“ከኤፊቆሮሳውያን” ተጠንቀቁ
“በጣም ጥሩ ሰው ነው! ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም አለው። አያጨስም፣ አደንዛዥ ዕፅ አይወስድም ወይም አነጋገሩ የታረመ ነው። እንዲያውም ክርስቲያን ነን ከሚሉ ከአንዳንዶች የተሻለ ነው!”
አንዳንዶች አጉል ጓደኝነት በሚጀምሩበት ጊዜ ስህተታቸውን ላለመቀበል ይህን የመሰለ ሰበብ ሲያቀርቡ ሰምተሃል? ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በቅዱስ ጽሑፉ ሲመረመር ትክክል ሆኖ ይገኛል? በአንድ የጥንት ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ትምህርት ሰጪ ሆኖ እናገኘዋለን።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤን “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቋል። ምናልባትም አንዳንድ የቆሮንቶስ ጉባኤ ክርስቲያኖች፣ የግሪክ ፍልስፍና ተጽእኖ ካሳደረባቸው ሰዎች ጋር፣ ከኤፊቆሮሳውያን ጋር ጭምር የቅርብ ጓደኝነት ሳይጀምሩ አልቀሩም። ኤፊቆሮሳውያን እነማን ናቸው? በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች አደገኛ የሆኑትስ በምን መንገድ ነው? በዛሬው ጊዜ እኛ ልንርቃቸው የሚገባን እንደ ኤፊቆሮሳውያን ያሉ ሰዎች አሉን?—1 ቆሮንቶስ 15:33
ኤፊቆሮሳውያን እነማን ነበሩ?
ኤፊቆሮሳውያን ኤፊቆሮስ የተባለው ከ341 እስከ 270 ከዘአበ የኖረው የግሪክ ፈላስፋ ተከታዮች ናቸው። ኤፊቆሮስ በሕይወት ውስጥ ብቸኛው ወይም ዋናው ነገር ደስታ ነው ብሎ አስተምሯል። ያ ማለት ታዲያ ኤፊቆሮሳውያን ዘወትር ደስታ ለማግኘት ሲሉ ወራዳ ድርጊቶችን በመፈጸም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗር ይከተሉ ነበር ማለት ነውን? በጣም የሚያስገርመው ኤፊቆሮስ ተከታዮቹ ይህን የመሰለ አኗኗር እንዲከተሉ አላስተማረም! ከዚህ ይልቅ ከፍተኛ ደስታ የሚገኘው ከአስተዋይነት፣ ከድፍረት፣ ራስን ከመግዛትና ከፍትህ ጋር ተስማምቶ በመኖር ነው ብሎ አስተምሯል። አጥብቆ የደገፈው ቅጽበታዊና ጊዜያዊ ደስታን ሳይሆን በሕይወት ዘመን ሁሉ የሚዘልቅ ደስታ መከታተልን ነው። ስለዚህ ኤፊቆሮሳውያን ከባድ ኃጢአት ከሚሰሩ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ በጎ ሥነ ምግባር ያላቸው ሊመስሉ ይችላሉ።—ከቲቶ 1:12 ጋር አወዳድር።
አኗኗራቸው ከክርስትና አኗኗር ጋር ይመሳሰላልን?
የጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባል ብትሆን ኖሮ በኤፊቆሮሳውያን አኗኗር ትማረክ ነበርን? አንዳንድ ክርስቲያኖች ኤፊቆሮሳውያን ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸው ሰዎች ስለሆኑ ለክርስቲያኖች መልካም ጓደኞች ሊሆኑ ይችላሉ ብለው አስበው ይሆናል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከአምላክ ቃል ጋር ይመሳሰላሉ ያሏቸውን የኤፊቆሮሳውያን የአቋም ደረጃዎች በመጥቀስ ከእነርሱ ጋር ለመወዳጀት ተጨማሪ ምክንያት እንዳላቸው አስበው ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል ኤፊቆሮሳውያን ደስታን በተመለከተ ልከኛ አመለካከት ነበራቸው። ከሥጋዊ እርካታ ይልቅ አእምሮአዊ እርካታን ከፍ አድርገው ይመለከቱ ነበር። አንድ ሰው የተመገበው ነገር አብሮት ከተመገበው ሰው ጋር ያለው ዝምድና ያህል አስፈላጊ አልነበረም። ኤፊቆሮሳውያን በፖለቲካ ውስጥ ከመግባትና ስውር የሆኑ መጥፎ ድርጊቶችን ከመሥራት ይርቁ ነበር። “በብዙ መንገዶች ከእኛ ጋር ይመሳሰላሉ!” የሚል አስተሳሰብ ለመያዝ እንዴት ቀላል ነበር።
የሆነ ሆኖ ኤፊቆሮሳውያን እውን የጥንት ክርስቲያኖችን ይመስሉ ነበር? በጭራሽ አይመስሉም። በደንብ የሰለጠነ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ክርስቲያኖች ዐቢይ የሆኑ ልዩነቶችን ማግኘት ይችላሉ። (ዕብራውያን 5:14) አንተስ ትችላለህ? እስቲ የኤፊቆሮስን ትምህርቶች ቀረብ ብለን እንመርምር።
የኤፊቆሮሳውያን ትምህርት መጥፎ ገጽታ
ሰዎች የአማልክትንና የሞትን ፍራቻ እንዲያስወግዱ ለመርዳት፣ ኤፊቆሮስ አማልክት ስለ ሰው ዘር ደንታ የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ በሰብዓዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም ብሎ አስተምሯል። እንደ ኤፊቆሮስ አባባል ከሆነ አማልክት አጽናፈ ዓለምን አልፈጠሩም፤ በተጨማሪም ሕይወት ወደ ሕልውና የመጣው በአጋጣሚ ነው። ይህ አባባል ለሰብዓዊ ፍጥረቶቹ የሚያስብ ፈጣሪ ማለትም “አንድ አምላክ” አለ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር በግልጽ አይጋጭምን?—1 ቆሮንቶስ 8:6፤ ኤፌሶን 4:6፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
ኤፊቆሮስ ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር አይችልም ብሎም አስተምሯል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ ከሚያስተምረው ጋር በእርግጥ የሚጋጭ ነው። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ባስተማረበት ወቅት በትንሣኤ መሠረተ ትምህርት ላይ ከእርሱ ጋር ካልተስማሙት መካከል ኤፊቆሮሳውያን ሳይኖሩበት አይቀሩም።—ሥራ 17:18, 31, 32፤ 1 ቆሮንቶስ 15:12-14
በጣም አደገኛውና የረቀቀው የኤፊቆሮስ ፍልስፍና ይህ ሳይሆን አይቀርም። ኤፊቆሮስ ከሞት በኋላ እንደገና ሕይወት መኖሩን አለመቀበሉ ሰው በምድር ላይ በሕይወት ሳለ በሚያሳልፈው አጭር ጊዜ በተቻለው መጠን መደሰት መቻል አለበት ወደሚል መደምደሚያ መርቶታል። ከላይ እንደተመለከትነው የእርሱ አመለካከት በኃጢአተኝነት ለመኖር ሳይሆን ከዚያ ይልቅ ያለን የአሁኑ ጊዜ ብቻ በመሆኑ ጊዜያችንን በአግባቡ እንድናጣጥም ነው።
ይህም በመሆኑ እያዛለሁ በሚል ፍራቻ በስውር የሚሰራ ክፉ ድርጊት ላሁኑ ጊዜ ደስታ አደገኛ በመሆኑ ኤፊቆሮስ አውግዞታል። አሁን ሊገኝ ለሚችለው ደስታ እንቅፋት የሚሆነው ሌላው ነገር ከመጠን በላይ መብላትና መጠጣት ስለሆነ ኤፊቆሮስ በዚህም ረገድ ልከኝነትን አበረታቷል። በተጨማሪም ውለታ ሊመልሱልን ስለሚችሉ፣ ለሌሎች ሰዎች መልካም ማድረግ ጥሩ እንደሆነ ይናገራል። እርግጥ ነው በስውር መጥፎ ነገር አለመስራት፣ ልከኛ መሆን እና ለሌሎች መልካም ማድረግ ምንም ክፋት የሌለባቸው ነገሮች ናቸው። ታዲያ የኤፊቆሮስ ፍልስፍና ለአንድ ክርስቲያን አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የእርሱ ምክር የተመሰረተው እምነት የለሽ በሆነ “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” በሚል አመለካከት ላይ ስለሆነ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:32
መጽሐፍ ቅዱስ ባሁኑ ጊዜ በደስታ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ሆኖም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” ብሎ ይመክረናል። (ይሁዳ 21) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለወደፊቱ ዘላለማዊ ሕይወት እንጂ ብን ብሎ ለሚጠፋው ለአሁኑ ሕይወት አይደለም። የአንድ ክርስቲያን ዋና ፍላጎት አምላክን ማገልገል ነው። አምላክን በአንደኛ ደረጃ ሲያስቀምጥ ደስታና እርካታ ያገኛል። በተመሳሳይም ኢየሱስ በራሱ የግል ፍላጎቶች ከመጠመድ ይልቅ ጉልበቱን ይሖዋን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ሁኔታ ለማገልገልና ሰዎችን ለመርዳት ተጠቅሞበታል። ውለታ ይመለስልኛል ብለው በመጠበቅ ሳይሆን ለሰዎች ካላቸው እውነተኛ ፍቅር በመነሳት ለሌሎች ጥሩ እንዲያደርጉ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯል። በግልጽ እንደሚታየው የኤፊቆሮሳውያን ትምህርትና የክርስትና እምነት መሠረታዊ ግፊቶች ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው።—ማርቆስ 12:28-31፤ ሉቃስ 6:32-36፤ ገላትያ 5:14፤ ፊልጵስዩስ 2:2-4
ስውር የሆነ አደጋ
በጣም የሚያስገርመው ኤፊቆሮሳውያን ደስተኛ ስለመሆን ይህን ያህል የተጋነነ አመለካከት ቢኖራቸውም በተመቻቹ ሁኔታዎች ስር እንኳን የተሟላ ደስታ የላቸውም። ኤፊቆሮስ ‘የእግዚአብሔር ደስታ’ ስለ ሌለው ሕይወትን “አሳዛኝ ስጦታ” ብሎ ጠርቶታል። (ነህምያ 8:10) በአንፃሩ ግን የጥንት ክርስቲያኖች እንዴት ደስተኞች ነበሩ! ኢየሱስ ራስን በመጨቆን ደስታ የሌለውን ሕይወት ማበረታታቱ አልነበረም። እንዲያውም የእርሱን አርአያ መከተል ከሁሉ ወደ ላቀው ደስታ ይመራል።—ማቴዎስ 5:3-12
አንዳንድ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባሎች እምነታችንን አደጋ ላይ ሳንጥል የኤፊቆሮሳውያን ትምህርት ተጽእኖ ካሳደረባቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ እንችላለን ብለው ማሰባቸው ስህተት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤውን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት አንዳንዶቹ በትንሣኤ ላይ የነበራቸውን እምነት ቀደም ሲል አጥተው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:12-19
የኤፊቆሮሳውያን ትምህርት ዛሬም አለን?
ምንም እንኳ የኤፊቆሮሳውያን ትምህርት በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቢጠፋም በአሁኑ ሕይወታችን እንደሰት የሚል ተመሳሳይ አመለካከት የያዙ ሰዎች ዛሬም አሉ። እነዚህ ሰዎች አምላክ ተስፋ በሰጠው የዘላለም ሕይወት ላይ ትንሽ እምነት ይኖራቸው ወይም ምንም እምነት አይኖራቸው ይሆናል። ሆኖም አንዳንዶቹ ከሌሎች አንፃር ሲታዩ ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ይኖሯቸው ይሆናል።
አንድ ክርስቲያን እነዚህ ሰዎች ያላቸውን ጥሩ ሥነ ምግባር እንደ ማሳበቢያ በማድረግ ከእነርሱ ጋር የጠበቀ ቅርርብ ለመመስረት ይፈተን ይሆናል። ራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን የምንመለከት ባይሆንም እንኳ በረቀቀ መንገድ ተጽእኖ የሚያሳድሩብንን ሰዎች ጨምሮ “መጥፎ ባልንጀሮች” ሁሉ “መልካሙን አመል” እንደሚያጠፉ ማስታወስ አለብን።
ሕይወት የአሁኑ ብቻ ነው የሚለው ፍልስፍና በአንዳንድ የንግድ ሴሚናሮች፣ በራስ አገዝ መጻሕፍት፣ በልብ ወለድ መጻሕፍት፣ በፊልሞች፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በሙዚቃዎች በኩል ብቅ ይላል። ምንም እንኳ በቀጥታ የኃጢአተኝነት ባሕርይ ባያስፋፋም ይህ እምነት የለሽ አመለካከት በረቀቀ ሁኔታ ተጽእኖ ሊያሳድርብን ይችል ይሆን? ለምሳሌ ያህል ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት የተነሳው አከራካሪ ጥያቄ ጨርሶ እስኪዘነጋን ድረስ የራሳችንን ጉዳዮች በማሳደድ እንጠመድ ይሆን? ‘ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የበዛልን’ ከመሆን ይልቅ በአገልግሎቱ ‘ጥቂት በመሥራት’ ተዘናግተን ይሆን? ወይም የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች ትክክለኛነትና ጠቃሚነታቸውን በመጠራጠር አቅጣጫችንን ስተን ይሆን? ከሥነ ምግባር ብልግና፣ ከዓመፅና ከመናፍስትነት እንዲሁም ዓለማዊ አመለካከቶች ተጽእኖ ካሳደሩባቸው ሰዎች ራሳችንን መጠበቅ ያስፈልገናል!—1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ቆላስይስ 2:8
ስለዚህ በሙሉ ልባቸው የይሖዋን መመሪያ ከሚከተሉ ጋር ጓደኝነት እንመስርት። (ኢሳይያስ 48:17) እንዲህ ካደረግን መልካም አመላችን ይጎለብታል። እምነታችንም ይጠናከራል። ባሁኑ ጊዜ ተደስተን መኖር የምንችል ከመሆኑም በላይ ወደፊት የዘላለም ሕይወት ይጠብቀናል—መዝሙር 26:4, 5፤ ምሳሌ 13:20
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤፊቆሮስ፣ አማልክት ለሰው ዘር ምንም ግድ የላቸውም በማለት አስተምሯል
[ምንጭ]
Courtesy of The British Museum