳ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበርኩ። አንዳንዶች የሚከፍሉኝ ምግብ ወይም የቤት ዕቃ ነበር። ለምሳሌ አራት ሳሙና ቢሰጡኝ ሁለቱን እጠቀምበታለሁ፤ የቀረውን ደግሞ እሸጠዋለሁ። ከጊዜ በኋላ 40 የዶሮ ጫጩቶች አገኘሁ። እነሱ ሲያድጉ ሸጥኳቸውና 300 ተጨማሪ ጫጩቶች ገዛሁ። ከዚያም 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሁለት ከረጢት የበቆሎ ዱቄት በ50 ዶሮዎች መለወጥ ቻልኩ። በዚህ ሁለት ከረጢት የበቆሎ ዱቄት ቤተሰቤንና ሌሎች ቤተሰቦችን ረዘም ላለ ጊዜ መመገብ ቻልኩ።”
በተጨማሪም ፖል ከሁሉ የተሻለው የጥበብ እርምጃ በአምላክ መታመን እንደሆነ ያውቅ ነበር። አምላክ የሚለንን የምናደርግ ከሆነ እሱ ይረዳናል። ኢየሱስ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማግኘትን በተመለከተ “አትጨነቁ፤ . . . አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 12:29-31
የሚያሳዝነው ነገር የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን አብዛኞቹን ሰዎች፣ ሕይወታቸው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ አታሏቸዋል። ሰዎች አሁን የሚያስፈልጓቸውንም ሆነ ገና ለገና ሊያስፈልጓቸው እንደሚችሉ አድርገው የሚያስቧቸውን ነገሮች ስለማግኘት ከልክ በላይ ይጨነቃሉ፤ አልፎ ተርፎም እምብዛም የማያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት ይዋትታሉ። ብዙዎች ዕዳ ውስጥ ይዘፈቁና “ተበዳሪም የአበዳሪው ባሪያ ነው” የሚለውን ሐቅ ከመከራ ይማራሉ።—ምሳሌ 22:7
አንዳንዶች ለችግር የሚዳርጋቸውን ውሳኔ ይወስናሉ። ፖል “በአካባቢያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ ቤተሰባቸውንና ወዳጅ ዘመዳቸውን ጥለው ወደ ውጭ አገር ሄደዋል” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶቹ ከአገር የወጡት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ስላልሆነ ሥራ ማግኘት አልቻሉም። ብዙውን ጊዜ የሚንቀሳቀሱት ከፖሊስ ተደብቀው ሲሆን የሚተኙትም በየጎዳናው ነው። አምላክ እንዲረዳቸው ወደ እሱ ዞር አላሉም። እኛ ግን ያጋጠመንን የኢኮኖሚ ችግር አምላክ በሚሰጠን እርዳታ በመታገዝ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ለመጋፈጥ ቆርጠን ነበር።”
የኢየሱስን ምክር መከተል
ፖል በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ‘ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው’ ብሏል። በመሆኑም በየዕለቱ ወደ አምላክ የምጸልየው ‘የዕለቱን ምግባችንን እንዲሰጠንና’ በሕይወት መቀጠል እንድንችል ብቻ ነው። ደግሞም ኢየሱስ በገባው ቃል መሠረት ይሖዋ ረድቶናል። እርግጥ ሁልጊዜ የምንፈልገውን እናገኝ ነበር ማለት አይደለም። አንድ ቀን፣ ምን እየተሸጠ እንዳለ ሳላውቅ ምግብ ለመግዛት ተሰለፍኩ። ወረፋዬ ሲደርስ የሚሸጠው ነገር እርጎ መሆኑን አወቅኩ። እኔ ደግሞ እርጎ አልወድም። ይሁንና እርጎም ቢሆን ምግብ ስለሆነ ያን ዕለት እሱን በልተን አደርን። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ቤተሰቤ ጾሙን አድሮ ስለማያውቅ አምላክን አመሰግናለሁ።”a
አምላክ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል።—ዕብራውያን 13:5
“እርግጥ አሁን የገንዘብ ችግራችን በተወሰነ መጠን ተቃሏል። ይሁን እንጂ ከሁሉ የተሻለው የጭንቀት ማርከሻ በአምላክ መታመን እንደሆነ ካሳለፍነው ተሞክሮ ተምረናል። ይሖዋb ፈቃዱን ለማድረግ ጥረት እስካደረግን ድረስ ምንጊዜም ይረዳናል። ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው’ የሚለው በመዝሙር 34:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑን ተመልክተናል። በመሆኑም ዳግመኛ የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥመን አንፈራም።
አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ‘የዕለት ምግባቸውን’ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል
“ሰዎች በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ሥራ ወይም ገንዘብ ሳይሆን ምግብ እንደሆነ አሁን በግልጽ ገብቶናል። ‘በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል’ የሚለው አምላክ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ‘ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።’ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ያበረታታናል፦ ‘አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። እሱ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” ብሏልና። ስለዚህ በሙሉ ልብ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም”’ እንላለን።”c
ፖልና ቤተሰቡ እንዳደረጉት ‘ከአምላክ ጋር መሄድ’ ጠንካራ እምነት ይጠይቃል። (ዘፍጥረት 6:9) በአሁኑ ጊዜ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሞን ከሆነ አሊያም ወደፊት ካጋጠመን፣ ፖል በአምላክ በመታመንና ጥበብ የታከለበት እርምጃ በመውሰድ ረገድ ከተወው ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
ይሁን እንጂ እያስጨነቀን ያለው የቤተሰብ ችግር ቢሆንስ?
a ማቴዎስ 6:11, 34ን ተመልከት።
b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።
c መዝሙር 72:16ን፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8ን እና ዕብራውያን 13:5, 6ን ተመልከት።
-
-
ስለ ቤተሰብ መጨነቅመጠበቂያ ግንብ—2015 | ሐምሌ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ስለ ቤተሰብ መጨነቅ
“አባቴ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቴ ሌላ ሴት እንደወደደ ነገረኝ” በማለት ጃኔት ትናገራለች። “ከዚያም ሳይሰናበተን ድንገት ልብሱን ጠቅልሎ እኔንና ሁለት ልጆቼን ጥሎን ሄደ።” ጃኔት ሥራ ብታገኝም ደሞዟ የቤቱን ዕዳ ለመክፈል የሚበቃ አልነበረም። ደግሞም የሚያሳስባት የገንዘብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። እንዲህ ብላለች፦ “የወደቀብኝ ከባድ ኃላፊነት የፈጠረብኝ ጭንቀት ብቻዬን ልሸከመው የምችለው አልነበረም። ሌሎች ወላጆች እንደሚያደርጉት እኔም ለልጆቼ ማድረግ ባለመቻሌ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሰዎች ስለ እኔም ሆነ ስለ ልጆቼ ያላቸው አመለካከት አሁንም ያስጨንቀኛል። ትዳሬን ለመታደግ ምንም ጥረት እንዳላደረግኩ አድርገው ያስቡ ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።”
ጃኔት
ጃኔት ስሜቷን ለመቆጣጠርና ከአምላክ ጋር ያላትን ዝምድና ለማጠናከር የረዳት ጸሎት ነው። “በጣም የሚከብደኝ፣ ሁሉም ነገር ጸጥ ረጭ የሚልበትና የሚያስጨንቁኝን ሐሳቦች መቋጨት የማልችልበት የሌሊቱ ሰዓት ነው። ጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንቅልፍ እንዲወስደኝ ይረዳኛል። በጣም የምወደው ጥቅስ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።’ ብዙ ጊዜ ስጸልይ አድሬአለሁ፤ ይሖዋ የሚሰጠውም ሰላም አረጋግቶኛል።”
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ‘አባታችሁ ገና ሳትለምኑት እንኳ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል’ በማለት ስለ ጸሎት የተናገረው የሚያጽናና ሐሳብ ማንኛውንም ዓይነት ጭንቀት ለመቋቋም ይረዳል። (ማቴዎስ 6:8) ደግሞም አምላክን መለመን ያስፈልገናል። ጸሎት ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ነው። እኛ ወደ አምላክ ከቀረብን ‘እሱ ወደ እኛ ይቀርባል።’—ያዕቆብ 4:8
በጸሎት አማካኝነት ጭንቀታችንን መግለጻችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ያለፈ ጥቅም አለው። በተጨማሪም “ጸሎት ሰሚ” የሆነው ይሖዋ በእምነት አጥብቀው ለሚፈልጉት ሁሉ ሲል እርምጃ ይወስዳል። (መዝሙር 65:2) ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ምንጊዜም ተስፋ ሳይቆርጡ የመጸለይን አስፈላጊነት” ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 18:1) አምላክ ለእምነታችን ወሮታ እንደሚከፍል እርግጠኞች በመሆን አመራር እንዲሰጠንና እንዲረዳን ሁልጊዜ መለመን አለብን። እኛን ለመርዳት ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳለው ፈጽሞ መጠራጠር የለብንም። በዚህ መንገድ ‘ዘወትር መጸለያችን’ ጠንካራ እምነት እንዳለን ያሳያል።—1 ተሰሎንቄ 5:17
እምነት አለን ሲባል ምን ማለት ነው?
ይሁንና እምነት ምንድን ነው? እምነት አምላክን እንደ አንድ እውን አካል አድርጎ ‘ማወቅን’ ይጨምራል። (ዮሐንስ 17:3) ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ አምላክ በመማር ነው። አምላክ እያንዳንዳችንን እንደሚመለከትና ሊረዳን እንደሚፈልግ ከቃሉ እንረዳለን። ሆኖም ጠንካራ እምነት ስለ አምላክ መሠረታዊ ነገር ብቻ በማወቅ የተወሰነ አይደለም። ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረትን ይጨምራል። ከአንድ ሰው ጋር በአንድ ጀምበር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንደማይቻል ሁሉ ከአምላክ ጋርም እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜ ይጠይቃል። ስለ እሱ እያወቅን ስንሄድ፣ “እሱን ደስ የሚያሰኘውን” ነገር ስናደርግና እኛን ለመርዳት ሲል የሚወስደውን እርምጃ ስንመለከት እምነታችን “እያደገ” ይሄዳል። (2 ቆሮንቶስ 10:15፤ ዮሐንስ 8:29) ጃኔት ጭንቀቷን እንድትቋቋም የረዳት እንዲህ ዓይነት እምነት ነው።
ጃኔት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በእያንዳንዱ እርምጃዬ የይሖዋን እጅ ማየቴ እምነቴን ለመገንባት ረድቶኛል። በተደጋጋሚ ጊዜ መፍትሔ የሌለው የሚመስል በደል ደርሶብናል። ደግሜ ደጋግሜ ስጸልይ ይሖዋ ፈጽሞ ባላሰብኩት አቅጣጫ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል። ለእሱ ምስጋና በማቀርብበት ጊዜ ያደረገልኝ ብዙ ነገር ትዝ ይለኛል። እሱ ሁሌም በትክክለኛው ጊዜ እንደሚደርስልን አይቻለሁ። ደግሞም ከልብ የሚወዱኝ እውነተኛ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ሰጥቶኛል። እነዚህ ወዳጆቼ ምንጊዜም ከጎኔ የማይጠፉ ሲሆን ለልጆቼም ጥሩ ምሳሌ ናቸው።”a
“በሚልክያስ 2:16 ላይ ይሖዋ ‘ፍቺን እጠላለሁ’ ያለው ለምን እንደሆነ ይገባኛል። ታማኝ ለሆነ አንድ የትዳር ጓደኛ እንደ ክህደት ያለ ስሜትን የሚጎዳ ነገር የለም። ባለቤቴ ጥሎን ከሄደ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም በውስጤ የባዶነት ስሜት የሚሰማኝ ጊዜ አለ። እንዲህ በሚሰማኝ ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ፤ ይህም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።” ጃኔት ራስን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በዚህ መንገድ ተግባራዊ ማድረጓ ጭንቀቷን እንድትቋቋም ረድቷታል።b—ምሳሌ 18:1
አምላክ “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ ነው።”—መዝሙር 68:5
ጃኔት እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ ‘አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለመበለቶች ደግሞ ጠባቂ’ መሆኑን ማወቄ ከምንም ነገር በላይ ያጽናናኛል። ባለቤቴ ጥሎን ቢሄድም ይሖዋ ግን ፈጽሞ አልተወንም።” (መዝሙር 68:5) ጃኔት፣ አምላክ “በክፉ ነገር” እንደማይፈትነን ታውቃለች። ከዚህ ይልቅ እሱ ጥበብን “ለሁሉም በልግስና ይሰጣል”፤ እንዲሁም ጭንቀቶቻችንን ለመቋቋም የሚረዳንን ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ይሰጠናል።—ያዕቆብ 1:5, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7
ይሁን እንጂ የምንጨነቀው ሕይወታችን ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ የተነሳ ከሆነስ?
a 1 ቆሮንቶስ 10:13ን እና ዕብራውያን 4:16ን ተመልከት።
b ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?” የሚለውን በሐምሌ 2015 ንቁ! ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት። www.pr2711.com/am ላይም ይገኛል።
-
-
ስለ አደጋ በማሰብ መጨነቅመጠበቂያ ግንብ—2015 | ሐምሌ 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ስለ አደጋ በማሰብ መጨነቅ
አሎና “የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉን ስሰማ ልቤ በኃይል መምታት ይጀምራል” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከቦምብ ድብደባው ለመሸሸግ ወደተዘጋጀው መጠለያ እየሮጥኩ እሄዳለሁ፤ እዚያም ሆኜ ግን እጨነቃለሁ። ምንም መደበቂያ የሌለበት አካባቢ ስሆንማ ጭንቀቴ ይጨምራል። አንድ ቀን መንገድ ላይ እየሄድኩ ሳለ የምሆነው ጠፍቶኝ ማልቀስ ጀመርኩ፤ መተንፈስም አቃተኝ። ለመረጋጋት ሰዓታት ፈጅቶብኛል። ከዚያም የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉ በድጋሚ ጮኸ።”
አሎና
ጦርነት ከብዙ የአደጋ መንስኤዎች አንዱ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንተ ወይም የቤተሰብህ አባል ለሕይወት የሚያሰጋ በሽታ እንዳለባችሁ ስታውቅ በመብረቅ የተመታህ ያህል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ሌሎች ደግሞ ስለወደፊቱ ጊዜ በመፍራት ሊጨነቁ ይችላሉ። ብዙዎች ‘ጦርነት፣ ወንጀል፣ ብክለት፣ የአየር ንብረት መዛባትና ወረርሽኝ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው፤ ታዲያ ልጆቻችን ወይም የልጅ ልጆቻችን በምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ለመኖር ይገደዱ ይሆን?’ እያሉ ይጨነቃሉ። እንዲህ ዓይነቱን ጭንቀት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
መጥፎ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድመን ማወቃችን “ብልህ ሰው አደጋ አይቶ ይሸሸጋል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል። (ምሳሌ 27:12) አካላዊ ጤንነታችንን ለመንከባከብ ጥረት እንደምናደርግ ሁሉ አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነታችንንም ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል። ዓመፅ የሞላበት መዝናኛ ሌላው ቀርቶ ዘግናኝ ምስሎች የሚታዩባቸው የዜና ዘገባዎች እኛንም ሆነ ልጆቻችንን ለጭንቀት ሊዳርጉ ይችላሉ። ከእነዚህ ነገሮች መራቅ በገሃዱ ዓለም ያለውን እውነታ ላለማየት ዓይንን እንደመጨፈን ሊቆጠር አይገባም። አምላክ የፈጠረን መጥፎ ነገሮችን እያውጠነጠንን እንድንጨነቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘እውነት፣ ጽድቅ፣ ንጹሕና ተወዳጅ ስለሆኑ ነገሮች’ እንድናስብ ነው። እንዲህ ካደረግን ‘የሰላም አምላክ’ አእምሯችንንና ልባችንን ያረጋጋልናል።—ፊልጵስዩስ 4:8, 9
ጸሎት ይረዳል
ጠንካራ እምነት ጭንቀትን ለመቋቋም ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 4:7) አምላክ ‘የምንጠይቀውን ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ’ እንዲረዳን እንዲሁም ጥበብና ድፍረት እንዲሰጠን መለመን እንችላለን፤ ይህም ያለንን አጋጣሚ ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ያስችለናል።—1 ዮሐንስ 5:15
ከባሏ ከአቪ ጋር
መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” አምላክ ሳይሆን ሰይጣን እንደሆነና “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር” እንደሚገኝ ይገልጻል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በመሆኑም ኢየሱስ “ከክፉው አድነን” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እየተናገረ አልነበረም። (ማቴዎስ 6:13) አሎና እንዲህ ብላለች፦ “የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉ መጮኽ ሲጀምር ከልክ በላይ እንዳልረበሽ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ውዱ ባለቤቴ ስልክ ይደውልልኝና አብሮኝ ይጸልያል። ጸሎት በእርግጥ ይረዳል።” መጽሐፍ ቅዱስም “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በቅንነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ይላል።—መዝሙር 145:18 የግርጌ ማስታወሻ
የወደፊቱ ተስፋችን
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት አላግባብ የሚያስጨንቁንን ነገሮች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግድልናል። አምላክ “የሰላም መስፍን” በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (ኢሳይያስ 9:6፤ መዝሙር 46:9) “[አምላክ] በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ . . . አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም። . . . የሚያስፈራቸውም አይኖርም።” (ሚክያስ 4:3, 4) ደስተኛ ቤተሰቦች “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።” (ኢሳይያስ 65:21) “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24
በዛሬው ጊዜ የተለያዩ የአደጋ ማስጠንቀቂያዎች ቢኖሩም “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሙሉ በሙሉ እንዳይደርሱ መከላከል ወይም ባልሆነ ሰዓት ያልሆነ ቦታ መገኘት ከሚያስከትለው አደጋ ማምለጥ ሁልጊዜ ይቻላል ማለት አይደለም። (መክብብ 9:11) ባለፉት መቶ ዘመናት እንደታየው ሁሉ ጦርነት፣ ዓመፅና በሽታ የጥሩ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፋቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ምን ተስፋ ይኖራቸዋል?
ምን ያህል ሰዎች የዚህ ሰለባ እንደሆኑ የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነው፤ ያም ሆነ ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙታን እንደገና በሕይወት ይኖራሉ። ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ከዚያ የሚወጡበት’ ጊዜ እስኪመጣ ይኸውም ፍጹም የማስታወስ ችሎታ ያለው አምላክ እስኪያስነሳቸው ድረስ ግን በሞት አንቀላፍተው ይቆያሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን” በማለት ትንሣኤ የተረጋገጠ ተስፋ መሆኑን ይነግረናል። (ዕብራውያን 6:19) ደግሞም አምላክ “[ኢየሱስን] ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።”—የሐዋርያት ሥራ 17:31
በአሁኑ ጊዜ አምላክን ለማስደሰት የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ሰዎችም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ፖል፣ ጃኔትና አሎና ተግባራዊ የሆኑ የጥበብ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ በመቅረብና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚገልጸው ተስፋ ላይ እምነት በማሳደር የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን በተሳካ መንገድ ተቋቁመው እየኖሩ ነው። እናንተም ‘በእሱ ስለታመናችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ እንዲሞላባችሁ’ እንመኛለን።—ሮም 15:13
-