ጥናት 11
ወዳጃዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ
በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የተለያዩ ስሜቶች ይንጸባረቃሉ። አንድ ሰው ስሜቱን ሲገልጽ በልቡ ያለውን ያወጣል፣ ውስጣዊ ማንነቱ ይገለጣል እንዲሁም ስለ ሰዎችም ሆነ ስለ አንዳንድ ሁኔታዎች ያለው ስሜት ይንጸባረቃል። ብዙ ሰዎች በልጅነታቸው ተሸማቅቀው በማደጋቸውና አንዳንድ ጊዜም የአካባቢው ባሕል ከሚያሳድረው ተጽእኖ የተነሳ ስሜታቸውን መግለጽ ይቸግራቸዋል። ይሖዋ ግን መልካም ባሕርያትን እንድናዳብርና እነዚህን ባሕርያት በተገቢው መንገድ እንድናሳይ ያበረታታናል።—ሮሜ 12:10፤ 1 ተሰ. 2:7, 8
አድማጮች ምን ዓይነት ስሜት መግለጽ እንደፈለግን ከምንጠቀምባቸው ቃላት በትክክል ሊረዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ቃላቱን ስንጠራ ተገቢውን ስሜት የማናንጸባርቅ ከሆነ ከልብ እየተናገርን ስለመሆናችን ሊጠራጠሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ተገቢውን ስሜት በሚገልጽ መንገድ ቃላቱን የምንጠራ ከሆነ ንግግራችን የአድማጮቻችንን ልብ የሚነካ፣ ውብና ማራኪ ይሆናል።
ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት:- ብዙውን ጊዜ ወዳጃዊ ስሜት እንድታሳይ የሚያደርግህ ለሰዎች ያለህ አሳቢነት ነው። ድንቅ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ስንናገርና ስለ ጥሩነቱ ያለንን አድናቆት ስንገልጽ ድምፃችን ውስጣዊ ስሜታችንን የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል። (ኢሳ. 63:7-9) ከሰዎች ጋር ስንነጋገርም ቢሆን አነጋገራችን ሌሎችን የሚማርክ ወዳጃዊ ስሜት ሊንጸባረቅበት ይገባል።
የሥጋ ደዌ የያዘው አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ይመጣና እንዲፈውሰው ይማጸነዋል። ኢየሱስ “እወዳለሁ፣ ንጻ” ሲለው ምን ዓይነት የድምፅ ቃና እንደተጠቀመ እስቲ ገምት። (ማር. 1:40, 41) እንዲሁም ለ12 ዓመት ደም ሲፈስሳት የነበረች ሴት ከኢየሱስ ኋላ ቀስ ብላ ተጠግታ የመጎናጸፊያውን ጫፍ ስትነካ የሆነውን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ሴቲቱ መጋለጧ እንዳልቀረላት አውቃ ወደ ኢየሱስ ፊት እየተንቀጠቀጠች ትመጣና እግሩ ላይ ወድቃ በዚያ ለነበረው ሕዝብ በሙሉ ለምን የመጎናጸፊያውን ዘርፍ እንደነካችና እንዴት እንደተፈወሰች ትናገራለች። ኢየሱስ ይህችን ሴት “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” ሲላት በምን ዓይነት የድምፅ ቃና እንደተናገረ አስብ። (ሉቃስ 8:42ለ-48) ኢየሱስ በእነዚህ ወቅቶች ያሳየው ወዳጃዊ ስሜት እስከዛሬም ድረስ የሰዎችን ልብ የሚነካ ሆኗል።
እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ ተሰምቶን ሰዎችን ከልብ ለመርዳት የምንፈልግ ከሆነ ይህ ስሜታችን በአነጋገራችን ይንጸባረቃል። እንዲህ ያለው ወዳጃዊ ስሜት ከልብ የሚመነጭ ነው። የምናንጸባርቀው ወዳጃዊ ስሜት ሰዎች ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል። በመስክ አገልግሎት ሰዎችን በምክንያት ለማስረዳት ስንሞክር፣ ስናበረታታ፣ ስንመክርና ችግራቸውን ለመረዳት ስንጥር እንዲህ ያለውን ከልብ የመነጨ ስሜት ማንጸባረቅ የምንችልበት አጋጣሚ አለን።
ለሰዎች ያለህ ወዳጃዊ ስሜት በፊትህም ላይ ሊንጸባረቅ ይገባል። የበረደው ሰው ወደ እሳት እንደሚጠጋ ሁሉ ሞቅ ያለ ስሜት የምታሳይ ከሆነ አድማጮችህም ወደ አንተ ይሳባሉ። በውስጥህ ያለው ወዳጃዊ ስሜት ፊትህ ላይ የማይነበብ ከሆነ ግን አድማጮችህ ከልብ እንደምታስብላቸው ሊጠራጠሩ ይችላሉ። ለአድማጮችህ ያለህ ይህ ስሜት ከውስጥ ፈንቅሎ ካልመጣ በስተቀር እንዲሁ ለማስመሰል ያህል ብቻ ልታሳየው የምትችለው ነገር አይደለም።
ለአድማጮችህ ያለህ ወዳጃዊ ስሜት በድምፅህ ቃናም ጭምር መንጸባረቅ ይኖርበታል። ኃይለኛና ጎርናና ድምፅ ካለህ በንግግርህ ይህን ስሜት ማንጸባረቅ ሊያስቸግርህ ይችላል። ይሁን እንጂ ከልብ ጥረት ካደረግህ ከጊዜ በኋላ ማሻሻል ትችላለህ። ከአነጋገር አንጻር ካየነው ቁርጥ፣ ቁርጥ ያሉ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች ንግግርህ ድርቅ ያለ እንዲሆን እንደሚያደርጉት መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል። አንዳንድ ቃላትን ለስለስ ባለ የድምፅ ቃና መጥራትን ተለማመድ። ይህም ንግግርህ ወዳጃዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ያደርጋል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። ይህም ዋናው ትኩረትህ ምን ላይ ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። ስለምታነጋግራቸው ሰዎች ከልብ የምታስብና እነርሱን የሚጠቅም ሐሳብ ለማካፈል የምትጨነቅ ከሆነ ይህ ስሜት በአነጋገርህ መንጸባረቁ አይቀርም።
በጋለ ስሜት የሚቀርብ ንግግር አድማጮችን የሚቀሰቅስ ቢሆንም ለስለስ ያለ አነጋገር መጠቀምም አስፈላጊ ነው። አእምሮአቸውን መማረክ ብቻ ሳይሆን ልባቸው እንዲነካ ማድረግም ያስፈልጋል።
ሌሎች ስሜቶችን ማንጸባረቅ። በጭንቀት የተዋጠ ሰው እንደ ስጋትና ፍርሃት የመሳሰሉ ስሜቶች ያንጸባርቅ ይሆናል። ደስታ በሕይወታችን ውስጥ በጉልህ ሊንጸባረቅና ከሰዎችም ጋር ስንነጋገር በግልጽ ሊታይ የሚገባው ስሜት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከክርስቲያናዊ ባሕርይ ጋር የማይጣጣሙ አንዳንድ ስሜቶችን ማስወገድ ያስፈልጋል። (ኤፌ. 4:31, 32፤ ፊልጵ. 4:4) የትኛውንም ዓይነት ስሜት ቢሆን በምንመርጣቸው ቃላት፣ በድምፃችን ቃናና ኃይል፣ ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜትና በአካላዊ መግለጫዎቻችን ማሳየት እንችላለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉም ዓይነት ስሜቶች ተገልጸዋል ማለት ይቻላል። አንዳንዶቹ በቀጥታ ተጠቅሰዋል። ሌሎቹ ደግሞ በሚዘግባቸው ታሪኮች ውስጥ ተንጸባርቀዋል። እንዲህ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ ስሜቶቹን በድምፅህ ማንጸባረቅህ አንተም ሆነ አድማጮችህን በጥልቅ የሚነካ ይሆናል። ይህን ለማድረግ ግን ራስህን በባለ ታሪኮቹ ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልግሃል። ይሁን እንጂ ንግግር ስታቀርብ ቲያትር የምትሠራ መምሰል ስለሌለብህ በጣም እንዳይጋነን መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ምንባቡ በአድማጮችህ አእምሮ ውስጥ ሕያው ሆኖ እንዲሳል አድርግ።
ለትምህርቱ የሚስማማ። በጋለ ስሜት ለመናገር የሚረዳህ የትምህርቱ ይዘት እንደሆነ ሁሉ ወዳጃዊ መንፈስንም ሆነ ሌሎች ስሜቶችን ማሳየትህ በአብዛኛው የተመካው በመልእክቱ ይዘት ላይ ነው።
ማቴዎስ 11:28-30ን አውጣና ተመልከት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያንን በማውገዝ የተናገረው ሐሳብ የሚገኝበትን ማቴዎስ ምዕራፍ 23ን አንብብ። እነዚህን ኃይለኛ የውግዘት ቃላት የተናገረው ልዝብ ባለ የድምፅ ቃና ነው ማለት አይቻልም።
ይሁዳ ስለ ወንድሙ ስለ ብንያም ሲማጸን የተናገረውን ነገር የያዘው የዘፍጥረት ምዕራፍ 44 ታሪክ በምን ዓይነት ስሜት መነበብ የሚኖርበት ይመስልሃል? በቁጥር 13 ላይ የተንጸባረቀውን ስሜት አስተውል። በተጨማሪም በቁጥር 16 ላይ ይሁዳ፣ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው በምን ምክንያት እንደሆነ በሚጠቁም መንገድ ሲናገር የተሰማውንና በዘፍጥረት 45:1 ላይ የተንጸባረቀውን የዮሴፍ ስሜት ልብ በል።
እንግዲያው ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማንበብም ሆነ ለመናገር ስለ ቃሎቹና ስለ መልእክቱ ብቻ ሳይሆን ስለሚነገሩበት ስሜት ጭምር ማሰብ ይኖርብናል።