-
ማጽናኛ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ!መጠበቂያ ግንብ—2000 | ሚያዝያ 15
-
-
“ለምኜ ወይም ሰርቄ ገንዘብ እንዳመጣ ወላጆቼ ይልኩኝ ነበር። የቤተሰቤ አኗኗር በጣም የተበላሽ ከመሆኑ የተነሳ አንዱ የቅርብ ዘመዴ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሞብኛል። በቡና ቤት ውስጥ የአስተናጋጅነት ሥራ አገኘሁ። ያገኘሁትን ገንዘብ በሙሉ የምሰጠው ለእናቴ ሲሆን ሥራውን ብለቅ ራሷን የምትገድል መሆኗን ነገረችኝ። ይህ ሁሉ ተደራርቦ የዝሙት አዳሪነት ሕይወት ውስጥ እንድገባ አደረገኝ። ይህ ሁሉ ሲሆን ገና የ13 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከጊዜ በኋላ አረገዝኩና ፅንሱን አስወረድኩ። የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ ለሚያየኝ ሰው ሁሉ የ30 ዓመት ሴት ነበር የምመስለው።”
በላትቪያ የሚኖረው ላይመንስ ማጽናኛ ማግኘት ያስፈለገው ለምን እንደሆነና ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ነገር ምን እንደነበረ መለስ ብሎ በማስታወስ ተናግሯል። በ29 ዓመቱ የመኪና አደጋ ደረሰበትና ከወገቡ በታች ሽባ ሆነ። እጅግ ተስፋ ስለቆረጠ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ጀመረ። ከአምስት ዓመት በኋላ የወደፊቱ ተስፋው ሁሉ የጨለመበት የለየለት የአልኮል ሱሰኛ ሆነ። ማጽናኛ ከየት ሊያገኝ ይችላል?
ወይም አንጂ የገጠማትን ሁኔታ ተመልከት። ባሏ ሦስት ጊዜ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ሲሆን የመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ግማሽ አካሉን ሽባ አድርጎት ነበር። ከዚያም የመጨረሻው ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት ከአምስት ዓመት በኋላ ለሞት ሊዳርግ የሚችል ከባድ አደጋ ደረሰበት። ሚስቱ ወደ ድንገተኛ ክፍል ስትገባ ባለቤቷ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ራሱን ስቶ ተኝቶ በተመለከተችው ጊዜ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚጠብቃት ታወቃት። በእርሷና በቤተሰቧ የወደፊት ሕይወት ላይ ሊደርስ የሚችለው ችግር ወለል ብሎ ታያት። ድጋፍና ማበረታቻ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
ፓት ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀዝቃዛው የክረምት ወቅት አንድ ቀን ጠዋት የነበራት ስሜት ከወትሮው የተለየ አልነበረም። ይሁን እንጂ በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት የሆነውን ሁሉ አታውቅም። ከጊዜ በኋላ ባለቤቷ እንደነገራት ደረቷ ላይ ከፍተኛ ሕመም ከተሰማት በኋላ ልቧ መምታቱን አቆመ። ልቧ ከተለመደው የልብ አመታት ሥርዓት ለየት ባለ መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት መምታት ጀመረና ወዲያው ደግሞ ጸጥ አለ። መተንፈስ አቆመች። “የሞትኩኝ ያህል ነበር” ትላለች ፓት። የሆነ ሆኖ ከሞት ተረፈች። በሐኪም ቤት ስለቆየችባቸው ረዥም ጊዜያት ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “በርካታ ምርመራዎች ያደርጉልኝ በነበረ ጊዜ በተለይ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ተከስቶ እንደነበረው ልቤ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲመታና ምቱን እንዲያቆም ለማድረግ በሚሞክሩበት ጊዜ ከፍተኛ ፍርሃት አድሮብኝ ነበር።” ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት የሚያስፈልጋትን ማጽናኛና እፎይታ ሊሰጣት የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
ጆ እና ሪቤካ የ19 ዓመት ልጃቸው በደረሰበት የመኪና አደጋ ሞተ። “እንደዚህ አድርጎ ከፍተኛ ሃዘን ውስጥ የከተተን ነገር አጋጥሞን አያውቅም” በማለት ይናገራሉ። “ከዚህ ቀደም የሚወዱትን ሰው በሞት ካጡ ሰዎች ጋር አብረን ያዘንን ቢሆንም እንኳ እንደ አሁኑ ልባችን በከፍተኛ ሃዘን የተመታበት ወቅት የለም።” የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን “ከፍተኛ ሃዘን” ለማስታገስ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?
እነዚህም ሆኑ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተወዳዳሪ የሌለው የማጽናኛ ምንጭ አግኝተዋል። አንተም ከዚህ የማጽናኛ ምንጭ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ መረዳት ትችል ዘንድ እባክህ የጀመርከውን ንባብ ሳታቋርጥ ማንበብህን ቀጥል።
-
-
ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት ማጽናኛ ማግኘትመጠበቂያ ግንብ—2000 | ሚያዝያ 15
-
-
ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት ማጽናኛ ማግኘት
“አቤቱ፣ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።”—መዝሙር 94:19
መጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛ ማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ የሚሆኑ አጽናኝ ቃላት በውስጡ ይዟል። ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ችግርና ግራ የሚያጋባ ሁኔታ በገጠማቸው ጊዜ ማጽናኛ፣ ተስፋና መመሪያ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዞር ብለዋል” ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም። ለምን?
ይህ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመከራችን ሁሉ በሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ በሆነው አፍቃሪ ፈጣሪያችን መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለሆነ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ይሖዋ ‘አጽናኝ አምላክ’ ነው። (ሮሜ 15:5) ይሖዋ ለሁላችንም እፎይታ የምናገኝበትን መንገድ በማዘጋጀት ምሳሌ ትቷል። ተስፋና ማጽናኛ እንድናገኝ አንድያ ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስተምሯል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “ሸክማችንን በየቀኑ የሚያቀልልንና እኛን የሚያድን” በማለት ይገልጸዋል። (መዝሙር 68:19 የ1980 ትርጉም ) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች እንደሚከተለው በማለት በልበ ሙሉነት ሊናገሩ ይችላሉ:- “ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም።”—መዝሙር 16:8
ይሖዋ አምላክ ለእኛ ለሰው ልጆች የጠለቀ ፍቅር እንዳለው እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሳያሉ። እኛን ለማጽናናትና ጭንቀት ውስጥ በምንገባበት ጊዜ ሥቃያችንን ለማስታገስ ልባዊ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳለው ግልጽ ነው። “ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።” (ኢሳይያስ 40:29) ታዲያ ይሖዋ ከሚሰጠው ብርታት ማጽናኛ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
የይሖዋ እንክብካቤ የሚያስገኘው እፎይታ
መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።” (መዝሙር 55:22) አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ቤተሰብ ያስባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እርሱ [አምላክ] ስለ እናንተ ያስባል” በማለት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ ሰዎችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ጠበቅ አድርጎ ገልጿል:- “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳቸሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።” (ሉቃስ 12:6, 7) በአምላክ ፊት ከፍተኛ ዋጋ ያለን ከመሆኑ የተነሳ ስለ እያንዳንዳችን ጥቃቅኗን ነገር እንኳ ሳይቀር ያውቃል። ስለ እያንዳንዳችን በግል የሚያስብ በመሆኑ እኛ እንኳ ስለ ራሳችን የማናውቀውን ነገር እርሱ ያውቃል።
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ስቬትላና የተባለችው ዝሙት አዳሪ ወጣት፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያስብልን መሆኑን ማወቋ ከፍተኛ የመጽናኛ ምንጭ ሆኖላታል። ራሷን ለመግደል በዝግጅት ላይ እያለች የይሖዋ ምሥክሮች ያገኟታል። ከዚያም ከእነርሱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ይሖዋ እውን አካል እንደሆነና ስለ ደህንነቷ የሚያስብ መሆኑን ከጥናቷ ለመገንዘብ ቻለች። ይህም ልቧን ስለነካው የአኗኗር መንገዷን ቀይራ ራሷን ለአምላክ እንድትወስን አነሳሳት። ከዚህም በተጨማሪ ስቬትላና ችግሮች ቢኖሩባትም እንኳ በጽናት ወደፊት እንድትገፋና ለሕይወት አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራት የሚረዳትን ለራስ ጥሩ ግምት የማሳደር ባሕርይ በተወሰነ መጠን እንድታዳብር አስችሏታል። “ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወኝ እርግጠኛ ነኝ። ‘የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ [በይሖዋ] ላይ ጣሉት’ የሚሉት በ1 ጴጥሮስ 5:7 ላይ የሚገኙት ቃላት እውነት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ” በማለት ትናገራለች።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ ያጽናናል
አምላክ ማጽናኛ የሚሰጥበት አንደኛው መንገድ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ በያዘው በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) ጳውሎስ የሚከተለውን በጻፈ ጊዜ በእውነተኛ ተስፋና ማጽናኛ መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ አድርጓል:- “የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽና[ናው] በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽ[ናችሁ]።” (2 ተሰሎንቄ 2:16, 17) ይህ ‘በጎ ተስፋ’ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም፣ አስደሳችና መጨረሻ የሌለው ሕይወት አግኝቶ የመኖርን ተስፋ ይጨምራል።—2 ጴጥሮስ 3:13
እንዲህ ያለው የተረጋገጠና ብሩህ ተስፋ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን ሽባ የሆነውን የአልኮል ሱሰኛ ላይመኒስን አበረታቶታል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ሲያነብ በአምላክ መንግሥት በሚተዳደረው አዲስ ዓለም ውስጥ ሙሉ ጤና እንደሚያገኝ ማወቁ አስደሰተው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ወደፊት ተአምራዊ ፈውስ እንደሚካሄድ የሚገልጸውን የሚከተለውን ብሩህ ተስፋ አነበበ:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) በገነት ውስጥ ለመኖር የሚያስችለውን ብቃት ለማግኘት ሲል ላይመኒስ ከፍተኛ ለውጥ አደረገ። መጠጣት አቆመ። ያደረገው ለውጥ በጎረቤቱና በጓደኞቹ ሳይስተዋል አላለፈም። አሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ የሚሰጠውን ማጽናኛ ለሌሎች በማካፈል በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ላይ ይገኛል።
ጸሎት የሚጫወተው ሚና
ልባችን በሆነ ምክንያት ሃዘን ሲገባው ወደ ይሖዋ በመጸለይ ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን የተጫነንን ሸክም ሊያቃልልልን ይችላል። ልመና በምናቀርብበት ጊዜ በአምላክ ቃል ውስጥ የተነገሩ ነገሮችን በማስታወስ ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ረዥሙ መዝሙር እንደ አንድ ውብ ጸሎት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። የመዝሙሩ አቀናባሪ እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፣ አቤቱ፣ ተጽናናሁም።” (መዝሙር 119:52) ከባድ ችግር የገጠመው በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የጤና እክል የገጠመው ሰው ለችግሮቹ ሁሉ የሚሆን መልስ በአንድ ጊዜ ላያገኝ ይችላል። በራሳችን ብርታት ወዴት መሄድ እንዳለብን በትክክል ላናውቅ እንችላለን። ብዙዎች የቻሉትን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጸሎት ወደ አምላክ ዞር ማለታቸው ከፍተኛ ማጽናኛና አንዳንድ ጊዜም ያልታሰበ መፍትሔ አስገኝቶላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል በፍጥነት የተወሰደችው ፓት ጸሎት ያለውን የማጽናናት ኃይል በራሷ ሕይወት ተመልክታዋለች። ከህመሟ ካገገመች በኋላ እንዲህ አለች:- “ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ፈቃዱ የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ በመተማመን ሕይወቴን ለእርሱ መተው ተምሬአለሁ። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት መረጋጋትን አግኝቻለሁ፤ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የተጠቀሰውን የአምላከ ሰላም አግኝቻለሁ።” ይህ ጥቅስ ሁላችንንም እጅግ ሊያጽናና የሚችል ነው! እዚያ ላይ ጳውሎስ እንዲህ በማለት መክሮናል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”
መንፈስ ቅዱስም ያጽናናናል
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት፣ ብዙም ሳይቆይ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ለሐዋርያቱ ነገራቸው። ይህም ጭንቀትና ሐዘን ውስጥ ከተታቸው። (ዮሐንስ 13:33, 36፤ 14:27-31) ኢየሱስ ያልተቋረጠ ማጽናኛ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ የሚከተለውን ቃል ገባላቸው:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል።” (ዮሐንስ 14:15, 16) ኢየሱስ እዚህ ላይ ይጠቅስ የነበረው የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ነው። ሐዋርያት መከራ በገጠማቸው ጊዜ ሁሉ የአምላክ መንፈስ አጽናንቷቸዋል እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አጠናክሯቸዋል።—ሥራ 4:31
አንጂ ባሏ በደረሰበት ከባድ አደጋ ምክንያት ለሞት ተቃርቦ በነበረበት ጊዜ የገጠማትን ጭንቀትና የስሜት መረበሽ በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ችላለች። የረዳት ነገር ምንድን ነው? እንዲህ ትላለች:- “የይሖዋን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ባናገኝ ኖሮ የደረሱብንን ችግሮች ሁሉ ማለፍና ጠንካራ ሆነን መኖር አንችልም ነበር። የይሖዋ ብርታት በእኛ ድካም ላይ ግልጽ ሆኖ የታየ ሲሆን በጭንቀታችን ጊዜ ሁሉ መሸሸጊያ ሆኖልናል።”
አጽናኝ የሆነው የወንድማማች ማኀበር
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የገጠመው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ እንዲሁም የደረሰበት ችግር ምንም ያህል የሚያሠቃይ ቢሆን በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ከሚገኘው የወንድማማች ማኀበር ያለ ጥርጥር ማጽናኛ ሊያገኝ ይችላል። ይህ የወንድማማች ማኀበር በውስጡ ለታቀፉት ሁሉ መንፈሳዊ ድጋፍና እርዳታ ይሰጣል። አንድ ሰው በዚህ የወንድማማች ማኀበር ውስጥ ሌሎችን በጭንቀታቸው ወቅት ለመርዳትና ለማጽናናት ዝግጁና ፈቃደኞች የሆኑ አፍቃሪ፣ አሳቢና አጽናኝ ወዳጆችን ሊያገኝ ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 7:5-7
የክርስቲያን ጉባኤ አባላት “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ [ሰዎቻቸው] መልካም” ማድረግን ተምረዋል። (ገላትያ 6:10) የተማሯቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶች አንዳቸው ለሌላው የወንድማማች ፍቅርና የርኀራኄ ስሜት እንዲያንጸባርቁ ይገፋፋቸዋል። (ሮሜ 12:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:8) በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ደግ፣ አጽናኝና ከአንጀት የመራራት ስሜት እንዲያሳዩ ይገፋፋሉ።—ኤፌሶን 4:32
ልጃቸውን አሳዛኝ በሆነ መንገድ በሞት ያጡት ጆ እና ሪቤካ እንዲህ ያለውን ማጽናኛ ከክርስቲያን ጉባኤ አባላት አግኝተዋል። እንዲህ ይላሉ:- “በችግሮቻችን ወቅት ሁሉ ይሖዋና አፍቃሪ ጉባኤው እርዳታ አድርገውልናል። በመቶ የሚቆጠሩ ካርዶች፣ ደብዳቤዎችና የስልክ ጥሪዎች ተቀብለናል። ይህም የወንድማማች ማኀበራችን ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንድንገነዘብ አድርጎናል። በአደጋው ምክንያት በጣም ተደናግጠን ሳለ በአካባቢያችን የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች ምግብ በማዘጋጀትና ቤታችንን በማጽዳት ከጎናችን ቆመዋል።”
አንተም ማጽናኛ አግኝ!
ኃይለኛ የመከራ ነፋስ በሚነፍስበትና የጭንቀት ዝናብና በረዶ በሚወርድበት ጊዜ አምላክ አጽናኝ ጥበቃውን ለመስጠት ዝግጁ ነው። መዝሙራዊው፣ አምላክ አጽናኝ መጠጊያ እንደሆነ የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር:- “በላባዎቹ ይጋርድሃል፣ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ።” (መዝሙር 91:4) እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ተደርጎ የተገለጸው ንስር ሳይሆን አይቀርም። አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ክንፎቿን በመዘርጋት ጫጩቶቿን ከአደጋ የምትጠብቅ ወፍ ምሳሌ ነው። ይሖዋም እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ እውነተኛ ጠባቂ ይሆንላቸዋል።—መዝሙር 7:1
ስለ አምላክ፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ዓላማዎቹና ማጽናኛ ለመስጠት ስላለው ችሎታ ይበልጥ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ ቃሉን እንድታጠና እንጋብዝሃለን። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ዝግጁዎች ናቸው። አዎን፣ አንተም ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት ማጽናኛ ማግኘት ትችላለህ!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰጠው ተስፋ ሊያጽናና ይችላል
-