የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 2/1 ገጽ 24-28
  • ሙዚቃ በዘመናዊ አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሙዚቃ በዘመናዊ አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሙዚቃ በአምልኮ ውስጥ ይዞት የቆየው ታሪካዊ ቦታ
  • መዝሙር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ የነበረው ቦታ
  • የሐሰት አምልኮ ያሳደረው ተጽእኖ
  • ሙዚቃን በአምልኮ ውስጥ ወደ ትክክለኛው ቦታ መመለስ
  • ‘በልባችን ለይሖዋ መዘመር’
  • ለይሖዋ ዘምሩ
  • በደስታ ዘምሩ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ለይሖዋ ዘምሩ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሙዚቃ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 2/1 ገጽ 24-28

ሙዚቃ በዘመናዊ አምልኮ ውስጥ ያለው ቦታ

መዝሙር የመዘመር ችሎታችን ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። ድምፃችንን አውጥተን መዘመራችን ለእኛም ሆነ ለፈጣሪያችን ደስታ ሊያስገኝ ይችላል። በመዝሙር አማካኝነት የሐዘንም ሆነ የደስታ ስሜታችንን ልንገልጽ እንችላለን። ከዚያም አልፎ የዜማ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ ያለንን ፍቅር፣ አምልኮታዊ ክብርና ውዳሴ ልንገልጽበት እንችላለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙዚቃን አስመልክቶ ሦስት መቶ ጊዜ ያህል የተጠቀሰ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የተጠቀሰው ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ነው። መዘመር ከደስታም ጋር ዝምድና አለው፤ የሚዘምሩት ሰዎች ከሚያገኙት ደስታ ጋር ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ከሚሰማው ደስታ ጋርም የተያያዘ ነው። መዝሙራዊው “ይዘምሩለት። እግዚአብሔር በሕዝቡ ተደስቶአልና” ሲል ጽፏል።​— መዝሙር 149:​3, 4

ይሁን እንጂ በዘመናዊው አምልኮ ውስጥ መዝሙር ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ዛሬ የይሖዋ ሕዝቦች ድምፃቸውን አውጥተው በመዘመር ይሖዋን ሊያስደስቱት የሚችሉት እንዴት ነው? ሙዚቃ በእውነተኛ አምልኮ ውስጥ ምን ቦታ ሊይዝ ይገባል? ሙዚቃ በአምልኮ ውስጥ የነበረውን ቦታ ከታሪክ ማኅደር መመርመሩ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳል።

ሙዚቃ በአምልኮ ውስጥ ይዞት የቆየው ታሪካዊ ቦታ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በቀጥታ ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ አይደለም። በዘፍጥረት 4:​21 ላይ ዩባል የመጀመሪያዎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች በመፈልሰፍ ወይም ደግሞ አንድ ዓይነት የሙዚቃ ሙያ በመፍጠር የመጀመሪያው ሰው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ይሁን እንጂ ሙዚቃ የሰው ልጆች ከመፈጠራቸው በፊት እንኳ ሳይቀር የይሖዋ አምልኮ ክፍል ነበር። በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መላእክት እንደዘመሩ ይገልጻሉ። ኢዮብ 38:​7 መላእክት በደስታ ‘እንደዘመሩና እልል እንዳሉ’ ይናገራል። ስለዚህ መዝሙር በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ሰው ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት የነበረ ነገር እንደሆነ ለማመን የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለ።

አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የጥንቱ የዕብራውያን ዝማሬ አጃቢ ሙዚቃ የሌለው ዜማ ነበር ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ በምናገኘው በገና በተባለው መሣሪያ በአንድ ጊዜ ከአንድ ኖታ በላይ መደርደር ይቻላል። በገናውን የሚጫወቱት ሰዎች የተለያዩ ቃናዎችን በማቀናጀት መሣሪያው ሊያወጣው የሚችለውን ኅብረ ድምፅ አስተውለው መሆን አለበት። ሙዚቃቸው ኋላ ቀር ሳይሆን የመጠቀ እንደነበረ አያጠራጥርም። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ግጥምና ስድ ንባብ በመመልከት የእስራኤላውያን ሙዚቃ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ እንደነበረ ማስተዋል እንችላለን። በእርግጥም ሙዚቃን ለመድረስ የሚያነሳሳቸው ነገር በጎረቤት አገሮች የነበሩትን ሰዎች ለዚህ ዓላማ ከሚያነሳሳቸው ነገር የተለየና ክቡር ነበር።

የጥንቱ ቤተ መቅደስ አደረጃጀት በቤተ መቅደሱ በሚካሄደው የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ውስብስብ የሆነ የሙዚቃ ቅንብርና መዝሙር እንዲፈጠር አድርጓል። (2 ዜና መዋዕል 29:​27, 28) “መሪዎች፣” ‘አስተማሪዎች፣’ ‘ተማሪዎች’ እና “የመዘምራን አለቆች” ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 15:​21 NW፤ 25:​7, 8፤ ነህምያ 12:​46) የታሪክ ምሁር የሆኑት ኩርት ሳክስ የእነሱን የተራቀቀ የሙዚቃ ችሎታ አስመልክተው የሚከተለውን አስተያየት ጽፈዋል:- “በኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ የነበሩት የመዝሙርና የሙዚቃ ጓዶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የሙዚቃ ትምህርት፣ ችሎታና እውቀት ዳብሮ እንደነበረ ያመለክታሉ። . . . በጥንት ዘመን የነበረው ሙዚቃ ምን ዓይነት ቃና እንደነበረው ባናውቅም ኃይል ያለው፣ ክብራማና እጅግ የተዋጣለት እንደነበረ የሚጠቁም በቂ ማስረጃ አለን።” (በጥንቱ ዓለም የነበረው የሙዚቃ ዕድገት:- ምሥራቅና ምዕራብ [The Rise of Music in the Ancient World: East and West] 1943 ገጽ 48, 101-2) የሰሎሞን መዝሙር የዕብራይስጥ የሙዚቃ ድርሰቶች ላይ የተንጸባረቀውን የፈጠራ ችሎታና ምጥቀት የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ከኦፔራ ጽሑፍ ጋር የሚመሳሰል በመዝሙር የተገለጸ ታሪክ ነው። መዝሙሩ በዕብራይስጥ ጽሑፍ ውስጥ “መኃልየ መኃልይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ከመዝሙሮች ሁሉ የላቀ መዝሙር ማለት ነው። ለጥንቶቹ ዕብራውያን መዝሙር የአምልኮ ሥርዓታቸው አንዱ አካል ነበር። ለይሖዋ በሚያቀርቡት ውዳሴ ገንቢ የሆነ ስሜት ለመግለጽ አስችሏቸዋል።

መዝሙር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ የነበረው ቦታ

ሙዚቃ በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ቋሚ የሆነ የአምልኮ ክፍል ሆኖ ቀጥሎ ነበር። በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት መዝሙሮች ሌላ ለአምልኮ ሥርዓት የሚያገለግሉ አዲስ ሙዚቃና ግጥሞች ሳያቀናብሩ አይቀርም፤ ይህም በዘመናችን ክርስቲያናዊ መዝሙሮችን ለማቀነባበር በዋቢነት አገልግሏል። (ኤፌሶን 5:​19) በዎልዶ ሴልደን ፕራት የተዘጋጀው የሙዚቃ ታሪክ (The History of Music) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የጥንት ክርስቲያኖች በሕዝብ ፊትና በግል በሚካሄድ የአምልኮ ሥርዓት የመዘመር ልማድ ነበራቸው። ወደ ክርስትና የተለወጡ አይሁዶች ይህ በምኩራብም ያከናውኑት የነበረው ዓይነት ልማድ ነው። . . . አዲሱ እምነት . . . ከዕብራይስጥ መዝሙራት ሌላ በየጊዜው አዳዲስ መዝሙሮች ያወጣ ነበር፤ መጀመሪያ ላይ መዝሙሮቹ ይዘጋጁ የነበሩት አንድ ወጥ ባልሆኑና ከፍተኛ የደስታ ስሜት በሚገለጽባቸው ራፕሶዲ በሚባሉ የግጥም ዓይነቶች መልክ የነበረ ይመስላል።”a

ኢየሱስ የጌታ ራትን ሲያቋቁም እሱና ሐዋርያቱ የሐሌል መዝሙሮችን ሳይዘምሩ አይቀርም። ይህም የመዝሙርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ማቴዎስ 26:​26-30) እነዚህ መዝሙሮች የማለፍ በዓል ሲከበር የሚዘመሩና በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ይሖዋን የሚያወድሱ መዝሙሮች ናቸው።​— መዝሙር 113-118

የሐሰት አምልኮ ያሳደረው ተጽእኖ

የጨለማው ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት ላይ ሃይማኖታዊ ሙዚቃ ወደ ሐዘን እንጉርጉሮነት ተለወጠ። በ200 እዘአ ገደማ የእስክንድሪያው ክሌመንት “እኛ የሚያስፈልገን አንድ መሣሪያ ነው፤ እሱም በገና ወይም ታምቡር ወይም ዋሽንት ወይም ደግሞ መለከት ሳይሆን ምንም የማይረብሸውና አምልኮታዊ አክብሮት የሚገለጽበት የሰው ድምፅ ነው” ብሏል። ዕገዳዎች በመጣላቸው የቤተ ክርስቲያን ሙዚቃ በድምፅ የተወሰነ ሆነ። ይህ የሙዚቃ ስልት እንጉርጉሮ ወይም በድምፅ ብቻ የሚዜም መዝሙር ይባላል። የሙዚቃ ቅርሳችን (Our Musical Heritage) የተባለው መጽሐፍ “ቁስጠንጢንያ በተገነባች አርባ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሎዶቅያ ጉባኤ (367 ዓ. ም.) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጠቀምንም ሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መሰብሰብን የሚያግድ ደንብ ደነገገ። የቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ሙዚቃ በድምፅ ብቻ የሚዜም ሆኖ ቆይቷል” በማለት ይገልጻል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እነዚህ እገዳዎች በጥንቱ ክርስትና ያልነበሩ ነገሮች ናቸው።

በጨለማው ዘመን ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አያውቀውም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ የደፈሩ ክርስቲያኖች ይሰደዱ ነበር፤ አልፎ ተርፎም ይገደሉ ነበር። እንግዲያው በዚያ የጨለማ ዘመን አምላክን በመዝሙር የማወደስ ልማድ በእጅጉ ጠፍቶ የነበረ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። ተራው ሕዝብ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማግኘት ካልቻለ አንድ አሥረኛ የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መዝሙር መሆኑን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? አምላክ “ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ መንፈሳውያን ሰዎች በጉባኤ አመስግኑት” ብሎ አምላኪዎቹን እንዳዘዘ ማን ይነግራቸዋል?​— መዝሙር 149:​1 የ1980 ትርጉም

ሙዚቃን በአምልኮ ውስጥ ወደ ትክክለኛው ቦታ መመለስ

የይሖዋ ድርጅት ሙዚቃንና መዝሙርን በአምልኮ ውስጥ ወደ ትክክለኛው ቦታ ለመመለስ ብዙ ጥረት አድርጓል። ለምሳሌ ያህል የየካቲት 1, 1896 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እትም መዝሙሮችን ብቻ ይዞ ወጥቶ ነበር። “የመጀመሪያዎቹ የጽዮን የደስታ መዝሙሮች” የሚል ርዕስ ተሰጥቷቸው ነበር።

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመዘመሩ ልማድ በ1938 በአብዛኛው ቀርቶ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያዊውን ምሳሌና መመሪያ መከተሉ ጠቃሚ እንደሆነ ታመነበት። በ1944 በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ፍሬድሪክ ዊልያም ፍራንዝ “የመንግሥት አገልግሎት መዝሙር” የሚል ንግግር አቀረበ። የሰው ልጅ ከመፈጠሩ ከብዙ ጊዜ በፊት የአምላክ ሰማያዊ ፍጥረታት ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር እንደዘመሩ ከገለጸ በኋላ “የአምላክ ምድራዊ አገልጋዮች ድምፃቸውን አውጥተው መዘመራቸው ተገቢና አምላክን የሚያስደስት ነው” ሲል ተናገረ። መዝሙርን ለአምልኮ የመጠቀምን አስፈላጊነት የሚያሳዩ አሳማኝ ሐሳቦችን ካቀረበ በኋላ በሳምንታዊ የአገልግሎት ስብሰባዎች ላይ ለመዘመር የሚያገለግል የመንግሥት አገልግሎት መዝሙር መጽሐፍ መውጣቱን አስታወቀ።b ከዚያም የታኅሣሥ 1944 ኢንፎርማንት (አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን የሚባለው) ሌሎቹም ስብሰባዎች የመክፈቻና የመደምደሚያ መዝሙሮች እንደሚኖራቸው አስታወቀ። መዝሙር እንደገና የይሖዋ አምልኮ ክፍል ሆነ።

‘በልባችን ለይሖዋ መዘመር’

ከልብ በመነጨ ስሜት የመዘመር ጥቅም ለብዙ ዓመታት መከራና ስደት በደረሰባቸው በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ በሚኖሩ ወንድሞቻችን ላይ ታይቷል። ሎታር ዋግነር ለሰባት ዓመታት ብቻውን ታስሮ ነበር። ጸንቶ ሊቆም የቻለው እንዴት ነው? “ለበርካታ ሳምንታት የማስታውሳቸውን የመንግሥት መዝሙሮች ሳሰባስብ ቆየሁ። ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ ማስታወስ ሳልችል ስቀር የራሴን አንድ ሁለት ስንኞች አዘጋጅ ነበር። . . . የመንግሥት መዝሙሮቻችን ብዙ የሚያበረታቱና የሚያንጹ ሐሳቦችን የያዙ ናቸው!”​— የ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 226-8

ሃሮልድ ኪንግ በያዘው የታማኝነት አቋም ምክንያት ብቻውን ታስሮ ባሳለፋቸው አምስት ዓመታት ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙሮችን በማዘጋጀትና በመዘመር መጽናኛ ሊያገኝ ችሏል። በአሁኑ ጊዜ እሱ ያቀናበራቸውን በርካታ መዝሙሮች የይሖዋ ምሥክሮች በአምልኮ ሥርዓታቸው ይጠቀሙባቸዋል። በመዘመር የሚገኘው ደስታ ብርታት ይሰጣል። ሆኖም ለአምላክ የውዳሴ መዝሙሮችን መዘመር የሚያስገኘውን ጥቅም አምነን ለመቀበል የግድ ስደትን መቅመስ አያስፈልገንም።

የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ በመዝሙር ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ምንም እንኳ ስሜታችንን በንግግር እንዳንገልጽ የተፈጥሮ ፍርሃትና ዓይናፋርነት ሊያግዱን ቢችሉም ለይሖዋ ያለንን ስሜት በመዝሙር እንደ ልባችን መግለጽ እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” ብሎ ክርስቲያኖችን በመከረ ጊዜ የውዳሴ መዝሙሮችን በመዘመር እንዴት ደስታ ልናገኝ እንደምንችል አመልክቷል። (ኤፌሶን 5:​19) ልባችን በመንፈሳዊ ነገሮች ሲሞላ ስሜታችንን በሚገባ በመዝሙር መግለጽ እንችላለን። ስለዚህ በተሻለ ሁኔታ ለመዘመር ቁልፉ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ነው።

ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ካለን ደስተኛ መንፈስ እንዲኖረን በማድረግ ስለ ይሖዋ እንድንናገር፣ እንድንዘምርና እንድናወድሰው ይገፋፋናል። (መዝሙር 146:​2, 5) ስላገኘናቸው አስደሳች ነገሮች ከልብ እንዘምራለን። መዝሙሩን ወይም የመዝሙሩን ሐሳብ ከወደድነው ከልብ በመነጨ ስሜት መዘመራችን አይቀርም።

አንድ ሰው በስሜት ለመዘመር የግድ ጮክ ብሎ መዘመር አያስፈልገውም። ጮክ ብለን ስለዘመርን ብቻ መዝሙሩ ጥሩ ይሆናል ማለት አይደለም፤ ድምፃችን የማይሰማ ከሆነም መዝሙሩ ጥሩ ሊሆን አይችልም። በተፈጥሮአቸው የሚያስተጋቡ አንዳንድ ድምፆች ዝግ ባለ ድምፅ በሚዘመርበት ጊዜም እንኳ ለየት ብለው ሊሰሙ ይችላሉ። በርከት ካሉ ሰዎች ጋር በጥሩ ሁኔታ መዘመርን ፈታኝ ከሚያደርጉት ሁኔታዎች አንዱ ድምፅን አጣጥሞ አንድ ላይ መዘመር የመቻሉ ጉዳይ ነው። ሐርሞኒ በሚባለው የአዘማመር ስልትም ሆነ በኅብረት አንድ ዓይነት ድምፅ በማሰማት በሚዘመርበት ጊዜ የድምፅህ መጠን አጠገብህ ሆነው ከሚዘምሩት ሰዎች ድምፅ ጋር የሚመጣጠን ከሆነ መዝሙሩ ጣዕምና አንድነት ያለው ይሆናል። አንድ ሰው ከሌላው ልቆ ለመታየት ያለመፈለግን ክርስቲያናዊ ባሕርይ የሚያሳይ ከሆነና አዳማጭ ጆሮ ካለው የሌሎችን ድምፅ ሳይውጥ በጋለ መንፈስ መዘመር ይችላል። ይሁን እንጂ ጥሩ የመዘመር ችሎታ ያዳበሩ ወይም ደግሞ ጥሩ ድምፅ ያላቸው ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዳይዘምሩ ሊከለከሉ አይገባም። ጥሩ ጣዕም ያለው ድምፅ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ለሚዘምር ጉባኤ ጠንካራ ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል።

በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ መዘመር ሐርሞኒ የሚባሉትን የዜማዎችን አጃቢ ክፍሎች ለመዘመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ኖታዎችን ሳይጠቀሙ ሐርሞኒውን መዘመር የሚችሉ ወይም ደግሞ በመዝሙር መጽሐፉ ላይ ያሉትን የሐርሞኒውን ምልክቶች እያዩ መዘመር የሚችሉ ሰዎች ድምፃቸውን ከመዝሙሩ ጋር አጣጥመው በመዘመር ለሙዚቃው ጣዕም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እናበረታታቸዋለን።c

አንዳንዶች ‘ዜማውን በትክክል ማዜም አልችልም’ ወይም ደግሞ ‘መጥፎ ድምፅ ነው ያለኝ፤ የመዝሙሩ ድምፅ ከፍ ብሎ በቀጭኑ በሚወጣበት ጊዜ ድምፄ ስልል ይላል’ ይሉ ይሆናል። ስለዚህ በመንግሥት አዳራሽ እንኳ ለመዘመር ይፈራሉ። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ለይሖዋ ውዳሴ የሚዘምር ማንኛውም ሰው ድምፁ በይሖዋ ፊት “መጥፎ” አይደለም። አንድ ሰው ልምምድ በማድረግና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚሰጡትን ጠቃሚ ሐሳቦች በሥራ በማዋል ለንግግር የሚጠቀምበትን ድምፅ ማሻሻል እንደሚችል ሁሉ የአዘማመር ችሎታንም እንደዚሁ ማሻሻል ይቻላል። አንዳንዶች ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ ከንፈራቸውን ገጥመው በማዜም ድምፃቸውን ማሻሻል ችለዋል። ከንፈርን ገጥሞ ማዜም የድምፅን ቃና ለማስተካከል ይረዳል። ብቻችንን በምንሆንባቸው ወይም ሌሎችን በማንረብሽባቸው ቦታዎች በምንሠራባቸው አመቺ ጊዜያት የመንግሥቱን ጣዕመ ዜማዎች መዘመር ድምፅን ለማለማመድ የሚያስችል ግሩም መንገድ ከመሆኑም በላይ አንድን ሰው እንዲደሰትና አእምሮው ዘና እንዲል ያደርገዋል።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች በርከት ብለን በምንሰባሰብበት ጊዜም ጥቂት የመንግሥቱን መዝሙሮች ልንዘምር እንችላለን። በጊታር ወይም በፒያኖ ወይም ደግሞ ማኅበሩ ባዘጋጃቸው የፒያኖ ቅጂዎች በመታገዝ በምንዘምርበት ጊዜ በዝግጅቱ ላይ መንፈሳዊ አየር እንዲሰፍን ያደርጋል። በተጨማሪም መዝሙሮቹን ለመማርና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በጥሩ ሁኔታ ለመዘመር ይረዳል።

ጉባኤዎች በጋለ ስሜት እንዲዘምሩ ለማገዝ ማኅበሩ በሙዚቃ የሚያጅቡ ካሴቶችን አዘጋጅቷል። ካሴቶቹ በሚጫወቱበት ጊዜ በድምፅ ክፍል የሚሠራው ወንድም የድምፁን መጠን በንቃት መከታተል አለበት። ሙዚቃው በደንብ የማይሰማ ከሆነ ጉባኤው ድምፁን ከፍ አድርጎ ለመዘመር ሊፈራ ይችላል። የድምፅ ክፍሉን የሚቆጣጠረው ወንድም ከጉባኤው ጋር አንድ ላይ በሚዘምርበት ጊዜ ሙዚቃው ጥሩ እገዛ እየሰጠ መሆን አለመሆኑን መገንዘብ ይችላል።

ለይሖዋ ዘምሩ

መዝሙር ለፈጣሪያችን ያለንን ስሜት መግለጽ የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። (መዝሙር 149:​1, 3) እንዲሁ በስሜት ግንፋሎት የሚደረግ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜታችንን በመቆጣጠር፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድና በደስታ ስሜት ምስጋናችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። በጉባኤ ስብሰባ ከልባችን መዘመራችን አእምሯችንና ልባችን ለቀጣዩ ፕሮግራም ዝግጁ እንዲሆን ያደርግልናል፤ በይሖዋ አምልኮም ይበልጥ እንድንካፈል ሊያነሳሳን ይችላል። መዝሙር የሚያመጣው ለውጥ በስሜት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ቃላቱም ትምህርት ሊሰጡን ይችላሉ። ስለዚህ በኅብረት አንድ ዓይነት ኖታ በመዘመርም ሆነ ሐርሞኒ በሚባለው የአዘማመር ስልት በመጠቀም ስሜታችንን በመግለጽ አንድ ላይ ተሰብስበን መማር እንድንችል በቅንነትና በትሕትና ልባችንን እናዘጋጃለን።​— ከመዝሙር 10:​17 ጋር አወዳድር።

መዝሙር ምንጊዜም የይሖዋ አምልኮ ክፍል እንደሆነ ይኖራል። እንግዲያው “በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ” ሲል መዝሙራዊው የገለጸው ዓይነት ስሜት ይዘን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን።​— መዝሙር 146:​2

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ራፕሶዲ ተብሎ የሚጠራው ከፍተኛ የደስታ ስሜት የሚገለጽበት የግጥም ዓይነት በተለያዩ ክፍሎቹ ላይ የነፃነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት የሙዚቃ አካል ነው። እንዲህ ዓይነቱ ግጥም ብዙውን ጊዜ የጀግንነት ድርጊቶችን ወይም ሰዎችን ያወድሳል።

b መዝሙር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ ጎልቶ የሚታይ ቋሚ የአምልኮ ሥርዓት ገጽታ እንደነበር አንደኛ ቆሮንቶስ 14:​15 የሚጠቁም ይመስላል።

c ሐርሞኒውን መዘመር ለሚፈልጉ ሰዎች ጥቅም ሲባል በአሁኑ ጊዜ በምንጠቀምበት ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ያሉት አንዳንድ መዝሙሮች አራቱንም የሐርሞኒ ዓይነቶች የያዙ ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ መዝሙሮች በፒያኖ ለመጫወት እንዲመቹ ሆነው የተዘጋጁ ከመሆናቸውም በላይ ዜማዎቹ ዓለም አቀፋዊ መሠረታቸውን እንዳይለቁ ሲባል አንድ ወጥ በሆነ መንገድ የተዘጋጁ ናቸው። አራቱን የሐርሞኒ ዓይነቶች በጥብቅ ባልተከተለ መንገድ የተጻፉትን መዝሙሮች በስብሰባዎች ላይ ስንዘምር የሐርሞኒ ኖታዎችን እየጨመርን መዘመራችን መዝሙሮቹ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በተሻለ መንገድ ለመዘመር የሚያስችሉ አንዳንድ ሐሳቦች

1. በምትዘምርበት ጊዜ የመዝሙር መጽሐፉን ወደ ላይ ከፍ አድርገህ ያዝ። ይህ አንድ ሰው ይበልጥ በትክክል መተንፈስ እንዲችል ይረዳዋል።

2. በእያንዳንዱ ሐረግ መጀመሪያ ላይ በደንብ አድርገህ አየር ሳብ።

3. ከወትሮው የበለጠ አፍን ከፈት ማድረግ የድምፅን መጠንና ጥራት ይጨምረዋል።

4. ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚዘመረው መዝሙር በሚያስተላልፈው ሐሳብ ላይ ትኩረት አድርግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ