-
ጥቅስ ስታነብብ ተፈላጊውን ነጥብ ማጉላትበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 21
ጥቅስ ስታነብብ ተፈላጊውን ነጥብ ማጉላት
ከሰዎች ጋር ስትወያይም ይሁን ንግግር ስትሰጥ ስለ አምላክ ዓላማ የምትጠቅሰው ሐሳብ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብ የሚጠይቅ ሲሆን ጥቅሶቹ በሚገባ መነበብ ይኖርባቸዋል።
ተገቢውን ስሜት በሚያንጸባርቅ መንገድ ማንበብ። ጥቅሶችን የምታነብበት መንገድ ድርቅ ያለ መሆን የለበትም። ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት። መዝሙር 37:11ን በምታነብበት ጊዜ ድምፅህ በጥቅሱ ላይ የተገለጸውን የሰላም ተስፋ እንደምትናፍቅ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባል። ስቃይና ሞት እንደሚያከትም የሚናገረውን ራእይ 21:4ን ስታነብብ የሰው ልጅ ስለሚያገኘው ታላቅ እፎይታ ያለህ ጥልቅ አድናቆት በድምፅህ ቃና መንጸባረቅ ይኖርበታል። ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ከደረሰው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ እንድንወጣ ጥሪ የሚያቀርበው ራእይ 18:2, 4, 5 የመልእክቱን አጣዳፊነት በሚያሳይ መንገድ ሊነበብ ይገባል። ይህ ሲባል ግን በንባብህ የምታንጸባርቀው ስሜት ከውስጥህ የሚመነጭ እንጂ የተጋነነ መሆን የለበትም። የምታነብበትን ስሜት ለመመጠን የሚረዳህ ጥቅሱና የተጠቀሰበት ምክንያት ነው።
ትክክለኛዎቹን ቃላት ማጉላት:- በአንድ ጥቅስ ላይ የምትሰጠው ማብራሪያ በተወሰነው ክፍል ላይ ብቻ ያተኮረ ከሆነ በምታነብበት ጊዜ ያንን የጥቅሱን ክፍል ማጉላት ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል ‘አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለ መፈለግ’ እያብራራህ ከሆነ ማቴዎስ 6:33ን ስታነብብ “ጽድቁንም” ወይም “ይህም ሁሉ” የሚሉትን መግለጫዎች ማጉላት አይኖርብህም።
በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ንግግር ስታቀርብ ማቴዎስ 28:19ን ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል። ታዲያ ማጉላት የሚኖርብህ የትኞቹን ቃላት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉ ማበረታታት ከፈለግህ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ማጉላት ይኖርብሃል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመንገር ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን በተመለከተ ስትናገር ወይም አንዳንድ አስፋፊዎች እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ ሄደው እንዲያገለግሉ ስታበረታታ “አሕዛብን ሁሉ” የሚለውን የጥቅሱን ክፍል ማጉላት ትችላለህ።
ብዙውን ጊዜ ጥቅስ የሚጠቀሰው ለአንድ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ወይም አንድን ሐሳብ ለመደገፍ ነው። በጥቅሱ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ሐሳብ ካጎላህ አድማጮች ጥቅሱ ከጉዳዩ ጋር ያለውን ዝምድና ማስተዋል ሊቸገሩ ይችላሉ። ነጥቡ ለአንተ ግልጽ ሆኖልሃል ማለት ለእነርሱም ግልጽ ይሆንላቸዋል ማለት አይደለም።
ለምሳሌ ያህል የያዝኸው መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 83:18 ላይ መለኮታዊውን ስም የሚጠቀም ከሆነ “ልዑል” የሚለውን ቃል ብቻ ብታጎላ የምታነጋግረው ሰው አምላክ የግል መጠሪያ አለው የሚለውን ለአንተ ግልጽ የሆነ እውነት ሳያስተውል ሊቀር ይችላል። ጠበቅ አድርገህ መግለጽ ያለብህ “ይሖዋ” የሚለውን ስም ነው። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ለማስረዳት በማሰብ ይህንኑ ጥቅስ ስታነብብ ማጉላት ያለብህ “ልዑል” የሚለውን ቃል ነው። በተመሳሳይም እምነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት ለማስረዳት አስበህ ያዕቆብ 2:24ን ስታነብብ “በሥራ” የሚለውን ቃል ትተህ “እንዲጸድቅ” የሚለውን ቃል ብታጎላ አንዳንድ አድማጮችህ የተፈለገውን ነጥብ ላይረዱት ይችላሉ።
ሮሜ 15:7-13ም ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ይህ ጥቅስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከአሕዛብ ወገን የሆኑና በትውልድ አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖችን ላቀፈ አንድ ጉባኤ በጻፈው መልእክት ውስጥ የሚገኝ ነው። ጳውሎስ የክርስቶስ አገልግሎት የተገረዙ አይሁዳውያንን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ የመጡትን ጭምር የሚጠቅም እንደሆነ እያብራራ ነው። ይህም ‘አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ’ ምክንያት እንደሚሆን ጠቅሷል። ጳውሎስ አሕዛብ ያገኙትን ይህንን አጋጣሚ የሚያረጋግጡ አራት ጥቅሶች ተጠቅሟል። እያብራራ ያለውን ሐሳብ ለማጉላት ከፈለግህ እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ልታነባቸው ይገባል? ለማጉላት በፈለግኸው ቃል ላይ ምልክት የምታደርግ ከሆነ ከቁጥር 8 እና 9 “አሕዛብ፣” ከቁጥር 11 “እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ” እና “ሕዝቦቹም ሁሉ” እንዲሁም ከቁጥር 12 “አሕዛብ” የሚሉትን ቃላት ትመርጥ ይሆናል። እነዚህን ቃላት እያጎላህ ሮሜ 15:7-13ን ለማንበብ ሞክር። እንዲህ ካደረግህ ጳውሎስ እያብራራው ያለው ነጥብ ይበልጥ ግልጽና ለመረዳትም ቀላል ይሆናል።
ለማጉላት የሚረዱ ዘዴዎች። ለየት ብለው እንዲታዩ የምትፈልጋቸውን መልእክት አዘል ቃላት በተለያየ መንገድ ማጉላት ትችል ይሆናል። ይሁንና የምትጠቀምበት ዘዴ ከጥቅሱ ይዘትና ከንግግሩ ነጥቦች ጋር የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ቀጥሎ ለማጉላት የሚረዱ አንዳንድ ዘዴዎችን እንመለከታለን።
ድምፅን መለዋወጥ። ይህም መልእክት አዘል የሆኑት ቃላት ከቀረው ዓረፍተ ነገር ለየት ብለው እንዲታዩ የሚያደርግን ማንኛውንም የድምፅ ለውጥ ያመለክታል። በአንዳንድ ቋንቋዎች የድምፅን መጠን በመጨመር ወይም በመቀነስ ማጉላት ይቻል ይሆናል። በሌሎች ቋንቋዎች ግን እንዲህ ማድረግ ጭራሽ ትርጉሙን ሊቀይረው ይችላል። ቁልፍ የሆነው ቃል ላይ ስትደርስ ዝግ ካልክ ለዚያ ቃል ትኩረት እንዲሰጠው ታደርጋለህ። ቋንቋህ ድምፅን በመለዋወጥ ቃላትን ማጉላት የማይፈቅድ ከሆነ ይህንን ለማድረግ በቋንቋው የተለመደውን ማንኛውንም ዘዴ መጠቀም ያስፈልግ ይሆናል።
ቆም ማለት። ልታጎላው ከፈለግኸው የጥቅሱ ክፍል በፊት ወይም በኋላ ወይም በሁለቱም ቦታ ቆም ማለት ይቻላል። ዋናው ነጥብ ላይ ስትደርስ ቆም ማለት አድማጮች ቀጥሎ የሚነበበውን በጉጉት እንዲጠባበቁ የሚያደርግ ሲሆን ከተነበበ በኋላ ቆም ማለት ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ እንዲያስቡበት ያደርጋል። ሆኖም አሁንም አሁንም ቆም የምትል ከሆነ ጎላ ብሎ የሚታይ ነጥብ አይኖርም።
መደጋገም። ወደኋላ መለስ ብለህ ቃሉን ወይም ሐረጉን ደግመህ በማንበብ አንድን ነጥብ ማጉላት ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ የተሻለ የሚሆነው ጥቅሱን አንብበህ ከጨረስህ በኋላ ማጉላት የምትፈልገውን ሐሳብ መድገሙ ነው።
አካላዊ መግለጫ። ፊታችን ላይ የሚነበበውን ስሜት ጨምሮ ማንኛውም አካላዊ መግለጫ ቃሉን ይበልጥ ያጠናክረዋል።
የድምፅ ቃና። በአንዳንድ ቋንቋዎች ቃላቱ የሚነበቡበት ቃና ትርጉማቸውን ሊለውጥ እንዲሁም ለየት ብለው እንዲታዩ ሊያደርግ ይችላል። በዚህም ረገድ በተለይ ደግሞ አነጋገሩ የምጸት በሚሆንበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
ጥቅሱን ሌሎች በሚያነቡበት ጊዜ። የምታነጋግረው ሰው ጥቅሱን ሲያነብብ የማይፈለገውን ቃል ሊያጎላ ወይም ደግሞ ምንም ቃል ሳያጎላ ሊቀር ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? ብዙውን ጊዜ የጥቅሱን መልእክት ማብራራቱ የተሻለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ያንን ሐሳብ የሚያስተላልፉት የጥቅሱ ቃላት ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ ትችል ይሆናል።
-
-
ጥቅሶችን ከነጥቡ ጋር ማገናዘብበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 22
ጥቅሶችን ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ
በምታስተምርበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ ማንበብህ ብቻ በቂ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት አጋሩ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- ‘የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።’—2 ጢሞ. 2:15
ለጥቅሶች የምንሰጠው ማብራሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መሆን አለበት ማለት ነው። ከጥቅሱ ውስጥ እኛ ደስ ያለንን ሐሳብ መርጠን በመሰለን መንገድ ከማብራራት ይልቅ በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ማጤን ይጠይቅብናል። ይሖዋ ከእርሱ አፍ የሰሙትን እንደሚናገሩ አስመስለው “ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ” የሚናገሩትን ነቢያት በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አስጠንቅቋቸዋል። (ኤር. 23:16) ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል በሰብዓዊ ፍልስፍናዎች እንዳይበርዙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል:- “የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኰል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም።” በዘመኑ የነበሩ አጭበርባሪ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች ወይን ጠጁ እንዲበዛላቸውና ብዙ ትርፍ እንዲያገኙ ሲሉ ይበርዙት ነበር። እኛ ግን የአምላክን ቃል በሰብዓዊ ፍልስፍና አንበርዝም። ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን” ብሏል።—2 ቆሮ. 2:17፤ 4:2
ለአንድ መሠረታዊ ሥርዓት እንደ ማስረጃ አድርገህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትጠቅስ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ለተለያዩ ሁኔታዎች መመሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ይሁን እንጂ ጥቅሱን አላግባብ በመጠቀም አንተ የምትፈልገውን ሐሳብ የሚደግፍ አስመስለህ በተሳሳተ መንገድ እንዳታቀርብ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። (መዝ. 91:11, 12፤ ማቴ. 4:5, 6) ጥቅሱን የተጠቀምህበት መንገድ ከይሖዋ ዓላማና ከጠቅላላው የአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል።
በተጨማሪም ‘የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀም’ የጥቅሱን መንፈስ መረዳት ይጠይቃል። ሌሎችን በቃላት ለመደብደብ የሚያገለግል “በትር” አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ይቃወሙ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ላሉት አምላክ ለሚፈልጋቸው ዋነኛ ባሕርያት ግዴለሽ የነበሩ ቢሆንም ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ይናገሩ ነበር። (ማቴ. 22:23, 24፤ 23:23, 24) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ሲያስተምር የአባቱን ባሕርያት አንጸባርቋል። ለእውነት ካሳየው ቅንዓት በተጨማሪ ለሚያስተምራቸውም ሰዎች ልባዊ ፍቅር ነበረው። እኛም የእርሱን ምሳሌ ለመኮረጅ መጣር ይኖርብናል።—ማቴ. 11:28
ጥቅሱን ከነጥቡ ጋር በትክክል ማገናዘባችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባችን በዚህ ረገድ ትልቅ ጥቅም አለው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለእምነት ቤተሰቦች መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በሚጠቀምበት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ያደረገልንን ዝግጅት ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። (ማቴ. 24:45) ታማኝና ልባም ባሪያ ከሚሰጠው ትምህርት ለመጠቀም የግል ጥናት ማድረግ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትና መሳተፍ ያስፈልገናል።
ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነና በሚገባ ከተጠቀምህበት በአገልግሎት ላይ ብዙ ጊዜ የምንጠቅሳቸውን በመቶ የሚቆጠሩ ጥቅሶች እንዴት ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ እንደምትችል ለማወቅ ይረዳሃል። ልትጠቀምበት ያሰብኸውን ጥቅስ በደንብ የማታውቀው ከሆነ ምርምር ማድረግህ ትሑት መሆንህን ያሳያል። እንዲህ ካደረግህ የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም ትችላለህ።—ምሳሌ 11:2
ጥቅሱ ከነጥቡ ጋር ያለውን ዝምድና ግልጽ ማድረግ። በምታስተምርበት ጊዜ አድማጮችህ እያብራራህ ባለኸው ነጥብና በጠቀስኸው ጥቅስ መካከል ያለው ዝምድና ግልጽ ሆኖ እንዲታያቸው ልታደርግ ይገባል። ጥቅሱን ከማንበብህ በፊት አንድ ጥያቄ አንስተህ ከነበረ የምትጠቅሰው ጥቅስ ላነሳኸው ጥያቄ መልስ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ አድማጮችህ በግልጽ መረዳት መቻል አለባቸው። ጥቅሱን የጠቀስኸው አንድ ሐሳብ ለመደገፍ ብለህ ከሆነ ደግሞ ጥቅሱ ለነጥቡ እንዴት ማስረጃ እንደሚሆን ለተማሪው ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል።
ብዙውን ጊዜ ጥቅሱን ማንበባችን ብቻውን በቂ አይሆንም። ምናልባትም ስናነብ ተፈላጊውን ነጥብ አጉልተን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛው ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ብዙም ትውውቅ እንደሌለውና ጥቅሱን አንዴ ስላነበብክለት ብቻ ነጥቡን ይረዳዋል ማለት እንደማይቻል አትዘንጋ። እየተወያያችሁበት ካለው ሐሳብ ጋር በቀጥታ የሚያያዘውን ነጥብ እንዲያስተውለው አድርግ።
ይህም ብዙውን ጊዜ እየተወያያችሁበት ካለው ነጥብ ጋር በቀጥታ የሚዛመዱትን ቁልፍ ቃላት መለየት ይጠይቅብሃል። ቀላሉ ዘዴ መልእክት አዘል የሆኑትን እነዚህን ቃላት መድገም ነው። ከአንድ ሰው ጋር እየተወያየህ ከሆነ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለመለየት የሚረዳ ጥያቄ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል። ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ደግሞ አንዳንድ ተናጋሪዎች እንደሚያደርጉት ቁልፍ የሆኑት ቃላት ለየት ብለው እንዲታዩ ለማድረግ ስትል ሌላ ተመሳሳይ ቃል ትጠቀም ወይም ሐሳቡን ደግመህ ትጠቅስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህንን ለማድረግ ከመረጥህ አድማጮች በምትወያዩበት ነጥብና በጥቅሱ አቀማመጥ መካከል ያለው ዝምድና እንዳይድበሰበስባቸው መጠንቀቅ ይኖርብሃል።
ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለይተህ ካወጣህ መሠረት ጥለሃል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣዩ እርምጃ ማለፍ ትችላለህ። ጥቅሱን ያስተዋወቅህበት መንገድ የጠቀስህበትን ዓላማ የሚጠቁም ነውን? ከሆነ አድማጮችህ ከጥቅሱ በሚጠብቁት ሐሳብና ጎላ አድርገህ በገለጽኻቸው ቃላት መካከል ያለውን ዝምድና እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብሃል። ጥቅሱን ለማስተዋወቅ የተጠቀምህበት ዘዴ የምታነብበትን ምክንያት በግልጽ የሚጠቁም ባይሆንም እንኳ ሌላ ልታደርገው የሚገባ ነገር አለ።
ፈሪሳውያን ከባድ ነው ብለው ያሰቡትን አንድ ጥያቄ ይዘው ወደ ኢየሱስ በመምጣት “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ መልስ የሰጠው ዘፍጥረት 2:24ን መሠረት በማድረግ ነበር። በጥቅሱ የተወሰነ ነጥብ ላይ ብቻ እንዳተኮረና ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ግልጽ እንዳደረገላቸው ልብ በል። ኢየሱስ ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እንደሆኑ ከተናገረ በኋላ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ደምድሟል።—ማቴ. 19:3-6
አንድ ጥቅስ የተጠቀሰበትን ዓላማ ግልጽ ለማድረግ ምን ያህል ማብራሪያ መስጠት ይኖርብሃል? ይህን የሚወስነው አድማጮችህ እነማን ናቸው? ደግሞስ ውይይት እየተደረገበት ያለው ነጥብ ምን ያህል ክብደት የሚሰጠው ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። ግብህ ቀላልና ቀጥተኛ ማብራሪያ መስጠት ሊሆን ይገባል።
ጥቅሶችን ተጠቅሞ ማስረዳት። ሥራ 17:2, 3 ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስላከናወነው አገልግሎት ሲገልጽ ‘ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳቸው’ እንደነበር ይናገራል። እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ይህን ችሎታ ለማዳበር ሊጥር ይገባል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ከገለጸና እነዚህ ነገሮች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በትንቢት እንደተነገሩ ካስረዳ በኋላ “እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” በማለት ሐሳቡን ደምድሟል።
ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ጠቅሷል። የሚፈልገውን ነጥብ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ወይም ለማብራራት አንድ ቃል ወይም አጭር ሐረግ በመምረጥ ትርጉሙን ያስረዳ ነበር። (ዕብ. 12:26, 27) ጳውሎስ ዕብራውያን ምዕራፍ 3 ላይ መዝሙር 95:7-11ን ጠቅሶ ጽፏል። ከጥቅሱ ሦስት ነጥቦችን ነጥሎ በማውጣት ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደሰጠ ልብ በል:- (1) ስለ ልብ የተጠቀሰውን ሐሳብ (ዕብ. 3:8-12)፣ (2) “ዛሬ” የሚለውን ቃል (ዕብ. 3:7, 13-15፤ 4:6-11) እንዲሁም (3) “ወደ እረፍቴ አይገቡም” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ትርጉም (ዕብ. 3:11, 18, 19፤ 4:1-11) አብራርቷል። የምትጠቅሰውን እያንዳንዱን ጥቅስ ከነጥቡ ጋር ስታዛምድ ይህንን የጳውሎስን ምሳሌ ለመኮረጅ ሞክር።
በሉቃስ 10:25-37 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ታሪክ ኢየሱስ ጥቅሶችን በመጠቀም እንዴት ጥሩ አድርጎ እንዳስረዳ ለማስተዋል ሞክር። ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም በመጀመሪያ ሰውዬው ራሱ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንዲገልጽ በመጋበዝ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት። ቀጥሎም የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን መፈጸም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። ከዚያ በኋላ ግን ኢየሱስ ሰውዬው ዋናውን ቁም ነገር እንዳልተገነዘበ ሲያስተውል ከጥቅሱ መካከል “ባልንጀራ” የሚለውን ቃል በመውሰድ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠው። እንዲሁ የቃሉን ፍቺ ከመንገር ይልቅ ሰውዬው ራሱ ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ እንዲደርስ የሚረዳ ምሳሌ ተጠቅሟል።
ኢየሱስ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ዝምድና ያላቸውን ጥቅሶች ብቻ ይጠቀም እንዳልነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ጥቅሶቹን በማስተዋል ከተነሳው ጥያቄ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ያብራራ ነበር።
ሰዱቃውያን የትንሣኤን ተስፋ ውድቅ ለማድረግ በማሰብ ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ኢየሱስ በዘጸአት 3:6 ላይ በሚገኝ አንድ ነጥብ ላይ ብቻ በማተኮር መልስ ሰጥቷል። ይሁንና ጥቅሱን ጠቅሶ ብቻ ዝም አላለም። ከጥቅሱ በመነሳት ትንሣኤ የአምላክ ዓላማ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል።—ማር. 12:24-27
ጥቅሶችን ተጠቅመህ በትክክልና በጥሩ ሁኔታ የማስረዳት ችሎታ ማዳበርህ የተዋጣልህ አስተማሪ እንድትሆን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
-
-
የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግበቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
-
-
ጥናት 23
የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግ
ከአንድ ግለሰብ ጋር ስትወያይም ይሁን ንግግር ስትሰጥ አንተ በትምህርቱ ስለተማረክህ ብቻ አድማጮችም ተመሳሳይ ስሜት ያድርባቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። የያዝከው መልእክት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ጥቅሙን ለአድማጮችህ ግልጽ ካላደረግህላቸው ብዙም ሳይቆይ አእምሮአቸው መባዘን ሊጀምር ይችላል።
ይህ አባባል በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ላሉ አድማጮችም ይሠራል። አዲስ ምሳሌ ስትጠቀም ወይም ከዚያ ቀደም ያልሰሙትን ተሞክሮ ስትናገር በጉጉት ያዳምጡህ ይሆናል። ስለሚያውቋቸው ነገሮች መናገር ስትጀምር ግን በተለይ ከምሳሌዎቹና ከተሞክሮዎቹ ጋር እያዛመድህ ካልሄድክ ሐሳባቸው እንደገና ሊባዝን ይችላል። እየተናገርህ ያለኸው ነገር እነርሱን የሚጠቅማቸው ለምንና እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ መርዳት ይኖርብሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ በጥበብ እንድናስብ ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:21) ሕዝቡን ‘ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ’ ይሖዋ መጥምቁ ዮሐንስን ተጠቅሞበታል። (ሉቃስ 1:17) ይህ ለይሖዋ ከሚኖረን ጤናማ ፍርሃት የሚመነጭ ጥበብ ነው። (መዝ. 111:10) የዚህን ጥበብ አስፈላጊነት የሚገነዘቡ ሰዎች ዛሬ ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ ለመምራት ከመቻላቸውም በላይ መጪውን እውነተኛ ሕይወት ማለትም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችላሉ።—1 ጢሞ. 4:8፤ 6:19
አድማጮችን በሚጠቅም መንገድ ማቅረብ። የምታቀርበው ንግግር አድማጮችን የሚጠቅም እንዲሆን ስለ ትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ስለ አድማጮችህም ጭምር ማሰብ ይኖርብሃል። ይህ ሲባል እንዲሁ በደፈናው ሳይሆን በተናጠል ስለ አድማጮችህ ማሰብ ማለት ነው። በአድማጮችህ መካከል የተለያዩ ግለሰቦችና ቤተሰቦች አሉ። ትናንሽ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አንዳንድ አረጋውያንም ይኖሩ ይሆናል። እንግዶች ሌላው ቀርቶ አንተ ከመወለድህ በፊት ይሖዋን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶች በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሌሎቹ ደግሞ ገና አሁንም ከአንዳንድ የዓለም አስተሳሰቦችና ልማዶች ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የማቀርበው ትምህርት በአድማጮቼ መካከል ያሉትን ሰዎች የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? ነጥቡን እንዲያስተውሉት ልረዳቸው የምችለው እንዴት ነው?’ ዋና ትኩረትህን ከላይ ከተዘረዘሩት አድማጮችህ መካከል በአንዱ ወይም በሁለቱ ላይ ማድረግ ትፈልግ ይሆናል። ይሁንና ሌሎችን ጭራሽ መርሳት አለብህ ማለት አይደለም።
የምታቀርበው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርት የሚያብራራ ቢሆንስ? ትምህርቱን አድማጮችህ የሚያምኑበት ከሆነ ለእነርሱ የሚጠቅም አድርገህ ልታቀርበው የምትችለው እንዴት ነው? በጉዳዩ ላይ ያላቸውን እምነት ይበልጥ የሚያጠናክር አድርገህ ለማቅረብ ሞክር። እንዴት? ድጋፍ የሚሆኑትን ጥቅሶች በጥልቀት በማብራራት ነው። በተጨማሪም ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር ልትረዳቸው ትችላለህ። ትምህርቱ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና ከይሖዋ ባሕርያት ጋር የሚጣጣመው እንዴት እንደሆነ በማብራራት ይህን ማድረግ ትችል ይሆናል። ይህን ትምህርት በማወቃቸው የተጠቀሙ እና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸውን አመለካከት ማስተካከል የቻሉ ሰዎችን እንደ ምሳሌ አድርገህ ጥቀስ።
ትምህርቱ ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ የምትገልጸው የግድ በንግግርህ መደምደሚያ ላይ በምትሰጠው አጭር ማጠቃለያ መሆን የለበትም። ከንግግሩ መጀመሪያ አንስቶ እያንዳንዱ አድማጭ “ይህ ትምህርት ለእኔ ነው” በሚል ስሜት ሊከታተልህ ይገባል። ከዚህ በኋላ የንግግርህን እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ስታብራራም ሆነ መደምደሚያህ ላይ ትምህርቱ ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ ከመግለጽ ወደኋላ አትበል።
አድማጮች ትምህርቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የምታስረዳበት መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። ይህ ምን ማለት ነው? ፍቅር ልታሳያቸውና ራስህን በእነርሱ ቦታ ልታስቀምጥ ይገባል ማለት ነው። (1 ጴጥ. 3:8፤ 1 ዮሐ. 4:8) ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስለነበረው ከባድ ችግር በጻፈበት ጊዜ እንኳ በዚያ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉትን መንፈሳዊ እድገት በተመለከተ በጎ ጎናቸውን ሳይጠቅስ አላለፈም። የጻፈላቸውንም ምክር እንደሚሠሩበት ያለውን ትምክህት ገልጿል። (1 ተሰ. 4:1-12) ይህ ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው!
የንግግርህ ዓላማ አድማጮች ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ እንዲሳተፉ ማበረታታት ነው? ለዚህ መብት አድናቆት እንዲያድርባቸውና በቅንዓት እንዲነሳሱ አድርግ። ይሁንና እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያደርገው ተሳትፎ መጠን እንደሚለያይና መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ጉዳይ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ መዘንጋት አይኖርብህም። (ማቴ. 13:23) ወንድሞችህ የጥፋተኛነት ስሜት እንዲያድርባቸው አታድርግ። ዕብራውያን 10:24 ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ’ ይመክረናል። ለፍቅር ካነሳሳናቸው ከልብ ተገፋፍተው ይሠራሉ። ሌሎችን በግፊት ለሥራ ለማነሳሳት ከመሞከር ይልቅ ይሖዋ ‘በእምነት የመታዘዝን’ መንፈስ በውስጣቸው እንድንኮተኩት እንደሚፈልግ መገንዘብ ይኖርብሃል። (ሮሜ 16:26) የራሳችንንም ሆነ የወንድሞቻችንን እምነት ለማጠንከር ስንጥር ይህንን መዘንጋት አይኖርብንም።
የትምህርቱን ጠቀሜታ እንዲያስተውሉ መርዳት። በምትመሰክርበት ጊዜ ምሥራቹ ለእነርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ጎላ አድርገህ ልትገልጽ ይገባል። ይህ ደግሞ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉት ሰዎች የሚያሳስባቸው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ይጠይቅብሃል። ይህንን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ዜናዎችን አዳምጥ። በጋዜጦች ላይ ትኩረት የተሰጣቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ተመልከት። እንዲሁም ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል መስጠትና ማዳመጥ ያስፈልግሃል። ሥራ ማጣት፣ የኪራይ ዋጋ መናር፣ ሕመም፣ የቤተሰብን አባል በሞት ማጣት፣ የወንጀል ፍርሃት፣ ባለ ሥልጣናት የሚፈጽሙት ግፍ፣ የትዳር መፍረስ፣ ልጆችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግና እነዚህን የመሳሰሉ ከባድ ችግሮች እንደሚያስጨንቋቸው ትገነዘብ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳቸው ይችላል? ሊረዳቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ከአንድ ሰው ጋር ለመወያየት ስታስብ ልትነግረው የምትፈልገው ነገር እንደሚኖር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሰውዬውን ይበልጥ የሚያሳስበው ሌላ ጉዳይ እንዳለ ካስተዋልህ በተቻለ መጠን በዚህ ጉዳይ ላይ ለማወያየት ሞክር። ወይም በሌላ ጊዜ ጠቃሚ ሐሳቦችን ልታካፍለው እንደምትችል ንገረው። ይህን ስንል ‘በማይመለከተን ጉዳይ ውስጥ እንገባለን’ ማለት ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር ከማካፈል ወደኋላ አንልም። (2 ተሰ. 3:11) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከእነርሱ ሕይወት ጋር የተያያዘ ምክር እንደሚሰጥ ሲያስተውሉ በጣም እንደሚነኩ የታወቀ ነው።
መልእክታችን እነርሱን በግል የሚጠቅማቸው እንዴት እንደሆነ ካልታያቸው ቶሎ ብለው ውይይቱን ሊያቋርጡ ይችላሉ። ቢያዳምጡን እንኳን ርዕሰ ጉዳዩ ለእነርሱ ያለውን ጥቅም ግልጽ ሳናደርግላቸው ከቀረን የምንነግራቸው ነገር ብዙም ልባቸውን ላይነካው ይችላል። በተቃራኒው ግን መልእክቱ ለእነርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ግልጽ ካደረግንላቸው ውይይታችን በሕይወታቸው ውስጥ ወሳኝ ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ሁልጊዜ ትምህርቱ ያለውን ጥቅም ለማጉላት መጣር ይኖርብሃል። (ምሳሌ 4:7) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም በይሖዋ መንገድ መመላለስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል የሚረዷቸውን ምሳሌዎች ልብ እንዲሉ እርዳቸው። በይሖዋ መንገድ መመላለስ የሚያስገኝላቸውን ጥቅም ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። (ኢሳ. 48:17, 18) ይህም ተማሪዎቹ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። ለይሖዋ ፍቅር እንዲኮተኩቱና እርሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉት ከልባቸው ተነሳስተው እንዲሆን አድርግ።
-