የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁትና የሚተረጎሙት እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 23

      ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁትና የሚተረጎሙት እንዴት ነው?

      ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል እየሠራ ያለ ሰው

      የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      በደቡብ ኮሪያ የሚገኝ አንድ የትርጉም ቡድን

      ደቡብ ኮሪያ

      አርሜንያ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎመ መጽሐፍ የያዘ ሰው

      አርሜንያ

      ቡሩንዲ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎመ መጽሐፍ የያዘች ልጅ

      ቡሩንዲ

      ስሪ ላንካ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎሙ መጽሔቶችን የያዘች ሴት

      ስሪ ላንካ

      ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ ምሥራቹን’ በማወጁ ሥራ የተቻለንን ለማድረግ ስንል ከ750 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ጽሑፎችን እናዘጋጃለን። (ራእይ 14:6) ይህን ከባድ ሥራ የምንወጣው እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ጸሐፊዎችና በርካታ ተርጓሚዎች እገዛ ሲሆን በሥራው ላይ የሚካፈሉት በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

      ዋናው ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ይዘጋጃል። የበላይ አካሉ በዋናው መሥሪያ ቤታችን የሚገኘውን የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል እንቅስቃሴ በበላይነት ይቆጣጠራል። ይህ ክፍል፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና በአንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ሆነው የሚሠሩት ጸሐፊዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ይከታተላል። የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ጸሐፊዎች መኖራቸው ጽሑፎቻችን በልዩ ልዩ ባሕሎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚማርኩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ እንዲሆኑ አድርጓል፤ ይህም ጽሑፎቹ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

      ጽሑፉ ለተርጓሚዎች ይላካል። የተዘጋጀው ጽሑፍ ከታረመና እንዲወጣ ከጸደቀ በኋላ በምድር ዙሪያ ወደሚገኙ የትርጉም ቡድኖች በኤሌክትሮኒክ ፋይል ይላካል፤ እነዚህ ቡድኖች ጽሑፉን የሚተረጉሙ፣ ትርጉሙን ከእንግሊዝኛው ጋር እያመሳከሩ የሚያርሙና የማጣሪያ ንባብ የሚያከናውኑ ተርጓሚዎችን ያቀፉ ናቸው። ተርጓሚዎቹ የእንግሊዝኛውን መልእክት፣ በሚተረጉሙበት ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ የሚያስችላቸውን ‘ትክክለኛውን ቃል’ ለመምረጥ ጥረት ያደርጋሉ።—መክብብ 12:10

      ኮምፒውተር ሥራውን ያቀላጥፈዋል። ኮምፒውተር፣ ጸሐፊዎችና ተርጓሚዎች የሚያከናውኑትን ሥራ መተካት አይችልም። ይሁን እንጂ ተርጓሚዎች፣ መዝገበ ቃላቶችንና ለትርጉም ሥራ የሚያግዙ ሌሎች ጽሑፎችን በኮምፒውተር ማግኘታቸው ሥራቸውን ለማፋጠን ይረዳቸዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች መልቲላንጉዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፐብሊሺንግ ሲስተም (ሜፕስ) የተባለ የኮምፒውተር ፕሮግራም ሠርተዋል፤ ይህ ፕሮግራም ትርጉሙን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለመጻፍ፣ ጽሑፉን ከሥዕሉ ጋር ለማቀናበርና ለሕትመት ለማዘጋጀት ያስችላል።

      በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ብቻ ባሏቸው ቋንቋዎች እንኳ ጽሑፎቻችንን ለመተርጎም ይህን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የይሖዋ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ስለሆነ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

      • ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁት እንዴት ነው?

      • ጽሑፎቻችንን በበርካታ ቋንቋዎች የምንተረጉመው ለምንድን ነው?

  • በዓለም ዙሪያ ለምናከናውነው ሥራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 24

      በዓለም ዙሪያ ለምናከናውነው ሥራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?

      በፈቃደኝነት ተነሳስቶ መዋጮ የሚያደርግ ሰው
      የይሖዋ ምሥክሮች እየሰበኩ

      ኔፓል

      በቶጎ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች

      ቶጎ

      በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች

      ብሪታንያ

      ድርጅታችን በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች ጽሑፎችን አትሞ ያለ ምንም ክፍያ ያሰራጫል። የስብሰባ አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንገነባለን እንዲሁም እንጠግናለን። በሺዎች የሚቆጠሩት ቤቴላውያንና ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዲሟሉላቸው እናደርጋለን፤ እንዲሁም አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እርዳታ እንሰጣለን። ‘ታዲያ ለእነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚሆን ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

      አሥራት ወይም የአባልነት ክፍያ አንጠይቅም፤ ሙዳየ ምጽዋትም አናዞርም። የወንጌላዊነት ሥራችንን ማከናወን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም የገንዘብ እርዳታ አንጠይቅም። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የወጣው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሁለተኛ እትም፣ ‘ይሖዋ እንደሚደግፈን ስለምናምን ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም እንደማንለምን ወይም እንደማንማጠን’ ገልጾ ነበር፤ ደግሞም እንዲህ አድርገን አናውቅም!—ማቴዎስ 10:8

      ለሥራችን የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው በፈቃደኝነት ከሚሰጥ መዋጮ ነው። ብዙ ሰዎች ለምናከናውነው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ አድናቆት ስላላቸው የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮችም በመላው ምድር ለሚከናወነው የአምላክን ፈቃድ የመፈጸም ሥራ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ሌላ ጥሪታቸውን በደስታ ይሰጣሉ። (1 ዜና መዋዕል 29:9) በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መዋጮ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች መዋጯቸውን የሚያስገቡባቸው ሣጥኖች ይገኛሉ። መዋጮ ለማድረግ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንንም መጠቀም ይቻላል። መዋጮ ሣጥኖች ውስጥ ከሚገኘው ገንዘብ አብዛኛውን የሚያዋጡት፣ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች በቤተ መቅደሱ መዋጮ ዕቃ ውስጥ በመጨመሯ ኢየሱስ እንዳመሰገናት ድሃ መበለት ያሉ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ሉቃስ 21:1-4) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ማንኛውም ሰው “በልቡ ያሰበውን” መስጠት እንዲችል በየጊዜው ‘የተወሰነ ገንዘብ ማስቀመጥ’ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 16:2፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7

      የተለያዩ ሰዎች፣ በሚያደርጉት መዋጮ አማካኝነት የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በመደገፍ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ ይሖዋም ‘ባሏቸው ውድ ነገሮች እሱን ማክበር’ የሚፈልጉትን የእነዚህን ሰዎች ልብ ማነሳሳቱን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ምሳሌ 3:9

      • ድርጅታችንን ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው ምንድን ነው?

      • በፈቃደኝነት የሚደረጉትን መዋጮዎች የምንጠቀምባቸው እንዴት ነው?

  • የስብሰባ አዳራሾችን የምንሠራው ለምንድን ነው? የሚገነቡትስ እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 25

      የስብሰባ አዳራሾችን የምንሠራው ለምንድን ነው? የሚገነቡትስ እንዴት ነው?

      በቦሊቪያ የሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ቡድን

      ቦሊቪያ

      በናይጄሪያ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ እንደገና ከመገንባቱ በፊት
      በናይጄሪያ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ እንደገና ከተገነባ በኋላ

      ናይጄሪያ፣ በፊትና አሁን

      በታሂቲ የስብሰባ አዳራሽ ሲገነባ

      ታሂቲ

      በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የሚሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያጠነጥነው የኢየሱስ አገልግሎት ዋነኛ ጭብጥ በነበረው በአምላክ መንግሥት ዙሪያ ነው።—ሉቃስ 8:1

      በማኅበረሰቡ ውስጥ የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል ናቸው። የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ የሚደራጀው በእነዚህ የስብሰባ አዳራሾች ነው። (ማቴዎስ 24:14) የስብሰባ አዳራሾች መጠናቸውም ሆነ አሠራራቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም ልከኛ የሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ናቸው፤ በአብዛኛው በአንድ አዳራሽ ውስጥ ከአንድ የሚበልጡ ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ። በቅርብ ዓመታት ውስጥ የጉባኤዎቻችን ቁጥር በጣም በመጨመሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ (በአማካይ በየቀኑ አምስት) አዳዲስ የስብሰባ አዳራሾችን ገንብተናል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?—ማቴዎስ 19:26

      አዳራሾቹ የሚገነቡት ለዚህ ዓላማ በሚደረጉ መዋጮዎች ነው። እነዚህ መዋጮዎች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው የሚላኩ ሲሆን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት ወይም ማደስ የሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎች በዚህ ገንዘብ መጠቀም ይችላሉ።

      አዳራሾቹን የሚገነቡት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ደሞዝ የማይከፈላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። በብዙ አገሮች የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች አሉ። የግንባታ አገልጋዮችና ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚገኙባቸው ቡድኖች በአንድ አገር ውስጥ ከጉባኤ ወደ ጉባኤ አልፎ ተርፎም በጣም ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች እየሄዱ ጉባኤዎች የራሳቸውን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት እንዲችሉ እገዛ ያበረክታሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ ብቃት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በተመደበላቸው አካባቢ ውስጥ የሚከናወኑትን የስብሰባ አዳራሽ ግንባታና እድሳት ሥራዎች እንዲከታተሉ ይሾማሉ። በፈቃደኝነት በሥራው የሚካፈሉ ችሎታ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች ቢኖሩም እንኳ በእያንዳንዱ የግንባታ ቦታ አብዛኛውን የግንባታ ሥራ የሚያከናውኑት የጉባኤው አባላት ናቸው። ይህ ሁሉ ሥራ መከናወን የቻለው በይሖዋ መንፈስ ድጋፍና የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ነፍሳቸው በሚያደርጉት እገዛ ነው።—መዝሙር 127:1፤ ቆላስይስ 3:23

      • የስብሰባ አዳራሾችን የምንገነባው ለምንድን ነው?

      • በመላው ዓለም የስብሰባ አዳራሾችን መገንባት የተቻለው እንዴት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ