ጥናት 20
ጥቅሶችን ጥሩ አድርጎ ማስተዋወቅ
በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርበው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነው። በአገልግሎት ለሰዎች ለምንናገረው መልእክትም ቢሆን መሠረት የሚሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው። ይሁን እንጂ ጥቅሶቹ ለውይይታችን የሚኖራቸው ጠቀሜታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተመካው ጥሩ አድርገን በማስተዋወቃችን ላይ ነው።
ጥቅሱን ተናግረህ ሰውዬው አብሮህ እንዲያነብብ መጋበዝ ብቻ በቂ አይደለም። አንድን ጥቅስ በምታስተዋውቅበት ጊዜ (1) አድማጮች ጥቅሱን የማንበብ ጉጉት እንዲያድርባቸው እንዲሁም (2) ጥቅሱ የሚነበብበት ምክንያት ግልጽ እንዲሆንላቸው ለማድረግ መጣር ይኖርብሃል። ይህን ለማሳካት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል።
ጥያቄ ጠይቅ። መልሱን አድማጮች በግልጽ የማያውቁት ከሆነ ይህ ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል። ጥያቄህን የአድማጮችን አእምሮ በሚያመራምር መንገድ አቅርብ። ኢየሱስ ይህንኑ ዘዴ ተጠቅሟል። ፈሪሳውያን በቤተ መቅደስ ተገኝተው ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለውን እውቀት ለመፈተን በሞከሩ ጊዜ ኢየሱስ “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?” ሲል ጠይቋቸዋል። እነርሱም “የዳዊት ልጅ” በማለት መለሱለት። ከዚያም ኢየሱስ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ለምን ‘ጌታዬ’ ይለዋል?” ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም መዝሙር 110:1ን ጠቀሰ። ፈሪሳውያኑ መልስ አልነበራቸውም። የተሰበሰቡት ሰዎች ግን ደስ ብሏቸው ኢየሱስን ያዳምጡት ነበር።—ማቴ. 22:41-46 አ.መ.ት
በአገልግሎት ሰዎችን ስታነጋግር ጥቅስ ለማስተዋወቅ የሚረዱትን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ማንሳት ትችል ይሆናል:- “እርስዎም ሆኑ እኔ የየራሳችን መጠሪያ ስም አለን። አምላክስ የራሱ መጠሪያ ስም ያለው ይመስልዎታል? መልሱን በዘጸአት 6:3 [የ1879 ትርጉም ] ላይ ማግኘት እንችላለን።” “መላው የሰው ዘር በአንድ መንግሥት የሚተዳደርበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ? ዳንኤል 2:44 ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ እንደሚሰጥ ልብ ይበሉ።” “መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ስላለው ሁኔታ የሚገልጸው ነገር አለ? እስቲ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች በተጨባጭ ከሚያዩት ነገር ጋር ለማዛመድ ይሞክሩ።” “ስቃይና ሞት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በራእይ 21:4, 5 ላይ ይገኛል።”
ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ የታሰበባቸው ጥያቄዎችን ተጠቅመህ ጥቅሶችን የምታስተዋውቅ ከሆነ አድማጮች የሚያውቋቸውን ጥቅሶች ሳይቀር በጉጉት እንዲጠባበቁ ልታደርጋቸው ትችላለህ። ሆኖም ይህን ግብ ለማሳካት የምታነሳቸው ጥያቄዎች በቀጥታ እነርሱን የሚመለከቱ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ትምህርቱ የአድማጮችን ትኩረት የሚስብ ቢሆንም እንኳ በተደጋጋሚ የሰሟቸውን ጥቅሶች ስታነብብ ሐሳባቸው ሊሰረቅ ይችላል። ይህ እንዳይሆን የአድማጮችን ትኩረት በሚስብ መንገድ ጥቅሱን እንዴት ማስተዋወቅ እንደምትችል አስቀድመህ ልታስብበት ይገባል።
አንድ ችግር ጥቀስ። አንድ ችግር በመጥቀስ መፍትሔውን በሚጠቁም ጥቅስ ላይ እንዲያተኩሩ ልታደርግ ትችል ይሆናል። አድማጮች በጣም የተጋነነ ነገር እንዲጠብቁ አታድርግ። ብዙውን ጊዜ አንድ ጥቅስ መፍትሔውን ሙሉ በሙሉ ላይጠቁም ይችላል። ይሁን እንጂ በምታነብበት ጊዜ አድማጮች ችግሩን በተመለከተ ጥቅሱ ምን መመሪያ እንደያዘ ልብ እንዲሉ ልታሳስባቸው ትችል ይሆናል።
በተመሳሳይም ጥሩ ምግባርን በተመለከተ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ከጠቀስህ በኋላ በዚያ መሠረት መመላለስ ምን ጥቅም እንዳለው የሚያጎላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምሳሌ አድርገህ ልታቀርብ ትችላለህ። አንዳንድ ተናጋሪዎች አንድ ጥቅስ ከትምህርቱ ጋር በቀጥታ የሚዛመዱ ሁለት (ወይም ከዚያ በላይ) ነጥቦች በሚኖሩት ጊዜ አድማጮች እነዚህን ነጥቦች ልብ እንዲሉ ያደርጋሉ። የተጠቀሰው ችግር ለአድማጮች ውስብስብ እንደሆነባቸው ከተሰማህ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን በመዘርዘር እንዲያስቡ ካደረግህ በኋላ ከጥቅሱ መልስ እንዲያገኙ ልትረዳቸው ትችላለህ።
ወሳኝ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርግ። አድማጮችህ ለትምህርቱ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ካደረግህና የተለያዩ ሰዎች ስለጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት የሚጠቁም አንድ ወይም ሁለት ሐሳብ ከጠቀስህ በኋላ ጥቅሱን እንደሚከተለው በማለት ብቻ ማስተዋወቅ ትችል ይሆናል:- “ስለዚህ ጉዳይ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ልብ በሉ።” ይህም ቀጥሎ የምታነብበው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ወሳኝ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያደርጋል።
ይሖዋ እንደ ዮሐንስ፣ ሉቃስ፣ ጳውሎስ እና ጴጥሮስ ያሉት ሰዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንዲጽፉ ተጠቅሞባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንደ ጸሐፊ ቢያገለግሉም የመልእክቱ ምንጭ ይሖዋ ነው። በተለይ የምታነጋግራቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ካልሆኑ አንድን ጥቅስ “ጴጥሮስ እንደጻፈው” ወይም “ጳውሎስ እንዳለው” ብሎ ማስተዋወቅ የአምላክ ቃል እንደሆነ የመናገሩን ያህል ኃይል ላይኖረው ይችላል። ኤርምያስ “የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ” ብሎ መልእክቱን እንዲያስተዋውቅ ይሖዋ ራሱ መመሪያ ሰጥቶት እንደነበር ልብ ማለት ይኖርብናል። (ኤር. 7:2፤ 17:20፤ 19:3፤ 22:2) አንድን ጥቅስ ስናስተዋውቅ የይሖዋን ስም ተጠቀምንም አልተጠቀምን ውይይታችንን ከመደምደማችን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ የእርሱ ቃል እንደሆነ መጠቆም ይኖርብናል።
በዙሪያው ያለውን መልእክት ግምት ውስጥ አስገባ። አንድን ጥቅስ እንዴት እንደምታስተዋውቅ ስታስብ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን መልእክት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። አንዳንድ ጊዜ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ መሠረት አድርገህ ታስተዋውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዙሪያው ያለው ሐሳብ ራሱም ጥቅሱን የምታስተዋውቅበትን መንገድ ሊወስን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ የተናገረውንና ከሐሰት አጽናኞቹ አንዱ የተናገረውን የምታስተዋውቅበት መንገድ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ሉቃስ ቢሆንም ያዕቆብ፣ ጳውሎስ፣ ፊልጶስ፣ እስጢፋኖስ እና መላእክት አልፎ ተርፎም ገማልያልና ክርስቲያን ያልነበሩ ሌሎች አይሁዳውያን የተናገሩትን ነገር ጠቅሶ ጽፏል። ጥቅሱን ማን እንደተናገረው አድርገህ ታስተዋውቃለህ? ለምሳሌ ያህል ሁሉንም መዝሙራት ዳዊት እንዳልጻፋቸው ወይም መላው የምሳሌ መጽሐፍ በሰሎሞን እንዳልተጻፈ አስታውስ። ጸሐፊው መልእክቱን የተናገረው ለማን እንደሆነና አጠቃላይ ርዕሰ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ማወቁም በጣም አስፈላጊ ነው።
የጥቅሱን ሥረ መሠረት አስረዳ። በተለይ ይህን ማድረግህ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው በመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሁኔታዎች እየተወያያችሁበት ካለው ሐሳብ ጋር በሚገባ ማዛመድ ከቻልክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአንድን ጥቅስ ይዘት ለመረዳት ሥረ መሠረቱን ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ስለ ቤዛ የሚገልጽ ንግግር ስትሰጥ ዕብራውያን 9:12, 24ን ለመጠቀም ፈለግህ እንበል። በዚህ ጊዜ ጥቅሱን ከማንበብህ በፊት ስለ ማደሪያው ድንኳን ውስጠኛ ክፍል አጠር ያለ ማብራሪያ መስጠቱን አስፈላጊ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ይህ ውስጠኛ ክፍል ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የገባበትን ቦታ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደሚያመለክት ቅዱሳን ጽሑፎች ይጠቁማሉ። ይሁንና ስለ ጥቅሱ ሥረ መሠረት የምትሰጠው ማብራሪያ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ የምታስተዋውቀው ጥቅስ የያዘውን መልእክት የሚሸፍን መሆን የለበትም።
ጥቅሶችን የምታስተዋውቅበትን መንገድ ለማሻሻል እንድትችል ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ልብ በል። እነዚህ ዘዴዎች ጥቅሱን ጥሩ አድርጎ በማስተዋወቅ ረገድ ያላቸውን ጠቀሜታ አገናዝብ። የራስህን ክፍል ስትዘጋጅ ቁልፍ የሆኑትን ጥቅሶች በመምረጥ የተጠቀሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ አስተውል። እያንዳንዱን ጥቅስ ጥሩ አድርገህ መጠቀም እንድትችል ምን ብለህ እንደምታስተዋውቀው በደንብ ተዘጋጅ። ቀስ እያልክ ደግሞ የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች ሁሉ በዚሁ መንገድ ማስተዋወቅን ልትለማመድ ትችላለህ። በዚህ ረገድ ማሻሻያ እያደረግህ ከሄድህ የአምላክ ቃል ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ትችላለህ።