የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሰኔ 2018
ከሰኔ 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 15–16
“ኢየሱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል”
(ማርቆስ 15:3-5) የካህናት አለቆቹ ግን በእሱ ላይ በርካታ ክስ መደርደራቸውን ቀጠሉ። 4 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “ምንም መልስ አትሰጥም? በስንት ነገር እየከሰሱህ እንዳሉ ተመልከት” ሲል እንደገና ጠየቀው። 5 ሆኖም ኢየሱስ ምንም ተጨማሪ መልስ አልሰጠም፤ በመሆኑም ጲላጦስ ተገረመ።
(ማርቆስ 15:24) ከዚያም እንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ማን ምን እንደሚወስድ ለመወሰንም ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።
(ማርቆስ 15:29, 30) በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡትና ራሳቸውን እየነቀነቁ እንዲህ ይሉት ነበር፦ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ! 30 እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ወርደህ ራስህን አድን።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ማር 15:24, 29
መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ፦ በዮሐ19:23, 24 ላይ የሚገኘው ዘገባ የሚከተሉትን በማቴዎስ፣ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌሎች ላይ ያልተጠቀሱ ዝርዝር ጉዳዮች ይዟል፦ የሮም ወታደሮች በመደረቢያውም ሆነ ከውስጥ ለብሶት በነበረው ልብስ ላይ ዕጣ ተጣጥለው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል፤ ወታደሮቹ መደረቢያዎቹን ‘እያንዳንዱ ወታደር አንድ አንድ ቁራጭ እንዲደርሰው አራት ቦታ እንደቆራረጧቸው’ ይገልጻል፤ ከውስጥ የለበሰውን ልብስ መቆራረጥ ስላልፈለጉ ዕጣ እንደተጣጣሉበት ይናገራል፤ እንዲሁም በመሲሑ ልብስ ላይ ዕጣ መጣጣላቸው በመዝ 22:18 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ እንዳደረገ ይገልጻል። የሞት ፍርዱን የሚያስፈጽሙት ሰዎች ቅጣት የሚያስፈጽሙባቸውን ሰዎች ልብስ መውሰዳቸው የተለመደ ነገር ሳይሆን አይቀርም፤ በመሆኑም ወንጀለኞቹ ከመገደላቸው በፊት ልብሳቸውን ይገፈፉ እንዲሁም የያዙት ነገር ሁሉ ይወሰድባቸው ነበር። ይህም ወንጀለኞቹን ይበልጥ ለውርደት ይዳርጋቸው ነበር።
ራሳቸውን እየነቀነቁ፦ አብዛኛውን ጊዜ ንግግርንም የሚጨምረው ይህ ድርጊት ሹፈትን፣ ንቀትን ወይም ፌዝን ያንጸባርቃል። በመንገድ የሚያልፉት ሰዎች ሳያውቁት በመዝ 22:7 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርገዋል።
(ማርቆስ 15:43) የተከበረ የሸንጎ አባል የሆነውና የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ መጣ። ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።
(ማርቆስ 15:46) እሱም በፍታ ገዝቶ አስከሬኑን ካወረደ በኋላ በበፍታው ገነዘው፤ ከዚያም ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ድንጋይ አንከባሎም የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 15:43
ዮሴፍ፦ የወንጌል ጸሐፊዎች ስለ ዮሴፍ የተለያየ መግለጫ መስጠታቸው እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ስብዕና እንዳላቸው ያሳያል። ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ “ሀብታም” እንደነበር ገልጿል፤ በዋነኝነት ሮማውያንን ታሳቢ በማድረግ የጻፈው ማርቆስ የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረ “የተከበረ የሸንጎ አባል” እንደሆነ ጽፏል፤ ሩኅሩኅ ሐኪም የነበረው ሉቃስ ሸንጎው በኢየሱስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ያልደገፈ “ጥሩና ጻድቅ ሰው” እንደሆነ ገልጿል፤ “አይሁዳውያንን ይፈራ ስለነበር [ደቀ መዝሙር መሆኑን] ለማንም አልተናገረም” በማለት የዘገበው ደግሞ ዮሐንስ ብቻ ነው።—ማቴ 27:57-60፤ ማር 15:43-46፤ ሉቃስ 23:50-53፤ ዮሐ 19:38-42
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ማርቆስ 15:25) እንጨት ላይ ሲቸነክሩትም ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማር 15:25
ሦስት ሰዓት፦ አንዳንዶች ይህ ዘገባና በዮሐ 19:14-16 ላይ የሚገኘው ዘገባ እርስ በርሱ እንደሚጋጭ ይሰማቸዋል፤ ምክንያቱም በዮሐ 19:14-16 ላይ የሚገኘው ዘገባ ጲላጦስ ኢየሱስን እንዲሰቀል አሳልፎ ሲሰጠው ሰዓቱ “ስድስት ሰዓት ገደማ” እንደነበር ይገልጻል። ቅዱሳን መጻሕፍት ይህ ልዩነት የተፈጠረው ለምን እንደሆነ ሙሉ ማብራሪያ ባይሰጡም የሚከተሉትን ነጥቦች ግምት ውስጥ ማስገባት እንችላለን፦ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን የተከናወኑት ነገሮች የተፈጸሙበትን ጊዜ አስመልክቶ በአራቱም የወንጌል ዘገባዎች ላይ የሰፈረው ሐሳብ እርስ በርሱ ይስማማል። አራቱም ወንጌሎች ካህናትና ሽማግሌዎች ማለዳ ላይ እንደተሰበሰቡና ከዚያም ኢየሱስን ወደ ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ እንደወሰዱት ይናገራሉ። (ማቴ 27:1, 2፤ ማር 15:1፤ ሉቃስ 22:66–23:1፤ ዮሐ 18:28) ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ከተሰቀለ በኋላ “ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ” አገሩ በሙሉ በጨለማ እንደተሸፈነ ዘግበዋል። (ማቴ 27:45, 46፤ ማር 15:33, 34፤ ሉቃስ 23:44) ኢየሱስ ስለተሰቀለበት ሰዓት በሚናገሩት ዘገባዎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ይህ ሊሆን ይችላል፦ አንዳንዶች ግርፋት የስቅላት ቅጣቱ ክፍል እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግርፋቱ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ግለሰቡ ሊሞት ይችላል። ኢየሱስም ቢሆን የመከራውን እንጨት መጀመሪያ ላይ ብቻውን ተሸክሞ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ሌላ ሰው እንዲሸከምለት ማድረግ እስኪያስፈልግ ድረስ በኃይል ተገርፎ ነበር። (ሉቃስ 23:26፤ ዮሐ 19:17) ግርፋቱ የቅጣት ሂደቱ የመጀመሪያ ክፍል ተደርጎ የሚታይ ከሆነ ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ከመሰቀሉ በፊት የተወሰነ ሰዓት አልፎ መሆን አለበት። ማቴ 27:26 እና ማር 15:15 መገረፉንና እንጨት ላይ መሰቀሉን አብረው የሚጠቅሱ መሆኑ ይህን ሐሳብ ይደግፋል። በመሆኑም የተለያዩ ግለሰቦች ኢየሱስ የተሰቀለበትን ጊዜ በተመለከተ የተለያየ ሰዓት ሊጠቅሱ ይችላሉ፤ ይህን የሚወስነው ግለሰቦቹ የስቅላቱ ሂደት ጀምሯል ብለው ያሰቡበትን ሰዓት በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ነው። ጲላጦስ፣ ኢየሱስ እንጨት ላይ ከተሰቀለ ብዙም ሳይቆይ እንደሞተ ሲሰማ የተገረመውም ለዚህ ሊሆን ይችላል። (ማር 15:44) በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የቀኑን ክፍለ ጊዜ ልክ እንደ ሌሊቱ ክፍለ ጊዜ የሦስት ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው አራት ክፍሎች የመከፋፈልን ልማድ ይከተሉ ነበር፤ የቀኑ ክፍለ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ፀሐይ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ነው። ሦስት ሰዓት፣ ስድስት ሰዓትና ዘጠኝ ሰዓት የሚሉት አገላለጾች በተደጋጋሚ ተጠቅሰው የምናገኘውም በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴ 20:1-5፤ ዮሐ 4:6፤ ሥራ 2:15፤ 3:1፤ 10:3, 9, 30) ከዚህም ሌላ በጥቅሉ ሲታይ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ትክክለኛውን ሰዓት የሚያውቁበት መንገድ ስላልነበረ አብዛኛውን ጊዜ ሰዓት ሲጠቅሱ ዮሐ 19:14 ላይ እንደሚገኘው “ገደማ” የሚለውን ቃል ይጨምሩበታል። (ማቴ 27:46፤ ሉቃስ 23:44፤ ዮሐ 4:6፤ ሥራ 10:3, 9) ለማጠቃለል ያህል፦ ማርቆስ የዘገበው ከግርፋቱ ጀምሮ ያለውን ሰዓት በአእምሮው ይዞ፣ ዮሐንስ ደግሞ እንጨት ላይ የተሰቀለበትን ሰዓት ብቻ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ሁለቱም ጸሐፊዎች ሰዓቱን ቅርብ ወደሆነው የሦስት ሰዓት ክፍልፋይ አጠጋግተው ሊሆን ይችላል፤ ዮሐንስ ደግሞ ሰዓቱን ሲጠቅስ “ገደማ” የሚለውን መግለጫ ተጠቅሟል። በሁለቱ ዘገባዎች መካከል የሰዓት ልዩነት ሊፈጠር የቻለው በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል። በመጨረሻም ዘገባውን ከአሥርተ ዓመታት በኋላ የጻፈው ዮሐንስ፣ ማርቆስ ከጠቀሰው የተለየ ሰዓት መጥቀሱ ዮሐንስ የማርቆስን ዘገባ ቀጥታ ገልብጦ እንዳልጻፈ ያሳያል።
(ማርቆስ 16:8) እነሱም ከመቃብሩ ከወጡ በኋላ በአድናቆት ተውጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ሸሽተው ሄዱ። ከፍርሃታቸውም የተነሳ ለማንም ምንም ነገር አልተናገሩም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ማርቆስ 16:8
ከፍርሃታቸውም የተነሳ፦ የማርቆስን የመጨረሻ ክፍል ከያዙት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል በጣም በቆዩት ላይ የወንጌል ዘገባው የሚደመደመው በቁጥር 8 ላይ ባለው ሐሳብ ነው። አንዳንዶች ዘገባው ድንገት ቁርጥ እንዳለ ስለሚሰማቸው የመጀመሪያው ጽሑፍ በዚህ ሐሳብ ሊደመደም እንደማይችል ይናገራሉ። ሆኖም በጥቅሉ ሲታይ ማርቆስ እጥር ምጥን ያለ የአጻጻፍ ስልት ስለሚከተል እንዲህ ብሎ መናገሩ ላያስኬድ ይችላል። በተጨማሪም ጀሮምና ዩሲቢየስ የተባሉት በአራተኛው መቶ ዘመን የኖሩ ምሁራን፣ የመጀመሪያው ጽሑፍ “ከፍርሃታቸውም የተነሳ” በሚሉት ቃላት እንደሚደመደም ጠቁመዋል።
ከቁጥር 8 በኋላ ረጅም ወይም አጭር መደምደሚያ የሚያካትቱ በርካታ በግሪክኛ የተዘጋጁ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎችና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎሙ ቅጂዎች ይገኛሉ። ረጅሙ መደምደሚያ (12 ተጨማሪ ቁጥሮችን ይዟል) በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በተዘጋጁት በኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ፣ በኮዴክስ ኢፍራይሚ ሲሪ ሬስክሪፕተስና ኮዴክስ ቤዜ ካንታቢይሪኤንሲስ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በላቲን ቩልጌት፣ በኪዩርተኒያን ሲሪያክና በሲሪያክ ፐሺታ ላይ ይገኛል። ሆኖም ቀደም ብለው ይኸውም በአራተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጁ ሁለት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎች ላይ ማለትም በኮዴክስ ሲናይቲከስ እና በኮዴክስ ቫቲካነስ ላይ አሊያም በአራተኛው ወይም በአምስተኛው መቶ ዘመን በተዘጋጀው ኮዴክስ ሲናይቲከስ ሲሪያከስ ላይ አይገኝም፤ በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የሳሂዲክ ኮፕቲክ ቅጂዎችም ላይ ቢሆን አይገኝም። በተመሳሳይም በአርመንኛና በጆርጂያኛ ከተዘጋጁት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የማርቆስ መጽሐፍ ቅጂዎች መካከል በጣም በቆዩት ላይ የወንጌል ዘገባው የሚደመደመው በቁጥር 8 ላይ ባለው ሐሳብ ነው።
ከጊዜ በኋላ የተዘጋጁ አንዳንድ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎችና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎሙ ቅጂዎች አጭሩን መደምደሚያ (ጥቂት አረፍተ ነገሮችን ብቻ የያዘ ነው) ያካትታሉ። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጀው ኮዴክስ ሬጂየስ ሁለቱንም መደምደሚያዎች ያካተተ ሲሆን አስቀድሞ የሚጠቅሰው አጭሩን መደምደሚያ ነው። ከእያንዳንዱ መደምደሚያ በፊት እነዚህ ዘገባዎች በአንዳንዶች ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው የሚገልጽ ሐሳብ ቢይዝም ሁለቱንም መደምደሚያዎች እንደማይደግፍ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።
አጭር መደምደሚያ
ከማር 16:8 በኋላ ያለው አጭር መደምደሚያ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አይደለም። እንደሚከተለው ይነበባል፦
እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው።
ረጅም መደምደሚያ
ከማር 16:8 በኋላ ያለው ረጅም መደምደሚያ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አይደለም። እንደሚከተለው ይነበባል፦
9 ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፣ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። 10 እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 11 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። 12 ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ 13 እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። 14 ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፣ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 15 እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል፣ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 17 ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶቸ ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ 18 እባቦችን ይይዛሉ፣ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ።
19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20 እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፣ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፣ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ማርቆስ 15:1-15) ወዲያውኑ በማለዳ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ማለትም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ተሰብስበው ተማከሩ፤ ኢየሱስንም አስረው በመውሰድ ለጲላጦስ አስረከቡት። 2 ጲላጦስም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው። 3 የካህናት አለቆቹ ግን በእሱ ላይ በርካታ ክስ መደርደራቸውን ቀጠሉ። 4 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “ምንም መልስ አትሰጥም? በስንት ነገር እየከሰሱህ እንዳሉ ተመልከት” ሲል እንደገና ጠየቀው። 5 ሆኖም ኢየሱስ ምንም ተጨማሪ መልስ አልሰጠም፤ በመሆኑም ጲላጦስ ተገረመ። 6 ጲላጦስ ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ ይፈታልን ብለው የጠየቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። 7 በወቅቱ፣ በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ሰው ገድለው ከታሰሩ ዓመፀኞች መካከል በርባን የሚባል ሰው ይገኝ ነበር። 8 ሕዝቡም መጥተው ጲላጦስ እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ ይጠይቁት ጀመር። 9 እሱም መልሶ “የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 10 ጲላጦስ ይህን ያለው የካህናት አለቆች አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው። 11 ይሁንና የካህናት አለቆቹ በኢየሱስ ምትክ በርባንን ይፈታላቸው ዘንድ እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሳሱ። 12 ጲላጦስም እንደገና መልሶ “እንግዲያው የአይሁዳውያን ንጉሥ የምትሉትን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው። 13 እነሱም “ይሰቀል!” ብለው እንደገና ጮኹ። 14 ሆኖም ጲላጦስ “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ የባሰ ጮኹ። 15 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ሕዝቡን ለማስደሰት ስለፈለገ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ካስገረፈው በኋላ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።
ከሰኔ 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 1
“ማርያም ትሕትና በማሳየት ረገድ የተወችውን ምሳሌ ተከተሉ”
(ሉቃስ 1:38) በዚህ ጊዜ ማርያም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ።
“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!”
12 ማርያም፣ ለገብርኤል “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት የሰጠችውን ትሕትና እና ታዛዥነት የሚንጸባረቅበት መልስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ያውቁታል። (ሉቃስ 1:38) አንዲት ባሪያ ከአገልጋዮች ሁሉ ያነሰች ተደርጋ ትታይ የነበረ ሲሆን መላ ሕይወቷ በጌታዋ እጅ ነበር። ማርያም ጌታዋ የሆነውን ይሖዋን የምትመለከተው እንዲህ ነበር። ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላት፣ ለታማኝ አገልጋዮቹ ታማኝ እንደሚሆን እንዲሁም ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት እንደሚባርክላት ታውቅ ነበር።—መዝ. 18:25
(ሉቃስ 1:46-55) ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ 47 መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል፤ 48 ምክንያቱም የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷል። እነሆ፣ ከአሁን ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ደስተኛ ይሉኛል፤ 49 ምክንያቱም ኃያል የሆነው አምላክ ታላላቅ ነገሮች አድርጎልኛል፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ 50 ምሕረቱም በሚፈሩት ሁሉ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። 51 በክንዱም ታላላቅ ሥራዎች አከናውኗል፤ በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል። 52 ኃያላን ሰዎችን ከዙፋናቸው አውርዷል፤ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓል፤ 53 የተራቡትን በመልካም ነገሮች አጥግቧል፤ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል። 54 ምሕረቱን በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቷል፤ 55 ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረት ለማሳየት ነው።”
“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!”
15 በመቀጠል ደግሞ ማርያም ተናገረች። ማርያም የተናገረችው ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። (ሉቃስ 1:46-55ን አንብብ።) ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው ከሚገኙት ማርያም ከተናገረቻቸው ሐሳቦች ሁሉ ረጅሙ ሲሆን ስለ እሷም ብዙ ነገር ይጠቁመናል። ማርያም፣ የመሲሑ እናት እንድትሆን ለተሰጣት መብት ይሖዋን ለማወደስ የተጠቀመችባቸው ቃላት የአመስጋኝነትና የአድናቆት መንፈስ እንዳላት ያሳያሉ። ይሖዋ ትዕቢተኞችንና ኃያላንን እንደሚያዋርድ እንዲሁም እሱን ለማገልገል የሚጥሩ የተናቁና ምስኪን ሰዎችን እንደሚረዳ የተናገረችው ሐሳብ የእምነቷን ጥንካሬ ያሳያል። ከዚህም በላይ ምን ያህል እውቀት እንደነበራት ይጠቁማል። እዚህ ላይ ማርያም ከ20 ጊዜ በላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሳ እንደተናገረች ይገመታል!
16 ማርያም በአምላክ ቃል ላይ በጥልቅ ታሰላስል እንደነበር ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ትሑት ስለነበረች የራሷን ሐሳብ ከመናገር ይልቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት ለመጥቀስ መርጣለች። በወቅቱ በማህፀኗ ውስጥ የነበረው ልጅም ካደገ በኋላ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ብሎ በመናገር የእሷ ዓይነት መንፈስ እንዳለው አሳይቷል። (ዮሐ. 7:16) እኛም ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘እኔስ ለአምላክ ቃል እንዲህ ያለ አክብሮት አለኝ? ወይስ የራሴን አመለካከትና ሐሳብ መናገር ይቀናኛል?’ ማርያም በዚህ ረገድ ያላት አቋም ግልጽ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 1:69) ደግሞም በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድ አስነስቶልናል፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 1:69
የመዳን ቀንድ፦ ወይም “ኃያል አዳኝ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእንስሳት ቀንድ አብዛኛውን ጊዜ ብርታትን፣ ማሸነፍንና ድል መንሳትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (1ሳሙ 2:1፤ መዝ 75:4, 5, 10፤ 148:14 ግርጌዎች) በተጨማሪም ጻድቅም ሆኑ ክፉ ገዢዎች ወይም በመግዛት ላይ ያሉ ሥርወ መንግሥታት በቀንድ የተመሰሉ ሲሆን ድል መቀዳጀታቸው ደግሞ በቀንድ ከመግፋት ጋር ተመሳስሏል። (ዘዳ 33:17፤ ዳን 7:24፤ 8:2-10, 20-24) “የመዳን ቀንድ” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ መሲሑ የማዳን ኃይል እንዳለው ማለትም ኃያል አዳኝ እንደሆነ ይጠቁማል።
(ሉቃስ 1:76) ደግሞም አንተ ሕፃን፣ መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በይሖዋ ፊት ስለምትሄድ የልዑሉ ነቢይ ትባላለህ፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 1:76
ቀድመህ በይሖዋ ፊት ስለምትሄድ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ‘ቀድሞ በይሖዋ ፊት እንደሚሄድ’ የተገለጸው የአባቱ ወኪል የሆነውና በአባቱ ስም የሚመጣው የኢየሱስ መንገድ ጠራጊ ስለሆነ ነው።—ዮሐንስ 5:43፤ 8:29፤ ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀውን በይሖዋ የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
በይሖዋ፦ በዚህ ጥቅስ ሁለተኛ ክፍል ላይ የሚገኙት ዘካርያስ የተናገራቸው ትንቢታዊ ቃላት በኢሳ 40:3 እና በሚል 3:1 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ያንጸባርቃሉ፤ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ መለኮታዊውን ስም የሚወክሉትን አራቱን የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት (በአማርኛ የሐወሐ በሚሉት ፊደላት ይጻፋሉ) ይዟል። በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ኪርዮስ (ጌታ) የሚሉ ቢሆንም ጥቅሱ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያለውን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ ከመሆኑ አንጻር መለኮታዊው ስም እዚህ ቦታ ላይ ሊገባ ችሏል። በተጨማሪም እዚህ ጥቅስ ላይም ሆነ በሉቃስ ምዕራፍ 1 ላይ ኪርዮስ የሚለው ቃል በሚገኝባቸው በርካታ ቦታዎች ላይ ከቃሉ በፊት ጠቃሽ አመልካች እንዳልተጨመረ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ በመደበኛው የግሪክኛ ሰዋስው ሕግ መሠረት ጠቃሽ አመልካች መጨመር የነበረበት ቢሆንም አለመጨመሩ ኪርዮስ የሚለውን ቃል ልክ እንደ ተጸውኦ ስም ያደርገዋል። ከዚህም ሌላ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ አምላክን እየጠቀሱ እንዳለ ለማመልከት እንደ ይሖዋ፣ ያህቬህ፣ ያህዌህ፣ יהוה (የሐወሐ፣ ወይም የይሖዋ ስም የሚጻፍባቸው አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት) የሚሉትን ቃላት ይጠቀማሉ አሊያም ጌታ እና አዶናይ የሚሉትን ቃላት ለየት ባለ የፊደል አጣጣል ይጽፋሉ። ይህን የሚደግፉ በርካታ የማመሣከሪያ ጽሑፎች አሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 1:46-66) ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ 47 መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል፤ 48 ምክንያቱም የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷል። እነሆ፣ ከአሁን ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ደስተኛ ይሉኛል፤ 49 ምክንያቱም ኃያል የሆነው አምላክ ታላላቅ ነገሮች አድርጎልኛል፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ 50 ምሕረቱም በሚፈሩት ሁሉ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። 51 በክንዱም ታላላቅ ሥራዎች አከናውኗል፤ በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል። 52 ኃያላን ሰዎችን ከዙፋናቸው አውርዷል፤ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓል፤ 53 የተራቡትን በመልካም ነገሮች አጥግቧል፤ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል። 54 ምሕረቱን በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቷል፤ 55 ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረት ለማሳየት ነው።” 56 ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያህል ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። 57 ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። 58 ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ይሖዋ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰምተው የደስታዋ ተካፋዮች ሆኑ። 59 በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። 60 እናትየው ግን መልሳ “አይሆንም! ዮሐንስ ይባል” አለች። 61 በዚህ ጊዜ “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። 62 ከዚያም አባቱን ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። 63 እሱም የእንጨት ጽላት እንዲያመጡለት ጠየቀና “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደነቁ። 64 ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈቶ መናገር ጀመረ፤ አምላክንም አወደሰ። 65 ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በፍርሃት ተዋጡ፤ የሆነውም ነገር ሁሉ በተራራማው የይሁዳ አገር በሙሉ ይወራ ጀመር። 66 ይህን የሰሙም ሁሉ “የዚህ ሕፃን መጨረሻ ምን ይሆን?” በማለት ነገሩን በልባቸው ያዙ። የይሖዋ እጅ ከእሱ ጋር እንደሆነ በግልጽ ይታይ ነበርና።
ከሰኔ 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 2–3
“ልጆች—መንፈሳዊ እድገት እያደረጋችሁ ነው?”
(ሉቃስ 2:41, 42) ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ልማድ ነበራቸው። 42 ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ እንደተለመደው በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 2:41
ወላጆቹ . . . ልማድ ነበራቸው፦ ሕጉ ሴቶች በፋሲካ በዓል ላይ እንዲገኙ አያዝም። ሆኖም ማርያም በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም በየዓመቱ በሚደረገው ጉዞ ላይ ከዮሴፍ ጋር አብራ የመሄድ ልማድ ነበራት። (ዘፀ 23:17፤ 34:23) ዮሴፍና ማርያም በቁጥር እየጨመረ የሚሄደውን ቤተሰባቸውን ይዘው 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ያለውን የደርሶ መልስ ጉዞ በየዓመቱ ያደርጉ ነበር።
(ሉቃስ 2:46, 47) በመጨረሻም ከሦስት ቀን በኋላ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት። 47 በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 2:46, 47
ሲጠይቃቸው፦ ኢየሱስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ከሰጡት ምላሽ መረዳት እንደሚቻለው የኢየሱስ ጥያቄዎች አንድ ትንሽ ልጅ እንደሚጠይቀው ያሉ የማወቅ ጉጉትን ለማርካት የቀረቡ ጥያቄዎች አልነበሩም። (ሉቃስ 2:47) “ሲጠይቃቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአንዳንድ አገባቡ በፍርድ ምርመራ ጊዜ የሚቀርቡ ጥያቄዎችንና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሊጨምር ይችላል። (ማቴ 27:11፤ ማር 14:60, 61፤ 15:2, 4፤ ሥራ 5:27) የታሪክ ምሁራን የተለያዩ በዓላት ተከብረው ካበቁ በኋላ አንዳንድ የታወቁ የሃይማኖት መሪዎች እዚያው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆይተው ሰፋፊ ከሆኑት በረንዳዎች በአንዱ ላይ ሆነው የማስተማር ልማድ እንደነበራቸው ይናገራሉ። ሰዎችም ለማዳመጥና ጥያቄ ለመጠየቅ እግራቸው አጠገብ ይቀመጡ ነበር።
ተደንቀው፦ “ተደንቀው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ የሰዎቹ አግራሞት ቀጣይነት ያለው ወይም ተደጋጋሚ እንደሆነ ሊያመለክት ይችላል።
(ሉቃስ 2:51, 52) ከዚያም ኢየሱስ አብሯቸው ወደ ናዝሬት ተመለሰ፤ እንደ ወትሮውም ይገዛላቸው ነበር። እናቱም የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በልቧ ትይዝ ነበር። 52 ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 2:51, 52
እንደ ወትሮውም ይገዛላቸው፦ ወይም “እንደ ወትሮው ለሥልጣናቸው ይገዛ፤ ይታዘዛቸው።” እዚህ ላይ የገባው ቀጣይ የሆነ ድርጊትን የሚያመለክተው የግሪክኛ ግስ ኢየሱስ ስለ አምላክ ቃል ባለው እውቀት በቤተ መቅደሱ ያሉ አስተማሪዎችን ካስደመመ በኋላ ቤቱ ሲመለስ ለወላጆቹ በትሕትና ራሱን እንዳስገዛ ይጠቁማል። የኢየሱስ ታዛዥነት ሌሎች ልጆች ሁሉ ካሳዩት ታዛዥነት የላቀ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም የእሱ ታዛዥነት ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ እንደፈጸመ አሳይቷል።—ዘፀ 20:12፤ ገላ 4:4
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 2:14) “በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 2:14
በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን፦ በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች “ለምድር ሰላም፣ ለሰውም ሞገስ ይሁን” የሚሉ ሲሆን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን አገላለጽ ይጠቀማሉ። ሆኖም ይበልጥ የቆዩና አስተማማኝ የሆኑ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች የሚደግፉት በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን አገላለጽ ነው። መላእክት የተናገሩት ይህ ሐሳብ አምላክ የትኛውም ዓይነት ዝንባሌ ላላቸው ወይም የትኛውንም ዓይነት ድርጊት ለሚፈጽሙ ሰዎች ሞገሱን እንደሚያሳይ የሚጠቁም አይደለም። አምላክ ሞገሱን የሚያሳየው በእሱ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳላቸው ለሚያሳዩና የልጁ ተከታዮች ለሆኑ ሰዎች ነው።—በዚህ ጥቅስ ሥር የሚገኘውን አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች፦ ዩዶኪአ የሚለው የግሪክኛ ቃል “በጎ ፈቃድ፣ ደስ መሰኘት፣ መቀበል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ተዛማጅነት ያለው ዩዶኪኦ የሚለው ግስ በማቴ 3:17፤ በማር 1:11 እና በሉቃስ 3:22 ላይ በሚገኘው አምላክ ልጁ ከተጠመቀ በኋላ ለእሱ በተናገረው ሐሳብ ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። (ለማቴ 3:17 የተዘጋጁትን ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች ተመልከት፤ ማር 1:11) ይህ ግስ “መቀበል፤ መደሰት፤ በሞገስ ዓይን መመልከት፤ በጣም ደስ መሰኘት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ያስተላልፋል። ከዚህ አንጻር ‘አምላክ ሞገስ የሚያሳያቸው ሰዎች’ (አንትሮፖይስ ዩዶኪያስ) የሚለው አገላለጽ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውንና የእሱን በጎ ፈቃድ ያገኙ ሰዎችን የሚያመለክት ሲሆን “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች፤ አምላክ በጣም ደስ የሚሰኝባቸው ሰዎች” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም መላእክት የተናገሩት ይህ ሐሳብ አምላክ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የሚያሳየውን ሞገስ ሳይሆን በእሱ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳላቸው በማሳየትና የልጁ ተከታዮች በመሆን እሱን ደስ ለሚያሰኙት ሰዎች የሚያሳየውን ሞገስ ያመለክታል። ዩዶኪአ የሚለው የግሪክኛ ቃል በአንዳንድ አገባቡ ሰዎች የሚያሳዩትን ሞገስ (ሮም 10:1፤ ፊልጵ 1:15) ሊያመለክት ቢችልም በአብዛኛው የሚሠራበት አምላክ ከሚያሳየው ሞገስ ወይም በጎ ፈቃድ አሊያም በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ካለው መንገድ ጋር በተያያዘ ነው። (ማቴ 11:26፤ ሉቃስ 10:21፤ ኤፌ 1:5, 9፤ ፊልጵ 2:13፤ 2ተሰ 1:11) የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በመዝ 51:18 [50:20, LXX] ላይ ይህን ቃል ከአምላክ “በጎ ፈቃድ” ጋር በተያያዘ ተጠቅሞበታል።
(ሉቃስ 3:23) ኢየሱስ ሥራውን ሲጀምር 30 ዓመት ገደማ ሆኖት ነበር፤ ሕዝቡም የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር፤ ዮሴፍ የሄሊ ልጅ፣
ይህን ያውቁ ኖሯል?
የዮሴፍ አባት ማን ነው?
ናዝሬት ውስጥ አናጺ የነበረው ዮሴፍ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ነው። ይሁንና የዮሴፍ አባት ማን ነው? በማቴዎስ ወንጌል ላይ ያለው የኢየሱስ የዘር ሐረግ ያዕቆብ ስለሚባል አንድ ሰው የሚናገር ሲሆን የሉቃስ ዘገባ ግን “ዮሴፍ የሄሊ ልጅ” መሆኑን ይናገራል። ይህ ልዩነት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?—ሉቃስ 3:23፤ ማቴዎስ 1:16
የማቴዎስ ዘገባ “ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ” የሚል ሲሆን እዚህ ላይ የተሠራበት ግሪክኛ ቃል ያዕቆብ የዮሴፍ ወላጅ አባት መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል። በመሆኑም ማቴዎስ የዮሴፍን የዘር ሐረግ የቆጠረው በንጉሣዊው የዳዊት መስመር በኩል ነው፤ ዮሴፍ ያሳደገው ልጅ ማለትም ኢየሱስ ዙፋኑን የመውረስ ሕጋዊ መብት የሚያገኘው በዚህ መሠረት ይሆናል።
በሌላ በኩል ግን የሉቃስ ዘገባ “ዮሴፍ የሄሊ ልጅ” ይላል። እዚህ ላይ የገባው “ልጅ” የሚለው ቃል “አማች” በሚል ሊወሰድም ይችላል። ሉቃስ 3:27 ላይ ተመሳሳይ ዘገባ የሚገኝ ሲሆን የሰላትያል ትክክለኛ አባት ኢኮንያን ሆኖ ሳለ ዝርዝሩ ላይ የሰፈረው ግን “የኔሪ ልጅ” ተብሎ ነው። (1 ዜና መዋዕል 3:17፤ ማቴዎስ 1:12) ሰላትያል በስም ያልተጠቀሰችን የኔሪን ሴት ልጅ በማግባቱ የኔሪ አማች ሳይሆን አይቀርም። ዮሴፍም የሄሊን ሴት ልጅ ይኸውም ማርያምን ስላገባ በተመሳሳይ ሁኔታ የሄሊ “ልጅ” ሊባል ይችላል። ስለዚህ ሉቃስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ የቆጠረው ‘ከሥጋዊ ዘር’ አንጻር ማለትም በወላጅ እናቱ በማርያም በኩል ነው። (ሮም 1:3) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ያቀርብልናል፤ ሁለቱም ደግሞ ጠቃሚ መረጃ ይዘዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 2:1-20) በዚያ ዘመን፣ አውግስጦስ ቄሳር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲመዘገብ አዋጅ አወጣ። 2 (ይህ የመጀመሪያ ምዝገባ የተካሄደው ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዢ በነበረበት ጊዜ ነው።) 3 ሁሉም ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ። 4 ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለነበር በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ በይሁዳ ወዳለች ቤተልሔም ተብላ ወደምትጠራ የዳዊት ከተማ ወጣ። 5 ለመመዝገብ የሄደውም በታጨችለት መሠረት ካገባትና የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከማርያም ጋር ነበር። 6 በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ። 7 የበኩር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅም ወለደች፤ በእንግዶች ማረፊያም፣ ቦታ ስላላገኙ ልጁን በጨርቅ ጠቅልላ በግርግም ውስጥ አስተኛችው። 8 በዚያው ክልል፣ ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። 9 በድንገት የይሖዋ መልአክ መጥቶ በፊታቸው ቆመ፤ የይሖዋም ክብር በዙሪያቸው አንጸባረቀ፤ እነሱም በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። 10 መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ እነሆ፣ ለሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ 11 በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋልና፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። 12 ይህም ምልክት ይሁናችሁ፦ አንድ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” 13 በድንገት ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ አምላክንም እያመሰገኑ እንዲህ አሉ፦ 14 “በሰማያት ለአምላክ ክብር ይሁን፤ በምድርም አምላክ ሞገስ ለሚያሳያቸው ሰዎች ሰላም ይሁን።” 15 መላእክቱም ከእነሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ እረኞቹ እርስ በርሳቸው “አሁኑኑ ወደ ቤተልሔም ሄደን ይሖዋ በገለጠልን መሠረት በዚያ የተፈጸመውን ነገር ማየት አለብን” ተባባሉ። 16 በፍጥነትም ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኟቸው፤ ሕፃኑም በግርግም ተኝቶ ነበር። 17 ይህን ባዩ ጊዜ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን መልእክት አወሩ። 18 ይህን የሰሙ ሰዎች ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ 19 ማርያም ግን የሰማቻቸውን ነገሮች በውስጧ ይዛ በልቧ ታሰላስል ነበር። 20 እረኞቹም የሰሙትና ያዩት ነገር ሁሉ ልክ እንደተነገራቸው ሆኖ ስላገኙት አምላክን እያከበሩና እያወደሱ ተመለሱ።
ከሰኔ 25–ሐምሌ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 4–5
“ልክ እንደ ኢየሱስ ፈተናዎችን ተቋቋሙ”
(ሉቃስ 4:1-4) ከዚያም ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም ሳለ መንፈስ ይመራው ነበር፤ 2 በዚያም 40 ቀን ቆየ፤ ዲያብሎስም ፈተነው። በእነዚህም ቀናት ምንም ስላልበላ መጨረሻ ላይ ተራበ። 3 በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህ ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን እዘዝ” አለው። 4 ኢየሱስ ግን “‘ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት።
ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ
8 ሰይጣን፣ ኢየሱስን በምድረ በዳ በፈተነው ወቅትም ይህንኑ ዘዴ ተጠቅሟል። ኢየሱስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሞ በተራበበት ወቅት ሰይጣን ሊፈትነው ሞከረ፤ ዲያብሎስ በዚህ ወቅት የተጠቀመው ኢየሱስ ምግብ ለማግኘት ያለውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። ኢየሱስን “እስቲ የአምላክ ልጅ ከሆንክ ይህ ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን እዘዝ” አለው። (ሉቃስ 4:1-3) ኢየሱስ ሁለት አማራጮች ነበሩት፦ ተአምራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ረሃቡን ማስታገሥ አሊያም ኃይሉን በዚህ መንገድ ላለመጠቀም መምረጥ ይችላል። ኢየሱስ የራሱን ፍላጎት ለማርካት ኃይሉን ሊጠቀምበት እንደማይገባ ያውቃል። ተርቦ የነበረ ቢሆንም ረሃቡን ከማስታገሥ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም’ ተብሎ ተጽፏል” በማለት መለሰ።—ማቴ. 4:4፤ ሉቃስ 4:4
(ሉቃስ 4:5-8) ቀጥሎም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍ ያለ ቦታ አወጣውና የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። 6 ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ይህ ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህ መንግሥታት ክብር ተሰጥቶኛል፤ እኔ ደግሞ ለፈለግኩት መስጠት ስለምችል ለአንተ እሰጥሃለሁ። 7 ስለዚህ አንድ ጊዜ በፊቴ ተደፍተህ ብታመልከኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።” 8 ኢየሱስም መልሶ “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው።
ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ
10 ሰይጣን፣ ኢየሱስን ለማታለልስ በዚህ ዘዴ የተጠቀመው እንዴት ነው? “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ [ለኢየሱስ] በቅጽበት አሳየው፤ ከዚያም እንዲህ አለው፦ ‘ይህን ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህን መንግሥታት ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ።’” (ሉቃስ 4:5, 6) ኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ ቃል በቃል በቅጽበት ሊያያቸው አይችልም፤ ሆኖም ሰይጣን እነዚህን መንግሥታት ለኢየሱስ በራእይ መልክ በማሳየት ሊማርከው እንደሚችል አስቦ መሆን አለበት። ከዚያም “አንድ ጊዜ በፊቴ ተደፍተህ ብታመልከኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል” በማለት ዓይን አውጥቶ ጠየቀው። (ሉቃስ 4:7) ኢየሱስ ግን ሰይጣን የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ፈጽሞ ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠ። “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው።—ሉቃስ 4:8
(ሉቃስ 4:9-12) ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት ላይ አቁሞ እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ 10 እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘አንተን እንዲጠብቁ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ 11 እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’” 12 ኢየሱስም መልሶ “‘አምላክህን ይሖዋን አትፈታተነው’ ተብሏል” አለው።
nwtsty ሚዲያ
የቤተ መቅደሱ አናት
ሰይጣን ኢየሱስን ቃል በቃል “በቤተ መቅደሱ አናት ላይ” ካቆመው በኋላ ራሱን ወደ ታች እንዲወረውር ነግሮት ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ኢየሱስ የትኛው ቦታ ላይ ቆሞ ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት አይታወቅም። “ቤተ መቅደስ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የቤተ መቅደሱን ሕንፃዎች በሙሉ ሊያመለክት ስለሚችል ኢየሱስ የቆመው የቤተ መቅደሱ ደቡብ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ (1) ሊሆን ይችላል። ወይም ከቤተ መቅደሱ ሕንፃዎች መካከል በአንዱ ጫፍ ላይ ቆሞ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እስካላዳነው ድረስ ከእነዚህ ቦታዎች ከየትኛውም ላይ ቢወድቅ መሞቱ እንደማይቀር የታወቀ ነው።
ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ አስቡ
12 ከሔዋን በተቃራኒ ኢየሱስ በትሕትና ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! ሰይጣን፣ ኢየሱስ ሌሎችን ለማስደመም ሲል አምላክን የሚፈታተን ነገር እንዲፈጽም በማድረግ ሊፈትነው ሞከረ፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ስለ መፈጸም ማሰብ እንኳ አልፈለገም። ሰይጣን ያለውን ነገር ቢያደርግ የትዕቢት ዝንባሌ እንዳለው የሚጠቁም ይሆን ነበር። ኢየሱስ ግን “‘አምላክህን ይሖዋን አትፈታተነው’ ተብሏል” በማለት ግልጽና የማያሻማ መልስ ሰጠ።—ሉቃስ 4:9-12ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 4:17) የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልልም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም ተርትሮ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፦
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 4:17
የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልልም፦ በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል 17 ብራናዎችን በመገጣጠም የተሠራ ነው፤ ይህ ጥቅልል 7.3 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 54 ረድፎች አሉት። በናዝሬት ባለው ምኩራብ የነበረው ጥቅልልም ተመሳሳይ ርዝመት ሳይኖረው አይቀርም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ቅዱሳን መጻሕፍት በምዕራፎችና ቁጥሮች ስላልተከፋፈሉ ኢየሱስ ማንበብ የሚፈልገውን ክፍል ፈልጎ ማግኘት ይጠበቅበት ነበር። ያም ሆኖ የሚፈልገው ሐሳብ የተጻፈበትን ቦታ ማግኘቱ የአምላክን ቃል ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ያሳያል።
(ሉቃስ 4:25) እውነቱን ልንገራችሁ፦ ለምሳሌ በኤልያስ ዘመን ሰማይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋና በምድሪቱ ሁሉ ላይ ጽኑ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 4:25
ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር፦ አንደኛ ነገሥት 18:1 ኤልያስ ድርቁ እንደሚያበቃ የተናገረው “በሦስተኛው ዓመት” እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም አንዳንዶች ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ በ1 ነገሥት ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር እንደሚጋጭ ይሰማቸዋል። ሆኖም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኘው ዘገባ ድርቁ ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዳበቃ አይጠቁምም። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው “በሦስተኛው ዓመት” የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው ኤልያስ ድርቅ እንደሚከሰት ለአክዓብ መጀመሪያ ላይ ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ወቅት ነው። (1ነገ 17:1) ኤልያስ ይህን ሐሳብ የተናገረው አብዛኛውን ጊዜ ለስድስት ወራት ገደማ የሚቆየው ሆኖም ከተለመደው ረዘም ላለ ጊዜ ሊዘልቅ የሚችለው ደረቁ ወቅት ከጀመረ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም ኤልያስ “በሦስተኛው ዓመት” ከአክዓብ ጋር በድጋሚ ከተነጋገረ በኋላ ድርቁ ወዲያውኑ አላበቃም፤ ከዚህ ይልቅ ድርቁ ያበቃው ኤልያስ ከዚያ ቀጥሎ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ እሳት እንዲወርድ ካደረገ በኋላ ነው። (1ነገ 18:18-45) በመሆኑም እዚህ ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብም ሆነ የክርስቶስ ወንድም በያዕ 5:17 ላይ ያሰፈረው ተመሳሳይ ሐሳብ በ1ነገ 18:1 ላይ ከተጠቀሰው ጊዜ ጋር አይጋጭም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 4:31-44) ከዚያም በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሄደ። እዚያም በሰንበት ሕዝቡን ያስተምር ነበር፤ 32 በሥልጣን ይናገር ስለነበረም ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ። 33 በምኩራቡም ውስጥ ርኩስ መንፈስ ማለትም ጋኔን ያደረበት አንድ ሰው ነበር፤ ሰውየውም በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ጮኸ፦ 34 “እንዴ! የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን? የመጣኸው ልታጠፋን ነው? ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ ነህ።” 35 ሆኖም ኢየሱስ “ዝም በል፤ ከእሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ፊት ከጣለው በኋላ ምንም ሳይጎዳው ለቆት ወጣ። 36 በዚህ ጊዜ ሁሉም በመገረም “እንዴ! ይህ ምን ዓይነት አነጋገር ነው? ርኩሳን መናፍስትን በሥልጣንና በኃይል ያዛል፤ እነሱም ታዘው ይወጣሉ!” ሲሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር። 37 ስለ ኢየሱስ የሚወራው ወሬም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተዳረሰ። 38 ኢየሱስ ከምኩራቡ ከወጣ በኋላ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት ኃይለኛ ትኩሳት ይዟት እየተሠቃየች ነበር፤ እነሱም እንዲረዳት ለመኑት። 39 እሱም አጠገቧ ቆመና ጎንበስ ብሎ ትኩሳቱን ገሠጸው፤ ትኩሳቱም ለቀቃት። ወዲያውም ተነስታ ታገለግላቸው ጀመር። 40 ፀሐይ ስትጠልቅም ሰዎች በተለያየ በሽታ የተያዙ ሕመምተኞቻቸውን ወደ እሱ አመጡ። እሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው። 41 አጋንንትም “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” እያሉና እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ። እሱ ግን ገሠጻቸው፤ ክርስቶስ መሆኑንም አውቀው ስለነበር እንዳይናገሩ ከለከላቸው። 42 በነጋም ጊዜ ወጥቶ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ። ሕዝቡ ግን ፈልገው ፈላልገው ያለበት ቦታ ድረስ መጡ፤ እንዳይሄድባቸውም ለመኑት። 43 እሱ ግን “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” አላቸው። 44 በመሆኑም በይሁዳ ምኩራቦች መስበኩን ቀጠለ።