የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መጽሔቶችን ለማበርከት የሚያስችሉ መግቢያዎችን መዘጋጀት የሚቻለው እንዴት ነው?
    የመንግሥት አገልግሎት—2006 | ኅዳር
    • መጽሔቶችን ለማበርከት የሚያስችሉ መግቢያዎችን መዘጋጀት የሚቻለው እንዴት ነው?

      1. በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን የናሙና አቀራረቦች በቃላችን ሸምድደን ለመናገር ከመጣር ይልቅ የራሳችንን መግቢያ መዘጋጀታችን የተሻለ የሚሆነው ለምንድን ነው?

      1 ‘በእያንዳንዱ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ መጽሔቶችን ለማበርከት የሚያስችሉ አቀራረቦች እያሉ ሌሎች የመግቢያ ሐሳቦችን መዘጋጀት ለምን አስፈለገ?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ምንም እንኳ ብዙዎች እነዚህ የናሙና አቀራረቦች ተስማሚ እንደሆኑ ቢሰማቸውም በግል ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። በአንድ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ውጤታማ የሆነ አቀራረብ በሌላኛው ክልል ተስማሚ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ መጽሔት ስናበረክት የናሙና አቀራረቦችን ምንም ማስተካከያ ሳናደርግባቸው የመጠቀም ግዴታ እንዳለብን ሆኖ ሊሰማን አይገባም። እነዚህን የናሙና አቀራረቦች ለመጠቀም ብንመርጥ እንኳ በራሳችን አባባል ብንናገራቸው ጥሩ ይሆናል።

      2. የምታስተዋውቀውን ርዕስ በመምረጥ ረገድ ግምት ውስጥ ልታስገባቸው የሚገቡት ነገሮች ምንድን ናቸው?

      2 አንድ ርዕስ ምረጥ:- መጽሔቱን አንብበህ ከጨረስህ በኋላ ለአገልግሎት ክልልህ አመቺ የሆነውን እንዲሁም አንተን ያስደሰተህን ርዕስ ምረጥ። መጽሔቱን በምታስተዋውቅበት ወቅት እምነትህ እንዲሁም የምታሳየው ሞቅ ያለ ስሜት የቤቱ ባለቤት ጽሑፉን እንዲያነበው ሊገፋፋው ይችላል። ምንም እንኳ ለአገልግሎት ክልሉ ይበልጥ ተስማሚ የሆነውን ርዕስ መምረጥ ቢኖርብህም በመጽሔቶቹ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ርዕሶችም በደንብ ልታውቃቸው ይገባል። እንዲህ ማድረግህ ግለሰቡን የሚያሳስበው ነገር አንተ ከተዘጋጀህበት ነጥብ የተለየ በሚሆንበት ጊዜ መግቢያህን እንደሁኔታው እንድታስተካክል ይረዳሃል።

      3. ጥሩ ውጤት ለማግኘት ምን ዓይነት መግቢያዎችን ትጠቀማለህ?

      3 ጥያቄ ጠይቅ:- ከዚያም መግቢያህ ላይ የምትናገረውን ነገር በደንብ ተዘጋጅ። የምትጠቀምበት መግቢያ በጣም ወሳኝ ነው። የቤቱ ባለቤት ስለመረጥከው ርዕስ የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርበት ለማድረግ አመራማሪ ጥያቄ በመጠየቅ መጀመርህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ የአመለካከት ጥያቄዎች መጠቀምም ይበልጥ ውጤታማ ነው። የቤቱን ባለቤት የሚያሳፍር ወይም ለጭቅጭቅ የሚጋብዝ ጥያቄ ከመጠየቅ ተቆጠብ።

      4. ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ለቤቱ ባለቤት ጥቅስ ማንበባችን ምን ጥቅሞች አሉት?

      4 አንድ ጥቅስ አንብብ:- በመጨረሻም የቤቱ ባለቤት ሁኔታ የሚፈቅድ ከሆነ የምታነበውን ጥቅስ አስቀድመህ ምረጥ፤ ምናልባትም ጥቅሱ ልታስተዋውቀው ካሰብከው ርዕስ ውስጥ የተወሰደ ሊሆን ይችላል። ጥቅስ ማንበባችን የቤቱ ባለቤት የምንሰብከው መልእክት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን እንዲያስተውል ይረዳዋል። (1 ተሰ. 2:13) ምናልባት መጽሔቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ የተነበበው ጥቅስ በራሱ ምሥክርነት ይሰጠዋል። አንዳንዶች ጥያቄ ከመጠየቃቸው በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንበብ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ። ምናልባትም ጥቅሱን እንዲህ በማለት ማስተዋወቅ ትችላለህ:- “በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ስለተጠቀሰው ሐሳብ ምን እንደሚሰማዎት ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል?” ከዚያም ያነበብከው ጥቅስ ልታበረክተው ካሰብከው መጽሔት ጋር እንዴት እንደሚያያዝ አሳየው፤ መጽሔቱን ከማበርከትህ በፊት ግን ግለሰቡ ያለውን ፍላጎት ይበልጥ ለመቀስቀስ አጭር ሐሳብ ተናገር።

      5. መጽሔቶችን ለማበርከት የሚያገለግሉ የመግቢያ ሐሳቦችን ስንዘጋጅ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሐሳቦች የትኞቹ ናቸው?

      5 መጽሔቶችን ስናበረክት ምን ማለት እንዳለብን የሚገልጽ ድርቅ ያለ ደንብ የለም። አብዛኛውን ጊዜ አቀራረብን ቀላል እንዲሁም አጭር ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው። ለአንተ የሚስማማህን እንዲሁም ጥሩ ውጤት የሚያስገኝልህን መግቢያ መጠቀም ትችላለህ። መጽሔቶቹ ባላቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ላይ አተኩር፤ እንዲሁም ስትናገር ግለት ይኑርህ። ጥሩ ዝግጅት ካደረግህ ‘ለዘላለም ሕይወት ለተዘጋጁ’ ሰዎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በማበርከት ረገድ ይበልጥ የተዋጣልህ ትሆናለህ።—ሥራ 13:48

  • መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?
    የመንግሥት አገልግሎት—2006 | ኅዳር
    • መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?

      መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 1

      “የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በሽታን ለማስወገድና ዕድሜያችንን ለማራዘም ጥረት እያደረጉ ነው። ይዋል ይደር እንጂ ለዘላለም መኖር የሚቻልበት ጊዜ እንደሚመጣ አስበው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ረጅም ዕድሜ መኖር የምንመኘው ለምን እንደሆነ እስቲ ይመልከቱ። [መክብብ 3:11ን አንብብ።] አምላክ ሲፈጥረን ለዘላለም የመኖር ፍላጎትን የሰጠን ለምን እንደሆነ ይህ መጽሔት ያብራራል።”

      ንቁ! ጥቅምት 2006

      “አብዛኞቻችን የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት አጥተናል። ታዲያ ከሞቱ በኋላም ቢሆን እነርሱን ለመርዳት ማድረግ የምንችለው ነገር እንዳለ ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ይህ ርዕስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ይዟል። ከዚህም በላይ ይህንን የሚያጽናና ተስፋ ያብራራል።” ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ። ከዚያም በገጽ 10 ላይ ያለውን ርዕስ አስተዋውቀው።

      መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 15

      “አንዳንድ ሰዎች፣ አምላክ የሚኖረው በሰማይ ስለሆነ እርሱን ማወቅ አይቻልም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። እርስዎስ እንደዚህ ይሰማዎታል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው። ከዚያም ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] ይህ መጽሔት አምላክን ማወቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።”

      ንቁ! ኅዳር 2006

      “አፍቃሪ፣ ፍትሐዊና ኃያል የሆነ አምላክ ካለ ብዙ መከራና ሥቃይ የኖረው ለምን እንደሆነ ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ይህ ጥቅስ የመከራ መንስኤ የሆነውን አካል በተመለከተ ምን እንደሚል ይመልከቱ። [1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።] ይህ መጽሔት አምላክ የሰው ልጆችን ሥቃይ ለማስወገድ ያደረገውን ዝግጅት ከመጽሐፍ ቅዱስ ያብራራል።”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ