የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ዓለም አቀፍ ችግር
    ንቁ!—2001 | ኅዳር 8
    • ዓለም አቀፍ ችግር

      “የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት አሳሳቢ የሆነ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ጠንቅ ነው።”—ዴቪድ ሳቸር የተባሉ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለ ሥልጣን በ1999 የተናገሩት

      አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለ ሥልጣን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ትልቅ የመወያያ ርዕስ አድርጎ ሲያቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ውስጥ በሌሎች እጅ ከሚገደሉት ሰዎች ይልቅ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት ሰዎች ቁጥር ልቆ ተገኝቷል። የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚያሻ መግለጹ ምንም አያስደንቅም።

      ይሁንና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ1997 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ሰዎች ቁጥር ከ100, 000 ሰዎች መካከል 11.4 የነበረ ሲሆን ይህም ከዓለም አቀፉ አኃዝ ያነሰ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2000 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ሰዎች ቁጥር ከ100, 000 ሰዎች መካከል 16 ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት 45 ዓመታት ውስጥ 60 በመቶ ጨምሯል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ። ይህ በግምት በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ያጠፋል እንደ ማለት ነው!

      ይሁን እንጂ አኃዛዊ መረጃዎች ሁኔታውን በተሟላ መልኩ ቁልጭ አድርገው አያሳዩም። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል የራሱን ሕይወት ማጥፋቱን በግልጽ መናገር አይፈልጉም። ከዚህም በላይ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ባጠፋ ቁጥር ከ10 እስከ 25 የሚደርሱ ራስን የመግደል ሙከራዎች እንደሚካሄዱ ይገመታል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚገኙት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት ጥናቱ ከመካሄዱ በፊት በነበረው ዓመት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ተነሳስተው እንደነበረ የተናገሩ ሲሆን ጥናቱ ከተካሄደባቸው ተማሪዎች መካከል 8 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ራሳቸውን ለመግደል ሙከራ አድርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዐዋቂ ከሆኑት ሰዎች መካከል ከ5 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት በሆነ ወቅት ላይ የራሳቸውን ሕይወት የማጥፋት ሐሳብ በአእምሯቸው ተጸንሶ እንደነበረ ሌሎች ጥናቶች አመልክተዋል።

      የባሕል ልዩነቶች

      ሰዎች የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለያያል። አንዳንዶች ወንጀል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፣ ሌሎች የፈሪዎች ሽሽት ነው የሚል አመለካከት ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው በግድ የለሽነት በሠራው ትልቅ ስህተት መጸጸቱን ለማሳየት የሚወስደው አድናቆት የሚቸረው እርምጃ እንደሆነ ያስባሉ። እንዲያውም አንዳንዶች የቆሙለትን ዓላማ ለማራመድ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲህ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ባሕል ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ሄልዝ ሌተር የተሰኘው ጽሑፍ ባሕል “የራስን ሕይወት ወደ ማጥፋት ሊመራ” ይችላል ሲል ገልጿል።

      በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኘውን ሀንጋሪን እንውሰድ። ዶክተር ዞልታን ሪመር በሃገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋውን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት የሀንጋሪ “አሳዛኝ ‘ባሕል’” ሲሉ ገልጸውታል። የሀንጋሪ ብሔራዊ የጤና ተቋም ዲሬክተር የሆኑት ቤላ ቡዳ ሀንጋሪያውያን በረባ ባልረባው ሁሉ ማለት ይቻላል፣ ያላንዳች ማመንታት የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ቡዳ አባባል “ካንሰር ከያዘው እንዴት እንደሚገላገል ያውቃል።” ይህ የተለመደ እርምጃ ነው።

      በአንድ ወቅት በሕንድ አገር ሰቲ የሚባል ሃይማኖታዊ ልማድ ነበር። ባልዋ የሞተባት ሴት የባልዋ አስከሬን የሚቃጠልበት እሳት ውስጥ በመግባት የምትፈጽመው ይህ ልማድ ከታገደ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። አንዲት ሴት በዚህ መንገድ ሕይወቷን እንዳጠፋች በተነገረ ጊዜ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በእጅጉ አወድሰዋታል። ኢንዲያ ቱዴይ እንደዘገበው ከሆነ በዚህ የሕንድ ክልል “በ25 ዓመት ውስጥ 25 ሴቶች የባሎቻቸው አስከሬን የሚቃጠልበት እሳት ውስጥ በመግባት ራሳቸውን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርገዋል።”

      የሚያስገርመው፣ በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት ሰዎች ቁጥር በመኪና አደጋ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ሦስት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል! ጃፓን​—⁠አን ኢለስትሬትድ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደገለጸው “የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን በማያወግዘው የጃፓን ባሕል የራስን የአካል ክፍል ቆርጦ የማውጣት (ሴፑኩ ወይም ሃሪ-ኪሪ) ሥርዓትና ወግ በእጅጉ የተለመደ ነው።”

      ከጊዜ በኋላ የቃል ኪዳኑ ማኅበር ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ኢናዞ ኒቶቤ ቡሺዶ ዘ ሶል ኦቭ ጃፓን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ብዙዎችን የሚማርከውንና ለሞት የሚዳርገውን ይህን ባሕል አስመልክተው የሰጡት ሐሳብ አለ። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በመካከለኛው መቶ ዘመን የተፈለሰፈው [ሴፑኩ] ተዋጊዎች የሠሩትን ወንጀል ለማስተሠረይ፣ ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ለመጠየቅ፣ ከውርደት ለማምለጥ፣ በጓደኞቻቸው ላይ ያደረሱትን ችግር ለማካካስ ወይም ቅንነታቸውን ለማሳየት የሚፈጽሙት ልማድ ነው።” ይህ በልማዳዊ ሥርዓት መልክ የሚፈጸመው የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት በጥቅሉ ጊዜ ያለፈበት ቢሆንም አሁንም አንዳንዶች ማኅበራዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ሲሉ ሲፈጽሙት ይታያል።

      በአንጻሩ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት ከረጅም ጊዜ አንስቶ እንደ ወንጀል ሲቆጠር የኖረ ነው። በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመናት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎችን ከአባልነት በመሰረዝ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳይካሄድላቸው አግዳለች። በአንዳንድ ቦታዎች ይታይ የነበረው ሃይማኖታዊ ቀናኢነት የራስን ሕይወት ከማጥፋት ድርጊት ጋር በተያያዘ የሰውየውን አስከሬን በእንጨት ላይ መስቀልን አልፎ ተርፎም ልቡን በእንጨት መብሳትን የመሳሰሉ እንግዳ የሆኑ ልማዶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

      የሚገርመው ነገር የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎች የሞት ቅጣት ሊደርስባቸው ይችል ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ እንግሊዛዊ አንገቱን በመገዝገዝ ራሱን ለመግደል በመሞከሩ በስቅላት ተቀጥቷል። በመሆኑም ባለ ሥልጣናቱ ሰውየው በራሱ ማድረግ የተሳነውን ነገር ፈጽመዋል። ራሳቸውን ለመግደል በሞከሩ ሰዎች ላይ የሚበየነው ቅጣት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የተለወጠ ቢሆንም የብሪታንያ ፓርላማ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትም ሆነ ራስን ለመግደል የሚደረግ ሙከራ እንደ ወንጀል ተደርጎ የመታየቱ ጉዳይ ያከተመ መሆኑን ያስታወቀው በ1961 ነው። በአየርላንድ ደግሞ እስከ 1993 ድረስ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር።

      በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ደራሲዎች የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት እንደ አንድ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ይናገራሉ። በማይድን በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎችን ዕድሜ ለማሳጠር የሚወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በ1991 የወጣ አንድ መጽሐፍ የሕመምተኛው ሕይወት እንዲያልፍ ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶችን ጠቁሟል። ውሎ አድሮ ግን በእንዲህ ዓይነት አስከፊ በሽታ ያልተያዙ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ በርካታ ሰዎች በመጽሐፉ ላይ ከተጠቆሙት መንገዶች አንዱን ተጠቅመዋል።

      ከችግር ለመላቀቅ መፍትሔው የራስን ሕይወት ማጥፋት ነው? ወይስ በሕይወት ለመቀጠል የሚገፋፉ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ከማግኘታችን በፊት የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱት ነገሮች ምን እንደሆኑ እንመርምር።

      [በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      በዓለም ዙሪያ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ። ይህም በየ40 ሴኮንዱ አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ያጠፋል እንደ ማለት ነው!

  • ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2001 | ኅዳር 8
    • ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ለምንድን ነው?

      “ሕይወቱን የሚያጠፋ ሰው ሁሉ የራሱ የሆነ እጅግ ምሥጢራዊ፣ ድብቅና ከባድ ጭንቀት ውስጥ የሚከት ምክንያት አለው።”—ኬይ ሬድፊልድ ጄሚሰን፣ የሥነ አእምሮ ባለሙያ።

      “በሕይወት መኖር መከራ ነው።” ይህ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖር የነበረ ሪዩኖሱኬ አኩታጋዋ የተባለ የታወቀ ደራሲ የራሱን ሕይወት ከማጥፋቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት የጻፈው ነው። ይሁንና ይህን ዐረፍተ ነገር የከፈተው “እርግጥ መሞት አልፈልግም፤ ግን . . .” በሚሉት ቃላት ነበር።

      እንደ አኩታጋዋ ሁሉ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ብዙ ሰዎችም መሞት ባይፈልጉም እንኳ “እየደረሰባቸው ካለው ነገር መገላገል” እንደሚፈልጉ አንድ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር ገልጸዋል። የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች በአብዛኛው የሚተዉት ማስታወሻ ይህንኑ የሚጠቁም ነው። ‘በቃኝ’ ወይም ‘ከዚህ በኋላ የእኔ መኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?’ የሚሉት አባባሎች በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ አስከፊ ሁኔታዎች ለመገላገል ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት የሚያመለክቱ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ ባለሙያ እንደገለጹት የራስን ሕይወት ማጥፋት “የጉንፋን በሽታን በኑክሊየር ቦምብ ለማከም እንደ መሞከር ይቆጠራል።”

      ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች የሚለያዩ ቢሆንም እንኳ ለዚህ ድርጊት የሚገፋፉ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ አንዳንድ የተለመዱ ሁኔታዎች አሉ።

      የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱ ሁኔታዎች

      ልጆች ለሌሎች ተራ መስለው ሊታዩ በሚችሉ ነገሮች ሳይቀር ተስፋ ቆርጠው የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋታቸው ያልተለመደ አይደለም። በደል እንደተፈጸመባቸውና ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ሆኖ ከተሰማቸው የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት የበደሏቸውን ሰዎች መበቀል እንደሚችሉ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚነሳሱ ሰዎችን በመርዳት ሙያ ላይ የተሰማሩት ሂሮሺ ኢናሙራ “ልጆች የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት ሥቃይ ያደረሰባቸውን ሰው መቅጣት ይፈልጋሉ” ሲሉ ጽፈዋል።

      በቅርቡ በብሪታንያ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ልጆች ከባድ በደል በሚደርስባቸው ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርጉበት አጋጣሚ በሰባት እጥፍ ገደማ ይጨምራል። በልጆቹ ስሜት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። ራሱን ሰቅሎ የሞተ አንድ የ13 ዓመት ልጅ በተወው ማስታወሻ ላይ ያሠቃዩትን አልፎ ተርፎም አስፈራርተው ገንዘቡን የወሰዱበትን አምስት ልጆች ስም የጠቀሰ ሲሆን “እባካችሁ ሌሎች ልጆችን ታደጓቸው” ሲል ጽፏል።

      ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤት ወይም ሕግ በመተላለፋቸው የተነሳ ችግር ሲገጥማቸው፣ ከፍቅረኛቸው ሲለያዩ፣ ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጡ፣ የትምህርት ቤት ፈተና ጭንቀት ሲፈጥርባቸው ወይም የወደፊቱ ሕይወታቸው ተስፋ ሲያስቆርጣቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡና በሁሉ ነገር ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ የሚታይባቸው አንዳንድ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች አንድ ሳንካ ወይም እክል ሲገጥማቸው ወይም እንደገጠማቸው አድርገው ሲያስቡ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ።

      ዐዋቂ የሆኑ ሰዎችን ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከገንዘብ ወይም ከሥራ ጋር የተያያዙ ችግሮች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ያደርጓቸዋል። በጃፓን በርከት ላሉ ዓመታት ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ከመጣ ወዲህ በዓመት ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ከ30, 000 በላይ ሆኗል። ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የራሳቸውን ሕይወት ካጠፉት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ይገኙ ከነበሩ ወንዶች መካከል ሦስት አራተኛ ገደማ የሚሆኑት ይህን ድርጊት የፈጸሙት “ከዕዳ፣ በንግድ ሥራ ላይ ከሚደርስ ኪሳራ፣ ከድህነትና ከሥራ አጥነት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ” ነው። ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮችም የራስን ሕይወት ለማጥፋት ሊያነሳሱ ይችላሉ። አንድ የፊንላንድ ጋዜጣ “ከትዳር ጓደኞቻቸው ከተፋቱ ብዙም ያልቆዩ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች” የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ያላቸው ዕድል በእጅጉ የሰፋ ነው ሲል ዘግቧል። በሀንጋሪ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ከሚነሳሱት ልጃገረዶች መካከል አብዛኞቹ በተፋቱ ወላጆች ሥር ያደጉ ናቸው።

      ጡረታ መውጣትና አካላዊ ሕመምም በተለይ አረጋውያን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። አንድ በሽታ የማይድን ዓይነት በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሕመምተኛው ሥቃዩን መቋቋም እንደማይችል አድርጎ በሚያስብበት ጊዜም የራሱን ሕይወት ማጥፋት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አድርጎ ሊያስብ ይችላል።

      ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የገጠሙት ሰው ሁሉ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ይነሳሳል ማለት አይደለም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ አብዛኞቹ ሰዎች ውጥረት ውስጥ የሚከቱ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት አያስቡም። አብዛኞቹ እንዲህ የማያስቡ ከሆነ ታዲያ አንዳንዶች መፍትሔው የራስን ሕይወት ማጥፋት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡት ለምንድን ነው?

      ከበስተጀርባ ያሉት ምክንያቶች

      በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬይ ሬድፊልድ ጄሚሰን “ሰዎች በአብዛኛው ራሳቸውን ለመግደል እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው ላጋጠሟቸው ሁኔታዎች የሚሰጡት ትርጉም ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “አብዛኞቹ ጤናማ አእምሮ ያላቸው ሰዎች የገጠማቸው ሁኔታ ምንም ያህል አስከፊ ቢሆን የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያበቃ ምክንያት አድርገው አይመለከቱትም” ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኢቭ ኬ ሞሽቺትስኪ ከበስተጀርባ ያሉትን መንስኤዎች ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ተደራርበው አንድ ሰው ራሱን ለመግደል እንዲነሳሳ ያደርጉታል በማለት ተናግረዋል። እነዚህ ከበስተጀርባ ያሉ ምክንያቶች የአእምሮ ሕመምን፣ ከሱሰኝነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን፣ ጀነቲካዊ ቅንብርንና በአንጎል ውስጥ ያለውን ኬሚካላዊ አሠራር የሚያጠቃልሉ ናቸው። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

      ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ እንደ የመንፈስ ጭንቀት፣ ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደርስ፣ እና ስኪትሶፍሪኒያ ያሉ የአእምሮ ሕመሞችና አልኮልን አላግባብ የመጠጣት ወይም አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ ናቸው። በአውሮፓም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው ምርምር እንዳመለከተው የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሰዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት እንዲህ ዓይነት ችግሮች ያሉባቸው ናቸው። እንዲያውም የስዊድን ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ምርመራ ተደርጎላቸው እንዲህ ዓይነት ችግሮች ካልታዩባቸው 100, 000 ወንዶች መካከል የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት 8.3 የሚያክሉት ሲሆኑ የመንፈስ ጭንቀት ካለባቸው 100, 000 ወንዶች መካከል ግን 650 የሚሆኑት የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ! በምሥራቃውያን አገሮችም ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ተመሳሳይ እንደሆኑ ጠበብት ይናገራሉ። ይህ ማለት ግን የመንፈስ ጭንቀትና የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱ ሁኔታዎች የተደራረቡበት ሰው ሁሉ ራሱን መግደሉ አይቀሬ ነው ማለት አይደለም።

      በአንድ ወቅት ራሳቸውም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገው የነበሩት ፕሮፌሰር ጄሚሰን “ሰዎች ሁኔታዎች ይሻሻላሉ የሚል እምነት እስካላቸው ድረስ የመንፈስ ጭንቀትን የመቋቋም ወይም የመቻል አቅም ያላቸው ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እያደር እየጨመረ የሚመጣው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሸከሙት የማይችሉት ደረጃ ላይ ሲደርስ አእምሮም የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚገፋፋውን ስሜት ለመዋጋት ያለው አቅም ቀስ በቀስ እየተዳከመ እንደሚሄድ ፕሮፌሰሯ አመልክተዋል። ሁኔታውን በተደጋጋሚ በሚደርስበት ጫና እየሳሳ ከሚሄድ የመኪና ፍሬን ሸራ ጋር አመሳስለውታል።

      የመንፈስ ጭንቀት በሕክምና እርዳታ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነገር በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን አዝማሚያ ልብ ማለቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የተስፋ መቁረጥን ስሜት በአዎንታዊ አመለካከት መተካት ይቻላል። ከበስተጀርባ ያሉት መንስኤዎች ተለይተው ታውቀው መፍትሔ ሲፈለግላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ የሚያደርጓቸውን እጅግ አሳዛኝና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በተለየ መንገድ መመልከት ሊጀምሩ ይችላሉ።

      አንዳንዶች ጀነቲካዊ ቅንብር ብዙዎች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ሊያደርግ የሚችል ስውር መንስኤ እንደሆነ ያምናሉ። እርግጥ ነው፣ ጂኖች የአንድን ሰው ባሕርይ በመወሰን ረገድ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ሲሆን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት በአንዳንድ የዘር ሐረጎች ውስጥ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ ጥናቶች አመልክተዋል። ሆኖም “በጀነቲካዊ ቅንብር ሳቢያ የራስን ሕይወት ለማጥፋት ድርጊት የተጋለጡ ሰዎች ድርጊቱን ፈጽሞ ሊያስቀሩት አይችሉም ማለት እንዳልሆነ ሊስተዋል ይገባል” ይላሉ ጄሚሰን።

      የአንጎል ኬሚካላዊ አሠራርም ስውር መንስኤ ሊሆን ይችላል። በአንጎል ውስጥ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሕዋሳተ ነርቭ ኤሌክትሮኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ግንኙነት ያደርጋሉ። ወደተለያየ አቅጣጫ ተዘርግተው በሚገኙት የነርቭ ቃጫዎች ጫፍ ጋጥሚያ ሕዋሳተ ነርቭ (synapses) በመባል የሚታወቁ ትናንሽ ክፍተቶች አሉ። ኒውሮትራንስሚተር የሚባሉት ንጥረ ነገሮች በእነዚህ ጋጥሚያ ሕዋሳተ ነርቭ በኩል መረጃውን ኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ያስተላልፋሉ። ሴሮቶኒን የሚባለው ኒውሮትራንስሚተር ያለው መጠን አንድ ሰው ከሥነ ሕይወት አኳያ የራስን ሕይወት ለማጥፋት ድርጊት የተጋለጠ እንዲሆን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ኢንሳይድ ዘ ብሬን የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሴሮቶኒን መጠን ማነስ . . . የሕይወትን ደስታ ሊሰርቅ፣ የሰውን የመኖር ፍላጎት ሊያጠፋ፣ ለመንፈስ ጭንቀት ይበልጥ ሊያጋልጥና የራስን ሕይወት ለማጥፋት ሊያነሳሳ ይችላል።”

      ይሁን እንጂ የራሱን ሕይወት እንዲያጠፋ ተደርጎ የተፈጠረ ሰው እንደሌለ መታወቅ አለበት። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እጅግ አሳዛኝ የሆኑና ውጥረት ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ይኖራሉ። አንዳንዶች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ነገር ለሚያጋጥማቸው ጫና አእምሯቸውና ልባቸው ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ነው። ጎልተው የሚታዩት ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ ከበስተጀርባ ያሉት መንስኤዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

      እንግዲያው የመኖርን ፍላጎት መልሶ ሊያቀጣጥል የሚችል ይበልጥ አዎንታዊ የሆነ አመለካከት መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ፆታና የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት

      በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ሴቶች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ሙከራቸው ተሳክቶ ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ወንዶች ቁጥር ግን ከሴቶቹ በአራት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል። በመንፈስ ጭንቀት የሚጠቁ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት በሚያደርጉት ሙከራ ረገድ ከወንዶቹ በልጠው ሊገኙ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ይሁንና የሚያድርባቸው የመንፈስ ጭንቀት በጣም ከባድ ላይሆን ስለሚችል ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚጠቀሙበት ዘዴም ያን ያህል አደገኛ ላይሆን ይችላል። በአንጻሩ ግን ወንዶች ሙከራቸው ስኬታማ እንዲሆን ይበልጥ ኃይለኛና የማያዳግም እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።

      ይሁን እንጂ በቻይና ከወንዶቹ ይልቅ ሙከራቸው ይበልጥ የሚሳካላቸው ሴቶቹ ናቸው። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደጠቆመው በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሴቶች መካከል 56 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በቻይና በተለይ ደግሞ በገጠራማው ክፍል የሚኖሩ ናቸው። ሴቶቹ በግብታዊነት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ የሚሳካበት አንዱ ምክንያት ቀሳፊ የሆኑ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች እንደ ልብ ስለሚገኙ እንደሆነ ይነገራል።

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትና ብቸኝነት

      ሰዎች የመንፈስ ጭንቀት እንዲይዛቸውና የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የብቸኝነት ስሜት ነው። በፊንላንድ በተፈጸሙ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊቶች ላይ የተካሄደውን ጥናት የመሩት ዮኡኮ ሎንክዊስት “[የራሳቸውን ሕይወት ካጠፉት ሰዎች መካከል] ብዙዎቹ የብቸኝነት ኑሮ ይኖሩ የነበሩ ናቸው። ብዙ ትርፍ ጊዜ የነበራቸው ቢሆንም ከሌሎች ጋር እምብዛም ማኅበራዊ ግንኙነት አልነበራቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። በጃፓን በሃማማትሱ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የሥነ አእምሮ ባለሙያ የሆኑት ኬንሺሮ ኦሃራ በአገሪቱ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ነገር “ብቸኝነት” እንደሆነ ገልጸዋል።

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ብዙውን ጊዜ ዐዋቂ የሆኑ ሰዎችን ከገንዘብ ወይም ከሥራ ጋር የተያያዙ ችግሮች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ያደርጓቸዋል

  • እርዳታ ማግኘት ትችላለህ
    ንቁ!—2001 | ኅዳር 8
    • እርዳታ ማግኘት ትችላለህ

      በስዊዘርላንድ የሚኖር አንድ የ28 ዓመት ሰው ‘አርባ ዘጠኝ የእንቅልፍ ክኒን ብርጭቆ ውስጥ ከጨመረ በኋላ ልዋጠው አልዋጠው?’ ሲል ራሱን ጠየቀ። ሚስቱና ልጆቹ ጥለውት በመሄዳቸው በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ተውጧል። መድኃኒቱን ከዋጠ በኋላ ግን ‘የለም፣ መሞት አልፈልግም!’ ሲል ለራሱ ተናገረ። ደግነቱ ከሞት ተርፎ ሁኔታውን ለመተረክ በቅቷል። የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚገፋፉ ስሜቶች ሁልጊዜ ለሞት አያበቁም።

      የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት ባልደረባ የሆኑት አሊክስ ክሮዝቢ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉትን ሙከራ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ለጥቂት ሰዓታት እንኳን ድርጊቱን ማስተው ከቻላችሁ ሙሉ በሙሉ ማስጣል ትችላላችሁ። ድርጊቱን በማስተጓጎል ብዙዎች ሕይወታቸውን ወደማጥፋት ደረጃ እንዳይሸጋገሩ መከላከል ትችላላችሁ። እንዲህ በማድረግ ሕይወታቸውን መታደግ ትችላላችሁ።”

      ፕሮፌሰር ሂሳሺ ኩሮሳዋ በጃፓን የሕክምና ኮሌጅ የሕይወት አድንና የአደጋ መከላከያ ማዕከል በሚሠሩበት ወቅት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የተነሳሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመርዳት የመኖር ፍላጎታቸው በውስጣቸው እንዲያንሰራራ አድርገዋል። አዎን፣ በሆነ መንገድ እርዳታ በመስጠት የብዙዎችን ሕይወት መታደግ ይቻላል። ምን ዓይነት እርዳታ ነው የሚያስፈልገው?

      ከበስተጀርባ ያሉትን ችግሮች መጋፈጥ

      ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት የሥነ አእምሮ ሕመም ወይም ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን አላግባብ የመውሰድ ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በመሆኑም የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኢቭ ኬ ሞሽቺትስኪ “በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ከማጥፋት እንዲታቀቡ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው አማራጭ የአእምሮ ሕመምንና ሱሰኝነትን መዋጋት ነው” ብለዋል።

      የሚያሳዝነው እንዲህ ያሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ብዙዎቹ ሰዎች እርዳታ የመፈለግ ዝንባሌ የላቸውም። ለምን? “በኅብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የተዛባ አመለካከት ያለ በመሆኑ ነው” ይላሉ የቶኪዮ የሥነ አእምሮ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዮሺቶሞ ታካሃሺ። በመሆኑም ደህና እንዳልሆኑ በመጠኑም ቢሆን የሚታወቃቸው ሰዎች እንኳ ወዲያውኑ ሕክምና ለማግኘት አይሞክሩም ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

      አንዳንዶች ግን ኀፍረት እንዲያሸንፋቸው አይፈቅዱም። በጃፓን ለ17 ዓመታት በቴሌቪዥን የራሱን ፕሮግራም ሲያቀርብ የነበረ ሂሮሺ ኦጋዋ የተባለ አንድ የታወቀ ሰው የመንፈስ ጭንቀት እንዳለበትና እንዲያውም የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ተቃርቦ እንደነበረ በይፋ አምኗል። “የመንፈስ ጭንቀት የአእምሮ ጉንፋን ነው ሊባል ይችላል” ሲል ኦጋዋ ተናግሯል። ማንኛውም ሰው ሊይዘው ይችላል፤ ቢሆንም ማገገም ይቻላል በማለት ገልጿል።

      ችግርህን ለሌላ ሰው አዋየው

      ቀደም ሲል የተጠቀሱት ቤላ ቡዳ የተባሉ የሀንጋሪ የጤና ባለሥልጣን “አንድ ሰው ችግሩን ለብቻው ሲጋፈጥ ብዙውን ጊዜ ከልክ በላይ አግዝፎ የሚመለከተው ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ ሊፈታ እንደማይችል አድርጎ ያስባል” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አስተያየት የሚከተለው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥበብ የተሞላበት መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”​—⁠ምሳሌ 18:​1

      እነዚህን ጥበብ የተሞላባቸው ቃላት ልትሠራባቸው ይገባል። በችግር ባሕር ውስጥ ተዘፍቀህ ብቻህን የምትታገልበት ምንም ምክንያት የለም። እምነት ልትጥልበትና ችግርህን ልታካፍለው የምትችለው ሰው ፈልግ። ምናልባት ‘ችግሬን ላካፍለው የምችለው ሰው የለኝም’ ትል ይሆናል። የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ናኦኪ ሳቶ እንደሚሉት ከሆነ ብዙዎች እንዲህ ይሰማቸዋል። ሳቶ እንደገለጹት ሕሙማን ድክመቶቻቸውን መግለጥ ስለማይፈልጉ ችግራቸውን ለሌሎች ከማዋየት ይቆጠባሉ።

      አንድ ሰው ችግሩን ሊያዋየው የሚችለው ሰው የት ሊያገኝ ይችላል? በብዙ አገሮች ግለሰቡ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትን ለመከላከል ከተቋቋመ ማዕከል ወይም በስልክ የምክር አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ደግሞ ከስሜታዊ ችግሮች ጋር የተያያዘ ሕክምና ከሚሰጥ የታወቀ ሐኪም እርዳታ ማግኘት ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ጠበብት ሃይማኖትም ጥሩ የእርዳታ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ሃይማኖት ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

      አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘት

      በቡልጋሪያ የሚኖር ማሪን የተባለ አካላዊ እክል ያለበት ሰው ራሱን እንዲገድል የሚገፋፋ ስሜት አደረበት። አንድ ቀን በአጋጣሚ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ጽሑፍ አገኘ። የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩት ይፈልግ እንደሆነ መጽሔቱ ላይ ለቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠ። ማሪን የተገኘውን ውጤት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሕይወት የሰማያዊ አባታችን ስጦታ እንደሆነና ሆን ብለን ራሳችንን የመጉዳት ወይም ሕይወታችንን የማጥፋት መብት እንደሌለን እንድገነዘብ አደረጉኝ። በመሆኑም ሕይወቴን ለማጥፋት የነበረኝ ፍላጎት ተወግዶ የመኖር ፍላጎት ዳግም በውስጤ ተጸነሰ!” በተጨማሪም ማሪን ከክርስቲያን ጉባኤ ፍቅራዊ እርዳታ አገኘ። ምንም እንኳ አሁንም አካላዊ እክል ያለበት ቢሆንም “ዛሬ በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ መንፈሴ ተረጋግቷል። ልሠራቸው የምችል በርካታ አስደሳች ነገሮች ስላሉ ጊዜ እንኳን አይበቃኝም! ለዚህ ሁሉ ይሖዋንና ምሥክሮቹን ላመሰግን እወዳለሁ” ብሏል።

      በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ስዊዘርላንዳዊ ወጣትም ከይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ አግኝቷል። ወደ ቤታቸው የወሰዱት “አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ያሳዩትን ደግነት” ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማስታወስ ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በኋላ ደግሞ [የይሖዋ ምሥክሮች] ጉባኤ አባላት በየተራ እየወሰዱ ይጋብዙኝ ጀመር። በእጅጉ የረዳኝ ነገር ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ የተደረገልኝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሐሳቤን ላካፍለው የምችለው ሰው ማግኘቴ ጭምር ነው።”

      ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው ትምህርት በተለይ ደግሞ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅር ማወቁ ይበልጥ አበረታቶታል። (ዮሐንስ 3:​16) በእርግጥም ይሖዋ አምላክ ‘ልብህን በፊቱ በምታፈስስበት’ ጊዜ ይሰማሃል። (መዝሙር 62:​8) “ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ።” ይህን የሚያደርገው በሰዎች ላይ ስህተት ለመፈለግ ሳይሆን “ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን” ለማጽናት ነው። (2 ዜና መዋዕል 16:​9) ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ” ሲል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።​—⁠ኢሳይያስ 41:​10

      ስዊዘርላንዳዊው ሰው አምላክ ስለ አዲሱ ዓለም የገባውን ቃል አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ተስፋ እንደ ሸክም የተጫነኝን ሐዘንና ብስጭት ለማቅለል በጣም ረድቶኛል” ብሏል። የ“ነፍስ መልሕቅ” ተብሎ የተገለጸው ይህ ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘትን የሚጨምር ነው።​—⁠ዕብራውያን 6:​19፤ መዝሙር 37:​10, 11, 29

      ሕይወትህ በሌሎች ዘንድ ውድ ነው

      እርግጥ ነው፣ ሙሉ በሙሉ ብቻህን እንደሆንክና የአንተ መሞት አለመሞት በሌሎች ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ እንዲሰማህ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊገጥሙህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በብቸኝነት ስሜት እና ብቸኛ በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን አስታውስ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ነቢዩ ኤልያስ በጣም ተስፋ የቆረጠበት ጊዜ ነበር። “ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ” ሲል ለይሖዋ ተናግሮ ነበር። አዎን፣ ኤልያስ ብቻውን እንደቀረ ተሰምቶት ነበር። ለዚህም ምክንያት ነበረው። እንደሱው ያሉ በርካታ ነቢያት የተገደሉ ሲሆን እርሱም ራሱ የግድያ ዛቻ ስለተሰነዘረበት ሕይወቱን ለማዳን በሽሽት ላይ ነበር። ግን በእርግጥ ብቻውን ነበርን? አልነበረም። ይሖዋ በእነዚያ የጨለማ ዘመናት እንደ እሱ እውነተኛውን አምላክ በታማኝነት ለማገልገል እየጣሩ ያሉ 7, 000 ገደማ የሚሆኑ ታማኝ ሰዎች መኖራቸውን እንዲገነዘብ አደረገው። (1 ነገሥት 19:​1-18) ስለ አንተስ ምን ለማለት ይቻላል? አንተም የምታስበውን ያህል ብቸኛ አልሆንክ ይሆናል።

      ለአንተ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ወላጆችህን፣ የትዳር ጓደኛህን፣ ልጆችህንና ጓደኞችህን ልታስብ ትችላለህ። ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያስቡልህ፣ በትዕግሥት የሚያዳምጡህና አብረውህም ሆነ በግላቸው ለአንተ የሚጸልዩ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ልታገኝ ትችላለህ። (ያዕቆብ 5:​14, 15) በተጨማሪም አለፍጽምና ያለባቸው ሰዎች ሁሉ እንደጠበቅካቸው ሆነው ባይገኙ እንኳ ከቶ የማይተውህ አካል መኖሩን አትዘንጋ። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 27:​10፣ አ.መ.ት) አዎን፣ ይሖዋ ‘ያስብልሃል።’ (1 ጴጥሮስ 5:​7) በይሖዋ ዓይን ውድ መሆንህን ፈጽሞ አትዘንጋ።

      ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ስጦታ ከመሆን ይልቅ ሸክም ሆኖ ሊታይ እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ ለአንድ ሰው ውድ የሆነ ስጦታ ብትሰጠውና ግለሰቡ ስጦታውን ሳይጠቀምበት ቢጥለው ምን ሊሰማህ እንደሚችል መገመት ትችላለህ? እኛ አለፍጽምና ያለብን ሰዎች የሕይወትን ስጦታ ምንም ያህል አልተጠቀምንበትም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዓይን ሲታይ አሁን እየኖርነው ያለነው ሕይወት ‘እውነተኛው ሕይወት’ እንዳልሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​19) አዎን፣ በቅርቡ ሕይወታችን ይበልጥ የተሟላና ትርጉም ያለው እንዲሁም አስደሳች ይሆናል። እንዴት?

      መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ይላል። (ራእይ 21:​3, 4) እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖርህ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ጊዜ ወስደህ የተሟላና ማራኪ ስዕል በምናብህ ለመሳል ሞክር። ይህ ምናባዊ ስዕል ባዶ ቅዠት አይደለም። ባለፉት ዘመናት ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት ይዟቸው እንደነበር ስታሰላስል በእሱ ላይ ያለህ ትምክህት የሚያድግ ከመሆኑም በላይ ይህ ምናባዊ ስዕል ይበልጥ እውን ሆኖ ይታይሃል።​—⁠መዝሙር 136:​1-26

      የመኖር ፍላጎትህን ሙሉ በሙሉ ለመቀስቀስ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። ‘በመከራችን ሁሉ ወደሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ መጸለይህን ቀጥል። (2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4፤ ሮሜ 12:​12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​17) ይሖዋ የሚያስፈልግህን ብርታት ይሰጥሃል። በሕይወት መኖርን የመሰለ ነገር እንደሌለ ያስተምርሃል።​—⁠ኢሳይያስ 40:​29

      [በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      ራሱን የመግደል አዝማሚያ የሚታይበትን ሰው እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?

      አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ማጥፋት እንደሚፈልግ ቢነግርህ ማድረግ ያለብህ ነገር ምንድን ነው? የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) “ጥሩ አዳማጭ ሁን” ሲል ይመክራል። የሚሰማውን አውጥቶ እንዲናገር ፍቀድለት። ብዙውን ጊዜ ግን የራሱን ሕይወት ለማጥፋት የተነሳሳ ሰው ራሱን የሚያገልል ከመሆኑም በላይ ሐሳቡን ለማካፈል ፈቃደኛ አይደለም። ጥልቅ ሐዘን ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳደረበት ልታውቅለት ይገባል። በጠባዩ ላይ የታዩ አንዳንድ ለውጦችን ጠቅሰህ በለዘበ አንደበት ብታነጋግረው የልቡን አውጥቶ ለመናገር ሊገፋፋ ይችላል።

      በምታዳምጥበት ጊዜ እንደ ራስህ ችግር አድርገህ በመመልከት አሳቢነት አሳይ። “የግለሰቡ ሕይወት በአንተም ሆነ በሌሎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ጠበቅ አድርጎ መግለጹ አስፈላጊ ነው” ይላል ሲ ዲ ሲ። የእሱ ሞት በአንተም ሆነ በሌሎች ላይ ምን ያህል ከባድ የመንፈስ ስብራት ሊያደርስ እንደሚችል እንዲገነዘብ አድርግ። ግለሰቡ ፈጣሪው የሚያስብለት መሆኑን እንዲያስተውል እርዳው።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​7

      በተጨማሪም ግለሰቡ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን ነገሮች በሙሉ በተለይም እንደ ሽጉጥ ያሉ መሣሪያዎችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ጠበብት ይመክራሉ። ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ ከታየህ ግለሰቡ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ልታበረታታው ትችላለህ። ከዚህ የከፋ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ያለህ አማራጭ አንተ ራስህ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ባለሙያዎችን መጥራት ይሆናል።

      [በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ‘እንዲህ ዓይነት ነገር አስቤ አምላክ ይቅር ይለኛል?’

      ብዙዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመገናኘታቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ አድርጓቸው የነበረውን ስሜት ማሸነፍ ችለዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ውጥረት ውስጥ ከሚከትቱ ሁኔታዎችና ከመንፈስ ጭንቀት ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ሰው የለም። የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ተነሳስተው የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ለማድረግ ማሰባቸው ብዙውን ጊዜ የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ይህ የበደለኛነት ስሜት ሸክማቸውን ከማክበድ በቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እንግዲያው እንዲህ ዓይነቱን ስሜት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

      በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስለ ሕይወት ያደረባቸውን እጅግ አሉታዊ የሆነ ስሜት የገለጹባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው። የዕብራውያን አባት የሆነው የይስሐቅ ሚስት ርብቃ በአንድ ወቅት በቤተሰባቸው ውስጥ በተፈጠረ ችግር ሳቢያ በጣም ከማዘኗ የተነሳ “ሕይወቴን ጠላሁት” ስትል ተናግራለች። (ዘፍጥረት 27:​46) ልጆቹን፣ ጤናውን፣ ሀብቱንና በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን ቦታ ያጣው ኢዮብ “ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 10:​1) ሙሴ በአንድ ወቅት “እባክህ፣ ፈጽሞ ግደለኝ” ሲል አምላክን ተማጽኗል። (ዘኁልቁ 11:​15) የአምላክ ነቢይ የሆነው ኤልያስ በአንድ ወቅት “ይበቃኛል፤ አሁንም፣ አቤቱ፣ . . . ነፍሴን ውሰድ” ብሎ ነበር። (1 ነገሥት 19:​4) በተጨማሪም ነቢዩ ዮናስ በተደጋጋሚ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” ሲል ተናግሮ ነበር።​—⁠ዮናስ 4:​8

      ይሖዋ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ ስሜት ስለተሰማቸው ኮንኗቸዋልን? አልኮነናቸውም። እንዲያውም የተናገሩት ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ እንዲቀመጥ አድርጓል። ይሁንና ከእነዚህ ታማኝ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ያደረባቸው ስሜት የራሳቸውን ሕይወት ወደማጥፋት ድርጊት እንዲመራቸው እንዳልፈቀዱ ልብ ማለት ያሻል። ይሖዋ ከፍ አድርጎ ተመልክቷቸዋል፤ በሕይወት እንዲቀጥሉም ፈልጓል። እንዲያውም አምላክ ለክፉዎች ሕይወት ሳይቀር ያስባል። መንገዳቸውን እንዲለውጡና ‘በሕይወት እንዲኖሩ’ ያሳስባቸዋል። (ሕዝቅኤል 33:​11) የእርሱን ሞገስ ለማግኘት ለሚጥሩት ሰዎች ሕይወት ደግሞ የበለጠ እንደሚያስብ የተረጋገጠ ነው!

      አምላክ የልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት፣ የክርስቲያን ጉባኤን፣ መጽሐፍ ቅዱስንና የጸሎት መብት ሰጥቶናል። ከአምላክ ጋር የምንነጋገርበት የጸሎት መስመር ተይዞብን አያውቅም። አምላክ ትሁትና ቅን በሆነ ልቦና የሚቀርቡትን ሁሉ ሊሰማ ይችላል፣ ደግሞም ይሰማል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”​—⁠ዕብራውያን 4:​16

      [በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      የራሱን ሕይወት ያጠፋ የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጅ አለህን?

      አንድ ሰው የራሱን ሕይወት በሚያጠፋበት ጊዜ የቤተሰቡ አባላትና የቅርብ ጓደኞቹ ከባድ የአእምሮ መረበሽ ይደርስባቸዋል። ብዙዎች ለደረሰው ሁኔታ ራሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ‘ምነው ያን ቀን ትንሽ አብሬው በቆየሁ ኖሮ፣’ ‘ምነው ምላሴን በቆረጠው ኖሮ’ ‘ይበልጥ በረዳሁት ኖሮ’ ይላሉ። በሌላ አባባል ‘እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ባልሞተ ነበር’ ማለታቸው ነው። ይሁን እንጂ ሌላው ሰው በሕይወቱ ላይ ለወሰደው እርምጃ ራስን ተጠያቂ ማድረጉ አግባብ ነውን?

      ሁኔታው ከተፈጸመ በኋላ ግለሰቡ ራሱን ለመግደል አስቦ እንደነበረ የሚጠቁሙ ምልክቶችን መለየት እንደማይከብድ አትዘንጋ። ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት እነዚህን ምልክቶች ማስተዋል መቻል እንዲህ ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም” ይላል። (ምሳሌ 14:​10፣ አ.መ.ት ) አንዳንድ ጊዜ ሌላው ሰው የሚያስበውን ወይም የሚሰማውን ስሜት መረዳት አይቻልም። የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ያሰቡ ብዙዎቹ ሰዎች ለሌሎች፣ ለቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ሳይቀር ውስጣዊ ስሜታቸውን ሙሉ በሙሉ መግለጥ ይሳናቸዋል።

      ጊቪንግ ሶሮው ወርድስ የተሰኘው መጽሐፍ አንድ ሰው ራሱን ለመግደል ማሰቡን ሊጠቁሙ ስለሚችሉ ምልክቶች ሲናገር “ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉትን ምልክቶች መረዳት ቀላል አይደለም” ብሏል። አንዳንድ ፍንጮች አግኝተህ የነበረ ቢሆን እንኳ ይህ በራሱ ድርጊቱን ማስቀረት ያስችልህ የነበረ ነገር ተደርጎ ሊታይ አይችልም ሲል ይኸው መጽሐፍ አክሎ ገልጿል። ራስህን በበደለኝነት ስሜት ከማሰቃየት ይልቅ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በሚሉት የጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ቃላት ልትጽናና ትችላለህ። (መክብብ 9:​5) በሞት ያጣኸው የምትወደው ሰው እሳታማ ሲኦል ውስጥ ገብቶ እየተሠቃየ አይደለም። በተጨማሪም የራሱን ሕይወት ወደማጥፋት ደረጃ ያደረሰው የአእምሮም ሆነ የስሜት ሥቃይ አብቅቶለታል። ሥቃይ ላይ ሳይሆን ዕረፍት ላይ ነው ያለው።

      አሁን ራስህን ጨምሮ በሕይወት ስላሉት ሰዎች ደህንነት ማሰቡ የተሻለ ይሆናል። ሰሎሞን በመቀጠል በሕይወት ሳለህ “እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” ብሏል። (መክብብ 9:​10) የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች የወደፊት ተስፋ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ እጅ ያለ ጉዳይ መሆኑን አትጠራጠር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​3 a

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች የወደፊት ተስፋቸው ምን እንደሚመስል ሚዛናዊ አመለካከት ይኖርህ ዘንድ በመስከረም 8, 1990 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች ትንሣኤ ይኖራቸዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      [በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

      ችግርህን ለሌላ ሰው አዋየው

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ሕይወትህ በሌሎች ዘንድ ውድ ነው

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ