የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሐዘን የሚፈጥረው ሥቃይ
    ንቁ!—2018 | ቁጥር 3
    • ሐዘን የደረሰበት ሰው ምግብ ቤት ውስጥ ብቻውን ቁጭ ብሎ

      ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

      ሐዘን የሚፈጥረው ሥቃይ

      “ባለቤቴ ሶፊያa ለረጅም ጊዜ ታማ ከቆየች በኋላ በሞት አንቀላፋች፤ ከእሷ ጋር ከ39 የሚበልጡ ዓመታት በትዳር አሳልፈናል። ወዳጆቼ ከጎኔ ያልተለዩ ሲሆን እኔም ራሴን በሥራ ለማስጠመድ እጥር ነበር። ሆኖም እሷ ከሞተች በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል፣ ግማሽ አካሌ በድን እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ስሜቴ እየዋዠቀ ያስቸግረኝ ነበር። ሶፊያ ከሞተች ሦስት ዓመት ሊሞላት ነው፤ ያም ቢሆን አሁንም በሐዘን የምደቆስበት ጊዜ አለ። ደግሞም እንዲህ ያለው ስሜት የሚመጣብኝ በድንገት ነው።”—ኮስታስ

      አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ የኮስታስን ስሜት ትጋራ ይሆናል። የትዳር ጓደኛን፣ የቤተሰብ አባልን ወይም የወዳጅን ሞት ያህል ሥቃይ የሚያስከትል ወይም ልብ የሚሰብር ነገር የለም ማለት ይቻላል። ሐዘን ስለሚያስከትለው ሥቃይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች በዚህ ይስማማሉ። ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሳይካያትሪ የተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ፣ ብዙዎች በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች ዳግም እንደማያገኟቸው ስለሚያስቡ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚሰማቸው ገልጿል። እንደዚህ ዓይነት ከባድ መከራ የደረሰበት ሰው ‘እንዲህ የሚሰማኝ እስከ መቼ ነው? ከዚህ በኋላ እንደገና ደስታ ማግኘት እችል ይሆን? ሐዘኑ ቀለል እንዲልልኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብሎ ያስብ ይሆናል።

      ይህ የንቁ! እትም የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይዟል። ሐዘን ሊያስከትላቸው የሚችላቸው አንዳንድ ነገሮች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ተገልጸዋል። በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ ደግሞ ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዱ ነጥቦች ተብራርተዋል። አንተም የምትወደውን ሰው በቅርቡ በሞት አጥተህ ከሆነ እነዚህን ርዕሶች ማንበብህ ሊጠቅምህ ይችላል።

      በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ የቀረቡት ሐሳቦች መሪር ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች እንደሚያጽናኗቸውና እንደሚረዷቸው ተስፋ እናደርጋለን።

      a በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

  • ሐዘን ምን ሊያስከትል ይችላል?
    ንቁ!—2018 | ቁጥር 3
    • በሐዘን የተዋጡ ባልና ሚስት

      ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

      ሐዘን ምን ሊያስከትል ይችላል?

      አንዳንድ ባለሙያዎች ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች፣ ደረጃ በደረጃ የተለያዩ ስሜቶች እንደሚፈጠሩባቸው ይናገራሉ፤ ያም ቢሆን እያንዳንዱ ግለሰብ ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም። ታዲያ ሰዎች የሚያዝኑበት መንገድ የሚለያይ መሆኑ አንዳንዶች ጥልቅ ሐዘን እንዳልተሰማቸው ወይም ስሜታቸውን “እያፈኑት” እንደሆነ የሚጠቁም ነው? ላይሆን ይችላል። ሐዘን የደረሰበት ግለሰብ፣ የሚወደው ሰው መሞቱን አምኖ መቀበሉና ሐዘኑን መግለጹ ለመጽናናት ሊረዳው ቢችልም ሐዘን የሚገለጽበት “ትክክለኛ” መንገድ አንድ ብቻ ነው ማለት ግን አይደለም። የአንድ ሰው ባሕል፣ ተፈጥሯዊ ባሕርይ፣ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ነገሮች እንዲሁም የሚወደው ሰው የሞተበት መንገድ ሐዘኑን በሚገልጽበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

      ሐዘኑ ምን ያህል ሊከብድ ይችላል?

      ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች የሚወዱትን ሰው ማጣታቸው ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ግራ ይገባቸው ይሆናል። በእርግጥ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችና የሚፈጠሩባቸው ስሜቶች ተመሳሳይ ናቸው። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት፦

      ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት። ማልቀስ፣ ሟቹን መናፈቅና ድንገተኛ የሆነ የስሜት መለዋወጥ ሊያጋጥም ይችላል። በተጨማሪም ሐዘን የደረሰበት ሰው ከሟቹ ጋር የተያያዙ ትዝታዎች ፊቱ ላይ ድቅን እያሉ ያስቸግሩት አሊያም ስለ ሟቹ የሚያያቸው ሕልሞች ይረብሹት ይሆናል። እርግጥ አንድ ሰው፣ የሚወደው ግለሰብ መሞቱን ሲያውቅ መጀመሪያ ላይ በድንጋጤ ይዋጥ እንዲሁም ነገሩን ለማመን ይቸገር ይሆናል። ቲና የተባለች ሴት፣ ባሏ ቲሞ በድንገት ሲሞት የተፈጠረባትን ስሜት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ደነዘዝኩ። ማልቀስ እንኳ አልቻልኩም። አንዳንድ ጊዜ ሐዘኑ ከአቅሜ በላይ ሲሆንብኝ መተንፈስ እንኳ ያቅተኝ ነበር። ነገሩን ማመን በጣም ከብዶኝ ነበር።”

      ጭንቀት፣ ንዴትና የጥፋተኝነት ስሜትም የተለመደ ነው። አይቫን እንዲህ ብሏል፦ “ልጃችን ኤሪክ በ24 ዓመቱ ከሞተ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እኔና ባለቤቴ ዮላንዳ ብስጩ ሆነን ነበር! ቁጡ ሰዎች እንደሆንን ከዚያ በፊት አስበን ስለማናውቅ እንዲህ ያለ ባሕርይ ማሳየታችን አስገርሞናል። ‘ለልጃችን ሳናደርግ የቀረነው ነገር ይኖር ይሆን?’ የሚለው ሐሳብ ደግሞ በጥፋተኝነት ስሜት እንድንዋጥ አደረገን።” ባለቤቱ ለረጅም ጊዜ በሕመም ተሠቃይታ የሞተችበት አሌሃንድሮ የጥፋተኝነት ስሜት ይበጠብጠው ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ፣ ‘አምላክ ይህን ያህል እንድሠቃይ ከፈቀደ መጥፎ ሰው ነኝ ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ። ከዚያ ደግሞ ለደረሰው ነገር አምላክን ተወቃሽ እያደረግኩት እንደሆነ ስለተሰማኝ የጥፋተኝነት ስሜት አደረብኝ።” ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ኮስታስም እንዲህ ብሏል፦ “ሶፊያ በመሞቷ በእሷ ላይ የተናደድኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲህ በማሰቤ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። ሶፊያ፣ በመሞቷ ጨርሶ ተጠያቂ ልትሆን አትችልም።”

      በትክክል ለማሰብ መቸገር። የሐዘንተኛው አስተሳሰብ ግራ የሚያጋባ ወይም ከትክክለኛው ወጣ ያለ የሚሆንባቸው ጊዜያትም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዘንተኛው የሟቹን ድምፅ እንደሰማ ወይም ሟቹን እንዳየው አድርጎ ሊያስብ ይችላል፤ አሊያም ሟቹ አጠገቡ ያለ ያህል ሆኖ እንደሚሰማው ይናገር ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሐዘንተኛው ሐሳቡን ለመሰብሰብ ወይም ነገሮችን ለማስታወስ ሊቸገር ይችላል። ቲና እንዲህ ትላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር እየተጫወትኩ ቢሆንም ከቀልቤ ላልሆን እችላለሁ! አእምሮዬ የሚያውጠነጥነው ከቲሞ አሟሟት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ነው። በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አለመቻሌ በራሱ ጭንቀት ይፈጥርብኛል።”

      ራስን ማግለል። ሐዘን ላይ ያለ ሰው ከሌሎች ጋር ሲሆን ይነጫነጭ ይሆናል፤ አሊያም ከሰዎች ጋር መሆን ላይፈልግ ይችላል። ኮስታስ “ከባለትዳሮች ጋር ስሆን አለቦታዬ እንደገባሁ ይሰማኝ ነበር። ካላገቡ ሰዎች ጋር መሆንም ተመሳሳይ ስሜት ይፈጥርብኛል” ብሏል። የአይቫን ባለቤት ዮላንዳም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “እኛ ከደረሰብን ሐዘን ጋር ሲወዳደር ያን ያህል ከባድ በማይመስል ነገር ከሚያማርሩ ሰዎች ጋር መሆን በጣም አስቸጋሪ ነበር! አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ልጆቻቸው ስላገኙት ስኬት ይነግሩናል። ልጆቻቸው ስለተሳካላቸው ደስ ቢለኝም የሚነግሩኝን መስማቱ ግን ይረብሸኛል። እኔና ባለቤቴ ሕይወት እንደተለመደው እንደሚቀጥል ብናውቅም ከሌሎች ጋር እንዲህ ዓይነት ነገር ለማውራት ፍላጎቱም ሆነ ትዕግሥቱ አልነበረንም።”

      የጤና ችግሮች። ብዙዎች የምግብ ፍላጎታቸውና ክብደታቸው ይቀንሳል እንዲሁም እንቅልፋቸው ይዛባል። አሮን አባቱ ከሞተ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ያጋጠመውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ እንቅልፍ ስለማይወስደኝ በጣም እቸገር ነበር። ሁልጊዜ የተወሰነ ሰዓት ላይ የምነቃ ሲሆን ስለ አባቴ ሞት እያሰብኩ እቆዝም ነበር።”

      አሌሃንድሮ ደግሞ መንስኤው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሕመም ይሰማው እንደነበረ ያስታውሳል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ የተመረመርኩ ሲሆን ሐኪሙ ጤነኛ እንደሆንኩ አረጋግጦልኛል። ሕመም ይሰማኝ የነበረው በሐዘኑ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም።” ውሎ አድሮ የሕመሙ ምልክቶች እየጠፉ ሄዱ። ያም ቢሆን አሌሃንድሮ ሐኪም ቤት መሄዱ ጠቃሚ ነበር። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያዳክም፣ ቀድሞውንም የነበረ የጤና ችግርን ሊያባብስ አልፎ ተርፎም ሌላ ሕመም ሊያስከትል ይችላል።

      አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን መቸገር። አይቫን እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ኤሪክ መሞቱን ለዘመዶቻችንና ለወዳጆቻችን ብቻ ሳይሆን ለአሠሪውና ለቤት አከራዩ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች መናገር ነበረብን። ከሕግ ጋር የተያያዙ በርካታ ሰነዶችንም መሙላት ያስፈልገን ነበር። ከዚያም የኤሪክን የግል ንብረቶች ቦታ ቦታ ማስያዝ ነበረብን። ይህ ሁሉ ትኩረት የሚጠይቅ ሲሆን እኛ ደግሞ በዚያ ወቅት አእምሯችንም ሆነ አካላችን ዝሎና ስሜታችን ተደቁሶ ነበር።”

      አንዳንዶች ደግሞ የበለጠ ፈታኝ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው በኋላ ላይ ይኸውም ሟቹ ያከናውናቸው የነበሩትን ጉዳዮች ማከናወን በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ነው። ቲና ያጋጠማት ሁኔታ ይህ ነበር። እንዲህ ትላለች፦ “ከባንክ ጋር የተያያዙም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮቻችንን ምንጊዜም የሚከታተለው ቲሞ ነበር። አሁን ኃላፊነቱ ሁሉ እኔ ላይ ወደቀ፤ ይህም ይባስ እንድጨነቅ አደረገኝ። ‘ይህን ሁሉ ኃላፊነት በትክክል መወጣት እችላለሁ?’ የሚል ስጋት አደረብኝ።”

      ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ያጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ ሐዘን የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም በጣም ከባድ እንዲመስል ሊያደርጉ ይችላሉ። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከባድ ሐዘን እንደሚያስከትል የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን በቅርቡ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ይህን አስቀድመው ማወቃቸው ሐዘናቸውን ለመቋቋም ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ሁሉም ሰው ከሐዘን ጋር ተያይዘው የሚመጡት ችግሮች በሙሉ ይደርሱበታል ማለት እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። ከዚህም ሌላ በሐዘን የተደቆሱ ሰዎች፣ ሌሎችም የሚወዱትን ሰው ሲያጡ እንደ እነሱ ዓይነት ስሜት እንደተፈጠረባቸው ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል።

      እንደገና ደስታ ማግኘት እችል ይሆን?

      ምን መጠበቅ ትችላለህ? የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ግለሰብ መጀመሪያ ላይ የተሰማው መሪር ሐዘን እያደር እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው ከሐዘኑ ሙሉ በሙሉ ይጽናናል ወይም የሞተውን ሰው ይረሳዋል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ጊዜ ባለፈ መጠን ሐዘኑ እየቀለለው ይሄዳል። በእርግጥ አንዳንድ ትዝታዎች ወደ አእምሮው ሲመጡ አሊያም ደግሞ እንደ ሠርጋቸው ቀን ባሉት ጊዜያት ሐዘኑ ያገረሽበት ይሆናል። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ስሜታቸው ቀስ በቀስ እየተረጋጋ ስለሚሄድ እንደ ቀድሞው በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ይጠመዳሉ። በተለይ ደግሞ የሐዘንተኛው ቤተሰብ ወይም ጓደኞቹ ግለሰቡን የሚደግፉት ከሆነና እሱም አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎችን ከወሰደ ሐዘኑን መቋቋም ይችላል።

      ከሐዘን ለመጽናናት ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? አንዳንዶች ሐዘኑ በጣም የሚከብዳቸው ለተወሰኑ ወራት ሊሆን ይችላል። ሌሎች ብዙ ሰዎች ደግሞ ሐዘናቸው ቀለል እያለላቸው እንደሆነ የሚሰማቸው ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ግን ከዚህም የበለጠ ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል።a አሌሃንድሮ “ለሦስት ዓመት ያህል ሐዘኑ በጣም ከብዶኝ ነበር” ብሏል።

      ትዕግሥተኛ ሁን። ነገ የሚሆነውን እያሰብክ አትጨነቅ፤ ከሐዘንህ ለመጽናናት የሚወስድብህን ጊዜ ከሌሎች ጋር አታወዳድር፤ እንዲሁም መሪር ሐዘን በጊዜ ሂደት እየቀለለ እንደሚሄድ አስታውስ። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሐዘንህን ለማቅለል ብሎም ሳያስፈልግ እንዳይራዘም ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች ይኖራሉ?

      ብዙዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው መሪር ሐዘን ያስከትልባቸዋል

      a አንዳንዶች ሐዘናቸው በጣም ሊጸናባቸውና ከሐዘኑ መላቀቅ ሊቸግራቸው ይችላል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች የአእምሮ ጤና ባለሙያ እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

  • ሐዘንን መቋቋም—አሁን ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች
    ንቁ!—2018 | ቁጥር 3
    • በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ሰዎች በወላንዶ ሲጫወቱና ፎቶግራፍ ሲነሱ

      ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

      ሐዘንን መቋቋም—አሁን ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች

      ሐዘንን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ብዙ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የበለጠ ጠቃሚ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባትም ሐዘን በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ስሜት የተለያየ መሆኑ ለዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። አንድን ሰው ለመጽናናት የሚረዳው ሐሳብ፣ ለሌላው ብዙም አይጠቅመው ይሆናል።

      ያም ሆኖ ለብዙዎች ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ምክሮች አሉ። ሐዘንን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎች እነዚህን ሐሳቦች ብዙ ጊዜ ይጠቅሷቸዋል፤ ምክሮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ዘመን የማይሽራቸው መመሪያዎች ጋር የሚስማሙ ናቸው።

      1. ቤተሰብህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል

      • በባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ሰዎች በወላንዶ ሲጫወቱና ፎቶግራፍ ሲነሱ

        ሐዘንን ለመቋቋም ከሚረዱ በጣም ጠቃሚ ነገሮች ዋነኛው፣ ቤተሰብና ወዳጆች የሚያደርጉት ድጋፍ እንደሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ብቻህን መሆን ትፈልግ ይሆናል። እንዲያውም ሊረዱህ በሚፈልጉት ሰዎች ትበሳጭ ይሆናል። ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው።

      • ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር መሆን እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሊረዱህ የሚፈልጉ ሰዎችን አትግፋቸው። ወደፊት የእነሱ ድጋፍ የሚያስፈልግህ ጊዜ ይመጣ ይሆናል። አሁን የምትፈልገውና የማትፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በደግነት ንገራቸው።

      • እንደ አስፈላጊነቱ፣ ከሌሎች ጋር የምትሆንበትና ለብቻህ የምታሳልፈው ጊዜ ይኑርህ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ . . . አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና።”—መክብብ 4:9, 10

      2. ለአመጋገብህ ትኩረት ስጥ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴ አድርግ

      • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ከሐዘን ጋር ተያይዞ የሚመጣ ውጥረትን ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል። የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችንና ቅባት ያልበዛባቸው ምግቦችን ለመመገብ ጥረት አድርግ።

      • ውኃና ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች ፈሳሾችን በብዛት ጠጣ።

      • የምግብ ፍላጎትህ ከቀነሰ በትንሽ በትንሹ እያደረግክ ብዙ ጊዜ ለመብላት ሞክር። እንዲሁም እንደ ቫይታሚን ያሉ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እንዲያዙልህ ሐኪሞችን መጠየቅ ትችል ይሆናል።a

      • የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለምሳሌ ፈጠን ፈጠን ባለ እርምጃ መሄድ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች መካፈል አሉታዊ ስሜቶችን ሊቀንስ ይችላል። አንዳንዶች የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በሕይወታቸው ውስጥ ስላጋጠማቸው ለውጥ ለማሰላሰል ያስችላቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ስለ ሐዘኑ እንዳያስቡ ይረዳቸዋል።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል።”—ኤፌሶን 5:29 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

      3. በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር

      • አልጋ

        እንቅልፍ ምንጊዜም አስፈላጊ ቢሆንም በተለይ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች የበለጠ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘኑ ከወትሮው የተለየ ድካም እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

      • እንደ ቡናና ሻይ እንዲሁም አልኮል ያሉ መጠጦችን እንዳታበዛ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጥሩ እንቅልፍ እንዳትተኛ እንቅፋት ይሆናሉ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6

      4. አመለካከትህን እንደ ሁኔታው አስተካክል

      • ሐዘን የደረሰባት ሴት ስሜቷን ለወዳጇ ስትናገር

        እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ እንደሆነ አስታውስ። ሐዘንህ እንዲወጣልህ የሚረዳህ ምን እንደሆነ የምታውቀው አንተ ራስህ ነህ።

      • ብዙ ሰዎች ስሜታቸውን ለሌሎች መናገራቸው ሐዘናቸውን ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ሐዘናቸው አለማውራትን ይመርጣሉ። ስሜትን አውጥቶ መናገር ሐዘንን ለመቋቋም ጠቃሚ ስለመሆኑ ባለሙያዎች የተለያየ አስተያየት ይሰነዝራሉ። አንተም የልብህን አውጥተህ መናገር ብትፈልግም እያመነታህ ሊሆን ይችላል፤ ከሆነ ለቅርብ ወዳጅህ የተወሰኑ ነገሮችን ቀስ በቀስ መናገርህ ይጠቅምህ ይሆናል።

      • አንዳንድ ሰዎች ማልቀስ ሐዘናቸውን ለመቋቋም እንደረዳቸው ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ብዙ ባያለቅሱም ሐዘናቸውን መቋቋም የቻሉ ይመስላል።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል።”—ምሳሌ 14:10 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

      5. ከጎጂ ልማዶች ራቅ

      • የአልኮል መጠጥ የሚጠጣ ሰው

        ሐዘን የደረሰባቸው አንዳንድ ሰዎች አልኮል ከመጠን በላይ በመጠጣት ወይም ዕፅ በመውሰድ ስሜታዊ ሥቃያቸውን ለማስታገሥ ይሞክራሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው የሐዘን “ማስረሻ” ጎጂ ነው። ግለሰቡ በዚህ መንገድ የሚያገኘው እፎይታ ጊዜያዊ ከመሆኑም ሌላ ብዙ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል። ጭንቀትህን ለማረጋጋት፣ ጎጂ ያልሆኑ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሞክር።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”—2 ቆሮንቶስ 7:1

      6. ፋታ የምታገኝበት ጊዜ ይኑርህ

      • ብዙዎች፣ ሁልጊዜ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ሐዘናቸውን ለጊዜውም ቢሆን ለመርሳት በሚረዷቸው እንቅስቃሴዎች አልፎ አልፎ መካፈሉ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

      • አዳዲስ ወዳጆች ለማፍራት ወይም የነበረህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት ማድረግ፣ አዳዲስ ሙያዎችን መማር አሊያም ደግሞ መዝናናት ከሐዘንህ ጊዜያዊ ፋታ ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል።

      • በሐዘን የምትቆዝምበት ጊዜ ውሎ አድሮ እየቀነሰ ይሄዳል። ስለደረሰብህ ሐዘን ብቻ ከማሰብ ይልቅ በሌሎች እንቅስቃሴዎች የምትጠመድበት ጊዜ እያደር እየጨመረ እንደሄደ ታስተውል ይሆናል፤ ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለዋይታ ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1, 4

      7. ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ

      • አንዲት ሴት በቀን መቁጠሪያ ተጠቅማ ፕሮግራም ስታወጣ

        ከሐዘኑ በኋላ ብዙም ሳትቆይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህ መካፈልህን ቀጥል።

      • የምትተኛበት፣ ሥራህን የምታከናውንበት እንዲሁም ሌሎች እንቅስቃሴዎችህን የምትፈጽምበት ቋሚ ፕሮግራም መከተልህ ሕይወትህ እንዲረጋጋ ሊረዳህ ይችላል።

      • ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ራስህን ማስጠመድህ ሐዘኑ ያስከተለብህ ሥቃይ እንዲቀንስ ይረዳሃል።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛው አምላክ ልቡን ደስ በሚያሰኙ ነገሮች እንዲጠመድ ስለሚያደርገው [ሰው] የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኑን ፈጽሞ ልብ አይለውም።”—መክብብ 5:20

      8. ትላልቅ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ ተቆጠብ

      • የሚወዱት ሰው ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚያደርጉ ሰዎች ከጊዜ በኋላ በውሳኔያቸው ይቆጫሉ።

      • የሚቻል ከሆነ፣ ቤት ከመቀየርህ ወይም ሥራህን ከመለወጥህ አሊያም የሟቹን ንብረቶች ከማስወገድህ በፊት የተወሰነ ጊዜ ብትቆይ ጥሩ ነው።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤ ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።”—ምሳሌ 21:5

      9. ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች አድርግ

      • አንድ ሰው በሞት ያጣትን ሚስቱን ፎቶግራፍ ለጓደኞቹ ሲያሳያቸው

        የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ብዙዎች፣ ሟቹን የሚያስታውሷቸውን ነገሮች ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

      • ፎቶግራፎችን ወይም ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች መሰብሰብህ አሊያም ከሟቹ ጋር የተያያዙ ክንውኖችንና ታሪኮችን የምትመዘግብበት ማስታወሻ ደብተር ማዘጋጀትህ ሊያጽናናህ ይችላል።

      • አስደሳች ትዝታዎችን የሚቀሰቅሱ የሟቹን ንብረቶች አስቀምጥ፤ በኋላ ላይ ስሜትህ ሲረጋጋ እያወጣህ ልትመለከታቸው ትችላለህ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የጥንቱን ዘመን አስታውስ።”—ዘዳግም 32:7

      10. የሚያዝናናህ ነገር አድርግ

      • ለተወሰነ ጊዜ እረፍት ወስደህ ወጣ በል።

      • ረጅም እረፍት መውሰድ ካልቻልክ አንድ ወይም ሁለት ቀናት የሚያስደስትህን ነገር በማድረግ ማሳለፍ ትችል ይሆናል፤ ለምሳሌ ሽርሽር መሄድ፣ ሙዚየም መጎብኘት ወይም ተራራ መውጣት ትችላለህ።

      • ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከተለመደው እንቅስቃሴህ ለየት ያለ ነገር ማድረግህ ሐዘንህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።”—ማርቆስ 6:31

      11. ሌሎችን እርዳ

      • አንዲት ወጣት፣ በዕድሜ የገፋችን ሴት ገበያ ላይ ስታግዛት

        ሌሎችን የሚጠቅም ነገር በማድረግ የምታሳልፈው ጊዜ አንተም ሐዘንህ ቀለል እንዲልልህ ሊረዳህ እንደሚችል አስታውስ።

      • አንተ በሞት ያጣኸውን ሰው በማጣታቸው በሐዘን የተዋጡ ቤተሰቦችህን ወይም ጓደኞችህን ማጽናናት ትችላለህ፤ እነዚህ ሰዎች ሐዘናቸውን የሚጋራቸውና ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ሰው ይፈልጋሉ።

      • ሌሎችን መርዳትና ማጽናናት ደስታ የሚያስገኝልህ ከመሆኑም ሌላ ትርጉም ያለው ነገር ማከናወን በመቻልህ እርካታ ታገኛለህ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

      12. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች ገምግም

      • ሐዘን፣ በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ እንድታስተውል ሊያደርግህ ይችላል።

      • በሕይወትህ ምን እያደረግክበት እንደሆነ ለመገምገም ይህን አጋጣሚ ተጠቀምበት።

      • ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ሞት ነውና፤ በሕይወት ያለ ሰውም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።”—መክብብ 7:2

      ሐዘንን መቋቋም | ዋና ዋና ነጥቦች

      • 1. ቤተሰብህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል

        እንደ አስፈላጊነቱ፣ ከሌሎች ጋር የምትሆንበትና ለብቻህ የምታሳልፈው ጊዜ ይኑርህ።

      • 2. ለአመጋገብህ ትኩረት ስጥ፤ እንዲሁም እንቅስቃሴ አድርግ

        ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ተመገብ፤ ውኃ በብዛት ጠጣ እንዲሁም መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ።

      • 3. በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክር

        ሐዘን የሚያስከትለውን ከፍተኛ ድካም ለመቋቋም እንቅልፍ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስታውስ።

      • 4. አመለካከትህን እንደ ሁኔታው አስተካክል

        እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ ነው፤ ሐዘንህ እንዲወጣልህ የሚረዳህን ነገር ለማወቅ ጥረት አድርግ።

      • 5. ከጎጂ ልማዶች ራቅ

        አልኮል ከመጠን በላይ ከመጠጣት ወይም ዕፆችን ከመውሰድ ተቆጠብ፤ እነዚህ ነገሮች የባሰ ችግር ይፈጥራሉ።

      • 6. ፋታ የምታገኝበት ጊዜ ይኑርህ

        ሁልጊዜ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ከሌሎች ጋር በመሆን ወይም በመዝናኛ የምታሳልፈው ጊዜ እንዲኖር አድርግ።

      • 7. ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ

        የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህን የምታከናውንበት ቋሚ ፕሮግራም ማውጣትህ ሕይወትህ እንዲረጋጋ ይረዳሃል።

      • 8. ትላልቅ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ ተቆጠብ

        የሚቻል ከሆነ፣ ከሐዘኑ በኋላ ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ትላልቅ ውሳኔዎችን አታድርግ፤ ይህም በኋላ ላይ ልትቆጭበት የምትችል ውሳኔ ከማድረግ ይጠብቅሃል።

      • 9. ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች አድርግ

        ፎቶግራፎችን ወይም ሟቹን የሚያስታውሱህን ነገሮች ሰብስብ፤ አሊያም ከሟቹ ጋር የተያያዙ ነገሮችን የምትመዘግብበት ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅ።

      • 10. የሚያዝናናህ ነገር አድርግ

        ለአንድ ቀን ወይም ለተወሰኑ ሰዓታትም እንኳ ቢሆን ከተለመደው እንቅስቃሴ ወጣ ያለ ነገር ለማከናወን ጊዜ መድብ።

      • 11. ሌሎችን እርዳ

        አንተ በሞት ያጣኸውን ሰው በማጣታቸው በሐዘን የተዋጡ ሌሎች ሰዎችን በማጽናናት፣ ትርጉም ያለው ነገር ማከናወን የሚያስገኘውን ደስታ አጣጥም።

      • 12. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች ገምግም

        ይህን አጋጣሚ፣ በሕይወት ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ቆም ብለህ ለማሰብ ተጠቀምበት። እንዲሁም ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ረገድ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግ።

      ሐዘንህን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድ ነገር እንደሌለ አይካድም። ይሁን እንጂ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ብዙ ሰዎች፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተጠቀሱት ያሉ ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ለመጽናናት እንደረዳቸው ይናገራሉ። እርግጥ ነው፣ ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዱ ሐሳቦች በሙሉ እዚህ ላይ ቀርበዋል ማለት አይደለም። ሆኖም ከእነዚህ ጠቃሚ ሐሳቦች መካከል አንዳንዶቹን ተግባራዊ ብታደርግ በተወሰነ መጠን መጽናናት ትችላለህ።

      a ንቁ! አንድን የሕክምና ዘዴ ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።

  • ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን የላቀ ማጽናኛ
    ንቁ!—2018 | ቁጥር 3
    • በገነት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሞት የተለዩአቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች በደስታ ሲቀበሉ

      ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

      ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን የላቀ ማጽናኛ

      የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ስለሚያስከትለው ሐዘን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰፊ ጥናት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የተሻለ የሚባለው የባለሙያዎች ምክር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ጠቃሚ ሐሳብ ጋር ብዙውን ጊዜ ይስማማል። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ዘመን የማይሽረው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው፣ እምነት የሚጣልበት ምክር ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የትም ቦታ የማይገኙና ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች የላቀ ማጽናኛ የሚሰጡ ሐሳቦችን ይዟል።

      • በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች እየተሠቃዩ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ

        መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 9:5 ላይ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም ‘ሐሳባቸው ሁሉ ይጠፋል’ ይላል። (መዝሙር 146:4) ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ሰላማዊ ከሆነ እንቅልፍ ጋር ያመሳስለዋል።—ዮሐንስ 11:11

      • አፍቃሪ በሆነ አምላክ ማመን የሚያስገኘው ማጽናኛ

        መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 34:15 ላይ “የይሖዋa ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማሉ” በማለት ይናገራል። ስሜታችንን አውጥተን በጸሎት ለአምላክ መግለጻችን ሥቃያችንን ከማስታገስ ወይም ሐሳባችንን ከማረጋጋት የበለጠ ጥቅም አለው። ጸሎት፣ እኛን ለማጽናናት ኃይሉን መጠቀም ከሚችለው ፈጣሪያችን ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት ይረዳናል።

      • ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚመጣ የሚገልጽ ተስፋ

        በመቃብር ያሉ ሁሉ ወደፊት ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚመጣ በተደጋጋሚ ይናገራል። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” ይላል።—ራእይ 21:3, 4

      በይሖዋ አምላክ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች፣ በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች እንደገና እንደሚያዩአቸው የሚገልጸውን ተስፋ በማመናቸው ሐዘናቸውን መቋቋም ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለ65 ዓመታት አብሯት የኖረውን የትዳር ጓደኛዋን በሞት ያጣችው አን እንዲህ ትላለች፦ “የምንወዳቸው ሰዎች ቢሞቱም እየተሠቃዩ እንዳልሆነና አምላክ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉትን ሙታን በሙሉ እንደሚያስነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል። ባሌን በሞት እንዳጣሁ በማስብበት ጊዜ፣ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ወደ አእምሮዬ ስለሚመጡ የደረሰብኝን ከሁሉ የከፋ ሐዘን መቋቋም ችያለሁ!”

      በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቲና እንዲህ ትላለች፦ “ቲሞ ከሞተበት ቀን ጀምሮ የአምላክ ድጋፍ አልተለየኝም። በሐዘኔ ወቅት ይሖዋ በእጅጉ እንደረዳኝ ይሰማኛል። ደግሞም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የትንሣኤ ተስፋ እውን ሆኖ ይታየኛል። የትንሣኤ ተስፋ፣ ቲሞን እንደገና እስካገኘው ድረስ በጽናት ለመቀጠል ብርታት ይሰጠኛል።”

      እነዚህ አስተያየቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ተስፋ እንደያዘ አጥብቀው የሚያምኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስሜት የሚያስተጋቡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር እውን ሊሆን እንደማይችል ወይም ምኞት ብቻ እንደሆነ ቢሰማህ እንኳ ምክሮቹና ተስፋዎቹ አስተማማኝ እንደሆኑ የሚያሳየውን ማስረጃ መመርመርህ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ስታደርግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን የላቀ ማጽናኛ እንደሚሰጥ መገንዘብ ትችላለህ።

      ሙታን ስላላቸው ተስፋ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ከዚህ ርዕስ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ቪዲዮዎች jw.org/am ላይ ተመልከት

      በገነት ውስጥ ያሉ ሰዎች በሞት የተለዩአቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች በደስታ ሲቀበሉ

      መጽሐፍ ቅዱስ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና የምናገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል

      ስንሞት ምን እንሆናለን?

      ስንሞት ምን እንሆናለን?

      ስንሞት ምን እንሆንለን? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ግልጽ መልስ በጣም የሚያጽናና ነው

      ላይብረሪ >ቪድዮዎች በሚለው ሥር ተመልከት (ቪዲዮው መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ሥር ይገኛል።)

      ምሥራች መስማት ትፈልጋለህ?

      ምሥራች መስማት ትፈልጋለህ?

      መጥፎ ዜናዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ውስጥ ምሥራች ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

      የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች >ሰላም እና ደስታ በሚለው ሥር ተመልከት

      a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ