የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ያስፈልገዋል
“የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”—ምሳሌ 2:5
1. የሰው ልብ ድንቅ የመለኮታዊ ሥራ ውጤት ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
በዚህ በአሁኑ ቅጽበት በመላው ምድር ላይ 5,600,000,000 የሚያክሉ ሰብዓዊ ልቦች በመምታት ላይ ናቸው። የእያንዳንዳችሁ ልብ በየቀኑ 100,000 ጊዜ እየመታ 7,600 ሊትር የሚያክል ደም የ100,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባሏቸው የደም ሥሮቻችሁ ይረጫል። የዚህን ድንቅ የሆነ የመለኮታዊ ሥራ ውጤት ያህል ከባድ ሥራ የሚሠራ የአካል ክፍል የለም።
2. ምሳሌያዊው ልብ እንዴት ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል?
2 በተጨማሪም በመላው ምድር ላይ 5,600,000,000 ምሳሌያዊ ልቦች አሉ። በምሳሌያዊው ልብ ውስጥ ስሜቶቻችን፣ ዝንባሌዎቻችንና ምኞቶቻችን ይኖራሉ። የሐሳባችን፣ የማስተዋል ችሎታችንና ፍላጎታችን መቀመጫ ምሳሌያዊ ልባችን ነው። ምሳሌያዊ ልባችን ትዕቢተኛ ወይም ትሑት፣ ሐዘንተኛ ወይም ደስተኛ፣ በጨለማ የተዋጠ ወይም የበራ ሊሆን ይችላል።—ነህምያ 2:2፤ ምሳሌ 16:5፤ ማቴዎስ 11:29፤ ሥራ 14:17፤ 2 ቆሮንቶስ 4:6፤ ኤፌሶን 1:16-18
3, 4. ምሥራቹ ለሰዎች ልብ እየተዳረሰ ያለው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ አምላክ የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። ምሳሌ 17:3 [የ1980 ትርጉም] “ወርቅና ብር በእሳት እንደሚፈተን እግዚአብሔርም የሰውን ልብ ይፈትናል” ይላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲሁ የሰዎችን ልብ እያነበበ ብቻ ፍርድ ከመስጠት ይልቅ በምሥክሮቹ አማካኝነት ምሥራቹ ወደ ሰዎች ልብ እንዲደርስ እያደረገ ነው። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ከተናገራቸው ቃላት ጋር የሚስማማ ነው፦ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?”—ሮሜ 10:13-15
4 ምሥክሮቹ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄደው “መልካሙን የምሥራች” እንዲናገሩና ተቀባይ ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልገው እንዲያገኙ የይሖዋ መልካም ፈቃድ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ ቁጥራችን ከ5,000,000 በላይ ሆኗል። አንድ የይሖዋ ምሥክር በአማካይ 1,200 ለሚያክሉ የምድር ሰዎች ይደርሳል ማለት ነው። ምሥራቹን በቢልዮን ለሚቆጠሩት የምድር ነዋሪዎች ማዳረስ ቀላል ሥራ አይደለም። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እየመራ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ እርሱ እየሳበ ነው። በዚህም ምክንያት በኢሳይያስ 60:22 ላይ የተመዘገበው ትንቢት በትክክል በመፈጸም ላይ ይገኛል። “ታናሹ ለሺህ፣ የሁሉም ታናሽ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል። እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” ይላል።
5. እውቀት ምንድን ነው? ስለ ዓለም ጥበብስ ምን ማለት ይቻላል?
5 ይህ የተፈጸመው በዚህ በአሁኑ ዘመን ሲሆን አንድ ነገር ግልጽ ሆኗል። በቢልዮን የሚቆጠሩት የምድር ሕዝቦች እውቀት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በመሠረቱ እውቀት ማለት በተሞክሮ፣ በምርምር ወይም በጥናት ከተገኘ ሐቅ ጋር መተዋወቅ ማለት ነው። ዓለም ብዙ እውቀት አካብቷል። እንደ መጓጓዣ፣ ጤና አጠባበቅና መገናኛ ባሉት መስኮች እድገት ተደርጓል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በአንደኛ ደረጃ የሚያስፈልገው ዓለማዊ እውቀት ነውን? በፍጹም አይደለም! የሰው ልጅ በጦርነት፣ በጭቆና፣ በበሽታና በሞት እየተሠቃየ ነው። የዓለም ጥበብ በበረሃ አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንደሚንከራተት አሸዋ ሆኗል።
6. ደምን በተመለከተ አምላክ የሚሰጠው እውቀትና ዓለማዊ ጥበብ የሚነጻጸሩት እንዴት ነው?
6 በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ሰውነትን መብጣት እንደ ጥሩ ሕክምና ይቆጠር ነበር። የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የነበሩት ጆርጅ ዋሽንግተን በሕይወታቸው የመጨረሻ ሰዓቶች በተደጋጋሚ ተበጥተው ነበር። በዚህ ጊዜ “ከእንግዲህ ብዙ ስለማልቆይ እባካችሁ ተውኝና ልሙት” ብለው ነበር። እንዳሉትም ይህን በተናገሩበት ቀን ታኅሣሥ 14, 1799 አርፈዋል። ዛሬ ደግሞ ደም ሥር መብጣት ቀርቶ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ደም በደም ሥር በኩል ወደ ሰውነት ማስገባት ነው። ሁለቱም ዘዴዎች ሞት የሚያስከትሉ ችግሮች ሆነው ተገኝተዋል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን የአምላክ ቃል “ከደም . . . ራቁ” ይል ነበር። (ሥራ 15:29) አምላክ የሚሰጠው እውቀት ሁልጊዜ ትክክለኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ዘመን የማይሽረው ነው።
7. ልጆችን ማሳደግ በተመለከተ ከቅዱስ ጽሑፉ የሚገኘው እውቀትና ዓለማዊ ጥበብ የሚነጻጸሩት እንዴት ነው?
7 የዓለም ጥበብ አስተማማኝ አለመሆኑን የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ለብዙ ዓመታት የሥነ ልቦና ሊቃውንት ልጆች እንደፈለጋቸው ሆነው ማደግ አለባቸው ብለው ይከራከሩ ነበር። ይሁን እንጂ ለዚህ አስተሳሰብ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ከነበሩት አንዱ ተሳስተው እንደነበረ አምነዋል። በአንድ ወቅት የጀርመን የሥነ ልሳን ማኅበር “በአሁኑ ጊዜ በወጣቶቻችን ረገድ ለገጠመን ችግር ቢያንስ በተዘዋዋሪ ሁኔታ ምክንያት የሆነው” ልጆች ስድ ተለቀው ማደጋቸው እንደሆነ ተናግሯል። ዓለማዊ ጥበብ በንፋስ እንደሚገፋ ያህል ወዲያና ወዲህ ቢዋዥቅም ትክክለኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ግን ሳይለወጥ ጸንቶ ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጆች አስተዳደግ ሚዛናዊ ምክር ይሰጣል። ምሳሌ 29:17 እንዲህ ይላል፦ “ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል።” ጳውሎስ “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት ስለጻፈ እንዲህ ያለው ተግሣጽ መሰጠት ያለበት በፍቅር ነው።—ኤፌሶን 6:4
‘የአምላክ እውቀት’
8, 9. የሰው ልጅ በአንደኛ ደረጃ የሚያስፈልገውን እውቀት በተመለከተ ምሳሌ 2:1-6 ስለሚናገረው ነገር ምን ማለት ይቻላል?
8 ምንም እንኳ ጳውሎስ ራሱ በወቅቱ የተማረ ሰው ቢሆንም እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና።” (1 ቆሮንቶስ 3:18, 19) የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን እውቀት ሊሰጠው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ምሳሌ 2:1-6 ስለዚህ እውቀት ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ።”
9 ጥሩ ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክ በሚሰጠው እውቀት በተገቢ መንገድ በመጠቀም ለጥበብ ልዩ ትኩረት ያደርጋሉ። የሚማሩትን ነገር በጥንቃቄ በማመዛዘን ልባቸው ወደ ማስተዋል እንዲያዘነብል ያደርጋሉ። ይህን በማድረጋቸውም ለማስተዋል ወይም የአንድ ርዕሰ ጉዳይ የተለያዩ ክፍሎች እንዴት እርስ በርሳቸው እንደሚዛመዱ ለመረዳት ለሚያስችለው ግንዛቤ ድምፃቸውን ያነሳሉ። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ብር ወይም የተቀበረ ንብረት ቆፍሮ እንደሚያወጣ ሰው በትጋት ይሠራሉ። ይሁን እንጂ ተቀባይ ልብ ያላቸው ሰዎች የሚያገኙት ትልቅ ሀብት ምንድን ነው? ‘አምላክ የሚሰጠውን እውቀት’ ያገኛሉ። ይህ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ምንድን ነው? በቀላል አነጋገር የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውቀት ነው።
10. ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት እንዲኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
10 አምላክ የሚሰጠው እውቀት አስተማማኝ፣ የማይለዋወጥ፣ ሕይወት ሰጪና ጠንካራ መሠረት ያለው ነው። መንፈሳዊ ጤንነት ያዳብራል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደሚከተለው ሲል መክሮታል፦ “ከእኔ የሰማኸውን የጤናማ ቃላት ሥርዓት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዝምድና ካለው እምነትና ፍቅር ጋር ጠብቅ። ይህን መልካም አደራ በእኛ በሚኖር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ።” (2 ጢሞቴዎስ 1:13 አዓት) እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ የቃላት ሥርዓት አለው። በተመሳሳይም የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነት የያዘው “ንጹሕ ልሳንም” በዋነኛነት በመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ላይ የተመሠረተ “የጤናማ ቃላት ሥርዓት” አለው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ደግሞ የይሖዋ ልዕልና በመንግሥቱ አማካኝነት መረጋገጡ ነው። (ሶፎንያስ 3:9) ይህን የጤናማ ቃላት ሥርዓት በአእምሮአችንና በልባችን ውስጥ ማኖር ያስፈልገናል። ምሳሌያዊ ልባችን እክሎች እንዳይገጥሙት ለመጠበቅና በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነን ለመኖር ከፈለግን ቅዱሳን ጽሑፎችን በዕለታዊ ኑሯችን ሥራ ላይ ማዋልና አምላክ “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት ባዘጋጀልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ቲቶ 2:2) አምላክ የሚሰጠው እውቀት ለጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ምን ጊዜም አንዘንጋ።
11. የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት እንደሚያስፈልገው የሚጠቁሙት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
11 በቢልዮን የሚቆጠሩት የምድር ነዋሪዎች አምላክ የሚሰጠው ይህ ልዩ የሆነ እውቀት የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ሌሎች ምክንያቶችን እንመርምር። ሁሉም ሰዎች ምድርና የሰው ልጅ እንዴት እንደተገኙ ያውቃሉን? አያውቁም። ሁሉም የሰው ልጆች እውነተኛውን አምላክና ልጁን ያውቃሉን? አያውቁም። ሰይጣን በመለኮታዊው ልዕልናና በሰው ልጆች ፍጹም አቋም ጠባቂነት ላይ ስላስነሳው ክርክር ሁሉም ሰው ያውቃልን? አሁንም አያውቅም። ሰዎቸ በአጠቃላይ ለምን እንደምናረጅና እንደምንሞት ያውቃሉን? አሁንም እንደገና አያውቁም ብለን ለመመለስ እንገደዳለን። የአምላክ መንግሥት ሰማይ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለና በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር መላው የምድር ነዋሪ ይገነዘባልን? ስለክፉ መናፍስታዊ ኃይላት ያውቃሉን? ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ እንዴት እንደሚመሠርቱ አስተማማኝ የሆነ እውቀት አግኝተዋልን? ፈጣሪያችን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ያዘጋጀው ዓላማ በገነት ውስጥ በደስታ መኖር እንደሆነ ብዙሐኑ ሕዝብ ያውቃልን? ለእነዚህም ጥያቄዎች መልሳችን አሉታዊ ነው። እንግዲያውስ የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ያስፈልገዋል።
12. አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ልናመልከው የምንችለው እንዴት ነው?
12 የሰው ልጅ ከአምላክ የሚገኝ እውቀት ለምን እንደሚያስፈልገው የሚያሳየውን ተጨማሪ ምክንያት ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ የመጨረሻ ሌሊት ባቀረበው ጸሎት ውስጥ ጠቅሷል። “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ሲሰሙ ሐዋርያት በጥልቅ ተነክተው መሆን አለበት። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ያለውን እውቀት በገቢር መተርጎም አምላክን ተቀባይነት ባለው መልኩ ለማገልገል የሚያስችል ብቸኛ መንገድ ነው። ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24) አምላክን “በመንፈስ” የምናመልከው በእምነትና በፍቅር የተሞላ ልብ ሲያንቀሳቅሰን ነው። ‘በእውነትስ’ የምናመልከው እንዴት ነው? ቃሉን በማጥናትና ከገለጠልን እውነቱ ጋር ማለትም ‘ከአምላክ እውቀት’ ጋር ተስማምተን ስናመልከው ነው።
13. በሥራ 16:25-34 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ምን ዓይነት አጋጣሚ ነው? ከዚህስ ምን እንማራለን?
13 በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን ማምለክ ይጀምራሉ። ይሁንና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የግድ አስፈላጊ ነው ወይስ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ጥምቀት ደረጃ እንዲደርሱ መርዳት ይቻላል? ሥራ 16:25-34 ላይ የተጠቀሰው የወህኒ ቤት ዘበኛና ቤተሰቡ ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ታስረው ነበር። እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነና የእስር ቤቱ በሮች ተከፈቱ። የወህኒ ቤቱ ዘበኛ እስረኞቹ በሙሉ ያመለጡ መሰለውና የሚደርስበትን ከባድ ቅጣት በመፍራት ራሱን ሊገድል ሲል ጳውሎስ ሁሉም ያሉ መሆናቸውን ነገረው። ጳውሎስና ሲላስም “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሯቸው።” ይህ ዘበኛም ሆነ ቤተሰቡ አይሁዳውያን ስላልነበሩ ምንም ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት አልነበራቸውም። ቢሆንም በዚያችው ሌሊት አማኞች ሆኑ። ከዚህም አልፎ “ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ።” እነዚህ አጋጣሚዎች እንግዳ ነበሩ። ይሁን እንጂ አዳዲስ ሰዎች መሠረታዊ እውነቶችን ከተማሩ በኋላ ሌሎቹን ተጨማሪ ነገሮች ከጉባኤ ስብሰባዎች ይማሩ ነበር። ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መቻል ይኖርብናል።
መከሩ ብዙ ነው!
14. አጠር ባለ ጊዜ በርከት ያሉ ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
14 የይሖዋ ምሥክሮች አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ቢችሉ በጣም ጥሩ ይሆናል። ይህን ማድረግ መቻላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ አገሮች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርላቸው ተመዝግበው ተራ እስኪደርሳቸው ለመጠበቅ ተገደዋል። በሌሎች አካባቢዎችም እንዲህ ያለ ሁኔታ ይታያል። በዶሚኒካን ሪፓብሊክ በሚገኝ አንድ ትንሽ ከተማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ሰዎች በጣም በመብዛታቸው በዚያ የሚኖሩት አምስት ምሥክሮች ሁሉንም ጥናቶች ለመምራት አልቻሉም። ታዲያ ምን አደረጉ? እነዚህ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙና ተራ ሲደርሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደሚመራላቸው ነግረዋቸዋል። በምድር ዙሪያ በሚገኙ ብዙ ቦታዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል።
15, 16. አምላክ የሚሰጠውን እውቀት በበለጠ ፍጥነት ለማሰራጨት ምን ተዘጋጅቶልናል? ይዘቱስ ምን ይመስላል?
15 ለአምላክ ሕዝቦች ሠፊ የአገልግሎት ክልል ማለትም መከር የሚሰበስቡበት ትልቅ መስክ እየተከፈተላቸው ነው። “የመከሩ ጌታ” የሆነው ይሖዋ ተጨማሪ ሠራተኞችን እየላከ ቢሆንም ገና ብዙ ሥራ አለ። (ማቴዎስ 9:37, 38) አምላክ የሚሰጠውን እውቀት በበለጠ ፍጥነት ለማሰራጨት እንዲቻል ‘ታማኙ ባሪያ’ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከእያንዳንዱ ትምህርት በኋላ በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የሚያስችል በተወሰኑ ርዕሶች ላይ የሚያተኩር አጠር ያለ ጽሑፍ አዘጋጅቷል። አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ከተቻለም በጥቂት ወራት በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊሸፈን የሚችል አዲስ ጽሑፍ ነው። በቀላሉ በቦርሳችን ወይም በኪሳችን እንኳ ሳይቀር ሊያዝ የሚችል ነው! በ“ደስተኛ አወዳሾች” የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን ይህን ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።
16 በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጁአቸው የተለያዩ ክፍሎች አንድ ላይ ተጠናቅረው እውቀት የተባለው ይህ መጽሐፍ ተዘጋጅቷል። ስለዚህ መጽሐፉ ለመላው ዓለም አንባቢዎች እንዲጥም ሆኖ የተዘጋጀ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ እስኪወጣ ድረስ ብዙ ጊዜ ይቆይ ይሆን? ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ ከትላልቅ መጻሕፍት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊተረጎም ስለሚችል ረዥም ጊዜ አይፈጅም። እስከ ጥቅምት 1995 ድረስ የአስተዳደር አካሉ የጽሑፍ ኮሚቴ ይህ መጽሐፍ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደ ሌሎች ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ሰጥቷል።
17. እውቀት በተባለው መጽሐፍ መጠቀምን ቀላል የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
17 እውቀት በተባለው መጽሐፍ በእያንዳንዱ ምዕራፍ የሠፈሩት ዝርዝር ሐሳቦች አንባቢዎቹ ፈጠን ያለ መንፈሳዊ እድገት እንዲያሳዩ የሚያስችሉ ናቸው። መጽሐፉ እውነትን የሚያስተዋውቀው አዎንታዊ በሆነ መንገድ ነው። የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን ስለማጋለጥ ብዙም ትኩረት አይሰጥም። አቀራረቡና የሐሳቦቹ ቅደም ተከተል በጣም ግልጽ በመሆኑ መጽሐፉን ተጠቅሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራትና ሰዎች አምላክ የሚሰጠውን እውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል አስቸጋሪ አይሆንም። ሐሳቦቻቸው ሙሉ በሙሉ ከተጻፉት ጥቅሶች በተጨማሪም ቁጥራቸውና ምዕራፋቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶች አሉ። ተማሪዎች ለውይይት በሚዘጋጁበት ጊዜ እነዚህን ጥቅሶች አውጥተው እንዲያነቡ መበረታታት ይኖርባቸዋል። በጥናቱም ወቅት ጊዜ በፈቀደ መጠን አውጥቶ ማንበብ ይቻላል። ይሁን እንጂ ዋናዎቹ ነጥቦች ጉልህ ሆነው እንዳይታዩ የሚያደርጉ በርካታ ሐሳቦች ከውጭ መጨመር ጥበብ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፉ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ሊያረጋግጥ የፈለገውን ነገር በሚገባ ለመረዳትና ለተማሪው ለማስገንዘብ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ አስተማሪው ራሱ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በአእምሮው ውስጥ ግልጽ ሆነው እንዲታዩት መጽሐፉን በትጋት ማጥናት ይኖርበታል።
18. እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ረገድ ምን ሐሳቦች ቀርበዋል?
18 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ሊያፋጥን የሚችለው እንዴት ነው? ይህ 192 ገጾች ያሉት መጽሐፍ አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ ተጠንቶ ሊያልቅ ከመቻሉም በላይ ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች’ መጽሐፉን በማጥናት ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ የሚያስችላቸውን እውቀት ለማግኘት ይችላሉ። (ሥራ 13:48 አዓት) እንግዲያውስ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በአገልግሎታችን በሚገባ እንጠቀምበት። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሌላ መጽሐፍ ብዙ ምዕራፎች ያገባደደ ከሆነ የጀመረውን መጨረሱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አለበለዚያ ግን ጥናቱን እውቀት ወደ ተባለው መጽሐፍ ማስለወጡ የተሻለ ይሆናል ብለን እናምናለን። ይህን አዲስ መጽሐፍ ከጨረሰ በኋላ ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍ ማስጠናቱን አናበረታታም። እውነትን የተቀበሉ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በግላቸው በማንበብ እውቀታቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ።—2 ዮሐንስ 1
19. እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራታችን በፊት አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 175 እስከ 218 መከለሱ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
19 እውቀት የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሽማግሌዎች ካልተጠመቁ አስፋፊዎች ጋር የሚከልሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲረዳው ታስቦ ነው። በመሆኑም ጥናቶቻችሁን ወደዚህ መጽሐፍ ከማዛወራችሁ በፊት አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 175 እስከ 218 ያሉትን ጥያቄዎች ለጥቂት ጊዜ በግላችሁ ብትከልሱ ጥሩ ይሆናል።a እንዲህ ማድረጋችሁ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በምታስጠኑበት ጊዜ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ጠበቅ እንድታደርጉ ይረዳችኋል።
20. ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?
20 በየትም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን መስማት ይኖርባቸዋል። አዎን፣ መላው የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ያስፈልገዋል። ይሖዋ ደግሞ ይህን እውቀት ለማዳረስ በምሥክሮቹ ይጠቀማል። አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ያዘጋጀልንን አዲስ መጽሐፍ አግኝተናል። ይህን መጽሐፍ እውነትን ለሰዎች ለማስተማርና ለይሖዋ ስም ክብር ለማምጣት ትጠቀሙበታላችሁን? ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ የተቻላችሁን ሁሉ ጥረት ስታደርጉ ይሖዋ አብዝቶ እንደሚባርካችሁ ምንም አያጠራጥርም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ምሳሌያዊው ልብ እንዴት ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል?
◻ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ምንድን ነው?
◻ የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ማግኘት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
◻ ምን አዲስ መጽሐፍ ተዘጋጅቶልናል? እንዴት ልትጠቀሙበት አቅዳችኋል?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የሚሰጠው እውቀት በቢልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች አስፈላጊ የሆነባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ