-
የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ ከመተርጎም ተጠንቀቁመጠበቂያ ግንብ—1997 | ግንቦት 15
-
-
የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ ከመተርጎም ተጠንቀቁ
አንድ ታዋቂ የቴሌቪዥን ወንጌላዊ አብሮት የሚያገለግል ሰባኪ ምንዝር እንደፈጸመ በመግለጽ በሕዝብ ፊት በጽኑ አውግዞት ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ራሱ ከአንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር ተያዘ።
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንድ ልዕለ ኃያል መንግሥት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አንጃዎችን በሰላም ጠረጴዛ ዙሪያ ለማደራደር መልእክተኞችን ይልካል። ይሁንና ይኸው መንግሥት በብዙ ቢልዮን ዶላር ለሚገመት የጦር መሣሪያ ሽያጭ ለመደራደር መልእክተኞቹን በምሥጢር ወደ ሌሎች መንግሥታት ልኳል።
ዓይን ያወጣ የግብዝነት ተግባር በሰፊው የተለመደ በመሆኑ ሌላውን በማመን ፋንታ ጥርጣሬ ቢነግሥ ምን ያስገርማል? ብዙ ሰዎች የሌሎችን ሐሳብ በጥርጣሬ ዓይን ማየታቸው የተለመደ ነገር ሆኗል።
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ታማኝ ከሆኑ የእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲነካብን ላለመፍቀድ ጠንቃቆች ልንሆን ይገባናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በጠላቶቻችን መካከል ስንመላለስ “እንደ እባብ ልባሞች” እንድንሆን ሲመክረን እውነተኛ ተከታዮቹን በጥርጣሬ ዓይን እንድናያቸው መናገሩ አልነበረም። (ማቴዎስ 10:16) ታዲያ የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ መተርጎም የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው? በተለይ እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ለማስወገድ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡን ዘርፎች የትኞቹ ናቸው? ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ያለንን ውድ ዝምድና መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ከጥንቱ ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት
ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ መተርጎም በእነርሱ ላይ ከመፍረድ ተለይቶ አይታይም። የተናገሩት ወይም ያደረጉት ነገር ጠማማነትና ተንኮል ያለበትን ነገር ጥሩ አስመስሎ ለማቅረብ የተደረገ ብልሃት ነው ብለን በችኮላ እንደመደምደም ይሆንብናል። በኢያሱ መጽሐፍ ምዕራፍ 22 ላይ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት እንደሚቻለው ብዙውን ጊዜ ዋነኛው ችግር ነገሩን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ነው።
እስራኤላውያኑ የተስፋይቱን ምድር ድል አድርገው የየነገዳቸውን ክልል ገና መቀበላቸው ነበር። የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ግማሹ ነገድ በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ “ታላቅ” መሠዊያ ይሠራሉ። በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ነገዶች ይህ የክህደት ድርጊት እንደሆነ አድርገው በስህተት አሰቡ። እነዚህ ሦስት ነገዶች ይህንን ታላቅ ነገር የሠሩት ለአምልኮ ወደተዘጋጀው በሻይሎ ወደሚገኘው የመገናኛ ድንኳን ላለመሄድና እዚያው መሥዋዕት ለማቅረብ እንደሆነ አድርገው አሰቡ። ከሳሾቹ ነገዶች ወዲያውኑ ለጦርነት ተዘጋጁ።— ኢያሱ 22:10-12
ይሁን እንጂ በፊንሐስ የሚመራ አንድ የአለቆች ልዑክ ከእስራኤላውያን ወንድሞቻቸው ጋር እንዲነጋገር በፍጥነት መላካቸው የሚያስመሰግን ነው። ጥፋት ሠርታችኋል የተባሉት ነገዶች የቀረበባቸውን የእምነት ማጉደል፣ የዓመፀኝነትና የክህደት ክስ ካዳመጡ በኋላ ይህን ግዙፍ መሠዊያ የገነቡበትን ምክንያት ገለጹ። ለመሥዋዕት ማቅረቢያ የተሠራ ሳይሆን ይሖዋን በማምለክ ረገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ላለው አንድነት ‘ምሥክር እንዲሆን’ የተገነባ መሠዊያ ነበር። (ኢያሱ 22:26, 27) ልዑካኑ ወንድሞቻቸው ምንም የፈጸሙት ጥፋት እንደሌለ አምነውበት ወደ አገራቸው ተመለሱ። በዚህ መንገድ ከእርስ በርስ ጦርነትና አስከፊ ከሆነ ደም መፋሰስ ዳኑ።
ቸኩለን የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ እንዳንተረጉም ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር ላይ ላዩን ብቻ አይተን የምናገኘው ግንዛቤ ቀረብ ብለን በመመልከት ከምንረዳው እውነታ ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህ ነገር በአንድ ክርስቲያን ሕይወት የተለያዩ ዘርፎች ይንጸባረቃል።
ስለ ሽማግሌዎች ያለን አመለካከት
አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች ‘የአምላክን ጉባኤ የመጠበቅ’ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ሰዎች ምክር መስጠቱን አስፈላጊ ሆኖ ያገኙታል። (ሥራ 20:28) ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ መጥፎ ባልንጀርነትን ወይም ደግሞ ከአንድ ተቃራኒ ጾታ ጋር ያላቸውን ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ በተመለከተ ስለ ልጆቻችን ቢያነጋግረን ምን ይሰማናል? እንዲህ ያለበት ሌላ ስውር ምክንያት እንደሚኖረው በመገመት ‘እርሱ ድሮም የእኛ ቤተሰብ ነገር አይዋጥለትም’ ብለን እናስባለንን? እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን ከጊዜ በኋላ ልንጸጸትበት እንችላለን። ምናልባት የልጆቻችን መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ የሚሰጠንን ጠቃሚ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ልናደንቅ ይገባናል።— ምሳሌ 12:15
አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ምክር ሲሰጠን ከበስተጀርባው ሌላ ምክንያት ይኖረዋል ብለን አናስብ። ከዚህ ይልቅ ከሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር መጠቀም የምንችልበት መንገድ ምን እንደሆነ ራሳችንን እንመርምር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:11) እንግዲያውስ አመስጋኞች እንሁን፤ ነገሮችን ሚዛናዊ ሆነን እንመልከት። እኛ ምክር ለመቀበል እንደሚከብደን ሁሉ ብዙውን ጊዜ ለሽማግሌዎችም ምክር መስጠቱ ያን ያክል ከባድ እንደሚሆንባቸው አትዘንጉ።
ስለ ወላጆች የሚሰማን ስሜት
አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው አንዳንድ ዕገዳዎችን ሲያደርጉባቸው እንዲህ ያደረጉበትን ምክንያት መጠራጠር ይጀምራሉ። አንዳንድ ወጣቶች ‘ወላጆቼ እንደዚህ ሕግ የሚያበዙት ለምንድን ነው? በሕይወቴ እንድደሰት አይፈልጉም ማለት ነው?’ ሊሉ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሁኔታውን በሚዛናዊነት መመርመር ይኖርባቸዋል።
ወላጆች ልጆቻቸውን በመንከባከብ ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የገንዘብና የሌሎች ነገሮች መሥዋዕትነት ጠይቆባቸዋል። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ልጆቻቸው ሕይወት አስቸጋሪ እንዲሆን ለማድረግ ቆርጠው ይነሣሉ ብለን የምናስብበት ምክንያት ይኖራልን? ከዚህ ይልቅ እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያነሳሳቸው ፍቅር ነው ብሎ ማሰቡ ይበልጥ ምክንያታዊ አይሆንምን? በዚህ ዕድሜያቸው አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለሚገጥሟቸው ልጆቻቸው አንዳንድ ገደቦችን እንዲያወጡ ያነሳሳቸው ይህ ፍቅር አይደለምን? አፍቃሪ የሆኑ ወላጆችን ሐሳብ በመጥፎ መተርጎም ምንኛ ደግነትና አመስጋኝነት የጎደለው ድርጊት ይሆናል!— ኤፌሶን 6:1-3
ለመሰል ክርስቲያኖች የሚኖረን አመለካከት
ብዙዎች በሌሎች ላይ አስቀድመው መፍረድና ሁሉንም በአንድ ዓይን ማየት ይቀናቸዋል። እኛ ራሳችንስ በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ የነበረንና የተወሰኑ ሰዎችን በጥርጣሬ ዓይን የምናይ ከነበርንስ? በዚህ ረገድ ዓለም ተጽዕኖ ያሳድርብናልን?
ለምሳሌ ያህል አንድ መንፈሳዊ ወንድማችን ጥሩ ቤትና በውድ ዋጋ የተገዛ ተሽከርካሪ አለው እንበል። “ፍቅረነዋይ የተጠናወተውና በሕይወቱ ውስጥ መንግሥቱን የማያስቀድም ሰው ነው” ብለን ለመደምደም መቸኮል ይኖርብናልን? አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሊኖራቸው ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይህ መጥፎ ዝንባሌ አላቸው ወይም ደግሞ ‘መንግሥቱን አያስቀድሙም’ የሚያሰኝ አይደለም። በመንፈሳዊ ሥራ የተጠመዱና ያላቸውን ቁሳዊ ሀብት በልግስና ምናልባትም የይታይልኝ ባይነት መንፈስ በሌለበት ሁኔታ የመንግሥቱን ሥራ ለማራመድ የሚያውሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።— ማቴዎስ 6:1-4, 33
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ማለትም ድሆችና ሀብታሞች ነበሩ። (ሥራ 17:34፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ 6:17፤ ያዕቆብ 2:5) አምላክ ሰዎችን ባላቸው ቁሳዊ ሀብት አይገመግምም፤ እኛም ብንሆን እንደዚያ ማድረግ አይገባንም። የተፈተኑና የታመኑ የእምነት አጋሮቻችንን ‘ያላንዳች አድልዎ’ ልንወዳቸው ይገባል።— 1 ጢሞቴዎስ 5:21 የ1980 ትርጉም
በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሁሉንም ሰዎች በአንድ መፈረጅና በጥርጣሬ ማየት የተለያየ መልክ ይዘው ብቅ ይላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ካሳለፈው ታሪክ አንጻር ብቻ እንደ ዓመፀኛ ወይም በፍቅረነዋይ እንደተጠመደ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ልንጠመድ አይገባም። ወገናዊነትና ጥርጣሬ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ቦታ የለውም። ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች “በደልና ለሰው ፊት ማድላት” የማያውቀውን ይሖዋ አምላክን መምሰል ይኖርባቸዋል።— 2 ዜና መዋዕል 19:7፤ ሥራ 10:34, 35
ፍቅር ስሜታችሁን እንዲቆጣጠር ፍቀዱለት
ቅዱሳን ጽሑፎች “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራሉ። (ሮሜ 3:23) እንግዲያው የአምልኮ አጋሮቻችንን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ አብረውን እንደሚጣጣሩ ሰዎች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ጥርጣሬ ወይም ሌሎች አፍራሽ ስሜቶች ከመንፈሳዊ ወንድማችን ወይም እህታችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲያናጉብን ፈቅደን ከሆነ በሰይጣን መዳፍ እንዳንወድቅ እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ለማስወገድ አምላክ እንዲረዳን እንጸልይ። (ማቴዎስ 6:13) ሔዋን፣ ይሖዋ ስውር ዓላማ እንዳለው፣ ስለ እርሷ ደህንነት እንደማያስብና ትልቅ ደስታ ሊሰጣት ይችል የነበረውን ነፃነት እንደነፈጋት አድርጋ እንድታስብ ሰይጣን አሳምኗታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) የወንድሞቻችንንም ሐሳብ በመጥፎ መተርጎም የሰይጣንን ዓላማ ማራመድ ነው።— 2 ቆሮንቶስ 2:11፤ 1 ጴጥሮስ 5:8
የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ የመተርጎም ዝንባሌ እንዳለብን ከተገነዘብን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ልብ እንበል። ፍጹም የሆነ የአምላክ ልጅ የነበረ ቢሆንም የደቀ መዛሙርቱን ሐሳብ በመጥፎ ለመተርጎም አልሞከረም። እንዲያውም ኢየሱስ ጥሩ ጥሩ ባሕርያቸውን ለማየት ይጥር ነበር። የከበሬታ ቦታ ለማግኘት እርስ በርሳቸው ሲሻኮቱ በተመለከተ ጊዜ የተሳሳተ ውስጣዊ ዝንባሌ እንዳላቸው በማሰብ በ12 አዳዲስ ሐዋርያት አልተካቸውም። (ማርቆስ 9:34, 35) ፍጹማን ሰዎች ባለመሆናቸው ለኩራትና ለመደብ ልዩነት ከፍተኛ ግምት ይሰጥ የነበረው የከሃዲዋ ይሁዳ ባሕል ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲከተሉት ያነሳሳቸው ዋነኛ ነገር ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር በማሳየታቸውና ከኢየሱስ ጋር በመጣበቃቸውም በእጅጉ ተባርከዋል።— ሉቃስ 22:28-30
የታመኑ የእምነት አጋሮቻችንን በጥርጣሬ ዓይን የምናያቸው ከሆነ የምናየው አዛብቶ በሚያሳይ ሌንስ ነው ማለት ነው። እውነታው አይታየንም። እንግዲያውስ በፍቅር ሌንስ እንመልከት። ታማኝ የሆኑ መሰል ክርስቲያኖች እንደሚወዱንና እኛም በደግነት ላይ የተመሠረተ አሳቢነት ልናሳያቸው እንደሚገባ የሚያረጋግጡ በቂ ማስረጃዎች አሉ። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8) እንግዲያው ለእምነት አጋሮቻችን ፍቅር የምናሳይና የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ ከመተርጎም የምንጠነቀቅ ያድርገን።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታማኝነት አምላክን የሚያገለግሉትን ሰዎች የምትመለከታቸው እንዴት ነው?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እርስ በርስ መተማመንና መከባበር የይሖዋ ምሥክሮችን እንደ አንድ ደስተኛ ቤተሰብ ያስተሳስራቸዋል
-
-
‘ሃይማኖታቸው ከሚሰጣቸው ማሠልጠኛ ጋር ተስማምተው ይኖራሉ’መጠበቂያ ግንብ—1997 | ግንቦት 15
-
-
‘ሃይማኖታቸው ከሚሰጣቸው ማሠልጠኛ ጋር ተስማምተው ይኖራሉ’
በሚያሚ፣ ፍሎሪዳ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት ሴት በከተማው እየታተመ ለሚወጣ አንድ ጋዜጣ የሚከተለውን ደብዳቤ ላከች:- “ታኅሣሥ 10 ቀን ልጄ ገበያ ላይ ሳለ የገንዘብ ቦርሳውን ሌባ ሰረቀው። በቦርሳው ውስጥ የመንጃ ፈቃድ፣ ከመንግሥት የገንዘብ ድጎማ የሚያገኝበት መታወቂያ ካርድና ሌሎች ነገሮች እንዲሁም 260 የአሜሪካ ዶላር ነበር።
“የጠፋበትን ንብረት ለሥራ አስኪያጁ ካመለከተ በኋላ ወደ ቤት መጣ። አመሻሹ ላይ የስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች አንዲት ሴት ስልክ ደወለችለት። የገንዘብ ቦርሳውን እንዳገኘችው በስልክ ኦፕሬተር አስተርጓሚነት ነገረችው።
“አድራሻዋን ሰጠችው። . . . 260 የአሜሪካ ዶላሩን ጨምሮ ምንም ሳይጎድል የገንዘብ ቦርሳውን እንዳለ ሰጠችው።
“ሌባው የገንዘብ ቦርሳውን ከኪሱ ሲሰርቅ አይታው ጮኸች። ሌባው የገንዘብ ቦርሳውን ጥሎ ሮጠ። በዚህ ጊዜ ልጄን ማግኘት ስላልቻለች ቦርሳውን ወደ ቤቷ ወሰደችና ስልክ ደወለች።
“እርሷና ቤተሰቦቿ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ሃይማኖታቸው ከሚሰጣቸው ማሠልጠኛ ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩ ግልጽ ነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኝነትን የሚያሳዩት ከሰዎች ውዳሴ ለማግኘት ሲሉ አይደለም። (ኤፌሶን 6:7) ከዚህ ይልቅ ለሰማዩ አባታቸው ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ከልብ ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ለአምላክና ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ‘ምሥራች’ እንዲያውጁ ይገፋፋቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ምድርን ውብ ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል። በዚያን ጊዜ ምድር ውበትን ከመላበሷም በላይ ሐቀኝነት ለዘላለም የሚሰፍንባትና ጥሩ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባት ቦታ ትሆናለች።— ዕብራውያን 13:18፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
-