-
ከመርከበኛ የሚገኝ ትምህርትመጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 15
-
-
ከመርከበኛ የሚገኝ ትምህርት
ለብቻ ሆኖ የባሕር ላይ ጉዞ ማድረግ አድካሚ ሊሆን ይችላል። በድካም ምክንያት የሚፈጠረው የመደንዘዝ ስሜት በማሰብ ችሎታው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድርበት መርከበኛው ስህተት ሊሠራና የተሳሳቱ ውሳኔዎች ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም መርከበኛው መልሕቅ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ይገነዘባል። መልሕቁ፣ የደከመው መርከበኛ ወደ አደገኛ አቅጣጫ ከመቅዘፍ ይልቅ እንዲያርፍና ኃይሉን እንዲያድስ ያስችለዋል። በተጨማሪም መልሕቁ መርከቡ ፊቱን ወደ ነፋሱና ሞገዱ አቅጣጫ እንዲያዞርና አንድ ቦታ ረግቶ እንዲቆይ ያደርገዋል።
መርከበኞች በባሕር ላይ ብዙ አደጋዎች እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ክርስቲያኖችም ከዚህ ዓለም ከሚደርስባቸው የማያቋርጥ ተጽእኖ የተነሳ እረፍት የማድረጉን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። እንዲያውም ኢየሱስ በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ” ብሏቸው ነበር። (ማርቆስ 6:31) ዛሬም አንዳንዶች ለጥቂት ሳምንታት ጉዞ ለማድረግ ወይም በሳምንቱ መጨረሻ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመዝናናት ራቅ ወዳለ ቦታ ይሄዱ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ወቅቶች መንፈስን የሚያድሱና የሚያነቃቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? መንፈሳዊ የባሕር መልሕቅ ሆኖ በማገልገል እንዳንዋልልና በአንድ ቦታ ረግተን እንድንቆይ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
ይሖዋ በልግስና ለዚህ የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርጎልናል። ይህ ዝግጅት ከቅዱስ ቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብና ምን ጊዜም ቢሆን ከእርሱ እንዳንርቅ ይረዳናል። በውስጡ ያሉት ምክሮች ደግሞ ሊያረጋጉንና ሰይጣንና የእርሱ ዓለም የሚያመጡብንን ፈተናዎች እንድንቋቋማቸው ሊረዱን ይችላሉ። ከዘወትር ልማዳችን በተለየ ሁኔታ ላይ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ካደረግን እንደ መንፈሳዊ መልሕቅ ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል።—ኢያሱ 1:7, 8፤ ቆላስይስ 2:7
መዝሙራዊው ‘በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW ] እንደሆነ’ ተናግሯል። (መዝሙር 1:1, 2) የአምላክን ቃል በየቀኑ ማንበባችን ክርስቲያናዊ ጉዞአችንን እንድንቀጥል በሚያስችል መንገድ ኃይላችንንና መንፈሳችንን በማደስ “ደስተኛ” እንድንሆን ያደርገናል።
-
-
መጥተን እንድናነጋግርዎ ይፈልጋሉን?መጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 15
-
-
መጥተን እንድናነጋግርዎ ይፈልጋሉን?
በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለምም እንኳ ስለ አምላክ፣ ስለ መንግሥቱና ለሰው ልጆች ስላለው አስደናቂ ዓላማ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘት ደስተኛ መሆን ይችላሉ። ተጨማሪ መረጃ ብንሰጥዎ ደስ የሚልዎት ከሆነ ወይም አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎትና መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።
-