-
ሃይማኖታዊ ነፃነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?መጠበቂያ ግንብ—1997 | የካቲት 1
-
-
ትስስር ይመሰርቱና የሌላ እምነት ተከታዮችን ለፖለቲካዊ ሥልጣናቸው እንደሚያሰጉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሃይማኖቶች ከፖለቲካዊ መንግሥት ይልቅ ለአምላክ ታማኝ መሆንን ሊያስበልጡ ስለሚችሉ አንድ መንግሥት አንድን ሃይማኖት ለፖለቲካ አደገኛ እንደሆነ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል።”
ከዚህ የተነሳ አንዳንድ መንግሥታት በሃይማኖት ላይ እገዳዎችን ይጥላሉ። ጥቂት መንግሥታት ደግሞ ማንኛውንም እምነት ማራመድን እስከ ጭራሹ ይከለክላሉ። ሌሎች ደግሞ የአምልኮ ነፃነትን እንደሚደግፉ ይናገሩ እንጂ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በጥብቅ ይቆጣጠራሉ።
ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮ ለብዙ ዓመታት ሰፍኖ የቆየውን ሁኔታ ተመልከት። ሕገ መንግሥቱ ምንም እንኳ የሃይማኖት ነፃነት ቢሰጥም የሚከተለውን ገደብ አስቀምጧል:- “ለአምልኮ የሚያገለግሉ አብያተ ክርስቲያናት በፌደራላዊ አስተዳደር የተወከለው መንግሥት ንብረቶች ናቸው፤ የትኛው በአገልግሎቱ መቀጠል እንደሚችልና እንደማይችል የሚወስነው ፌደራላዊው መንግሥት ነው።” ይህን እገዳ ለማንሳት በ1991 በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። የሆነ ሆኖ ይህ ምሳሌ የሃይማኖት ነፃነት በተለያዩ አገሮች የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ያሳያል።
ሌላ ዓይነት ሃይማኖታዊ ነፃነት
አንተ በምትኖርበት አገር የሃይማኖት ነፃነት አለን? ካለ በምን መልክ ተቀምጧል? አምላክን በመረጥከው መንገድ ማምለክ ትችላለህ ወይስ የመንግሥትን ሃይማኖት እንድትከተል ትገደዳለህ? ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ማንበብም ሆነ ማሰራጨት ተፈቅዶልሃል ወይስ እንደዚህ ዓይነት ጽሑፎች ፈጽሞ በመንግሥት የታገዱ ናቸው? ስለ እምነትህ ለሌሎች መናገር ትችላለህ ወይስ ይህ ድርጊት የሌሎችን ሃይማኖታዊ መብት እንደመጋፋት ይቆጠራል?
ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ እንደየምትኖርበት አገር ይለያያል። ደስ የሚለው ግን የምትኖርበት አካባቢ የማይወስነው ሃይማኖታዊ ነፃነት አለ። ኢየሱስ በ32 እዘአ በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ለተከታዮቹ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ትሆናላችሁ፤ እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏቸው ነበር።— ዮሐንስ 8:31, 32 የ1980 ትርጉም
ኢየሱስ ይህን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? አይሁዳውያን አድማጮቹ ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ የሚወጡበትን ጊዜ ይናፍቁ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከፖለቲካዊ ጭቆና ነፃ ስለመውጣት እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቀጥሎ በሚቀርበው ርዕስ እንደምንመለከተው ለደቀ መዛሙርቱ ከዚህ በጣም የተሻለ ነገር ቃል እየገባላቸው ነበር።
-
-
እውነት የሚያስገኘው ነፃነትመጠበቂያ ግንብ—1997 | የካቲት 1
-
-
እውነት የሚያስገኘው ነፃነት
ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉት ሞት የተፈረደባቸው ናቸው። እስቲ ራስህን በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። እንዴት ይሰማሃል? እርግጥ እንዲህ ስላለው ሁኔታ ማሰብ አያስደስትም። በሌላ በኩል ግን ጠቅላላው የሰው ዘር ያለበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) አዎን፣ የአዳም ዘሮች እንደመሆናችን መጠን የኃጢአት “እስረኞች” ነን። (ሮሜ 5:12) “ከአእምሮዬ ሕግ ጋር እየተቃረነ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ለሚሠራው የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ” ሲል የጻፈው ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተሰማው ሁሉ እኛም ያለንበት የእስር ሁኔታ ያስከተለው ውጤት በየዕለቱ ይሰማናል።— ሮሜ 7:23 የ1980 ትርጉም
መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ስለሚል በሌላ አባባል ካለንበት የኃጢአተኝነት ሁኔታ የተነሳ የሞት ፍርድ የተፈረደብን ያህል ነን። (ሮሜ 6:23) መዝሙራዊው ሙሴ ያለንበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ሲል በሚገባ ገልጾታል:- “ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ እርሱም በመከራና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።”— መዝሙር 90:10 የ1980 ትርጉም፤ ከያዕቆብ 4:14 ጋር አወዳድር።
ኢየሱስ “እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ሲል ለተከታዮቹ የተናገረው የሰው ዘር የኃጢአትና የሞት ባሪያ መሆኑን በአእምሮው ይዞ ነበር። (ዮሐንስ 8:32 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ይህን ሲናገር በተከታዮቹ ፊት ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ከመውጣት የሚበልጥ ሌላ ተስፋ ማለትም ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የመሆን አጋጣሚ ከፊታቸው እንደተዘረጋላቸው መግለጹ ነው! ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው? ኢየሱስ “ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ” ሲል ነገራቸው። (ዮሐንስ 8:36 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ አዳም ያጠፋውን መልሶ ለመግዛት “ወልድ” ሕይወቱን ቤዛዊ የሥርየት መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። (1 ዮሐንስ 4:10) ይህም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ የሚወጡበትን መንገድ ከፍቷል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” የአምላክ አንድያ ልጅ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል።— ዮሐንስ 3:16
ስለዚህ ነፃ ሊያወጣን የሚችለው እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚያተኩር ነው። የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ጊዜ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የመውጣት ተስፋ አላቸው። የአምላክ ቃል የሚናገረውን እውነት የሚቀበሉ ሰዎች ሌላው ቀርቶ አሁን እንኳን እውነተኛ ነፃነት ያገኛሉ። በምን መንገድ?
ሙታንን ከመፍራት ነፃ መሆን
በዛሬው ጊዜ ሙታንን የሚፈሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ለምን? ምክንያቱም ሃይማኖታቸው በሞት ጊዜ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ወደ መንፈሳዊ ዓለም ትሄዳለች ብሎ ስላስተማራቸው ነው። ከዚህ የተነሳ በአንዳንድ አገሮች የሟች ዘመዶች ለበርካታ ሌሊትና ቀን አስከሬኑን የመጠበቅ ልማድ አላቸው። ይህም ብዙውን ጊዜ ጮክ ብሎ መዘመርና ከበሮ መምታት ይጨምራል። የሟቹ ዘመዶች እንዲህ ማድረጉ የሞተውን ሰው ከማስደሰቱም በላይ መንፈሱ ተመልሶ መጥቶ በሕይወት የሚኖሩትን ሰዎች እንዳያሠቃይ ይከላከላል ብለው ያምናሉ። ሕዝበ ክርስትና ስለ ሙታን የምታስተምረው የሐሰት ትምህርት እንዲህ ያለው አጉል ልማድ እንዲቀጥል ከማድረግ በስተቀር ሌላ የፈየደው ነገር የለም።
ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ሐቁን ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። ነፍስህ ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል አንዲት ረቂቅ ነገር ሳትሆን አንተ ራስህ ነፍስ መሆንህን በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 እትም፤ ሕዝቅኤል 18:4) ከዚህም በተጨማሪ ሙታን በእሳታማ ሲኦል ውስጥ እየተሠቃዩ ወይም በሕያዋን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ በሚችሉበት መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ እየኖሩ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም” ይላል።— መክብብ 9:5, 10
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ብዙ ሰዎች ሙታንን ከመፍራት ነፃ እንዲወጡ አድርገዋቸዋል። የሞቱትን ዘመዶቻቸውን ለመለማመን ሲሉ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መሥዋዕቶችን ከማቅረብም ሆነ በሠሩት ስሕተት ምክንያት በጭካኔ እየተሠቃዩ ይሆናል ብሎ ከመጨነቅ ተገላግለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ስላላቸው ግሩም ተስፋ ምን እንደሚል ያውቃሉ፤ አምላክ በቀጠረው ጊዜ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን” እንደሚነሱ ይናገራል። (ሥራ 24:15፤ ዮሐንስ 5:28, 29) በመሆኑም ሙታን በጥሩ እንቅልፍ ላይ እንደሚገኝ ሰው እረፍት ላይ ናቸው።— ከዮሐንስ 11:11-14 ጋር አወዳድር።
ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገረው እውነት ሞት ከሚያስከትለው ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነፃ ሊያወጣን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት የአራት ዓመት ልጃቸውን በድንገተኛ አደጋ ባጡበት ወቅት ይህ ዓይነቱ ተስፋ ሐዘናቸውን እንዲቋቋሙት ረድቷቸዋል። “በትንሣኤ አማካኝነት ልጃችንን እንደገና እስክናየው ድረስ ሊጠፋ የማይችል መጥፎ ስሜት በውስጣችን አለ” በማለት እናቲቱ የሚሰማትን ሳትሸሽግ ተናግራለች። “ሆኖም ይሖዋ የሐዘን እንባችንን እንደሚጠርግ ቃል ስለገባልን በሐዘን የምንሠቃየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን።”— ራእይ 21:3, 4
የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራት ነፃ መሆን
ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን? ምድራችን በኑክሌር ቦምብ ትጋይ ይሆን? የምድር አካባቢ እየተበከለ መሄዱ ፕላኔታችን ወደፊት ሕይወት አልባ እንድትሆን ያደርጋት ይሆን? የሥነ ምግባር መውደቅ ወደ ሥርዓት አልበኝነትና ግራ መጋባት ይመራ ይሆን? ዛሬ ብዙዎችን ሰዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ የጣሏቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከእንዲህ ዓይነቱ ከፍተኛ ስጋት ነፃ ያደርጋል። ‘ምድር ለዘላለም እንደምትኖር’ ዋስትና ይሰጠናል። (መክብብ 1:4) ይሖዋ የምንኖርባትን ፕላኔት የፈጠራት ምንም ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ስትጠፋ ዝም ብሎ ለመመልከት አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ምድርን የፈጠራት አንድነት ላለው ሰብዓዊ ቤተሰብ ገነታዊ መኖሪያ እንድትሆን ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ዓላማው አሁንም ቢሆን አልተለወጠም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ምድርን የሚያጠፉትን” እንደሚያጠፋ ይነግረናል። (ራእይ 11:18) ከዚያም ‘ገሮች ምድርን እንደሚወርሱና በብዙም ሰላም ደስ እንደሚላቸው’ ይገልጻል።— መዝሙር 37:11
አምላክ ስለማይዋሽ ይህ ተስፋ የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካኝነት “ከአፌ የሚወጣው ቃሌ . . . የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ሲል ገልጿል። (ኢሳይያስ 55:11፤ ቲቶ 1:2) ስለዚህ በ2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ የሚገኘው “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በትምክኽት መጠባበቅ እንችላለን።
ሰውን ከመፍራት ነፃ መሆን
መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ በደፋርነታቸው በአርዓያነት የሚጠቀሱ ወንዶችንና ሴቶችን ታሪክ ይዟል። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ጌዴዎን፣ ባርቅ፣ ዲቦራ፣ ዳንኤል፣ አስቴር፣ ኤርምያስ፣ አቢጋኤልና ኢያኤል ይገኙበታል። እነዚህ የታመኑ ወንዶችና ሴቶች “በእግዚአብሔር ታመንሁ፣ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” ሲል የጻፈው መዝሙራዊ ያለውን ዝንባሌ አንጸባርቀዋል።— መዝሙር 56:11
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስም ሃይማኖታዊ ባለሥልጣኖች እንዳይሰብኩ ባዘዟቸው ጊዜ ተመሳሳይ ቆራጥነት አሳይተዋል። “እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” የሚል መልስ ሰጥተዋል። ጴጥሮስና ዮሐንስ በወሰዱት የጸና አቋም የተነሳ ከጊዜ በኋላ ታስረዋል። በተአምር ከእስር ሲለቀቁ በቀጥታ የስብከት ሥራቸውን ተያያዙት፤ “የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሃት በድፍረት” መናገራቸውን ቀጠሉ። ወዲያው ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት በአይሁድ የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት እንዲቀርቡ ተደረገ። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል” ሲል ተናገራቸው። ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ደግሞ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ መለሱ።— ሥራ 4:16, 17, 19, 20, 31 የ1980 ትርጉም፤ 5:18-20, 27-29
ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያሳዩትን ቅንዓት ለመኮረጅ ይጥራሉ። በመካከላቸው ያሉ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ ስለ እምነታቸው ለሌሎች በመናገር በኩል ደፋሮች መሆናቸውን እያስመሰከሩ ነው። ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት።
ስታሲ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ በተፈጥሮዋ ዓይን አፋር የሆነች ወጣት ናት። ከዚህ የተነሳ በመጀመሪያ አካባቢ ስለ እምነቷ ለሌሎች መናገር ትልቅ ፈተና ሆኖባት ነበር። ዓይን አፋርነቷን ለማሸነፍ ምን አደረገች? “መጽሐፍ ቅዱስን አጠናሁ፤ ለሌሎች ስለምን እንደምናገር በሚገባ ተረዳሁ። ይህም ለሌሎች መናገር ቀላል እንዲሆንልኝና ይበልጥ በራሴ እንድተማመን አደረገኝ” ትላለች። ስታሲ ያተረፈችው መልካም ስም በአካባቢው በሚታተም ጋዜጣ ላይ ሊወጣ በቅቷል። አንዲት የትምህርት ቤቷ መምህር ያዘጋጀችው መጣጥፍ የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል:- “የስታሲ እምነት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች የሚሰሟቸውን የተለያዩ ግፊቶች ለመዋጋት የሚያስችል ጥንካሬ ሳይሰጣት አልቀረም። . . . ለአምላክ የሚቀርበው አገልግሎት በአእምሮዋ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መያዝ እንዳለበት ይሰማታል።”
ቶሚ በወላጆቹ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው የአምስት ዓመት ልጅ ገደማ ሳለ ነበር። ገና በልጅነቱ ሳይቀር ለእውነተኛው አምልኮ ድፍረት የተሞላበት አቋም ወስዷል። የክፍሉ ተማሪዎች የተለያዩ በዓላትን የሚያንጸባርቁ ሥዕሎችን ሲሥሉ ቶሚ ደግሞ አምላክ ቃል የገባውን ገነት የሚያሳዩ ሥዕሎችን ሣለ። ቶሚ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ አብዛኞቹ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት በተመለከተ ግራ እንደሚጋቡ ተገነዘበ። ተማሪዎቹን ፈርቶ አፉን ዘግቶ ቁጭ ከማለት ይልቅ ለጥያቄዎቻቸው ሁሉ በአንድ ላይ መልስ ለመስጠት ከክፍሉ ተማሪዎች ጋር በጥያቄና መልስ ውይይት ማድረግ ይችል ዘንድ ከአስተማሪዎቹ አንዱን ቀርቦ ፈቃድ ጠየቀ። ቶሚ ተፈቀደለትና ግሩም ምስክርነት መስጠት ቻለ።
ማርኪታ የ17 ዓመት ወጣት ሳለች በክፍሏ ውስጥ ላሉ ተማሪዎች ስለ እምነቷ ለመናገር የሚያስችላት አንድ ግሩም አጋጣሚ አገኘች። “ንግግር ተዘጋጅተን በክፍል ውስጥ እንድናቀርብ ተነገረን። ንግግር የማቀርብበትን ርዕስ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ከተባለው መጽሐፍ መረጥኩ።a አምስት ምዕራፎችን ከመረጥኩ በኋላ ርዕሳቸውን ጥቁር ሰሌዳው ላይ ጻፍኩ። ከዚያም የክፍሉ ተማሪዎች ይበልጥ አስፈላጊ ነው ብለው የሚያስቡትን ርዕስ እንዲመርጡ አደረኩ” ትላለች። የክፍሉ ተማሪዎች የተሳተፉበት ውይይት ተደረገ። ማርኪታ “ለክፍሉ ተማሪዎች መጽሐፉን አሳየኋቸውና በርካታ ተማሪዎች መጽሐፉን እንዳመጣላቸው ጠየቁ። ሌላው ቀርቶ አስተማሪዬም ጭምር መጽሐፉን እንደምትፈልግ ነገረችኝ” በማለት ታጠቃልላለች።
እውነት ነፃ ሊያወጣህ ይችላል
ከላይ እንዳየነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት እስካጠኑትና መልእክቱን ከልብ እስከተቀበሉ ድረስ በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ነፃ ሊያወጣ ይችላል። ሙታንን ከመፍራት፣ የወደፊቱን ጊዜ ከመፍራትና ሰውን ከመፍራት ነፃ ያወጣቸዋል። በመጨረሻ ደግሞ የኢየሱስ ቤዛ ታዛዥ የሆኑ የሰው ዘሮችን በሙሉ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ያወጣቸዋል። ከወረስነው የኃጢአተኝነት እስር ተላቅቆ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!— መዝሙር 37:29
አምላክ ቃል ስለገባልን በረከቶች ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህን? የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቃል የገባላቸውን ነፃነት ማግኘት ከፈለግህ ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ማወቅ አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ስለሚል የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅና ፈቃዱን ማድረግ ይኖርብሃል።— 1 ዮሐንስ 2:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ የሰው ዘር በመጨረሻ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ይወጣል
-