የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መኖር ምን ዋጋ አለው?
    ንቁ!—2014 | ሚያዝያ
    • ተስፋ የቆረጠ አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት ሲያስብ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

      መኖር ምን ዋጋ አለው?

      ከዳያናa ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ቢኖርህ ብልህ፣ ተግባቢና ተጫዋች ወጣት እንደሆነች ማሰብህ አይቀርም። ከውጭ ስትታይ ደስተኛ ብትመስልም በውስጧ ያለው የዋጋ ቢስነት ስሜት ግን ለቀናት፣ ለሳምንታት አንዳንድ ጊዜም ለወራት ያሠቃያታል። “ስለ መሞት ያላሰብኩበት አንድም ቀን የለም። እኔ ብሞት ዓለማችን እፎይ እንደምትል ይሰማኛል” ብላለች።

      “አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንድ ሰው ራሱን ሲያጠፋ በዚያው ቅጽበት 200 ሰዎች ራስን የማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ፤ አራት መቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ራስን ስለ ማጥፋት ያስባሉ።”—ዘ ጋዜት፣ ሞንትሪያል፣ ካናዳ

      ዳያና ፈጽሞ ራሷን እንደማታጠፋ ተናግራለች። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ፣ መኖሯ ምንም ጥቅም እንደሌለው ይሰማታል። “በጣም የምመኘው ነገር ቢኖር በአደጋ መሞት ነው። ሞትን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወዳጅ አድርጌ ማየት ጀምሬያለሁ” ብላለች።

      ብዙ ሰዎች እንደ ዳያና የሚሰማቸው ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ራሳቸውን ለማጥፋት አስበው አሊያም ሞክረው ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ራሳቸውን ለማጥፋት ከሚሞክሩ ሰዎች አብዛኞቹ ይህን እርምጃ የሚወስዱት ሕይወታቸውን የማጥፋት ፍላጎት ኖሯቸው ሳይሆን የሚደርስባቸውን መከራ ማጥፋት ስለሚፈልጉ ነው። በአጭሩ እነዚህ ሰዎች ለመሞት ምክንያት እንዳላቸው ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም የሚያስፈልጋቸው በሕይወት ለመቀጠል የሚያበቃ ምክንያት ነው።

      ታዲያ መኖር ምን ዋጋ አለው? ዋጋ እንዳለው የሚያሳዩ ሦስት ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።

      የተሳሳተ አመለካከት፦ ራስን ስለ ማጥፋት ማውራት ሌላው ቀርቶ ቃሉን ማንሳት እንኳ ሰዎች ድርጊቱን እንዲሞክሩት ይገፋፋል።

      እውነታው፦ ስለ ጉዳዩ በግልጽ መነጋገር ራሱን የማጥፋት ሐሳብ የነበረው ሰው ሌሎች አማራጮችን እንዲሞክር ይረዳዋል።

      a ስሟ ተቀይሯል።

  • 1 ሁኔታዎች ይለወጣሉ
    ንቁ!—2014 | ሚያዝያ
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?

      1 ሁኔታዎች ይለወጣሉ

      “በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8

      ራስን ማጥፋት “ጊዜያዊ ለሆነ ችግር ዘላቂ የሆነ መፍትሔ መስጠት” እንደሆነ ተደርጎ ይገለጻል። ለማመን ቢከብድህም እንኳ ማንኛውም ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ሌላው ቀርቶ ከአንተ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ የሚሰማህም ጭምር ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ባልጠበቅከው መንገድ ሊስተካከል ይችላል።—“ሁኔታቸው ተለውጧል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      ይህ ባይሆን እንኳ ስለ ነገ ሳትጨነቅ ዛሬ በሚያጋጥሙህ ችግሮች ላይ ብቻ በማተኮር መፍትሔ መፈለግህ የተሻለ ነው። ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ብሏል።—ማቴዎስ 6:34

      ይሁንና ሁኔታህ ሊለወጥ የማይችል ቢሆንስ? ለምሳሌ ሥር የሰደደ ሕመም ይኖርብህ ይሆናል። አሊያም ያስጨነቀህ ነገር የትዳር መፍረስ ወይም የቤተሰብህን አባል በሞት እንደማጣት ያለ ልትቀይረው የማትችል ነገር ቢሆንስ?

      በዚህ ጊዜም ቢሆን ልትለውጠው የምትችለው ነገር ይኖራል፤ ስለ ሁኔታው ያለህን አመለካከት መለወጥ ትችላለህ። ልትለውጠው የማትችለውን ነገር ተቀብለህ ለመኖር ስትጥር ነገሮችን ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ማየት ትጀምራለህ። (ምሳሌ 15:15) በተጨማሪም ሞትን እንደ መፍትሔ ከመቁጠር ይልቅ ሁኔታውን ለመቋቋም የምትችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ትጀምራለህ። ውጤቱ? ልትቆጣጠረው የማትችለው እንደሆነ ይሰማህ የነበረውን ሁኔታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን መቆጣጠር ትጀምራለህ።—ኢዮብ 2:10

      ይህን አስታውስ፦ አንድን ተራራ በአንድ እርምጃ ለመውጣት መሞከር የማይመስል ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ እየተራመድክ አስቸጋሪውን ጉዞ መወጣት ትችላለህ። አብዛኞቹ የሚያጋጥሙህ ችግሮች ምንም ያህል እንደ ተራራ ገዝፈው ቢታዩህ በተመሳሳይ መንገድ ልትወጣቸው ትችላለህ።

      ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሁኔታውን በተመለከተ ከአንድ ሰው ምናልባትም ከጓደኛህ ወይም ከቤተሰብህ አባል ጋር ተነጋገር። ይህ ሰው ያለህበትን ሁኔታ ይበልጥ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንድታይ ሊረዳህ ይችል ይሆናል።—ምሳሌ 11:14

      ሁኔታቸው ተለውጧል

      መኖር እስኪያስጠላቸው ድረስ በሕይወታቸው የተመረሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አራት ታማኝ ሰዎችን እንመልከት።

      • ርብቃ፦ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ።”—ዘፍጥረት 27:46

      • ሙሴ፦ “አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”—ዘኍልቍ 11:15

      • ኤልያስ፦ “በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት።”—1 ነገሥት 19:4

      • ኢዮብ፦ “ምነው ገና ስወለድ በጠፋሁ!”—ኢዮብ 3:11

      የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስታነብ የነበሩበት ሁኔታ ባልጠበቁት መንገድ እንደተለወጠ ማየት ትችላለህ። የአንተም ሁኔታ ሊለወጥ ይችላል። (መክብብ 11:6) በመሆኑም ተስፋ አትቁረጥ!

  • 2 እርዳታ ማግኘት ይቻላል
    ንቁ!—2014 | ሚያዝያ
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?

      2 እርዳታ ማግኘት ይቻላል

      “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም [አምላክ] ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

      ያለህበትን ሁኔታ ለማሻሻል ምንም ማድረግ እንደማትችል ሲሰማህ ሞትን ልትመርጥ ትችላለህ። ይሁን እንጂ እርዳታ ልታገኝ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

      ጸሎት፦ ጸሎት አእምሮን ለማረጋጋት የሚረዳ ነገር እንደሆነ ብቻ አድርገህ ማሰብ የለብህም፤ ወይም አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ብቻ የምታደርገው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለ አንተ ከሚያስበው ከይሖዋ አምላክ ጋር የምትነጋገርበት መንገድ ነው። ይሖዋ የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ እንድትነግረው ይፈልጋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” ይላል።—መዝሙር 55:22

      ለምን ዛሬውኑ አምላክን በጸሎት አታነጋግረውም? ይሖዋ በተባለው ስሙ ተጠቅመህ የልብህን ንገረው። (መዝሙር 62:8) ይሖዋ፣ እሱን የቅርብ ወዳጅ እንድታደርገው ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 55:6፤ ያዕቆብ 2:23) ጸሎት በማንኛውም ጊዜና በማንኛውም ቦታ ከአምላክ ጋር ልትነጋገር የምትችልበት መንገድ ነው።

      “ራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች መካከል በጣም ብዙዎቹ ማለትም 90 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የአእምሮ ችግር” እንደነበራቸው ጥናቶች በተደጋጋሚ ማረጋገጣቸውን በአሜሪካ የሚገኝ ራስን ማጥፋትን ለመከላከል የተቋቋመ አንድ ድርጅት ገልጿል። “ይሁን እንጂ በአብዛኛው እነዚህ ሰዎች ችግሩ እንዳለባቸው አልተስተዋለም ወይም በምርመራ አልተረጋገጠም አሊያም አስፈላጊውን ሕክምና አላገኙም።”

      የሚያስቡልህ ሰዎች፦ የቤተሰብህን አባሎችና ወዳጆችህን ጨምሮ የአንተ ሕይወት የሚያሳስባቸው ሰዎች አሉ፤ ምናልባትም ይህን ነግረውህ ሊሆን ይችላል። ለአንተ ከሚያስቡልህ ሰዎች መካከል ጨርሶ አግኝተህ የማታውቃቸውም ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰብኩበት ጊዜ በጣም የተጨነቁ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች የደረሱላቸው እርዳታ በጣም በሚያስፈልጋቸውና ራሳቸውን ለማጥፋት በሚያስቡበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉት የስብከት ሥራ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን አርዓያ ስለሚከተሉ ለሰዎች ከልብ ያስባሉ። ለአንተም ያስባሉ።—ዮሐንስ 13:35

      የባለሙያ እርዳታ፦ ራስን የማጥፋት ሐሳብ በአብዛኛው እንደ መንፈስ ጭንቀት ያለ የጤና ችግር መኖሩን የሚጠቁም ነው። አንድ ዓይነት አካላዊ ሕመም ቢኖርብህ በዚህ እንደማታፍር ሁሉ የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥምህም ልታፍር አይገባም። እንዲያውም የመንፈስ ጭንቀት “የአእምሮ ጉንፋን” ተብሎ ተጠርቷል። ማንም ሰው ላይ ሊደርስ ይችላል፤ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ ሊደረግለት ይችላል።a

      ይህን አስታውስ፦ ብዙ ጊዜ ከገባህበት የጭንቀት ጉድጓድ በራስህ ጥረት መውጣት አትችልም። ሌሎች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉልህ የምትጠይቅ ከሆነ ግን ሊሳካልህ ይችላል።

      ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? የመንፈስ ጭንቀት ላለባቸው ሰዎች የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ጥሩ ስም ያተረፈ ሐኪም ፈልግ።

      a ራስህን የማጥፋቱ ሐሳብ እያየለብህ ከመጣ ወይም ከአእምሮህ ሊጠፋ ካልቻለ የባለሙያዎችን እርዳታ ለማግኘት ሞክር፤ ምናልባትም የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ነፃ የስልክ መስመሮችን መጠቀም ወይም ወደ አእምሮ ሆስፒታል መሄድ ትችላለህ። እንደነዚህ ያሉት ድርጅቶች እርዳታ ለመስጠት የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሏቸው።

  • 3 ተስፋ አለ
    ንቁ!—2014 | ሚያዝያ
    • አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ያለው ሰው

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?

      3 ተስፋ አለ

      “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:11

      ሕይወት “በመከራ የተሞላ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በዛሬው ጊዜ አሳዛኝ ሁኔታ የማያጋጥመው ሰው የለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ዓይነት የተስፋ ጭላንጭል አይታያቸውም፤ ወይም የተሻለ ነገር ይመጣል ብለው አያስቡም። አንተስ የሚሰማህ እንዲህ ነው? ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለአንተ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የሚሰጠው እውነተኛ ተስፋ አለ። ለምሳሌ ያህል፦

      • የይሖዋ አምላክ ዓላማ አሁን ካለው በጣም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:28

      • ይሖዋ አምላክ ምድራችንን ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:21-25

      • ይሖዋ የገባው ይህ ቃል እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል፦

        “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”

      ይህ ተስፋ የሕልም እንጀራ አይደለም። ይሖዋ አምላክ ይህን ተስፋ እውን እንደሚያደርገው ምን አያጠያይቅም፤ ደግሞም ይህን ለማድረግ ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ አስተማማኝ ነው፤ እንዲሁም “መኖር ምን ዋጋ አለው?” ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

      ይህን አስታውስ፦ ስሜትህ በሚናወጥ ባሕር ላይ እንዳለ ጀልባ እየወጣና እየወረደ ቢያስቸግርህም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደ መልሕቅ ሆኖ ሊያረጋጋህ ይችላል።

      ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠውን እውነተኛ ተስፋ መመርመር ጀምር። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም jw.org/ama በተባለው ድረ ገጻቸው ላይ ጠቃሚ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

      a ለጥቆማ ያህል፦ jw.org/amን ክፈት፤ ከዚያም “የሕትመት ውጤቶች” በሚለው ሥር የሚገኘውን “የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት” ክፈት። ቤተ መጻሕፍቱን ከከፈትክ በኋላ “የመንፈስ ጭንቀት” ወይም “ራስን መግደል” እንደሚሉት ያሉ ለፍለጋ የሚረዱ ቁልፍ ቃላትን ተጠቅመህ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ