የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lv ምዕ. 4 ገጽ 36-49
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
  • ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
  • በቤተሰብ ክልል ውስጥ
  • በጉባኤ ውስጥ
  • ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • በእናንተ ላይ ሥልጣን የተሰጣቸውን አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • አንድ ክርስቲያን ለባለ ሥልጣን ያለው አመለካከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የይሖዋን ሥልጣን ተቀበሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
lv ምዕ. 4 ገጽ 36-49
አንድ አባት ቤተሰቡን ሲያስተምር

ምዕራፍ 4

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

“ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ።”​—1 ጴጥሮስ 2:17

1, 2. (ሀ) ከሥልጣን ጋር በተያያዘ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥመናል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

አንድ⁠ ትንሽ ልጅ ማድረግ የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ሲጠየቅ እንዴት እንደሚሆን አይተህ ታውቃለህ? ላድርግ አላድርግ በሚል ስሜት ከራሱ ጋር ሙግት እንደገጠመ በፊቱ ላይ በግልጽ ታነብ ይሆናል። ወላጁ ምን አድርግ እንዳለው ሰምቷል፣ ሥልጣኑን ማክበር እንዳለበትም ያውቃል። በዚህ ጊዜ ግን ጨርሶ መታዘዝ አልፈለገም። ይህ ልጅ ያጋጠመው ሁኔታ ሁላችንንም የሚያጋጥመንን አንድ ሐቅ ያስታውሰናል።

2 ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በአንተ ላይ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ማክበር አስቸጋሪ የሚሆንብህ ጊዜ አለ? እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያጋጥምህ አንተ ብቻ አይደለህም። የምንኖረው ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት በጠፋበት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በእኛ ላይ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ማክበር እንደሚገባን ይናገራል። (ምሳሌ 24:21) እንዲያውም ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን እንዲህ ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተገቢ ነው። ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሚሆንብን ለምንድን ነው? ይሖዋ ለሥልጣን አክብሮት እንድናሳይ የሚፈልግብን ለምንድን ነው? ታዛዥ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? በመጨረሻም ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

3, 4. ኃጢአትና አለፍጽምና የጀመረው እንዴት ነው? የወረስነው ኃጢአት ለሥልጣን አክብሮት ማሳየትን አስቸጋሪ የሚያደርግብን እንዴት ነው?

3 ሥልጣን ላላቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት አስቸጋሪ እንዲሆንብን የሚያደርጉትን ሁለት ምክንያቶች በአጭሩ እንመልከት። አንደኛው እኛ ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሥልጣን ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ ፍጹማን አለመሆናቸው ነው። ከብዙ ዘመናት በፊት አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ በአምላክ ሥልጣን ላይ ባመጹበት ጊዜ የሰው ልጆች ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ። ስለዚህ ኃጢአት የጀመረው በዓመጽ ነው። በዚህም ምክንያት አሁንም ድረስ በሥልጣን ላይ የማመጽ ዝንባሌ በውስጣችን አለ።​—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:1-7፤ መዝሙር 51:5፤ ሮም 5:12

4 በወረስነው ኃጢአት ምክንያት አብዛኞቻችን የኩራትና የትዕቢት ባሕርይ ማሳየት ይቀናናል፤ በተቃራኒው ትሕትናን ማዳበር ብዙ ጥረት ስለሚጠይቅ እምብዛም የሚታይብን ባሕርይ አይደለም። ለበርካታ ዓመታት አምላክን በታማኝነት ካገለገልን በኋላም እንኳ የእልኸኝነትና የትዕቢት መንፈስ ሊጠናወተን ይችላል። ለምሳሌ፣ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በታማኝነት ብዙ መከራዎችን ያሳለፈውን ቆሬን ተመልከት። ተጨማሪ ሥልጣን ለማግኘት በመቋመጡ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ትሑት በነበረው በሙሴ ላይ ዓመጽ አነሳሳ። (ዘኍልቍ 12:3፤ 16:1-3) በተጨማሪም በትዕቢት ተነሳስቶ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ የገባውንና ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ቅዱስ ሥራ ያከናወነውን ንጉሥ ዖዝያንን አስብ። (2 ዜና መዋዕል 26:16-21) እነዚህ ሰዎች ለሠሩት ዓመጽ ከባድ ቅጣት ተቀብለዋል። የእነሱ መጥፎ ምሳሌ ለሁላችንም ጠቃሚ ማሳሰቢያ ይሆነናል። ለሥልጣን አክብሮት እንዳናሳይ እንቅፋት የሚሆንብንን የትዕቢት ባሕርይ መዋጋት አለብን።

5. ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሥልጣናቸውን አለአግባብ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

5 በሌላ በኩል ደግሞ በሥልጣን ላይ ያሉት ራሳቸው ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ሰዎች ለሥልጣን አክብሮት እንዲያጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ብዙዎች ጨካኞች፣ ግፈኞችና አምባገነኖች ነበሩ። እንዲያውም የሰው ልጅ ታሪክ በአብዛኛው ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀም ባስከተለው ግፍ የተሞላ ነው። (መክብብ 8:9) ለምሳሌ ያህል፣ ሳኦል ይሖዋ ንጉሥ እንዲሆን በመረጠው ጊዜ ትሑትና ጥሩ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በትዕቢትና በቅናት ተሸንፎ ታማኙን ዳዊትን ማሳደድ ጀመረ። (1 ሳሙኤል 9:20, 21፤ 10:20-22፤ 18:7-11) ውሎ አድሮ ዳዊት በእስራኤል ላይ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ የተሻለ ንጉሥ ሆነ፤ ይሁን እንጂ እሱም ቢሆን የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ሰርቆ ንጹሕ ሰው የነበረውን ባሏን በጦር ግንባር እንዲገደል በማድረግ ሥልጣኑን አለአግባብ ተጠቅሟል። (2 ሳሙኤል 11:1-17) አዎ፣ አለፍጽምና ሰዎች ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙበት ያደርጋቸዋል። ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ይሖዋን የማያከብሩ በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ ሁኔታው የከፋ ይሆናል። አንድ የብሪታንያ ታዋቂ የፖለቲካ ሰው አንዳንድ የካቶሊክ ሊቃነ ጳጳሳት በሰዎች ላይ በስፋት ስላደረሱት ሥቃይ ከገለጹ በኋላ “ሥልጣን ያባልጋል፣ ገደብ የሌለው ሥልጣን ደግሞ የባሰ ያባልጋል” ብለዋል። በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ሰዎች ያስመዘገቡትን ይህን ታሪክ በአእምሯችን ይዘን ‘ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ እንመርምር።

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል? ለምንስ? (ለ) መገዛት ምን ዓይነት ዝንባሌ ማሳየትን ይጨምራል?

6 ለሥልጣን አክብሮት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ፣ ለሰዎች፣ ሌላው ቀርቶ ለራሳችን ያለን ፍቅር ነው። ይሖዋን ከምንም በላይ ስለምንወደው ልቡን ደስ ማሰኘት እንፈልጋለን። (ምሳሌ 27:11፤ ማርቆስ 12:29, 30) በኤደን ዓመጽ ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ሉዓላዊነቱ ማለትም ጽንፈ ዓለሙን የመግዛት መብቱ በምድር ላይ ጥያቄ የተነሳበት ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ የሰው ልጆች ከሰይጣን ጎን በመቆም የይሖዋን አገዛዝ እንደተቃወሙ እናውቃለን። እኛ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አቋም በመያዛችን በጣም ደስተኞች ነን። በራእይ 4:11 ላይ የሚገኙትን ግሩም ቃላት በምናነብበት ጊዜ ልባችን በጥልቅ ይነካል። እኛ ጽንፈ ዓለሙን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ መሆኑን በግልጽ ተገንዝበናል! በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የይሖዋን አመራር በመቀበል እሱ ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን እንደምንደግፍ እናሳያለን።

7 እንዲህ ያለው አክብሮት ከታዛዥነት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ይሖዋን ስለምንወደው ሳናንገራግር እንታዘዘዋለን። ይሁን እንጂ መታዘዝ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንብን ጊዜ መኖሩ አይቀርም። እንዲህ ባለ ጊዜ፣ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ትንሽ ልጅ መገዛትን መማር ያስፈልገናል። ኢየሱስ መታዘዝ በጣም አስቸጋሪ በሚመስልበት ጊዜም እንኳ ለአባቱ ፈቃድ እንደተገዛ እናውቃለን። ለአባቱ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ተናግሯል።​—ሉቃስ 22:42

8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ለይሖዋ ሥልጣን መገዛት በአብዛኛው ምንን ይጨምራል? በዚህ ረገድ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው የሚያሳየው የትኛው ታሪክ ነው? (ለ) ምክርን እንድንሰማና ተግሣጽን እንድንቀበል ምን ሊረዳን ይችላል? (“ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

8 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በየግላችን አያነጋግረንም፤ ከዚህ ይልቅ ቃሉንና በምድር ላይ ያሉ ሰብዓዊ ተወካዮቹን ይጠቀማል። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ ለይሖዋ ሥልጣን የምንገዛ መሆናችንን የምናሳየው እሱ ሥልጣን የሰጣቸውን ወይም ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የፈቀደላቸውን ሰዎች በማክበር ነው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ብናምጽ፣ ለምሳሌ የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርና እርማት ለመቀበል እምቢተኛ ብንሆን አምላካችንን እናሳዝናለን። እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ባጉረመረሙና ባመጹ ጊዜ ይሖዋ በእሱ ላይ እንዳመጹ አድርጎ ቆጥሮት ነበር።​—ዘኍልቍ 14:26, 27

9. ለሌሎች ሰዎች ያለን ፍቅር በሥልጣን ላይ ላሉት አክብሮት እንድናሳይ የሚገፋፋን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

9 በተጨማሪም ለሥልጣን አክብሮት የምናሳየው ለሰዎች ፍቅር ስላለን ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ራስህን በአንድ ሠራዊት ውስጥ እንዳለ ወታደር አድርገህ አስብ። የዚህ ሠራዊት ድል ማድረግና ሕልውና የተመካው እያንዳንዱ ወታደር የበላዮቹን በመታዘዙ፣ በማክበሩና ከእነሱ ጋር በመተባበሩ ላይ ነው። አንተ ለበላዮችህ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባትሆን የመላው ሠራዊት ደህንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሚያደራጁት ወታደራዊ ሠራዊት በዓለም ላይ ለከፍተኛ ጥፋት መንስኤ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሖዋ ግን በጎ ነገር ብቻ የሚያደርግ ሠራዊት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ አምላክን “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” በማለት ይጠራዋል። (1 ሳሙኤል 1:3 NW) ይሖዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃያል መንፈሳዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ነው። አንዳንድ ጊዜ ምድራዊ አገልጋዮቹንም ከሠራዊት ጋር ያመሳስላቸዋል። (መዝሙር 68:11፤ ሕዝቅኤል 37:1-10) ይሖዋ ሥልጣን በሰጣቸው ሰዎች ላይ ብናምጽ አብረውን የተሰለፉትን መንፈሳዊ ወታደሮች ደህንነት አደጋ ላይ አንጥልም? አንድ ክርስቲያን በተሾሙ ሽማግሌዎች ላይ ሲያምጽ ሌሎች የጉባኤው አባሎችም ይሠቃያሉ። (1 ቆሮንቶስ 12:14, 25, 26) አንድ ልጅ ዓመጸኛ ሲሆን መላው ቤተሰብ ይሠቃያል። ስለዚህ ሥልጣን ለተሰጣቸው አክብሮት በማሳየትና ከእነሱ ጋር በመተባበር ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።

10, 11. ለራሳችን ጥቅም የምናስብ መሆናችን ሥልጣን ላላቸው ሰዎች እንድንታዘዝ የሚገፋፋን እንዴት ነው?

10 ከዚህም በላይ ለሥልጣን አክብሮት የምናሳየው ለራሳችን ጥቅም ስንል ነው። ይሖዋ ለሥልጣን አክብሮት እንድናሳይ ሲነግረን መታዘዛችን የሚያስገኝልንን ጥቅም ጭምር ይገልጽልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች ዕድሜያቸው እንዲረዝምና ጥሩ ሕይወት እንዲኖሩ ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 5:16፤ ኤፌሶን 6:2, 3) የጉባኤ ሽማግሌዎችን ባናከብር መንፈሳዊ ጉዳት እንደሚደርስብን በመግለጽ ሥልጣናቸውን እንድናከብር ነግሮናል። (ዕብራውያን 13:7, 17) ከዚህም በላይ ለራሳችን ደህንነት ስንል የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን እንድንታዘዝ ነግሮናል።​—ሮም 13:4

11 ይሖዋ ታዛዥ እንድንሆን የሚፈልግበትን ምክንያት ማወቃችን ለሥልጣን አክብሮት እንድናሳይ ይረዳናል ቢባል አትስማማም? አሁን በሦስት ዋና ዋና የሕይወታችን ዘርፎች ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

በቤተሰብ ክልል ውስጥ

12. ይሖዋ በቤተሰብ ውስጥ ለባል ወይም ለአባት ምን የሥራ ድርሻ ሰጥቶታል? ይህን ኃላፊነቱን እንዴት መወጣት ይኖርበታል?

12 የቤተሰብን ዝግጅት የመሠረተው ይሖዋ ራሱ ነው። የሥርዓት አምላክ የሆነው ይሖዋ ቤተሰብን ስኬታማ ሊሆን በሚችልበት መንገድ አደራጅቶታል። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ለባል ወይም ለአባት የቤተሰቡ ራስ እንዲሆን ሥልጣን ሰጥቶታል። ባል፣ ኢየሱስ በጉባኤው ላይ ያለውን የራስነት ሥልጣን እንዴት እንደሚሠራበት በመኮረጅ፣ ራሱ ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ አክብሮት እንዳለው ያሳያል። (ኤፌሶን 5:23) በመሆኑም ባል የተጣለበትን ኃላፊነት ከራሱ ላይ ለማውረድ ከመሞከር ይልቅ በቆራጥነት ሊወጣው ይገባል፤ እንዲሁም አምባገነን ወይም ጨቋኝ ሳይሆን አፍቃሪ፣ ምክንያታዊና ደግ መሆን ይኖርበታል። የተሰጠው ሥልጣን አንጻራዊ እንደሆነ ማለትም ከእሱ ሥልጣን በላይ የይሖዋ ሥልጣን እንዳለ ይገነዘባል።

አንድ ክርስቲያን አባት ክርስቶስ የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበትን መንገድ ይኮርጃል

13. አንዲት ሚስት ወይም እናት ኃላፊነቷን ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ልትወጣ የምትችለው እንዴት ነው?

13 የሚስት ወይም የእናት የሥራ ድርሻ ደግሞ የባሏ ረዳት ወይም ማሟያ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የእናትህንም ትምህርት አትተው” ስለሚል እሷም በቤተሰቡ ውስጥ የተሰጣት ሥልጣን አለ። (ምሳሌ 1:8) እርግጥ ነው፣ የእሷ ሥልጣን ከባሏ ሥልጣን በታች ነው። አንዲት ክርስቲያን ሚስት፣ ባሏ የራስነት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በመርዳት ሥልጣኑን እንደምታከብር ታሳያለች። አታቃልለውም፣ በተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅማ እንደፈለገች ልትጠመዝዘው አትሞክርም ወይም ሥልጣኑን አትነጥቅም። ከዚህ ይልቅ ትደግፈዋለች፤ እንዲሁም ትተባበረዋለች። እሷ ያልተስማማችበትን ውሳኔ በሚወስንበት ጊዜ ሐሳቧን በአክብሮት ልትገልጽለት ብትችልም ትገዛለታለች። ባሏ የማያምን ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሟት ይሆናል፤ ሆኖም በአኗኗሯ ተገዢ መሆኗ ባሏ ይሖዋን ለማወቅ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።​—1 ጴጥሮስ 3:1

አባት፣ ቤቱን በጭቃ ያበላሸ ልጁን በፍቅር ሲያርም

14. ልጆች ወላጆቻቸውንና ይሖዋን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ልጆች አባትና እናታቸውን ሲታዘዙ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛሉ። ወላጆቻቸውንም ያስደስታሉ እንዲሁም ያስከብራሉ። (ምሳሌ 10:1) ነጠላ ወላጅ ያላቸው ልጆችም ወላጃቸው የእነሱ ድጋፍና ትብብር በይበልጥ እንደሚያስፈልገው በመገንዘብ ይህንኑ የታዛዥነት መንፈስ ያሳያሉ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አምላክ የሰጠውን የሥራ ድርሻ በአግባቡ የሚወጣ ከሆነ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላምና ደስታ ይሰፍናል። ይህ ደግሞ የሁሉም ቤተሰብ መሥራች የሆነውን ይሖዋ አምላክን ያስከብረዋል።​—ኤፌሶን 3:14, 15

በጉባኤ ውስጥ

15. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ የይሖዋን ሥልጣን እንደምናከብር ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጡን ታዛዥ እንድንሆን የሚረዱን የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? (“ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ይሖዋ ልጁን በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ገዥ አድርጎ ሾሞታል። (ቆላስይስ 1:13) ኢየሱስ ደግሞ በምድር ላይ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦችን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያሟላ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። (ማቴዎስ 24:45-47) የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የታማኝና ልባም ባሪያ ወኪል ሆኖ ያገለግላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያን ጉባኤዎች ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በዘመናችንም ሽማግሌዎች ከበላይ አካሉ መመሪያና ምክር ያገኛሉ። ይህን መመሪያና ምክር የሚያገኙት በቀጥታ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በመሰሉ የታማኝና ልባም ባሪያ ተወካዮች አማካኝነት ነው። ለጉባኤ ሽማግሌዎች ሥልጣን ስንታዘዝ ይሖዋን መታዘዛችን ነው።​—ዕብራውያን 13:17

16. ሽማግሌዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

16 ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ፍጹም አይደሉም። ልክ እንደ እኛ እነሱም የየራሳቸው ድክመት አላቸው። ሆኖም ሽማግሌዎች ጉባኤው በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለመርዳት ‘እንደ ስጦታ የተሰጡ ወንዶች’ ናቸው። (ኤፌሶን 4:8) ሽማግሌዎች የሚሾሙት በመንፈስ ቅዱስ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) እንዴት? እነዚህ ወንዶች ከመሾማቸው በፊት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ውስጥ የሚገኙትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7, 12፤ ቲቶ 1:5-9) ከዚህም በላይ አንድ ወንድም እነዚህን ብቃቶች ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚመዝኑት ሽማግሌዎች የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራቸው አጥብቀው ይጸልያሉ።

17. ሴቶች በጉባኤ ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን መሸፈን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

17 በጉባኤ ውስጥ፣ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባን እንደመምራት ያሉ በአብዛኛው በሽማግሌዎች ወይም በጉባኤ አገልጋዮች የሚሠሩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ የተሾሙ ወንዶች የሚታጡበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ሌሎች የተጠመቁ ወንድሞች እነዚህን ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። የተጠመቁ ወንድሞች ካልተገኙ ደግሞ ለቦታው ብቁ የሆኑ ክርስቲያን እህቶች ሊሠሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንዲት ሴት የተጠመቀ ወንድ ሊያከናውን ይገባ የነበረውን ተግባር በምታከናውንበት ጊዜ ሁሉ ራሷን ትሸፍናለች።a (1 ቆሮንቶስ 11:3-10) ይህ መመሪያ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳዩበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።

ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት

18, 19. (ሀ) በሮም 13:1-7 ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ትገልጻቸዋለህ? (ለ) ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት አክብሮት የምናሳየው እንዴት ነው?

18 እውነተኛ ክርስቲያኖች በ⁠ሮም 13:1-7 ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ ያከብራሉ። ይህን ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ እዚያ ላይ የተጠቀሱት ‘የበላይ ባለ ሥልጣናት’ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት መሆናቸውን ትገነዘባለህ። ይሖዋ፣ እነዚህ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት እንዲኖሩ እስከፈቀደ ጊዜ ድረስ በተወሰነ ደረጃ ሥርዓት በማስፈንና አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን በመስጠት ጠቃሚ ተግባር ያከናውናሉ። ሕግ አክባሪዎች በመሆን ለእነዚህ ባለ ሥልጣናት አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። የተጣለብንን ግብር እንከፍላለን፤ መንግሥት የሚፈልግብንን ማንኛውንም ቅጽና ሰነድ በተገቢ ሁኔታ እንሞላለን፤ እንዲሁም እኛን፣ ቤተሰባችንን፣ ሥራችንን ወይም ንብረታችንን የሚመለከቱ ማንኛውም ዓይነት ሕጎችን እናከብራለን። ይሁን እንጂ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የአምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ቢጠይቁን አንገዛላቸውም። ከዚህ ይልቅ የጥንቶቹ ሐዋርያት እንዳሉት “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት መልስ እንሰጣለን።​—የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29፤ “ማክበር የሚኖርብኝ የማንን ሥልጣን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ማክበር የሚኖርብኝ የማንን ሥልጣን ነው?

መሠረታዊ ሥርዓት:- “ይሖዋ ዳኛችን ነው፤ ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፤ ይሖዋ ንጉሣችን ነው።” —ኢሳይያስ 33:22 NW

ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:-

  • ይሖዋ ያወጣቸውን መመሪያዎች እንድጥስ ብጠየቅ ምን አደርጋለሁ?​—ማቴዎስ 22:37-39፤ 26:52፤ ዮሐንስ 18:36

  • የይሖዋን ትእዛዛት መፈጸሜን እንዳቆም ብታዘዝ ምን አደርጋለሁ?​—የሐዋርያት ሥራ 5:27-29፤ ዕብራውያን 10:24, 25

  • ሥልጣን ላላቸው ሰዎች የመታዘዝ ፍላጎት እንዲኖረኝ ምን ሊረዳኝ ይችላል?​—ሮም 13:1-4፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 6:1-3

19 በተጨማሪም በጠባያችን ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር በቀጥታ የሚያገናኘን ጉዳይ ይገጥመን ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳና እንደ ገዥው ፊስጦስ ባሉ ባለ ሥልጣናት ፊት የቀረበበት ጊዜ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከባድ ጉድለቶች የነበሩባቸው ቢሆኑም ጳውሎስ አክብሮት በተሞላበት መንገድ አነጋግሯቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 26:2, 25) እኛም የምናነጋግረው ሰው ከፍተኛ ባለ ሥልጣንም ይሁን ተራ ፖሊስ የጳውሎስን አርዓያ እንከተላለን። ወጣት ክርስቲያኖችም ለመምህሮቻቸው እንዲሁም ለትምህርት ቤት ባለ ሥልጣናትና ሠራተኞች ተመሳሳይ አክብሮት ለማሳየት ይጥራሉ። እንዲህ ያለ አክብሮት የምናሳየው እምነታችንን ለሚያከብሩልን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ለሚቃወሙ ጭምር ነው። እምነታችንን የማይጋሩ ሰዎች በአጠቃላይ፣ ሰው አክባሪዎች መሆናችንን ሊመለከቱ ይገባል።—ሮም 12:17, 18፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

20, 21. ለሥልጣን ተገቢውን አክብሮት ማሳየት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

20 ለሌሎች አክብሮት ለማሳየት የምናንገራግር አንሁን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ሰዎች ከልብ እንደምናከብራቸው ሲሰማቸው ልባቸው በጥልቅ ይነካል። ሰው አክባሪነት እየጠፋ የመጣ ባሕርይ እንደሆነ አስታውስ። በመሆኑም ለሰው ሁሉ አክብሮት ማሳየት ኢየሱስ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ከምንፈጽምባቸው መንገዶች አንዱ ነው።​—ማቴዎስ 5:16

21 በዚህ በጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ መንፈሳዊ ብርሃን ይሳባሉ። ስለሆነም በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ላለው ሥልጣን እንዲሁም ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት አክብሮት ማሳየታችን አንዳንዶችን ሊማርካቸውና ከእኛ ጋር በብርሃን እንዲመላለሱ ሊያነሳሳቸው ይችላል። እንዲህ ያለ ውጤት ቢገኝ እንዴት አስደሳች ይሆናል! ይህም ባይሆን እንኳ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለሰዎች አክብሮት ማሳየታችን ይሖዋ አምላክን ያስደስተዋል፣ ከፍቅሩ ሳንወጣ እንድንኖርም ይረዳናል። ከዚህ የበለጠ ምን በረከት ሊኖር ይችላል!

a “ክርስቲያን ሴቶች ራሳቸውን መሸፈን የሚኖርባቸው መቼ ነው? ለምንስ?” የሚለው ተጨማሪ መረጃ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆንባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ይመረምራል።

“ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል”

ዛሬ ያለው ዓለም በሰይጣን መንፈስ ይኸውም በዓመጸኝነትና በጠበኝነት መንፈስ የተሞላ ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የአየሩ ሥልጣን ገዥ” ብሎ የሚጠራው ሲሆን ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ስላለው’ የሰይጣን መንፈስም ይገልጻል። (ኤፌሶን 2:2) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በማንኛውም ዓይነት ሥልጣን ሥር መሆን አይፈልጉም። እንዲህ ያለው በሌሎች ሥልጣን ሥር ለመሆን ያለመፈለግ ዝንባሌ ወደ አንዳንድ ክርስቲያኖችም መጋባቱ የሚያሳዝን ነው። ለምሳሌ፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የብልግና ወይም የጭካኔ ድርጊት የሚያሳዩ መዝናኛዎች ስለሚያስከትሉት አደጋ በደግነት ምክር ሊሰጥ ይችላል። አንዳንዶች ግን ምክሩን ለመቀበል ሊያንገራግሩ ወይም እስከ መቃወም ሊደርሱ ይችላሉ። ሁላችንም “ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ” የሚለውን የ⁠ምሳሌ 19:20 ምክር ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገናል።

በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል? ሰዎች ምክር ወይም ተግሣጽ እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸውን ሦስት የተለመዱ ምክንያቶች ተመልከት። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ምክንያቶች ምን እንደሚል ልብ በል።

  • “ምክሩ ተገቢ አይመስለኝም።” የተሰጠው ምክር እኛ ላለንበት ሁኔታ እንደማይሠራ ወይም ምክሩን የሰጠው ሰው ያልተረዳው ነገር እንዳለ ይሰማን ይሆናል። በዚህ ጊዜ የሚቀናን ምክሩን ማቃለል ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 12:5) ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን እንደመሆናችን መጠን መስተካከል ያለበት ምክር የሰጠን ግለሰብ አመለካከት ሳይሆን የእኛ የራሳችን አመለካከት ሊሆን አይችልም? (ምሳሌ 19:3) ሽማግሌው ምክሩን እንዲሰጥ ያነሳሳው ቢያንስ አንድ ምክንያት መኖር አለበት። እንግዲያው ማተኮር የሚኖርብን በዚያ ላይ ነው። የአምላክ ቃል “ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና” ሲል ይመክረናል።—ምሳሌ 4:13

  • “ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ደስ አላለኝም።” እርግጥ ነው፣ የአምላክ ቃል ምክር እንዴት በጥሩ መንገድ መሰጠት እንዳለበት የሚናገር ግሩም ሐሳብ ይዟል። (ገላትያ 6:1) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” የሚል ሐሳብም ይዟል። (ሮም 3:23) ፍጹም ትክክለኛ የሆነ ምክር በጥሩ መንገድ ማግኘት የምንችለው ፍጹም ከሆነ ሰው ብቻ ነው። (ያዕቆብ 3:2) ይሖዋ ምክር የሚሰጠን ፍጹም ባልሆኑ ሰዎች በኩል ነው። በመሆኑም ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት አለማድረጋችን አስተዋይነት ነው። ከዚህ ይልቅ የምክሩን ይዘት ተመልክተህ እንዴት በሥራ ላይ ልታውለው እንደምትችል በጸሎት አስብበት።

  • “እሱ ማነውና ነው እኔን የሚመክረኝ!” ምክር ሰጪው ጉድለቶች ያሉበት መሆኑ ምክሩን ዋጋ ያሳጣዋል የሚል አመለካከት ካለን ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ልብ ማለት ያስፈልገናል። በተጨማሪም በዕድሜያችን፣ ባካበትነው ተሞክሮ ወይም በጉባኤ ውስጥ ባለን ኃላፊነት ምክንያት ምክር እንደማያስፈልገን መስሎ ከታየን አስተሳሰባችንን ማስተካከል ያስፈልገናል። በጥንቷ እስራኤል ንጉሡ ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ይሁን እንጂ ነቢያት፣ ካህናት፣ እንዲሁም ተገዥዎቹ ከሆኑት መካከል አንዳንድ ሰዎች የሚሰጡትን ምክር መስማት ነበረበት። (2 ሳሙኤል 12:1-13፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16-20) ዛሬም የይሖዋ ድርጅት፣ ምክር እንዲሰጡ በኃላፊነት የሾመው ፍጽምና የሚጎድላቸውን ሰዎች ነው። ጎልማሳ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚሰጣቸውን ምክር በደስታ ተቀብለው ሥራ ላይ ያውላሉ። ከሌሎች የበለጠ ኃላፊነት ወይም ተሞክሮ ካለን፣ ምክር በመቀበልና ሥራ ላይ በማዋል ረገድ ምክንያታዊና ትሑት በመሆን ለሌሎች ጥሩ አርዓያ ሆነን መገኘት እንዳለብን ሊሰማን ይገባል።​—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3፤ ቲቶ 3:2

ከመካከላችን ምክር የማያስፈልገው ሰው የለም። ስለዚህ የሚሰጠንን ምክር ሳናንገራግር ለመቀበልና በታዛዥነት ሥራ ላይ ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲሁም ይሖዋን ሕይወት አድን ለሆነው ለዚህ ስጦታው ከልብ እናመስግነው። በእርግጥም ምክር ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት መንገድ ነው፤ የእኛ ፍላጎት ደግሞ ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር ነው።​—ዕብራውያን 12:6-11

“ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ”

በአንድ ወቅት በጥንቷ እስራኤል ሕዝቡን ማደራጀት አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ነበር። አደገኛ በሆነ ምድረ በዳ ይጓዝ የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሙሴ ብቻውን ሊመራ አልቻለም። ታዲያ ምን አደረገ? “ከእስራኤል መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠና፤ የሕዝብ መሪዎች፣ በሺዎች፣ በመቶዎች፣ በአምሳዎች በዐሥሮች ላይም አለቆች አደረጋቸው።”​—ዘፀአት 18:25

በተመሳሳይም ዛሬ ያለውን የክርስቲያን ጉባኤ ማደራጀት አስፈላጊ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አንድ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን የበላይ ተመልካች እንዲኖረው፣ እንዲሁም አንድ ጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲኖሩት፣ የተለያዩ ጉባኤዎች ደግሞ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲኖራቸው ተደርጓል፤ በተጨማሪም የተለያዩ ወረዳዎች የአውራጃ የበላይ ተመልካች ያላቸው ሲሆን አንድ አገር ደግሞ በአገር ኮሚቴ ወይም በቅርንጫፍ ኮሚቴ ይመራል። የአምላክ ሕዝብ በዚህ መንገድ መደራጀቱ፣ እረኛ ሆኖ የሚያገለግል እያንዳንዱ ወንድ በሥሩ ያሉትን የይሖዋ በጎች በቅርብ ለመከታተል ያስችለዋል። እነዚህ እረኞች በይሖዋና በክርስቶስ ዘንድ ተጠያቂዎች ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 20:28

ጉባኤዎች በዚህ መንገድ የተደራጁ መሆናቸው እያንዳንዳችን ታዛዦችና ተገዥዎች እንድንሆን ይጠይቅብናል። በዘመኑ አመራር ይሰጡ ለነበሩት ወንድሞች አክብሮት እንዳላሳየው እንደ ዲዮጥራጢስ መሆን አንፈልግም። (3 ዮሐንስ 9, 10) ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የሰጠውን ምክር በተግባር ማዋል እንፈልጋለን:- “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ፤ ምክንያቱም እነሱ ስሌት እንደሚያቀርቡ ሰዎች በመሆን ነፍሳችሁን ተግተው ይጠብቃሉ፤ ይህም ሥራቸውን በደስታ እንዲያከናውኑ ነው፤ አለበለዚያ ሥራቸውን በሐዘን ያከናውናሉ፤ ይህ ደግሞ እናንተን ይጎዳችኋል።” (ዕብራውያን 13:17) አንዳንዶች አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን የሚታዘዙት በሚሰጧቸው መመሪያዎች ከተስማሙ ነው። ካልተስማሙ ወይም ምክንያቱ ካልታያቸው ግን ለመታዘዝ ፈቃደኞች አይሆኑም። ይሁን እንጂ መገዛት ሲባል መታዘዝ በማንፈልግበት ጊዜም መታዘዝን እንደሚጨምር መዘንጋት የለብህም። ስለዚህ ሁላችንም ‘ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጡኝ ወንድሞች ታዛዥና ተገዥ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

እርግጥ ነው፣ የአምላክ ቃል በጉባኤ ውስጥ ነገሮች እንዴት መከናወን እንዳለባቸው የሚገልጽ ዝርዝር ደንብና መመሪያ አይሰጥም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:40) የበላይ አካሉ ይህን መመሪያ በመታዘዝ ጉባኤዎች ሰላማዊና ሥርዓታማ በሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችሏቸውን የአሠራር ሂደቶችና መመሪያዎች ያወጣል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የተጣለባቸው ክርስቲያን ወንዶች እነዚህን መመሪያዎች ያለማንገራገር ሥራ ላይ በማዋል በታዛዥነት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በተጨማሪም ‘ምክንያታዊና’ የበላይ ተመልካቾቻቸው የሆኑትን ‘ለመታዘዝ የተዘጋጁ’ ናቸው። (ያዕቆብ 3:17) ይህ መሆኑ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን፣ ጉባኤ፣ ወረዳ፣ አውራጃና አገር ደስተኛ የሆነውን አምላክ የሚያስከብሩ፣ አንድነት ያላቸውና ሥርዓታማ የሆኑ አማኞችን ያቀፈ እንዲሆን ያስችለዋል።​—1 ቆሮንቶስ 14:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11

በሌላ በኩል ደግሞ በዕብራውያን 13:17 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ታዛዥ ያለመሆን ዝንባሌ ጎጂ የሆነበትን ምክንያት ይገልጽልናል። እንዲህ ያለው ዝንባሌ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች ሥራቸውን “በሐዘን” እንዲያከናውኑ ያደርጋቸዋል። በመንጋው መካከል ተባባሪና ታዛዥ ያልሆኑ ግለሰቦች መኖራቸው ለአንድ ወንድም እንደ መብት የሚቆጠረው ቅዱስ አገልግሎት ሸክም እንዲሆንበት ሊያደርግ ይችላል። ይህም “እናንተን” ማለትም መላውን ጉባኤ የሚጎዳ ይሆናል። አንድ ሰው ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት ለመገዛት እምቢተኛ መሆኑ የሚያስከትለው ሌላም ጉዳት አለ። ትሑት ሆኖ ካልታዘዘ በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር ያለው ዝምድና ስለሚሻክር መንፈሳዊነቱ ይጎዳል። (መዝሙር 138:6) በመሆኑም ሁላችንም ምንጊዜም ታዛዦችና ተገዥዎች ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ