የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 4/12 ገጽ 7-8
  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
km 4/12 ገጽ 7-8

ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

የተወደዳችሁ የይሖዋ አገልጋዮች፦

በአሁኑ ጊዜ ቁጥራችሁ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ለሆነው ለእናንተ ውድ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ይህን ደብዳቤ ስንጽፍላችሁ እጅግ ደስ ይለናል። ከሌላ የዓለም ክፍል የመጣ አንድ የእምነት ባልንጀራችሁን ስታገኙ ወዲያውኑ ለዚያ ሰው የጠለቀ ፍቅር ያድርባችኋል። (ዮሐ. 13:34, 35) በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ያሳዩትን እምነትና ታማኝነት የሚገልጹትን ማራኪ ታሪኮች በዚህ የዓመት መጽሐፍ ውስጥ ስታነቡም ይህ ዓይነቱ የጠለቀ ፍቅር በውስጣችሁ እንደሚሰማችሁ ምንም ጥርጥር የለውም።

ብዙዎቻችሁ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን በቁም ነገር እንደያዛችሁት ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ትንንሽ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች የልጆቻችሁን ትኩረት ለመሳብና እንዳይሰላቹ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ትጠቀማላችሁ። (ኤፌ. 6:4) ባለትዳሮችም በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት አብረው መንፈሳዊ ነገሮችን ማጥናታቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ እያደረጋቸው ነው። (ኤፌ. 5:28-33) በእርግጥም የአምላክን ቃል በጥልቀት ለማጥናት በሚያስችለው በዚህ ዝግጅት በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ እየተጠቀምን ነው።​—ኢያሱ 1:8, 9

በቅርቡ በተከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባችሁ ሁሉ ከልብ እናዝናለን። እንዲህ ያሉ አደጋዎች በደረሱበት ወቅት እርዳታ በመስጠቱ ሥራ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ የተሳተፉትን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ልናመሰግናቸው እንወዳለን። (ሥራ 11:28-30፤ ገላ. 6:9, 10) በተጨማሪም በየጉባኤው የወንድሞቻችንን ቁሳዊ ችግር አይታችሁ በራሳችሁ ተነሳሽነት እነሱን ለመርዳት የምትጥሩ አላችሁ። በጥንት ጊዜ እንደነበረችው እንደ ዶርቃ ሁሉ እናንተም “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት” ትታወቃላችሁ። (ሥራ 9:36) ይሖዋ የምታደርጉትን ሁሉ እንደሚያይና በዚያው መጠን ወሮታ እንደሚከፍላችሁ እርግጠኞች ሁኑ።​—ማቴ. 6:3, 4

በአንዳንድ አገሮች ደግሞ “ዐመፃን ሕጋዊ” ለማድረግ ሕግን በሚያጣምሙ ሰዎች መብታችሁ እየተረገጠ ነው። (መዝ. 94:20-22) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ስደት እንደሚኖር አስቀድሞ መናገሩን ስለተገነዘባችሁ የሚደርስባችሁን ስደት በጽናት እየተወጣችሁ እንዲሁም ይሖዋን መጠጊያችሁ እያደረጋችሁ ነው። (ዮሐ. 15:19, 20) “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት” ጥረት ማድረጋችሁን ስትቀጥሉ እናንተን ውድ ወንድሞቻችንን ዘወትር በጸሎታችን እንደምናስባችሁ እርግጠኞች ሁኑ።​—1 ጴጥ. 3:13-15

ሰይጣን የሥነ ምግባር ርኩሰትን በረቀቀ ዘዴ ያለ እረፍት እያስፋፋ ባለበት በዚህ ጊዜ የሥነ ምግባር ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ ለመኖር ጥረት የምታደርጉትን ሁሉ ከልብ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። የዓለም የሥነ ምግባር አቋም ከዕለት ወደ ዕለት እያዘቀጠ በሄደ መጠን እናንተ ግን “ከጌታና ከታላቅ ብርታቱ ኃይል” እያገኛችሁ በመሄድ ላይ ናችሁ። (ኤፌ. 6:10) “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ” ለብሳችኋል፤ በመሆኑም “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች” እየተቋቋማችሁ ነው። (ኤፌ. 6:11, 12) ይሖዋ እናንተን በመጥቀስ ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ እንደሚሰጥ እወቁ።​—ምሳሌ 27:11

በ2011 በተከበረው የጌታችን ሞት መታሰቢያ ላይ 19,374,737 ሰዎች መገኘታቸው በጣም አስደስቶናል። ይህን ያህል ብዛት ያለው ተሰብሳቢ እንዲገኝ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር በሚያዝያ ወር ረዳት አቅኚዎች እንድትሆኑ ለቀረበው ጥሪ የሰጣችሁት አስደናቂ ምላሽ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች በአንድነት ለእሱ የሚያቀርቡትን ውዳሴ መስማት ይችላሉ። (ሮም 10:18) በዚያ ወር ረዳት አቅኚዎች ሆናችሁ ያገለገላችሁት 2,657,377 አስፋፊዎችም ሆናችሁ በተቻለ መጠን የአገልግሎት እንቅስቃሴያችሁን ከፍ ለማድረግ ጥረት ያደረጋችሁት ሁሉ ለሥራው ባሳያችሁት ቅንዓትና የፈቃደኝነት መንፈስ እጅግ ተደስተናል።​—መዝ. 110:3፤ ቆላ. 3:23

ባለፈው ዓመት 263,131 አዲስ ወንድሞችና እህቶች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳይተዋል። ለዚህም ይሖዋን እናመሰግነዋለን፤ “የሚሰማም ሁሉ “ና!” ይበል። የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ ለሌሎች በማቅረቡ ሥራ አሁንም ከእኛ ጋር እየተባበራችሁ ያላችሁትን ሁሉ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። (ራእይ 22:17) በተለይ በ2011 ባደረግነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በሰማይ የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ስላሉት የተለያዩ ገጽታዎች ከተማርን በኋላ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በጋለ ስሜት ‘የአምላክ መንግሥት ይምጣ!’ እንላለን። ኢየሱስ “ቶሎ እመጣለሁ” በማለት የሰጠውን ማረጋገጫ በማሰብ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር በሙሉ ልባችን “አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና” እንላለን።​—ራእይ 22:20

ይህን አስደሳች ክንውን በንቃት በምትጠባበቁበት ጊዜ ለይሖዋ ያላችሁን ፍቅር “በተግባርና በእውነት” የምታስመሰክሩትን ውድ ወንድሞችና እህቶች ሁሉ ከልብ እንደምንወዳችሁ ስንገልጽላችሁ ደስ ይለናል!​—1 ዮሐ. 3:18

ወንድሞቻችሁ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ