ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሰውን ፍርሃት እንዲያሸንፉ እርዱ
1 ምሳሌ 29:25 “ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው” በማለት ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የዚህን አባባል እውነተኝነት እንመለከታለን። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሰውን ማለትም ጎረቤትን፣ ዘመድን፣ የትምህርት ቤት ጓደኛን፣ የሥራ ባልደረባን አሊያም ቀሳውስትን መፍራታቸው ገና ከጅምሩም ቢሆን የምንነግራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳያዳምጡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። የሰው ፍርሃት ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግላቸውን ሰዎች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ፍላጎት ያዳፍናል። ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች እንደደረሰባቸው ሁሉ ዛሬም ብዙዎች ሰውን በመፍራት የተትረፈረፈ በረከት ሳያገኙ ይቀራሉ።—ዮሐ. 12:42, 43፤ 7:10-13፤ 9:18-22
2 አንድ የአገልግሎት ክልል አጥባቂ ሃይማኖተኞች እንደሚበዙበት የሚታወቅ ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን? እንዲህ ያለውን ክልል ለመሸፈን አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይኖርብን ይሆናል። ሰዎች በሰሙት ወሬ ብቻ ለእኛ ጭፍን ጥላቻ አድሮባቸው ሊሆን ስለሚችል ውይይታችንን እንዲህ በማለት ልንጀምር እንችላለን:- “ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ይነሳሉ ሲባል ሳይሰሙ አልቀሩም፤ እነዚህን ሐሰተኛ ክርስቲያኖች እንዴት ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል ኢየሱስ የተናገረውን ያውቃሉ?” ከዚያ ማቴዎስ 7:15-20ን ልታነብላቸውና ቁጥር 13ን እና 14ን ልታብራራላቸው ትችላለህ። ወይም እንዲህ ማለት ይቻላል:- “እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጠበቅ ያለባቸው ብዙዎች እንደሚወዷቸው ነው ወይስ እንደሚጠሏቸው?” ከዚያም ማቴዎስ 5:11, 12ን ወይም 10:22ን የመሳሰሉ ጥቅሶች አንብብ። ሌላው አማራጭ ደግሞ:- “ኢየሱስ ያከናወነውን የስብከት ሥራ በሚመለከት አንድ ነጥብ አንስተን ብንወያይ ደስ ይለናል። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፤ ኢየሱስ ይሰብክ የነበረውን መልእክት ሁሉም ሰዎች ተቀብለውታል ወይስ ብዙዎቹ ተቃውመውታል?” ከዚያ ዮሐንስ 15:18-20ን ማንበብ ትችላለህ። እነዚህ አቀራረቦች በአንዳንድ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያለባቸውን ጭፍን ጥላቻ እንዲያስወግዱ ረድተዋቸዋል።
3 ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ድፍረት እንዲያገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ተቃዋሚዎች ጣልቃ ገብተው ከአዳዲስ ሰዎች ጋር የጀመርነውን ውይይት የሚያደናቅፉበት ሁኔታ ሲፈጠር አንዳንድ ጊዜ ለምናነጋግራቸው ሰዎች ከአምላክ ጋር ከሚኖረን ዝምድና እንዲሁም ከዘላለም ሕይወት የሚበልጥ ነገር ሊሰጠን የሚችል ሰው እንደሌለ በጥበብ ልንነግራቸው እንችላለን። አንድ አስፋፊ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመው “አእምሯችን ከአምላክ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው ቢባል አይስማሙም? ታዲያ ሌሎች ሰዎች አእምሯችንን ተጠቅመን የራሳችንን ውሳኔ እንዳናደርግ እንቅፋት እንዲሆኑብን ለምን እንፈቅድላቸዋለን?” በማለት የሚያነጋግረውን ሰው ለማግባባት ሞክሯል። አንዳንድ ጊዜ ግን አካባቢውን ለቅቀን በመሄድ ፍላጎት ያለውን ሰው ሌላ ቦታ ብንቀጥረው ጥሩ ይሆናል።
4 አንዳንድ ጊዜ እኛ አንድን ሰው አነጋግረን ከሄድን በኋላ ተቃዋሚዎች በሰውየው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩበት ይሰማን ይሆናል። ስለዚህ በመጀመሪያው ውይይታችን መደምደሚያ ላይ እንዲህ ብለን ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን:- “ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የሚያበረታታ አይደለም? ታዲያ የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን በዚህ ደስ ይለዋል? እንግዲያውስ እርስዎን ተስፋ ለማስቆረጥ ምን የሚያደርግ ይመስልዎታል?” ከዚህ በኋላ እንደ 1 ዮሐንስ 5:19 ወይም 1 ጴጥሮስ 5:8 ያሉትን ጥቅሶች ማንበብ ይቻላል። እንዲህ ብለህ ተጨማሪ ጥያቄ ማቅረብ ትችላለህ:- “ታዲያ አሁን አንድ ሰው መጥቶ ስለዚህ መልእክት አጥላልቶ ቢነግርዎት ምን መልስ ይሰጡታል?”
5 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተህ ለመነጋገር ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ:- “ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚከተሉትን የሕይወት ጎዳና ከጠባብ በርና ከቀጭን መንገድ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?” ከዚያም ማቴዎስ 7:13, 14፤ ማቴዎስ 5:11 እና 2 ጢሞቴዎስ 3:12ን የመሳሰሉ ጥቅሶችን ልታብራራ ትችላለህ። ቀጥሎም በምሳሌ 29:25 ወይም በመዝሙር 56:11 ላይ ያሉትን ሐሳቦች ተጠቅሞ ማበረታቻ መስጠት ይቻላል። የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ጸሎት ያለውን ጥቅም አጉላ። እንዲሁም ያደረጋችሁት ውይይት ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ መሆን አለመሆኑን መጠየቅ ትችላለህ። አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትን የሚቃወሙ ሰዎች ስካርን፣ የዕፅ ሱሰኝነትን ወይም ሌሎች መጥፎ ምግባሮችን ሲያወግዙ እንደማይታዩ ግለጽ። ይህም ጭፍን አስተሳሰብ እንደሚያጠቃቸው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጣም ውድ ሀብት በመሆኑ አንድ ሰው በሌሎች ድርጊት በቀላሉ ተስፋ ቆርጦ ሊተወው እንደማይገባ ጥቀስ፤ ሰውን ፈርቶ እውነትን መተው ለእኛም ሆነ ለዘመዶቻችን አሊያም ለጓደኞቻችን የሚሰጠው አንዳችም ጥቅም አይኖርም።
6 አንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመርክ በኋላ ተማሪውን ለተቃውሞ ማዘጋጀት እንዳለብህ አትዘንጋ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 17 አንቀጽ 22 ላይ ያለውን ሐሳብ ልታብራራለት ትችላለህ። ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በሚለው ብሮሹር ላይ የተመሠረተ ከሆነ በትምህርት 1 አንቀጽ 3 እንዲሁም በትምህርት 4 አንቀጽ 7 ላይ ጠቃሚ ሐሳብ ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን ገና ጥናት እንደተጀመረ ተቃውሞ የማያጋጥምበት ጊዜ ይኖራል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ እነዚህን የመሳሰሉ ነጥቦችን በሌላ ጊዜያት አንስቶ መወያየት ይቻላል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የጥንት ክርስቲያኖችም ክፉ ይወራባቸው እንደነበረ ልታስረዳው ትችላለህ። (ሥራ 28:22) እንዲሁም ኢየሱስ ስለ ሁለቱ መንገዶች የሰጠውን ምሳሌ እንደገና አንስተህ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንዱን መምረጥ እንዳለባቸው ጎላ አድርገህ ንገረው። (ማቴ. 7:13, 14) ከወጣት ጋር ለሚደረግ ውይይት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 73 እስከ 80 ያለው ሐሳብ በጣም ጠቃሚ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ለማስተጓጎል ለሚጥሩ ሰዎች የለዘበ መልስ መስጠት ያለውን ጥቅም ጠንከር አድርጎ መናገሩ ጥሩ ነው። የዚህን አስፈላጊነት ለማስረዳት እንደ ሮሜ 12:17-21፤ ምሳሌ 15:1 ወይም 1 ጴጥሮስ 3:15 ያሉትን ጥቅሶች መጠቀም ይቻላል።
7 በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት የጸሎትን ኃይል አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። ይሖዋ ልብን ያነብባል እንዲሁም ቅን ልብ ያላቸውንም ሰዎች ወደ እርሱ ይስባቸዋል። (ዮሐ. 6:44) አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት እጁ አጭር አይደለችም። እነርሱን ወክለን የምናቀርበውም ጸሎት ይረዳቸዋል። ስለዚህ እነዚህን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን በስም ጠቅሰን በጥናታቸው ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጣቸው ይሖዋን መጠየቃችን የተገባ ነው።—ያዕ. 5:16
8 ‘በዓለም ዙሪያ ካሉት ወንድሞቻችን’ መካከል የብዙዎቹ ተሞክሮ እንደሚያሳየው በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ በመታመን ማንም ሰው ቢሆን የሰውን ፍርሃት ማሸነፍ ይችላል። (1 ጴጥ. 5:9፤ ምሳሌ 29:25፤ መዝ. 27:1፤ ፊልጵ. 4:13) የአምላክ ታማኝ ፍቅር እንዲሁም የማዳን ኃይል አስፈላጊውን ብርታት ይሰጠናል። (መዝ. 37:28፤ 118:6፤ ኢሳ. 41:10፤ 54:17) ይሖዋ በእርግጥ ብርታት እንደሚሰጥና የሰውን ፍርሃት አሸንፈው የእርሱ አገልጋዮች ለሆኑት ሽልማት እንዳዘጋጀ መገንዘብ እንዲችሉ ሌሎችን እንርዳ።—ምሳሌ 27:11፤ መዝ. 15:1, 2