ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር በተስፋ መኖር
የሚከተሉት ነገሮች በአንተ ላይ ቢደርሱ ኖሮ ምን እንደሚሰማህ አስብ:- ንብረትህ በሙሉ ሙልጭ ብሎ ጠፍቶ ባዶ እጅህን ቀርተሃል። ለሕይወትህ የደስታ ምንጭ የሆኑት ልጆችህ አልቀዋል። ባለቤትህ ምንም የሞራል ድጋፍ አትሰጥህም። ጤንነትህ በእጅጉ ተቃውሷል። እያንዳንዱ ቀን በመከራ የተሞላ ነው።
እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ በሕይወት ለመኖር ትመኛለህ? ወይስ ጨርሶ ተስፋ ትቆርጣለህ?
ከላይ የተገለጸው አሳዛኝ መከራ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በኖረው በኢዮብ ሕይወት ውስጥ የተፈጸመ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮ ነው። (ኢዮብ ምዕራፍ 1, 2) ኢዮብ በጭንቀት ተውጦ በነበረበት ጊዜ “ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት” ሲል በምሬት ተናግሯል። ሞቶ ቢገላገል ደስ ባለው ነበር። (ኢዮብ 10:1፤ 14:13) ይሁን እንጂ ኢዮብ ከባድ ስቃይ ቢደርስበትም ለአምላክ ያለውን ጽኑ አቋም አላላላም። በዚህ ምክንያት ይሖዋ “ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን” ባርኮለታል። ስለዚህም “ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ” በሰላም ሞተ።— ኢዮብ 42:12, 17
ኢዮብ እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው የጽናት ምሳሌ ትቷል። የደረሰበት መከራ የተሻለ ባሕርይ እንዲያፈራ የረዳው ከመሆኑም በላይ ሌሎችንም ለመልካም ሥራ አነሳስቷል። (ያዕቆብ 5:10, 11) ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ ኢዮብ ያሳየው እንከን የለሽ የአቋም ጽናት የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል። (ምሳሌ 27:11) ይህ አሳዛኝ ገጠመኝ የኋላ ኋላ አምላካዊ አክብሮት፣ እምነትና የአቋም ጽናት ያስገኘለት ሲሆን እነዚህ ባሕርያት ለኢዮብም ሆነ የእርሱን ምሳሌ ለሚከተሉ ሰዎች ሁሉ በረከት አምጥተውላቸዋል።
የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩም ተስፋ አትቁረጥ
ኢዮብ የደረሱበት ዓይነት ፈተናዎች ሊደርሱብህ ይችላሉ። የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ ምክንያት ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ደርሶብህ ይሆናል። ከባድ ሕመም ሕይወትን እንድትጠላ አድርጎህ ይሆናል። ወይም ትዳርህ በሚያሳዝን መንገድ በመፍረሱ መላው ሕይወትህ ጭልም ብሎብህ ይሆናል። የኢኮኖሚ መሰናክሎች ባዶ እጅህን አስቀርተውህ ይሆናል። እውነተኛውን አምልኮ የሚጠሉ ተቃዋሚዎች የመረረ ስደት ያደርሱብህ ይሆናል። የደረሱብህን ፈተናዎች ለማሸነፍ የምታደርገው ትግል ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተስፋ ቢስነት ስሜት እንዲያድርብህ አድርጎህ ይሆናል።— 1 ጴጥሮስ 1:6
ጨርሰህ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ‘ስቃይ የሚደርስብኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ስቃይ የሚደርስብህ ‘በክፉው በሰይጣን ዲያብሎስ መዳፍ በተያዘው’ ዓለም ውስጥ ስለምትኖር ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ከዚህ የተነሣ ሁሉም ሰው ስቃይ ይደርስበታል። ዲያብሎስ በመንግሥቱ መልእክት ላይ የሚያስፋፋው ጥላቻ፣ ሌሎች የሚናገሯቸው ፍቅር የጎደላቸው ቃላት፣ ወይም በእነዚህ ‘አስጨናቂ ቀናት’ ውስጥ በጣም የተለመዱት አምላካዊ አክብሮት የጎደላቸው አድራጎቶች ሁላችንንም በሆነ መልኩ መንካታቸው አይቀርም።— 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
በሕይወት ውስጥ አንድ አሳዛኝ ነገር ገጥሞህ ከሆነ ይህ ሁኔታ ‘የጊዜና አጋጣሚ’ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። (መክብብ 9:11) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚፈጠሩት በወረስነው የራሳችን የኃጢአት ዝንባሌ ምክንያት ነው። (ሮሜ 5:12) ከባድ ኃጢአት ብትፈጽም እንኳ ንስሐ ከገባህና መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ከጣርክ አምላክ እንደተወህ ሊሰማህ አይገባም። (መዝሙር 103:10-14፤ ያዕቆብ 5:13-15) ከማንም ይበልጥ እርሱ ስለ እኛ ያስባል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ‘ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነና መንፈሳቸው የተሰበረውንም እንደሚያድናቸው’ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። (መዝሙር 34:18) የደረሰብህ ፈተና የቱንም ያህል አሳዛኝና ከባድ ቢሆን ይሖዋ ፈተናውን ለመወጣት የሚረዳህን ጥበብ ሊሰጥህ ይችላል። (ያዕቆብ 1:5-8) ይሖዋ የማይፈውሰው ዓይነት ቁስል እንደሌለ ዘወትር ትዝ ይበልህ። የአምላክን ሞገስ እስካገኘህ ድረስ የሕይወትን ሽልማት እንዳታገኝ የሚከለክልህ ነገር አይኖርም።— ሮሜ 8:38, 39
ከፈተና በጎ ነገር ሊገኝ ይችላልን?
“ምን ቢጠቁር ጉም ብርሃን አያጣም” የሚል አንድ የቆየ አባባል አለ። በሌላ አባባል ነገሮች የቱንም ያህል ቢከፉ የተስፋ ጭላንጭል የሚፈነጥቅልህ ነገር አታጣም ማለት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ነገር “ተስፋ ይሆንልን” ዘንድ ተጽፏል። (ሮሜ 15:4) የደረሰብህ መከራ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ደስታህንና ተስፋህን ሊያድሱልህ ይችላሉ።
መከራ አምላክን በሚወዱ ሰዎች ፊት ከተዘረጋው ዘላለማዊ በረከት ጋር ሲወዳደር ‘ጊዜያዊና ቀላል’ እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ይገልጻሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በፈተና ሥር ሆነን ያዳበርናቸው አምላካዊ ባሕርያት ከዝና ወይም ከቁሳዊ ብልጽግና የበለጠ ዋጋ እንዳላቸው ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) እንግዲያውስ ከስቃይም ቢሆን በጎ ነገር ይገኛል ማለት ነው። (ዕብራውያን 5:8) እንዲያውም ከደረሰብህ ፈተና ያገኘኸውን ትምህርት ሥራ ላይ ማዋል ያልተጠበቁ በረከቶችን ያስገኝልሃል።
ከባድ ፈተና ጠባይህ እንዲለሰልስ ሊያደርግ ይችላል። ቀደም ሲል ሌሎችን የሚያስቆጣና የራስህንም መንፈሳዊነት የሚያስተጓጉል ባሕርይ ኖሮህ ይሆናል። ምናልባት በራስህ ከልክ በላይ መመካት ሊሆን ይችላል። አንድ ዓይነት መከራ ከደረሰብህ በኋላ ወዲያው ምን ያህል ደካማ እንደሆንክና የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ትገነዘባለህ። ከደረሰብህ ፈተና ከተማርክና አስፈላጊውን ለውጥ ካደረግህ ፈተናው ጠቅሞሃል ማለት ነው።
ቀደም ሲል ስሜትህን መቆጣጠር የማትችል ሰው በመሆንህ ምክንያት ሌሎች ከአንተ ጋር ለመግባባት ይቸግራቸው ነበር እንበል። ይህም ጤንነትህን ሳይቀር አውኮብህ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 14:29, 30) ይሁን እንጂ አሁን ራስህን ለመግዛት እንዲረዳህ በአምላክ መንፈስ በመታመንህ ሁኔታው ተሻሽሎ ሊሆን ይችላል።— ገላትያ 5:22, 23
እንደ አንዳንዶቹ ሰዎች አንተም ኃጢአት ለፈጸሙ ሰዎች ምሕረት ለማሳየት የማትራራበት ጊዜ ኖሮ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንተ ራስህ ከፍተኛ ምሕረት እንደሚጠይቅ ባመንክበት አንድ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከወደቅህ በኋላ ለሌሎች ምሕረት የማሳየት ዝንባሌ እንደሚኖርህ እሙን ነው። ሌሎች ያሳዩህ የሚያጽናና አዘኔታ፣ አሳቢነት እና ምሕረት ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ተመሳሳይ ባሕርይ ማሳየት እንደሚገባህ እንድትገነዘብ አድርጎሃል ማለት ነው። ያሳለፍከው ስቃይ ያሉብህን እነዚህን የባሕርይ ድክመቶች እንድታስወግድ ካነሳሳህ ከገጠመህ ተሞክሮ ያገኘኸው አንዱ ጥቅም ይህ ነው ማለት ነው። ‘ምሕረትም በፍርድ ላይ እንደሚመካ’ ተምረሃል ማለት ነው።— ያዕቆብ 2:13፤ ማቴዎስ 5:7
በክርስቲያን ጉባኤ በኩል የተሰጠህ ቅጣት ውድ የሆነ መብትህንና በሌሎች ዘንድ ያለህን አክብሮት ቢያሳጣህስ? ተስፋ አትቁረጥ። የቅጣት እርምጃ የጉባኤውን ንጽህና ያስጠብቃል፤ ይሁን እንጂ ሌላው የቅጣቱ ዓላማ ኃጢአት የሠራውን ሰው መንፈሳዊ ሁኔታ ወደ ቀድሞው ቦታ መመለስ ነው። “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ” እንደማይመስል የታወቀ ነው፤ “ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:11፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ቅጣት ለጊዜው ከባድ ቢሆንም በትሕትና ንስሐ ለሚገባ ሰው ተስፋ የለውም ማለት አይደለም። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት በሠራው ኃጢአት ምክንያት ጠንከር ያለ ቅጣት ተቀብሏል፤ ይሁን እንጂ ንስሐ ገብቶ በመጨረሻው ግሩም የእምነት ሰው ተብሎ ተወድሷል።— 2 ሳሙኤል 12:7-12፤ መዝሙር 32:5፤ ዕብራውያን 11:32-34
ፈተና ባለህ አመለካከትም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ቀደም ሲል ቁሳዊ ግቦችህን ለማሳካት የምትሯሯጥ ሰው ኖረህ እነዚያ ነገሮች በዓለም ውስጥ እውቅናና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከበሬታን አትርፈውልህ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ከገንዘብ ኪሳራ ወይም ከንብረት ውድመት ጋር የተያያዘ ፈተና ደርሶብህ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድታተኩር አድርጎህ ይሆናል። (ከፊልጵስዩስ 1:10 ጋር አወዳድር።) ከዚህ በኋላ እውነተኛ ደስታና ዘላቂ እርካታ የሚያስገኙልህ ነገሮች በቅዱስ አገልግሎት ውስጥ የምትከታተላቸው መንፈሳዊ ቁም ነገሮችና ግቦች ብቻ እንደሆኑ ትገነዘባለህ።
በይሖዋ ታመን
ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብህ ክርስቲያናዊ እምነትህን ከሚቃወሙ ሰዎች ዘንድ ስደትና ስቃይ ሊያስከትልብህ ይችላል። ከዚህ ፈተና የተነሣ በግፍ እንደተደቆስክ ሊሰማህ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በጎ ነገርም ሊገኝበት ይችላል። ይህ ፈተና እምነትህን ሊያጠነክርልህ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች መከራ እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎች ያንተን ጽናት በማየት ሊበረታቱና ሊጠነክሩ ይችላሉ። የምታሳየውን መልካም ምግባር የሚመለከቱ ሰዎችም አምላክን ለማክበር ሊገፋፉ ይችላሉ። ተቃዋሚዎችህ እንኳን ሳይቀሩ በሥራቸው ሊያፍሩና ባደረግኸው መልካም ነገር ሊደነቁ ይችላሉ!— 1 ጴጥሮስ 2:12፤ 3:16
ስደት በሚደርስብህ ጊዜ ተስፋ ላለመቁረጥ በይሖዋ ላይ መታመን ይኖርብሃል። ቃሉ ከፈተና እረፍት የምናገኝበት ጊዜ መምጣቱ እንደማይቀር ያረጋግጥልናል፤ ይሁን እንጂ አንተ በፈለግኸው ጊዜ አይመጣ ይሆናል። እስከዚያው ግን ‘መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክት።’ (2 ተሰሎንቄ 3:13) ፈተናዎችን ለመቋቋምና ለመጽናት የሚያስችሉህን መንገዶች ከመፈለግ አትቦዝን። ሁኔታዎቹ ተስፋ አስቆራጭ መስለው በሚታዩበትም ጊዜ እንኳ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል። ለጻድቁም ሁከትን አይሰጠውም።” (መዝሙር 55:22) ስለ ራስህ እያዘንክ ከመተከዝ ይልቅ ይሖዋን በማወቅህ፣ በሕዝቦቹ መካከል በመገኘትህና መጨረሻ የሌለው ሕይወት የማግኘት ተስፋ በመያዝህ ያገኘሃቸውን በረከቶች አስብ።— ዮሐንስ 3:16, 36
የግድ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ብቻ አተኩር። ጥንካሬና ጽናት እንዲሰጥህ በየዕለቱ ይሖዋን በጸሎት ለምነው። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ስቃይ ያደረሱብህን ሰዎች ስለ መበቀል ፈጽሞ አታስብ። ለይሖዋ ተውለት። (ሮሜ 12:19) ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በመኮትኮት የተፈተነ ሁለንተናዊ ባሕርይ እንዲኖርህ የሚረዱህን አጋጣሚዎች ለማግኘት ተጣጣር። (2 ጴጥሮስ 1:5-8) የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ነገር ለማሟላት ፍቅራዊ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ሽማግሌዎች ጨምሮ ሌሎች ለሚያደርጉልህ ነገር ሁሉ አመስጋኝ ሁን። (ዕብራውያን 13:7, 17) ለአምላክ የታመንክ ሁን፤ የሕይወት ሽልማትህን ሞትም እንኳን ቢሆን እንደማይነጥቅህ እርግጠኛ በመሆን ዓይንህ በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር አድርግ።— ዮሐንስ 5:28, 29፤ 17:3
ከባድ ሐዘን ወይም አስቸጋሪ ፈተና ደርሶብህ ከሆነ ‘በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን፤’ ዛሬ የገጠመህ ኃዘንና መከራ ሁሉ በመጨረሻው በታላቅ ደስታ ይተካል። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ዮሐንስ 16:20) አምላክ ኢዮብን እንደባረከው አንተንም ሲባርክህ ሰቆቃው በደስታ ይለወጣል። በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብህ ስቃይ ከምታገኘው ወሮታ ጋር ሲወዳደር ከቁጥርም የሚገባ አይደለም። (ከሮሜ 8:18 ጋር አወዳድር።) የታመንክ በመሆን የምታሳየው ጽናት ሌሎችን ሊያበረታታና አንተንም ‘ከአዲሱ ሰውነት’ ጋር አብረው የሚመጡትን ማራኪ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያት እንድታፈራ ሊረዳህ ይችላል። (ኤፌሶን 4:23, 24፤ ቆላስይስ 3:10, 12-14) እንግዲያውስ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ጥበብ የሞላበት ምክር እያሰብክ በርታ:- “ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።”— 1 ጴጥሮስ 4:19
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ኢዮብ ሁን። በፍጹም ተስፋ አትቁረጥ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን