-
የስብሰባ አዳራሻችንን በመንከባከብ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 26
የስብሰባ አዳራሻችንን በመንከባከብ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ኢስቶንያ
ዚምባብዌ
ሞንጎሊያ
ፖርቶ ሪኮ
እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ የአምላክ ቅዱስ ስም ይጠራበታል። በመሆኑም የሕንፃውን ንጽሕናና ውበት በመጠበቁ እንዲሁም አዳራሹን በማደሱ ሥራ መካፈልን እንደ ትልቅ መብት የምንመለከተው ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ የሆነው አምልኳችን ክፍል እንደሆነ አድርገን እንቆጥረዋለን። በዚህ ሥራ ሁሉም ሰው መካፈል ይችላል።
ከስብሰባዎች በኋላ በሚደረገው መጠነኛ ጽዳት ተካፈል። ወንድሞችና እህቶች ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ቀለል ያለ ጽዳት ማከናወን ያስደስታቸዋል። በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ሰፋ ያለ ጽዳት ይደረጋል። አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ጽዳቱ የሚያካትታቸው ነገሮች የተጻፉበትን ዝርዝር በመያዝ ሥራውን ያስተባብራል። ወንድሞችና እህቶች እንደ አስፈላጊነቱ ወለሉን ይጠርጋሉ፣ ይወለውላሉ፣ አቧራ ያነሳሉ፣ ወንበሮችን ያስተካክላሉ፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳሉ፣ መስተዋቶችን ይወለውላሉ፣ ቆሻሻ ይደፋሉ፣ ግቢውን ያጸዳሉ እንዲሁም አትክልቶችን ይንከባከባሉ። ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ አዳራሹ የተሟላ ጽዳት ይደረግለታል። ልጆቻችንም በአንዳንድ ሥራዎች እንዲካፈሉ በማድረግ ለአምልኮ ቦታችን አክብሮት እንዲኖራቸው ልናሠለጥናቸው እንችላለን።—መክብብ 5:1
ለአዳራሹ ጥገና በሚደረግበት ጊዜ እገዛ አድርግ። በየዓመቱ የስብሰባ አዳራሹ ውስጡም ሆነ ውጭው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በደንብ ይገመገማል። ይህን መሠረት በማድረግ በየጊዜው የጥገና ሥራ ይከናወናል፤ ይህም አዳራሹ ምንጊዜም በጥሩ ሁኔታ እንዲገኝ ስለሚያደርግ አላስፈላጊ ከሆነ ወጪ ያድናል። (2 ዜና መዋዕል 24:13፤ 34:10) የስብሰባ አዳራሻችን ንጹሕና በተገቢው ሁኔታ የተያዘ ከሆነ አምላካችንን ለማምለክ የሚመጥን ይሆናል። በዚህ ሥራ በመካፈል ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ለአምልኮ ቦታችን ያለንን አክብሮት እናሳያለን። (መዝሙር 122:1) አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን መያዛችን የአካባቢው ሰዎች ስለ እኛ በጎ አመለካከት እንዲኖራቸውም ያደርጋል።—2 ቆሮንቶስ 6:3
የአምልኮ ቦታችንን ችላ ማለት የማይገባን ለምንድን ነው?
የስብሰባ አዳራሹን ንጽሕና ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል?
-
-
ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነውበዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 27
ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
እስራኤል
ቼክ ሪፑብሊክ
ቤኒን
ኬይመን ደሴቶች
የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ የሚረዳህ ምርምር ማድረግ ትፈልጋለህ? ስለ አንድ ጥቅስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰ አንድ ግለሰብ፣ ቦታ ወይም ሌላ ነገር ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? አሊያም በግል ባሳሰበህ አንድ ጉዳይ ረገድ ሊረዳህ የሚችል ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ምርምር ለማድረግ አስበሃል? ከሆነ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ለምን ጎራ አትልም?
ጠቃሚ የሆኑ የምርምር መሣሪያዎች ይገኙበታል። የይሖዋ ምሥክሮች በቋንቋህ ያዘጋጇቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በሙሉ አይኖሩህ ይሆናል። በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ግን በቅርብ የወጡት ብዙዎቹ ጽሑፎች ይገኛሉ። በተጨማሪም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ጥሩ መዝገበ ቃላትና ሌሎች ጠቃሚ የማመሳከሪያ መጻሕፍት ሊኖሩ ይችላሉ። ከስብሰባ በፊትና በኋላ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት መሣሪያዎች መጠቀም ትችላለህ። ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ኮምፒውተር ካለ ደግሞ ዎችታወር ላይብረሪ የተባለው ፕሮግራም ይኖረዋል። ይህ ፕሮግራም በርካታ ጽሑፎቻችንን የያዘ ሲሆን አንድን ቃል፣ ጥቅስ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ፈልጎ በማውጣት በቀላሉ ምርምር ለማድረግ ያስችላል።
በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ለሚካፈሉ ተማሪዎች ጠቃሚ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ክፍል እንድታቀርብ ከተመደብክ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ተጠቅመህ ክፍልህን መዘጋጀት ትችላለህ። የቤተ መጻሕፍቱን ሁኔታ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ነው። በቅርብ የወጡ ጽሑፎች በሙሉ መግባታቸውንና በሚገባ ተስተካክለው መቀመጣቸውን መከታተል የእሱ ኃላፊነት ነው። የምትፈልገውን መረጃ እንዴት እንደምታገኝ የስብሰባው የበላይ ተመልካች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህ ሊያሳዩህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ጽሑፍ ከስብሰባ አዳራሹ ይዞ መውጣት አይቻልም። መጻሕፍቱን በአግባቡ መያዝ እንዳለብንና ጽሑፎቹ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ማድረግ እንደማይገባንም የታወቀ ነው።
‘ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም’ ከፈለግን “እንደተሸሸገ ሀብት” አጥብቀን ልንሻው እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ምሳሌ 2:1-5) እንዲህ ያለውን እውቀት ለማግኘት በምታደርገው ፍለጋ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት መሣሪያዎች ሊረዱህ ይችላሉ።
በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ምን ዓይነት የምርምር መሣሪያዎች ይገኛሉ?
በቤተ መጻሕፍቱ በሚገባ መጠቀም እንድትችል እነማን ሊረዱህ ይችላሉ?
-
-
በድረ ገጻችን ላይ ምን መረጃ ማግኘት ይቻላል?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 28
በድረ ገጻችን ላይ ምን መረጃ ማግኘት ይቻላል?
ፈረንሳይ
ፖላንድ
ሩሲያ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:16) ይህንንም ለማድረግ ስንል ኢንተርኔትን ጨምሮ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንጠቀማለን። jw.org በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ ስለ እምነታችንና ስለምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ይህ ድረ ገጽ ምን ይዟል?
ብዙ ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ። ብዙ ሰዎች ለሚጠይቋቸው በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች በድረ ገጻችን ላይ መልስ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል? እና የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ? የተባሉት ትራክቶች ከ600 በሚበልጡ ቋንቋዎች በዚህ ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል፤ እንዲሁም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች ብሎም በቅርብ የወጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ድረ ገጻችን ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ጽሑፎች አብዛኞቹን እዚያው ድረ ገጹ ላይ ማንበብ ወይም ማዳመጥ ይቻላል፤ አሊያም እንደ ኤም ፒ3፣ ፒ ዲ ኤፍ ወይም ኢ ፐብ ባሉ የታወቁ ፎርማቶች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማውረድ ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ለምሥራቹ ፍላጎት ያለው ሰው ስታገኝ ከድረ ገጹ ላይ የተወሰኑ ገጾችን በራሱ ቋንቋ በማተም ልትሰጠው ትችላለህ! በበርካታ የምልክት ቋንቋዎችም በቪዲዮ የተቀረጹ ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። ከዚህም ሌላ በድራማ መልክ የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን ብሎም ዘና በምትልበት ጊዜ የምታዳምጣቸው ጣዕመ ዜማዎችንና መዝሙሮችን ማውረድ ትችላለህ።
ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚገልጹ ትክክለኛ መረጃዎች። ስለ ዓለም አቀፉ ሥራችን፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለሚመለከቱ ክንውኖች እንዲሁም አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳት ስለምናከናውነው እንቅስቃሴ የሚገልጹ ወቅታዊ ዜናዎችና ቪዲዮዎች ድረ ገጻችን ላይ ይወጣሉ። በቅርቡ ስለምናደርጋቸው የክልል ስብሰባዎች የሚገልጹ ማስታወቂያዎችንና የቅርንጫፍ ቢሮዎቻችንን አድራሻዎችም ማግኘት ትችላለህ።
በእነዚህ መንገዶች አማካኝነት በጣም ርቀው በሚገኙ የዓለም ክፍሎች ሳይቀር የእውነት ብርሃን እንዲበራ እናደርጋለን። አንታርክቲካን ጨምሮ በሁሉም አህጉራት የሚኖሩ ሰዎች ይህን ብርሃን ማየት ችለዋል። በምድር ሁሉ “የይሖዋ ቃል በፍጥነት መስፋፋቱን እንዲቀጥልና” በዚህም አምላክ እንዲከበር እንጸልያለን።—2 ተሰሎንቄ 3:1
jw.org ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
በድረ ገጻችን ላይ የትኞቹን ነገሮች መመልከት ትፈልጋለህ?
-