አስተማሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ
“ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ።”—ዮሐንስ 6:45
1. ኢየሱስ በቅፍርናሆም ምን እያደረገ ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ተአምራትን ካደረገ በኋላ በቅፍርናሆም ውስጥ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ምኩራብ እያስተማረ ነበር። (ዮሐንስ 6:1–21, 59) ብዙዎች ‘ከሰማይ ወርጃለሁ’ ሲላቸው አለማመናቸውን ገልጸዋል። “አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ፦ ከሰማይ ወርጄአለሁ እንዴት ይላል?” በማለት አጉረመረሙ። (ዮሐንስ 6:38, 42) ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” በማለት ገሠጻቸው።—ዮሐንስ 6:44
2. ኢየሱስ ትንሣኤን በተመለከተ የሰጠውን ተስፋ ለማመን ምን መሠረት አለ?
2 በመጨረሻው ቀን ማለትም የአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ወቅት ከሞት መነሣት እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ይህን ተስፋ የሰጠው አባታችን ይሖዋ አምላክ ስለሆነ ልናምንበት እንችላለን። (ኢዮብ 14:13–15፤ ኢሳይያስ 26:19) ሙታን እንደሚነሡ የሚያስተምረው ይሖዋ በእርግጥም “ከሁሉ የበለጠ አስተማሪ” ነው። (ኢዮብ 36:22፣ ቱደይስ እንግሊሽ ቨርሽን) ኢየሱስ ቀጠሎ በአባቱ ትምህርት ላይ በማተኮር “ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል” አለ።—ዮሐንስ 6:45
3. ቀጥለን የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ነቢዩ ኢሳይያስ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” ሲል ከጻፈላቸው ሰዎች መካከል መሆን በእርግጥም ልዩ መብት ነው! (ኢሳይያስ 54:13) ከይሖዋ የተማርን መሆን እንችላለንን? እንደ ልጆቹ የሆኑትና ከእሱ እየተማሩ ያሉት እነማን ናቸው? የእሱን በረከት ለማግኘት ከፈለግን ልናውቃቸውና ልንሠራባቸው የሚገቡን ዐበይት የይሖዋ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ ከዚህ በፊት ያስተማረው እንዴት ነው? ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ያስተምራልን? ቀጥለን የምንመረምራቸው ጥያቄዎች እነዚህ ይሆናሉ።
አባት፣ አስተማሪ፣ ባል
4. በመጀመሪያ ደረጃ ከእሱ የተማሩት የይሖዋ ልጆች እነማን ናቸው?
4 ይሖዋ መጀመሪያ አባትና አስተማሪ የሆነው ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን አንድያ ልጁን ኢየሱስን በፈጠረበት ወቅት ነው። ይህ ልጅ የይሖዋ ዋና ቃል አቀባይ በመሆኑ “ቃል” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 1:1, 14፤ 3:16) ቃል “በእርሱ ዘንድ [በአባቱ ዘንድ] ዋና ሠራተኛ” ነበር፤ ከአባቱም በሚገባ ተምሯል። (ምሳሌ 8:22, 30) እንዲያውም አብ መንፈሳዊ “የአምላክ ልጆች”ን ጨምሮ ሁሉን ነገር የፈጠረበት ማስገኛ ወይም መሣሪያ ሆኗል። እነዚህ የአምላክ ልጆች ከአምላክ በመማራቸው ምንኛ ተደስተው መሆን አለበት! (ኢዮብ 1:6፤ 2:1፤ 38:7፤ ቆላስይስ 1:15–17) ከዚህ በኋላ የመጀመሪያው ሰው አዳም ተፈጠረ። እሱም ቢሆን ‘የአምላክ ልጅ’ የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ እንዳስተማረው ይናገራል።—ሉቃስ 3:38፤ 2:7, 16, 17
5. አዳም ቀደም ሲል የነበረውን ምን ውድ መብት አጣ? ሆኖም ይሖዋ ያስተማረው እነማንን ነበር? ለምንስ?
5 የሚያሳዝነው አዳም ሳይታዘዝ በመቅረቱ የአምላክ ልጅ ሆኖ የመቀጠል መብቱን አጣ። ስለዚህ ዘሮቹ በትውልዳቸው መሠረት ብቻ የአምላክ ልጆች ነን ለማለት አይችሉም። ሆኖም ይሖዋ ከእሱ መመሪያ የፈለጉ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን አስተምሯል። ለምሳሌ ያህል ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው’ ኖኅ ‘ጻድቅ ሰው’ ስለነበር ይሖዋ አስተምሮታል። (ዘፍጥረት 6:9, 13 እስከ 7:5) አብርሃም በታዛዥነቱ ምክንያት “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ስለነበር እሱም ቢሆን ከይሖዋ ተምሯል።—ያዕቆብ 2:23፤ ዘፍጥረት 12:1–4፤ 15:1–8፤ 22:1, 2
6. ይሖዋ እንደ ‘ልጆቹ’ አድርጎ መመልከት የጀመረው እነማንን ነበር? ለእነሱ ምን ዓይነት አስተማሪ ነበር?
6 ይህ ከሆነ ከረጅም ጊዜ በኋላ በሙሴ ዘመን ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና ውስጥ ገባ። በዚህም ምክንያት ይህ ሕዝብ ምርጥ ሕዝቡ ሆነና እንደ ‘ልጁ’ ተቆጠረ። አምላክ “እስራኤል የበኩር ልጄ ነው” ብሏል። (ዘጸአት 4:22, 23፤ 19:3–6፤ ዘዳግም 14:1, 2) በዚህ የቃል ኪዳን ዝምድና መሠረት እስራኤላውያን በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ላይ እንደተመዘገበው “ይሖዋ ሆይ አንተ አባታችን ነህ” ሊሉ ይችሉ ነበር። (ኢሳይያስ 63:16 አዓት) ይሖዋ የአባትነት ኃላፊነቱን ተቀብሎ ልጆቹ የሆኑትን እስራኤላውያን በፍቅር አስተምሯቸዋል። (መዝሙር 71:17፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) እንዲያውም ታማኝ ሳይሆኑ ሲቀሩ “ከዳተኞች ልጆች ሆይ . . . ተመለሱ” በማለት በምሕረት ለምኗቸዋል።—ኤርምያስ 3:14
7. እስራኤል ከይሖዋ ጋር የነበራት ዝምድና ምን ነበር?
7 በተጨማሪም ይሖዋ ከእስራኤል ጋር በነበረው የቃል ኪዳን ዝምድና ምክንያት የሕዝቡ ምሳሌያዊ ባል ሲሆን እስራኤል ደግሞ ምሳሌያዊ ሚስቱ ሆና ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ እስራኤልን በተመለከተ ሲጽፍ “ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፣ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ነው” ብሏል። (ኢሳይያስ 54:5፤ ኤርምያስ 31:32) ይሖዋ እንደ ባል የመሆን ኃላፊነቱን በትክክል ቢወጣም የእስራኤል ሕዝብ ከዳተኛ ሚስት ሆነ። ይሖዋ “የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ሚስት ባሏን እንደምታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ” ብሏል። (ኤርምያስ 3:20) ይሖዋ የከዳተኛ ሚስቱን ልጆች መለመኑን ቀጠለ፤ ‘ታላቅ አስተማሪያቸው’ መሆኑን ቀጠለ።—ኢሳይያስ 30:20፤ 2 ዜና መዋዕል 36:15
8. ይሖዋ እስራኤልን በሕዝብ ደረጃ ቢተዋትም አሁንም ቢሆን የትኛዋ ዋነኛ ምሳሌያዊ ሚስት አለችው?
8 በመጨረሻ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳትቀበል ስለቀረችና ስለገደለችው አምላክ እስራኤልን ተዋት። ስለዚህ እስራኤል ምሳሌያዊ ሚስቱ መሆኗም ሆነ ይሖዋ የአስቸጋሪ ልጆቿ አስተማሪና አባት መሆኑ ቀረ። (ማቴዎስ 23:37, 38) ሆኖም እስራኤል ጥላ ወይም ምሳሌያዊ ሚስት ብቻ ነበረች። ሐዋርያው ጳውሎስ “ባል ካላት” የሥጋዊ እስራኤል ሴት ስለምትለየው ስለ አንዲት “መካን” ሴት የሚናገረውን ኢሳይያስ 54:1ን ጠቅሷል። ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ብሎ የጠራት የዚህች “መካን” ሴት ልጆች እንደሆኑ ገልጿል። ይህች ዋነኛ ምሳሌያዊ ሴት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችውን የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ታመለክታለች።—ገላትያ 4:26, 27
9. (ሀ) ኢየሱስ ‘ልጆችሽም ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ’ ብሎ ሲናገር እነማንን መጥቀሱ ነበር? (ለ) ሰዎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች የሚሆኑት በምን መሠረት ነው?
9 ስለዚህ ኢየሱስ በቅፍርናሆም ምኩራብ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” የሚለውን የኢሳይያስን ትንቢት ሲጠቅስ የአምላክ ሚስት መሰል ሰማያዊ ድርጅት የሆነችው የ“ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” “ልጆች” ስለሚሆኑት ሰዎች እየተናገረ ነበር። እነዚህ አይሁዳውያን አድማጮች ከሰማይ የመጣውን የአምላክን ወኪል ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት በመቀበል ቀደም ሲል መካን የነበረችው የአምላክ ሰማያዊ ሴት ልጆችና ‘የአምላክ እስራኤል’ የሆነው ‘ቅዱስ ሕዝብ’ አባላት ሊሆኑ ይችሉ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9, 10፤ ገላትያ 6:16) ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ ለመንፈሳዊ የአምላክ ልጆች የከፈተላቸውን ታላቅ አጋጣሚ በመግለጽ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።”—ዮሐንስ 1:11, 12
በጣም አስፈላጊ የሆኑት የይሖዋ ትምህርቶች
10. በኤደን ውስጥ ኃጢአት ከተሠራ በኋላ ወዲያውኑ ይሖዋ ‘ዘሩን’ በተመለከተ ያስተማረው ምን ነበር? ይህ ዘር የሆነው ማን ነበር?
10 ይሖዋ አፍቃሪ አባት እንደ መሆኑ መጠን ልጆቹን ስለ ዓላማዎቹ ያሳውቃቸዋል። ስለዚህ አንድ ዓመፀኛ መልአክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ባሳመፃቸው ወቅት ይሖዋ ወዲያውኑ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ምን እንደሚያደርግ ገለጸላቸው። በ“ቀድሞው እባብ” ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስና “በሴቲቱ” መካከል ጠላትነት እንዲኖር እንደሚያደርግ ተናገረ። ከዚያም የሴቲቱ ‘ዘር’ ሰይጣንን ለማጥፋት ‘ራሱን’ እንደሚቀጠቅጥ ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:1–6, 15፤ ራእይ 12:9፤ 20:9, 10) ከላይ እንደተመለከትነው ሴቲቱ በኋላ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” በመባል የታወቀችው መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችው የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ናት። ይሁን እንጂ የእሷ “ዘር” የሆነው ማን ነው? ከሰማይ የተላከውና በመጨረሻ ሰይጣንን የሚያጠፋው የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ገላትያ 4:4፤ ዕብራውያን 2:14፤ 1 ዮሐንስ 3:8
11, 12. ይሖዋ ‘ዘሩን’ በተመለከተ ያስተማረውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ያሰፋው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ “ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት . . . አበዛዋለሁ፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” በማለት ለአብርሃም ቃል በገባበት ወቅት ይህን “ዘር” በተመለከተ የሚያስተምረውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አስፋፍቶታል። (ዘፍጥረት 22:17, 18) ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ የተሰጠበት የአብርሃም ዘር እንደሆነና ሌሎችም የዚሁ “ዘር” ክፍል እንደሚሆኑ እንዲያብራራ ይሖዋ ሐዋርያው ጳውሎስን ተጠቅሞበታል። ጳውሎስ “የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” በማለት ጻፈ።—ገላትያ 3:16, 29
12 በተጨማሪም ይሖዋ ዘሩ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳ ንጉሣዊ የዘር መሥመር እንደሚመጣና ‘አሕዛብ ለእርሱ እንደሚታዘዙ’ ገልጿል። (ዘፍጥረት 49:10) ከይሁዳ ነገድ የነበረውን ንጉሥ ዳዊትን በተመለከተ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፣ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ። ዘሩ ለዘላለም፣ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል።” (መዝሙር 89:3, 4, 29, 36) መልአኩ ገብርኤል የኢየሱስን መወለድ ሲያበስር ልጁ የዳዊት ዘርና በአምላክ የተሾመ ገዢ እንደሆነ ገልጿል። ገብርኤል “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ብሏል።—ሉቃስ 1:32, 33፤ ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 7:13, 14
13. የይሖዋን በረከት ለማግኘት ከፈለግን ለሚሰጠው ትምህርት ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
13 የይሖዋን በረከት ለማግኘት ከፈለግን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ማወቅና በተግባር ላይ ማዋል ይኖርብናል። ኢየሱስ ከሰማይ እንደ መጣ፣ አምላክ የሾመው ንጉሥ ማለትም ገነት በምድር ላይ እንደገና መቋቋሟን የሚቆጣጠር ንጉሣዊ ዘር እንደሆነና ሙታንን እንደሚያስነሣ ማመን አለብን። (ሉቃስ 23:42, 43፤ ዮሐንስ 18:33–37) ኢየሱስ በቅፍርናሆም ውስጥ ስለ ሙታን ትንሣኤ በተናገረበት ወቅት እውነቱን እንደተናገረ ለአይሁዳውያን ግልጽ መሆን ነበረበት። እንዲያውም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ምናልባትም እዚያው ቅፍርናሆም ውስጥ የምኩራቡ አለቃን የ12 ዓመት ሴት ልጅ ከሞት አስነሥቶ ነበር! (ሉቃስ 8:49–56) እኛም ይሖዋ መንግሥቱን በተመለከተ የሰጠንን ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅ ትምህርት እንድናምንና ከትምህርቱ ጋር ተስማምተን እንድንኖር የሚያደርገን በቂ ምክንያት እንዳለን የተረጋገጠ ነው!
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ የይሖዋን መንግሥት ምን ያህል ከፍ አድርጎ ይመለከታት ነበር? (ለ) የይሖዋን መንግሥት ለመረዳትና ለሌሎች ለማብራራት እንድንችል ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
14 ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ስለ ይሖዋ መንግሥት በማስተማር አሳልፏል። መንግሥቲቱን የአገልግሎቱ ዋና መልእክት ከማድረጉም በላይ ተከታዮቹ ስለዚች መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ሉቃስ 4:43) ሥጋዊ አይሁዳውያን “የመንግሥት ልጆች” መሆን በሚችሉበት መሥመር ላይ የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ እምነት ስላልነበራቸው ይህንን መብት አጡ። (ማቴዎስ 8:12፤ 21:43) ኢየሱስ “የመንግሥት ልጆች” የመሆን መብት የሚያገኙት “ታናሽ መንጋ” ብቻ እንደሆኑ ገለጸ። እነዚህ “ልጆች” በሰማያዊ መንግሥቱ “ከክርስቶስ ጋር የሚገዙ” ይሆናሉ።—ሉቃስ 12:32፤ ማቴዎስ 13:38፤ ሮሜ 8:14–17፤ ያዕቆብ 2:5
15 ክርስቶስ ከእሱ ጋር ምድርን እንዲገዙ ወደ ሰማይ የሚወስዳቸው የመንግሥቱ ወራሾች ስንት ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ 144,000 ብቻ እንደሆኑ ይገልጻል። (ዮሐንስ 14:2, 3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ ራእይ 5:10፤ 14:1–3፤ 20:4) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የዚህች መንግሥት ምድራዊ ዜጎች የሆኑ “ሌሎች በጎች” እንዳሉት ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች በገነት ምድር ላይ ፍጹም ጤንነትና ሰላም አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4) እኛም ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን የይሖዋን ትምህርት ማስተዋልና ማብራራት መቻል አለብን።
16. ልንማረውና በሥራ ላይ ልናውለው የሚገባን በጣም አስፈላጊ የሆነ የይሖዋ ትምህርት የትኛው ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ ሌላውን በጣም አስፈላጊ የሆነ የይሖዋ ትምህርት ለይቶ አሳውቋል። “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋል” ሲል ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 4:9) ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል፤ እኛም ፍቅር በማሳየት የተወልንን ምሳሌ መከተል አለብን። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ኤፌሶን 5:1, 2) አብዛኞቹ ሰዎች አምላክ ባስተማረን መንገድ እንደነሱ ሰብዓዊ ፍጡራን የሆኑትን ሰዎች ማፍቀርን ለመማር አለመቻላቸው ያሳዝናል። እኛስ እንዴት ነን? ለዚህ የይሖዋ ትምህርት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠን ነውን?
17. የእነማንን ዝንባሌ ልንኮርጅ ይገባናል?
17 ይሖዋ የሚያስተምረንን በሙሉ መቀበላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ዝንባሌያችን እንዲህ በማለት እንደተናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መዘምራን ዓይነት ይሁን፦ “[ይሖዋ ሆይ አዓት] አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም።” “ሥርዓትህን አስተምረኝ። መልካም ምክርንና እውቀትን አስተምረኝ። ፍርድህንም አስተምረኝ።” (መዝሙር 25:4, 5፤ 119:12, 66, 108) የአንተ ስሜቶች ከእነዚያ መዘምራን ስሜት ጋር አንድ ከሆነ ከይሖዋ ከተማሩት እጅግ ብዙ ሰዎች መካከል ልትሆን ትችላለህ።
የተማሩት እጅግ ብዙ ሰዎች
18. ነቢዩ ኢሳይያስ በዘመናችን እንደሚፈጸም የተነበየው ነገር ምንድን ነው?
18 ነቢዩ ኢሳይያስ በዘመናችን ስለሚሆነው ነገር ሲተነብይ እንዲህ ብሏል፦ “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል . . . ይላሉ።” (ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ ሚክያስ 4:2) እነዚህ ከይሖዋ የተማሩ ሰዎች እነማን ናቸው?
19. ይሖዋ ካስተማራቸው መካከል በአሁኑ ወቅት እነማን ጭምር ይገኙበታል?
19 ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ከሚገዙት ሌላ ሌሎችንም ይጨምራሉ። ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ኢየሱስ የመንግሥቱ ወራሾች ከሆኑት “ታናሽ መንጋ” ሌላ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዢዎች የሆኑ “ሌሎች በጎች” እንዳሉት ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:16፤ ሉቃስ 12:32) ከ“ታላቁ መከራ” የሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሌሎች በጎች ክፍል ሲሆኑ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ ባላቸው እምነት መሠረት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም አላቸው። (ራእይ 7:9, 14) ሌሎች በጎች በቀጥታ በኢሳይያስ 54:13 ላይ ከተነገሩት “ልጆች” መካከል ባይሆኑም ይሖዋ ስላስተማራቸው ተባርከዋል። ስለዚህ “የዘላለም አባት” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አያታቸው የሆነውን አምላክ “አባት” ብለው መጥራታቸው ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 6:9፤ ኢሳይያስ 9:6
ይሖዋ የሚያስተምርበት መንገድ
20. ይሖዋ በምን በምን መንገዶች ያስተምራል?
20 ይሖዋ በብዙ መንገዶች ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል ሕልውናውንም ሆነ ታላቅ ጥበቡን በሚመሠክሩት በፍጥረት ሥራዎቹ አማካኝነት ያስተምራል። (ኢዮብ 12:7–9፤ መዝሙር 19:1, 2፤ ሮሜ 1:20) ከዚህም በላይ ኢየሱስን ሰው ከመሆኑ በፊት ባስተማረበት መንገድ ከሰዎች ጋር በቀጥታ የሐሳብ ግንኙነት በመፍጠር ያስተምራል። በተመሳሳይም ተመዝግበው በሚገኙት ሦስት ወቅቶች እንደታየው ምድር ላይ ላሉ ሰዎች ከሰማይ በቀጥታ ተናግሯል።—ማቴዎስ 3:17፤ 17:5፤ ዮሐንስ 12:28
21. ይሖዋ እንደ ወኪሉ አድርጎ በተለይ የተጠቀመበት መልአክ የትኛው ነው? ሆኖም በሌሎች መላእክትም እንደተጠቀመ እንዴት እናውቃለን?
21 በተጨማሪም ይሖዋ የበኩር ልጁ የሆነውን “ቃል”ን ጨምሮ በሌሎች መላእክታዊ ወኪሎች ተጠቅሞ ያስተምራል። (ዮሐንስ 1:1–3) ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ ፍጹም ልጁ ከነበረው ከአዳም ጋር በቀጥታ መነጋገር ቢችልም ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረውን ኢየሱስን እሱን ወክሎ ከአዳም ጋር እንዲነጋገር ሳይጠቀምበት አልቀረም። (ዘፍጥረት 2:16, 17) “በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ” እና ይሖዋ እስራኤላውያንን ‘ቃሉን አዳምጡ’ ብሎ እሱን በተመለከተ ያዘዛቸው፣ ኢየሱስ ሳይሆን አይቀርም። (ዘጸአት 14:19፤ 23:20, 21) ኢያሱን ለማበረታታት የተገለጠው “የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ” ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ኢየሱስ እንደነበረ አያጠራጥርም። (ኢያሱ 5:14, 15) ይሖዋ ለሙሴ ሕጉን ሲሰጥ እንዳደረገው ሁሉ በሌሎች መላእክትም ትምህርቶቹን ለመስጠት ተጠቅሟል።—ዘጸአት 20:1፤ ገላትያ 3:19፤ ዕብራውያን 2:2, 3
22. (ሀ) ይሖዋ በምድር ላይ ለማስተማር ወኪሎቹ አድርጎ የተጠቀመባቸው ሰዎች እነማን ናቸው? (ለ) ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ሰዎችን የሚያስተምርበት ዋነኛ መንገድ ምንድን ነው?
22 ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ አምላክ ሰብዓዊ ወኪሎችን ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል። በእስራኤል ውስጥ የነበሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ነበረባቸው፤ ነቢያት፣ ካህናትና ሌዋውያን የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ አስተምረዋል። (ዘዳግም 11:18–21፤ 1 ሳሙኤል 12:20–25፤ 2 ዜና መዋዕል 17:7–9) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአምላክ ዋና ቃል አቀባይ ነበር። (ዕብራውያን 1:1, 2) ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ያስተማረው ከአባቱ የተማረውን እንደሆነ ስለተናገረ አድማጮቹ ከይሖዋ የተማሩ ሆነዋል። (ዮሐንስ 7:16፤ 8:28፤ 12:49፤ 14:9, 10) ይሖዋ እሱ የተናገራቸው ነገሮች እንዲመዘገቡ አድርጓል፤ በዘመናችንም ሰዎችን የሚያስተምረው በተለይ በእነዚህ በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች አማካኝነት ነው።—ሮሜ 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
23. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራሩት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
23 ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በዘመኑ ፍጻሜ [አሁን በምንኖርበት ወቅት] ብዙ ሰዎች የይሖዋን መንገዶች ይማራሉ’ የሚል ተስፋ ስለሚሰጡ የምንኖረው በጣም አስፈላጊ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። (ኢሳይያስ 2:2, 3) ይህ ትምህርት የሚሰጠው እንዴት ነው? አሁን እየተካሄደ ካለው የይሖዋ ትምህርት ፕሮግራም ለመጠቀምም ሆነ ለሌሎች ትምህርቱን ለማካፈል ምን ማድረግ ይኖርብናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይብራራሉ።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ አባት፣ አስተማሪና ባል የሆነው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ‘ዘሩን’ በተመለከተ ያስተማረው ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ያስተማረንን የትኛውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት መታዘዝ አለብን?
◻ ይሖዋ የሚያስተምረው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢያኢሮስ ሴት ልጅ ከሞት መነሣቷ ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ተስፋ ለማመን መሠረት ይሆናል