የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | መስከረም 1
    • የይሖዋ ምሥክሮች ጋሪ ተጠቅመው በአደባባይ እያገለገሉ ሳሉ አንዲት ሴት ስትመለከታቸው

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?

      “ማይክን ሳውቀው ብዙ ዓመቴ ነው። ማይክ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ተከታይ ነው። ይሄ ሃይማኖቱ ግን ሁልጊዜ ግራ ያጋባኛል። ይሖዋ የሚባለው ማን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ዓመት በዓሎችን የማያከብሩት ለምንድን ነው? ማይክ ከመናፍቃን ጋር ኅብረት ፈጥሮ ይሆን?”—ቤኪ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      “ጎረቤቶቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመሩ ጊዜ ‘ለመሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው ስም ምን ማለት ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ። እንዲህ ዓይነት የሃይማኖት ስም ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም!”—ዜነን፣ ኦንታሪዮ፣ ካናዳ

      “እኔና ባለቤቴ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን የሚመጡት ቤተ ክርስቲያን ባለመሄዳችን በሚሰማን የበደለኛነት ስሜት ለመጠቀም ፈልገው ነው ብለን እናስብ ነበር። እንዲሁም ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ፍላጎታችንን ማርካት ካልቻሉ እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ያለ ምንነቱ የማይታወቅ ኑፋቄማ ምንም አይጠቅመንም ብለን አሰብን።”—ኬንት፣ ዋሽንግተን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      “እውነቱን ለመናገር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ማንነትም ሆነ ስለ ዓላማቸው የማውቀው ነገር አልነበረም።”—ሴሲልየ፣ ኤስቤርግ፣ ዴንማርክ

      የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ወይም በአደባባይ ሲሰብኩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ሲያሠራጩና ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲማሩ ሲጋብዙ አይተህ ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም ይህን መጽሔት የሰጡህ እነሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ማንነት ጥያቄ ሊኖርህ ይችላል። ምናልባት አንተም ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከተናገሩት ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ይኖርህ ይሆናል።

      እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ተፈጥረውብህ ከሆነ መልሶቹን የት ማግኘት ትችላለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጥ ምን ብለው እንደሚያምኑ፣ አገልግሎታቸውን ለማካሄድና የአምልኮ ቦታቸውን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከየት እንደሚያገኙ እንዲሁም ወደ ቤትህ የሚመጡትና መንገድ ላይ ቀርበው የሚያነጋግሩህ ለምን እንደሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

      ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሴሲልየ እንዲህ ብላለች፦ “ኢንተርኔት ላይ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ነገር አንብቤያለሁ። ደግሞም አንዳንድ አሉባልታዎችን ሰምቻለሁ፤ በጭፍን ጥላቻ የተነገሩ ብዙ ወሬዎችንም አዳምጫለሁ። ከዚህ የተነሳ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም።” ይሁንና ሴሲልየ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግራ ለጥያቄዎቿ አጥጋቢ መልስ አግኝታለች።

      አንተስ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ላሉህ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ብታገኝ ደስ ይልሃል? ከሆነ ለጥያቄዎችህ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡህ የሚችሉትንና የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮችን እንድትጠይቅ እናበረታታሃለን። (ምሳሌ 14:15) ቀጥሎ የቀረቡት ርዕሶች ስለ እኛ ማንነት፣ ምን ብለን እንደምናምንና ስለምናከናውነው ሥራ እንድታውቅ ይረዱሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

  • የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | መስከረም 1
    • የተለያየ ዘር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሰላምታ ሲለዋወጡ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

      ድርጅታችን ዓለም አቀፋዊ ነው፤ ይሁንና ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የለንም። ዋናው መሥሪያ ቤታችን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ቢሆንም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩት በሌሎች አገሮች ውስጥ ነው። እንዲያውም ወደ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እናስተምራለን። ይህን የምናደርገው ደግሞ ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ሲል የሰጠውን መመሪያ በማክበር ነው።—ማቴዎስ 24:14

      የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ መንግሥት ያወጣውን ሕግ እናከብራለን። በፖለቲካ ጉዳዮች ግን ፍጹም ገለልተኛ አቋም አለን። እንዲህ የምናደርገው ኢየሱስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ሲናገር “የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት የሰጠውን መመሪያ ስለምናከብር ነው። በመሆኑም በፖለቲካ ጉዳዮችና እንቅስቃሴዎች አንካፈልም ወይም ጦርነትን አንደግፍም። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16) እንዲያውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እስራትና ድብደባ አልፎ ተርፎም የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጳጳስ የነበሩ አንድ ጀርመናዊ “ሦስተኛውን ራይክ [የሂትለርን አገዛዝ] እንደተቃወሙ በትክክል መናገር የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል።

      “[የይሖዋ ምሥክሮች] ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም አላቸው። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ለከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ ልንጠቀምባቸው እንችል ነበር፤ ይሁንና ፖለቲካ ውስጥ ይገባሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። . . . የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን የሚታዘዙ ቢሆንም የሰው ልጆች የገጠሟቸውን ችግሮች በሙሉ የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።”—ኖቨ ስቮቦደ ጋዜጣ፣ ቼክ ሪፑብሊክ

      ያም ሆኖ ከሰዎች ተገልለን አንኖርም። ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው እንድትጠብቃቸው ነው” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:15) በመሆኑም በመኖሪያ አካባቢያችን በሥራና በገበያ ቦታ እንዲሁም በትምህርት ቤት ልታየን ትችላለህ።

      የይሖዋ ምሥክሮች በብዛት የሚገኙባቸው አገሮች

      • ዩናይትድ ስቴትስ 1,190,000

      • ሜክሲኮ 800,000

      • ብራዚል 770,000

      • ናይጄሪያ 330,000

      • ጣሊያን 250,000

      • ጃፓን 220,000

      ዘመናዊዋ እስራኤል

      www.pr2711.com ላይ ስፔሻል ኮንቬንሽን ኢን ኢዝራኤል በተባለው ቪዲዮ ላይ የእስራኤልና የፍልስጤም ተወላጅ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የብሔርና የጎሣ ልዩነቶችን እንዴት እንዳሸነፉ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን። (በእንግሊዝኛ “አባውት አስ > ኮንቬንሽንስ” በሚለው ሥር ይገኛል)

  • የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | መስከረም 1
    • የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ባልና ሚስት ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

      የይሖዋ ምሥክሮች ‘ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉና ጠቃሚ’ እንደሆኑ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ፈጣሪ ለመማርና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር እንደሚረዳ ስለምናምን የሕይወታችን መመሪያ ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ” ይላል። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም ይሖዋ አምላክን ብቻ የምናመልክ ሲሆን የእሱ ምሥክሮች በመሆናችን የግል ስሙን ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን።—ኢሳይያስ 43:10-12

      ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ደግሞ “የአምላክ ልጅ”a የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር እንደመጣና መሲሕ ሆኖ እንደተሾመ እናምናለን። (ዮሐንስ 1:34, 41፤ 4:25, 26) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሄዷል። (1 ቆሮንቶስ 15:3, 4) ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኗል። (ራእይ 11:15) ይህ መንግሥት ምድርን ዳግመኛ ገነት የሚያደርግ በተጨባጭ ያለ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44) መጽሐፍ ቅዱስ “የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል” ይላል።—መዝሙር 37:11, 29

      “የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ አምላክ እያነጋገራቸው እንዳለ ይሰማቸዋል። በሕይወታቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው መፍትሔውን ከአምላክ ቃል ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። . . . ለእነሱ የአምላክ ቃል አሁንም ሕያው ነው።”—የካቶሊክ ቄስ ቤንጃሚን ቼራያዝ፣ ሚዩንስተርላንደሽ ፎልክስጻይቱንግ ጋዜጣ፣ ጀርመን

      የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በዛሬው ጊዜ እንኳ ሳይቀር ለሰዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ስለዚህ እነዚህን መመሪያዎች በጥብቅ እንከተላለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አእምሯችንንና አካላችንን ከሚበክሉ ልማዶች እንድንርቅ ስለሚያስጠነቅቀን ሲጋራ አናጨስም ወይም በአደንዛዥ መድኃኒቶች አላግባብ አንጠቀምም። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በተጨማሪም እንደ ስካር፣ ስርቆትና የፆታ ብልግና ካሉ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ከሚያወግዛቸው ልማዶች እንርቃለን።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

      a መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የአምላክ አንድያ ልጅ” በማለትም ይጠራዋል፤ እንዲህ የተባለው በይሖዋ አምላክ በቀጥታ የተፈጠረው የመጀመሪያው ፍጡር እሱ ብቻ ስለሆነ ነው።—ዮሐንስ 3:18፤ ቆላስይስ 1:13-15

      አንድ ትንሽ ልጅ የተሰጠውን ስጦታ ሲከፍት ወላጆቹ በፈገግታ ሲያዩት

      www.pr2711.com ላይ ስለ እኛ > ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች በሚለው ሥር በዓላትን የማናከብርበትን ወይም ለሕክምና ደም የማንወስድበትን ምክንያት ጨምሮ ስለምናምንባቸው ነገሮች ማወቅ ትችላለህ።

  • የስብከቱ ሥራ ወጪ የሚሸፈነው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | መስከረም 1
    • አንድ ሰው መዋጮ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ ሲጨምር

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?

      የስብከቱ ሥራ ወጪ የሚሸፈነው እንዴት ነው?

      በየዓመቱ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አትመን እናሠራጫለን። በዓለም ዙሪያ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንና የማተሚያ ሕንፃዎችን የምንገነባ ከመሆኑም ሌላ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሰፊ ሥራ እናከናውናለን። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሽ ተብለው በሚጠሩ ባልተንቆጠቆጡ ሆኖም በሚያምሩ የአምልኮ ቦታዎች ውስጥ ይሰበሰባሉ። ታዲያ ይህ ሁሉ ወጪ የሚሸፈነው እንዴት ነው?

      ሥራችን ሙሉ በሙሉ የሚካሄደው ሰዎች በፈቃደኝነት በሚሰጡት መዋጮ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7) በ1879 የዚህ መጽሔት ሁለተኛ እትም የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሮ ነበር፦ “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ [በዚያን ጊዜ የመጽሔቱ ስም ይህ ነበር] ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በመሆኑም መጠበቂያ ግንብ፣ ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም።” አሁንም ቢሆን በዚህ ፖሊሲ ላይ ያደረግነው አንዳች ለውጥ የለም።

      ግለሰቦች የገንዘብ መዋጮ በቀጥታ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን ይልካሉ፤ አሊያም በመሰብሰቢያ አዳራሾቻችን በሚገኝ የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ይከታሉ። ይሁን እንጂ አሥራት አናስከፍልም፣ ሙዳየ ምፅዋት አናዞርም ወይም ለምናከናውነው አገልግሎትም ሆነ ለጽሑፎቻችን ገንዘብ አንጠይቅም። በስብከቱ ሥራ ስንካፈል፣ በጉባኤ ውስጥ ስናስተምር ወይም የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባቱ ሥራ እገዛ ስናበረክት ገንዘብ አይከፈለንም። ኢየሱስም ቢሆን “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏል። (ማቴዎስ 10:8) በቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላትን ጨምሮ በዋናው መሥሪያ ቤታችን ያሉት የሃይማኖታዊ ማኅበሩ አባላት በሙሉ ደሞዝ አይከፈላቸውም።

      “የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎችም ላይ ማየት እንደሚቻለው አንድ ሰው ለሃይማኖቱ ‘መዋጮ’ የሚሰጠው በራሱ ፈቃድ ሲሆን የመዋጮውን መጠንም ሆነ የሚሰጥበትን ጊዜ የሚወስነው ግለሰቡ ራሱ ነው።”—የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ 2011

      በተጨማሪም በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ ለመስጠት ይውላል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መከራ ለደረሰባቸው ወንድሞቻቸው የበኩላቸውን እርዳታ ማበርከት በመቻላቸው ደስተኞች ነበሩ። (ሮም 15:26) እኛም በአደጋ ለተጎዱ የእምነት ባልንጀሮቻችን መኖሪያ ቤታቸውንና የአምልኮ ቦታቸውን መልሰን በመገንባት እንዲሁም ምግብ፣ ልብስና ሕክምና በመስጠት እርዳታ እናበረክታለን።

      ፈገግ ያለ ትንሽ ልጅ

      www.pr2711.com ላይ በፊሊፒንስ የደረሰው አውሎ ነፋስ—እምነት መከራን ያሸንፋል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት። (ስለ እኛ > እንቅስቃሴዎች በሚለው ሥር ይገኛል)

  • የምንሰብከው ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | መስከረም 1
    • ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ የመኖሪያ አካባቢ ሲሰብኩ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው?

      የምንሰብከው ለምንድን ነው?

      ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይና ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ የምናከናውነው ሰፊ የስብከት ሥራ በዋነኝነት ተለይተን የምንታወቅበት ተግባር ነው። የምንሰብከው ለምንድን ነው?

      የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት አምላክ እንዲከበርና ስሙ እንዲታወቅ ስለሚፈልጉ ነው። (ዕብራውያን 13:15) በተጨማሪም ክርስቶስ ኢየሱስ ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር ስለምንፈልግ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20

      ከዚህም ሌላ ሰዎችን ሁሉ እንወዳለን። (ማቴዎስ 22:39) እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸው እምነት እንዳላቸውና መልእክታችንን መስማት የሚፈልገው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሕይወት እንደሚያስገኝ እናምናለን። ከዚህም የተነሳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ ‘ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራችንንና ማወጃችንን’ እንቀጥላለን።—የሐዋርያት ሥራ 5:41, 42

      የሥነ ኅብረተሰብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አንቶኒዮ ኮቫ ማዱሮ “የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ጥረትና ልፋት፣ ጉልበታቸውን ምንም ሳይቆጥቡ . . . የቅዱስ ጽሑፉን መልእክት እስከ ምድር ዳር ድረስ አዳርሰዋል” በማለት ጽፈዋል።—ኤል ኡኒቨርሳል ጋዜጣ፣ ቬንዙዌላ

      ጽሑፎቻችንን የሚያነቡ አብዛኞቹ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። እንዲሁም ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ናቸው። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸው መጥተው ስለሚያነጋግሯቸው አመስጋኞች ናቸው።

      እርግጥ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ሌሎች ጥያቄዎችም ሊኖሩህ ይችላሉ። ከሆነ በሚከተሉት መንገዶች መልሶቹን ማግኘት ትችላለህ፦

      • የይሖዋ ምሥክሮችን በመጠየቅ።

      • www.pr2711.com ድረ ገጻችንን በመጎብኘት።

      • ክፍያ በማይጠየቅባቸውና ለሁሉም ሰው ክፍት በሆኑት ስብሰባዎቻችን ላይ በመገኘት።

      ኢየሱስ እንዲሰብኩ ሁለት ደቀ መዛሙርትን ሲልክ
      አናቱ በበረዶ የተሸፈነ ተራራ

      የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት www.pr2711.com ላይ የይሖዋ ምሥክሮች—ምሥራቹን ለመስበክ የተደራጀ ሕዝብ የሚለውን ረጅም የቪዲዮ ፊልም ተመልከት። (የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ይገኛል)

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ