ትክክለኛ ፍርድ መቼና እንዴት?
ወንጀል ያልፈጸመ ሰው የሚፈራበት ምንም ምክንያት የለም። እርግጥ ነው በተቻለ መጠን ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሕግ ባለው አገር የሚኖሩ ዜጎች ሁሉ አመስጋኝ የሚሆኑበት በቂ ምክንያት አላቸው። ይህ የሕግ ሥርዓት የረቀቁ ሕጎች፣ እነዚህን ሕጎች የሚያስከብር የፖሊስ ኃይልና ፍትሕ የሚያስፈጽሙ ፍርድ ቤቶችን አካቶ የያዘ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች “በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች” ተገዙ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር በመስማማት የሚኖሩበት አገር ያወጣውን የሕግ ሥርዓት ያከብራሉ።—ሮሜ 13:1-7
ይሁን እንጂ በተለያዩ አገሮች በፍርድ አሠራር ረገድ ጎጂና አሳፋሪ የሆኑ ስህተቶች ተፈጽመዋል።a ጥፋተኛውን ከመቅጣትና ንጹሑን ከመጠበቅ ይልቅ አንዳንድ ጊዜ ባልፈጸሙት ወንጀል ንጹሐን ሰዎች እንዲቀጡ ተደርገዋል። ሌሎች ግለሰቦች ደግሞ በጥርጣሬ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ጉዳያቸው ተጣርቶ እስከሚፈቱ ድረስ በርካታ ዓመታት በእስር ቤት ያሳልፋሉ። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች ለሁሉም ያልተዛባ ፍርድ የሚበየንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚመጣ ከሆነስ መቼና እንዴት? ንጹሐን ሰዎችን ይታደጋል ብለን በማን ላይ ልንታመን እንችላለን? በተዛባ ፍርድ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ምን ተስፋ ይኖራቸዋል? ብለው ይጠይቃሉ።
የተዛባ ፍርድ
አንዲት እናት ሁለት ሴት ልጆቿን ገድላለች ተብሎ የተፈረደባት የዕድሜ ልክ እስራት ጀርመን በ1980ዎቹ ዓመታት ማለትም “ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ካጋጠሟት የፍርድ ጉዳዮች ሁሉ ይበልጥ ትኩረት የሳበ ነበር።” ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ በሴትዮዋ ላይ የቀረበው ክስ እንደገና ታየና ጉዳይዋን በይደር በማቆየት ተለቀቀች። ዲ ሳይት በ1995 ሲዘግብ በመጀመሪያ የተተላለፈው ብያኔ “የተሳሳተ እንደነበረ ማረጋገጥ ይቻል ነበር” ብሏል። ይህ ርዕስ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ይህች ሴት ጥፋተኛ ትሁን ወይም ንጹሕ ሳይረጋገጥ ለዘጠኝ ዓመታት በእስር ቤት ቆይታለች።
በኅዳር 1974 አንድ ምሽት ላይ በእንግሊዝ በበርሚንግሃም ማዕከላዊ ከተማ ሁለት ቦምቦች ፈንድተው ከተማዋን አናውጠዋት ነበር። በዚህም ፍንዳታ 21 ሰዎች ተገድለዋል። ይህ “ማንም የበርሚንግሃም ነዋሪ ፈጽሞ የማይረሳው” ክስተት ነው በማለት የፓርላማ አባል የሆኑት ክሪስ ሙለን ጽፈዋል። ከጊዜ በኋላ “ስድስት ንጹሐን ሰዎች በብሪታኒያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ የነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰሱ።” በመጨረሻም 16 ዓመታት በእስር ቤት ከማቀቁ በኋላ ከተወነጀሉበት ክስ ነፃ ተለቀቁ!
ኬን ክሪስፕን የተባሉ አንድ የሕግ አማካሪ “በአውስትራሊያ የሕግ ታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ በዓይነቱ ልዩ ስለሆነና የብዙዎችን ትኩረት ስለ ሳበ” የፍርድ ጉዳይ ዘግበዋል። አንድ ቤተሰብ አየርስ ሮክ አቅራቢያ መኖር እንደጀመሩ ሕፃን ልጃቸው የት እንደገባች ሳይታወቅ ጠፋች። እናትየው በግድያ ወንጀል ተከሰሰችና የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባት። ከሦስት ዓመት በላይ እስር ቤት ከቆየች በኋላ በ1987 የተደረገው ይፋዊ ምርመራ በሴትዮዋ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች በጥፋተኝነት ሊያስጠይቋት እንደማይችሉ አረጋገጠ። ምሕረት ተደርጎላት ተለቀቀች።
በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ትኖር የነበረች አንዲት የ18 ዓመት ወጣት ሴት በ1986 ተገደለች። አንድ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ተወንጅሎ የሞት ፍርድ ተበየነበት። ከወንጀሉ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንደሌለው እስኪረጋገጥ ድረስ የሞት ፍርድ እየተጠባበቀ ለስድስት ዓመታት በእስር ቤት ቆየ።
በፍርድ ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙት እንዲህ ዓይነቶቹ ስህተቶች አልፎ አልፎ ብቻ የሚከሰቱ ናቸውን? የፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ ሩዶፍስኪ “በፍርድ አሰጣጥ ለ25 ዓመታት ያክል ያሳለፍኩ ሲሆን በርካታ ጉዳዮችንም ተመልክቻለሁ። ምንም ዓይነት በደል ሳይፈጽሙ የሚወነጀሉት ሰዎች . . . ከአምስት እስከ 10 በመቶ ይደርሳሉ ብዬ እገምታለሁ።” ክሪስፕን “ምንም ዓይነት ወንጀል ሳይፈጽሙ በእስር ቤት የተጣሉ ኃዘንና ትካዜ የዋጣቸው ሌሎች ሰዎች ይኖሩ ይሆን?” በማለት አሳዛኝ ጥያቄ ያቀርባሉ። እንደዚህ ያሉ አሳዛኝ ስህተቶች ሊፈጸሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
ሰብዓዊ ድክመት የሚታይበት የፍርድ አሠራር
በ1991 የብሪታንያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት “የትኛውም የሰው ሥርዓት ፍጹም ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም” ሲል በአጽንኦት ተናግሯል። አንድ የፍርድ አሠራር ትክክልና እምነት የሚጣልበት መሆኑ የተመካው ሕጉን በሚያረቅቁትና በሚያስፈጽሙት ሰዎች ላይ ነው። ሰዎች ስህተት ለመፈጸም፣ እምነት ለማጉደልና ወገናዊ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው። በመሆኑም ሰብዓዊ የፍርድ አሠራር እንዲህ የመሰሉ ጉድለቶች ቢታዩበት ምንም አያስገርምም።
እንደ ጀርመናዊው ዳኛ ሮልፍ ቤንድር አባባል 95 በመቶ ለሚሆኑ ወንጀሎች ምሥክሮች የሚሰጡት ቃል እንደ ጠንካራ ማስረጃ ተደርጎ ይታያል። ይሁን እንጂ እነዚህ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን የሚሰጡ ምሥክሮች ሁልጊዜ ሐቁን ይናገራሉ? ዳኛ ቤንድር እንደዚያ አይሰማቸውም። ችሎት ፊት ከሚቀርቡት ምሥክሮች መካከል ግማሽ የሚሆኑት እውነት እንደማይናገሩ ይገምታሉ። በጀርመን ሙኒክ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የወንጀለኛ መቅጫ ፕሮፌሰር የሆኑት በርንት ሹኔማን ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል። ዲ ሳይት ላደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ሹኔማን ሲመልሱ ምሥክሮች የሚሰጡት ቃል ምንም እንኳ የማያስተማምን ቢሆንም እንደ ዋነኛ ማስረጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል። “በፍትሕ ላይ ለሚፈጸሙት ስህተቶች ዓይነተኛ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው ዳኛው በማያስተማምኑ የምሥክሮች ቃል ላይ መታመኑ ነው።”
ምሥክሮችም ሆኑ ፖሊሶች ሊሳሳቱ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ የሕዝብን ቁጣ የሚያነሳሳ አንድ ዓይነት ወንጀል ሲፈጸም ፖሊስ ያገኘውን ሁሉ እንዲያስር ይገደዳል። እንዲህ የመሰለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ አንዳንድ ፖሊሶች የሃሰት ማስረጃ የማሰባሰብ ወይም ተጠርጣሪው እንዲያምን የማስገደድ ፈተና ውስጥ ወድቀዋል። በበርሚንግሃም ለደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ተወንጅለው የነበሩት ስድስቱ ሰዎች ከእስር በተለቀቁ ጊዜ ዚ ኢንዲፔንደት የተሰኘው የብሪታኒያ ጋዜጣ “ፖሊስ በሃሰት የወነጀላቸው ስድስት ሰዎች” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ዘ ታይምስ በዘገበው መሠረት “ፖሊስ ዋሽቷል፣ ተንኮል ሠርቷል እንዲሁም አጭበርብሯል።”
አንዳንድ ፖሊስ ወይም ሕዝብ በመሠረተ ቢስ ጥላቻ ተነሳስቶ አንድን ዓይነት ዘር፣ ሃይማኖት ወይም የአንድን አገር ዜጋ በጥርጣሬ ሊመለከት ይችላል። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የሰጠው አስተያየት እንደሚያመለክተው አንድ የወንጀል ጉዳይ “የተፈጸመውን ወንጀል በትክክል ከማየት ጉዳዩ ወደ ዘረኝነት” ይለወጣል።
አንድ ጉዳይ ችሎት ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ውሳኔው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ምሥክሮች የሚሰጡት ቃል ብቻ ሳይሆን ቴክኒካዊ ማስረጃዎችም ናቸው። የረቀቁ ቴክኒካዊ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈለሰፉ በመሄዳቸው ዳኞች ወይም የእማኝ ዳኞች ወንጀሉ በተፈጸመበት መሣሪያ ወይም በእጅ አሻራ፣ በእጅ ጽሑፍ፣ በደም ዓይነት፣ በጠጉር ቀለም፣ በልብስ ቁራጭ ወይም በዲ ኤን ኤ ናሙናዎች መሠረት አንድን ሰው ወንጀለኛ ወይም ከወንጀል ነፃ መሆኑን እንዲፈርዱ ሊጠየቁ ይችላሉ። አንድ ጠበቃ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቶች “ከፊታቸው ቆመው ውስብስብ ሂደቶችን የሚያብራሩ በርካታ ሳይንቲስቶች በሚሰጡት መግለጫ ግራ ይጋባሉ።”
ከዚህም በላይ ኔቸር የተባለው መጽሔት እንደተናገረው ቴክኒካዊ በሆኑ የወንጀል ምርመራ ውጤቶች ላይ በሚሰጡት ትርጉሞች ሁሉም ሳይንቲስቶች አይስማሙም። “ቴክኒካዊ የወንጀል ምርመራ በሚያካሄዱ ሳይንቲስቶች መካከል ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል።” የሚያሳዝነው “የተሳሳቱ ቴክኒካዊ የወንጀል ምርመራ ውጤቶች ለብዙዎቹ የተሳሳቱ ብያኔዎች መከሰት ምክንያት መሆናቸው ነው።”
በየትም ቦታ እንኑር በአሁኑ ጊዜ ያሉ የፍርድ አሠራሮች ሰብዓዊ ድክመቶችን የሚያንጸባርቁ ናቸው። ታዲያ ንጹሐን ፍትሐዊ ፍርድ ሊያገኙ የሚችሉት ከማን ነው? ፍትሐዊ ፍርድ ይሰፍናል ብለን በተስፋ ልንጠባበቅ እንችላለን? በተዛባ ፍርድ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
“እኔ ይሖዋ ፍትሕን የምወድድ ነኝ”
አንተ ወይም ከቤተሰብህ አባል መካከል አንዱ በተዛባ ፍርድ በደል ደርሶባችሁ ከሆነ ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ በምን ሁኔታ ሥር እንዳላችሁ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በታሪክ ዘመን ሁሉ ከሁሉም የከፋ ግፍ የተፈጸመው ክርስቶስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በተገደለ ጊዜ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ “ኃጢአት አላደረገም” በማለት ይነግረናል። ሆኖም በሐሰት ምሥክሮች ተከሶ እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ ተገደለ።—1 ጴጥሮስ 2:22፤ ማቴዎስ 26:3, 4, 59-62
ይሖዋ እንዲህ የመሰለ በደል በልጁ ላይ ሲፈጸም እንዴት ተሰምቶት እንደነበረ ገምቱ። ከዋና ዋናዎቹ የይሖዋ ባሕርያት መካከል አንዱ ፍትሕ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትህ ናቸውና” በማለት ይነግረናል።—ዘዳግም 32:4 NW፤ መዝሙር 33:5
ይሖዋ ለእስራኤላውያን ተወዳዳሪ የማይገኝለት የፍትሕ ሥርዓት ሰጣቸው። የነፍስ ግድያ ቢፈጸምና ገዳዩ ግን ባይታወቅ ለተገደለው ሰው መሥዋዕት በማቅረብ ይሸፈን ነበር። ለእያንዳንዱ ወንጀል እልባት ለማግኘት ሲባል ንጹህ በሆነ ግለሰብ ላይ እንዲፈርዱ የሚያደርጋቸው ተጽዕኖ አልነበረባቸውም። ማንም ሰው ቢሆን በጥርጣሬ ወይም በአንዳንድ ሳይንሳዊ በሆኑ መረጃዎች ብቻ ሊፈረድበት አይችልም ነበር። የግድ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጉ ነበር። (ዘዳግም 17:6፤ 21:1-9) ይሖዋ ከፍተኛ የአቋም ደረጃ እንዳለውና ፍትሕ ተገቢ በሆነ መንገድ መፈጸሙ እንደሚያሳስበው እነዚህ ምሳሌዎች ያሳያሉ። በእርግጥም “እኔ ይሖዋ ፍትሕን የምወድድ ነኝ” ማለቱ ትክክል ነው።—ኢሳይያስ 61:8 NW
እርግጥ ነው በእስራኤላውያን ዘንድ የነበረውን የፍትሕ ሥርዓት የሚያስፈጽሙት የእኛ ዓይነት ጉድለት የነበረባቸው ሰብዓዊ ሰዎች ነበሩ። ሕጉ በተሳሳተ መንገድ ሥራ ላይ የዋለበት ጊዜም ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን “በአገሩ ድሆች ሲገፉ፣ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ” በማለት ጽፏል።—መክብብ 5:8
ይሖዋ በልጁ ላይ የተፈጸመውን የፍትሕ መጓደል ማስተካከል ይችል ነበር። ኢየሱስ በዚህ ላይ የነበረው ሙሉ ትምክህት ‘በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል እንዲታገሥ’ ኃይል ሰጥቶታል። በተመሳሳይም መሲሑ በሚያስተዳድረው ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ የመኖር አስደሳች ተስፋ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ የምንሰማውንም ሆነ ሌላው ቀርቶ የሚደርስብንን የፍትሕ መጓደል እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል። ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ሊስተካከል የማይችል ምንም ዓይነት ጥፋት ወይም ጉዳት አይኖርም። ሌላው ቀርቶ በተዛባ ፍርድ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች እንኳን በትንሣኤ ይነሳሉ።—ዕብራውያን 12:2፤ ሥራ 24:15
በተዛባ ፍርድ ምክንያት በደል ደርሶብንም ከሆነ ብዙዎቹ የፍትሕ ሥርዓቶች ሁኔታዎችን ለማስተካከል እንድንችል የሚረዱ ይግባኝ የማለት መብት በመስጠታቸው አመስጋኝ ልንሆን እንችላለን። ክርስቲያኖች በእዚህ የይግባኝ መብት መጠቀም ይችላሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ፍጽምና የጎደለው የፍርድ አሠራር እንደገና ማዋቀር የሚያስፈልገው የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ነጸብራቅ መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። አምላክ ይህን በቅርቡ ይፈጽማል።
በቅርቡ ይሖዋ ይህን ፍትሕ አልባ የነገሮች ሥርዓት አስወግዶ በምትኩ ‘ጽድቅ የሚኖርበትን’ አዲስ ሥርዓት ያመጣል። በዚያን ጊዜም ፈጣሪያችን በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ፍትሕ እንደሚያሰፍን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እያንዳንዱ ሰው እውነተኛ ፍትሕ የሚያገኝበት ጊዜ ቀርቧል! እንዲህ ያለውን ተስፋ ማወቃችን ምንኛ አመስጋኞች ነን።—2 ጴጥሮስ 3:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመጠበቂያ ግንብ ዓላማ በዚህ ርዕስ ውስጥ ጉዳያቸው የተነሳው ግለሰቦች ጥፋተኛ ናቸው ወይም አይደሉም የሚል ሐሳብ ማቅረብ ወይም ደግሞ የአንዱን አገር የፍርድ አሰጣጥ ለመደገፍና የሌላውን ለመንቀፍ አይደለም። እንዲሁም መጽሔቱ የአንዱ አገር የፍትሕ ሥርዓት ከሌላው እንደሚሻል የድጋፍ ሐሳብ አይሰጥም። ከዚህም በላይ ይህ መጽሔት አንዱ ዓይነት ቅጣት ከሌላው የተሻለ እንደሆነ አይናገርም። ይህ ርዕስ በተዘጋጀበት ወቅት በሰፊው የታወቁ ጉዳዮችን መግለጹ ብቻ ነው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ፍጽምና የጎደላቸው የፍትሕ ሥርዓቶች ብልሹ ከሆነው መስተዳድር፣ ከረከሰ ሃይማኖትና በሥነ ምግባር ካዘቀጠው ንግድ ጋር ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልጋቸው የሰብዓዊ ኅብረተሰብ ነጸብራቅ ናቸው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡት ማጽናኛ
ኅዳር 1952 ዴሪክ ቤንትሊ እና ክሪስቶፈር ክሬግ በእንግሊዝ፣ ለንደን አቅራቢያ በክሮይደን የሚገኝ አንድ መጋዘን ሰብረው ገብተው ይዘርፋሉ። ቤንትሊ 19 ዓመቱ ሲሆን ክሬግ ደግሞ 16 ዓመቱ ነበር። ፖሊስ ተጠርቶ ሲመጣ ክሬግ አንዱን ፖሊስ ተኩሶ ይገድላል። ክሬግ ዘጠኝ ዓመት እንዲታሰር ሲፈረድበት ቤንትሊ ግን ጥር 1953 በነፍስ ግድያ ወንጀል በስቅላት ተገደለ።
የቤንትሊ እህት አይሪስ ወንድሟ የነፍስ ግድያ ወንጀል አለመፈጸሙን ለማሳወቅ ለ40 ዓመታት ለፍታለች። በ1993 የዘውድ ሥርዓቱ ዴሪክ ቤንትሊ በስቅላት መገደል እንዳልነበረበት በማመን ፍርዱን በማስመልከት ይቅርታ ጠየቀ። አይሪስ ሌት ሂም ሃቭ ጀስቲስ በተባለው መጽሐፏ ውስጥ ጉዳዩን በማስመልከት ጽፋለች:-
“ግድያው ከመፈጸሙ ከአንድ ዓመት አካባቢ በፊት ዴሪክ አንዲት የይሖዋ ምሥክር መንገድ ላይ አግኝቶ ነበር . . . እህት ሌን የምትኖረው ከእኛ ብዙም በማይርቀው በፌይርቪው ጎዳና ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እንዲያዳምጥ ዴሪክን ቤቷ ጋበዘችው። . . . ጥሩ አጋጣሚ የነበረው ደግሞ እህት ሌን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘ የቴፕ ክር ስለ ነበራት [ዴሪክ እምብዛም ማንበብ ስለማይችል] አዋሰችው። . . . ቤት ሲመጣ እርሷ የነገረችውን ከሞትን በኋላ እንደገና እንነሳለን የሚሉ የመሰሉ ነገሮችን ይነግረኝ ነበር።”
አይሪስ ቤንትሊ ወንድሟ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ጠይቃው ነበር። ምን ተሰምቶት ነበር? “እህት ሌን የነገረችው ነገሮች ሁሉ በእነዚያ ጥቂት ቀናት ውስጥ ረድተውት ነበር።”—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
በፍትሕ መጓደል ምክንያት ሥቃይ ደርሶብህ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን እውነቶች ብታነብና ብታሰላስልባቸው ጥሩ ይሆናል። ይሖዋ አምላክ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ’ ስለሆነ ትልቅ ማጽናኛ ሊሰጥህ ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ በተገደለበት ወቅት አስደንጋጭ የፍትሕ መጓደል ተፈጽሟል