የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 10/15 ገጽ 5-7
  • እውነተኛ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እውነተኛ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መንፈሳዊ መሆን ደስታ ያስገኛል
  • ምርጫ የማድረግ ችሎታችን
  • ቁልፉ አምላካዊ ጥበብና ታዛዥነት ነው
  • ደስታ ስለሚገኝበት መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እውነተኛ ደስታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ‘ደስተኛውን አምላክ’ የሚያገለግሉ ደስተኞች ናቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 10/15 ገጽ 5-7

እውነተኛ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ሰዎች የተፈጠሩት ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ነበር። እንዲህ ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? እስቲ የሰውን አፈጣጠር መለስ ብለን እንመልከት።

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት መደሰት እንዲችሉ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። አዳምንና ሔዋንን ኤደን ተብሎ በሚጠራ አስደሳች የአትክልት ቦታ ማለትም በገነት ውስጥ አስቀመጣቸው። ፈጣሪ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን ሁሉ ሰጣቸው። በአትክልት ቦታው ‘ለማየት ደስ የሚያሰኝና ለመብላትም መልካም የሆነ ዛፍ ሁሉ’ ነበር። (ዘፍጥረት 2:​9) አዳምና ሔዋን ጤናሞች፣ ጠንካሮችና የሚያምሩ ነበሩ። ፍጹም የነበሩ ከመሆኑም በላይ እውነተኛ ደስታ ነበራቸው።

ይሁን እንጂ ደስተኞች እንዲሆኑ ያስቻላቸው ነገር ምን ነበር? በገነት ውስጥ መኖራቸው ነው ወይስ በአካል ፍጹም መሆናቸው? ከአምላክ ያገኟቸው እነዚህ ስጦታዎች በሕይወታቸው ውስጥ ተጨማሪ ደስታ እንደሚያስገኙላቸው እሙን ነው። ሆኖም ደስታቸው እንዲህ በመሰሉ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ የተመካ አልነበረም። ኤደን ገነት የሚያምር መናፈሻ ብቻ አልነበረም። አምላክን የሚያመልኩበት መቅደስም ነበር። ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ነገር ከፈጣሪ ጋር ፍቅራዊ ዝምድና መሥርተውና ይህን ዝምድና ጠብቀው መኖር መቻላቸው ነበር። ደስተኞች እንዲሆኑ በመጀመሪያ መንፈሳዊ መሆን ነበረባቸው።​—⁠ከማቴዎስ 5:​3 ጋር አወዳድር።

መንፈሳዊ መሆን ደስታ ያስገኛል

አዳም መጀመሪያ ላይ ከአምላክ ጋር መንፈሳዊ ዝምድና ነበረው። ይህም አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር የሚኖረው ዓይነት ፍቅራዊና ርኅራኄ የተላበሰ ዝምድና ነበር። (ሉቃስ 3:​38) በኤደን ገነት አዳምና ሔዋን አምልኳቸውን የማከናወን ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ ነበራቸው። ይሖዋን በፈቃደኝነትና በፍቅራዊ መንገድ በመታዘዝ እንስሳት ሊያስገኙለት የማይችሉትን ዓይነት ክብርና ምስጋና ሊያመጡለት ይችሉ ነበር። በማሰብ ኃይላቸው ተጠቅመው አስደናቂ ለሆኑት ባሕርያቱ ውዳሴ ሊያቀርቡና ሉዓላዊነቱን ደግፈው ሊቆሙ ይችሉ ነበር። ይሖዋም ዘወትር በፍቅርና በርኅራኄ እየተንከባከበ ሊያኖራቸው ይችል ነበር።

ከፈጣሪ ጋር ያላቸው እንዲህ ዓይነቱ ቁርኝትና ለሕጉ ታዛዥ መሆናቸው ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን እውነተኛ ደስታ አምጥቶላቸው ነበር። (ሉቃስ 11:​28) አዳምና ሔዋን ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ፈልገው ለማግኘት ብዙ ዓመታት የሚፈጅ ሙከራ ማድረግ አያስፈልጋቸውም ነበር። ከተፈጠሩባት ጊዜ ጀምሮ ደስተኞች ነበሩ። ከአምላክ ጋር በሰላም መኖራቸውና ለሥልጣኑ ተገዥ መሆናቸው ደስተኞች አድርጓቸው ነበር።

ይሁን እንጂ የአምላክን ትእዛዝ በጣሱ ጊዜ ያ ሁሉ ደስታ ከሰመ። አዳምና ሔዋን በማመፃቸው ከይሖዋ ጋር የነበራቸው መንፈሳዊ ዝምድና ተቋረጠ። የአምላክ ወዳጆች መሆናቸው አከተመ። (ዘፍጥረት 3:​17-19) ከገነት ከተባረሩበት ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠ ይመስላል። ፍጽምናቸውን፣ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውንና ገነታዊ መኖሪያቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:​23) ከሁሉም በላይ ግን ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና በማጣታቸው ምክንያት ደስታ የሚያስገኘውን ቁልፍ አጡ።

ምርጫ የማድረግ ችሎታችን

አዳምና ሔዋን ከመሞታቸው በፊት ሰብዓዊ ጠባያቸውን፣ በተፈጥሮ ያገኙትን ሕሊናቸውንና መንፈሳዊ የመሆን ችሎታቸውን ለልጆቻቸው አስተላለፉ። ሰብዓዊው ቤተሰብ እንስሶች ወዳሉበት ደረጃ ዝቅ አልተደረገም። እኛ ከፈጣሪ ጋር መታረቅ እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 5:​18) ሰው የማሰብ ችሎታ ያለው ፍጡር እንደመሆኑ መጠን አምላክን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ያለው የመምረጥ ችሎታ እንደተጠበቀ ነው። ይሖዋ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ አዲስ ለተቋቋመው የእስራኤል ብሔር ሕይወትን ወይም ሞትን እንዲመርጥ በፊቱ ምርጫ ባስቀመጠ ጊዜ ይህ ሁኔታ ታይቷል። አምላክ ቃል አቀባዩ በሆነው በሙሴ በኩል “ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፣ ሞትንና ክፋትን” አስቀምጫለሁ ብሎ ተናግሯል።​—⁠ዘዳግም 30:​15-18

የመጀመሪያው ገነት ከጠፋ ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላም እንኳ ዛሬ እኛም ትክክለኛውን ምርጫ የማድረግ ችሎታ አለን። የሚሠራ ሕሊናና የአምላክን ሕጎች የመታዘዝ መሠረታዊ የሆነ ችሎታ አለን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ውስጣዊ ሰውነት’ እና “ውስጣዊ” ሰው በማለት ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 4:​16፤ ሮሜ 7:​22) እነዚህ አባባሎች የአምላክን ባሕርይ የማንጸባረቅ፣ እርሱ በሚያስብበት መንገድ የማሰብና መንፈሳዊ የመሆን ተፈጥሯዊ ችሎታ እንዳለን የሚያሳዩ ናቸው።

ሥነ ምግባራዊ ተፈጥሯችንንና ሕሊናችንን በማስመልከት ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ” በማለት ጽፏል።​—⁠ሮሜ 2:​14, 15

ቁልፉ አምላካዊ ጥበብና ታዛዥነት ነው

አንድ ሰው ‘አምላክን የማምለክ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ካለንና ይህም እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ከሆነ ሐዘን ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ይህ የሆነበት ምክንያት ደስተኛ ለመሆን እያንዳንዳችን መንፈሳዊነትን ማዳበር ስላለብን ነው። መጀመሪያ ላይ ሰው የተፈጠረው በአምላክ መልክ ቢሆንም አሁን ግን ከፈጣሪው በጣም ርቋል። (ኤፌሶን 4:​17, 18) ስለዚህ እያንዳንዳችን ከአምላክ ጋር መንፈሳዊ ዝምድና ለመመሥረትና ይህንንም ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ አለብን። እንዲህ የመሰለው ዝምድና በአንድ ጀንበር የሚመሠረት አይደለም።

ኢየሱስ መንፈሳዊነትን ለማሳደግ የሚረዱ ሁለት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ገልጿል። አንደኛው ስለ አምላክ ትክክለኛ የሆነ እውቀት ማግኘት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለርሱ ፈቃድ በፈቃደኝነት መገዛት ነው። (ዮሐንስ 17:​3) ኢየሱስ ከአምላክ ቃል በመጥቀስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:​4) በሌላም ወቅት ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:​34) ደስታ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በመፈለግ በርካታ አሥርተ ዓመታት ማሳለፍ አያስፈልገንም። ደስታ የሚገኘው በተሞክሮ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ ሊያስገኙ የሚችሉት አምላካዊ ጥበብና ለፈጣሪ ታዛዥ መሆን ብቻ ናቸው።​—⁠መዝሙር 19:​7, 8፤ መክብብ 12:​13

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላካዊ ጥበብ በማሳየት የሚገኘው ደስታና በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም መያዝ ልንደርስበት የማንችለው ነገር አይደለም። (ሥራ 17:​26, 27) የይሖዋ እውቀትና የእሱ ዓላማ ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች በቢልዮን በሚቆጠር ቅጂ የሚገኝ በመሆኑ በዓለም ካሉት መጻሕፍት ሁሉ የበለጠ ስርጭት ያለው መጽሐፍ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ወዳጅ እንድትሆንና እውነተኛ ደስታ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎች “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው” በማለት ያረጋግጡልናል።​—⁠መዝሙር 144:​15 NW

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ደስታ ለማግኘት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች

1. መንፈሳዊ ነገሮችን ጠንቅቀህ ለማወቅና መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ተጣጣር። ኢየሱስ “ብፁዓንስ [“ደስተኞችስ፣” Nw] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ብሏል።​—⁠ሉቃስ 11:​28

2. በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከሃብት ወይም ከቅንጦት ዕቃዎች የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዘብ። ጳውሎስ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ . . . ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​6-8

3. በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ለማዳበርና ለእንዲህ ዓይነቱ ሕሊና አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ተጣጣር።​—⁠ሮሜ 2:​14, 15

4. ይሖዋ አምላክን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ በዚህ መንገድ ከሕዝቡ እንደ አንዱ የሚያስቆጥርህን ብቃት ታገኛለህ። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ዳዊት “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል።​—⁠መዝሙር 144:​15 Nw

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው።”​—⁠ማቴዎስ 5:​3 NW

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ