-
መጠመቅ ለምን አስፈለገ?መጠበቂያ ግንብ—2002 | ሚያዝያ 1
-
-
15. የጥምቀት እጩዎች የሚጠመቁት ለምንድን ነው?
15 በክርስቶስ በኩል ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ሕይወታችንን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሠፍሮ ከሚገኘው መለኮታዊ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችንን የሚያሳይ ነው። የጥምቀት እጩዎች ይህን ውሳኔያቸውን ለማሳየት ልክ ኢየሱስ ራሱን ለአምላክ ማቅረቡን ለማሳየት በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንደተጠመቀ ሁሉ እነርሱም በውኃ ይጠመቃሉ። (ማቴዎስ 3:13) ኢየሱስ በዚህ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው ወቅት ላይ መጸለዩ ትኩረት የሚስብ ነው።—ሉቃስ 3:21, 22
16. ሰዎች ሲጠመቁ በምናይበት ጊዜ ደስታችንን በተገቢው መንገድ መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
16 የኢየሱስ ጥምቀት አስደሳች ወቅት ቢሆንም አክብሮት የሚሰጠው ክንውን ነበር። ዛሬ የሚከናወነው ክርስቲያናዊ ጥምቀትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች በሚጠመቁበት ጊዜ ደስታችንን አክብሮት በሚንጸባረቅበት ጭብጨባና ሞቅ ባለ ምስጋና መግለጽ እንችል ይሆናል። ሆኖም ይህ የእምነት መግለጫ ካለው ቅድስና አንጻር ደስታችንን በእልልታ፣ በፉጨትና ይህን በመሳሰሉ መንገዶች ከመግለጽ እንቆጠባለን። ደስታችንን መግለጽ የሚኖርብን አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መሆን አለበት።
17, 18. ግለሰቦች ለመጠመቅ ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን የሚረዳው ምንድን ነው?
17 የይሖዋ ምሥክሮች ሕፃናትን በመርጨት ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት የሌላቸውን ሰዎች አስገድደው በጅምላ እንደሚያጠምቁ ሰዎች ማንንም ሰው አስገድደው አያጠምቁም። እንዲያውም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃት የማያሟሉ ሰዎች እንዲጠመቁ አይፈቅዱም። ሌላው ይቅርና አንድ ሰው ያልተጠመቀ የምሥራቹ ሰባኪ ከመሆኑ በፊት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ግለሰቡ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በትክክል የተረዳ፣ ከትምህርቶቹ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለስ መሆኑንና “ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ለመሆን በእርግጥ ትፈልጋለህ?” ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ መስጠቱን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።
18 በአብዛኛው በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ላይ ያሉ ሰዎች መጠመቅ እንደሚፈልጉ በሚገልጹበት ጊዜ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አማኞች መሆናቸውንና ለመጠመቅ የሚያበቃቸውን መለኮታዊ መስፈርት ያሟሉ እንደሆነ ለማረጋገጥ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከግለሰቦቹ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። (ሥራ 4:4፤ 18:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረቱ ከ100 ለሚበልጡ ጥያቄዎች በግል የሚሰጡት መልስ ሽማግሌዎች ተጠያቂዎቹ ለጥምቀት የሚያበቁትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ያሟሉ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለመወሰን ያስችላቸዋል። አንዳንዶች ብቃቱን ስለማያሟሉ ለክርስቲያናዊ ጥምቀት ብቁ ሳይሆኑ ይቀራሉ።
ወደኋላ እንድትል የሚያደርግህ ነገር ይኖር ይሆን?
19. ከዮሐንስ 6:44 አንጻር ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?
19 ተገድደው በጅምላ የተጠመቁ ብዙ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ተነግሯቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፈለጉን የሚከተሉ ሰዎችን በማስመልከት “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44) ይሖዋ በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙትን 144, 000 ሰዎች ወደ ክርስቶስ ስቧቸዋል። ሰዎችን በማስገደድ የሚፈጸመው ጥምቀት አንድን ሰው አምላክ ላዘጋጀው ለዚህ ክብራማ ዝግጅት ፈጽሞ ሊያበቃው አይችልም።—ሮሜ 8:14-17፤ 2 ተሰሎንቄ 2:13፤ ራእይ 14:1
20. እስከ አሁን ያልተጠመቁ አንዳንድ ሰዎች ምን ነገር ሊረዳቸው ይችላል?
20 “ከታላቁ መከራ” በሕይወት አልፈው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ እጅግ ብዙ ሰዎች በተለይ ከ1930ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ከኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ጋር ተቀላቅለዋል። (ራእይ 7:9, 14፤ ዮሐንስ 10:16) ሕይወታቸውን ከአምላክ ቃል ጋር ያስማሙና ‘በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ ኃይላቸውና አሳባቸው’ እሱን የሚወድዱ በመሆናቸው ለጥምቀት ብቁ ይሆናሉ። (ሉቃስ 10:25-28) ምንም እንኳን አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ‘አምላክን በመንፈስና በእውነት እንደሚያመልኩ’ ቢገነዘቡም እንደ ኢየሱስ በመጠመቅ ለአምላክ ልባዊ ፍቅር እንዳላቸውና ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ያደሩ እንደሆኑ የሚያሳይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ ይላሉ። (ዮሐንስ 4:23, 24፤ ዘዳግም 4:24፤ ማርቆስ 1:9-11) ይህን አስፈላጊ እርምጃ በቀጥታ በመጥቀስ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ ከአምላክ ቃል ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ ለመኖር የሚያስችል ኃይልና ድፍረት እንዲያገኙና ያለምንም ገደብ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ወስነው እንዲጠመቁ ሊረዳቸው ይችላል።
21, 22. አንዳንዶች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ከመጠመቅ ወደኋላ የሚሉባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
21 አንዳንዶች በዓለም ጉዳዮች ወይም ሃብት በማሳደድ ከልክ በላይ ከመጠላለፋቸው የተነሳ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ ያጣሉ፤ ይህም ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። (ማቴዎስ 13:22፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) አመለካከታቸውንና ግባቸውን ቢለውጡ ኖሮ ምንኛ ደስተኛ ይሆኑ ነበር! ወደ ይሖዋ መቅረባቸው በመንፈሳዊ ያበለጽጋቸዋል፣ ከጭንቀት እፎይ እንዲሉ ይረዳቸዋል እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ሰላምና እርካታ ያስገኝላቸዋል።—መዝሙር 16:11፤ 40:8፤ ምሳሌ 10:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
22 ሌሎች ደግሞ ይሖዋን እንደሚወዱ ይናገራሉ ሆኖም በአምላክ ፊት ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርጋቸው ስለሚመስላቸው ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው አይጠመቁም። ይሁን እንጂ ሁላችንም ለአምላክ መልስ እንሰጣለን። የይሖዋን ቃል መስማት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ኃላፊነት አለብን። (ሕዝቅኤል 33:7-9፤ ሮሜ 14:12) ‘የተመረጠ ሕዝብ’ የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን ራሱን ለይሖዋ በወሰነ ብሔር ውስጥ በመወለዳቸው ምክንያት እርሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት በታማኝነት የማገልገል ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር። (ዘዳግም 7:6, 11) ዛሬ እንዲህ በመሰለ ብሔር ውስጥ የተወለደ የለም። ሆኖም ትክክለኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ካገኘን በእምነት እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል።
23, 24. ግለሰቦች ምንን በመፍራት ከመጠመቅ ወደኋላ ማለት አይኖርባቸውም?
23 አንዳንዶች በቂ እውቀት የለኝም የሚለው ፍርሃት ከመጠመቅ ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸው ይሆናል። ሆኖም ‘እውነተኛው አምላክ ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ ማግኘት’ ስለማይችል ሁላችንም መማር የሚኖርብን ገና ብዙ ነገር አለ። (መክብብ 3:11) ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። ወደ ይሁዲነት የተለወጠ እንደመሆኑ መጠን ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰነ እውቀት ነበረው፤ ሆኖም የአምላክን ዓላማ በሚመለከት ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ መልስ መስጠት ይችላል ማለት አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ ጃንደረባ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የመዳን ዝግጅት እንዳደረገ ከተረዳ በኋላ ወዲያውኑ በውኃ ተጠመቀ።—ሥራ 8:26-38
24 ሌሎች ደግሞ ቃላችንን ጠብቀን መኖር አንችል ይሆናል በሚል ፍርሃት ራሳቸውን ለአምላክ ሳይወስኑ ይቀራሉ። የ17 ዓመቷ ሞኒክ “እስከ ዛሬ ድረስ ሳልጠመቅ የቆየሁት ራሴን ስወስን ከምገባው ቃል ጋር ተስማምቼ መኖር ቢያቅተኝስ የሚል ፍርሃት ይዞኝ ነው” ብላለች። ይሁን እንጂ በሙሉ ልባችን በይሖዋ ከታመንን ‘መንገዳችንን ያቀናልናል።’ ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን ታማኝ አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ‘በእውነት መሄዳችንን’ እንድንቀጥል ይረዳናል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 3 ዮሐንስ 4
25. የትኛውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል?
25 ለይሖዋ ባላቸው የማያወላውል እምነትና ልባዊ ፍቅር ተነሳስተው በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ይጠመቃሉ። ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ለእርሱ ታማኝ ሆነው መኖር እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። ሆኖም የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ውስጥ በመሆኑ ልዩ ልዩ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ምን ማድረግ እንችላለን? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው ይሆናል።
-
-
በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉመጠበቂያ ግንብ—2002 | ሚያዝያ 1
-
-
በጽኑ ልብ ይሖዋን ማገልገላችሁን ቀጥሉ
“እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤ ልቤ ጽኑ ነው።”—መዝሙር 57:7 አ.መ.ት
1. የዳዊትን የመሰለ ጽኑ እምነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን አገልጋዮቹ በመሆን እውነተኛውን ክርስትና የሙጥኝ ብለን መኖር እንችል ዘንድ ይሖዋ በክርስቲያናዊ እምነት እንድንጸና ሊያደርገን ይችላል። (ሮሜ 14:4) በዚህም ምክንያት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው” በማለት ለመዘመር እንደተገፋፋው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት እኛም ጽኑ እምነት ሊኖረን ይችላል። (መዝሙር 108:1) ልባችን ጽኑ ከሆነ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም እንገፋፋለን። መመሪያና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እርሱ እየተመለከትን እኛም ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ እንደበዛላቸው’ ጽኑ አቋም ጠባቂዎች የማንነቃነቅ ከጽኑ አቋማችንና ከእምነታችን ፍንክች የማንል መሆናችንን ማስመስከር እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 15:58
2, 3. አንደኛ ቆሮንቶስ 16:13 ላይ ሠፍሮ የሚገኘው የጳውሎስ ማሳሰቢያ ትርጉም ምንድን ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ ለሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች “ነቅታችሁ ኑሩ፣ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፣ እንደ ወንድ ሆናችሁ ወደፊት ግፉ፣ እየጎለበታችሁ ሂዱ” የሚል ጥብቅ ምክር ሰጥቷቸው ነበር። ይህ ማሳሰቢያው ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖችም ይሠራል። (1 ቆሮንቶስ 16:13 NW ) በግሪክኛ እነዚህ ትእዛዛት በአሁን ጊዜ ግሥ ስለተቀመጡ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታሉ። ይህ ማሳሰቢያ ያዘለው ትርጉም ምንድን ነው?
3 ዲያብሎስን በመቃወምና ወደ አምላክ ተጠግቶ በመኖር በመንፈሳዊ ‘ነቅተን መኖር’ እንችላለን። (ያዕቆብ 4:7, 8) በይሖዋ መታመናችን አንድነታችንን ጠብቀን እንድንኖርና ‘በክርስቲያናዊ እምነት ጸንተን እንድንቆም’ ያስችለናል። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን አምላክን በድፍረት እያገለገልን በመካከላችን የሚገኙ ብዙ ሴቶችን ጨምሮ ሁላችንም ‘እንደ ወንድ ሆነን ወደፊት እንግፋ።’ (መዝሙር 68:11 NW ) ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስችለንን ብርታት እንዲሰጠን ያለማቋረጥ የሰማዩ አባታችንን በመመልከት ‘እየጎለበትን እንሄዳለን።’—ፊልጵስዩስ 4:13 አ.መ.ት
4. ክርስቲያን ለመሆን ከመጠመቃችን በፊት የወሰድናቸው እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?
4 ያለ ምንም ገደብ ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ይህን
-