-
ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
-
-
ምዕራፍ 4
ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?
እውነት ወይስ ሐሰት?
መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።
□ እውነት
□ ሐሰት
አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።
□ እውነት
□ ሐሰት
መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።
□ እውነት
□ ሐሰት
ይህን ጉዳይ ብዙ ጊዜ አስበህበት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከአንዲት ወጣት ጋር እየተጠናናህ ከሆነ ፍቅራችሁን የምትገልጹበት መንገድ ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። እስቲ እውነት ወይም ሐሰት ብለህ እንድትመልስ ከላይ የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፤ ከዚያም “ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል እንዴት እንደሚረዳን እንመለከታለን።
● መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።
ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ባለውና ተገቢ በሆነ መልኩ ፍቅርን መግለጽን አይከለክልም። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ስለሚዋደዱ አንዲት ሱላማጢስ ወጣትና አንድ እረኛ የሚናገር ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ወጣቶች የሚጠናኑት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ነበር። ያም ሆኖ ከመጋባታቸው በፊትም ቢሆን በአንዳንድ መንገዶች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን ይገልጹ እንደነበር ከታሪኩ በግልጽ መመልከት ይቻላል። (ማሕልየ መሓልይ 1:2፤ 2:6፤ 8:5) በዛሬው ጊዜም ለመጋባት የወሰኑ አንድ ወንድና ሴት ንጹሕ በሆነ መንገድ ፍቅራቸውን መግለጻቸው ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል።a
ይሁንና የሚጠናኑ ሰዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መሳሳም፣ መተቃቀፍ ወይም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም ሊያመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንዲህ ያሉትን የፍቅር መግለጫዎች የሚያሳዩት በንጹሕ ልቦና ተነሳስተው ቢሆንም እንኳ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በቀላሉ የፆታ ብልግና ሊፈጽሙ ይችላሉ።—ቆላስይስ 3:5
● አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።
እውነት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒያ የተባለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። ይህ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ግንኙነትና የፆታ ብልቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል። በመሆኑም ዝሙት የሚለው ቃል የሚያመለክተው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን በአፍና በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸምና የሌላውን የፆታ ብልት እንደ ማሻሸት የመሳሰሉትን ድርጊቶች ጭምር ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ዝሙት መፈጸምን ብቻ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነሱም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ብልግና [ናቸው።] . . . እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—ገላትያ 5:19-21
“ርኩሰት” ምንድን ነው? “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በንግግርም ሆነ በድርጊት የጎደፉ መሆንን ያመለክታል። እጅን የሌላው ሰውነት ውስጥ ማስገባት፣ የሌላውን ልብስ ለማወላለቅ መሞከር ወይም ሊነኩ የማይገባቸውን የሰውነት ክፍሎች ለምሳሌ ጡትን መደባበስ ርኩስ ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጡትን መደባበስን የሚገልጸው በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ ከሚፈጸሙ ድርጊቶች እንደ አንዱ አድርጎ ነው።—ምሳሌ 5:18, 19
አንዳንድ ወጣቶች ያለምንም እፍረት የአምላክን መሥፈርቶች ይጥሳሉ። ሆን ብለው ገደቡን ያልፋሉ፤ አሊያም ስግብግብ በመሆን ካገኙት ሰው ሁሉ ጋር የፆታ ርኩሰት ለመፈጸም ይፈልጋሉ። እንደዚህ የሚያደርጉ ወጣቶች ሐዋርያው ጳውሎስ “ብልግና” ብሎ የጠራውን ድርጊት ፈጽመዋል ሊባል ይችላል። “ብልግና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘ጋጠወጥነት፣ ልቅነት፣ ስድነት፣ ገደብ የለሽ የፆታ ፍላጎት’ የሚል ፍቺ አለው። “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ለብልግና አሳልፈው ሰጥተዋል” እንደተባሉት ሰዎች መሆን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።—ኤፌሶን 4:17-19
● መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።
ሐሰት። አንዳንዶች ከሚያስቡት በተቃራኒ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ በመካከላቸው መከባበርና መተማመን እንዳይኖር ያደርጋሉ። ሎራ የገጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን እናቴ ባልነበረችበት ሰዓት የወንድ ጓደኛዬ ቴሌቪዥን ለማየት በሚል ሰበብ ቤታችን መጣ። መጀመሪያ ላይ እጄን ብቻ ነበር የያዘኝ። ይሁንና ሳላስበው ሰውነቴን ይደባብሰኝ ጀመር። እጁን እንዲሰበስብ ብነግረው ተበሳጭቶ ሊሄድ ይችላል ብዬ ስላሰብኩ ‘ተው’ እንዳልለው ፈራሁ።”
የሎራ የወንድ ጓደኛ ከልቡ የሚወዳት ይመስልሻል? ወይስ የሚፈልገው የራሱን ስሜት ለማርካት ብቻ ነበር? አንድ ሰው ርኩሰት እንድትፈጽሙ ሊያነሳሳሽ የሚሞክር ከሆነ ከልቡ ይወድሻል ማለት ይቻላል?
አንድ ወጣት፣ የሴት ጓደኛው ካገኘችው ክርስቲያናዊ ሥልጠና ጋር የሚጋጭና ሕሊናዋን የሚያቆሽሽ ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋት ከሆነ የአምላክን ሕግ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ለእሷ ያለው ፍቅር እውነተኛ መሆኑ አጠያያቂ እንዲሆን ያደርጋል። እንዲህ ያለው ድርጊት እንዲፈጸምባት የምትፈቅድ ወጣትም ብትሆን መጠቀሚያ እየሆነች ነው። ከዚህ የከፋው ደግሞ ርኩሰት መፈጸሟ ነው፤ አልፎ ተርፎም ዝሙት ልትፈጽም ትችላለች።b—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አብጁ
እየተጠናናችሁ ከሆነ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ከማሳየት መቆጠብ የምትችሉት እንዴት ነው? ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አስቀድሞ ማበጀት የጥበብ እርምጃ ነው። ምሳሌ 13:10 (NW) “እርስ በርስ በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ . . . ጥበብ አለ” ይላል። ተገቢ የሚባለው የፍቅር መግለጫ ምን ዓይነት እንደሆነ አስቀድማችሁ ተነጋገሩ። ስሜታችሁ ከተነሳሳ በኋላ ገደብ ለማበጀት መሞከር ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ድረስ እርምጃ ሳትወስዱ እንደመቆየት ይሆናል።
እርግጥ ነው፣ በተለይ መጠናናት እንደጀመራችሁ አካባቢ እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረግ ከባድ እንዲያውም የሚያሳፍር ሊሆንባችሁ ይችላል። ሆኖም አስቀድማችሁ ገደብ ማበጀታችሁ በኋላ ላይ ከባድ ችግር ውስጥ እንዳትገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ገደቦች ማበጀታችሁ እሳት ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ከማስወገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ እነዚህ ጉዳዮች መወያየት መቻላችሁ ግንኙነታችሁ የሚያዛልቅ መሆኑን ይጠቁማል። ደግሞም በጋብቻ ውስጥ በፆታ ግንኙነት ለመደሰት ራስን መግዛትንና ትዕግሥትን ማዳበር እንዲሁም ራስ ወዳድነትን ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:3, 4
ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ያም ቢሆን ይሖዋ በሚሰጥህ ምክር መተማመን ትችላለህ። በኢሳይያስ 48:17 ላይ ይሖዋ “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኝ ይመኝልሃል!
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት
አንዲት ወጣት ድንግልናዋን ጠብቃ ስለቆየች ችግር አለባት ማለት አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጓ የጥበብ አካሄድ ነው። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያልተጋቡ ወንድና ሴት በሰዎች ፊት ፍቅራቸውን መግለጻቸው ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከመሆኑም ሌላ እንደ ነውር ይቆጠራል። ክርስቲያኖች ሌሎችን የሚያሰናክል ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ አለባቸው።—2 ቆሮንቶስ 6:3
b በዚህ አንቀጽ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች እንደሚሠሩ ግልጽ ነው።
ቁልፍ ጥቅስ
“ፍቅር . . . ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5
ጠቃሚ ምክር
ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር ለመጠናናት ስትገናኙ ሌሎችም እንዲኖሩ አድርጉ፤ አሊያም ቢያንስ አንድ ሰው አብሯችሁ መሆን ይኖርበታል። ችግር ውስጥ እንድትገቡ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አስወግዱ፤ ለምሳሌ የቆመ መኪና ወይም ቤት ውስጥ ብቻችሁን አትሁኑ።
ይህን ታውቅ ነበር?
ተጫጭታችሁ ከሆነ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋችኋል። ይሁን እንጂ በስልክ ስታወሩም ሆነ የጽሑፍ መልእክት ስትላላኩ የፆታ ስሜትን ለመቀስቀስ የታሰቡ ቃላትን መጠቀም ርኩሰት ነው።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
የሥነ ምግባር ብልግና ወደ መፈጸም ሊመሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
የፍቅር ጓደኛዬ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንድንፈጽም ሊገፋፋኝ ቢሞክር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ በመካከላችሁ በሚኖረው አካላዊ ቅርበት ረገድ ምን ዓይነት ገደብ ታበጃላችሁ?
● በዝሙት፣ በርኩሰትና፣ በብልግና መካከል ያለውን ልዩነት አብራራ።
[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እኔና እጮኛዬ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ስለመቆየት የሚገልጹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አብረን አንብበናል። እነዚህ ጽሑፎች ንጹሕ ሕሊና እንድንይዝ እንደረዱን ይሰማናል።”—ለቲሺያ
[በገጽ 44 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ገደቡን አልፋችሁ ብትሄዱስ?
ተገቢ ያልሆነ ነገር ከፈጸማችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? ችግሩን በራሳችሁ እንደምታስተካክሉት በማሰብ ራሳችሁን አታታልሉ። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “‘ሁለተኛ እንዲህ እንዳናደርግ እርዳን’ ብዬ እጸልይ ነበር። ገደቡን ሳናልፍ በመመላለስ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ቢሳካልንም የተሳሳትንባቸው ወቅቶችም ነበሩ።” ስለዚህ ጉዳዩን ለወላጆቻችሁ መንገር ያስፈልጋችኋል። መጽሐፍ ቅዱስም ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድትጠሩ’ የሚያበረታታ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ያዕቆብ 5:14) እነዚህ ክርስቲያን እረኞች ከአምላክ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዳችሁ ምክር፣ ተግሣጽና ወቀሳ ይሰጧችኋል።
[በገጽ 47 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እርምጃ ለመውሰድ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ትጠብቃላችሁ? በፍቅር መግለጫዎች ረገድ ገደብ ለማበጀትም ስሜታችሁ እስኪነሳሳ መጠበቅ የለባችሁም
-
-
ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
-
-
ምዕራፍ 5
ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?
“ከየአቅጣጫው የሚመጣው ተጽዕኖ ‘የፆታ ግንኙነት ምን እንደሚመስል ሞክሬ ባየው’ ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል።”—ኬሊ
“የፆታ ግንኙነት ሳልፈጽም እስካሁን መቆየቴ ያሳፍረኛል።”—ጆርደን
“ዘንድሮም ድንግል ነሽ?”a እንዲህ ያለው ጥያቄ ሽምቅቅ እንድትዪ ያደርግሽ ይሆናል። በብዙ ቦታዎች አንዲት ወጣት ድንግል ከሆነች ችግር እንዳለባት ተደርጋ ትታያለች። ከዚህ አንጻር በርካታ ወጣቶች ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆኑ ምንም አያስገርምም!
ፍላጎታችሁና እኩዮቻችሁ የሚያሳድሩባችሁ ተጽዕኖ
ክርስቲያን ከሆንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት እንድትርቂ’ የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ታውቂያለሽ። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ያም ሆኖ የፆታ ስሜትሽን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንብሽ ይችላል። ፖል የተባለ ወጣት እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሐሳቦች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ሳልፈልግ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።” አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ስሜት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው።
ይሁንና ድንግል በመሆንሽ ጓደኞችሽ ነጋ ጠባ የሚያሾፉብሽና የሚነዘንዙሽ ከሆነ ሁኔታው ከባድ ነው። ለምሳሌ፣ አንድን ወጣት እኩዮቹ ‘የፆታ ግንኙነት የማትፈጽም ከሆነማ ወንድ ነኝ አትበል’ የሚሉት ቢሆንስ? አሊያም ደግሞ አንዲትን ወጣት ጓደኞቿ ‘የፆታ ግንኙነት ካልፈጸምሽ ምኑን ሴት ሆንሽው’ ቢሏትስ? ሔለን እንዲህ ብላለች፦ “እኩዮቻችሁ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስደስትና ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም ከዚያም ጋር ካልተኛችሁ ከሰው የተለያችሁ እንደሆናችሁ አድርገው ይቆጥሯችኋል።”
ይሁንና ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ እኩዮችሽ የሚደብቁሽ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸመች ማሪያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ድርጊቱን ከፈጸምኩ በኋላ በኀፍረትና በጥፋተኝነት ስሜት ተዋጥኩ። ራሴን ጠላሁት፤ የወንድ ጓደኛዬንም ጨርሶ ላየው አልፈለግኩም።” አብዛኞቹ ወጣቶች ባያውቁትም እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ብዙውን ጊዜ የስሜት ሥቃይ የሚያስከትል ከመሆኑም ሌላ አስከፊ መዘዞች አሉት!
ያም ሆኖ ሻንዳ የተባለች ወጣት “አምላክ በጋብቻ ውስጥ ካልሆነ በቀር የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሌለባቸው እያወቀ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለምን አደረገ?” የሚል ጥያቄ አንስታለች። ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፦
ከፆታ ፍላጎት ሌላ ኃይለኛ ስሜት አድሮብሽ አያውቅም? እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አምላክ የፈጠረሽ የተለያየ ዓይነት ፍላጎትና ስሜት እንዲኖርሽ አድርጎ ነው።
እንዲህ ያሉ ስሜቶች በውስጥሽ በተቀሰቀሱ ቁጥር ልታስተናግጃቸው ይገባል ማለት ነው? በፍጹም። ምክንያቱም አምላክ ሲፈጥርሽ ስሜትሽን የመቆጣጠር ችሎታም ሰጥቶሻል።
ታዲያ ነጥቡ ምንድን ነው? አንዳንድ ስሜቶች በውስጥሽ እንዳይቀሰቀሱ ማድረግ አትችዪ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህን ፍላጎቶችሽን ከመፈጸም ራስሽን መግታት ትችያለሽ። እውነቱን ለመናገር፣ የፆታ ስሜትሽ በተቀሰቀሰ ቁጥር ፍላጎትሽን ለማርካት መነሳት አንድ ሰው ባናደደሽ ቁጥር ከመማታት ባልተናነሰ ስህተትና ቂልነት ነው።
አምላክ የመራቢያ አካላችንን የሰጠን አላግባብ እንድንጠቀምበት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት [ሊያውቅ ይገባል]” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ “ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው” ይላል። በተመሳሳይም የፆታ ፍላጎትን ለማርካትም ሆነ ይህን ከማድረግ ለመቆጠብ ጊዜ አለው። (መክብብ 3:1-8) በዚያም ሆነ በዚህ ስሜትሽን መቆጣጠር የምትችይው አንቺ ነሽ!
ይሁን እንጂ አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ጊዜ መደናገጥ የለብሽም። ዓላማዋ በአንቺ ላይ ማሾፍ ከሆነ “አዎ፣ አሁንም ድንግል ነኝ። ደግሞም ድንግል በመሆኔ ቅንጣት ታክል አላፍርም!” ብለሽ ልትመልሺላት ትችያለሽ። አሊያም “ይህ የግል ጉዳዬ ስለሆነ አንቺን አይመለከትሽም” ማለት ትችያለሽ።b (ምሳሌ 26:4፤ ቆላስይስ 4:6) በሌላ በኩል ግን እንዲህ ላለችሽ ወጣት ስለ አቋምሽ የበለጠ ልታስረጃት እንደሚገባ ይሰማሽ ይሆናል። ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋምሽን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች ልትነግሪያት ትችያለሽ።
አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ሌላስ ምን ልትያት ትችያለሽ? መልስሽን ከታች አስፍሪው።
․․․․․
ውድ ስጦታ
ሰዎች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ አምላክ ምን ይሰማዋል? ለአንድ ጓደኛሽ ስጦታ ገዝተሻል እንበል። ይሁንና ጓደኛሽ ስጦታውን ገና ሳትሰጫት ለማየት ጓጉታ ብትከፍተው ምን ይሰማሻል? በሁኔታው አትበሳጪም? አንቺም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚ አምላክ ምን እንደሚሰማው ልትገምቺ ትችያለሽ። አምላክ ከሰጠሽ ስጦታ ማለትም ከፆታ ግንኙነት ደስታ ለማግኘት እስክታገቢ ድረስ እንድትቆዪ ይፈልጋል።—ዘፍጥረት 1:28
‘ታዲያ የፆታ ስሜቴ እንዳያስቸግረኝ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። በአጭር አነጋገር፣ ስሜትሽን መቆጣጠር መማር ይኖርብሻል። ደግሞም እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ብቃት አለሽ! ይሖዋ እንዲረዳሽ ጸልዪ። የአምላክ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ ይበልጥ እንድታዳብሪ ሊረዳሽ ይችላል። (ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ “በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” የሚለውን ጥቅስ አስታውሺ። (መዝሙር 84:11) ጎርደን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ማሰብ ከጀመርኩ እንዲህ ያለው ድርጊት በመንፈሳዊነቴ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት አሰላስላለሁ፤ ይህም ኃጢአት በመፈጸም የማገኘው ደስታ የፈለገ ቢሆን ከይሖዋ ጋር ካለኝ ዝምድና ሊበልጥብኝ እንደማይችል እንድገነዘብ ያደርገኛል።”
ድንግል መሆንሽ ችግር እንዳለብሽ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ክብርን ዝቅ የሚያደርገውና የሚያሳፍረው ብሎም ጎጂ የሚሆነው የፆታ ብልግና መፈጸም ነው። በመሆኑም ዓለም የሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖርሽ ስህተት እንደሆነ እንዲሰማሽ አያድርግሽ። ድንግልናሽን ጠብቀሽ መቆየትሽ ስሜታዊ ጉዳት እንዳይደርስብሽ የሚረዳሽ ከመሆኑም ሌላ ጤንነትሽን ለመጠበቅ ያስችልሻል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለሽ ዝምድና እንዳይበላሽ ይረዳሻል።
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
b ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሄሮድስ ጥያቄ ሲያቀርብለት ዝምታን እንደመረጠ መገለጹ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 23:8, 9) ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ብዙውን ጊዜ የተሻለው ነገር መልስ አለመስጠት ነው።
ቁልፍ ጥቅስ
“[አንድ ሰው] ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር በልቡ ከወሰነ . . . መልካም ያደርጋል።”—1 ቆሮንቶስ 7:37
ጠቃሚ ምክር
አንዳንድ ወጣቶች እንደ አንቺ ዓይነት እምነት እንዳላቸው ቢናገሩም እንኳ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ከሌላቸው ከእነሱ ጋር ጓደኝነት ላለመመሥረት ተጠንቀቂ።
ይህን ታውቅ ነበር?
ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ካገቡም በኋላ ይህ አመላቸው አይለቃቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ ከማግባታቸው በፊት ለአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ታማኝ የነበሩ ሰዎች ካገቡም በኋላ ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
እስከማገባ ድረስ ድንግልናዬን ጠብቄ ለመቆየት እንድችል እንዲህ ማድረግ ያስፈልገኛል፦ ․․․․․
ጓደኞቼ በአቋሜ እንዳልጸና የሚያስቸግሩኝ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● አንዳንዶች፣ ድንግል የሆኑ ወጣቶች ላይ የሚያሾፉባቸው ለምንድን ነው?
● ድንግልናን ጠብቆ መቆየት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
● እስኪያገቡ ድረስ ድንግል ሆኖ መቆየት ምን ጥቅሞች አሉት?
● ድንግልናን ጠብቆ መቆየት ያለውን ጥቅም ለታናናሾቻችሁ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 51 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ሴሰኛ ወይም ርኩስ የሆነ ማንኛውም ሰው በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ እንደሌለው’ ሁልጊዜ ማስታወሴ የፆታ ብልግና እንድፈጽም የሚያጋጥመኝን ፈተና ለመቋቋም አስችሎኛል።” (ኤፌሶን 5:5)—ሊዲያ
[በገጽ 49 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመልመጃ ሣጥን
በእርግጥ ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል?
አብዛኛውን ጊዜ እኩዮችሽም ሆኑ በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ አድበስብሰው ያልፉታል። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ሁኔታዎች እንመልከት። እነዚህ ወጣቶች በእርግጥ ምን ያጋጠማቸው ይመስልሻል?
● አብሮሽ የሚማር አንድ ወጣት ከበርካታ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንደፈጸመ በጉራ ይናገራል። ሁኔታው በጣም አስደሳች እንደሆነና ማናቸውም ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው ይገልጻል። ይሁንና እሱም ሆነ ሴቶቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ያጋጠማቸው ነገር በእርግጥ እንደጠበቁት የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․
● አንድ ፊልም እየተመለከትሽ ነው እንበል፤ ፊልሙ የሚደመደመው ሁለት የሚዋደዱ ወጣቶች ገና ሳይጋቡ የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ በማሳየት ነው። በገሃዱ ዓለም ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ ምን የሚያጋጥማቸው ይመስልሻል? ․․․․․
● አንድ ቆንጆ ወጣት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ጠየቀሽ። ድርጊቱን ብትፈጽሙ ማንም እንደማያውቅባችሁ ነግሮሻል። ከልጁ ጋር የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚና ሁኔታውን ለመደበቅ ብትሞክሪ ከዚያ በኋላ የሚያጋጥምሽ ነገር በእርግጥ እንደጠበቅሽው የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․
[በገጽ 54 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድ ስጦታ ሳይሰጥህ አስቀድመህ እንደመክፈት ነው
-