ጥናት 19
መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው እንዲከታተሉ ማበረታታት
ሁሉም ሰው የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩር መርዳት እንፈልጋለን። የምንሰብከው መልእክት የሚገኘው እዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ሰዎችም የምንናገረው መልእክት ከራሳችን የመነጨ ሳይሆን ከአምላክ የመጣ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንፈልጋለን። ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸው እምነት መዳበር ይኖርበታል።
በመስክ አገልግሎት። ሁልጊዜ ለአገልግሎት ስትዘጋጅ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች የምታነብበው አንድ ወይም ከዚያ በላይ ጥቅስ ምረጥ። አጠር ያለ መግቢያ ተጠቅመህ ጽሑፍ ለማበርከት ባሰብክበት ጊዜም እንኳ ቢሆን ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ ማንበብህ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ከምንናገረው ቃል ይልቅ በግ መሰል ሰዎችን የመሳብ ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠህ ለማንበብ ሁኔታው የማይፈቅድልህ ከሆነ ሐሳቡን በቃልህ መናገር ትመርጥ ይሆናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅልል እንደልብ አይገኝም ነበር። ይሁንና ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ ከቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ይጠቅሱ ነበር። እኛም ጥቅሶችን ለመያዝና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አገልግሎት ላይ በቃላችን ለመጥቀስ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠህ የማንበብ አጋጣሚ ስታገኝ የምታነጋግረው ሰው አብሮህ እንዲከታተል አሳየው። ሰውዬው የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ የሚከታተል ከሆነ በሚያነብበው ነገር ይበልጥ ሊነካ ይችላል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች በአምላክ ቃል ላይ አንዳንድ ለውጥ እንዳደረጉ መዘንጋት አይኖርብህም። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች የሚያስተላልፉት መልእክትና የእነርሱ አተረጓጎም የማይጣጣሙባቸው ቦታዎች አሉ። ብዙ ዘመናዊ ትርጉሞች የአምላክን ስም አውጥተዋል፣ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ በመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች የተቀመጡት ጥቅሶች የሚያስተላልፉትን መልእክት ሰውረዋል እንዲሁም አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሐሳብ አድበስብሰዋል። አንድ ሰው የተደረገውን ለውጥ እንዲያስተውል ለመርዳት ከተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሶች ወይም በዚያው ቋንቋ ከሚገኙ ቀደምት ትርጎሞች ላይ ቁልፍ የሆኑትን ጥቅሶች እያወዳደርህ ማሳየት ያስፈልግህ ይሆናል። ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ብዙ ጊዜ በሚጠቀሱ ጥቅሶች ላይ ያሉትን ቁልፍ ቃላት፣ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዴት እንዳስቀመጧቸው እያወዳደረ የሚያቀርብባቸው ቦታዎች አሉ። እውነትን የሚወድድ ማንኛውም ሰው ትክክለኛውን ነገር ሲረዳ መደሰቱ አይቀርም።
በጉባኤ ስብሰባዎች። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሁሉም መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አውጥተው እንዲከታተሉ ማበረታታት ያስፈልጋል። ይህም ብዙ ጥቅም አለው። አድማጮች ትምህርቱን በትኩረት እንዲከታተሉ ይረዳቸዋል። ከተናጋሪው የሚሰሙትን መልእክት በዓይናቸው ማየታቸው ተጨማሪ ማጠናከሪያ ይሆንላቸዋል። እንዲሁም ስብሰባው ላይ የተገኙ አዲሶች እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል።
ጥቅስ ስታነብብ አድማጮችህ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው መከታተላቸው በእጅጉ የተመካው አንተ በምትሰጠው ማበረታቻ ላይ ነው። ከሁሉ የተሻለው ዘዴ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አውጥተው እንዲከታተሉ በቀጥታ መጋበዝ ነው።
አጽንዖት እንዲሰጠው የምትፈልገውን ጥቅስ አድማጮች አውጥተው እንዲያነብቡት አድርግ። ዋና ዋና ነጥቦችህን ለማዳበር የሚረዱ ጥቅሶችን ማንበቡ የተሻለ ነው። ከዚያ ደግሞ ጊዜ በፈቀደልህ መጠን ነጥቡን የሚያጠናክሩ ተጨማሪ ጥቅሶች አንብብ።
ብዙውን ጊዜ ጥቅሱን መናገሩ ወይም አድማጮች ጥቅሱን አውጥተው እንዲከታተሉ መጋበዙ ብቻ በቂ አይሆንም። አንድ ጥቅስ አንብበህ አድማጮችህ ለማውጣት እንኳ ጊዜ ሳያገኙ ወደ ሌላ ጥቅስ የምትሸጋገር ከሆነ ተስፋ ይቆርጡና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ከድነው ቁጭ ይላሉ። ማሰብ ያለብህ አንተ ማውጣትህን ብቻ አይደለም። አብዛኞቹ እስኪያወጡ ድረስ መጠበቅ አለብህ።
የምታነብበት ጊዜ ከመድረሱ ትንሽ ቀደም ብለህ ጥቅሱን ንገራቸው። ይህም አድማጮች ጥቅሱን እስኪያገኙት ድረስ በመጠበቅ የምታጠፋውን ጊዜ ይቆጥብልሃል። አድማጮች ጥቅሱን እስኪያወጡ ድረስ መጠበቅህ ጊዜ ሊሻማብህ ይችላል። ሆኖም ጥቅሱ ሲነበብ መከታተላቸው ከፍተኛ ጥቅም አለው።