-
የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 3
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
“የኔ ፍቅር . . . አምላክ የተሻለውን ነገር ስለሚያውቅ . . . በቃ አታልቅሺ።”
አንዲት ሴት ወደ ቤቤ ጠጋ ብላ ይህን ሐሳብ በጆሮዋ ሹክ አለቻት። በዚህ ወቅት ቤቤ፣ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ባለፈው የአባቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ነበረች።
ቤቤ ከአባቷ ጋር በጣም ትዋደድ ነበር። መግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ በአሳቢነት ተነሳስታ የተናገረችው የቤቤ የቅርብ ወዳጅ ብትሆንም ንግግሩ ቤቤን ከማጽናናት ይልቅ ጎዳት። ቤቤ “አባባ ባይሞት ይሻል ነበር” እያለች ታጉተመትም ነበር። ከዓመታት በኋላ ቤቤ በጻፈችው መጽሐፍ ላይ ይህን ገጠመኝ ማውሳቷ በዚህ ጊዜም ቢሆን ሐዘኑ እንዳልወጣላት በግልጽ ያሳያል።
ቤቤ በራሷ ሕይወት እንደተመለከተችው፣ አንድ ሐዘንተኛ በተለይ ከሟቹ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከነበረው ከሐዘኑ ለመጽናናት ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞት “የመጨረሻው ጠላት” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ሞት ልንቋቋመው በማንችለው ሁኔታ ሕይወታችንን የሚያመሰቃቅልብን ከመሆኑም ሌላ አብዛኛውን ጊዜ ባልጠበቅነው ሰዓት በጣም የምንወዳቸውን ሰዎች ይነጥቀናል። ሞት ከሚያስከትለው ከባድ ጉዳት ማምለጥ የሚችል የለም። በመሆኑም የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን የተነሳ ግራ ብንጋባ የሚያስገርም አይደለም።
ምናልባት እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎች ተፈጥረውብህ ይሆናል፦ ‘ሐዘኑን ለመርሳት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብኛል? አንድ ሰው ከደረሰበት ሐዘን መጽናናት የሚችለው እንዴት ነው? ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት ምን ማድረግ እችላለሁ? በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?’
-
-
ማዘን ስህተት ነው?መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 3
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
ማዘን ስህተት ነው?
ለአጭር ጊዜ ታመህ ታውቃለህ? ምናልባትም ቶሎ ከመዳንህ የተነሳ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ ረስተኸው ሊሆን ይችላል። ሐዘን ግን እንዲህ በቀላሉ የሚረሳ ነገር አይደለም። ዶክተር አለን ውልፌልት ሂሊንግ ኤ ስፓውዝስ ግሪቪንግ ኸርት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “‘ሐዘንን መርሳት’ ብሎ ነገር የለም” ሲሉ ጽፈዋል። አክለው ግን “በጊዜ ሂደት እና ሌሎች በሚሰጧችሁ እርዳታ ሐዘኑ እየቀለላችሁ ይመጣል” ብለዋል።
ለምሳሌ ያህል፣ የቤተሰብ ራስ የነበረው አብርሃም ሚስቱ ሣራ ስትሞት የተሰማውን ስሜት እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “አብርሃምም በሣራ ሞት ያዝንና ያለቅስ ጀመር” ይላል። “ጀመር” የሚለው ቃል አብርሃም ከሐዘኑ ለመጽናናት የተወሰነ ጊዜ እንደፈጀበት ያሳያል።a ሌላው ምሳሌ ደግሞ ያዕቆብ ነው፤ ያዕቆብ ልጁ በአውሬ እንደተበላ የተነገረውን የሐሰት ወሬ አምኖ በመቀበሉ “ለብዙ ቀናት” አልቅሷል። እንዲያውም የቤተሰቡ አባላት ሊያጽናኑት አልቻሉም። ዓመታት ካለፉ በኋላም የዮሴፍ ሞት ያደረሰበት ሐዘን ከልቡ አልወጣም።—ዘፍጥረት 23:2፤ 37:34, 35፤ 42:36፤ 45:28
አብርሃም የሚወዳት ሚስቱ ሣራ ስትሞት በጣም አዝኗል
በዛሬው ጊዜ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።
“ባለቤቴ ሮበርት የሞተው ሐምሌ 9, 2008 ነው። ለሞት የዳረገው አደጋ በደረሰበት ዕለት ጠዋት የነበረው ሁኔታ ከሌሎች ቀናት የተለየ አልነበረም። ቁርስ በልተን ስንጨርስ ሁሌ ወደ ሥራ ሲሄድ እንደምናደርገው ተቃቅፈን ከተሳሳምን በኋላ ‘እወድሃለሁ’ ‘እወድሻለሁ’ ተባብለን ተለያየን። ከስድስት ዓመታት በኋላም ሐዘኑ ከውስጤ አልወጣም። ሮብን ማጣቴ ካስከተለብኝ ሐዘን መቼም ቢሆን የምጽናና አይመስለኝም።”—ጌል፣ ዕድሜ 60
“የምወዳት ባለቤቴን በሞት ካጣሁ 18 ዓመት አልፎኛል፤ ያም ሆኖ አሁንም ልቤ ውስጥ አለች፤ ሐዘኑም ቢሆን አለቀቀኝም። በአካባቢዬ ውብ የሆነ ተፈጥሮ ባየሁ ቁጥር ትዝ ትለኛለች፤ በሕይወት ኖራ እኔ የማየውን ነገር ብታይ ምን ያህል ልትደሰት እንደምትችል አስባለሁ።”—ኤይቴና፣ ዕድሜ 84
እንዲህ ያለ ከባድ ጉዳት የሚያደርስና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ስሜት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው። ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ከሰው ሰው ስለሚለያይ ሌሎች አሳዛኝ ሁኔታ ሲገጥማቸው በሚሰጡት ምላሽ ላይ መፍረድ ተገቢ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ሐዘናችን ከልክ እንዳለፈ በሚሰማን ጊዜ ራሳችንን ከመኮነን መቆጠብ ይኖርብናል። ታዲያ የደረሰብንን ሐዘን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
a የአብርሃም ልጅ ይስሐቅም ቢሆን ከደረሰበት ሐዘን ለመጽናናት ረጅም ጊዜ ወስዶበታል። በዚህ እትም ውስጥ ከሚገኘው “በእምነታቸው ምሰሏቸው” ከሚለው ርዕስ መረዳት እንደምንችለው ይስሐቅ እናቱ ሣራ ከሞተች ከሦስት ዓመታት በኋላም ሐዘኑ አልወጣለትም ነበር።—ዘፍጥረት 24:67
-
-
የደረሰብህን ሐዘን መቋቋምመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 3
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም
ሐዘን የደረሰበትን ሰው ከማጽናናት ጋር በተያያዘ ምክር የማይሰጥ ሰው የለም ቢባል ይቀልላል። ይሁንና ሁሉም ምክር ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች እንዳታለቅስ ወይም ስሜትህን ዋጥ አድርገህ እንድትይዝ ሊመክሩህ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ስሜትህን ሁሉ እንድታወጣ ይገፋፉህ ይሆናል። ከዚህ በተለየ መጽሐፍ ቅዱስ ሚዛናዊ የሆነ ሐሳብ ይዟል፤ በዘመናችን ያሉ ተመራማሪዎችም ይህን ሐሳብ ይጋራሉ።
በአንዳንድ ባሕሎች ወንድ ልጅ ማልቀስ እንደሌለበት ይነገራል። ይሁንና አንድ ሰው በሰው ፊት ማልቀስ አሳፋሪ ነገር እንደሆነ ሊሰማው ይገባል? የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ማልቀስ የተለመደ የሐዘን ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። የደረሰብህ ጉዳት መራራ ቢሆንም ስሜትህን ማውጣትህ፣ ውሎ አድሮ ሁኔታውን ተቋቁመህ እንድትቀጥል ሊረዳህ ይችላል። ይሁን እንጂ ሐዘንን ማፈን ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ማልቀስ ተገቢ አይደለም የሚለውንም ሆነ ወንድ ልጅ ማልቀስ የለበትም የሚለውን አስተሳሰብ አይደግፍም። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ኃይል ቢኖረውም እንኳ ወዳጁ አልዓዛር በሞተበት ወቅት በሰው ፊት አልቅሷል!—ዮሐንስ 11:33-35
በተለይ አንድን ሰው በሞት ያጣነው በድንገት ከሆነ አልፎ አልፎ የብስጭት ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ሐዘን የደረሰበት ሰው እንዲበሳጭ የሚያደርገው ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ በአክብሮት የምናየው ሰው ያልታሰበበትና አግባብ ያልሆነ ነገር ሲናገር እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጠርብን ይችላል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ሲሞት ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ አንድ የአንግሊካን ሰባኪ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አምላክ ጥሩ ሰዎች እንደሚያስፈልጉትና እነሱን በጊዜ እንደሚወስዳቸው ገለጸ።a አባታችን አብሮን መሆኑ በጣም ያስፈልገን ስለነበር ይህ አባባሉ አበሳጨኝ። ይህ ከሆነ 63 ዓመት ያለፈ ቢሆንም አባባሉ አሁንም ስሜቴ እንደጎዳው ነው።”
ስለ ጥፋተኝነት ስሜትስ ምን ማለት ይቻላል? በተለይ ግለሰቡ የሞተው በድንገት ከሆነ ሐዘንተኛው ‘እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ እኮ ባልሞተ ነበር’ በማለት ሊያውጠነጥን ይችላል። አሊያም ደግሞ ከሟቹ ጋር በተያያዘ ትዝ የሚልህ የመጨረሻው ነገር በመካከላችሁ የተፈጠረው ጭቅጭቅ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜቱን ያባብስብህ ይሆናል።
በጥፋተኝነት ስሜት እና በብስጭት ከተዋጥክ እነዚህን ስሜቶች አፍነህ አለመያዝህ በጣም ይረዳሃል። ከዚህ ይልቅ ለሚያዳምጥህና ሐዘን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያሉ ተገቢ ያልሆኑ ስሜቶች እንደሚታዩባቸው ሊነግርህ ለሚችል አንድ ወዳጅህ ስሜትህን አወያየው። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል።—ምሳሌ 17:17
ሐዘን የደረሰበት ሰው ከፈጣሪያችን፣ ከይሖዋ አምላክ የተሻለ ወዳጅ ሊያገኝ አይችልም። “እሱ ስለ [አንተ] ያስባል”፤ በመሆኑም የልብህን አፍስሰህ በጸሎት ንገረው። (1 ጴጥሮስ 5:7) በተጨማሪም ወደ እሱ ለሚጸልዩ ሁሉ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን የሚያረጋጋላቸው “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አምላክ፣ በሚያበረታታው ቃሉ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንዲያጽናናህም ፍቀድለት። የሚያጽናኑ ጥቅሶችን በዝርዝር ጻፍ። (ሣጥኑን ተመልከት።) እንዲያውም አንዳንዶቹን በቃልህ መያዝ ትፈልግ ይሆናል። በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰልህ በተለይ ሌሊት ላይ ብቻህን ስትሆንና እንቅልፍ አልወስድ ሲልህ አበረታች ይሆንልሃል።—ኢሳይያስ 57:15
ጃክb የተባለ የ40 ዓመት ሰው የሚወዳት ባለቤቱን በቅርቡ በካንሰር አጥቷል። ጃክ አንዳንድ ጊዜ የከፋ የብቸኝነት ስሜት እንደሚያድርበት ገልጿል። ሆኖም መጸለዩ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ ስጸልይ ፈጽሞ የብቸኝነት ስሜት አይሰማኝም። አብዛኛውን ጊዜ ሌሊት ላይ እነቃለሁ፤ ከዚያ በኋላ እንቅልፍ አይወስደኝም። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ የሚያጽናኑ ጥቅሶችን ሳነብ፣ ባነበብኩት ላይ ሳሰላስል ብሎም የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ ስጸልይ ከፍተኛ የሆነ የመረጋጋትና የደህንነት ስሜት ይሰማኛል፤ እንዲህ ማድረጌ አእምሮዬንና ልቤን የሚያሳርፍልኝ ከመሆኑም ሌላ እንቅልፍ እንዲወስደኝ ይረዳኛል።”
ቨኒሳ የተባለች ወጣት እናቷን በበሽታ ምክንያት አጥታለች። እሷም ጸሎት ያለውን ኃይል በሕይወቷ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ጭንቅ ሲለኝ የአምላክን ስም ጠርቼ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ እጸልያለሁ። ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶ ሁልጊዜ የሚያስፈልገኝን ብርታት ይሰጠኛል።”
ለሐዘንተኞች ምክር የሚሰጡ አንዳንድ ባለሙያዎች ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ሌሎችን እንዲረዱ ወይም ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ነገር በማከናወን የተወሰነ ጊዜ እንዲያሳልፉ ይመክራሉ። እንዲህ ማድረግ ደስታ ሊያስገኝና ግለሰቡ ሐዘኑ እንዲቀለው ሊያደርግ ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ሐዘን የደረሰባቸው በርካታ ክርስቲያኖች ሌሎችን ለመርዳት አንዳንድ ነገሮችን ማከናወናቸው ከፍተኛ ማጽናኛ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
a መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሞት ምክንያት የሆኑ ሦስት ነገሮችን ይጠቅሳል።—መክብብ 9:11፤ ዮሐንስ 8:44፤ ሮም 5:12
b ስሙ ተቀይሯል።
-
-
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናትመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 3
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት
አንድ ሰው የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ የተነሳ አጠገብህ ሆኖ ሲያለቅስ ምን ማድረግ እንዳለብህ ግራ ገብቶህ ያውቃል? አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ወይም መናገር እንዳለብን ይጠፋናል፤ በመሆኑም ምንም ሳንናገር ወይም ሳናደርግ እንቀራለን። ያም ሆኖ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ።
ብዙውን ጊዜ በቦታው መገኘትህና የተሰማህን ሐዘን መግለጽህ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በብዙ ባሕሎች ሐዘንተኛውን ማቀፍ ወይም እጁን ጭብጥ ማድረግ አሳቢነት የሚገለጽበት ጥሩ መንገድ ነው። ሐዘንተኛው መናገር ከፈለገ አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳምጠው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሐዘን የደረሰበትን ቤተሰብ የሚጠቅሙ ነገሮችን አከናውን፤ ሐዘንተኛው ማድረግ ያልቻላቸውን ነገሮች ማከናወን ለምሳሌ ምግብ ማብሰል፣ ልጆቹን መንከባከብ ወይም አስፈላጊ ከሆነ ከቀብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስፈጸም ትችላለህ። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ማራኪ ከሆኑ ቃላት የበለጠ ኃይል አላቸው።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ መልካም ባሕርያቱን በማንሳት አሊያም ስላሳለፋችሁት አስደሳች ጊዜ በመጥቀስ ስለ ሟቹ መናገር ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ጭውውቶች ሐዘንተኛውን ፈገግ ሊያሰኙት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከስድስት ዓመት በፊት ባለቤቷን ኢያንን በሞት ያጣችው ፓም “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከዚህ በፊት ያልሰማኋቸውን ኢያን ያደረጋቸውን ጥሩ ነገሮች ይነግሩኛል፤ ይህን ስሰማ ልቤ በደስታ ይሞላል” ብላለች።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ሪፖርት እንዳደረጉት፣ ሐዘንተኞች የለቅሶው ሰሞን የብዙ ሰዎችን እርዳታ የሚያገኙ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወዳጆቻቸው በራሳቸው ሕይወት ሲጠመዱ ችላ ይባላሉ። በመሆኑም ሐዘኑ ካለፈ በኋላም ሐዘንተኛውን በየጊዜው ለመጠየቅ ጥረት አድርግ።a ሐዘን የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ለረጅም ጊዜ በሐዘን እንዳይዋጡ የሚያግዛቸውን እንዲህ ያለውን አሳቢነት ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።
በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኘውን ካኦሪ የተባለች ጃፓናዊት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ካኦሪ እናቷን በሞት ባጣች በዓመት ከሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ታላቅ እህቷ በመሞቷ ከፍተኛ ሐዘን ደርሶባት ነበር። የሚያስደስተው ከታማኝ ወዳጆቿ ቀጣይ የሆነ እርዳታ አግኝታለች። ካኦሪን በዕድሜ በጣም የምትበልጣት ሪትሱኮ የቅርብ ወዳጅ ሆነችላት። ካኦሪ እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር እንዲህ ማድረጓ ብዙም አላስደሰተኝም ነበር። ማንም ሰው የእናቴን ቦታ እንዲወስድ አልፈለግኩም፤ እንዲሁም እሷን ሊተካ የሚችል እንዳለ አልተሰማኝም። ያም ቢሆን ማማ ሪትሱኮ እኔን የያዘችበት መንገድ እንድቀርባት አደረገኝ። በየሳምንቱ አብረን እንሰብካለን፤ እንዲሁም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አብረን እንሄዳለን። ሻይ እንድንጠጣ ትጋብዘኛለች፣ ምግብ ታመጣልኛለች፤ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ደብዳቤ ጽፋና ካርድ አዘጋጅታ ትሰጠኛለች። ማማ ሪትሱኮ የነበራት አዎንታዊ አመለካከት በእኔ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።”
የካኦሪ እናት ከሞቱ 12 ዓመታት ያለፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እሷና ባለቤቷ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። ካኦሪ እንዲህ ብላለች፦ “ማማ ሪትሱኮ አሁንም ታስብልኛለች። ወደ ቤት ስመለስ ሁልጊዜ ሄጄ እጠይቃታለሁ፤ ጥሩ ጊዜም እናሳልፋለን።”
ፖሊ በቆጵሮስ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት፤ ሐዘን ከደረሰባት በኋላ ቀጣይ የሆነ ማበረታቻ በማግኘቷ ተጠቅማለች። የፖሊ ባለቤት የነበረው ሶዞስ ደግ፣ አፍቃሪና ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን እረኛ ነበር፤ ወላጆቻቸውንና የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ቤቱ ምግብ ጋብዞ አብሯቸው የመጫወት ልማድ ነበረው። (ያዕቆብ 1:27) በጣም የሚያሳዝነው ሶዞስ አንጎሉ ውስጥ በተፈጠረው ዕጢ የተነሳ በ53 ዓመቱ ሞተ። ፖሊ “በትዳር ዓለም ለ33 ዓመት አብሮኝ ያሳለፈውን ታማኝ ባለቤቴን አጣሁ” ብላለች።
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ሊጠቅም የሚችል ነገር አድርግ
ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ፖሊ፣ 15 ዓመት የሆነውን የመጨረሻ ልጇን ዳንኤልን ይዛ ወደ ካናዳ ሄደች። በዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ጀመሩ። ፖሊ እንዲህ ብላለች፦ “በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ስላሳለፍነው ሕይወትም ሆነ ስላጋጠመን ችግር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህ ግን እኛን ከመቅረብና ከማበረታታት ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በአሳቢነት ያነጋግሩንና ጠቃሚ እርዳታ ይሰጡን ነበር። ልጄ፣ አባቱ በጣም በሚያስፈልገው በዚያ ወቅት እንዲህ ያለ እርዳታ ማግኘቱ ትልቅ ነገር ነው! በጉባኤው ውስጥ አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ዳንኤልን በጣም ያቀርቡት ነበር። በተለይ አንደኛው ወንድም ከጉባኤው አባላት ጋር ሲዝናኑም ሆነ ኳስ ሲጫወቱ ዳንኤልን አስታውሶ ይጠራዋል።” በአሁኑ ጊዜ ፖሊና ልጇ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ።
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳትና ለማጽናናት የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የያዘው የሚያጓጓ ተስፋም ቢሆን አጽናኝ ነው።
a አንዳንዶች በዕለቱ ወይም በዚያ ሰሞን ሐዘንተኞቹን አስታውሰው ማጽናናት እንዲችሉ ግለሰቡ የሞተበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያቸው ላይ አስፍረዋል።
-
-
የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 3
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጌል የባለቤቷ የሮብ ሞት ካስከተለባት ሐዘን መጽናናት እንደማትችል ተሰምቷት እንደነበር ትዝ ይልህ ይሆናል። ያም ቢሆን አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ሮብን እንደምታገኘው ተስፋ ታደርጋለች። “በጣም የምወደው ጥቅስ ራእይ 21:3, 4 ነው” ትላለች። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ . . . ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
ጌል እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ተስፋ መድኃኒት ነው። የሚወዱትን ሰው በሞት ቢያጡም ግለሰቡ ከሞት የመነሳት ተስፋ እንዳለው የማያውቁ ሰዎች በጣም ያሳዝኑኛል።” ጌል የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና በፈቃደኝነት በማገልገል ይህን እምነቷን በሥራ ታሳያለች፤ ‘ሞት ስለማይኖርበት ጊዜ’ የሚገልጸውን አምላክ የሰጠውን ተስፋ ለሰዎች ትናገራለች።
ኢዮብ ዳግመኛ እንደሚኖር እርግጠኛ ነበር
‘ይህ የማይታመን ነገር ነው!’ ትል ይሆናል። ኢዮብ የተባለውን ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢዮብ በጠና ታሞ ነበር። (ኢዮብ 2:7) ሞትን ተመኝቶ የነበረ ቢሆንም እንኳ አምላክ ከሞት አስነስቶ በድጋሚ ምድር ላይ እንደሚያኖረው እምነት ነበረው። በእርግጠኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ምነው በመቃብር ውስጥ በሰወርከኝ! . . . አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:13, 15) ኢዮብ፣ አምላኩ እሱን ለማግኘት እንደሚናፍቅና ከሞት ሊያስነሳው እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር።
በቅርቡ ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ አምላክ፣ ኢዮብንና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎችን ከሞት ያስነሳል። (ሉቃስ 23:42, 43) መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ሰዎች “ከሞት እንደሚነሱ” ማረጋገጫ ይሰጣል። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ [ደግሞም] ይወጣሉ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ኢዮብ ይህ ተስፋ ሲፈጸም ይመለከታል። “ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑ” የመመለስ ተስፋ አለው፤ “በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው” ለዘላለም ይለመልማል። (ኢዮብ 33:24, 25) ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ የመኖርን ተስፋ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሁሉ እነዚህን በረከቶች ያገኛሉ።
የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ የተነሳ ስሜትህ ተጎድቶ ከሆነ እስካሁን የተመለከትናቸው ነጥቦች ሐዘንህን ሙሉ በሙሉ አያስወግዱልህ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰል ግን እውነተኛ ተስፋ እንዲሁም ጥንካሬ ማግኘት ትችላለህ።—1 ተሰሎንቄ 4:13
የደረሰብህን ሐዘን ለመቋቋም የሚረዳ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትፈልጋለህ? አሊያም ደግሞ “አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” እንደሚለው ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀህ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተግባራዊ የሚሆንና የሚያጽናና መልስ ለማግኘት jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንድትጎበኝ እናበረታታሃለን።
-