-
ለሕዝብ የሚቀርብ ንግግር መዘጋጀትበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ለሕዝብ የሚቀርብ ንግግር መዘጋጀት
በአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በየሳምንቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ንግግር ይቀርባል። ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ከሆንክ ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪ ወይም አስተማሪ መሆንህ በግልጽ ይታያልን? እንደዚያ ከሆነ የሕዝብ ንግግር የማቅረብ አጋጣሚ ይሰጥህ ይሆናል። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች ለዚህ የአገልግሎት መብት ብቁ እንዲሆኑ ረድቷል። የሕዝብ ንግግር እንድታቀርብ በምትመደብበት ጊዜ ዝግጅትህን ለመጀመር በቅድሚያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አስተዋጽኦውን አጥና
ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ከመጀመርህ በፊት አስተዋጽኦውን በማንበብና በዚያ ላይ በማሰላሰል የንግግሩን መልእክት ለማግኘት ሞክር። ጭብጡን ማለትም የንግግሩን ርዕስ አስብ። አድማጮችህን የምታስተምራቸው ስለ ምን ነገር ነው? ዓላማህ ምንድን ነው?
የንግግሩን ዋና ዋና ነጥብ ከያዙት ርዕሶች ጋር በሚገባ ተዋወቅ። እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከጭብጡ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? በእነዚህ ነጥቦች ሥር የተወሰኑ ንዑስ ነጥቦች ተዘርዝረዋል። እነዚህን ንዑሳን ነጥቦች የሚደግፉ ሐሳቦች ደግሞ ከእነርሱ ሥር ይዘረዘራሉ። በእያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ ሥር ያለው ሐሳብ ከፊተኛው ጋር የሚዛመደውና ወደሚቀጥለው ንዑስ ርዕስ የሚያሸጋግረው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የንግግሩን ዓላማ ለማሳካት ምን ሚና እንደሚጫወት ልብ በል። ጭብጡን ማለትም የንግግሩን ዓላማ ከተረዳህና ዋና ዋና ነጥቦቹ ይህንን ዓላማ የሚያሳኩት እንዴት እንደሆነ ከተገነዘብክ ትምህርቱን ለማዳበር ዝግጁ ነህ ማለት ነው።
መጀመሪያ ላይ ንግግርህን በየንዑስ ርዕሱ ከፋፍለህ ማየቱ ይጠቅምህ ይሆናል። ይህም ማለት አንዱን ንግግር የየራሳቸው ዋና ነጥብ ያላቸው አራት ወይም አምስት አጫጭር ንግግሮች ስብስብ አድርገህ ትመለከተዋለህ ማለት ነው። ከዚያም ተራ በተራ ተዘጋጃቸው።
አስተዋጽኦው የሚረዳህ ለዝግጅት ብቻ ነው። ንግግርህን በምትሰጥበት ጊዜ በቀጥታ እንደ ማስታወሻ እንድትጠቀምበት ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም። አስተዋጽኦ የንግግሩ አፅም ብቻ ነው ለማለት ይቻላል። ይህን አፅም ሥጋ ልታለብሰውና ነፍስ ልትዘራበት ይገባል።
የጥቅሶች አጠቃቀም
ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ የሚያስተምሩት ጥቅሶችን መሠረት በማድረግ ነበር። (ሉቃስ 4:16-21፤ 24:27፤ ሥራ 17:2, 3) አንተም እንደዚህ ማድረግ ትችላለህ። የንግግርህ መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መሆን አለባቸው። በንግግር አስተዋጽኦው ላይ ያሉትን ዓረፍተ ነገሮች እያብራራህ በማስረዳት ብቻ መወሰን የለብህም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሶቹ ዓረፍተ ነገሮቹን የሚደግፉት እንዴት እንደሆነ በማስተዋል እነዚህን ጥቅሶች መሠረት አድርገህ አስተምር።
ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ እያንዳንዱን ጥቅስ አውጥተህ አንብብ። በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ተመልከት። አንዳንዶቹ ጥቅሶች ከጉዳዩ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ግልጽ ለማድረግ የገቡ ሊሆኑ ይችላሉ። በንግግርህ ወቅት የግድ ሁሉንም ጥቅስ እያነበብህ ሐሳብ ልትሰጥበት ይገባል ማለት አይደለም። ለአድማጮችህ ይበልጥ ይስማማሉ የምትላቸውን ጥቅሶች ምረጥ። በንግግሩ አስተዋጽኦ ላይ ባሉት ጥቅሶች ላይ ካተኮርህ ተጨማሪ ጥቅሶችን መጠቀም ላያስፈልግህ ይችላል።
ንግግርህ አድማጮችህን የሚጠቅም መሆኑ የተመካው በምታነብባቸው ጥቅሶች ብዛት ሳይሆን በትምህርቱ የአቀራረብ ጥራት ላይ ነው። ጥቅሶችን በምታስተዋውቅበት ጊዜ የተጠቀሱበትን ምክንያት ግልጽ አድርግ። ጥቅሶቹን ከነጥቡ ጋር ጥሩ አድርገህ ማዛመድ ይኖርብሃል። አንድ ጥቅስ ካነበብህ በኋላ ስለ ጥቅሱ ስታብራራ መጽሐፍ ቅዱስህን አትክደነው። አድማጮችህም እንደ አንተ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው እንደሚቆዩ የታወቀ ነው። አድማጮችህ በትኩረት እንዲከታተሉህና ከአምላክ ቃል ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? (ነህ. 8:8, 12) በማብራራት፣ ምሳሌ በመጠቀምና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን በማስረዳት ይህንን ማድረግ ትችላለህ።
ማብራራት። አንድን ቁልፍ የሆነ ጥቅስ ለማብራራት ስትወስን ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ምን ማለት ነው? በንግግሬ ውስጥ የምጠቅሰው ለምንድን ነው? አድማጮች ስለ ራሳቸው ምን ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል?’ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ፣ ከጥቅሱ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ፣ መቼቱን፣ ቃላቱ ያላቸውን ኃይል እንዲሁም ጸሐፊው በመንፈስ አነሳሽነት መልእክቱን ሲጽፍ ዓላማው ምን እንደነበረ ማጤን ያስፈልግህ ይሆናል። ይህ ደግሞ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ታገኛለህ። (ማቴ. 24:45-47) ስለ ጥቅሱ ሁሉንም ነገር ለማብራራት አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ አድማጮች ጥቅሱን እንዲያነብቡ ያደረግኸው ለምን እንደሆነ አብራራ።
በምሳሌ መጠቀም። በምሳሌ ማስረዳት አድማጮች ነጥቡን ይበልጥ በጥልቀት እንዲያስተውሉ እንዲሁም አንድን ነጥብ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት እንዲያስታውሱ ይረዳል። ምሳሌ መጠቀም አድማጮችህ እየተናገርህ ያለኸውን ነገር አስተውለው ከአሁን ቀደም ከሚያውቁት ጉዳይ ጋር እንዲያዛምዱ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ወቅት ያደረገው ይህንኑ ነበር። “የሰማይ ወፎች፣” “የሜዳ አበቦች፣” ‘የጠበበ ደጅ፣’ ‘በዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት’ የሚሉትና እነዚህን የመሰሉት ብዙ ምሳሌዎቹ ትምህርቱን ትኩረት የሚስብ፣ ግልጽና የማይረሳ እንዲሆን አድርገውታል።—ማቴ. ምዕ. 5–7
እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ማስረዳት። አንድን ጥቅስ ስታብራራና በምሳሌ ስታስረዳ አድማጮችህ እውቀት ያገኛሉ። ይሁን እንጂ ይበልጥ ውጤት የሚኖረው ያንን እውቀት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ማስረዳቱ ነው። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱሱን መልእክት ሰምቶ እርምጃ መውሰድ የእያንዳንዱ አድማጭ ኃላፊነት እንደሆነ አይካድም። ይሁንና ምን ማድረግ እንደሚገባቸው እንዲያስተውሉ ልትረዳቸው ትችላለህ። ጥቅሱ ለአድማጮችህ ግልጽ ከሆነላቸውና ከነጥቡ ጋር ያለው ዝምድና ከገባቸው በኋላ በእምነታቸውና በአኗኗራቸው ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እንዲያስተውሉ አድርግ። እየተብራራ ካለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የማይጣጣሙ አስተሳሰቦችን ወይም ድርጊቶችን መተው ምን ጥቅም እንዳለው ጎላ አድርገህ ግለጽ።
ጥቅሱ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለማስረዳት ስታስብ አድማጮችህ የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብህም። ምናልባት ፍላጎት ያሳዩ አዲሶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና ከተለያዩ ችግሮች ጋር የሚታገሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ንግግርህ አድማጮች በሕይወታቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉ እንዲሆን አድርግ። የተወሰኑ ሰዎችን በአእምሮህ ይዘህ እንደምትናገር የሚያስመስል ምክር ከመስጠት ተቆጠብ።
ለተናጋሪው የተተዉ ውሳኔዎች
ንግግርህን በተመለከተ አንዳንዶቹ ነገሮች አስቀድመው ተወስነዋል። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በግልጽ ተቀምጠዋል እንዲሁም እያንዳንዱን ንዑስ ርዕስ ለማብራራት የሚያስፈልገው ጊዜ ተመድቧል። ሌሎቹ ግን ለአንተ የተተዉ ናቸው። አንዳንዶቹን ንዑሳን ነጥቦች ለማብራራት ከሌሎቹ ይልቅ ሰፋ ያለ ጊዜ ትፈልግ ይሆናል። ሁሉንም ንዑስ ነጥብ በእኩል መጠን መሸፈን አለብኝ ብለህ አታስብ። ይህ ትምህርቱን ለመሸፈን ስትል እንድትሯሯጥና አድማጮችህ ሊይዙት ከሚችሉት በላይ ብዙ ሐሳብ እንድትጭንባቸው ሊያደርግ ይችላል። የትኛውን ነጥብ በጥልቀት አብራርተህ የትኛውን ነጥብ በአጭሩ እንደምትጠቅስ ወይም እግረ መንገድህን ጠቆም አድርገህ ብቻ እንደምታልፍ ለመወሰን የሚረዳህ ምንድን ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የንግግሩን ዋና መልእክት ለማስተላለፍ የሚረዱኝ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? አድማጮቼን ይበልጥ ሊጠቅሙ የሚችሉትስ የትኞቹ ናቸው? አንድን ጥቅስና ከዚያ ጋር ዝምድና ያለውን ሐሳብ ባስቀር የማቀርበውን ማስረጃ ያዳክምብኛልን?’
ግምታዊ ሐሳብ ወይም የግል አመለካከት ላለመጨመር ጥንቃቄ አድርግ። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ‘ከራሱ አንዳች አልተናገረም።’ (ዮሐ. 14:10) ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት መጽሐፍ ቅዱስ ሲብራራ ለማዳመጥ እንደሆነ አስታውስ። ጥሩ ተናጋሪ ነው የሚል ስም አትርፈህ ከሆነ እንዲህ ያለ ስም ልታተርፍ የቻልከው የሰዎችን ትኩረት ወደ ራስህ ስለሳብክ ሳይሆን አድማጮችህ በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩሩ ስላደረግህ እንደሆነ እሙን ነው። እንደዚያ ከሆነ ሰዎች የምትሰጠውን ንግግር ያደንቃሉ።—ፊልጵ. 1:10, 11
መሠረታዊ ነጥቦችን ብቻ የያዘውን አስተዋጽኦ በማዳበር ጥቅሶችን በጥልቀት የሚያብራራ ሕያው ንግግር አድርገኸዋል። አሁን ንግግርህን መለማመድ ያስፈልግሃል። ድምፅህን እያሰማህ ብትለማመድ ጥሩ ነው። የልምምዱ ዋና ዓላማ ሁሉም ነጥቦች በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጹ ማድረግ ነው። በንግግሩ ተመስጠህ፣ ሕያው አድርገህና ግለት ባለው መንገድ ልታቀርብ ይገባል። ንግግርህን ከማቅረብህ በፊት ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህን ንግግር ሳቀርብ ዓላማዬ ምንድን ነው? ዋና ዋና ነጥቦቹ ግልጽ ሆነው ተቀምጠዋልን? ንግግሬ በጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነውን? እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከሚቀጥለው ሐሳብ ጋር በቀላሉ ይያያዛልን? ንግግሩ አድማጮች ለይሖዋና ለዝግጅቶቹ አድናቆት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነውን? መደምደሚያው በቀጥታ ከጭብጡ ጋር የሚዛመድና አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም እንዲሁም ለሥራ የሚያነሳሳ ነውን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ አዎንታዊ ከሆነ ጉባኤውን በሚጠቅምና ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ ‘እውቀትን አሳምረህ ለማቅረብ’ ዝግጁ ነህ ማለት ነው!—ምሳሌ 15:2
-
-
የማስተማር ችሎታህን አዳብርበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
የማስተማር ችሎታህን አዳብር
የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ምን ግብ አውጥተሃል? ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጥቷል። አዲስ አስፋፊ ከሆንክ አንተም ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማስጠናት እንደሚቻል ማወቅ ትፈልግ ይሆናል። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ረገድ ልምድ አግኝተህ ከሆነ ደግሞ ቀጣዩ ግብህ የምትረዳቸውን ሰዎች በተሻለ መንገድ ማሳመን መቻል ይሆናል። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ በሚያነሳሳ መንገድ ማስተማር እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። (3 ዮሐ. 4) ሽማግሌ ከሆንክ ወይም ለዚህ ኃላፊነት ለመብቃት ጥረት እያደረግህ ከሆነ አድማጮችህ ለይሖዋ እና ለመንገዶቹ ጥልቅ አድናቆት እንዲያድርባቸው ማድረግ የምትችል ጥሩ ተናጋሪ መሆን ትፈልግ ይሆናል። እነዚህን ግቦች ዳር ማድረስ የምትችለው እንዴት ነው?
የተዋጣለት አስተማሪ ከነበረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ መማር ትችላለህ። (ሉቃስ 6:40) ኢየሱስ በአንድ ተራራ ጥግ ለተሰበሰቡ ሰዎችም ሆነ በመንገድ ላይ ላገኛቸው ሰዎች የተናገራቸው ቃላትና የተናገረበት መንገድ መልእክቱ ከአድማጮች አእምሮ እንዳይጠፋ የሚያደርግ ነበር። አድማጮቹ በንቃትና በጉጉት እንዲያዳምጡት አድርጓል፤ እንዲሁም ትምህርቱን እንዴት በሕይወታቸው ሊሠሩበት እንደሚችሉ በግልጽ አስረድቷቸዋል። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?
በይሖዋ ታመን
ኢየሱስ ጥሩ የማስተማር ችሎታ የኖረው ከሰማያዊ አባቱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለነበረውና አምላክ በመንፈሱ ስለባረከው ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስጠናት እንድትችል ከልብ ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ? ወላጅ ከሆንህ ልጆችህን ስታስተምር አምላክ መመሪያ እንዲሰጥህ አዘውትረህ ትጸልያለህ? ንግግር ለማቅረብ ወይም የጉባኤ ስብሰባ ለመምራት ስትዘጋጅ ልባዊ ጸሎት ታቀርባለህ? በዚህ መንገድ በመጸለይ በይሖዋ ላይ የምትታመን ከሆነ ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪ ትሆናለህ።
በይሖዋ እንደምትታመን የምታሳይበት ሌላው መንገድ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ መጠቀምህ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት “ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 17:14) ኢየሱስ ብዙ ተሞክሮ የነበረው ቢሆንም ምንም ነገር ከራሱ አመንጭቶ አልተናገረም። አባቱ ያስተማረውን ብቻ ይናገር ነበር። በዚህም ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 12:49, 50) የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ድርጊት፣ አስተሳሰብና ስሜት የመለወጥ ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) የአምላክን ቃል ይበልጥ እያወቅህ ስትሄድና በአገልግሎትህ በሚገባ ስትጠቀምበት ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት የሚያስችል የማስተማር ችሎታ ታዳብራለህ።—2 ጢሞ. 3:16, 17
ይሖዋን አስከብር
የክርስቶስን የማስተማር ዘዴ መኮረጅ ሲባል እንዲያው ጥሩ ንግግር ማቅረብ ማለት አይደለም። እርግጥ ሰዎች ከኢየሱስ አፍ በሚወጣው ‘የጸጋ ቃል’ እንደተገረሙ አይካድም። (ሉቃስ 4:22) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ግሩም ንግግር ያቀረበበት ዓላማ ምን ነበር? የሰዎችን አድናቆት ለማትረፍ ሳይሆን ይሖዋን ለማስከበር ነበር። (ዮሐ. 7:16-18) ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- ‘መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።’ (ማቴ. 5:16) በምናስተምርበት ጊዜም ይህን ምክር ልንሠራበት ይገባል። ምን ጊዜም ጥረታችን ይሖዋን ማስከበር መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም አንድ ነገር ለመናገር ስንፈልግ ወይም እንዴት እንደምንናገር ስናስብ ‘ንግግሬ ሰዎች ይሖዋን ከልብ እንዲያደንቁ የሚያነሳሳ ነው ወይስ ለእኔ ልዩ ግምት እንዲሰጡ የሚያደርግ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።
ለምሳሌ ያህል ምሳሌዎችንና እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን በመጠቀም ጥሩ አድርጎ ማስተማር ይቻላል። ይሁን እንጂ ረጅም የሆነ ምሳሌ ወይም እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ሳይቀር የሚጠቅስ ተሞክሮ የምንናገር ከሆነ የትምህርቱ ዋና ነጥብ ሊድበሰበስ ይችላል። በተመሳሳይም እንዲሁ ለማሳቅ ተብሎ የሚነገር ታሪክ አድማጮችን ከመልእክታችን ሊያዘናጋ ይችላል። በሌላ አባባል አንድ ሰው በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሚቀርብበትን ዋነኛ ዓላማ ዳር ከማድረስ ይልቅ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ይስባል።
“ለዩ”
አንድ ሰው ደቀ መዝሙር እንዲሆን የሚማረው ትምህርት ግልጽ ሊሆንለት ይገባል። እውነትን ማስተዋልና ከሌሎች እምነቶች ጋር ያለውን ልዩነት መገንዘብ ይኖርበታል። ነገሮችን እያነጻጸሩ ማቅረብ ይህን ለማድረግ ይረዳል።
ይሖዋ ሕዝቡ ንጹሕ የሆነውን ንጹሕ ካልሆነው ‘እንዲለይ’ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ዘሌ. 10:9-11) በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ የሚያገለግሉት “በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ” ሌሎችን እንደሚያስተምሩ ተናግሯል። (ሕዝ. 44:23) የምሳሌ መጽሐፍ ብዙ ጊዜ በጻድቃንና በክፉዎች እንዲሁም በጥበብና በስንፍና መካከል ያለውን ልዩነት እያነጻጸረ ያቀርባል። ተቃራኒ ያልሆኑ ነገሮችን እንኳ ሳይቀር ማነጻጸር ይቻላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 5:7 ላይ ጻድቅና ደግ ሰውን አነጻጽሯል። በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ የክርስቶስ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ከአሮን እንደሚልቅ አስረድቷል። በ17ኛው መቶ ዘመን የኖረው አስተማሪ ዮሐን አሞስ ኮሜኒየስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማስተማር የአንድ ነገር ዓላማ፣ ይዘትና አመጣጥ ከሌላው እንዴት እንደሚለይ ማስረዳት ነው ከማለት ሌላ ምንም ፍቺ ሊሰጠው አይችልም። . . . በመሆኑም ጥሩ አስተማሪ የሚባለው አንድ ነገር ከሌላው ጋር ያለውን ልዩነት በግልጽ ማስቀመጥ የሚችል ሰው ነው።”
ለምሳሌ ያህል አንድን ሰው ስለ አምላክ መንግሥት ለማስተማር አስበሃል እንበል። የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ የማያውቅ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ ነው በሚለው የሰዎች እምነት መካከል ያለውን ልዩነት ልታስረዳው ትችል ይሆናል። ወይም ደግሞ የአምላክ መንግሥት ከሰብዓዊ መንግሥታት እንዴት እንደሚለይ ልትገልጽለት ትችላለህ። ይህን መሠረታዊ እውነት ለሚያውቁ ሰዎች ግን ከዚህ ይበልጥ ጥልቀት ያላቸውን ጉዳዮች ማንሳት ትችላለህ። መሲሐዊው መንግሥት በመዝሙር 103:19 ላይ ተጠቅሶ ከሚገኘው ከይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ንግሥና ወይም በቆላስይስ 1:13 ላይ ከተጠቀሰው ‘የፍቅሩ ልጅ መንግሥት’ ወይም በኤፌሶን 1:10 ላይ ከተነገረለት ‘አስተዳደር’ እንዴት እንደሚለይ ማስረዳት ትችል ይሆናል። ነገሮችን እያነጻጸሩ የማስተማርን ዘዴ በመጠቀም ይህ አስፈላጊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለአድማጮች ቁልጭ ብሎ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል።
ኢየሱስ ይህንን የማስተማር ዘዴ ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ብዙዎች ስለ ሙሴ ሕግ የነበራቸውን ግንዛቤ ከሕጉ ትክክለኛ መንፈስ ጋር እያነጻጸረ ተናግሯል። (ማቴ. 5:21-48) ከልቡ ለአምላክ ያደረ ሰው በሚያሳየው ባሕርይና በፈሪሳውያን የግብዝነት ድርጊት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ አስረድቷል። (ማቴ. 6:1-18) ሌሎች የሚያሳዩትን በሰዎች ላይ ‘የመሠልጠን’ መንፈስ ተከታዮቹ ከሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ጋር አነጻጽሯል። (ማቴ. 20:25-28) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ በማቴዎስ 21:28-32 ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው አድማጮቹ ራስን በማመጻደቅና በእውነተኛ ንስሐ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያመዛዝኑ አድርጓል። ይህ ደግሞ ወደ ሌላኛው ጥሩ የማስተማር ዘዴ ይመራናል።
አድማጮች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡ ማድረግ
በማቴዎስ 21:28 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ወደ ንጽጽሩ ከመሄዱ በፊት “ምን ይመስላችኋል?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። አንድ ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ እንዲሁ እውነቱን ተናግሮ ብቻ ከማለፍ ይልቅ አድማጮቹ አእምሮአቸውን እንዲያሠሩ የሚያደርግ ዘዴ ይጠቀማል። (ምሳሌ 3:21፤ ሮሜ 12:1) ይህንን ማድረግ ከሚቻልበት መንገድ አንዱ ጥያቄ መጠየቅ ነው። በማቴዎስ 17:25 ላይ ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ጠይቋል:- ‘ስምዖን ሆይ፣ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች?’ አእምሮን የሚያመራምሩት እነዚህ የኢየሱስ ጥያቄዎች ጴጥሮስ የቤተ መቅደስ ቀረጥ መክፈልን በተመለከተ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ረድተውታል። በተመሳሳይም ኢየሱስ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ አንድ ካህን እና ሌዋዊ ያደረጉትን ነገር ከአንድ ሳምራዊ ድርጊት ጋር በማነጻጸር አስረድቷል። ከዚያም “እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። (ሉቃስ 10:29-36) እዚህም ላይ ቢሆን ኢየሱስ መልሱን ከመናገር ይልቅ አድማጩ አስቦ ለጥያቄው ራሱ መልስ እንዲሰጥ ማድረጉ ነበር።—ሉቃስ 7:41-43
የአድማጭህን ልብ መንካት
የአምላክን ቃል ትክክለኛ መንፈስ የተረዳ አስተማሪ እውነተኛ አምልኮ ሲባል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ማስታወስ ወይም የተወሰኑ ሕጎችን መታዘዝ ማለት ብቻ እንዳልሆነ ይገነዘባል። እውነተኛው አምልኮ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትንና የእርሱ መንገዶች የተሻሉ መሆናቸውን መገንዘብን ይጠይቃል። እንዲህ ያለው አምልኮ ከልብ የሚመነጭ ነው። (ዘዳ. 10:12, 13፤ ሉቃስ 10:25-27) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ልብ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ምኞትን፣ ፍቅርን፣ ስሜትንና ውስጣዊ ግፊትን ጨምሮ የሰውዬውን ማንነት የሚያመለክት ነው።
ሰዎች የሚያዩት ውጫዊውን ማንነት ቢሆንም አምላክ ልብን እንደሚያይ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (1 ሳሙ. 16:7) አምላክን የምናገለግለው ለእርሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን እንጂ የሰዎችን አድናቆት ለማትረፍ ብለን መሆን የለበትም። (ማቴ. 6:5-8) ፈሪሳውያን ግን ለሌሎች ለመታየት ብለው ብዙ ነገሮች ያደርጉ ነበር። በእነርሱ ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር ሕጉን አንድ በአንድ መጠበቅና እነርሱ ያወጡትን ደንብ ማክበር ነበር። አምላክን እናመልካለን ይበሉ እንጂ የእርሱ አገልጋዮች መሆናቸውን ለይተው የሚያሳውቁ ባሕርያትን ማፍራት ሳይችሉ ቀርተዋል። (ማቴ. 9:13፤ ሉቃስ 11:42) ኢየሱስ የይሖዋን ትእዛዛት ማክበር አስፈላጊ ቢሆንም እንድንታዘዝ የሚገፋፋን የልብ ዝንባሌ ወሳኝ እንደሆነ አስተምሯል። (ማቴ. 15:7-9፤ ማር. 7:20-23፤ ዮሐ. 3:36) የኢየሱስን ምሳሌ የምንኮርጅ ከሆነ በማስተማር ሥራችን ግሩም ውጤት እናገኛለን። ሰዎች አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲያውቁ መርዳታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ እውን ሊሆንላቸውና ከልብ ሊወድዱት ይገባል። እንዲህ ከሆነ አኗኗራቸው ከእውነተኛው አምላክ ጋር ዝምድና መመሥረትን ምን ያህል ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
እርግጥ እንዲህ ካለው ትምህርት ለመጠቀም ልባቸውን በሐቀኝነት መመርመር ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ሰዎች ውስጣዊ ግፊታቸውንና ስሜታቸውን እንዲመረምሩ አበረታትቷል። የአድማጮቹን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም ሲፈልግ አንድን ነገር ለምን እንዳሰቡ፣ እንደተናገሩ ወይም እንዳደረጉ ይጠይቃቸው ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ጠይቆ ብቻ ዝም አይልም። ተጨማሪ ሐሳብ በመናገር ወይም ምሳሌ በመጥቀስ አለዚያም አንድ ነገር በማድረግ ጉዳዩን ከትክክለኛው አቅጣጫ እንዲያዩት ይረዳቸው ነበር። (ማር. 2:8፤ 4:40፤ 8:17፤ ሉቃስ 6:41, 46) በተመሳሳይ አድማጮቻችን እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ራሳቸውን እንዲጠይቁ በማድረግ ልንረዳቸው እንችላለን:- ‘ይህ የተከተልኩት ጎዳና ለእኔ መልካም መስሎ የታየኝ ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረግሁት ለምንድን ነው?’ ከዚያም ጉዳዩን በይሖዋ ዓይን እንዲያዩት አነሳሳቸው።
ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ማስረዳት
አንድ ጥሩ አስተማሪ “ጥበብ ዓይነተኛ ነገር” መሆኑን ያውቃል። (ምሳሌ 4:7) ጥበብ ደግሞ ችግሮችን ለመፍታት፣ ከአደጋ ለመራቅ፣ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ እንዲሁም ሌሎችን ለመርዳት እውቀትን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ነው። ተማሪዎቹ እንዲህ ማድረግን እንዲማሩ መርዳት የአስተማሪው ኃላፊነት ነው። ይወስንላቸዋል ማለት ግን አይደለም። በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስትወያዩ ተማሪው እንዲያመዛዝን እርዳው። በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥም አንድ ምሳሌ በመጥቀስ ተማሪው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመው ያጠናችሁት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሊረዳው የሚችለው እንዴት እንደሆነ ጠይቀው።—ዕብ. 5:14
ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በሰጠው ንግግር ሰዎች አኗኗራቸውን እንዲለውጡ በሚያንቀሳቅስ ሁኔታ ትምህርቱን ተግባራዊ አድርጎ ካቀረበበት መንገድ መማር እንችላለን። (ሥራ 2:14-36) ጴጥሮስ ሰዎቹ እናምንባቸዋለን ከሚሏቸው መጻሕፍት የተወሰዱ ሦስት ጥቅሶች ተጠቅሞ አድማጮቹ ከሚያውቁት ነገር ጋር በማዛመድ ጥቅሶቹን ተግባራዊ በሆነ መንገድ አብራርቷል። ከዚህ የተነሣ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች አንድ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር። አንተስ የምታስተምረው ሰዎች እርምጃ እንዲወስዱ በሚያነሳሳ መንገድ ነው? እውነታውን ከማስረዳት አልፈህ ምክንያቱን ጭምር ታብራራለህ? እየተማሩት ያለው ነገር ሕይወታቸውን እንዴት ሊነካው እንደሚገባ እንዲያስተውሉ ታበረታታቸዋለህ? በጰንጠቆስጤ ዕለት ተሰብስቦ እንደነበረው ሕዝብ ቃል በቃል “ምን እናድርግ?” አይሉ ይሆናል። ይሁንና ጥቅሱን እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል ካስረዳሃቸው ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ይነሳሳሉ።—ሥራ 2:37
ወላጅ ከሆንክ ከልጆችህ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ እንዲያስቡ የማሠልጠን አጋጣሚ ይኖርሃል። (ኤፌ. 6:4) ለምሳሌ ያህል ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ጥቂት ጥቅሶችን መርጠህ ትርጉማቸውን ካብራራህ በኋላ እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ልታነሣ ትችላለህ:- ‘ይህ ጥቅስ መመሪያ የሚሆነን እንዴት ነው? እነዚህን ጥቅሶች በአገልግሎት ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋና እርሱ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ምን ይጠቁሙናል? ይህስ ለእርሱ ያለንን አድናቆት የሚጨምርልን እንዴት ነው?’ የቤተሰብህ አባላት በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ጎላ ያሉ ነጥቦች ላይ ውይይት ሲደረግ እነዚህን ነጥቦች በተመለከተ ሐሳብ እንዲሰጡ አበረታታ። ሐሳብ የሰጡባቸውን ጥቅሶች ፈጽሞ እንደማይረሷቸው የታወቀ ነው።
ጥሩ ምሳሌ ሁን
የምታስተምረው በንግግርህ ብቻ ሳይሆን በድርጊትህም ጭምር ነው። ድርጊትህ የምትናገረውን ነገር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ ይሆናል። ልጆች ደግሞ የሚማሩት ከድርጊትህ ነው። ወላጆቻቸውን የሚኮርጁ ከሆነ እንደ ወላጆቻቸው መሆን ይፈልጋሉ ማለት ነው። ወላጆቻቸው የሚያደርጉትን ነገር ማድረግ ያስደስታቸዋል። በተመሳሳይም ‘አንተ ክርስቶስን እንደምትመስል’ ሁሉ የምታስተምራቸውም ሰዎች አንተን ሲኮርጁ በይሖዋ መንገድ መመላለስ የሚያስገኘውን በረከት ያጭዳሉ። (1 ቆሮ. 11:1) በግላቸው አምላክ ለእኔ እንዲህ አድርጎልኛል የሚሉት ነገር ይኖራቸዋል።
ይህም ጥሩ ምሳሌ ሆኖ መገኘት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ግሩም ማሳሰቢያ ነው። ‘በቅዱስ ኑሮ ለአምላክ ያደርን ሆነን’ መመላለሳችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ለምናስተምራቸው ሰዎች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። (2 ጴጥ. 3:11) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የአምላክን ቃል አዘውትሮ እንዲያነብብ የምታበረታታ ከሆነ አንተ ራስህ ይህን በማድረግ ልትተጋ ይገባል። ልጆችህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመሩ የምትፈልግ ከሆነ አንተ የምታደርጋቸው ነገሮችም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ጉባኤው በአገልግሎት ቀናተኛ እንዲሆን የምታስተምር ከሆነ አንተ ራስህ በዚህ ሥራ ጥሩ ተሳትፎ ሊኖርህ ይገባል። የምታስተምረውን ነገር ከሠራህበት ሌሎችንም በቀላሉ ለሥራ ማነሳሳት ትችላለህ።—ሮሜ 2:21-23
የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል እንድትችል ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የማስተምረው አድማጮቼ በዝንባሌያቸው፣ በንግግራቸው ወይም በድርጊታቸው ለውጥ እንዲያደርጉ በሚረዳ መንገድ ነውን? በሁለት ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለአድማጮቼ ግልጽ አድርጌ አቀርባለሁን? መጽሐፍ ቅዱስ የማስተምራቸው ሰዎች፣ ልጆቼ ወይም በስብሰባ ላይ የተገኙ አድማጮቼ ትምህርቱን እንዲያስታውሱ ለመርዳት ምን ጥረት አደርጋለሁ? አድማጮቼ እየተማሩ ያሉትን ነገር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ግልጽ ይሆንላቸዋልን? እኔ ምሳሌ እሆናቸዋለሁን? ለትምህርቱ የሚሰጡት ምላሽ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዴት ሊነካው እንደሚችል ያስተውላሉን?’ (ምሳሌ 9:10) የማስተማር ችሎታህን ለማዳበር በምታደርገው ጥረት እነዚህን ጉዳዮች ፈጽሞ ቸል ልትል አይገባም። “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።”—1 ጢሞ. 4:16
-