ጥናት 3
የቃላት ትክክለኛ አጠራር
ሁሉም ክርስቲያኖች በትምህርት የገፉ ናቸው ማለት አይቻልም። ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ እንኳ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ተደርገው ተገልጸዋል። (ሥራ 4:13 አ.መ.ት ) የሆነ ሆኖ ቃላቱን በትክክል ባለመጥራትህ ምክንያት የአድማጮችህ ትኩረት ከምታቀርበው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳይሰረቅ መጠንቀቁ በጣም አስፈላጊ ነው።
ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ። ለሁሉም ቋንቋ የሚሠራ የቃላት አጠራር ደንብ ማውጣት አይቻልም። ብዙ ቋንቋዎች የሚጻፉት እያንዳንዳቸው አንድ ድምፅ የሚወክሉ ሆሄያትን በማገጣጠም ነው። ከአማርኛ ሌላ እንደ ላቲን፣ አረብኛ፣ ሲሪሊክ፣ ግሪክኛ እና ዕብራይስጥ ያሉ ቋንቋዎችም ድምፆችን የሚወክሉ ሆሄያት አሏቸው። የቻይና የጽሑፍ ቋንቋ የሚጠቀመው፣ እያንዳንዳቸው አንድ ድምፅ የሚወክሉ ፊደላትን ሳይሆን የተለያዩ መልእክቶችን አካትተው የያዙ ምልክቶችን ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ምልክቶች አንድን ቃል ወይም የቃል ክፍል የሚወክሉ ናቸው። የጃፓንና የኮሪያ ቋንቋዎች ከቻይና ቋንቋ የተወሰዱ ምልክቶችን ቢጠቀሙም ምልክቶቹ የሚወክሉት ድምፅም ሆነ የሚሰጡት ትርጉም ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል።
የተለያዩ ድምፆችን የሚወክሉ ሆሄያት ባሏቸው ቋንቋዎች ቃላቱን በትክክል ለመጥራት ለእያንዳንዱ ሆሄ ወይም አንድ ላይ ተጣምረው ለሚጻፉት ሆሄያት ትክክለኛውን ድምፅ መጠቀም ያስፈልጋል። ቋንቋው እንደ ግሪክኛ፣ ስፓንኛ እና ዙሉ ቋንቋዎች ወጥ የሆነ ሥርዓት የሚከተል በሚሆንበት ጊዜ ቃላቱን በትክክል በመጥራት ረገድ ችግር አይኖርም። ይሁን እንጂ ከቋንቋዎች መወራረስ የተነሣ ከባዕድ ቋንቋ የተወረሰ የአንድ ቃል አጠራር የቃሉን ምንጭ የሚያንጸባርቅበት ጊዜ ይኖራል። ከዚህ የተነሣ አንድ ሆሄ ወይም ከአንድ በላይ ሆሄያት የተለያየ አነባበብ ሊኖራቸው ወይም ደግሞ በቃሉ ውስጥ ጭራሽ ሳይነበቡም ሊታለፉ ይችላሉ። አንዳንድ ለየት ያለ ሁኔታ ያላቸውን ቃላት በቃል ማጥናትና በንግግርህ ደጋግመህ መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። በቻይና ቋንቋ ቃላትን በትክክል ለመጥራት በሺህ የሚቆጠሩ ምልክቶችን በቃል ማጥናት ያስፈልጋል። በአንዳንድ ቋንቋዎች ቃሉ የሚነበብበት ቃና ሲለወጥ የቃሉ ትርጉምም ይለወጣል። በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ካላደረግን የተሳሳተ መልእክት ልናስተላልፍ እንችላለን።
የአንድ ቋንቋ ቃላት በቀለማት (syllables) የተከፋፈሉ ከሆነ መጥበቅ ያለበትን ክፍል በተገቢው መንገድ የማጥበቁ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እንዲህ ዓይነት አወቃቀር ያላቸው ብዙ ቋንቋዎች ቃላቱ የሚጠብቁበት ወጥ የሆነ ሥርዓት አላቸው። ለየት ያለ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ቃሉ እንዴት እንደሚነበብ የሚጠቁሙ ምልክቶች ይጨመሩ ይሆናል። ይህም ቃላቱን በትክክል ለማንበብ ይረዳል። ቋንቋው ወጥ የሆነ የአነባበብ ሥርዓት ከሌለው ግን ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነገር በቃል ማጥናት ያስፈልጋል።
ቃላትን በትክክል በመጥራት ረገድ ጥንቃቄ የሚያሻቸው አንዳንድ ጉዳዮች አሉ። ቃሉን ስለምታነብበት መንገድ ከልክ በላይ የምትጨነቅ ከሆነ ሌላ ሰው ለመኮረጅ የምትጥር አልፎ ተርፎም አጉል የምትራቀቅ ሊያስመስልብህ ይችላል። በአብዛኛው የማይሠራበት ዓይነት የቃላት አጠራር መጠቀምም ተመሳሳይ መልእክት ሊኖረው ይችላል። ይህ ደግሞ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳችን ከመሳብ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በአንጻሩ ደግሞ ስለ አነጋገራችንም ሆነ ስለ ቃላት አጠራራችን ከልክ በላይ ግዴለሽ መሆን አይገባም። ከዚህ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦች “አጥርቶ መናገር” በሚለው ጥናት ውስጥ ተብራርተዋል።
በአንድ ቋንቋ ውስጥ ተቀባይነት ያለው የቃላት አጠራር ከአገር ወደ አገር፣ ሌላው ቀርቶ በአንድ አገር ውስጥ እንኳ ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል። ከሌላ አገር የመጣ አንድ ሰው የአገሬውን ቋንቋ በተለየ ዘዬ ሊናገረው ይችላል። መዝገበ ቃላትም ለአንድ ቃል ከአንድ በላይ ትክክለኛ አጠራር ሊያስቀምጡ ይችላሉ። በተለይ አንድ ሰው ብዙም የትምህርት አጋጣሚ ካላገኘ ወይም አሁን የሚናገረው ቋንቋ አፍ መፍቻ ቋንቋው ካልሆነ የአካባቢውን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ሰዎችን በጥሞና ማዳመጡና የእነርሱን የቃላት አጠራር መከተሉ በእጅጉ ይጠቅመዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት አክብሮት እንዲኖራቸው በሚያደርግና በቀላሉ እንዲረዱት በሚያስችል መንገድ መናገር እንፈልጋለን።
በዕለት ተዕለት ውይይት ወቅት ብዙውን ጊዜ በደንብ የምታውቃቸውን ቃላት መጠቀሙ የተሻለ ይሆናል። በአጠቃላይ ሲታይ ከሰዎች ጋር በምታደርገው ውይይት የቃላት ትክክለኛ አጠራር ብዙም ችግር አይፈጥርም። ይሁን እንጂ ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ በየዕለቱ ከሰዎች ጋር ስትወያይ የማትጠቀምባቸው ቃላት ይገጥሙህ ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ለሌሎች የሚያነብቡባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ለሰዎች ስንመሠክር መጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን። አንዳንድ ወንድሞች በመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንዲሁም በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ወቅት አንባቢ ሆነው ይመደቡ ይሆናል። በትክክል ማንበባችን እንዲሁም በተሳሳተ የቃላት አጠራር የአድማጮችን ትኩረት አለመስረቃችን አስፈላጊ ነው።
ማሻሻል የሚቻልባቸው መንገዶች። ቃላትን በትክከል የመጥራት ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ችግሩ እንዳለባቸው እንኳ አይገነዘቡም። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ቃላትን በትክክል በመጥራት ረገድ ማሻሻል ስለሚገባህ ጉዳይ ከጠቆመህ በአሳቢነት የሰጠህን ምክር በደስታ ተቀበል። ችግሩን ካወቅህ በኋላ ማሻሻያ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ቃላትን በትክክል የመጥራት ችሎታህን ማሻሻል የምትችልበት አንደኛው መንገድ ችሎታ ላለው ሰው ማንበብና የተሳሳትክባቸውን ቦታዎች እንዲጠቁምህ መጠየቅ ነው።
በዚህ ረገድ ሊረዳህ የሚችለው ሌላው መንገድ ጥሩ ተናጋሪዎችን ልብ ብሎ ማዳመጥ ነው። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ወይም የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን የካሴት ቅጂ ማግኘት የምትችል ከሆነ በሚገባ ተጠቀምባቸው። በምታዳምጥበት ጊዜ አንተ ከለመድኸው ለየት ያለ አጠራር ያላቸውን ቃላት ልብ በል። እነዚህን ቃላት በማስታወሻ ያዝና ተለማመዳቸው።
በብዙ ቋንቋዎች የቃላቱን ትርጉም ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ አጠራሩን የሚጠቁሙ መዝገበ ቃላት ይገኛሉ። በቋንቋህ እንዲህ ያለ መዝገበ ቃላት የሚገኝ ከሆነ የማታውቀው ቃል ሲገጥምህ ሊረዳህ ይችላል። የቃላቱን ትክክለኛ አጠራር የሚጠቁሙትን ምልክቶች መረዳት ከከበደህ በመዝገበ ቃላቱ የመጀመሪያ ገጾች ላይ የሚገኘውን ማብራሪያ ተመልከት ወይም ሌላ ሰው እንዲረዳህ ጠይቅ። መዝገበ ቃላቱ ቃሉን የት ላይ ማጥበቅ እንዳለብህ ሊጠቁምህ ይችላል። አንድ ቃል እንደ አገባቡ ከአንድ በላይ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ሊነበብ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። መዝገበ ቃላቱን ከመዝጋትህ በፊት የቃሉን ትክክለኛ አጠራር ድምፅህን እያሰማህ ደጋግመህ ተለማመደው። ከጊዜ በኋላ ንግግርህ ከቃላት ትክክለኛ አጠራር ግድፈት የጠራ ስለሚሆን የመናገር ችሎታህን ለማሻሻል ይረዳሃል።