የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 5

      ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?

      አርጀንቲና ውስጥ ባለ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      አርጀንቲና

      ሴራሊዮን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ሴራ ሊዮን

      ቤልጅየም ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ቤልጅየም

      ማሌዥያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ማሌዥያ

      ብዙ ሰዎች በሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ላይ መንፈሳዊ መመሪያም ሆነ ማጽናኛ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደነዚህ ወዳሉ ቦታዎች መሄድ አቁመዋል። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? እዚያ ምን ጥቅም ታገኛለህ?

      አፍቃሪና አሳቢ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሰብሰብ ትደሰታለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖች በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ይታቀፉ የነበረ ሲሆን አምላክን ለማምለክ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት እንዲሁም እርስ በርስ ለመበረታታት ይሰበሰቡ ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) በስብሰባዎቻቸው ላይ አፍቃሪ ከሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ጋር ስለሚገናኙ ከእውነተኛ ወዳጆቻቸው ጋር እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 1:3፤ 3 ዮሐንስ 14) እኛም የእነሱን ምሳሌ ስለምንከተል በስብሰባዎቻችን እንደሰታለን።

      የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ትማራለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ዛሬም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አንድ ላይ እንሰበሰባለን። ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርግ ማስተዋል እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያብራሩልናል። (ዘዳግም 31:12፤ ነህምያ 8:8) ሁሉም ሰው መዘመር እንዲሁም ውይይት በሚደረግባቸው የስብሰባው ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት የሚችል ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ለመግለጽ ያስችለናል።—ዕብራውያን 10:23

      በአምላክ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ከነበሩት ጉባኤዎች ለአንዱ ሲጽፍ “ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው” ብሎ ነበር። (ሮም 1:11, 12) በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አዘውትረን መገናኘታችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ለመጽናት ያስችለናል።

      አንተስ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። በስብሰባው ላይ ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግልህ አትጠራጠር። መግቢያ በነፃ ሲሆን ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም።

      • በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ የእነማንን ምሳሌ እንከተላለን?

      • በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ምን ጥቅም እናገኛለን?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በስብሰባዎቻችን ላይ ከመገኘትህ በፊት የስብሰባ አዳራሻችን ምን እንደሚመስል ማየት ከፈለግክ አንድ የይሖዋ ምሥክር አዳራሹን እንዲያስጎበኝህ መጠየቅ ትችላለህ።

  • ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 6

      ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ይቀራረባሉ

      ማዳጋስካር

      አንድ የይሖዋ ምሥክር የእምነት ባልንጀራውን ሲረዳ

      ኖርዌይ

      ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀራቸውን ሄደው ሲጠይቁ

      ሊባኖስ

      የይሖዋ ምሥክሮች አብረው ጊዜ ያሳልፋሉ

      ጣሊያን

      የበጋውን ሐሩርና የክረምቱን ቁር መቋቋም አሊያም ጥቅጥቅ ያለ ደን አቋርጠን መጓዝ ቢኖርብንም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳናሰልስ እንገኛለን። የዕለት ተዕለት ኑሮ ከሚያስከትለው ጫና በተጨማሪ ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥረን መዋላችን ኃይላችንን ቢያሟጥጥብንም በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለመሆን ይህን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው?

      ለደህንነታችን አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በአእምሮው በመያዝ “አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” ብሏል። (ዕብራውያን 10:24) ይህ አገላለጽ አንዳችን ስለ ሌላው “በጥልቅ ማሰብ” ይኸውም እርስ በርስ በደንብ መተዋወቅ እንደሚኖርብን ያመለክታል። በሌላ አባባል ሐዋርያው፣ ስለ ሌሎች እንድናስብ እያበረታታን ነው። በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ክርስቲያን ቤተሰቦች ጋር በደንብ ስንተዋወቅ አንዳንዶቹ እኛ ያጋጠመንን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመው እንዳለፉና እኛም እንዲህ እንድናደርግ ሊረዱን እንደሚችሉ እንገነዘባለን።

      ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። አብረውን ከሚሰበሰቡት ሰዎች ጋር ያለን ቅርርብ ከተራ ትውውቅ ያለፈ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የቅርብ ወዳጆቻችን ናቸው። በሌሎች አጋጣሚዎችም አብረናቸው በመሆን አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን። እንዲህ ያለው ቅርርብ ምን ጥቅም ያስገኛል? አንዳችን የሌላውን ባሕርያት ይበልጥ እንድናደንቅ የሚያነሳሳን ሲሆን ይህም በመካከላችን የጠበቀ ፍቅር እንዲኖር ያደርጋል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን ደግሞ ባልንጀሮቻችን የሆነ ችግር ሲያጋጥማቸው ቶሎ እንድንደርስላቸው ይገፋፋናል። (ምሳሌ 17:17) ከሁሉም የጉባኤያችን አባላት ጋር በመቀራረብ ‘እርስ በርሳችን እኩል እንደምንተሳሰብ’ እናሳያለን።—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26

      አንተም የአምላክን ፈቃድ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት እናበረታታሃለን። እንደነዚህ ያሉ ወዳጆችን በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ታገኛለህ። ከእኛ ጋር እንዳትቀራረብ ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ።

      • በስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      • በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ከእኛ ጋር የምትተዋወቀው መቼ ነው?

  • ስብሰባዎቻችን ምን ይመስላሉ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 7

      ስብሰባዎቻችን ምን ይመስላሉ?

      በኒው ዚላንድ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ኒው ዚላንድ

      በጃፓን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ጃፓን

      ኡጋንዳ ውስጥ አንድ ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ

      ኡጋንዳ

      በሊቱዌንያ ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ምን እንደሚመስል ሲያሳዩ

      ሊቱዌኒያ

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ይዘምሩ፣ ይጸልዩ እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍትን እያነበቡ ይወያዩ ነበር፤ የስብሰባው ዋነኛ ገጽታዎች እነዚህ ሲሆኑ ከዚህ ውጭ ለየት ያለ የአምልኮ ሥርዓት አያካሂዱም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:26) በእኛ ስብሰባዎች ላይ የሚከናወነው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።

      ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ 30 ደቂቃ የሚወስድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር የሚቀርብ ሲሆን ንግግሩም ቅዱሳን መጻሕፍት ከሕይወታችንና ከምንኖርበት ዘመን ጋር በተያያዘ በሚሰጡት መመሪያ ላይ ያተኮረ ነው። ጥቅሶች ሲነበቡ ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱሳችንን አውጥተን እንድንከታተል እንበረታታለን። ከንግግሩ በኋላ አንድ ሰዓት የሚወስድ “የመጠበቂያ ግንብ” ጥናት ይደረጋል፤ በመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ላይ በወጣ አንድ ርዕስ ላይ በሚደረገው በዚህ ውይይት ሁሉም የጉባኤው አባላት እንዲካፈሉ ይጋበዛሉ። ይህ ውይይት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል። በምድር ዙሪያ በሚገኙት ከ110,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚጠናው ርዕስ ተመሳሳይ ነው።

      የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል እርዳታ እናገኛለን። በሳምንቱ መሃል ደግሞ ሦስት ክፍሎች ያሉት ስብሰባ እናደርጋለን፤ ይህ ስብሰባ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን በመባል ይጠራል፤ ትምህርቱ የተመሠረተው በየወሩ በሚወጣው የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ ነው። የዚህ ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል “ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት” የሚባል ሲሆን የጉባኤው አባላት አስቀድመው ያነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይብራራል። ቀጥሎ የሚቀርበው “በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር” የተባለው ክፍል ደግሞ ከሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መወያየት እንደምንችል የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎችን ያካተተ ነው። ምክር ሰጪው የንባብና የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ነጥቦችን ይነግረናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​13) “ክርስቲያናዊ ሕይወት” የተባለው የመጨረሻው ክፍል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል። በዚህ ክፍል ውስጥ በጥያቄና መልስ የሚካሄድ ውይይት የሚካተት ሲሆን ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።

      በስብሰባዎቻችን ላይ በምትገኝበት ጊዜ በስብሰባው ላይ በሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መደነቅህ አይቀርም።—ኢሳይያስ 54:13

      • የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ምን ትምህርቶች ይቀርባሉ?

      • ከሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን በየትኛው ላይ መገኘት ትፈልጋለህ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በሚቀጥለው ጊዜ በሚኖረው ስብሰባ ላይ ከሚቀርቡት ትምህርቶች አንዳንዶቹ ምን እንደሆኑ ለማወቅ ሞክር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ የሚጠቅምህ ምን ትምህርት ማግኘት የምትችል ይመስልሃል?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ