ለጉባኤ የሚቀርቡ ንግግሮችን መዘጋጀት
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚካተቱት ክፍሎች ለሁሉም የጉባኤ አባላት ጥቅም ታስበው የሚዘጋጁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ጠቃሚ ትምህርቶች ይቀርባሉ። ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ክፍል እንድታቀርብ ከተመደብህ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎብሃል ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረው ጢሞቴዎስ ለማስተማር ሥራው እንዲጠነቀቅ አሳስቦታል። (1 ጢሞ. 4:16) ከአምላክ ጋር ስላላቸው ዝምድና ለመማር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ወደ እነዚህ ስብሰባዎች የሚመጡት ውድ ጊዜያቸውን ሠውተው ነው። አንዳንዶቹም ተጨማሪ መሥዋዕትነት ይጠይቅባቸዋል። በእርግጥም ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና በተመለከተ ሰዎችን ማስተማር ትልቅ መብት ነው! ታዲያ ይህንን መብት በአግባቡ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች
በትምህርት ቤቱ የሚቀርበው ይህ ክፍል ለሳምንቱ በሚመደበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ላይ የተመሠረተ ነው። ትምህርቱ እኛን እንዴት ይነካናል የሚለው ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በነህምያ 8:8 ላይ እንደተገለጸው ዕዝራና አብረውት የነበሩት ሰዎች የአምላክን ቃል ለሕዝቡ እያነበቡ በማብራራትና ‘ትርጉሙን በማስረዳት’ ሕዝቡ ማስተዋል እንዲያገኝ አድርገዋል። አንተም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦችን በምታቀርብበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ።
ይህን ክፍል ለማቅረብ መዘጋጀት የሚኖርብህ እንዴት ነው? ከቻልክ ክፍሉ የሚቀርብባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ከአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ከሚበልጥ ጊዜ በፊት አስቀድመህ አንብብ። ከዚያም ስለ ጉባኤህና ጉባኤው ስለሚያስፈልገው ነገር አስብ። ክፍሉን ለጉባኤው በሚጠቅም መንገድ ማቅረብ እንድትችል ጸልይ። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ውስጥ ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገር በተመለከተ ምን ምክር፣ ምሳሌ እና መሠረታዊ ሥርዓት ይገኛሉ?
ምርምር ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫን ምርምር ለማድረግ ልትጠቀምበት ትችላለህ። በማውጫው ላይ ያሉትን ጽሑፎች ተመርኩዘህ በመረጥካቸው ጥቅሶች ላይ ምርምር ስታደርግ እውቀት ሰጪ የሆኑ ተጨማሪ ነጥቦች፣ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች የተሰጠ ማብራሪያ፣ ጥቅሶቹ ስለ ይሖዋ ባሕርይ የሚገልጹትን እውነት በተመለከተ ወይም ስለ መሠረታዊ ሥርዓቶች የቀረበ ትምህርት ታገኝ ይሆናል። በጣም ብዙ ነጥቦች ለማብራራት አትሞክር። ከዚህ ይልቅ በተመረጡ ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ አተኩር። ጥቂት ቁጥሮች ላይ ብቻ አተኩሮ እነርሱን በሚገባ ማብራራቱ የተሻለ ይሆናል።
ክፍልህ አድማጮች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ያገኙትን ጥቅም እንዲናገሩ መጋበዝን የሚያካትት ሊሆን ይችላል። ለግልም ሆነ ለቤተሰብ ጥናት ወይም ለአገልግሎት የሚጠቅም ወይም በሕይወታቸው የሚሠሩበት ምን ትምህርት አግኝተዋል? ይሖዋ ከሰዎችና ከብሔራት ጋር ባደረገው ግንኙነት ስላሳያቸው ባሕርያት ምን ይነግረናል? የአድማጮች እምነት እንዲጠነክርና ለይሖዋ ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር የሚያደርግ ምን ትምህርት ይዟል? ዝርዝርና ውስብስብ ማብራሪያ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ የመረጥካቸውን ነጥቦች ትርጉምና ተግባራዊ ጠቀሜታ ጎላ አድርገህ ግለጽ።
ማስተማሪያ ንግግር
ይህ ንግግር በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት ርዕስ ወይም ከአንድ መጽሐፍ በተወሰደ ክፍል ላይ ተመሥርቶ የሚቀርብ ነው። በአብዛኛው በተመደበልህ ጊዜ ውስጥ ልታቀርበው ከምትችለው በላይ ብዙ ነጥቦች ይኖራሉ። ታዲያ ይህን ክፍል ማቅረብ የሚኖርብህ እንዴት ነው? አድማጮችህን ማስተማር አለብህ እንጂ እንዲሁ ትምህርቱን መሸፈንህ ብቻ በቂ አይሆንም። አንድ የበላይ ተመልካች “ለማስተማር የሚበቃ” ሊሆን ይገባል።—1 ጢሞ. 3:2
ለመዘጋጀት ስትነሣ በመጀመሪያ እንድታቀርበው የተመደበውን ጽሑፍ አጥና። ጥቅሶቹን አውጥተህ አንብብ። አሰላስል። ይህንን ማድረግ ያለብህ ክፍልህን የምታቀርብበት ቀን ከመድረሱ በፊት ነው። ንግግሩ የተመሠረተበትን ጽሑፍ ወንድሞችም አንብበውት እንደሚመጡ አትዘንጋ። የአንተ ኃላፊነት ነጥቦቹን መከለስ ወይም ጨምቆ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ማስረዳት ነው። ተስማሚ ሆነው ያገኘሃቸውን ነጥቦች ጉባኤውን ሊጠቅም በሚችል መንገድ አቅርባቸው።
እያንዳንዱ ልጅ የየራሱ ባሕርይ እንዳለው ሁሉ እያንዳንዱ ጉባኤም ልዩ የሚያደርገው የራሱ ባሕርይ ይኖረዋል። አንድ ወላጅ የሚያስተምረው ነገር ውጤት እንዲኖረው ከፈለገ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በመዘርዘር ብቻ አይወሰንም። አሳማኝ በሆነ መንገድ ያስረዳል። የልጁን ባሕርይና የሚያጋጥሙትን ችግሮች ግምት ውስጥ ያስገባል። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስተማሪዎች አድማጮቻቸው ምን እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ተስማሚ የሆነ ትምህርት ለማቅረብ ይጥራሉ። ይሁን እንጂ አስተዋይ የሆነ አስተማሪ በአድማጮቹ መካከል ያሉ ግለሰቦችን የሚያሸማቅቅ ምሳሌ አይጠቀምም። በይሖዋ መንገድ መመላለስ ያስገኘላቸውን ጥቅም ይጠቅሳል። እንዲሁም የጉባኤው አባላት የሚገጥማቸውን ችግር በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
ጥሩ የማስተማር ችሎታ የአድማጮችን ልብ ለመንካት ያስችላል። ይህ ደግሞ እውነታውን ከማስቀመጥ አልፎ የነጥቦቹን ትርጉም እንዲያስተውሉ መርዳትን ይጠይቃል። እንዲሁም ለአድማጮች ከልብ አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል። መንፈሳዊ እረኞች በጉባኤያቸው ያሉትን ወንድሞችና እህቶች በደንብ ሊያውቋቸው ይገባል። የጉባኤው አባላት ስለሚገጥሟቸው የተለያዩ ችግሮች ከልብ የሚያስቡ ከሆነ ችግራቸውን በመረዳት፣ በርኅራኄና በአዘኔታ ስሜት የሚያበረታታ ንግግር ያቀርባሉ።
ጥሩ አስተማሪ አንድ ንግግር ግልጽ የሆነ ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ ያውቃል። የትምህርቱ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ በሚያስችል መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ይህም እነዚህን ነጥቦች በቀላሉ ለማስታወስ ያስችላል። አድማጮች ሊሠሩባቸው የሚችሏቸውን ነጥቦች መጨበጥ መቻል አለባቸው።
የአገልግሎት ስብሰባ
በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ክፍሎች የምታቀርብበት መንገድ ትንሽ ለየት ያለ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ክፍል ብዙውን ጊዜ ጽሑፉ ላይ ያለውን ሐሳብ በሙሉ ማቅረብን እንጂ ይበልጥ ተስማሚ የሆነው ነጥብ የትኛው ነው ብሎ መምረጥን አይጠይቅም። አድማጮች በክፍሉ ውስጥ ለቀረበው ምክር ሁሉ መሠረት የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በደንብ እንዲገባቸው አድርግ። (ቲቶ 1:9) በአብዛኛው የሚመደበው ጊዜ ውስን ስለሆነ ተጨማሪ ነጥቦች ማካተት አይቻልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ክፍሉ እዚያ የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ላይኖር ይችላል። ምናልባት በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ ርዕስ ተጠቅሶ ሊሆን ይችላል። አለዚያም በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የተሰጠህ ስለ ክፍሉ የሚገልጽ ጥቂት ሐሳብ ብቻ ይሆናል። ከቀረበው ትምህርት ጋር በተያያዘ ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት የአንተ ኃላፊነት ነው። የተፈለገውን ነጥብ የሚያስጨብጥ አጠር ያለ ምሳሌ ወይም ለትምህርቱ የሚስማማ ተሞክሮ መናገር ያስፈልግህ ይሆናል። የተጣለብህ ኃላፊነት ክፍሉን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የጉባኤው አባላት የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን ሥራ እንዲሠሩና ይህንንም በደስታ እንዲያደርጉት በሚያበረታታ መንገድ ማስተማር እንደሆነ መዘንጋት የለብህም።—ሥራ 20:20, 21
ክፍልህን ስትዘጋጅ ስለ እያንዳንዱ የጉባኤው አባል አስብ። ስለሚያደርጉት ነገር አመስግናቸው። ክፍሉን በምታቀርብበት ጽሑፍ ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማና ደስተኛ እንዲሆኑ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
ክፍልህ ሠርቶ ማሳያ ወይም ቃለ ምልልስ አለው? ከሆነ አስቀድመህ ጥሩ ዝግጅት ልታደርግበት ይገባል። ሠርቶ ማሳያ የሚያቀርቡትንም ሆነ ቃለ ምልልስ የምታደርግላቸውን ሰዎች ሌላ ሰው እንዲያዘጋጅልህ ትነግር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት አይኖረውም። ሠርቶ ማሳያውንም ሆነ ቃለ ምልልሱን በተቻለ መጠን የስብሰባው ቀን ከመድረሱ በፊት ተለማመዱት። ይህ የንግግርህ ክፍል ስለሆነ ዋናውን ትምህርት በሚያጎለብት መንገድ እንዲቀርብ ማድረግ ይኖርብሃል።
ትላልቅ ስብሰባዎች
ግሩም መንፈሳዊ አቋም ያላቸው እንዲሁም ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪና አስተማሪ የሆኑ ወንድሞች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ክፍል እንዲያቀርቡ ይመደባሉ። እነዚህ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ትምህርት የሚቀርብባቸው ለየት ያሉ አጋጣሚዎች ናቸው። ክፍሉን እንድታቀርብ ስትመደብ በንባብ የሚቀርበው ጽሑፍ፣ የንግግር አስተዋጽኦ፣ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ መመሪያ ወይም ጥቂት መመሪያዎችን የያዘ አንድ አንቀጽ ብቻ ይሰጥህ ይሆናል። እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ ንግግር የማቅረብ መብት ስታገኝ የሚሰጥህን ክፍል ደጋግመህ አንብበው። የትምህርቱ ጠቀሜታ ግልጽ ሆኖ እስኪታይህ ድረስ በደንብ አጥናው።
በንባብ የሚቀርብ ንግግር እንዲሰጡ የተመደቡ ወንድሞች ምንም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ ማንበብ ይጠበቅባቸዋል። የቃላቱን ወይም የሐሳቡን አቀማመጥ አይቀይሩም። ዋና ዋና ነጥቦቹ የትኞቹ እንደሆኑና እንዴት እንደተዋቀሩ እስኪገባቸው ድረስ ያጠኑታል። በተገቢው ቦታ ላይ እያጠበቁ፣ በጋለ ስሜት፣ በወዳጃዊ መንፈስ፣ እንደሚያምኑበት በሚያሳይ መንገድና ለብዙ ተሰብሳቢዎች በሚመጥን የድምፅ መጠን ማቅረብ እስኪችሉ ድረስ ድምፃቸውን እያሰሙ ይለማመዱታል።
ከንግግር አስተዋጽኦ ክፍላቸውን እንዲያቀርቡ የሚመደቡ ወንድሞች እዚያ ላይ ካለው ሐሳብ ሳይወጡ ትምህርቱን እንዲያዳብሩ ይጠበቅባቸዋል። ተናጋሪው ከአስተዋጽኦው በቀጥታ ከማንበብ ወይም አስተዋጽኦውን በንባብ በሚቀርብ ንግግር መልክ ከማዘጋጀት ይልቅ መልእክቱን ተረድቶ በራሱ አባባል ሊያቀርበው ይገባል። ሁሉንም ዋና ዋና ነጥብ በደንብ ማብራራት እንዲችል በአስተዋጽኦው ላይ የተመደበውን እያንዳንዱን ጊዜ በጥብቅ መከተሉ በጣም አስፈላጊ ነው። ተናጋሪው በዋና ዋና ነጥቦቹ ሥር የተጠቀሱትን ሐሳቦችና ጥቅሶች ጥሩ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይገባል። እርሱ በግሉ የነኩትን ተጨማሪ ነጥቦች ለማስገባት ሲል የአስተዋጽኦውን ነጥቦች መተው አይኖርበትም። የትምህርቱ ዋና መሠረት የአምላክ ቃል ሊሆን እንደሚገባ ግልጽ ነው። የክርስቲያን ሽማግሌዎች ኃላፊነትም ‘ቃሉን መስበክ’ ነው። (2 ጢሞ. 4:1, 2) በመሆኑም አንድ ተናጋሪ በአስተዋጽኦው ላይ ያሉትን ጥቅሶች ትኩረት ሰጥቶ ማብራራትና ከነጥቡ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ማስረዳት ይኖርበታል።
ዛሬ ነገ አትበል
በጉባኤህ በተደጋጋሚ ንግግር የመስጠት አጋጣሚ አለህ? ሁሉንም በደንብ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? ባለቀ ሰዓት ክፍሎችህን ለመዘጋጀት ከምትጣደፍ ይልቅ አስቀድመህ ተዘጋጅ።
ጉባኤውን የሚጠቅም ክፍል ለማቅረብ አስቀድሞ በክፍሉ ላይ በደንብ ማሰብ ያስፈልጋል። እንግዲያው ክፍሉ እንደተሰጠህ የምታቀርበውን ትምህርት ወዲያውኑ የማንበብ ልማድ ሊኖርህ ይገባል። ይህም ሌላ ነገር እያደረግህም ትምህርቱን እንድታብላላው ይረዳሃል። ንግግሩን ከማቅረብህ በፊት ባሉት ቀናት ወይም ሳምንታት ትምህርቱን እንዴት በተሻለ መንገድ ተግባራዊ አድርገህ ማቅረብ እንደምትችል ለማስተዋል የሚረዱህን ሐሳቦች ትሰማ ይሆናል። የትምህርቱን አስፈላጊነት የሚያጠናክሩ ሁኔታዎችም ሊከሰቱ ይችላሉ። ክፍሉ እንደደረሰህ ማንበብና ስለእሱ ማሰብ መጀመር ጊዜ እንደሚወስድ የታወቀ ነው። ይሁንና ይህ በከንቱ የሚባክን ጊዜ አይደለም። አስቀድመህ ክፍሉን በሚገባ ማብላላትህ ያለውን ጥቅም የምታስተውለው የንግግርህን አስተዋጽኦ መዘጋጀት ስትጀምር ነው። በዚህ መንገድ መዘጋጀት በእጅጉ ውጥረት የሚቀንስ ከመሆኑም ሌላ ትምህርቱን ተግባራዊ በሆነና በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አድማጮች በሚጠቅም መንገድ ለማቅረብ ያስችላል።
ይሖዋ ሕዝቡን ለማስተማር ካደረገው ዝግጅት ጋር በተያያዘ ላገኘኸው መብት ከፍ ያለ አድናቆት ካለህ ይሖዋን ታስከብራለህ፤ እርሱን የሚወድዱትን ሰዎችም ትጠቅማለህ።—ኢሳ. 54:13፤ ሮሜ 12:6-8