የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 24 ገጽ 160-ገጽ 165 አን. 6
  • ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በየቀኑ ጥሩ ዓይነት አነጋገር መጠቀም
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ጥሩ ጣዕም ያላቸውን የእውነት ቃላት መናገር
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • አንደበታችሁ ያለውን ኃይል ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ ተናገር
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 24 ገጽ 160-ገጽ 165 አን. 6

ጥናት 24

ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አክብሮትንና ደግነትን የሚያንጸባርቁ፣ ለመረዳት የማያስቸግሩ፣ ያልተደጋገሙ እንዲሁም ንግግርህ ኃይል እንዲኖረውና ተገቢውን ስሜት እንዲያንጸባርቅ የሚያደርጉ ቃላትን ምረጥ። ከሰዋስው ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ ተጠቀምባቸው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ለምታስተላልፈው መልእክት ያለህን አክብሮት እንዲሁም ለምታነጋግራቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለህ ያንጸባርቃል። ሰዎች ለመልእክትህ የሚሰጡትንም ምላሽ ይወስናል።

ሐሳብን ለመግለጽ ቃላት ወሳኝ ናቸው። ይሁንና የታሰበላቸውን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ በጥንቃቄ የተመረጡ ሊሆኑ ይገባል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ተስማሚ ሆኖ የሚገኘው ቃል በሌሎች ሁኔታዎች ያልተፈለገ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ውበት ያለውን ቃል እንኳ ያለ ቦታው ከተጠቀምንበት ‘ሊያቆስል’ ይችላል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው ለሰዎች ስሜት ሳይጨነቅ እንዳመጣለት እንደሚናገር የሚያሳይ ይሆናል። አንዳንድ ቃላት ሁለት ትርጉም ይኖራቸውና አንደኛው ትርጉም ሌሎችን የሚያስከፋ ወይም የሚያንኳስስ ይሆናል። (ምሳሌ 12:​18፤ 15:​1) በሌላ በኩል ደግሞ “መልካም ቃል” ማለትም ሌሎችን የሚያበረታታ ቃል የሰሚዎቹን ልብ ደስ ያሰኛል። (ምሳሌ 12:​25) ትክክለኛውን ቃል መምረጥ ለጥበበኛ ሰው እንኳ ሳይቀር ጥረት ይጠይቅበታል። ሰሎሞን ‘ያማረውንና በቅንም የተጻፈውን እውነተኛ ቃል’ መርምሮ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።​—⁠መክ. 12:​10

በአንዳንድ ቋንቋዎች በዕድሜ ከገፉ ወይም ከባለ ሥልጣናት ጋር ስትነጋገር የምትጠቀምባቸው ለየት ያሉ መግለጫዎች አሉ። ከእኩዮችህ ወይም ከታናናሾችህ ጋር ስትነጋገር ግን በእነዚህ መግለጫዎች አትጠቀምም። እንዲህ ያለውን የአክብሮት አነጋገር አለመጠቀም እንደ ነውር ይቆጠራል። በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ልማድ ሌሎችን በአክብሮት ለማነጋገር የሚያገለግሉትን ቃላት ለራስህ ብትጠቀም ተገቢ አይሆንም። ሰዎችን ማክበርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው መስፈርት የትኛውም ሕግ ወይም አካባቢያዊ ልማድ ከሚጠይቀው የላቀ ነው። ክርስቲያኖች ‘ሁሉንም ሰው እንዲያከብሩ’ አጥብቆ ያሳስባል። (1 ጴጥ. 2:​17) ይህን መመሪያ ከልባቸው የሚታዘዙ ሁሉ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያነጋግሩት አክብሮት በተሞላበት መንገድ ነው።

ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ነውረኛ የሆኑና የብልግና ቃላት ሲናገሩ እንሰማለን። ኃይለ ቃል ከተናገሩ የሚሉት ነገር ተሰሚነት እንደሚኖረው ይሰማቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት አነጋገር የሚጠቀሙት የሚያውቋቸው ቃላት በጣም ውስን ስለሆኑ ሊሆን ይችላል። የይሖዋን መንገዶች ከመማሩ በፊት እንዲህ ዓይነት አነጋገር የመጠቀም ልማድ የነበረው ሰው ከዚህ ልማድ መላቀቅ ሊያስቸግረው ይችላል። ይሁንና መላቀቅ አይችልም ማለት አይደለም። አንድ ሰው የአነጋገር ልማዱን እንዲያስተካክል የአምላክ መንፈስ ሊረዳው ይችላል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ራሱም ለመስማት ደስ የሚሉና የሚያንጹ ቃላትን ለማሰባሰብና በእነዚህ ቃላት አዘውትሮ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።​—⁠ሮሜ 12:​2፤ ኤፌ. 4:​29፤ ቆላ. 3:​8

ለመረዳት የማያስቸግር አገላለጽ። አነጋገራችን ጥሩ እንዲሆን ካስፈለገ በቀላሉ የሚገባ መሆን አለበት። (1 ቆሮ. 14:​9) አድማጮችህ የምትጠቀምባቸውን ቃላት በግልጽ መረዳት ካልቻሉ ባዕድ ቋንቋ እንደሚናገር ሰው ልትሆንባቸው ትችላለህ።

በአንድ ዓይነት የሙያ መስክ የተሰማሩ ሰዎች የሚግባቡባቸው ለየት ያለ ትርጉም ያላቸው አንዳንድ ቃላት አሉ። እነርሱ እነዚህን ቃላት በየዕለቱ ይጠቀሙባቸው ይሆናል። አንተ ግን አለቦታው ብትጠቀምባቸው ከሰዎች ጋር ለመግባባት እንቅፋት ሊፈጥሩብህ ይችላሉ። ከዚህም በላይ የምትናገራቸው ቃላት የተለመዱ ቢሆኑ እንኳ ሳያስፈልግ ዝርዝር ሐሳብ የምታበዛ ከሆነ አድማጮችህ አንተን ማዳመጥ ትተው ሌላ ነገር ሊያብሰለስሉ ይችላሉ።

አስተዋይ የሆነ ተናጋሪ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው አድማጮቹ ሳይቀር ሊረዷቸው የሚችሉትን ቃላት ይመርጣል። የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ ‘ለምስኪኖች’ ያስባል። (ኢዮብ 34:​19) ተናጋሪው እንግዳ የሆነ ቃል መጠቀም ቢፈልግ እንኳ ትርጉሙን ግልጽ የሚያደርግ ቀላል መግለጫ ሊያክልበት ይገባል።

በጥንቃቄ የተመረጡና ለመረዳት ቀላል የሆኑ ቃላት የተፈለገውን መልእክት ጥሩ አድርጎ የማስተላለፍ ኃይል ይኖራቸዋል። አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችና ያልተወሳሰቡ ሐረጎች በቀላሉ ይያዛሉ። ንግግሩ በአጫጭር ዓረፍተ ነገር ብቻ የተሞላ እንዳይሆን ረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችን አሰበጣጥሮ ማስገባት ይቻላል። ይሁን እንጂ አድማጮችህ እንዲያስታውሱት የምትፈልገውን ሐሳብ ለመግለጽ ቀላል የሆኑ ቃላትንና እጥር ምጥን ያሉ ዓረፍተ ነገሮችን ተጠቀም።

የተለያዩና ትክክለኛ ቃላት ተጠቀም። በየትኛውም ቋንቋ ሐሳብን ለመግለጽ የሚያስችሉ በቂ ቃላት ይኖራሉ። በየቦታው ተመሳሳይ ቃል ከመጠቀም ይልቅ የተለያዩ ቃላት ተጠቀም። ይህም ንግግርህን ማራኪና ትርጉም ያለው ያደርግልሃል። የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው?

በምታነብበት ጊዜ የማታውቃቸው ቃላት ካጋጠሙህ ምልክት አድርግባቸውና ትርጉማቸውን ከመዝገበ ቃላት ተመልከት። ከዚያም በዚህ መልክ ካሰባሰብካቸው ቃላት መካከል የተወሰኑትን መርጠህ አጋጣሚውን ስታገኝ ለመጠቀም ሞክር። ሆኖም ቃላቱን በትክክል ለመጥራትና ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት አገባብ ለመጠቀም ጥረት አድርግ እንጂ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ አትሞክር። የምታውቃቸው ቃላት በበዙ መጠን ንግግርህም የዚያኑ ያህል በቃላት የበለጸገ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ የሚያሻው አንድ ነገር አለ። አንድ ሰው ቃላቱን በትክክል የማይጠራ ወይም አለቦታቸው የሚጠቀምባቸው ከሆነ አድማጮቹ የሚናገረውን አያውቀውም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።

አዳዲስ ቃላት ለማወቅ የምንጥረው አድማጮቻችንን ለማስደመም ሳይሆን ትክክለኛውን መልእክት ማስተላለፍ ስለምንፈልግ ነው። የተራቀቀ አነጋገርና ረጃጅም ቃላት አድማጮች በግለሰቡ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋሉ። ፍላጎታችን ለሚያዳምጡን ሰዎች ጆሮ በሚጥም መንገድ ጠቃሚ መልእክት ማስተላለፍ ሊሆን ይገባል። “የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ አስታውስ። (ምሳሌ 15:​2) ለሁኔታው የሚስማሙና ለመረዳት የማያስቸግሩ ቃላት የምንጠቀም ከሆነ ንግግራችን የሚያነቃቃ ይሆናል እንጂ አሰልቺና ለዛ የሌለው አይሆንም።

የምታውቃቸው ቃላት እየበዙ ሲሄዱ ትክክለኛውን ቃል ለመጠቀም በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል። ሁለት ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም ሊኖራቸው ቢችልም በተለያየ አገባብ እንድትጠቀምባቸው የሚያስችል መጠነኛ የትርጉም ልዩነት ይኖራቸዋል። ይህንን ማስተዋልህ የንግግርህን ጥራት እንድታሻሽል ከማስቻሉም በላይ አድማጮችህን ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳትናገር ይረዳሃል። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሲናገሩ ልብ ብለህ አዳምጥ። አንዳንድ መዝገበ ቃላት በእያንዳንዱ ቃል ሥር ተመሳሳይ እንዲሁም ተቃራኒ ትርጉም ያላቸውን ቃላት ይዘረዝራሉ። በዚህ መንገድ ያንኑ መልእክት የሚያስተላልፉ የተለያዩ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ቃሉ ሊኖረው የሚችለውን ለየት ያለ ትርጉምም ይጠቁሙሃል። ይህ ደግሞ ለአንድ ሁኔታ ይበልጥ ተስማሚ የሆነውን ትክክለኛ ቃል ለመምረጥ ይረዳል። አንድን አዲስ ቃል መጠቀም ከመጀመርህ በፊት ትርጉሙ በትክክል ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚጠራና መቼ ልትጠቀምበት እንደሚገባ ማወቅ ይኖርብሃል።

አንድን ሐሳብ ጠቅለል አድርጎ ከመግለጽ ይልቅ ዘርዘር አድርጎ ማስቀመጡ አድማጮች ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንላቸው ይረዳል። አንድ ተናጋሪ “በወቅቱ ብዙ ሰዎች በበሽታ ተጠቅተው ነበር” ሊል ይችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ይህንኑ ሐሳብ “ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ጥቂት ወራት ውስጥ 21, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች በኅዳር በሽታ አልቀዋል” ብሎ ሊያስቀምጠው ይችላል። ተናጋሪው “በወቅቱ፣” “ብዙ ሰዎች” እና “በበሽታ” የሚሉትን ቃላት ይበልጥ ግልጽ ሲያደርጋቸው ምን ያህል ልዩነት እንዳለው ልብ በል! በዚህ መንገድ ሐሳብህን ለመግለጽ ስለምትናገረው ርዕሰ ጉዳይ ጥሩ እውቀት ሊኖርህና ትክክለኞቹን ቃላት መርጠህ ልትጠቀም ይገባል።

ትክክለኛውን ቃል ከተጠቀምህ ቅልብጭ ባለ አነጋገር ነጥቡን መግለጽ ትችላለህ። ቃላት ካበዛህ ሐሳቡ ይድበሰበሳል። በሌላ በኩል ደግሞ ሐሳብህን በቀላል መንገድ ከገለጽህ አድማጮች የተናገርኸውን ነገር ለመረዳትም ሆነ ለማስታወስ አይቸገሩም። ትክክለኛውን እውቀት ለማስተላለፍ ይረዳሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቱን በቀላል አገላለጽ በማቅረብ ረገድ አቻ አይገኝለትም። አንተም ከእርሱ ምሳሌ ተማር። (በ⁠ማቴዎስ 5:​3-12 እና ማርቆስ 10:​17-21 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ምሳሌዎች ተመልከት።) በጥንቃቄ በተመረጡ ቃላትና እጥር ምጥን ባለ መንገድ ሐሳብህን መግለጽ ተለማመድ።

ኃይል ያላቸው፣ ስሜቱን የሚያስተላልፉና ገላጭ የሆኑ ቃላት። የምታውቃቸውን ቃላት ክምችት ለማሳደግ ስትጥር መፈለግ ያለብህ እንዲሁ አዲስ ቃል ብቻ ሳይሆን የራሳቸው ባሕርይ ያላቸውን ቃላት ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል የድርጊቱን ጥንካሬ የሚገልጽ ግስ፣ ሁኔታውን ሕያው አድርገው የሚገልጹ ቅጽሎችን እንዲሁም ፍቅርና ርኅራኄን፣ ደግነትን ወይም ቅንነትን የሚያንጸባርቁ ቃላት ልትፈልግ ትችላለህ።

እንዲህ ዓይነት ትርጉም አዘል ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ይሖዋ በነቢዩ አሞጽ አማካኝነት ‘መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ ክፉውን ጥሉ፣ መልካሙንም ውደዱ’ ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (አሞጽ 5:​14, 15) ነቢዩ ሳሙኤል ንጉሥ ሳኦልን ‘እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት ’ ብሎታል። (1 ሳሙ. 15:28) ይሖዋ ከሕዝቅኤል ጋር ሲነጋገር ‘የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸው’ በማለት የማይረሳ አገላለጽ ተጠቅሟል። (ሕዝ. 3:​7) ይሖዋ እስራኤላውያን የሠሩት ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገልጽ ‘ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል’ ብሏል። (ሚል. 3:​8) ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በባቢሎን ስላጋጠማቸው የእምነት ፈተና ዳንኤል ሲገልጽ ንጉሡ ላቆመው ምስል አንሰግድም በማለታቸው ‘ናቡከደነፆር ቁጣ ሞልቶበት’ ‘ወደሚነድደው እቶን እሳት’ አስረው እንዲጥሏቸው ትእዛዝ እንደሰጠ ተናግሯል። ንጉሡ ‘የእቶኑን እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት’ ትእዛዝ መስጠቱን በመዘገብ እሳቱ ምን ያህል ኃይለኛ እንደነበር እንድናስተውል ረድቶናል። እሳቱ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ የንጉሡ አገልጋዮች ገና ወደዚያ ሲቀርቡ ወላፈኑ በልቷቸዋል። (ዳን. 3:​19-22) ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት ከልቡ የተሰማውን ሐዘን በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሰዎች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- ‘ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።’​—⁠ማቴ. 23:​37, 38

በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላት ነጥቡ ለአድማጮች ቁልጭ ብሎ እንዲታይ ያደርጋሉ። የምትጠቀምበት ቃል አድማጮች የምትናገርለትን ነገር ‘እንዲያዩና’ ‘እንዲዳስሱ፣’ የምትጠቅሰውን ምግብ ‘እንዲያጣጥሙና’ ‘እንዲያሸትቱ’ እንዲሁም የምትጠቅሳቸውን ሰዎች ድምፅ ‘እንዲሰሙ’ ሊያደርጋቸው ይችላል። አድማጮችህ የምትናገረውን ነገር ሕያው አድርገህ ስላቀረብህላቸው ተመስጠው ያዳምጡሃል።

ሐሳቡን ሕያው አድርገው የሚገልጹ ቃላት ሰዎች ስሜታቸው ተነክቶ እንዲስቁ ወይም እንዲያለቅሱ ሊያደርጉ ይችላሉ። ተስፋ ቆርጦና ተክዞ የነበረ ሰው እንደገና የመኖር ጉጉት እንዲያድርበትና ፈጣሪውን እንዲወድድ በማድረግ ተስፋውን ሊያለመልሙለት ይችላሉ። በ⁠መዝሙር 37:​10, 11, 34፣ በ⁠ዮሐንስ 3:​16 እንዲሁም በ⁠ራእይ 21:​4, 5 ላይ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች በምድር ዙሪያ የሚገኙ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለውጠዋል።

መጽሐፍ ቅዱስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ስታነብብ የተለያዩ ቃላትንና አገላለጾችን ታገኛለህ። (ማቴ. 24:​45) አንብበሃቸው ብቻ አትለፍ። የማረኩህን ቃላት መርጠህ በዕለት ተዕለት ንግግርህ ተጠቀምባቸው።

የሰዋስውን ሕግ የጠበቀ አነጋገር። አንዳንድ ሰዎች ትክክለኛውን የሰዋስው ሕግ ተከትለው በመናገር ረገድ ሁልጊዜ እንደማይሳካላቸው ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ተማሪ ከሆንክ ጥሩ ሰዋስው መጠቀምንና ቃላትን በጥንቃቄ መምረጥን ለመማር አሁን ያለህን አጋጣሚ በሚገባ ልትጠቀምበት ይገባል። ግልጽ ያልሆነልህ የሰዋስው ሕግ ካለ አስተማሪህን ጠይቅ። እንዲሁ ፈተና ለማለፍ ብቻ ብለህ አታጥና። አንተ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንድትሰጥ የሚያደርግህ ከሌሎቹ ተማሪዎች የተለየ ዓላማ አለህ። የተዋጣልህ የምሥራቹ አገልጋይ መሆን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው።

በዕድሜ የገፋህ ከሆንክና አሁን የምትናገረው ቋንቋ አፍ መፍቻ ቋንቋህ ካልሆነስ? ወይም ደግሞ በቋንቋህ መደበኛ ትምህርት የመከታተል አጋጣሚ አላገኘህ ይሆናል። ሆኖም ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ ለምሥራቹ ስትል ለመሻሻል ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ስለ ሰዋስው ብዙ ነገር የምንማረው ሌሎች ሰዎች ሲናገሩ በማዳመጥ ነው። ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች ንግግር ሲሰጡ በጥሞና ተከታተል። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስታነብብ የዓረፍተ ነገሩን አቀነባበር፣ የቃላቱን አሰካክ እንዲሁም አገባባቸውን ለማስተዋል ሞክር። አንተም ንግግርህን በዚሁ መልክ ለማቅረብ ጥረት አድርግ።

ታዋቂ አርቲስቶች ከሰዋስው ሕግ ጋር የሚቃረን የአነጋገር ዘይቤ ይጠቀሙ ይሆናል። ሰዎች ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹን ግለሰቦች መኮረጅ ይቀናቸዋል። የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች እንዲሁም በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩና ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ያላቸው ሰዎች ሌላው ኅብረተሰብ ከሚያውቀው የተለየ ትርጉም የሰጧቸውን የራሳቸው ቃላት ይጠቀማሉ። ክርስቲያኖች እነዚህን ሰዎች መኮረጅ የለባቸውም። አነጋገራቸውን መኮረጅ ከእነርሱ ያስመድበናል።​—⁠ዮሐ. 17:​16

በየዕለቱ ጥሩ አነጋገር ይኑርህ። ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር ስትወያይ በአነጋገርህ ግዴለሽ ከሆንክ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ጥሩ አነጋገር ይኖረኛል ብለህ ልትጠብቅ አትችልም። በማንኛውም ጊዜ ጥሩ የአነጋገር ልማድ ካለህ ንግግር ስትሰጥም ሆነ ስለ እውነት ስትመሠክር አትቸገርም።

ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ

  • በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከቀረበው ትምህርት ልትሠራበት የምትፈልገውን አንድ ነጥብ ምረጥ። ለአንድ ወር ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በዚህ ላይ ለመሥራት ግብ አውጣ።

  • በምታነብበትም ሆነ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተናጋሪዎችን በምታዳምጥበት ጊዜ ይህንን ግብህን ማስታወስ ይኖርብሃል። በንግግርህ ልትጠቀምባቸው የምትፈልጋቸውን አገላለጾች በማስታወሻ ያዝ። በቀጣዮቹ አንድ ወይም ሁለት ቀናት ውስጥ በማስታወሻ የያዝኸውን እያንዳንዱን ቃል ተጠቀምበት።

መልመጃ:- በዚህ ሳምንት ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ስትዘጋጅ ትርጉማቸውን በደንብ የማታውቃቸውን ጥቂት ቃላት ምረጥ። መዝገበ ቃላት ካለህ አውጥተህ ተመልከት። አለዚያ ደግሞ ብዙ ቃላት የሚያውቅ ሰው ጠይቅ።

ልጠቀምባቸው የምፈልጋቸው ተጨማሪ ቃላት

ብዙ የቃላት ምርጫ እንዲኖረኝና በትክክል መግለጽ እንድችል የሚረዱ ቃላት ኃይል ያላቸው፣ ስሜቱን የሚያስተላልፉና ገላጭ የሆኑ ቃላት

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․ ․․․․․․․․․․․․․․

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ