የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ለማንበብ ትጋ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ለማንበብ ትጋ

      አሁን አንተ እያደረግህ ያለኸውን ነገር እንስሳት ሊያደርጉት አይችሉም። በዛሬው ጊዜ ከ6 ሰዎች አንዱ ማንበብ አይችልም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ዕድል አለማግኘት ነው። ማንበብ ከሚችሉት መካከልም ቢሆን ብዙዎቹ አዘውትሮ የማንበብ ልማድ የላቸውም። ይሁንና ማንበብ መቻልህ ስለ ሌሎች አገሮች ለማወቅ፣ ከሌሎች ሰዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሮ ለመማር እንዲሁም በሕይወትህ የሚገጥሙህን አሳሳቢ ነገሮች ለመወጣት የሚረዳ ተግባራዊ እውቀት ለመገብየት ያስችልሃል።

      በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      ለልጆችህ የምታነብብላቸው ነገር ባሕርያቸውን ለመቅረጽ ሊረዳ ይችላል

      አንድ ወጣት በትምህርት ዓለም ከሚያሳልፈው ጊዜ የሚያገኘው ጥቅም በማንበብ ችሎታው ላይ የተመካ ነው። የማንበብ ችሎታው ሥራ ሲፈልግ ሊያገኝ በሚችለው የሥራ ዓይነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። ወይም ደግሞ ኑሮውን ለማሸነፍ ምን ያህል መሥራት እንዳለበትም ሳይቀር የሚወስን ሊሆን ይችላል። ጥሩ የማንበብ ልማድ ያላቸው የቤት እመቤቶች ቤተሰባቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ቤታቸውን በንጽሕና በመያዝና የቤተሰባቸውን አባላት ከበሽታ በመጠበቅ ረገድ የተሻለ ብቃት ይኖራቸዋል። አንባቢ የሆኑ እናቶችም በልጆቻቸው የአእምሮ ብስለት ረገድ በጎ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል።

      እርግጥ ከሁሉ የላቀው የማንበብ ጥቅም የአምላክን እውቀት ማግኘት የሚያስችልህ መሆኑ ነው። (ምሳሌ 2:​5) አምላክን የምናገለግልባቸው ብዙዎቹ መንገዶች የማንበብ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ይነበባሉ። ንባብ በመስክ አገልግሎት በሚኖርህ ውጤታማነት ረገድ የሚኖረውም ድርሻ ከፍተኛ ነው። ለእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምታደርገው ዝግጅትም ቢሆን ማንበብን ይጠይቃል። ከዚህ የተነሣ መንፈሳዊ እድገትህ በንባብ ልማድህ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው ማለት ይቻላል።

      አጋጣሚውን በሚገባ ተጠቀምበት

      በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      ለሌሎች ሕያው አድርጎ የማንበብ ችሎታ አዳብር

      ዛሬ የአምላክን መንገድ እየተማሩ ካሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ያላቸው የትምህርት ደረጃ ውስን ነው። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ማንበብን መማር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ወይም ደግሞ የንባብ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በግል እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጉባኤዎች መሠረተ ትምህርት የሚሰጥበት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ዝግጅት ብዙ ተጠቅመዋል። ጥሩ የንባብ ችሎታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንዳንድ ጉባኤዎች የንባብ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ሲሉ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጎን ለጎን ተጨማሪ ዝግጅት ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች ባይኖሩም እንኳ አንድ ሰው በየዕለቱ ጮክ ብሎ ለማንበብ ጊዜ በመመደብና በትምህርት ቤቱ አዘውትሮ እየተገኘ ተሳትፎ በማድረግ የንባብ ችሎታውን ማሻሻል ይችላል።

      የሚያሳዝነው ግን አስቂኝ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረው ንባብ በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገው ምክንያት ሆነዋል። አንድ ሰው አዘውትሮ ቴሌቪዥን የሚመለከትና እምብዛም የማያነብብ ከሆነ የማንበብ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በትክክል የማሰብና የማመዛዘን እንዲሁም ሐሳቡን አቀነባብሮ የመግለጽ ችሎታው ይዳከማል።

      ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችሉንን ጽሑፎች ያቀርብልናል። እነዚህ ጽሑፎች ለመንፈሳዊነታችን ወሳኝ የሆነ ብዙ ትምህርት ይዘው ይወጣሉ። (ማቴ. 24:​45፤ 1 ቆሮ. 2:​12, 13) ዓበይት ስለሆኑ የዓለም ክንውኖችና እነዚህ ክንውኖች ስላላቸው ትርጉም ይነግሩናል፣ ከተፈጥሮ ጋር ይበልጥ እንድንተዋወቅ ይረዱናል እንዲሁም የሚያሳስቡንን አንዳንድ ጉዳዮች እንዴት መወጣት እንደምንችል ያስተምሩናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገልና የእርሱን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ በጥልቀት ያብራሩልናል። እንዲህ ያለው የሚገነባ ንባብ መንፈሳዊ ሰው እንድትሆን ይረዳሃል።

      እርግጥ ካልተጠነቀቅን ማንበብ ምንም አደጋ የለውም ማለት አይደለም። ይህን ችሎታ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። እንደምንመገበው ምግብ ሁሉ የምናነበውንም ነገር መምረጥ ይኖርብናል። ምንም ጠቀሜታ የሌለውን ወይም ሊመርዝህ የሚችልን ምግብ የምትመገብበት ምን ምክንያት ይኖራል? በተመሳሳይም ልብህንና አእምሮህን የሚበክል መረጃ የያዘ ጽሑፍ ከሆነ በአጋጣሚ ያገኘኸውም እንኳ ቢሆን ልታነብበው አይገባም። የምናነብባቸውን ነገሮች በመምረጥ ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል። አንድ ጽሑፍ ለማንበብ ከመወሰንህ በፊት እንደሚከተሉት ያሉትን ጥቅሶች አስብ:- መክ. 12:​12, 13፤ ኤፌ. 4:​22-24፤ 5:​3, 4፤ ፊልጵ. 4:​8፤ ቆላ. 2:​8፤ 1 ዮሐ. 2:​15-17 እንዲሁም 2 ዮሐ. 10

      ስታነብብ ተገቢው የልብ ዝንባሌ ይኑርህ

      በምናነብበት ጊዜ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል የሚለው ነጥብ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ መጻሕፍትን ጠንቅቀው የሚያውቁት የሃይማኖት መሪዎች ላቀረቡት መሰሪ ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት “አላነበባችሁምን?” እንዲሁም “ከቶ አላነበባችሁምን?” እያለ ይጠይቃቸው እንደነበር በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ማቴ. 12:3, 5፤ 19:4፤ 21:16, 42፤ 22:31) ስናነብብ ትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ከሌለን ወደተሳሳተ መደምደሚያ ልናመራ ወይም ጨርሶ ነጥቡን ልንስት እንደምንችል ከዚህ ታሪክ እንማራለን። ፈሪሳውያን በመጻሕፍት አማካኝነት የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉ ስለመሰላቸው ቅዱሳን ጽሑፎችን ያነብቡ ነበር። ኢየሱስ ለይሖዋ ፍቅር የሌላቸውና አምላክ ያደረገውን የመዳን ዝግጅት የማይቀበሉ ሰዎች ይህን ሽልማት እንደማያገኙ ጠቁሟል። (ዮሐ. 5:39-43) ፈሪሳውያኑ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመመርመር የተነሡበት ዓላማ ከራስ ወዳድነት የመነጨ ነበር። በዚህ ምክንያት የደረሱባቸው ብዙዎቹ መደምደሚያዎች የተሳሳቱ ነበሩ።

      የአምላክን ቃል እንድናነብብ የሚገፋፋን ዋነኛው ነገር ለይሖዋ ያለን ፍቅር መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል” ስለሚል ለይሖዋ ያለን እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ስለ ፈቃዱ እንድንማር ያነሳሳናል። (1 ቆሮ. 13:6) ከዚህ ቀደም የማንበብ ፍላጎት ያልነበረን ሰዎች ብንሆንም እንኳ ይሖዋን ‘በፍጹም አሳባችን’ የምንወድድ ከሆነ የአምላክን እውቀት ለመቅሰም እንጥራለን። (ማቴ. 22:​37) ፍቅር ለአንድ ነገር ጉጉት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ይህ ጉጉት ደግሞ የማወቅ ፍላጎት ያሳድርብናል።

      ለንባብ ፍጥነትህ ትኩረት መስጠት

      ንባብ ከቃላት ጋር የመተዋወቅ ጉዳይ ነው። አሁንም ቢሆን እያነበብህ ያለኸው ቃላቱን ስለምታውቃቸውና ትርጉማቸውን ስለምታስታውስ ነው። የምታውቃቸው ቃላት ብዛት እያደገ ከሄደ የንባብ ፍጥነትህ ሊጨምር ይችላል። እያንዳንዱን ቃል በተናጠል ከማየት ይልቅ ሁለት ሦስት ቃላትን በአንድ ጊዜ ለማየት ሞክር። ከቃላት ጋር ያለህ ትውውቅ እያደገና እየሰፋ ሲሄድ የምታነብበውን ነገር በቀላሉ መረዳት ትችላለህ።

      በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      አንድ ላይ ማንበብ የቤተሰብ አባላትን ያቀራርባል

      ትምህርቱ ከበድ ያለ በሚሆንበት ጊዜ ግን የምታደርገው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። ይሖዋ ቅዱሳን ጽሑፎችን ስለማንበብ ኢያሱን እንዲህ ሲል መክሮታል:- ‘የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ድምፅህን ዝቅ አድርገህ አንብበው።’ (ኢያሱ 1:8 NW ) በአብዛኛው አንድ ሰው ድምፁን ዝቅ አድርጎ ብቻውን የሚያወራው በሚያሰላስልበት ጊዜ ነው። በመሆኑም ‘ዝቅ ባለ ድምፅ ማንበብ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “ማሰላሰል” ተብሎም ተተርጉሟል። (መዝ. 63:6 አ.መ.ት ፤ መዝ. 77:​12 አ.መ.ት ፤ መዝ. 143:5) አንድ ሰው በሚያሰላስልበት ጊዜ ረጋ ብሎ ጥልቀት ባለው መንገድ ጉዳዩን ያብሰለስላል። እያሰላሰሉ ማንበብ የአምላክ ቃል በአእምሮና በልባችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን፣ ምክሮችን፣ ምሳሌዎችን፣ ግጥሞችን፣ መለኮታዊ የፍርድ ብያኔዎችን፣ ስለ ይሖዋ ዓላማ የሚገልጹ ማብራሪያዎችን እንዲሁም የብዙ ሰዎችን የሕይወት ተሞክሮ አካትቶ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ መልእክቶች በይሖዋ መንገድ መመላለስ ለሚፈልጉ ሁሉ እጅግ ጠቃሚ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን በአእምሮና በልብህ ውስጥ እንዲቀረጽ በሚያስችል መንገድ ማንበብህ ምንኛ ጠቃሚ ነው!

      ሐሳብህን መሰብሰብ ተማር

      በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      መንፈሳዊ እድገትህ በንባብ ልማድህ ላይ የተመካ ነው

      በምታነብበት ጊዜ ራስህን በታሪኩ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ባለ ታሪኮቹን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳልና ራስህን በእነርሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመጋራት ሞክር። በ⁠1 ሳሙኤል ምዕራፍ 17 ላይ የተገለጸውን የዳዊትንና የጎልያድን ታሪክ የመሰለ ዘገባ በምታነብበት ጊዜ ይህንን ማድረጉ ብዙም ላይከብድ ይችላል። ይሁን እንጂ ስለ ማደሪያው ድንኳን ግንባታ ወይም ስለ ክህነት አገልግሎቱ መቋቋም በዘጸአትና በዘሌዋውያን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ ስታነብም ቢሆን ስለ ድንኳኑ ስፋትና ጥቅም ላይ ስለዋሉት ቁሳቁሶች በዓይነ ሕሊናህ መሳልህ ወይም ስለ ዕጣኑ፣ ስለሚጠበሰው እሸት እንዲሁም ስለሚቃጠለው መሥዋዕት መዓዛ ማሰብህ ንባብህን ሕያው ሊያደርግልህ ይችላል። የክህነት አገልግሎት ማከናወን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደነበር አስብ! (ሉቃስ 1:​8-10) በምታነብበት ጊዜ ከላይ እንደተገለጸው መላ የስሜት ሕዋሳትህን በመጠቀም በንባቡ መመሰጥህ የምታነብበውን ነገር ጠቀሜታ እንድታስተውልና በኋላም እንዳትረሳው ይረዳሃል።

      ይሁንና ካልተጠነቀቅህ ለማንበብ ስትሞክር ሐሳብህ እየተበተነ ሊያስቸግርህ ይችላል። ዓይኖችህ የምታነበው ነገር ላይ ተተክለው ሐሳብህ ግን ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል። ሙዚቃ ወይም ቴሌቪዥን ተከፍቷል? የቤተሰብ አባላት እያወሩ ነው? በተቻለ መጠን ፀጥ ያለ ቦታ ሆኖ ማንበብ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ሐሳባችን እንዲበተን የሚያደርጉ ነገሮች ከራሳችንም ሊመነጩ ይችላሉ። ምናልባት በሥራ ተወጥረህ ውለህ ይሆናል። ከሆነ የቀኑ ውሎህ በተደጋጋሚ ወደ አእምሮህ እየመጣ ሊያስቸግርህ ይችላል! እርግጥ ውሎህን መለስ ብለህ መቃኘትህ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ያለብህ እያነበብክ ባለህበት ጊዜ አይደለም። ምናልባት ንባብህን የጀመርከው ሐሳብህን ሰብስበህ ወይም ደግሞ ጸልየህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ማንበብህን ስትቀጥል ሐሳብህ መበተን ይጀምራል። እንደገና ሐሳብህን ለመሰብሰብ ሞክር። አእምሮህ እያነበብከው ባለኸው ነገር ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ራስህን መግዛት ያስፈልግሃል። እንዲህ ካደረግህ ቀስ በቀስ እያሻሻልክ ትሄዳለህ።

      አንድ የማታውቀው ቃል ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? የአንዳንድ እንግዳ የሆኑ ቃላት ፍቺ በዚያው በጽሑፉ ውስጥ ይገለጽ ወይም ማብራሪያ ይሰጥበት ይሆናል። ወይም ደግሞ በዙሪያው ካለው ሐሳብ የቃሉን ትርጉም መረዳት ትችል ይሆናል። ካልሆነ ግን መዝገበ ቃላት ተመልከት። ወይም ሌላ ሰው መጠየቅ እንድትችል ቃሉን ምልክት አድርግበት። ይህም የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ያሳድግልሃል እንዲሁም አንብቦ የመረዳት ችሎታህን ያጎለብትልሃል።

      ለሌሎች ማንበብ

      በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል

      ለሌሎች ለማንበብ ትጋ

      ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለማንበብ እንዲተጋ ሲመክረው መጥቀስ የፈለገው ለሌሎች ስለ ማንበብ ነበር። (1 ጢሞ. 4:​13) ለሌሎች በምናነብበት ጊዜ ንባባችንን ጥሩ ነው የሚያሰኘው ቃላቱን መጥራት መቻላችን ብቻ አይደለም። አንባቢው የቃላቱን ትርጉም እንዲሁም የሚያስተላልፉትን መልእክት ሊረዳ ይገባል። ሐሳቡን በትክክል መግለጽና ተገቢውን ስሜት ማንጸባረቅ የሚችለው ይህንን ሲያደርግ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ጥልቀት ያለው ዝግጅትና ልምምድ ይጠይቃል። በመሆኑም ጳውሎስ ‘ለማንበብ ትጋ ’ ሲል አጥብቆ አሳስቧል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ በዚህ ረገድ ግሩም ሥልጠና ታገኛለህ።

      ለንባብ ጊዜ መድብ

      “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኮላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።” (ምሳሌ 21:​5 አ.መ.ት ) የማንበብ ፍላጎታችንን በተመለከተም ይህ አባባል በትክክል ይሠራል! ከንባባችን “ትርፍ” ለማግኘት ከፈለግን ሌሎች ነገሮች ለንባብ የሚሆን ጊዜ እንዳያሳጡን ትጋት የተሞላበት እቅድ ማውጣት ይኖርብናል።

      የምታነብበው መቼ መቼ ነው? አንተ የምትመርጠው ጠዋት በማለዳ ተነስተህ ማንበብ ነው? ወይስ ይበልጥ ነቃ የምትለው ረፋዱ ላይ ነው? በየዕለቱ ቢያንስ 15 ወይም 20 ደቂቃ ለንባብ መመደብ ብትችል ከጊዜ በኋላ ምን ያህል እንዳነበብህ መለስ ብለህ ስታስበው በጣም ትገረማለህ። ቁልፍ የሆነው ነገር አዘውታሪ መሆንህ ነው።

      ይሖዋ ታላቅ ዓላማው በጽሑፍ እንዲሰፍር የመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሰዎች ቃሉን አንብበው መመሪያ እንዲያገኙ ነው። ይህም የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ለመመርመር፣ ስለ ሥራዎቹም ለልጆቻቸው ለመንገርና አምላክ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁልጊዜ ለማስታወስ ያስችላቸዋል። (መዝ. 78:​5-7) እንዲህ ላለው የይሖዋ ልግስና ያለንን አድናቆት ለማሳየት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ሕይወት ሰጪ የሆነውን ቃሉን ለማንበብ መትጋት ነው።

  • ጥናት በረከት ያስገኛል
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት በረከት ያስገኛል

      ሰዎች ፍራፍሬ ሲመርጡ አስተውለህ ታውቃለህ? አብዛኞቹ ሰዎች መብሰል አለመብሰሉን ለመለየት ቀለሙንና መጠኑን ይመለከታሉ። አንዳንዶች ያሸቱታል። ሌሎች በእጃቸው ያገላብጡታል፣ አልፎ ተርፎም በጣታቸው ጫን ጫን ያደርጉታል። ሌሎች ደግሞ የትኛው የበለጠ ውኃ እንዳለው ለማወቅ በሁለት እጃቸው አንድ አንድ ይዘው ያወዳድራሉ። አእምሮአቸው ምን እያሰበ ይሆን? እያንዳንዱን ነገር እያጤኑ፣ ልዩነቱን እያነጻጸሩ፣ ከዚህ በፊት ያደረጉትን ምርጫ እያስታወሱና አሁን የሚያዩትን ቀደም ሲል ከሚያውቁት ነገር ጋር እያወዳደሩ ነው። እንዲህ በማድረጋቸው የመረጡትን ጣፋጭ ፍሬ በመብላት ይደሰታሉ።

      እርግጥ የአምላክን ቃል ማጥናት የሚያስገኘው በረከት ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። እንዲህ ያለውን ጥናት በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሰጠነው እምነታችን ይጠነክራል፣ ፍቅራችን ያድጋል፣ አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል እንዲሁም የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማስተዋልና መለኮታዊ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ይሆናሉ። ምሳሌ 3:​15 የአምላክን ቃል ማጥናት ስለሚያስገኘው በረከት ሲገልጽ “የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም” ይላል። አንተ ይህን በረከት እያገኘህ ነውን? የአጠናን ዘዴህ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ ሊኖረው ይችላል።​—⁠ቆላ. 1:​9, 10

      [በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ለማሰላሰል ጊዜ መድብ

      ለመሆኑ ጥናት ምንድን ነው? እንዲሁ ላይ ላዩን ማንበብ ሳይሆን የማሰብ ችሎታን ተጠቅሞ አንድን ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀትና በጥሞና መመርመር ማለት ነው። የምታነበውን ነገር ማጤንን፣ ከአሁን ቀደም ከምታውቀው ጉዳይ ጋር ማገናዘብንና የቀረቡትን ማስረጃዎች ማስተዋልን ይጨምራል። በጥናትህ ወቅት አዲስ ሆኖ ያገኘኸውን ነጥብ ለማጤን ሞክር። እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ልትሠራበት የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ። የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ይህን ትምህርት ሌሎችን ለመርዳት መጠቀም ስለምትችልበት አጋጣሚ ማሰብህ አይቀርም። ጥናት ማሰላሰልን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።

      አእምሮን ማዘጋጀት

      [በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ከግል ጥናትህ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ልብህን አዘጋጅ

      ለማጥናት በምትሰናዳበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስህን፣ የምታጠናውን ጽሑፍ፣ እርሳስ ወይም ብዕር፣ ማስታወሻ ደብተርና የመሳሰሉትን ነገሮች እንደምታዘጋጅ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ልብህንስ ታዘጋጃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ” እንደነበር ይነግረናል። (ዕዝራ 7:10) በዚህ መንገድ ልብን ማዘጋጀት ምንን ይጨምራል?

      ጸሎት የአምላክን ቃል በትክክለኛ ዝንባሌ እንድናጠና ይረዳናል። ልባችን ይሖዋ የሚሰጠንን ትምህርት የሚቀበል እንዲሆን እንፈልጋለን። ምን ጊዜም ጥናቱን ከመጀመርህ በፊት ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳህ ለምነው። (ሉቃስ 11:​13) የምታጠናው ነገር ትርጉም ምን እንደሆነ፣ ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ፣ መልካምና ክፉ የሆነውን በመለየት ረገድ እንዴት እንደሚረዳህ፣ መሠረታዊ ሥርዓቱን እንዴት በሕይወትህ ውስጥ ልትሠራበት እንደሚገባና ትምህርቱ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና የሚነካው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ትችል ዘንድ እንዲረዳህ ጸልይ። (ምሳሌ 9:​10) በጥናትህ ወቅትም ቢሆን አምላክ ‘ጥበብ እንዲሰጥህ ከመለመን ወደኋላ አትበል።’ (ያዕ. 1:​5) የተሳሳቱ ሐሳቦችን ወይም መጥፎ ምኞቶችን ለማስወገድ ይሖዋ እንዲረዳህ ከፈለግህ ባገኘኸው ትምህርት መሠረት ራስህን በሐቀኝነት መርምር። ይሖዋን ለሚሰጥህ ትምህርት ‘ዘወትር አመስግነው።’ (መዝ. 147:7) በዚህ መልኩ በጸሎት የተደገፈ ጥናት ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚያስተላልፈውን መልእክት አዳምጠን ተግባራዊ ምላሽ እንድንሰጥ ስለሚረዳን ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና እንዲጠናከር ያደርጋል።​—⁠መዝ. 145:​18

      የይሖዋን ሕዝቦች ከሌሎች የሚለያቸው የተማሩትን ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው። ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚጎድላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የመጠራጠርና የመቃወም ዝንባሌ አላቸው። እኛ ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የለንም። በይሖዋ እንታመናለን። (ምሳሌ 3:​5-7) አንድ ነገር ካልገባን በድፍረት ስህተት መሆን አለበት ወደሚል መደምደሚያ አናመራም። መልሱን ለማግኘት ምርምር ማድረጋችንንና መቆፈራችንን በመቀጠል ይሖዋን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። (ሚክ. 7:​7) እኛም ግባችን እንደ ዕዝራ የተማርነውን በሥራ ላይ ማዋልና ለሌሎች ማስተማር ነው። እንዲህ ያለ የልብ ዝንባሌ ካለን ከጥናታችን ብዙ በረከት እናጭዳለን።

      የአጠናን ዘዴ

      በቀጥታ ከአንቀጽ 1 ከመጀመርና እስከ መጨረሻው ድረስ ከመውጣት ይልቅ በመጀመሪያ የርዕሰ ጉዳዩን ወይም የምዕራፉን አጠቃላይ ይዘት ለመቃኘት ሞክር። በቅድሚያ ርዕሱ ምን እንደሚል አጢን። የምታጠናው ትምህርት ጭብጥ ይህ ነው። ከዚያም ንዑስ ርዕሶቹ ከጭብጡ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ሞክር። በመቀጠል ደግሞ ከትምህርቱ ጋር ተያይዘው የቀረቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ሰንጠረዦች ወይም የክለሳ ጥያቄዎች ካሉ እነሱን ተመልከት። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘በዚህ አጠቃላይ ግምገማ መሠረት ከዚህ ርዕስ የማገኘው ትምህርት ምን ሊሆን ይችላል? የሚጠቅመኝስ እንዴት ነው?’ ይህም ጥናትህ በምን ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ከወዲሁ ፍንጭ ይሰጥሃል።

      [በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      በቋንቋህ የሚገኙትን ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀምባቸው

      ከዚያ ነጥቦቹን አንድ በአንድ መርምር። የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች እንዲሁም አንዳንድ መጻሕፍት ለየአንቀጾቹ የተዘጋጀ ጥያቄ አላቸው። እያንዳንዱን አንቀጽ በምታነብበት ጊዜ የጥያቄውን መልስ ማስመር ጠቃሚ ነው። ጥያቄዎች ባይኖሩ እንኳ ልታስታውሳቸው በምትፈልጋቸው ዋና ዋና ነጥቦች ላይ አስምር። ከዚህ ቀደም የማታውቀው አዲስ ሐሳብ ካጋጠመህ በደንብ ለመረዳት ሞክር። ለአገልግሎት የሚጠቅሙህን ወይም በሚቀጥለው ጊዜ በምታቀርበው ክፍል ውስጥ ልታካትታቸው የምትችላቸውን ምሳሌዎች ወይም አሳማኝ ነጥቦች ልብ በል። እያጠናኸው ያለውን ትምህርት ብትነግራቸው እምነታቸው ይጠናከራል የምትላቸውን ሰዎች አስብ። ልትጠቀምባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች አስምርባቸውና ጥናትህን ስትጨርስ ከልሳቸው።

      ትምህርቱን በምታጠናበት ጊዜ ጥቅሶቹን አውጥተህ አንብብ። እያንዳንዱ ጥቅስ ከአንቀጹ ፍሬ ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አጢን።

      ያልገቡህ ወይም ይበልጥ ልትመረምራቸው የምትፈልጋቸው ነጥቦች ታገኝ ይሆናል። በእነዚህ ነጥቦች ከመዘናጋት ይልቅ ሌላ ጊዜ ቀስ ብለህ ልታያቸው እንድትችል በማስታወሻ ጽፈሃቸው እለፍ። አብዛኛውን ጊዜ ትምህርቱን እየመረመርክ ስትሄድ ነጥቦቹም ግልጽ እየሆኑልህ ይመጣሉ። ካልሆነ ተጨማሪ ምርምር ልታደርግ ትችላለህ። እንዲህ ዓይነት ምርምር የሚጠይቁት ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ምናልባት በግልጽ ያልተረዳኸው ጥቅስ ይኖር ይሆናል። ወይም ደግሞ ጥቅሱ እየተብራራ ካለው ነጥብ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ መረዳት ተቸግረህ ይሆናል። ወይም በትምህርቱ ውስጥ ያለ አንድ ሐሳብ ለራስህ ቢገባህም ለሌሎች ግልጽ አድርገህ ለማስረዳት ሊከብድህ ይችላል። እነዚህን ነጥቦች እንዲሁ ከማለፍ ይልቅ የጀመርከውን ጥናት ስትጨርስ በእነርሱ ላይ ምርምር ማድረጉ ጥበብ ሊሆን ይችላል።

      [በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ጥቅሶችን አውጥተህ ማንበብን አትርሳ

      ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ዝርዝር የያዘውን መልእክቱን ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ በመልእክቱ መሃል “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው” ሲል ጠቅሷል። (ዕብ. 8:​1) አንተስ አለፍ አለፍ እያልክ ዋናውን ነጥብ ትከልሳለህ? ጳውሎስ እንዲህ ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተመልከት። በዚሁ መልእክቱ ፊተኛ ምዕራፎች ውስጥ ታላቁ የአምላክ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደገባ ገልጾ ነበር። (ዕብ. 4:​14–5:​10፤ 6:​20) ይሁንና ጳውሎስ በምዕራፍ ዕብ. 8:​1 መጀመሪያ ላይ ይህንኑ ዋና ነጥብ ነጥሎ በመጥቀስና በማጉላት አንባቢዎቹ ትምህርቱ እነርሱን እንዴት እንደሚመለከታቸው በጥሞና እንዲያስቡበት አድርጓል። ክርስቶስ ስለ እነርሱ ይታይ ዘንድ በአምላክ ፊት እንደቀረበና እነርሱም ወደ ሰማያዊቷ “ቅድስት” ይገቡ ዘንድ መንገድ እንደከፈተላቸው ገልጿል። (ዕብ. 9:​24፤ 10:​19-22) ተስፋቸው እርግጠኛ መሆኑ በቀረው የመልእክቱ ክፍል ውስጥ ስለ እምነት፣ ጽናትና ክርስቲያናዊ አኗኗር የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ነበር። እኛም በተመሳሳይ በምናጠናበት ጊዜ በዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ላይ የምናተኩር ከሆነ ጭብጡ እንዴት እንደዳበረ ከማስተዋላችንም ሌላ ከዚያ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ የሚያበቁ አሳማኝ ምክንያቶችን በአእምሮአችን መቅረጽ እንችላለን።

      የግል ጥናትህ ለተግባር ያነሳሳህ ይሆን? ይህ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። አንድ ነገር ስትማር እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ትምህርት አመለካከቴንና በሕይወቴ ውስጥ የማወጣውን ግብ እንዴት ሊነካው ይገባል? የሚገጥሙኝን ችግሮች ለመፍታት፣ ውሳኔ ለማድረግ ወይም አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው? በቤተሰቤ ውስጥ፣ በመስክ አገልግሎትና በጉባኤ እንዴት ልሠራበት እችላለሁ?’ እውቀትህን ሥራ ላይ ማዋል የምትችልባቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ወደ አእምሮህ በማምጣት እነዚህን ጥያቄዎች በጸሎት አስብባቸው።

      አንድን ምዕራፍ ወይም ርዕሰ ትምህርት ከጨረስህ በኋላ በአጭሩ ከልሰው። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦችና እነርሱን የሚደግፉትን አሳማኝ ነጥቦች ማስታወስ ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ራስህን ፈትሽ። ይህን ማድረግህ ሐሳቡን ወደፊት ልትጠቀምበት በምትችለው መልኩ በአእምሮህ ለመቅረጽ ይረዳሃል።

      የምናጠናቸው ጽሑፎች

      የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ብዙ የምናጠናቸው ጽሑፎች አሉን። ይሁን እንጂ ከየትኛው እንጀምር? ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት ጥቅሱንና የተሰጠውን ሐሳብ በየዕለቱ ማጥናታችን የተገባ ይሆናል። በየሳምንቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለምንገኝ ለእነዚህ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት አስቀድመን የምናደርገው ጥናት የሚኖረው ጠቀሜታ የላቀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች እነርሱ እውነትን ከመስማታቸው በፊት የወጡትን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ለማጥናት ጊዜ መድበዋል። ሌሎች ደግሞ በመረጡት የሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው ክፍል ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት ያካሂዳሉ።

      በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች በሙሉ በጥልቀት ለማጥናት ሁኔታህ ባይፈቅድልህስ? እንዲሁ ተዘጋጅቻለሁ ለማለት ያህል ብቻ በጥድፊያ ትምህርቱን ለመሸፈን አትሞክር። ሁሉንም ተዘጋጅቼ ልጨርሰው አልችልም በሚል አንዱንም ሳይጀምሩ መቅረት ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው። ከዚህ ይልቅ ምን ያህሉን ልታጠና እንደምትችል ወስንና ያንኑ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ። በየሳምንቱ እንደዚያ አድርግ። ቀስ በቀስ ሌሎች ስብሰባዎችንም በዝግጅትህ ለማካተት ጥረት አድርግ።

      “ቤትህን ሥራ”

      ይሖዋ የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ያውቃል። ምሳሌ 24:​27 “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት” ይላል። ይሁንና የቤተሰብህ አባላት መንፈሳዊ ፍላጎትም ቢሆን ችላ ሊባል አይገባም። በመሆኑም ጥቅሱ “ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” በማለት ይቀጥላል። የቤተሰብ ራሶች ይህንን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 24:​3 እንዲህ ይላል:- “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል።”

      ማስተዋል ቤተሰብህን የሚጠቅመው እንዴት ነው? ማስተዋል በግልጽ ከሚታየው ነገር ባሻገር ያለውን ለመመልከት የሚረዳ የአእምሮ ችሎታ ነው። ውጤታማ የቤተሰብ ጥናት የሚጀምረው የቤተሰብህን ሁኔታ በማጥናት ነው ሊባል ይችላል። የቤተሰብህ አባላት መንፈሳዊ እድገት ምን ይመስላል? ከእነርሱ ጋር ውይይት ስታደርግ ልብ ብለህ አዳምጣቸው። የማጉረምረም ወይም የቅሬታ መንፈስ ይታይባቸዋል? ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ? ከልጆችህ ጋር በአገልግሎት ስትካፈል ምን አስተውለሃል? በእኩዮቻቸው ፊት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው በመታወቃቸው አይሸማቀቁም? በቤተሰብ መልክ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ለማጥናት ባወጣችሁት ፕሮግራም ደስ ብሏቸው ይካፈላሉ? በእርግጥ በይሖዋ መንገድ እየተመላለሱ ነውን? እነዚህን ነገሮች ልብ ብለህ መከታተልህ የቤተሰብ ራስ እንደመሆንህ መጠን በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውስጥ መንፈሳዊ ባሕርያትን ለመገንባት ምን እንደሚያስፈልግ ለመገንዘብ ይረዳሃል።

      ከመጠበቂያ ግንብ ወይም ከንቁ! መጽሔት ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ርዕስ ምረጥ። ከዚያም የቤተሰቡ አባላት አስቀድመው ሊዘጋጁበት ይችሉ ዘንድ የሚጠናው ርዕስ ምን እንደሆነ ንገራቸው። በጥናቱ ወቅት ፍቅራዊ መንፈስ እንዲሰፍን አድርግ። የትኛውንም የቤተሰብ አባል መገሰጽ ወይም ማሸማቀቅ ሳያስፈልግ ነጥቦቹ ለቤተሰባችሁ የሚሠሩት እንዴት እንደሆነ ለይተህ በመጥቀስ እያጠናችሁት ያለው ትምህርት ዋና ነጥብ ጎላ ብሎ እንዲታይ አድርግ። እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል እንዲሳተፍ አበረታታ። የይሖዋ ቃል ለኑሯችን የሚያስፈልገንን ምክር በመስጠት ረገድ እንዴት “ፍጹም” እንደሆነ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዲያስተውል እርዳ።​—⁠መዝ. 19:​7

      የሚያስገኘው በረከት

      አንዳንድ አስተዋይ ሰዎች ምንም መንፈሳዊ ግንዛቤ ሳይኖራቸውም ስለ አጽናፈ ዓለማችን፣ በዓለም ላይ ስለሚከናወኑት ነገሮችና ስለ ራሳቸውም ጥናት ሊያካሂዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የዚህ ሁሉ ትርጉም ምን እንደሆነ አይገነዘቡም። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው የሚያጠኑ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እየታገዙ በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት የተገለጡትን የአምላክን የእጅ ሥራዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ፍጻሜዎችና ለታዛዥ የሰው ዘሮች በረከት የሚሆነውን የአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ያስተውላሉ።​—⁠ማር. 13:​4-29፤ ሮሜ 1:​20፤ ራእይ 12:​12

      ይህ ትልቅ ነገር ቢሆንም ለመኩራራት ምክንያት ሊሆነን አይገባም። ይልቁንም የአምላክን ቃል በየዕለቱ መመርመራችን በትሕትና መመላለሳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (ዘዳ. 17:​18-20) እንዲሁም ‘ከኃጢአት መታለል’ ይጠብቀናል። ምክንያቱም የአምላክ ቃል በልባችን ውስጥ ሕያው ከሆነ ከኃጢአት ለመራቅ ያለን ቁርጥ አቋም የሚላላበትና በኃጢአት ማባበያዎች የምንሸነፍበት አጋጣሚ አይኖርም። (ዕብ. 2:​1፤ 3:​13፤ ቆላ. 3:​5-10) በዚህ መንገድ ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራን በነገር ሁሉ ደስ ልናሰኝ ለጌታ እንደሚገባ መመላለስ’ እንችላለን። (ቆላ. 1:​10) የአምላክን ቃል ስናጠና ዓላማችን ይኸው ነው። ይህንን ዓላማ ዳር ማድረስ መቻል ደግሞ ከሁሉ የላቀ ታላቅ በረከት ነው።

      ከሁሉ የላቁ በረከቶችን ለማግኘት

      • ልብህን አዘጋጅ

      • የሚጠናውን ጽሑፍ አጠቃላይ ይዘት ገምግም

      • ጉልህ የሆኑትን ነጥቦች ለይ

      • ጥቅሶቹ ለቀረበው ሐሳብ መሠረት ሆነው የሚያገለግሉት እንዴት እንደሆነ ልብ በል

      • ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ከልስ

      • የምታጠናው ትምህርት የግል ሕይወትህን እንዴት ሊነካው እንደሚገባ አሰላስል

      • ያገኘኸውን ትምህርት ሌሎችን ለመርዳት መጠቀም የምትችልበትን አጋጣሚ ፈልግ

      የትምህርቱን አጠቃላይ ይዘት መገምገም የሚቻለው እንዴት ነው?

      • የርዕሱን ቃላት አጢን

      • እያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ ከዋናው ርዕስ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለማስተዋል ሞክር

      • ሥዕላዊ መግለጫዎችን፣ ሰንጠረዦችን ወይም የክለሳ ሣጥኖችን ተመልከት

  • ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ምርምር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

      ንጉሥ ሰሎሞን ‘እውነተኛውን ቃል ለማስፈር’ ስለፈለገ ‘ጥልቅ ምርምርና ፍለጋ በማድረግ ብዙ ምሳሌዎችን አስማምቶ ጽፏል።’ (መክብብ 12:​9, 10) ሉቃስ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ሲል “ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ” ተከትሎ ጽፏል። (ሉቃስ 1:​3 አ.መ.ት ) ሁለቱም የአምላክ አገልጋዮች ምርምር አድርገዋል።

      ምርምር ምንድን ነው? ስለ አንድ ጉዳይ መረጃ ለማግኘት በጥንቃቄ የሚደረግ ፍለጋ ነው። ይህም ማንበብን እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑትን የአጠናን ዘዴዎች መጠቀምን ይጠይቃል። ከሰዎች መረጃ ማግኘትንም ሊያካትት ይችላል።

      ምርምር ልታደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። የግል ጥናት ስታደርግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ያጋጠሙህ መልስ ልታገኝላቸው የምትፈልጋቸው ጥያቄዎች ይኖሩ ይሆናል። አገልግሎት ላይ ያነጋገርከው ሰው ላነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ትፈልግ ይሆናል። ወይም ደግሞ ንግግር እንድትሰጥ ተመድበህም ሊሆን ይችላል።

      ንግግር እንድትሰጥ ተመድበሃል እንበል። የትምህርቱ ይዘት ሰፊ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለአድማጮችህ እንደሚስማማ አድርገህ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? ምርምር በማድረግ ትምህርቱን አዳብረው። በመጀመሪያ ግልጽ ነው ብለህ ያሰብኸውንም ነጥብ አንድ ሁለት አኃዛዊ መረጃ በማከል ወይም የአድማጮችህን ሕይወት የሚነካና ከትምህርቱ ጋር የሚስማማ ምሳሌ በመጨመር ግንዛቤያቸውን የሚያሰፋ አልፎ ተርፎም ቀስቃሽ ልታደርገው ትችላለህ። ምናልባት ትምህርቱ የተመሠረተበት ጽሑፍ በየትኛውም ቦታ ለሚገኙ አንባቢዎች ታስቦ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል። አንተ ግን ነጥቦቹን ለአንድ ጉባኤ ወይም ግለሰብ በሚስማማ መንገድ ማዳበር፣ በምሳሌ አስደግፎ ማቅረብ እንዲሁም እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚችል ማብራራት ያስፈልግሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      መረጃ ማሰባሰብ ከመጀመርህ በፊት አድማጮችህ እነማን እንደሆኑ አስብ። ስለ ጉዳዩ ያላቸው እውቀት ምንድን ነው? ምንስ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? ከዚያ በኋላ በንግግርህ ምን ማከናወን እንደምትፈልግ ወስን። ዓላማህ ማብራራት ነው? ማሳመን ነው? ሐሰት መሆኑን ማስረዳት ነው? ወይስ ለሥራ መቀስቀስ? ማብራራት ተጨማሪ መረጃ በማቅረብ ነጥቡን ግልጽ ማድረግን ይጠይቃል። መሠረታዊ የሆነው ሐሳብ የሚታወቅ ሊሆን ቢችልም መቼ ወይም እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል በመግለጽ ነጥቡን ማስፋት ያስፈልግህ ይሆናል። ማሳመን ‘ለምን ’ ለሚለው ጥያቄ በማስረጃ የተደገፈ መልስ ማቅረብን ይጠይቃል። አንድ ነገር ሐሰት መሆኑን ለማስረዳት የጉዳዩን ሁለቱንም ወገን ጠንቅቆ ማወቅና በማስረጃነት የሚቀርቡትን ነጥቦች በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል። እርግጥ አሳማኝ ማስረጃዎችንም ማቅረብ የሚኖርብን በደግነት ነው። ለሥራ ማነሳሳት ከልብ እንዲያምኑበት ማድረግን ይጠይቃል። ይህም አድማጮች የሰሙትን ነገር በሥራ የመተርጎም ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ማለት ነው። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያሉም እንኳ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ሰዎችን ተሞክሮ መጥቀስ የአድማጮችን ልብ ለማነሳሳት ሊረዳ ይችላል።

      አሁን ምርምር ለማድረግ ዝግጁ ነህ ማለት ነው? የሚቀርህ ነገር አለ። ምን ያህል መረጃ ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግህ አስብ። በዚህ ረገድ ጊዜ ወሳኝ ሊሆን ይችላል። ትምህርቱን ለማቅረብ የሚፈቀድልህ ጊዜ ምን ያህል ነው? አምስት ደቂቃ? ወይስ አርባ አምስት ደቂቃ? በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንደሚቀርቡት ክፍሎች በተወሰነ ጊዜ ማለቅ አለበት? ወይስ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና እንደ እረኝነት ጉብኝት እንደ ሁኔታው ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል?

      ከዚህ በኋላ የሚነሳው ጥያቄ ለምርምር የሚረዱ ምን መሣሪያዎች አሉህ? የሚል ነው። በመንግሥት አዳራሻችሁ ቤተ መጻሕፍት ውስጥስ ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ጽሑፎች ይገኛሉ? በይሖዋ ቤት ረዘም ላሉ ዓመታት የቆዩ ወንድሞች እንደነዚህ ያሉትን ጽሑፎቻቸውን እንድትጠቀም ሊፈቅዱልህ ይችላሉ? ሌሎች የማመሳከሪያ መጻሕፍት ቢያስፈልጉህ በአካባቢህ ቤተ መጻሕፍት ማግኘት ትችላለህ?

      መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ የምርምር መጽሐፋችን ነው

      ምርምር የምታደርገው የአንድን ጥቅስ ትርጉም ለማወቅ ከሆነ ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምር።

      በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ተመልከት። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ጥቅስ የተጻፈው ለማን ነበር? ከላይና ከታች ያሉት ቁጥሮች ይህ ሐሳብ ስለተጻፈበት ምክንያት ወይም በታሪኩ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎች ዝንባሌ ምን የሚጠቁሙት ነገር አለ?’ ይህን ማወቅህ ብዙውን ጊዜ አንድን ጥቅስ እንድትረዳው ከማገዙም ሌላ ንግግርህን ሕያው ለማድረግ ሊያገለግል ይችላል።

      ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል የሰዎችን ልብ የመንካትና ሕይወታቸውን የመለወጥ ኃይል እንዳለው ለማስረዳት ዕብራውያን 4:​12 ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ቃሉ የሰዎችን ልብ ሊነካ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ይሖዋ ለአብርሃም ቃል የገባለትን የተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው በፊት እስራኤላውያን ለ40 ዓመት በበረሃ ስላሳለፉት ጊዜ ይገልጻል። (ዕብ. 3:​7–4:​13) “የእግዚአብሔር ቃል” ማለትም አምላክ ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ወደ እረፍት ስፍራ እንደሚያስገባቸው የሰጠው ተስፋ፣ ሕያውና ፍጻሜውን እያገኘ ያለ እንጂ የተረሳ አልነበረም። እስራኤላውያን ይህንን ቃል የሚጠራጠሩበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከግብፅ አውጥቶ ወደ ሲና ተራራና ከዚያም ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመራቸው በተደጋጋሚ እምነት እንደሚጎድላቸው አሳይተዋል። በመሆኑም አምላክ ቃሉን ለማስፈጸም ሲል ላደረጋቸው ነገሮች የሰጡት ምላሽ በልባቸው ውስጥ ያለውን ዝንባሌ የሚያሳይ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ አምላክ የሰጠው የተስፋ ቃል በሰዎች ልብ ውስጥ ያለው ዝንባሌ ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ያደርጋል።

      ማጣቀሻዎቹን ተመልከት። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ማጣቀሻ አላቸው። አንተ የምትጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻ አለው? ካለው ሊረዳህ ይችላል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ የሚገኝ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በ⁠አንደኛ1 ጴጥሮስ 3:​6 ላይ ሣራ ክርስቲያን ሚስቶች ሊኮርጁዋት የሚገባ ሴት መሆኗ ተጠቅሷል። በማጣቀሻው ላይ የሚገኘው ዘፍጥረት 18:​12 ሣራ አብርሃምን “በልብዋ” ጌታ ብላ እንደጠራችው በመግለጽ ይህንን ነጥብ ያጠናክራል። በመሆኑም ለባሏ የምትገዛው ከልቧ ነበር ማለት ነው። ማጣቀሻዎቹ በዚህ መንገድ ተጨማሪ ማስተዋል እንድታገኝ ከማገዝም ሌላ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ወይም የሕጉን ቃል ኪዳን አሠራር እንድታስተውል የሚረዱ ጥቅሶችን ይጠቁሙሃል። ይሁን እንጂ የአንዳንድ ማጣቀሻዎች ዓላማ እንዲህ ያለውን ማብራሪያ መስጠት እንዳልሆነ መዘንጋት የለብህም። ሌላ ተመሳሳይ ሐሳብ ወይም የሕይወት ታሪክ ወይም ቦታ የተጠቀሰበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ።

      የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንስ ተጠቀም። የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸውን ቃላት በፊደል ቅደም ተከተል ይዘረዝራል። ምርምር እያደረግህበት ካለኸው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን ጥቅሶች ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል። ጥቅሶቹን አውጥተህ ስትመለከት ሌሎች ጠቃሚ ነጥቦችን ታገኛለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የእውነት ቃል እንዴት እርስ በእርሱ እንደሚደጋገፍ ለማስተዋል ይረዳሃል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጨረሻዎቹ ገጾች ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸው መሠረታዊ የሆኑ ቃላት ማውጫ አለው። ኮምፕሬሄንሲቭ ኮንኮርዳንስ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ ግን ከዚያ እጅግ የሚበልጥ ይዘት አለው። ይህ መጽሐፍ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እያንዳንዱ ዋና ቃል የሚገኝባቸውን ጥቅሶች በሙሉ ይጠቁምሃል።

      ለምርምር የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎችን መጠቀም

      በገጽ 33 ላይ የሚገኘው ሣጥን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ያዘጋጃቸውን ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ይዘረዝራል። (ማቴ. 24:​45-47) ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የአርዕስት ማውጫ አላቸው። በአንዳንዶቹ መጻሕፍት የመጨረሻ ገጾች ላይ ደግሞ የቃላት ማውጫ ይገኛል። ይህም የፈለግኸውን ነጥብ ነጥለህ ማውጣት እንድትችል ተብሎ የተዘጋጀ ነው። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በእያንዳንዱ ዓመት መጨረሻ ላይ በዓመቱ ውስጥ የወጡትን ርዕሶች ያካተተ ማውጫ ይኖራቸዋል።

      የትኛው ርዕሰ ጉዳይ በየትኛው ጽሑፍ ላይ እንደሚገኝ ማወቅህ የምታደርገውን ምርምር ያቀላጥፍልሃል። ለምሳሌ ያህል ስለ ትንቢት፣ ስለ መሠረተ ትምህርት፣ ስለ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስለሚሆኑበት መንገድ ማወቅ ፈልገሃል እንበል። እንዲህ የመሳሰሉትን ነጥቦች መጠበቂያ ግንብ ላይ እንደምታገኝ የታወቀ ነው። ንቁ! መጽሔት ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ በጊዜው ያሉ ችግሮችን፣ ሃይማኖትን፣ ሳይንስን እና በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሰዎችን ሁኔታ የሚዳስሱ ርዕሶች ይዞ ይወጣል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ በወንጌል ዘገባ ውስጥ ስላለው ስለ እያንዳንዱ ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ማብራሪያ ይገኛል። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር በቁጥር የሚያብራሩ ጽሑፎችም አሉ። ከእነዚህ መካከል ራእይ​—⁠ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!፣ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባሉት መጻሕፍትና በሁለት ጥራዝ የተዘጋጀው የኢሳይያስ ትንቢት​—⁠ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን የተባለው መጽሐፍ ይገኙበታል። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ አብዛኛውን ጊዜ በመስክ አገልግሎት ለሚነሡ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ታገኛለህ። ስለ ሌሎች ሃይማኖቶች፣ ስለሚያስተምሯቸው ትምህርቶችና ስለ ታሪካዊ አመሠራረታቸው ይበልጥ ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በዚህ ዘመን ስላሉት የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ ይገኛል። በምድር ዙሪያ እየተከናወነ ያለው የምሥራቹ ስብከት ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚገልጽ መረጃ ለማግኘት በቅርብ የወጣውን የጥር 1 መጠበቂያ ግንብ መመልከት ትችላለህ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሰዎች፣ ቦታዎች፣ ነገሮች፣ ቋንቋዎች ወይም ታሪካዊ ክንውኖች ዝርዝር መረጃ የያዘ ግሩም መጽሐፍ ነው።

      “የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ።” ከ20 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ የሚገኘው ይህ ማውጫ በተለያዩ ጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ይጠቁምሃል። የርዕሰ ጉዳይ ማውጫና የጥቅስ ማውጫ ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል። የርዕሰ ጉዳይ ማውጫውን ለመጠቀም ልትመረምረው የምትፈልገውን ርዕሰ ጉዳይ የሚወክል ቃል ምረጥ። የጥቅስ ማውጫውን ለመጠቀም ደግሞ ከተዘረዘሩት ጥቅሶች መካከል ማብራሪያ ማግኘት የምትፈልግበትን ጥቅስ ምረጥ። በማውጫው ውስጥ ከተካተቱት ጽሑፎች መካከል በቋንቋህ የወጡትና ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ ወይም ጥቅስ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ጽሑፎች ካሉ በማውጫው ዝርዝር ውስጥ ታገኛቸዋለህ። በማውጫው ላይ ያሉት አኅጽሮታዊ ስያሜዎች የትኞቹን ጽሑፎች እንደሚያመለክቱ ለማወቅ በመጀመሪያዎቹ ገጾች ላይ ያለውን መግለጫ ተመልከት። (በዚህ መሠረት ለምሳሌ w99 3/1 15 ቢል የ1999 መጠበቂያ ግንብ የመጋቢት 1 እትም ገጽ 15 ማለት ይሆናል።) “የመስክ አገልግሎት ተሞክሮዎች” (“Field Ministry Experiences”) እና “የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች” (“Life Stories of Jehovah’s Witnesses”) የሚሉት ርዕሶች ለጉባኤው ቀስቃሽ ክፍል ለማቅረብ ሊረዱህ ይችላሉ።

      ምርምር ስታደርግ ትኩረትህ በሌሎች ነጥቦች እንዳይወሰድ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። አሁን የተነሳኸው ምርምር እያደረግህበት ላለኸው ጉዳይ የሚረዳ ነጥብ ለማግኘት መሆኑን አትዘንጋ። ማውጫው ወደ አንድ ጽሑፍ ከመራህ የተጠቀሰውን ገጽ ገልጠህ እዚያ ላይ ያሉትን ንዑስ ርዕሶችና የአንቀጾቹን የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር በመመልከት ከምትፈልገው ነጥብ ጋር የሚዛመደውን ሐሳብ ብቻ ለማግኘት ጥረት አድርግ። የምትፈልገው ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተሰጠውን ማብራሪያ ከሆነ በማውጫው ላይ በተጠቀሰው ገጽ ላይ ጥቅሱ የሚገኝበትን ቦታ ለማግኘት ሞክር። ከዚያ በኋላ በጥቅሱ ዙሪያ የሚገኘውን ማብራሪያ ተመልከት።

      በሲዲ የተዘጋጁ “የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች።” ኮምፒውተር ማግኘት የምትችል ከሆነ በሲዲ የተዘጋጁትን የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች የመጠቀም አጋጣሚ ሊኖርህ ይችላል። በዚህ ሲዲ አማካኝነት ብዙ ጽሑፎችን ማግኘት ይቻላል። ይህ ፕሮግራም የምትፈልገው ቃል ወይም ጥቅስ የሚገኝበትን ጽሑፍ ፈልጎ ሊያገኝልህ ይችላል። ምርምር ለማድረግ የሚያግዘው ይህ ዝግጅት በቋንቋህ የማይገኝ እንኳ ቢሆን በሰፊው ከሚሠራባቸው ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መካከል አንተ በምታውቀው በአንዱ ልታገኘው ትችላለህ።

      ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች

      ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ላይ ወጣቱ ጢሞቴዎስ “ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን” ወደ ሮም ይዞለት እንዲመጣ ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:13 አ.መ.ት ) ጳውሎስ እንደ ውድ ነገር የሚመለከታቸውና በጥንቃቄ ያስቀመጣቸው ጽሑፎች ነበሩት። አንተም እንደዚያ ማድረግ ትችላለህ። የመጠበቂያ ግንብ፣ የንቁ! እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎታችን የግል ቅጂዎችህን በጉባኤ ከተጠኑ በኋላ ታስቀምጣቸዋለህ? ከሆነ እነዚህና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችህ ምርምር ለማድረግ ይረዱሃል። ብዙ ጉባኤዎች በመንግሥት አዳራሻቸው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አሏቸው። እነዚህ ጽሑፎች ሁሉም የጉባኤው አባላት መንግሥት አዳራሽ በሚመጡበት ጊዜ እንዲጠቀሙባቸው ሲባል የተዘጋጁ ናቸው።

      የግል ፋይል ይኑርህ

      ንግግር በምትሰጥበት ወይም በምታስተምርበት ጊዜ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ጥሩ ጥሩ ነጥቦች አሰባስብ። በጋዜጣ ወይም በመጽሔት ላይ የወጣ ዜና፣ አኃዛዊ መረጃ ወይም ምሳሌ ስታነብብ ለአገልግሎት የሚጠቅም ሆኖ ካገኘኸው ቀድደህ ወይም ሐሳቡን በሌላ ወረቀት ገልብጠህ አስቀምጠው። ቀኑን፣ ጽሑፉን እና ምናልባትም የጸሐፊውን ወይም የአሳታሚውን ስም ጻፍ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተህ ስታዳምጥ እውነትን ለሌሎች ለማስረዳት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ማሳመኛ ነጥቦችና ምሳሌዎች በማስታወሻ አስፍር። አንድ ጥሩ ምሳሌ ከሰማህ በወቅቱ የምትጠቀምበት አጋጣሚ ባይኖርም ጽፈህ አስቀምጠው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለረጅም ጊዜ በተካፈልህ መጠን የዚያኑ ያህል ብዙ ክፍሎችን ተዘጋጅተህ ማቅረብህ አይቀርም። እነዚህን ክፍሎች የተዘጋጀህባቸውን ማስታወሻዎች አትጣላቸው። በዝግጅትህ ወቅት ያደረግኸው ምርምር ከጊዜ በኋላ ሊጠቅምህ ይችላል።

      ሰዎችን ጠይቅ

      ከሰዎች ብዙ መረጃ ማግኘት ትችላለህ። ሉቃስ የወንጌል ዘገባውን ሲያጠናቅር የዓይን ምሥክሮችን በመጠየቅ ብዙ መረጃዎችን እንዳሰባሰበ ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 1:⁠1-4) ምናልባት ምርምር ለማድረግ እየጣርክ ስላለህበት ርዕሰ ጉዳይ አንድ ክርስቲያን ጠቃሚ መረጃ ሊሰጥህ ይችል ይሆናል። ክርስቶስ ‘ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት’ እንድናድግ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ እንደሚጠቀም በ⁠ኤፌሶን 4:​8, 11-16 ላይ ተገልጿል። አምላክን በማገልገል ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦችን ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል። ከሌሎች ጋር ስለ ጉዳዩ አንስቶ መነጋገርም እነርሱ ያላቸውን አመለካከት እንድታስተውል ስለሚረዳህ ተግባራዊ የሆነ ትምህርት ለመዘጋጀት ያስችልሃል።

      የምርምርህን ውጤት ገምግም

      ስንዴ ከተወቃ በኋላ ምርቱን ከገለባ መለየት እንደሚያስፈልግ ሁሉ የምርምርህንም ውጤት እንዲሁ መለየት ያስፈልጋል። በምርምርህ ካሰባሰብኻቸው ሐሳቦች መካከል ለጊዜው የማያስፈልግህን መለየት ይኖርብሃል።

      ያገኘኸውን ሐሳብ በንግግርህ ላይ የምትጠቀምበት ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘በእርግጥ ልጠቀምበት ያሰብኩት ነጥብ ለማቀርበው ርዕሰ ጉዳይ የሚጨምረው ጠቃሚ ነገር ይኖራል? ወይስ የአድማጮችን ትኩረት የሚስብ ሊሆን ቢችልም ላብራራው ከሚገባኝ ርዕሰ ጉዳይ ያርቀኛል?’ በቅርቡ ስለተከሰቱ ሁኔታዎች ለመጥቀስ የምታስብ ወይም በየጊዜው ማሻሻያና ለውጥ የሚያደርገውን የሳይንስ ወይም የሕክምና መስክ በተመለከተ የምትናገር ከሆነ የምታቀርበው መረጃ ወቅታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። በቆዩ ጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ አንዳንድ ነጥቦችም ማስተካከያ ተደርጎባቸው ሊሆን እንደሚችል አትዘንጋ። ስለዚህ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በቅርብ የወጣውን ማብራሪያ ማግኘት ይኖርብሃል።

      ከዓለማዊ ምንጮች መረጃዎችን ለማጠናቀር ካሰብህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ አትዘንጋ። (ዮሐ. 17:​17) በአምላክ ዓላማ ፍጻሜ ረገድ ኢየሱስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በመሆኑም ቆላስይስ 2:​3 “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነው” ይላል። የምርምርህን ውጤት ከዚህ አንጻር ገምግመው። ዓለማዊ ምንጮችን ተጠቅመህ የምታደርገውን ምርምር በተመለከተ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የተጋነነ፣ በግምት ላይ የተመሠረተ ወይም መንፈሳዊ ማስተዋል ያልተንጸባረቀበት ሐሳብ ነውን? ከራስ ወዳድነት በመነጨ ስሜት ወይም ከንግድ ጋር የተያያዘ ዓላማን ለማራመድ የተጻፈ ነውን? ተዓማኒነት ያላቸው ሌሎች ምንጮች ከዚህ አባባል ጋር ይስማማሉ? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ይስማማልን?’

      ምሳሌ 2:​1-5 እውቀትንና ማስተዋልን ‘እንደ ብርና እንደተቀበረ ገንዘብ’ እንድንፈልግ ያበረታታናል። ይህ ተጋድሎ የሚጠይቅ ቢሆንም በረከት አለው። ምርምር ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ይሁንና አምላክ ስለ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለመረዳት፣ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ለማረም እንዲሁም በእውነት ጎዳና ለመጽናት ያስችልሃል። ከዚህም በተጨማሪ የምታቀርበው ክፍል ቁምነገር ያዘለና ሕያው እንዲሆን ስለሚያደርግ አንተም ንግግሩን ለማቅረብ ልባዊ ጉጉት ይኖርሃል፤ አድማጮችም ደስ ብሏቸው ያዳምጡሃል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ