የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 18 ገጽ 143-ገጽ 144 አን. 4
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ መልስ መስጠት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ መልስ መስጠት
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥቅሶችን ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የአምላክን ቃል በመጠቀም ራስህንም ሆነ ሌሎችን እርዳ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “የአምላክ ቃል . . . ኃይለኛ ነው”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 18 ገጽ 143-ገጽ 144 አን. 4

ጥናት 18

በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ መልስ መስጠት

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ጥያቄ ሲነሳ የራስህን አስተያየት ከመስጠት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገህ ተጠቀም።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ተልዕኳችን ‘ቃሉን መስበክ’ ነው። ኢየሱስ “እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም” በማለት በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል።​—⁠2 ጢሞ. 4:​2፤ ዮሐ. 14:​10

ስለ እምነታችን፣ ስለምንመራባቸው ደንቦች፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ስላለን አመለካከትና ስለ ተስፋችን ጥያቄ ሲቀርብልን መልስ የምንሰጠው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው። እምነታችን የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። ሕይወታችንን የምንመራው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉትንም ነገሮች የምንመለከተው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ነው። ተስፋችንም በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው።​—⁠2 ጢሞ. 3:​16, 17

የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን በስሙ መጠራታችን ምን ኃላፊነት እንደሚያስከትልብን እንገነዘባለን። (ኢሳ. 43:​12) ከዚህ የተነሣ ለሚቀርቡልን ጥያቄዎች መልስ የምንሰጠው ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈውን ቃሉን ተጠቅመን እንጂ ሰብዓዊ ፍልስፍናን ተመርኩዘን አይደለም። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም የየራሳችን አመለካከት እንደሚኖረን የታወቀ ነው። ይሁንና የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ከልብ ስለምናምን በዚያ መሠረት እንመራለን። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የግል ምርጫዎቻችንን እንድናደርግ ይፈቅድልናል። ሰዎች የእኛን የግል አመለካከት እንዲከተሉ ከማድረግ ይልቅ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲያስተውሉ ልንረዳቸው ይገባል። ይህም የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነታቸውን እንዲጠቀሙበት ያስችላቸዋል። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛም ‘አምነው እንዲታዘዙ’ እንፈልጋለን።​—⁠ሮሜ 16:​26

ኢየሱስ በራእይ 3:​14 ላይ “የታመነውና እውነተኛው ምስክር” ተብሎ ተጠርቷል። ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ይሰጥና ለሚያጋጥሙት ሁኔታዎች መፍትሔ ያበጅ የነበረው እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ አእምሮን የሚያመራምሩ ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። ጠያቂው ራሱ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለውን ግንዛቤ እንዲገልጽ ያደረገበትም ጊዜ አለ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ጥቅሶችን ቀጥታ በመጥቀስ፣ የጥቅሱን ሐሳብ በመጠቀም ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በማውሳት ተናግሯል። (ማቴ. 4:3-10፤ 12:1-8፤ ሉቃስ 10:25-28፤ 17:32) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅልል ብዙውን ጊዜ ይቀመጥ የነበረው በምኩራቦች ውስጥ ነው። ኢየሱስ በግሉ የእነዚህ ጥቅልሎች ስብስብ እንደነበረው የሚጠቁም አንድም ማስረጃ አናገኝም። ይሁንና ቅዱሳን ጽሑፎቹን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር በሚያስተምርበት ጊዜ ከነዚህ መጻሕፍት ደጋግሞ የመጥቀስ ልማድ ነበረው። (ሉቃስ 24:27, 44-47) በእርግጥም ከአባቱ የሰማውን እንጂ ከራሱ አንዳች እንዳላስተማረ መናገሩ ተገቢ ነበር።​—⁠ዮሐ. 8:​26

የእኛም ፍላጎት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ነው። እኛ እንደ ኢየሱስ፣ አምላክ ራሱ ሲናገር የመስማት አጋጣሚ አላገኘንም። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። መልስ የምንሰጠው መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ከሆነ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳችን አንስብም። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን አመለካከት ከማስተጋባት ይልቅ ቁርጥ ውሳኔያችን አምላክ የሚለንን መከተል እንደሆነ እናሳያለን።​—⁠ዮሐ. 7:​18፤ ሮሜ 3:​4

እርግጥ ዋናው ግባችን መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ብቻ ሳይሆን አድማጫችን ከሚነበበው መልእክት የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ መርዳት ነው። ልቡን ከፍቶ እንዲያዳምጠን እንፈልጋለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትጠቅሰውን ሐሳብ እንደ ሰውዬው ሁኔታ እንደሚከተለው እያልክ ልታስተዋውቅ ትችላለህ:- “ወሳኝ የሚሆነው አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለው አመለካከት አይመስልህም?” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የሚናገረው ሐሳብ እንዳለ ታውቃለህ?” ልትል ትችላለህ። የምታወያየው ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የሌለው ከሆነ ሌላ ዓይነት መግቢያ መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። “እስቲ ስለ አንድ ጥንታዊ ትንቢት ልንገርህ” ልትለው ትችላለህ። ወይም ደግሞ “በሰው ዘር ታሪክ በስፋት ከተሰራጩት መጻሕፍት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል . . .” ማለትም ትችል ይሆናል።

አንዳንድ ጊዜ የጥቅሱን ሐሳብ በራስህ አባባል ጨመቅ አድርገህ ለመግለጽ ትፈልግ ይሆናል። ይሁን እንጂ አመቺ ሆኖ ባገኘኸው ጊዜ ሁሉ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ ማንበቡ የተሻለ ነው። ከተቻለም ጥቅሱን ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አሳየው። በዚህ መንገድ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ልብ ለመንካት ያስችላል።​—⁠ዕብ. 4:​12

በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሚሰጡበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ከሚያስፈልጉት ብቃቶች አንዱ ‘በማስተማር ጥበብ ረገድ በታመነው ቃል የሚጸና’ መሆኑ ነው። (ቲቶ 1:9) አንድ የጉባኤ አባል ሽማግሌው የሰጠውን ምክር መሠረት በማድረግ በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል። እንግዲያው ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክር ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መሆኑ ምንኛ አስፈላጊ ነው! አንድ ሽማግሌ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆኑ ሌሎችም በማስተማር ሥራቸው እንዲሁ እንዲያደርጉ ሊያበረታታ ይችላል።

በዚህ ረገድ የተዋጣልህ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ። ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም ይኑርህ።

  • በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መልስ ስትሰጥ ጥቅሶችን የመጠቀም ልማድ አዳብር።

  • ሁልጊዜ አንድ ጥያቄ ሲቀርብልህ ወይም መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ሲገጥምህ መልስ ከመስጠትህ ወይም ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ‘መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

  • አንድን ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ካላወቅህ ግምታዊ ሐሳብ ከመሰንዘር ወይም የራስህን አመለካከት ከመናገር ተቆጠብ። መልስ ከመስጠትህ በፊት ምርምር ማድረግ እንደሚያስፈልግህ መናገሩ የተሻለ ይሆናል።

መልመጃ፦ (1) በመስክ አገልግሎት ሊሆን ይችላል፣ ወይም (2) በቅርቡ በዜና ከቀረበ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወይም (3) ብዙ ሰዎች በሚሳተፉበት አንድ ዓይነት ተግባር መካፈልን በተመለከተ የቀረቡልህን አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎች ምረጥ። ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ የሚሆን ቢያንስ አንድ ጥቅስ ፈልግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ