የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 1

      የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

      በዴንማርክ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር

      ዴንማርክ

      በታይዋን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች

      ታይዋን

      በቬኔዙዌላ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች

      ቬኔዙዌላ

      በሕንድ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች

      ሕንድ

      የምታውቃቸው የይሖዋ ምሥክሮች አሉ? ምናልባትም ጎረቤቶችህ፣ የሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ የሚማሩት ልጆች የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። ወይም ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት አድርገህ ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ነን? ስለ እምነታችን ለሰዎች የምንናገረውስ ለምንድን ነው?

      እንደ ማንኛውም ሰው ነን። የተለያየ አስተዳደግና ማኅበራዊ ሁኔታ ያለን ሰዎች ነን። አንዳንዶቻችን የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት የሌላ ሃይማኖት አባላት ነበርን፤ ሌሎቻችን ደግሞ በአምላክ የማናምን ሰዎች ነበርን። የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት ግን ሁላችንም ጊዜ ወስደን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በጥንቃቄ መርምረናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) ከዚያም የተማርነውን ነገር ስላመንንበት ይሖዋ አምላክን ለማምለክ በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ አደረግን።

      መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ጠቅሞናል። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ እኛም ከተለያዩ ችግሮችና ከራሳችን ድክመት ጋር መታገል ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ በዕለታዊ ሕይወታችን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ስለምንጥር በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ለውጥ መመልከት ችለናል። (መዝሙር 128:1, 2) ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርናቸውን መልካም ነገሮች ለሌሎች የምናካፍልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

      የአምላክን መመሪያዎች አክብረን እንኖራለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ መመሪያዎች በአካልም ሆነ በአስተሳሰብ ጤናማ እንድንሆን የሚረዱን ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች አክብሮት እንዲኖረን እንዲሁም እንደ ሐቀኝነትና ደግነት ያሉትን ጥሩ ባሕርያት እንድናፈራ ያስችሉናል። የአምላክ መመሪያዎች፣ ዜጎች ጤናማና ጠቃሚ የማኅበረሰቡ አባላት እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ አልፎ ተርፎም ቤተሰቦች አንድነትና ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እገዛ ያደርጋሉ። “አምላክ እንደማያዳላ” ስለምናምን በዘርና በፖለቲካ ያልተከፋፈለና ዓለም አቀፋዊ የሆነ መንፈሳዊ የወንድማማች ማኅበር አለን። በዚህም የተነሳ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ብንሆንም ልዩ ሕዝብ መሆን ችለናል።—የሐዋርያት ሥራ 4:13፤ 10:34, 35

      • የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

      • የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው የትኞቹን መመሪያዎች ማወቅ ችለዋል?

  • የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 2

      የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?

      ኖኅ

      ኖኅ

      አብርሃምና ሣራ

      አብርሃምና ሣራ

      ሙሴ

      ሙሴ

      ኢየሱስ ክርስቶስ

      ኢየሱስ ክርስቶስ

      ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው መጠሪያ የአንድ አዲስ ሃይማኖት ስም ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ከ2,700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት እውነተኛው አምላክ፣ አገልጋዮቹን “ምሥክሮቼ” ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12) እስከ 1931 ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል እንታወቅ ነበር። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት የጀመርነው ለምንድን ነው?

      አምላካችንን ለይቶ ያሳውቃል። በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ይገኝ ነበር። በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይህ ስም እንደ ጌታ፣ አምላክ ወይም እግዚአብሔር (እንደ አማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ) በመሳሰሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል። ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ “ይሖዋ” የሚለውን የግል ስሙን የነገረው ሲሆን “ይህ ለዘላለም ስሜ ነው” ብሎታል። (ዘፀአት 3:15) እውነተኛው አምላክ በዚህ መንገድ ራሱን ከሌሎች የሐሰት አማልክት ለይቷል። እኛም በአምላክ ቅዱስ ስም በመጠራታችን እንኮራለን።

      ተልእኳችንን ይገልጻል። ከጻድቁ አቤል ጀምሮ የኖሩ በርካታ ሰዎች በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው መሥክረዋል። ከዚያ በኋላ በነበሩት ምዕተ ዓመታትም ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ዳዊትና ሌሎችም ከዚህ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ጋር ተባብረዋል። (ዕብራውያን 11:4 እስከ 12:1) አንድ ግለሰብ የፍርድ ችሎት ፊት ቀርቦ ስለ አንድ ሰው ንጽሕና እንደሚመሠክር ሁሉ እኛም ስለ አምላካችን እውነቱን ለማሳወቅ ቆርጠን ተነስተናል።

      የኢየሱስን ምሳሌ እንደምንከተል ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ታማኝና እውነተኛ ምሥክር” ይለዋል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ራሱም ‘የአምላክን ስም እንዳሳወቀ’ እንዲሁም ስለ አምላክ ‘እውነቱን እንደመሠከረ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:26፤ 18:37) እንግዲያው የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ በይሖዋ ስም መጠራት እና ስሙን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንን ለማድረግ ይጥራሉ።

      • የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው መጠራት የጀመሩት ለምንድን ነው?

      • ይሖዋ በምድር ላይ ምሥክሮች የነበሩት ከመቼ ጀምሮ ነው?

      • ከሁሉ የሚበልጠው የይሖዋ ምሥክር ማን ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ከጉባኤያችን አባላት ጋር ስትገናኝ ስለ እነሱ ይበልጥ ለማወቅ ሞክር። “የይሖዋ ምሥክር የሆንከው ለምንድን ነው?” ብለህ ጠይቃቸው።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ