-
ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 112
ኢየሱስ የሚያከብረው የመጨረሻ የማለፍ በዓል ተቃረበ
ኒሳን 11 ማክሰኞ እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለሐዋርያቱ ሲሰጥ የነበረውን ትምህርት ጨረሰ። እንዴት ያለ ሥራ የበዛበትና አድካሚ ዕለት ነበር! አሁን፣ ምናልባትም በቢታንያ ለማደር ወደዚያ እየተመለሱ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ [“የማለፍ በዓል፣” NW] እንዲሆን ታውቃላችሁ፣ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።
ኢየሱስ ቀጣዩን ቀን ማለትም ኒሳን 12 ረቡዕ ዕለትን ያሳለፈው ራሱን ከሰዎች ገለል በማድረግ ከሐዋርያቱ ጋር ብቻ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ቀን በፊት በነበረው ዕለት የሃይማኖት መሪዎቹን በሕዝብ ፊት ነቅፏቸው ነበር፤ በመሆኑም ሊገድሉት እንደሚፈልጉ አውቋል። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን ምሽት ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የሚያከብረውን የማለፍ በዓል ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልበት ስላልፈለገ ረቡዕ ዕለት በግልጽ አልታየም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ። ቀደም ሲል በነበረው ቀን ኢየሱስ የሰነዘረባቸው ነቀፋ በጣም ስላንገበገባቸው የተንኮል ዘዴ ተጠቅመው እሱን ለመያዝና ለማስገደል ሴራ እየሸረቡ ነው። ሆኖም “በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን” አሉ። ሕዝቡ ኢየሱስን ይወዱት ስለነበረ ሕዝቡን ፈርተው ነበር።
የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለመግደል እያሴሩ እያለ አንድ ሰው ወደ እነሱ መጣ። ሰውዬው ከኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ መሆኑ ሳያስገርማቸው አልቀረም! ሰይጣን ጌታውን አሳልፎ የመስጠት መጥፎ ሐሳብ በልቡ ውስጥ እንዲበቅል አድርጎ ነበር። ይሁዳ “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ?” ብሎ ሲጠይቃቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! ደስ እያላቸው 30 ብር ሊሰጡት ተስማሙ። ይህ በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን መሠረት የአንድ ባሪያ ዋጋ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ ሕዝብ በሌለበት ቦታ ኢየሱስን ለእነርሱ አሳልፎ ለመስጠት ምቹ አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ።
ረቡዕ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ኒሳን 13 ሆነ። ኢየሱስ ከኢያሪኮ የመጣው ዓርብ ስለሆነ አሁን በቢታንያ ሲያድር ይህ ስድስተኛውና የመጨረሻው ሌሊት ነው። በሚቀጥለው ቀን ማለትም ሐሙስ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ መከበር ለሚጀምረው የማለፍ በዓል የመጨረሻ ዝግጅቶች መከናወን አለባቸው። የማለፍ በዓሉ በግ መታረድና ሙሉ በሙሉ መጠበስ ያለበት በዚያን ጊዜ ነው። በዓሉን የሚያከብሩት የት ነው? ዝግጅቱንስ የሚያደርግላቸው ማን ይሆን?
ኢየሱስ ይህን በዝርዝር አልተናገረም፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ይሁዳ ለካህናት አለቆቹ ጠቁሞ የማለፍ በዓሉ እየተከበረ እያለ እንዳያስይዘው ለማድረግ ብሎ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አሁን፣ ሐሙስ ቀትር ላይ ሳይሆን አይቀርም፣ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “ፋሲካን [“የማለፍ በዓልን፣” NW] እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ከቢታንያ ላካቸው።
“ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ?” ብለው ጠየቁት።
“እነሆ፣ ወደ ከተማ ስትገቡ” አለ ኢየሱስ፤ “ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም:- መምህሩ:- ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን [“የማለፍ በዓልን፣” NW] የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”
የቤቱ ባለቤት የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ምናልባትም ኢየሱስ ይህን ልዩ በዓል በእሱ ቤት ለማክበር እንደሚጠይቀው ሲጠባበቅ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ሁሉም ነገር ኢየሱስ እንዳለው ሆኖ አገኙት። ስለዚህ ሁለቱ ሐዋርያት በጉ እንዲዘጋጅና የማለፍ በዓሉን የሚያከብሩት አሥራ ሦስቱ ሰዎች ማለትም ኢየሱስና አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የሚያስፈልጓቸው ሌሎች ነገሮች በሙሉ እንዲዘጋጁ አደረጉ። ማቴዎስ 26:1-5, 14-19፤ ማርቆስ 14:1, 2, 10-16፤ ሉቃስ 22:1-13፤ ዘጸአት 21:32
▪ ኢየሱስ ረቡዕ ዕለት ምን ሳያደርግ አይቀርም? ለምንስ?
▪ በሊቀ ካህናቱ ቤት ምን ስብሰባ ተካሄደ? ይሁዳ ወደ ሃይማኖት መሪዎቹ የሄደውስ ለምን ነበር?
▪ ኢየሱስ ሐሙስ ወደ ኢየሩሳሌም የላከው እነማንን ነው? የላካቸውስ ለምንድን ነው?
▪ እነዚህ የተላኩት ሰዎች አሁንም የኢየሱስን ተአምራዊ ኃይል የሚያሳይ ምን ነገር አገኙ?
-
-
በመጨረሻው የማለፍ በዓል ላይ የታየ ትሕትናእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 113
በመጨረሻው የማለፍ በዓል ላይ የታየ ትሕትና
ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለማለፍ በዓሉ ዝግጅት ለማድረግ ቀደም ብለው ኢየሩሳሌም ገብተዋል። ኢየሱስ፣ ከሌሎቹ አሥር ሐዋርያት ጋር ሆኖ ሳይሆን አይቀርም፣ ዘግየት ብሎ ቀኑ መገባደጃ ላይ ደረሰ። ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች ከደብረ ዘይት ተራራ ሲወርዱ ፀሐይዋ በአድማስ በኩል እየጠለቀች ነበር። ኢየሱስ ከሞት እስከተነሣበት ጊዜ ድረስ ከተማዋን በቀን ከዚህ ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከት ይህ የመጨረሻው ጊዜ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሐዋርያት ወደ ከተማዋ ገቡና የማለፍ በዓሉን ወደሚያከብሩበት ቤት አመሩ። ደረጃዎቹን ወጡና ደርብ ላይ ወደሚገኘው ትልቅ ክፍል ገቡ። በክፍሉ ውስጥ ብቻቸውን ሆነው ለሚያከብሩት የማለፍ በዓል የሚያስፈልጉት ዝግጅቶች ሁሉ ተደርገው ነበር። ኢየሱስ “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” ሲል እንደገለጸው ይህን በዓል በጉጉት ሲጠባበቀው ቆይቷል።
በባሕሉ መሠረት በማለፍ በዓሉ ላይ የሚጠጣው አራት ጽዋ ወይን ነው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሦስተኛውን ጽዋ ከተቀበለ በኋላ አመሰገነና እንዲህ አላቸው:- “ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም።”
ኢየሱስ በእራቱ መካከል ተነሳና ከላይ የደረበውን ልብስ አስቀምጦ ማበሻ ጨርቅ ያዘ፤ ከዚያም በአንድ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ውኃ ሞላ። በነበረው ልማድ መሠረት የእንግዶች እግር እንዲታጠብ የሚያደርገው ጋባዡ ነው። ሆኖም በዚህ ወቅት በቦታው ጋባዥ ስላልነበረ ኢየሱስ ይህን አገልግሎት ራሱ አከናወነ። ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው ይህን ሊያከናውኑ ይችሉ ነበር፤ ሆኖም አሁንም በመካከላቸው ትንሽ ፉክክር ስላለ ሳይሆን አይቀርም፣ ይህን ያደረገ የለም። አሁን ኢየሱስ እግራቸውን ማጠብ ሲጀምር አፈሩ።
ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም” በማለት ተቃወመው።— የ1980 ትርጉም
ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፣ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” አለው።
ጴጥሮስ መልሶ “ጌታ ሆይ፣ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው።
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፣ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፣ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም።” እንዲህ ብሎ የተናገረው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው እንዳሰበ ስላወቀ ነው።
ኢየሱስ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን ጨምሮ የአሥራ ሁለቱንም እግር ካጠበ በኋላ ልብሱን ደርቦ እንደገና ወደ ማዕዱ ተመልሶ ተቀመጠ። ከዚያም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባርያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፣ ብታደርጉትም ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ።”
የትሕትና አገልግሎትን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! ሐዋርያቱ ራሳቸውን በጣም ከፍ አድርገው በመመልከትና ሁልጊዜ በሌሎች ሊገለገሉ እንደሚገባቸው አድርገው በማሰብ ቀዳሚውን ቦታ ለማግኘት መጣጣር የለባቸውም። ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይገባቸዋል። ይህ አንድን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም ተብሎ የሚከናወን እግር አጠባ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሥራው ምንም ያህል ዝቅተኛ ወይም የማያስደስት ቢሆንም እንኳ ያላንዳች አድልዎ በፈቃደኝነት የማገልገልን መንፈስ የሚያሳይ ነው። ማቴዎስ 26:20, 21፤ ማርቆስ 14:17, 18፤ ሉቃስ 22:14-18፤ 7:44፤ ዮሐንስ 13:1-17
▪ ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋን የተመለከተበትን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?
▪ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የማለፍ በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት ካመሰገነ በኋላ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ያሳለፈው የትኛውን ጽዋ ነው?
▪ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ለእንግዶች ምን አገልግሎት የማቅረብ ልማድ ነበር? ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማለፍ በዓሉን ባከበሩበት ጊዜ ይህ አገልግሎት ያልቀረበው ለምን ነበር?
▪ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ዝቅተኛ አገልግሎት ያከናወነበት ዓላማ ምንድን ነው?
-
-
የመታሰቢያው እራትእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 114
የመታሰቢያው እራት
ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር ካጠበ በኋላ “እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ” በማለት በመዝሙር 41:9 ላይ ያለውን ጥቅስ ጠቀሰ። ከዚያም መንፈሱ ተረበሸ፤ “ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።
ሐዋርያቱ አዘኑና እያንዳንዳቸው ኢየሱስን “እኔ እሆንን?” እያሉ ይጠይቁት ጀመር። የአስቆሮቱ ይሁዳ እንኳን ሳይቀር ጠየቀው። በማዕዱ ከኢየሱስ አጠገብ ጋደም ያለው ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ደረት ጠጋ ብሎ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
ኢየሱስ “ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው” ሲል መለሰ። “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” ከዚያ በኋላ ክፉ በሆነው ልቡ ውስጥ ያለውን ክፍተት በመጠቀም ሰይጣን እንደገና ይሁዳ ውስጥ ገባበት። ኢየሱስ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በዚያው ምሽት ይሁዳን የ“ጥፋት ልጅ” ብሎ መጥራቱ ትክክል ነበር።
አሁን ኢየሱስ ይሁዳን “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ” አለው። ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም። አንዳንዶቹ የገንዘብ ከረጢቱን የሚይዘው ይሁዳ ስለነበረ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ” ወይም ደግሞ ሄደህ ለድሆች ምጽዋት ስጥ ያለው መሰላቸው።
ይሁዳ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ በዓል ወይም መታሰቢያ አቋቋመ። አንድ ቂጣ ወስዶ አመሰገነና ቆራርሶ “እንካችሁ ብሉ” ብሎ ሰጣቸው። “ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ሲል ገለጸ።
እያንዳንዳቸው ቂጣውን ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ወይን የያዘ ጽዋ አነሳ፤ ይኸኛው ጽዋ በማለፍ በዓሉ ሥርዓት ላይ የተጠቀሙበት አራተኛው ጽዋ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አሁንም አመስግኖ ከጽዋው ጠጡ አላቸው። “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” ሲል ገለጸ።
ስለዚህ ይህ የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ነው። ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ይህ በዓል በየዓመቱ ኒሳን 14 ለእሱ መታሰቢያነት ይከበራል። የበዓሉ አክባሪዎች ኢየሱስና ሰማያዊ አባቱ የሰው ዘር ሞት ካመጣበት ኩነኔ እንዲላቀቅ ለማድረግ ያከናወኗቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። በዓሉ የክርስቶስ ተከታዮች ለሆኑት አይሁዶች የማለፍ በዓል ምትክ ይሆንላቸዋል።
በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ ቃል ኪዳን አሮጌውን የሕግ ቃል ኪዳን ተክቷል። ይህ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ አስታራቂነት በሁለት ወገኖች መካከል ማለትም በይሖዋ አምላክና በመንፈስ በተወለዱት 144,000 ክርስቲያኖች መካከል የተካሄደ ነው። ይህ ቃል ኪዳን የኃጢአት ይቅርታ ከማስገኘቱም በላይ ነገሥታትና ካህናት የሆኑ ሰዎችን ያቀፈ ሰማያዊ ብሔር እንዲቋቋም ያደርጋል። ማቴዎስ 26:21-29፤ ማርቆስ 14:18-25፤ ሉቃስ 22:19-23፤ ዮሐንስ 13:18-30፤ 17:12፤ 1 ቆሮንቶስ 5:7
▪ ኢየሱስ ጓደኛን የሚመለከት ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጠቅሷል? ትንቢቱን የተጠቀመበትስ እንዴት ነው?
▪ ሐዋርያቱ በጣም ያዘኑት ለምን ነበር? እያንዳንዳቸውስ ምን ጥያቄ አቅርበዋል?
▪ ኢየሱስ ይሁዳን ምን እንዲያደርግ ነገረው? ሆኖም ሌሎቹ ሐዋርያት እነዚህን መመሪያዎች የተረዷቸው እንዴት ነው?
▪ ኢየሱስ፣ ይሁዳ ከሄደ በኋላ ምን በዓል አቋቋመ? ይህስ ለምን ዓላማ ያገለግላል?
▪ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ወገኖች እነማን ናቸው? ቃል ኪዳኑስ ምን ዓላማ ያከናውናል?
-
-
ክርክር ተነሣእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 115
ክርክር ተነሣ
ገና አመሻሹ ላይ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ የትሕትና አገልግሎትን በተመለከተ ግሩም ትምህርት ሰጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ እየተቃረበ ላለው ሞቱ የመታሰቢያ በዓል አቋቋመ። አሁን በተለይ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከተፈጸመው ሁኔታ አንጻር በጣም አስገራሚ የሆነ አንድ ነገር ተከሰተ። ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው የጦፈ ክርክር ማድረግ ጀመሩ! ይህ ቀደም ሲል ተካሄዶ የነበረው ክርክር ቀጣይ ክፍል ሳይሆን አይቀርም።
ኢየሱስ በተራራው ላይ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተለወጠ በኋላ ሐዋርያቱ በመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው ተከራክረው እንደነበረ አስታውስ። ከዚህም በተጨማሪ ያዕቆብና ዮሐንስ በመንግሥቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው በሐዋርያቱ መካከል ሌላ ጭቅጭቅ ተነስቶ ነበር። አሁን ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በሚያሳልፈው በዚህ የመጨረሻ ሌሊት እንደገና ሲጣሉ ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ኢየሱስ ምን እርምጃ ወሰደ?
ኢየሱስ ሐዋርያቱን ባሳዩት ጠባይ አልተቆጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አሁንም እንደገና በትዕግሥት እንዲህ ሲል አሳማኝ የሆነ ሐሳብ አቀረበላቸው:- “የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፣ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ . . . በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን?” ከዚያም የራሱን ምሳሌ እንዲያስቡ በማድረግ “እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ” አላቸው።
ምንም እንኳ ሐዋርያቱ አለፍጽምና የነበረባቸው ቢሆንም በፈተናዎቹ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ተጣብቀው ቆይተዋል። ስለዚህ እንዲህ አለ:- “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንደገባ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ።” (NW) ይህ በኢየሱስና በታማኝ ተከታዮቹ መካከል የተደረገ የግል ቃል ኪዳን ከእሱ ጋር የንጉሣዊ ሥልጣኑ ተካፋዮች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ወደዚህ የመንግሥት ቃል ኪዳን የሚገቡት ሰዎች ቁጥር 144,000 ብቻ ይሆናል።
ሐዋርያቱ ምንም እንኳ ይህን የመሰለ ከክርስቶስ ጋር በመንግሥታዊ አገዛዝ የመካፈል ግሩም ተስፋ የቀረበላቸው ቢሆንም በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ደካሞች ነበሩ። ኢየሱስ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን ስለ እሱ እንደጸለየ ከገለጸለት በኋላ “አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና” ሲል አጥብቆ አሳሰበው።
“ልጆች ሆይ፣” አለ ኢየሱስ፤ “ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም:- እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፣ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”
ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።
“ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፣” ሲል ኢየሱስ መለሰለት፤ “ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ” አለው።
“ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው?” ሲል ጴጥሮስ ጠየቀ። “ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ” አለው።
“ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቀው። “እውነት እልሃለሁ፣ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።
“ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፣ ከቶ አልክድህም” በማለት ጴጥሮስ ተቃውሞውን ገለጸ። ሌሎቹ ሐዋርያትም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ሲናገሩ ጴጥሮስ “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” በማለት ተኩራራ።
ኢየሱስ ሐዋርያቱን በገሊላ እየዞሩ እንዲሰብኩ ያለ ኮሮጆና ያለ ከረጢት ልኳቸው እንደነበረ በመጥቀስ “አንዳች ጐደለባችሁን?” ሲል ጠየቃቸው።
“አንዳች እንኳ” ሲሉ መለሱ።
“አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፣ ከረጢትም ያለው እንዲሁ” አላቸው፤ “የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፣ ይህ:- ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፣ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና።”
ኢየሱስ ከክፉ አድራጊዎች ወይም ከዓመፀኞች ጋር የሚሰቀልበትን ጊዜ መጥቀሱ ነበር። በተጨማሪም ከዚያ በኋላ ተከታዮቹ ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸው ማመልከቱ ነበር። እነርሱም “ጌታ ሆይ፣ እነሆ፣ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት።
እርሱም “ይበቃል” አላቸው። ወደፊት እንደምንመለከተው ሰይፎቹን መያዛቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲሰጣቸው አጋጣሚ ይፈጥርለታል። ማቴዎስ 26:31-35፤ ማርቆስ 14:27-31፤ ሉቃስ 22:24-38፤ ዮሐንስ 13:31-38፤ ራእይ 14:1-3
▪ የሐዋርያቱ ክርክር በጣም የሚያስገርመው ለምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ ለክርክሩ እልባት የሰጠው እንዴት ነው?
▪ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ዓላማው ምንድን ነው?
▪ ኢየሱስ ምን አዲስ ትእዛዝ ሰጠ? ትእዛዙስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
▪ ጴጥሮስ ከሚገባው በላይ በራሱ እንደተማመነ ያሳየው እንዴት ነው? ኢየሱስስ ምን አለው?
▪ ኢየሱስ ኮሮጆና ከረጢት ስለ መያዝ የሰጠው መመሪያ ቀደም ሲል ስለ እነዚህ ነገሮች ከሰጠው መመሪያ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?
-
-
ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ አዘጋጃቸውእስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
-
-
ምዕራፍ 116
ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ አዘጋጃቸው
የመታሰቢያው እራት ያበቃ ቢሆንም ኢየሱስና ሐዋርያቱ አሁንም ያሉት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ ነው። ምንም እንኳ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚለያቸው ቢሆንም ብዙ የሚነግራቸው ነገር ነበረው። “ልባችሁ አይታወክ፤” ሲል አጽናናቸው። “በእግዚአብሔር እመኑ።” አክሎም “በእኔም ደግሞ እመኑ” ሲል ተናገረ።
“በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤” በማለት ኢየሱስ ንግግሩን ቀጠለ። “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ . . . እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ . . . ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፣ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” ሐዋርያቱ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ስለ መሄድ እየተናገረ እንዳለ አልገባቸውም፤ ስለዚህ ቶማስ “ጌታ ሆይ፣ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” ሲል ጠየቀው።
“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ሲል ኢየሱስ መለሰ። አዎን፣ ማንኛውም ሰው ወደ አብ ሰማያዊ ቤት ሊገባ የሚችለው ኢየሱስን በመቀበልና አኗኗሩን በመኮረጅ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል።
ፊልጶስ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” ሲል ጠየቀው። ፊልጶስ ጥንት ለእነ ሙሴ፣ ኤልያስና ኢሳይያስ በራእይ እንደተገለጠላቸው ዓይነት የአምላክን የሚታይ መግለጫ እንዲያሳየው የፈለገ ይመስላል። ሆኖም ሐዋርያት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ራእዮች የበለጠ አጋጣሚ ነበራቸው፤ ኢየሱስ ይህን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “አንተ ፊልጶስ፣ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል።”
ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀ በመሆኑ ከእሱ ጋር መኖርና እሱን መመልከት አብን እንደ መመልከት የሚቆጠር ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም” በማለት እንደገለጸው አብ ከወልድ ይበልጣል። ኢየሱስ ትምህርቱ ሁሉ ከሰማያዊ አባቱ የመነጨ እንደሆነ በመግለጽ ክብሩን ለአባቱ መስጠቱ ተገቢ ነበር።
ሐዋርያቱ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ሲነግራቸው ምንኛ ተበረታተው ይሆን:- “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል”! ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱ ካከናወናቸው ተአምራት የላቁ ተአምራት ይፈጽማሉ ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአገልግሎቱን ሥራ ከእሱ በበለጠ ለረጅም ጊዜ፣ በጣም ሰፊ በሆነ ክልል ለብዙ ሰዎች ያከናውናሉ ማለቱ ነው።
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ከተለየ በኋላ አይተዋቸውም። “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ሲል ቃል ገባላቸው። በተጨማሪም እንዲህ አላቸው:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW] ይሰጣችኋል፤ እርሱም . . . የእውነት መንፈስ ነው።” ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ይህን ሌላ ረዳት ማለትም መንፈስ ቅዱስን በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያፈስስላቸዋል።
ኢየሱስ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም አያየኝም” ሲል እንደገለጸው ከእነርሱ የሚለይበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። (የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ማንም ሰው ሊያየው የማይችል መንፈሳዊ ፍጡር ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ እንደገና “እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ” በማለት ለታማኝ ሐዋርያቱ ቃል ገባላቸው። አዎን፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለእነርሱ ሰብዓዊ አካል ለብሶ የሚታይ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ ከሞት አስነስቶ መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው በሰማይ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።
ኢየሱስ በመቀጠል የሚከተለውን ቀላል ደንብ ሰጠ:- “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
በዚህ ጊዜ ታዴዎስ እየተባለም የሚጠራው ሐዋርያው ይሁዳ ንግግሩን አቋረጠውና “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።
ኢየሱስ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል . . . የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም” ሲል መለሰለት። ዓለም ታዛዥ ከሆኑት የኢየሱስ ተከታዮቹ የተለየ ነው፤ የክርስቶስን ትምህርቶች ወደ ጎን ገሸሽ ያደርጋል። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱን ለዓለም አይገልጥም።
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሐዋርያቱን ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል። እስከዚህ ወቅት ድረስ እንኳ ብዙ ነገር መረዳት የተሳናቸው በመሆኑ የተማሩትን ሁሉ እንዴት ሊያስታውሱት ይችላሉ? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል የገባላቸው መሆኑ የሚያስደስት ነው:- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ [“ረዳት፣” NW] እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”
ኢየሱስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ . . . ልባችሁ አይታወክ” በማለት በድጋሚ አጽናናቸው። እርግጥ ኢየሱስ ሊለያቸው ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ “የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” ሲል ገልጿል።
ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ አጭር ነው። “ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም” አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም [“በእኔ ላይ ምንም ማድረግ አይችልም፣” የ1980 ትርጉም]።” የዚህ ዓለም ገዥ የተባለው ይሁዳ ውስጥ መግባትና እርሱን መቆጣጠር የቻለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሆኖም ኢየሱስ አምላክን ማገልገሉን እንዲያቆም ለማድረግ ሰይጣን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት የሚችል የኃጢአት ድክመት የለበትም።
የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት
ኢየሱስ ከመታሰቢያው እራት በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር ዘና ባለ መንገድ ልብ ለልብ በመወያየት ሲያበረታታቸው ቆይቷል። አሁን እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። ስለዚህ ኢየሱስ “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ” አላቸው። ይሁን እንጂ ከመሄዳቸው በፊት ኢየሱስ ለእነሱ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ አንድ ቀስቃሽ የሆነ ምሳሌ በመስጠት መናገሩን ቀጠለ።
ኢየሱስ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው” በማለት ምሳሌውን መናገር ጀመረ። ታላቁ ገበሬ ይሖዋ አምላክ ይህን ምሳሌያዊ ወይን የተከለው ኢየሱስ በ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ሲጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ በቀባው ጊዜ ነው። ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል ወይኑ የሚያመለክተው እሱን ብቻ አለመሆኑን እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። . . . ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፣ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ።”
ሐዋርያቱና ሌሎች ሰዎች ከ51 ቀናት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ የወይኑ ቅርንጫፎች ሆነዋል። በመጨረሻ 144,000 ሰዎች የምሳሌያዊው ወይን ቅርንጫፎች ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች ከወይኑ ግንድ ማለትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ላይ ሆነው የአምላክን መንግሥት ፍሬዎች የሚያፈራ ምሳሌያዊ ወይን ይሆናሉ።
ኢየሱስ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል” በማለት ፍሬ ለማፍራት ቁልፉ ምን እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ፍሬ ካላፈራ “እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፣ ያቃጥሉአቸውማል” ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።”
በተጨማሪም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ አለ:- “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።” አምላክ ከቅርንጫፎቹ የሚፈልገው ፍሬ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት በተለይም ፍቅር ማሳየታቸውን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ እንደነበረ ሁሉ ከእነርሱ የሚፈለገው ፍሬ እሱ እንዳደረገው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መሳተፍ ይጠይቅባቸዋል።
ኢየሱስ በመቀጠል “በፍቅሬ ኑሩ” ሲል አጥብቆ አሳሰበ። ሆኖም ሐዋርያቱ ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? “ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ሲል ተናገረ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”
ኢየሱስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሕይወቱን ለሐዋርያቱና በእሱ ለሚያምኑ ሌሎች ሰዎች በሙሉ አሳልፎ በመስጠት ይህን ከሁሉ የላቀ ፍቅር ያሳያል። የእሱ ምሳሌ ተከታዮቹ ይህን የራስን ጥቅም በመሠዋት የሚገለጽ ፍቅር አንዳቸው ለሌላው እንዲያሳዩ ሊገፋፋቸው ይገባል። ቀደም ሲል ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት እንደገለጸው ይህ ፍቅር ማንነታቸውን ለይቶ ያሳውቃል።
ኢየሱስ ወዳጆቹን ለይቶ በመግለጽ እንዲህ አለ:- “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።”
የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መሆን እንዴት ያለ ውድ ዝምድና ነው! ሆኖም ተከታዮቹ ይህን ዝምድና እንደያዙ ለመቀጠል እንዲችሉ ‘ፍሬ ማፍራታቸውን መቀጠል’ አለባቸው። ኢየሱስ ፍሬ ማፍራታቸውን ከቀጠሉ ‘አብ በስሙ የለመኑትን ሁሉ እንደሚሰጣቸው’ ተናግሯል። በእርግጥም ይህ የመንግሥቱን ፍሬ በማፍራት የሚገኝ ታላቅ ወሮታ ነው! ኢየሱስ ሐዋርያቱ ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ በድጋሚ አጥብቆ ካሳሰባቸው በኋላ ዓለም እንደሚጠላቸው ገለጸ። ሆኖም “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ” በማለት አጽናናቸው። ኢየሱስ በመቀጠል ዓለም ተከታዮቹን ለምን እንደሚጠላቸው ሲገልጽ “እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ብሏል።
ኢየሱስ ዓለም እነርሱን የሚጠላበትን ምክንያት ይበልጥ በማብራራት እንዲህ ሲል መናገሩን ቀጠለ:- “የላከኝን [ይሖዋ አምላክን] አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በገለጸው መሠረት የፈጸማቸው ተአምራት እርሱን የሚጠሉትን ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው እንዲቆጠሩ ያደርጓቸዋል:- “ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ እኔንም አባቴንም ጠልተዋል።” (የ1980 ትርጉም) ስለዚህ ኢየሱስ እንደተናገረው “በከንቱ ጠሉኝ” የሚለው ጥቅስ ተፈጽሟል።
ኢየሱስ ቀደም ሲል እንዳደረገው አሁንም ረዳት የሆነውን የአምላክን ከፍተኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ማለትም መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል በመግባት አጽናናቸው። “እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ . . . ትመሰክራላችሁ” አላቸው።
ተጨማሪ የስንብት ማሳሰቢያ
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ወጥተው ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ” በማለት ኢየሱስ መናገሩን ቀጠለ። ከዚያም የሚከተለውን ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው:- “ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።”
ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሐዋርያቱ በዚህ ማስጠንቀቂያ በጣም ተረብሸዋል። ምንም እንኳ ኢየሱስ ዓለም እንደሚጠላቸው ቀደም ሲል የነገራቸው ቢሆንም ሊገደሉ እንደሚችሉ በቀጥታ አልገለጸላቸውም ነበር። “ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም” ሲል ኢየሱስ ገለጸ። ሆኖም ከእነርሱ ከመለየቱ በፊት ይህን መረጃ በመስጠት አስቀድመው እንዲዘጋጁ ማድረጉ እንዴት ጥሩ ነው!
“አሁን ግን” በማለት ኢየሱስ መናገሩን ቀጠለ፤ “ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም:- ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም።” ቀደም ሲል በዚያው ምሽት የሚሄድበትን ቦታ በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር፤ ሆኖም አሁን በነገራቸው ነገር በጣም ስለደነገጡ ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ጥያቄ አላቀረቡም። ኢየሱስ “ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል” አለ። ሐዋርያቱ ያዘኑት ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸውና እንደሚገደሉ ስላወቁ ብቻ ሳይሆን ጌታቸውም ከእነርሱ ሊለይ በመሆኑ ነው።
ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ [“ረዳቱ፣” NW] ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ በአንድ ጊዜ ከአንድ ቦታ በላይ መሆን አይችልም፤ ሆኖም ወደ ሰማይ ሲሄድ ተከታዮቹ በየትኛውም የምድር ክፍል ቢሆኑ ረዳት የሆነውን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊልክላቸው ይችላል። ስለዚህ የኢየሱስ መሄድ ጠቃሚ ነው።
ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ “ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል” ሲል ተናገረ። (NW) የዓለም ኃጢአት ማለትም በአምላክ ልጅ አለማመኑ ይጋለጣል። በተጨማሪም ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲያርግ የኢየሱስ ጽድቅ አሳማኝ ማስረጃ ይታያል። ሰይጣንና የእሱ ክፉ ዓለም የኢየሱስን የጸና አቋም ለማስለወጥ አለመቻላቸው የዓለም ገዥ እንደተፈረደበት የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው።
ኢየሱስ በመቀጠል “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ” ሲል ተናገረ፤ “ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” አላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን መንፈስ ቅዱስ በሚያፈስበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች መረዳት የሚችሉትን ያህል ማስተዋል እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸው ቃል ገባላቸው።
ሐዋርያቱ በተለይ ኢየሱስ እንደሚሞትና ከዚያም ከሞት ከተነሣ በኋላ እንደሚገለጥላቸው አልተረዱም። ስለዚህ እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተጠያየቁ:- “ጥቂት ጊዜ አለ፣ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፣ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ:- ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው?”
ኢየሱስ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ስለተረዳ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፣ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፣ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።” በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ ሲገደል ዓለማዊዎቹ የሃይማኖት መሪዎቹ ደስ ይላቸዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ያዝናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ሐዘናቸው ወደ ደስታ ይለወጣል! በተጨማሪም ምሥክሮቹ እንዲሆኑ በጰንጠቆስጤ ዕለት የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በእነርሱ ላይ በማፍሰስ ኃይል ሲሰጣቸው ደስታቸው ይቀጥላል!
ኢየሱስ የሐዋርያቱን ሁኔታ በምጥ ላይ ካለች ሴት ሁኔታ ጋር በማነጻጸር “ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች” ሲል ተናገረ። ሆኖም ኢየሱስ አንዴ ልጅዋን ከወለደች በኋላ መከራዋን እንደማታስታውሰው በመግለጽ ሐዋርያቱን እንዲህ ሲል አበረታታቸው:- “እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን [ከሞት ስነሳ] እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፣ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።”
ሐዋርያቱ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በኢየሱስ ስም ልመና አላቀረቡም። አሁን ግን እንዲህ አላቸው:- “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። . . . እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።”
የኢየሱስ ቃላት ለሐዋርያቱ ትልቅ ማበረታቻ ናቸው። “ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን” አሉት። “አሁን ታምናላችሁን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቃቸው። “እነሆ፣ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፣ አሁንም ደርሶአል።” ሁኔታው ለማመን የሚያስቸግር ቢመስልም ሌሊቱ ገና ሳይገባደድ ይህ ነገር ተፈጽሟል!
“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ኢየሱስ፣ ሰይጣንና የሰይጣን ዓለም የያዘውን የጸና አቋም ለማስለወጥ ያደረጉትን ሙከራ ሁሉ ተቋቁሞ በታማኝነት የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ዓለምን አሸንፏል።
ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል የተደረገ የመደምደሚያ ጸሎት
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በነበረው የጠለቀ ፍቅር በመገፋፋት በጣም እየተቃረበ ላለው ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ እያዘጋጃቸው ነበር። አሁን ረዘም ላለ ጊዜ አጥብቆ ሲመክራቸውና ሲያጽናናቸው ከቆየ በኋላ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ የሚከተለውን ልመና ለአባቱ አቀረበ:- “ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፣ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፣ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።”
ኢየሱስ ያስተዋወቀው የዘላለም ሕይወት የሚለው ጭብጥ ምንኛ ስሜት ቀስቃሽ ነው! ኢየሱስ ‘በሥጋ ሁሉ ላይ ሥልጣን የተሰጠው’ በመሆኑ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ጥቅሞች ሟች ለሆኑት የሰው ልጆች በሙሉ መስጠት ይችላል። ሆኖም “የዘላለምን ሕይወት” የሚሰጠው በአብ ዘንድ ተቀባይነት ላገኙት ብቻ ነው። ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት በሚለው በዚህ ጭብጥ ላይ በመመርኮዝ ጸሎቱን ቀጠለ:-
“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” አዎን፣ መዳናችን አምላክንና ልጁን በማወቃችን ላይ የተመካ ነው። ሆኖም ከጭንቅላት እውቀት የበለጠ ነገርም ይፈለጋል።
አንድ ሰው ከእነርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት በቅርብ ሊያውቃቸው ይገባል። አንድ ሰው ለነገሮች ያለው አመለካከት እነርሱ ካላቸው አመለካከት ጋር አንድ መሆን አለበት፤ በተጨማሪም ማንኛውንም ነገር በእነርሱ ዓይን መመልከት ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን የይሖዋንና የኢየሱስን ባሕርያት ለመኮረጅ መጣር አለበት።
ኢየሱስ በመቀጠል “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” ሲል ጸለየ። እስከዚህ ደረጃ ድረስ ያለውን ሥራውን በመፈጸሙና የተቀረውም እንደሚሳካለት በመተማመን “አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” የሚል ልመና አቀረበ። አዎን፣ በትንሣኤ አማካኝነት ቀድሞ ወደነበረው ሰማያዊ ክብር ለመመለስ መጠየቁ ነበር።
ኢየሱስ በምድር ላይ ያከናወነውን ዋነኛ ሥራ ጠቅለል አድርጎ በመግለጽ እንዲህ አለ:- “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል።” ኢየሱስ፣ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም በአገልግሎቱ ከመጠቀሙም በላይ የስሙን ትክክለኛ አጠራር አሳይቷል። ሆኖም የአምላክን ስም ለሐዋርያቱ ለመግለጽ ከዚህም የበለጠ ነገር አድርጓል። ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ስለ ዓላማዎቹ ያላቸውን እውቀትና ግንዛቤ አስፍቶላቸዋል።
ኢየሱስ እሱ ከበታቹ ሆኖ የሚያገለግለውን ይሖዋን የበላዩ አድርጎ ክብር በመስጠት እንዲህ ሲል በትሕትና ተናግሯል:- “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፣ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፣ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።”
ኢየሱስ በተከታዮቹና በተቀረው የሰው ዘር መካከል ልዩነት እንዳለ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ . . . ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ . . . እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም . . . ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም፤” እርሱም የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው። በዚህ ወቅት ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ርካሽ የሆነ ተልዕኮውን እያከናወነ ነበር። በዚህ መንገድ ይሁዳ ሳያውቀው ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲፈጸሙ እያደረገ ነበር።
“ዓለም ጠላቸው” በማለት ኢየሱስ ጸሎቱን ቀጠለ። “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።” የኢየሱስ ተከታዮች በዓለም ውስጥ ማለትም በሰይጣን በሚገዛው የተደራጀ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ናቸው። ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች ምን ጊዜም ከዚህ ዓለምና ከክፋቱ ራሳቸውን ገለልተኞች ያደርጋሉ፤ ማድረግም አለባቸው።
“በእውነትህ ቀድሳቸው” በማለት ኢየሱስ ቀጠለ፤ “ቃልህ እውነት ነው።” ኢየሱስ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሳቸውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እዚህ ላይ “እውነት” ብሎ ጠርቷቸዋል። ሆኖም እሱ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ትምህርቶችና ከጊዜ በኋላ በመንፈስ አነሳሽነት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አድርገው የጻፋቸው ጽሑፎችም “እውነት” ናቸው። ይህ እውነት አንድን ሰው መቀደስ፣ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ መለወጥና ከዓለም የተለየ ሰው ማድረግ ይችላል።
አሁን ኢየሱስ ‘ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ቃል አማካኝነት በእሱ ስለሚያምኑ ሰዎችም ጭምር’ ጸለየ። ስለዚህ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹ ስለሚሆኑትና ወደፊት ወደ ‘አንዱ መንጋ’ ተሰብስበው ደቀ መዛሙርቱ ስለሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ጸልዮአል። ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የጠየቀው ነገር ምንድን ነው?
“አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ . . . አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ።” ኢየሱስና አባቱ ቃል በቃል አንድ አካል አይደሉም፤ ሆኖም በሁሉም ነገሮች ስምም ናቸው። ኢየሱስ “ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው” ያውቅ ዘንድ ተከታዮቹ ይህን አንድነት እንዲያገኙ ጸልዮአል።
ኢየሱስ ወደፊት ቅቡዓን ተከታዮቹ ስለሚሆኑት ሰዎች ለሰማያዊ አባቱ ልመና አቀረበ። ያቀረበው ልመና ምንድን ነው? “ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት . . . እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ” ሲል ልመና አቅርቧል። ዓለም ሳይፈጠር ሲል አዳምና ሔዋን ልጅ ከመውለዳቸው በፊት ማለቱ ነበር። ይህ ከመሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን አንድያ ልጁን ወዶታል።
ኢየሱስ ጸሎቱን ሲደመድም እንዲህ በማለት በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ:- “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።” የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል ሐዋርያቱ በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ፍቅር ማወቅ ይጠይቅባቸው ነበር ማለት ነው። ዮሐንስ 14:1 እስከ 17:26፤ 13:27, 35, 36፤ 10:16፤ ሉቃስ 22:3, 4፤ ዘጸአት 24:10፤ 1 ነገሥት 19:9-13፤ ኢሳይያስ 6:1-5፤ ገላትያ 6:16፤ መዝሙር 35:19፤ 69:4፤ ምሳሌ 8:22, 30
▪ ኢየሱስ የሚሄደው ወዴት ነው? ወደዚያ ቦታ ስለሚኬድበት መንገድስ ቶማስ የተሰጠው መልስ ምንድን ነው?
▪ ፊልጶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ኢየሱስ ምን እንዲያደርግለት ፈልጎ የነበረ ይመስላል?
▪ ኢየሱስን ያየ አብንም አይቷል የሚባለው ለምንድን ነው?
▪ የኢየሱስ ተከታዮች እሱ ካከናወነው ሥራ የበለጠ የሚያከናውኑት እንዴት ነው?
▪ ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ምንም ማድረግ የማይችለው ከምን አንጻር ነው?
▪ ይሖዋ ምሳሌያዊውን ወይን የተከለው መቼ ነው? ሌሎች የወይኑ ክፍል የሆኑት መቼና እንዴት ነው?
▪ በመጨረሻ ምሳሌያዊው ወይን ምን ያህል ቅርንጫፎች ይኖሩታል?
▪ አምላክ ከቅርንጫፎቹ ምን ዓይነት ፍሬ ይፈልጋል?
▪ የኢየሱስ ወዳጆች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
▪ ዓለም የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠላቸው ለምንድን ነው?
▪ ሐዋርያቱን የረበሻቸው የትኛው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ነው?
▪ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ወዴት እንደሚሄድ ሳይጠይቁት የቀሩት ለምንድን ነው?
▪ ሐዋርያቱ በተለይ ያልተረዱት ነገር ምን ነበር?
▪ ኢየሱስ የሐዋርያቱ ሁኔታ ከሐዘን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
▪ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ ተናግሯል?
▪ ኢየሱስ ዓለምን ያሸነፈው እንዴት ነው?
▪ ኢየሱስ “በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን” የተሰጠው በምን መንገድ ነው?
▪ አምላክንና ልጁን ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው?
▪ ኢየሱስ የአምላክን ስም የገለጠው በምን መንገዶች ነው?
▪ “እውነት” ምንድን ነው? አንድን ክርስቲያን ‘የሚቀድሰውስ’ እንዴት ነው?
▪ አምላክ፣ ልጁና እውነተኛ አምላኪዎች በሙሉ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?
▪ “ዓለም ሳይፈጠር” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው የትኛውን ጊዜ ነው?
-