የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ነሐሴ 1
    • የአንባቢያን ጥያቄዎች

      ኢዮብ ይኖር በነበረበት ዘመን ለይሖዋ ታማኝ የነበረው ሰው እሱ ብቻ እንደሆነ አድርገን ከኢዮብ 1:8 መረዳት ይኖርብናልን?

      አይኖርብንም። እንደሚከተለው ከሚለው የኢዮብ 1:8 ጥቅስ እንደዚህ ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም።

      “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው።” አምላክ በኢዮብ 2:3 ላይም ሰይጣንን “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምን ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” ብሎ በመጠየቅ ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል።

      አምላክ ታማኝ አድርጎ የተቀበለው ሰው ኢዮብ ብቻ እንዳልነበረ የኢዮብ መጽሐፍ ራሱ ያመለክታል። ከምዕራፍ 32 ጀምረን ስለ ኤሊሁ እናነባለን። ምንም እንኳን ኤሊሁ ወጣት ቢሆንም የኢዮብን የተሳሳተ አመለካከት በማስተካከል እውነተኛውን አምላክ ከፍ ከፍ አድርጓል።—ኢዮብ 32:6 እስከ 33:6, 31-33፤ ኢዮብ 35:1 እስከ 36:2

      እንዲሁም ‘በምድር ላይ እንደ ኢዮብ ያለ ማንም የለም’ የሚለው የአምላክ አነጋገርም ቢሆን ኢዮብ በጻድቅነቱ በተለይ ከሌሎች ጎልቶ የሚታውቅ ነው ማለቱ ነው። ኢዮብ የኖረው ዮሴፍ በግብጽ ውስጥ በሞተበትና ሙሴ የአምላክ ነብይ ሆኖ ማገልገል በጀመረበት ጊዜ መካከል ነው። በዚህ ወቅት ብዙ እስራኤላውያን በግብፅ ይኖሩ ነበር። ሁሉም እስራኤላውያን ታማኝ አልነበሩም፣ በአምላክ ዘንድም ተቀባይነት አልነበራቸውም ብለን ለማሰብ ምንም ምክንያት አይኖረንም። በይሖዋ ላይ ትምክህት የነበራቸው ብዙ እስራኤላውያን ይኖራሉ። (ዘጸአት 2:1-10፤ ዕብራውያን 11:23) ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ እንደ ዮሴፍ ወይም የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ መርቶ እንዳወጣው እንደ ሙሴ በጣም የሚያሳውቃቸው ትልቅ ሚና አልተጫወቱም።

      ይሁን እንጂ በሌላ ቦታ የሚኖርና ታማኝነቱን በመጠበቅ ከሌሎች ሁሉ ጎልቶ የታወቀ አንድ ሰው ነበር። “ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ነበር።”—ኢዮብ 1:1

      ስለዚህ ይሖዋ የኢዮብን እምነትና ለአምላክ የማደርን ዓይነተኛ ወይም የታወቀ ምሳሌውን ጠቅሶ ለመናገር ችሏል። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆኑት ሕዝቅኤልና ያዕቆብ መለስ ብለው ኢዮብን የጽድቅና የጽናት ምሳሌ አድርገው ከሌሎች ነጥለው ጠቅሰውታል።—ሕዝቅኤል 14:14፤ ያዕቆብ 5:11

  • ዓመታዊ ስብሰባ—ጥቅምት 3, 1992
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ነሐሴ 1
    • ዓመታዊ ስብሰባ—ጥቅምት 3, 1992

      የፔንሲልቫንያ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ በኬኔዲ ቡልቫርድ 2932 ጀርሲ ሲቲ፣ ኒው ጀርሲ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ጥቅምት 3, 1992 ይካሄዳል። በመጀመሪያ በ3:30 ላይ አባላቱ ብቻ ስብሰባ ያደርጋሉ። ከዚያም በ4:00 ላይ አጠቃላዩ ዓመታዊ ስብሰባ ይደረጋል።

      የኮርፖሬሽኑ አባላት ቋሚ የሆኑት ደብዳቤዎችና የውክልና ካርዳቸው ከነሐሴ 1, 1992 በኋላ ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳቸው ባለፉት ዓመታት ባላቸው የፖስታ አድራሻቸው ላይ የተደረገ ለውጥ ካለ አሁኑኑ ለጸሐፊው ቢሮ ማስታወቅ ይኖርባቸዋል።

      ዓመታዊውን ስብሰባ ከሚያስታውቀው ደብዳቤ ጋር ለአባላቱ የሚላኩት የውክልና ሰነዶች ከነሐሴ 15, 1992 በፊት ተመልሰው ወደ ማህበሩ ጸሐፊ ቢሮ መድረስ አለባቸው። እያንዳንዱ አባል በስብሰባው ላይ ይገኝ እንደሆነና እንዳልሆነ በመግለጽ የውክልና ሰነዱን ወዲያውኑ አጠናቅቆ መመለስ ይኖርበታል። እያንዳንዱ ሰነድ ላይ የሚሰጠው መረጃ የተወሰነ መሆን አለበት። ምክንያቱም ማን በስብሰባው ላይ እንደሚገኝና እንደማይገኝ የሚወሰነው ከዚህ በሚገኘው መረጃ ነው።

      አጠቃላይ ስብሰባው የሒሳብ ሪፖርቶችን ጨምሮ በ7:00 ላይ ወይም ከዚያ ትንሽ ዘግየት ብሎ ይጠናቀቃል። ከሰዓት በኋላ ስብሰባ አይኖርም። ያለው ቦታ የተወሰነ ስለሆነ ወደ ስብሰባው ለመምጣት የሚፈቀደው ቲኬት ለያዙ ብቻ ነው። ዓመታዊ ስብሰባውን ከስልክ መስመሮች ጋር አገናኝቶ ለሌሎች ለማስተላለፍ ምንም ዓይነት ዝግጅት አይደረግም።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ