ጥናት 21
ጥቅስ ስታነብብ ተፈላጊውን ነጥብ ማጉላት
ከሰዎች ጋር ስትወያይም ይሁን ንግግር ስትሰጥ ስለ አምላክ ዓላማ የምትጠቅሰው ሐሳብ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብ የሚጠይቅ ሲሆን ጥቅሶቹ በሚገባ መነበብ ይኖርባቸዋል።
ተገቢውን ስሜት በሚያንጸባርቅ መንገድ ማንበብ። ጥቅሶችን የምታነብበት መንገድ ድርቅ ያለ መሆን የለበትም። ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት። መዝሙር 37:11ን በምታነብበት ጊዜ ድምፅህ በጥቅሱ ላይ የተገለጸውን የሰላም ተስፋ እንደምትናፍቅ የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባል። ስቃይና ሞት እንደሚያከትም የሚናገረውን ራእይ 21:4ን ስታነብብ የሰው ልጅ ስለሚያገኘው ታላቅ እፎይታ ያለህ ጥልቅ አድናቆት በድምፅህ ቃና መንጸባረቅ ይኖርበታል። ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ከደረሰው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ እንድንወጣ ጥሪ የሚያቀርበው ራእይ 18:2, 4, 5 የመልእክቱን አጣዳፊነት በሚያሳይ መንገድ ሊነበብ ይገባል። ይህ ሲባል ግን በንባብህ የምታንጸባርቀው ስሜት ከውስጥህ የሚመነጭ እንጂ የተጋነነ መሆን የለበትም። የምታነብበትን ስሜት ለመመጠን የሚረዳህ ጥቅሱና የተጠቀሰበት ምክንያት ነው።
ትክክለኛዎቹን ቃላት ማጉላት:- በአንድ ጥቅስ ላይ የምትሰጠው ማብራሪያ በተወሰነው ክፍል ላይ ብቻ ያተኮረ ከሆነ በምታነብበት ጊዜ ያንን የጥቅሱን ክፍል ማጉላት ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል ‘አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለ መፈለግ’ እያብራራህ ከሆነ ማቴዎስ 6:33ን ስታነብብ “ጽድቁንም” ወይም “ይህም ሁሉ” የሚሉትን መግለጫዎች ማጉላት አይኖርብህም።
በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ንግግር ስታቀርብ ማቴዎስ 28:19ን ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል። ታዲያ ማጉላት የሚኖርብህ የትኞቹን ቃላት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ተጨማሪ ጥረት እንዲያደርጉ ማበረታታት ከፈለግህ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ማጉላት ይኖርብሃል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመንገር ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን በተመለከተ ስትናገር ወይም አንዳንድ አስፋፊዎች እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ ሄደው እንዲያገለግሉ ስታበረታታ “አሕዛብን ሁሉ” የሚለውን የጥቅሱን ክፍል ማጉላት ትችላለህ።
ብዙውን ጊዜ ጥቅስ የሚጠቀሰው ለአንድ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ወይም አንድን ሐሳብ ለመደገፍ ነው። በጥቅሱ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ሐሳብ ካጎላህ አድማጮች ጥቅሱ ከጉዳዩ ጋር ያለውን ዝምድና ማስተዋል ሊቸገሩ ይችላሉ። ነጥቡ ለአንተ ግልጽ ሆኖልሃል ማለት ለእነርሱም ግልጽ ይሆንላቸዋል ማለት አይደለም።
ለምሳሌ ያህል የያዝኸው መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 83:18 ላይ መለኮታዊውን ስም የሚጠቀም ከሆነ “ልዑል” የሚለውን ቃል ብቻ ብታጎላ የምታነጋግረው ሰው አምላክ የግል መጠሪያ አለው የሚለውን ለአንተ ግልጽ የሆነ እውነት ሳያስተውል ሊቀር ይችላል። ጠበቅ አድርገህ መግለጽ ያለብህ “ይሖዋ” የሚለውን ስም ነው። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ለማስረዳት በማሰብ ይህንኑ ጥቅስ ስታነብብ ማጉላት ያለብህ “ልዑል” የሚለውን ቃል ነው። በተመሳሳይም እምነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት ለማስረዳት አስበህ ያዕቆብ 2:24ን ስታነብብ “በሥራ” የሚለውን ቃል ትተህ “እንዲጸድቅ” የሚለውን ቃል ብታጎላ አንዳንድ አድማጮችህ የተፈለገውን ነጥብ ላይረዱት ይችላሉ።
ሮሜ 15:7-13ም ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ይህ ጥቅስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከአሕዛብ ወገን የሆኑና በትውልድ አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖችን ላቀፈ አንድ ጉባኤ በጻፈው መልእክት ውስጥ የሚገኝ ነው። ጳውሎስ የክርስቶስ አገልግሎት የተገረዙ አይሁዳውያንን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ የመጡትን ጭምር የሚጠቅም እንደሆነ እያብራራ ነው። ይህም ‘አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ’ ምክንያት እንደሚሆን ጠቅሷል። ጳውሎስ አሕዛብ ያገኙትን ይህንን አጋጣሚ የሚያረጋግጡ አራት ጥቅሶች ተጠቅሟል። እያብራራ ያለውን ሐሳብ ለማጉላት ከፈለግህ እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ልታነባቸው ይገባል? ለማጉላት በፈለግኸው ቃል ላይ ምልክት የምታደርግ ከሆነ ከቁጥር 8 እና 9 “አሕዛብ፣” ከቁጥር 11 “እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ” እና “ሕዝቦቹም ሁሉ” እንዲሁም ከቁጥር 12 “አሕዛብ” የሚሉትን ቃላት ትመርጥ ይሆናል። እነዚህን ቃላት እያጎላህ ሮሜ 15:7-13ን ለማንበብ ሞክር። እንዲህ ካደረግህ ጳውሎስ እያብራራው ያለው ነጥብ ይበልጥ ግልጽና ለመረዳትም ቀላል ይሆናል።
ለማጉላት የሚረዱ ዘዴዎች። ለየት ብለው እንዲታዩ የምትፈልጋቸውን መልእክት አዘል ቃላት በተለያየ መንገድ ማጉላት ትችል ይሆናል። ይሁንና የምትጠቀምበት ዘዴ ከጥቅሱ ይዘትና ከንግግሩ ነጥቦች ጋር የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ቀጥሎ ለማጉላት የሚረዱ አንዳንድ ዘዴዎችን እንመለከታለን።
ድምፅን መለዋወጥ። ይህም መልእክት አዘል የሆኑት ቃላት ከቀረው ዓረፍተ ነገር ለየት ብለው እንዲታዩ የሚያደርግን ማንኛውንም የድምፅ ለውጥ ያመለክታል። በአንዳንድ ቋንቋዎች የድምፅን መጠን በመጨመር ወይም በመቀነስ ማጉላት ይቻል ይሆናል። በሌሎች ቋንቋዎች ግን እንዲህ ማድረግ ጭራሽ ትርጉሙን ሊቀይረው ይችላል። ቁልፍ የሆነው ቃል ላይ ስትደርስ ዝግ ካልክ ለዚያ ቃል ትኩረት እንዲሰጠው ታደርጋለህ። ቋንቋህ ድምፅን በመለዋወጥ ቃላትን ማጉላት የማይፈቅድ ከሆነ ይህንን ለማድረግ በቋንቋው የተለመደውን ማንኛውንም ዘዴ መጠቀም ያስፈልግ ይሆናል።
ቆም ማለት። ልታጎላው ከፈለግኸው የጥቅሱ ክፍል በፊት ወይም በኋላ ወይም በሁለቱም ቦታ ቆም ማለት ይቻላል። ዋናው ነጥብ ላይ ስትደርስ ቆም ማለት አድማጮች ቀጥሎ የሚነበበውን በጉጉት እንዲጠባበቁ የሚያደርግ ሲሆን ከተነበበ በኋላ ቆም ማለት ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ እንዲያስቡበት ያደርጋል። ሆኖም አሁንም አሁንም ቆም የምትል ከሆነ ጎላ ብሎ የሚታይ ነጥብ አይኖርም።
መደጋገም። ወደኋላ መለስ ብለህ ቃሉን ወይም ሐረጉን ደግመህ በማንበብ አንድን ነጥብ ማጉላት ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ የተሻለ የሚሆነው ጥቅሱን አንብበህ ከጨረስህ በኋላ ማጉላት የምትፈልገውን ሐሳብ መድገሙ ነው።
አካላዊ መግለጫ። ፊታችን ላይ የሚነበበውን ስሜት ጨምሮ ማንኛውም አካላዊ መግለጫ ቃሉን ይበልጥ ያጠናክረዋል።
የድምፅ ቃና። በአንዳንድ ቋንቋዎች ቃላቱ የሚነበቡበት ቃና ትርጉማቸውን ሊለውጥ እንዲሁም ለየት ብለው እንዲታዩ ሊያደርግ ይችላል። በዚህም ረገድ በተለይ ደግሞ አነጋገሩ የምጸት በሚሆንበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
ጥቅሱን ሌሎች በሚያነቡበት ጊዜ። የምታነጋግረው ሰው ጥቅሱን ሲያነብብ የማይፈለገውን ቃል ሊያጎላ ወይም ደግሞ ምንም ቃል ሳያጎላ ሊቀር ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? ብዙውን ጊዜ የጥቅሱን መልእክት ማብራራቱ የተሻለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ያንን ሐሳብ የሚያስተላልፉት የጥቅሱ ቃላት ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ ትችል ይሆናል።