እምነት የተሰጠውን ሥራ እንዲፈጽም አስችሎታል
ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ጭቆና ነፃ አውጥቶ ሕዝቡን እንዲመራ ለሙሴ ተልእኮ ሲሰጠው መጀመሪያ ላይ ሙሴ “ጌታ ሆይ እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም” በማለት ሌላ ሰው እንዲፈልግ ጠይቆ ነበር። (ዘጸአት 4:10) አዎን፣ ሙሴ ለዚህ ከባድ ሥራ ብቁ እንደሆነ አልተሰማውም ነበር።
ዛሬም ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ብቁ እንዳልሆኑ አልፎ አልፎ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ቲዎዶር የተባለ አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እንድሠራው ከሚጠይቀኝ ነገር ሁሉ እንደ መስክ አገልግሎት የሚከብደኝ የለም። ልጅ ሳለሁ በፍጥነት ወደ በሩ ሄጄ የበሩን ደውል የደወልኩ አስመስልና ማንም እንዳልሰማኝ ወይም እንዳላየኝ ተስፋ በማድረግ ወዲያው ከዚያ እሄዳለሁ። ትልቅ ከሆንኩ በኋላ እንዲህ ማድረግ ባቆምም ከቤት ወደ ቤት የመሄዱ ሐሳብ በሽታ ይለቅብኝ ነበር። ሌላው ቀርቶ እስካሁን ድረስ አገልግሎት ልወጣ ስል ያቅለሸልሸኛል ሆኖም እንደምንም ብዬ እወጣለሁ።”
ሙሴና እንደ ቲዎዶር ያሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለውን ፍርሃት ለመቋቋም ያስቻላቸው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “[ሙሴ] . . . የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” በማለት መልስ ይሰጠናል።—ዕብራውያን 11:27
ሙሴ በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደሩ ብቃት የለኝም የሚለውን አፍራሽ ስሜት አሸንፎ ዳኛ፣ ነቢይ፣ መሪ፣ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ፣ አዛዥ፣ ታሪክ ጸሐፊና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲሆን የተሰጠውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማከናወን ችሏል።
እኛም እንደ ሙሴ እምነት ካለን ‘የማይታየውን እንደሚታይ’ አድርገን እንመላለሳለን። እንዲህ ያለው እምነት ደፋር እንድንሆን ከማስቻሉም በላይ ብቃት እንደሌለን በሚሰማን ጊዜ እንኳ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን እንድንሸከም ያስችለናል።