-
አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 15
-
-
አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
በአከርካሪው ላይ በተደረገለት የቀዶ ሕክምና ምክንያት የሥራ መስኩን ለመቀየር የተገደደው ሃርሊ በማሽን ላይ መሥራቱን አቁሞ የቢሮ ጸሐፊ ሆነ። ሥራውን በመለወጡ ምክንያት ምን እንደተሰማው በተጠየቀ ጊዜ ሃርሊ “በማሽን ላይ ለመሥራት ባለመቻሌ ቅር ብሎኛል። እውነቱን ለመናገር ግን ከበፊቱ ይልቅ በአሁኑ ሥራዬ ይበልጥ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
ሃርሊ ደስተኛ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ለደስታዬ ምክንያት የሆነው አብሬያቸው የምሠራቸው ሰዎች ያላቸው አመለካከት ነው። ቀደም ሲል እሠራበት ከነበረው መሥሪያ ቤት በተቃራኒ የአሁኑ አለቃዬም ሆነ የሥራ ባልደረቦቼ የምሠራውን ሥራ ያደንቃሉ፤ ከማመስገንም ወደ ኋላ አይሉም። ትልቅ ለውጥ ያመጣው ነገር ይህ ነበር።” በአሁኑ ጊዜ ሃርሊ ጠቃሚና የሚፈለግ ሰው እንደሆነ ስለሚሰማው ደስተኛ ሠራተኛ ሆኗል።
ለሚገባው ሰው የሚነገሩ የአድናቆትና የምስጋና ቃላት ልብን በጣም እንደሚያስደስቱ የተረጋገጠ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሼክስፒር እንዳለው ውለታቢስነት ቅስምን የሚሰብር ሊሆን ይችላል:- “ንፈስ ንፈስ አንተ የክረምት ነፋስ፣ ምን ብትከፋ እንደ ሰው ውለታቢስነት አትከብድም።” ብዙዎች የዚህ ደግነት የጎደለው ድርጊት ሰለባ መሆናቸው የሚያሳዝን ነው።
ውለታቢስ ከመሆን ተጠበቁ
በጊዜያችን ባለው ዓለም ውስጥ ከልብ የመነጩ የምስጋና ቃላትን መናገር እየተረሳ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ደራሲ የሚከተለውን ጥያቄ አቅርቦ ነበር:- “አንዲት ሙሽራ 200 የሠርግ መጥሪያዎችን ለመላክ ጊዜ የምታገኝ ከሆነ እድምተኞቿ ላመጡላት 163 ስጦታዎች የምስጋና ደብዳቤዎችን ለመጻፍ የሚያስችል ጊዜ የምታጣው ለምንድን ነው?” ብዙውን ጊዜ ሰዎች “አመሰግናለሁ” የሚለውን ምንም ወጪ የማይጠይቅ ቃል እንኳን አይናገሩም። አመስጋኝነት ለእኔ ብቻ በሚለው አመለካከት በከፍተኛ መጠን እየተተካ ነው። ይህ ሁኔታ የመጨረሻውን ዘመን ለይተው ከሚያሳውቁ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “የመጨረሻዎቹ ቀናት በአደገኛ ሁኔታዎች የተሞሉ እንደሚሆኑ ማወቅ ይኖርብሃል። ሰዎች ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ ይሆናሉ። . . . ፈጽሞ ምስጋና ቢስ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2 ፊሊፕስ
በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አመስጋኝነት በሽንገላ ቃላት ይተካል። የአመስጋኝነት መግለጫዎች አንድ ሰው ስለ ግል ጥቅሙ ሳያስብ የሚናገራቸው ከልብ የሚፈልቁ ቃላት ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከልብ ያልመነጩና የተጋነኑ የሽንገላ ቃላት ወደፊት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ ወይም የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በስውር ዓላማ የሚሰነዘሩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ይሁዳ 16) ይህን የመሰለው ለስላሳ አነጋገር ተሸንጋዩን ሰው የሚያታልል ከመሆኑም በላይ የኩራትና ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ውጤት ነው። ታዲያ ልባዊ ባልሆኑ የሽንገላ ቃላት መታለል የሚፈልግ ማን ነው? ይሁን እንጂ እውነተኛ የምስጋና ቃላት መንፈስን እንደሚያድሱ የተረጋገጠ ነው።
አመስጋኝነቱን የሚገልጽ ሰው ይህን በማድረጉ ይጠቀማል። ምስጋና በማቅረቡ የሚሰማው ሞቅ ያለ ስሜት ለደስታውና ለሰላሙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (ከምሳሌ 15:13, 15 ጋር አወዳድር።) አመስጋኝነት አዎንታዊ ባህርይ ስለሆነ እንደ ቁጣ፣ ቅናትና ብስጭት ከመሳሰሉት አፍራሽ አስተሳሰቦች ይጠብቀዋል።
“የምታመሰግኑ ሁኑ”
መጽሐፍ ቅዱስ የአመስጋኝነትን መንፈስ እንድናዳብር አጥብቆ ይመክረናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (1 ተሰሎንቄ 5:18) እንዲሁም ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎችን ሲመክር “የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ” ብሏል። (ቆላስይስ 3:15) የምስጋና መግለጫዎችን የያዙ በርካታ መዝሙራት የሚገኙ ሲሆን ይህ ደግሞ ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረብ አምላካዊ ባህርይ መሆኑን ያመለክታል። (መዝሙር 27:4፤ 75:1) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አምላክ በዕለት ተለት የሕይወት ጉዳዮች ውስጥ አመስጋኝነታችንን ስናሳይ ይደሰታል።
ሆኖም በዚህ ውለታ ቢስ ዓለም ውስጥ የአመስጋኝነት መንፈስ እንዳናዳብር ጋሬጣ የሚሆኑብን ነገሮች ምንድን ናቸው? በዕለት ተለት የሕይወት ሂደት ውስጥ አመስጋኝ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።
-
-
የአመስጋኝነትን መንፈስ አዳብሩመጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 15
-
-
የአመስጋኝነትን መንፈስ አዳብሩ
በኒው ዮርክ ግዛት የሚገኝ አንድ ሐኪም በአደገኛ ሁኔታ ላይ የምትገኘውን የማሪን ሕይወት ከሞት ያድናል። ይሁን እንጂ የ50 ዓመቷ ማሪ ሐኪሙን ማመስገን ቀርቶ የታከመችበትን ሒሳብ እንኳ አልከፈለችም። እንዴት ያለ ውለታቢስነት ነው!
አንድ ጊዜ ኢየሱስ ወደ አንድ መንደር ሲገባ አስከፊው የሥጋ ደዌ በሽታ የያዛቸው አሥር ሰዎችን እንዳገኘ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰዎቹ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ፣ አቤቱ፣ ማረን አሉ።” ኢየሱስ “ሂዱ፣ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” ሲል አዘዛቸው። ለምጻሞቹ መመሪያውን ተቀብለው በመሄድ ላይ እያሉ ጤንነታቸው ሲመለስላቸው ይመለከቱና ይሰማቸው ጀመር።
ከተፈወሱት ለምጻሞች ውስጥ ዘጠኙ በዚያው መንገዳቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን ሳምራዊ የሆነው ሌላኛው ለምጻም ኢየሱስን ፍለጋ ተመለሰ። ቀደም ሲል ለምጻም የነበረው ይህ ሰው ኢየሱስን ሲያገኘው በእግሩ ሥር ተደፍቶ አመሰገነው። ኢየሱስም መልሶ:- “አሥሩ
-