-
በመንፈሳዊው ዓለም ስለሚኖሩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎችመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 6
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች
በመንፈሳዊው ዓለም ስለሚኖሩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎች
ስለ መንፈሳዊው ዓለምም ሆነ በዚያ ስለሚኖሩት አካላት ጥያቄ ተፈጥሮብህ ያውቃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰዎች ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ ግምታዊ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ ኖረዋል። አንዳንዶች መንፈሳዊው ዓለም፣ ልዩ ክብር ይገባቸዋል ብለው የሚያስቧቸው የቀድሞ አባቶች መኖሪያ እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መላእክትና በሞት ያንቀላፉ ጥሩ ሰዎች የሚኖሩበት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ እንደሆነ አድርገው በአእምሯቸው ይስሉታል። መንፈሳዊው ዓለም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማልክት የሚኖሩበት ቦታ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ።
አንዳንዶች ደግሞ ‘ሰማይ ሄዶ የመጣና ስለዚያ የነገረን ስለሌለ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ምንም ማወቅ አንችልም’ ብለው ይናገራሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የተሳሳተ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ማለትም በመንፈሳዊው ዓለም ይኖር ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች “ከሰማይ የመጣሁት የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። ስለሆነም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ” ብሎ ሲነግራቸው በገዛ ዓይኑ ስላየው ነገር እየገለጸ ነበር።—ዮሐንስ 6:38፤ 14:2
የኢየሱስ አባት የሆነው ይሖዋ ‘ቤቱ’ ማለትም መኖሪያው በሰማይ ነው። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም በዓይን ስለማይታየው ዓለም ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጠን የሚችል አካል የለም። ይሖዋና ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ባሳዩአቸው አስደናቂ ራእዮች አማካኝነት ስለ መንፈሳዊው ዓለም ብዙ ነገሮችን ገልጸውልናል።
ቀጣዩ ርዕስ ሰዎች ስላዩአቸው በርካታ ራእዮች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያብራራል። ስለ እነዚህ ራእዮች ስታነብ፣ መንፈሳዊው ዓለም እኛ የሰው ልጆች ልናያቸውና ልንዳስሳቸው በምንችላቸው ነገሮች የተሞላ ግዑዝ ነገር እንዳልሆነ አስታውስ። በመሆኑም አምላክ፣ መንፈሳዊውን ዓለም የገለጸው መንፈሳዊ አካላት ብቻ ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ለመግለጽ ሲል የተለያዩ ራእዮችን አሳይቷል። እነዚህ ራእዮች በመንፈሳዊው ዓለም ባለው “ብዙ መኖሪያ” ውስጥ የሚኖሩትን አካላት በተመለከተ ግንዛቤ እንድታገኝ ይረዱሃል።
-
-
በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮችመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 6
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች
በሰማይ ስለሚኖሩት አካላት የሚገልጹ ራእዮች
መጽሐፍ ቅዱስ በዓይን የማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ምን እንደሚመስል ፍንጭ የሚሰጡ በርካታ አስደናቂ ራእዮችን ይዟል። እነዚህን ራእዮች በትኩረት እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ራእዮቹ በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩትን አካላት በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንድንችል ብቻ ሳይሆን እነዚህ አካላት በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እንድንገነዘብ ጭምር ይረዱናል፤ እርግጥ በእነዚህ ራእዮች ላይ የተገለጹት ነገሮች ሁሉ ቃል በቃል ይወሰዳሉ ማለት አይደለም።
ከሁሉ የላቀው ይሖዋ
“በሰማይ አንድ ዙፋን ተቀምጦ ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበር። በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይና የሰርድዮን ድንጋይ ዓይነት መልክ ነበረው፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር።”—ራእይ 4:2, 3
“በዙሪያውም ደማቅ ብርሃን ነበር፤ ይህም ዝናባማ በሆነ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ነበር። በዙሪያው ያለው ደማቅ ብርሃን ይህን ይመስላል። ደግሞም የይሖዋን ክብር ይመስል ነበር።”—ሕዝቅኤል 1:27, 28
ሐዋርያው ዮሐንስና ነቢዩ ሕዝቅኤል የተመለከቷቸው እነዚህ ራእዮች በቀላሉ በዓይነ ሕሊናችን ልንስላቸው የምንችላቸውን ነገሮች ይኸውም የሚያብረቀርቁ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ቀስተ ደመናን እንዲሁም የዙፋንን ክብር በመጠቀም ልዑሉ አምላክ ይሖዋ ያለውን ግርማ ይገልጻሉ። እነዚህ ራእዮች፣ ይሖዋ የሚኖርበት ቦታ አስደናቂ ውበት የተላበሰና አስደሳች እንዲሁም ሰላም የሰፈነበት እንደሆነ ያሳያሉ።
አምላክ በዚህ መንገድ መገለጹ መዝሙራዊው ከጻፈው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው፦ “ይሖዋ ታላቅ ነው፤ ደግሞም እጅግ ሊወደስ ይገባዋል። ከሌሎች አማልክት ሁሉ በላይ እጅግ የሚፈራ ነው። የሌሎች ሕዝቦች አማልክት ሁሉ ከንቱ ናቸው፤ ይሖዋ ግን ሰማያትን የሠራ አምላክ ነው። ሞገስና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ ብርታትና ውበት በመቅደሱ ውስጥ አሉ።”—መዝሙር 96:4-6
ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ቢሆንም እንኳ ወደ እሱ በጸሎት እንድንቀርብ ያበረታታናል፤ እንዲሁም ጸሎታችንን እንደሚሰማ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 65:2) ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት መጻፉ አምላክ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን ያሳያል።—1 ዮሐንስ 4:8
ከአምላክ ጋር ያለው ኢየሱስ
“[የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነው እስጢፋኖስ] በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ፤ ከዚያም ‘እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ’ አለ።”—የሐዋርያት ሥራ 7:55, 56
እስጢፋኖስ ይህን ራእይ ከማየቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ኢየሱስ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ቀስቃሽነት ተገድሎ ነበር፤ እስጢፋኖስ ከላይ ያለውን የተናገረው ለእነዚሁ የሃይማኖት መሪዎች ነው። ራእዩ ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ በሰማይ ክብር እንደተጎናጸፈ ያረጋግጣል። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦ “[ይሖዋ] ክርስቶስን ከሞት [አስነስቶ] በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ [አስቀምጦታል]፤ . . . በዚህ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ጭምር ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት እንዲሁም ከተሰየመው ከየትኛውም ስም በላይ እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።”—ኤፌሶን 1:20, 21
ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ ያለውን ከፍ ያለ ቦታ ከመናገር ባለፈ እሱም እንደ ይሖዋ ለሰው ልጆች ከልቡ እንደሚያስብ ይገልጻሉ። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፣ ሕመምተኞችንና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ፈውሷል፤ እንዲሁም ሙታንን አስነስቷል። በተጨማሪም መሥዋዕት ሆኖ በመሞት ለአምላክና ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ኤፌሶን 2:4, 5) በአምላክ ቀኝ ያለው ኢየሱስ በቅርቡ ሥልጣኑን በመጠቀም በሁሉም ቦታ ለሚገኙ ታዛዥ የሰው ልጆች ታላቅ በረከት ያመጣል።
አምላክን የሚያገለግሉ መላእክት
“እኔም [ነቢዩ ዳንኤል] እየተመለከትኩ ሳለ ዙፋኖች ተዘጋጁ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውም [ይሖዋ] ተቀመጠ። . . . ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም በፊቱ ቆመው ነበር። ችሎቱ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።”—ዳንኤል 7:9, 10
ዳንኤል ባየው በዚህ ራእይ ላይ አንድ ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ መላእክትን ተመልክቷል። ይህን ራእይ ሲመለከት በጣም ተደንቆ መሆን አለበት! መላእክት፣ ክብር የተጎናጸፉ እንዲሁም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ኃያል መንፈሳዊ አካላት ናቸው። የተለያየ ማዕረግ ያላቸው መላእክት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሱራፌልና ኪሩቤል ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ250 ጊዜ በላይ ስለ መላእክት ተጠቅሷል።
መላእክት ቀደም ሲል ሰዎች የነበሩ ፍጥረታት አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አምላክ መላእክትን የፈጠረው የሰው ልጆች ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ምድር ስትመሠረት መላእክት በቦታው ተገኝተው የተመለከቱ ሲሆን ደስታቸውን በእልልታ ገልጸዋል።—ኢዮብ 38:4-7
ታማኝ መላእክት አምላክን ከሚያገለግሉባቸው መንገዶች አንዱ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ከሚከናወኑት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጁ ሥራ መካፈል ነው። (ማቴዎስ 24:14) ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው በሚከተለው ራእይ ላይ መላእክት በዚህ ሥራ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ተገልጿል፦ “ሌላም መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እሱም በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ ነበር።” (ራእይ 14:6) መላእክት በጥንት ዘመን ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ከሰዎች ጋር ባይነጋገሩም እንኳ የአምላክ አገልጋዮች ምሥራቹን ሲያውጁ ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ ይረዳሉ።
ሚሊዮኖችን የሚያስተው ሰይጣን
“በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና [ኢየሱስ ክርስቶስ] መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤ ነገር ግን አልቻሏቸውም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”—ራእይ 12:7-9
በሰማይ ያለውን ሰላም የሚያደፈርስ ሁኔታ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር። ገና በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ መልአክ ለመመለክ ባለው ከፍተኛ ምኞት የተነሳ በይሖዋ ላይ ዓመፀ፤ በዚህም ምክንያት ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ። በኋላም ሌሎች መላእክት ከእሱ ጋር ያመፁ ሲሆን እነዚህ መላእክት አጋንንት ተብለው ይጠሩ ጀመር። ሰይጣንና አጋንንቱ እጅግ ክፉ ከመሆናቸውም በላይ ይሖዋን አጥብቀው ይቃወማሉ፤ እንዲሁም ብዙ ሰዎችን ፍቅር ከሚንጸባረቅበት የይሖዋ አመራር እንዲርቁ አድርገዋል።
ሰይጣንና አጋንንቱ ያዘቀጠ ምግባር ያላቸው ከመሆኑም በላይ ጨካኝ ናቸው። ዋነኛ የሰው ልጅ ጠላቶች ሲሆኑ በምድር ላይ ያለው መከራ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን የታማኙን የኢዮብን ከብቶችና አገልጋዮች ገድሎበታል። በመቀጠል ደግሞ “ኃይለኛ ነፋስ” የኢዮብ ልጆች ያሉበትን ቤት እንዲመታ በማድረግ አሥሩንም ልጆቹን ገደለበት። ሰይጣን ይህም ሳይበቃው ኢዮብን “ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው።”—ኢዮብ 1:7-19፤ 2:7
ሆኖም በቅርቡ ሰይጣን ይወገዳል። ሰይጣን ወደ ምድር ከተወረወረበት ጊዜ አንስቶ “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው” ያውቃል። (ራእይ 12:12) ሰይጣን ጥፋት ተፈርዶበታል፤ ይህ ታዲያ የምሥራች አይደለም?
ከምድር የተዋጁ ሰዎች
“በደምህም ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ ሰዎችን ለአምላክ ዋጅተሃል፤ እንዲሁም ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ አድርገሃቸዋል፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”—ራእይ 5:9, 10
ኢየሱስ በምድር ላይ ትንሣኤ እንዳገኘና በሰማይ እንዲኖር ሕይወት እንደተሰጠው ሁሉ ሌሎች ሰዎችም በሰማይ ሕይወት ያገኛሉ። ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁና። ደግሞም . . . እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።”—ዮሐንስ 14:2, 3
እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለአንድ ዓላማ ነው። ወደፊት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከኢየሱስ ጋር በመሆን በመላው የምድር ነዋሪዎች ላይ ይገዛሉ፤ ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ ተከታዮቹ ስለዚህ መንግሥት እንዲህ ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።”—ማቴዎስ 6:9, 10
በሰማይ የሚኖሩት አካላት ወደፊት ምን ያደርጋሉ?
“ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ ‘እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።’”—ራእይ 21:3, 4
ይህ ትንቢታዊ ራእይ፣ ኢየሱስና ከምድር ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች የሚያስተዳድሩበት የአምላክ መንግሥት የሰይጣንን ግዛት አጥፍቶ ምድርን ገነት ስለሚያደርግበት ጊዜ የሚናገር ነው። የሰው ልጆችን ለሥቃይና ለሰቆቃ የሚዳርጉ ነገሮች ከዚያ በኋላ አይኖሩም። ሞትም ጭምር ይወገዳል።
ከሞቱ በኋላ ትንሣኤ የሚያገኙት ሆኖም ወደ ሰማይ የማይሄዱት በቢሊዮን የሚቆጠሩት ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? እነዚህ ሰዎች ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል።—ሉቃስ 23:43
እነዚህ ራእዮች ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ታማኝ መላእክትና ከምድር የተዋጁ ሰዎች በጥልቅ እንደሚያስቡልንና የእኛን ደኅንነት እንደሚመኙ ያረጋግጡልናል። ወደፊት ስለሚያከናውኑት ነገር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግክ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድታነጋግር ወይም www.pr2711.com/am ከተባለው ድረ ገጻችን ላይ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንድታወርድ እናበረታታሃለን።
-