የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ነሐሴ 2019
ከነሐሴ 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ጢሞቴዎስ 1-4
“አምላክ . . . የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም”
(2 ጢሞቴዎስ 1:7) አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።
ወጣቶች—እድገታችሁ በግልጽ እንዲታይ አድርጉ
9 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ለመርዳት ሲል እንዲህ ብሎታል፦ “አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም።” (2 ጢሞ. 1:7) “ጤናማ አእምሮ” ሲባል ማስተዋል በታከለበት መንገድ ማሰብና ነገሮችን ማመዛዘን ማለት ነው። ሁኔታዎች እንዳሰብከው ባይሆኑም እንኳ ያጋጠሙህን ችግሮች ተቋቁመህ መኖርንም ይጨምራል። ክርስቲያናዊ ጉልምስናን ያላዳበሩ አንዳንድ ወጣቶች አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የፍርሃት መንፈስ ሲያንጸባርቁ ይታያሉ፤ እነዚህ ወጣቶች ጊዜያቸውን በእንቅልፍ በማሳለፍ ወይም ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ዕፆች በመውሰድና የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ በመጠጣት፣ አዘውትረው ጭፈራ ቤት በመሄድ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸም ካጋጠማቸው ችግር ለመሸሽ ይጥራሉ። እኛ ክርስቲያኖች ግን “አምላካዊ ያልሆነ ምግባርንና ዓለማዊ ምኞቶችን ክደን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” ተመክረናል።—ቲቶ 2:12
(2 ጢሞቴዎስ 1:8) ስለሆነም ስለ ጌታችን መመሥከር አያሳፍርህ፤ ደግሞም ለእሱ ስል እስረኛ በሆንኩት በእኔ አትፈር፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ኃይል በመታመን አንተም ለምሥራቹ የበኩልህን መከራ ተቀበል።
‘ደፋሮችና ጠንካሮች ሁኑ!’
7 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት “እግዚአብሔር የኃይል . . . መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት . . . አትፈር” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7, 8፤ ማርቆስ 8:38) እነዚህን ቃላት በምናነብበት ጊዜ ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ስለ እምነቴ አፍራለሁ? ወይስ ደፋር ነኝ? በሥራ ቦታዬ ወይም ትምህርት ቤት ለማገኛቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን እነግራቸዋለሁ? ወይስ ለመደበቅ እሞክራለሁ? ከሌሎች የተለየሁ ሆኜ መታየት ያሳፍረኛል? ወይስ ከይሖዋ ጋር ባለኝ ዝምድና ተለይቼ ብታወቅ ያኮራኛል?’ ምሥራቹን መስበክን ወይም በሰዎች ዘንድ የማይወደድ እምነት መያዝን በተመለከተ አፍራሽ ስሜት ያለው ማንም ቢኖር ይሖዋ ለኢያሱ “ጽና፣ እጅግ በርታ” በማለት የሰጠውን ምክር ያስታውስ። ትልቁን ቦታ የሚይዘው የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን የሚሰጡት አስተያየት ሳይሆን የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ አመለካከት መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ።—ገላትያ 1:10
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር እንደመሆንህ መጠን አንተም በበኩልህ መከራ ተቀበል። 4 ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም።
እውነተኛ የሆነውን ሀብት መፈለግ
13 ጢሞቴዎስ የእምነት ሰው ነበር። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር” ብሎ ከጠራው በኋላ “ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ አያጠላልፍም” ብሎታል። (2 ጢሞ. 2:3, 4) በዛሬው ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ጨምሮ በምድር ላይ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች በሙሉ፣ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ይጥራሉ። የማስታወቂያው ኢንዱስትሪና በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ነገሮች የሚያሳድሩባቸውን ጫና ይቋቋማሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ተበዳሪ የአበዳሪው ባሪያ ነው’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አይዘነጉም። (ምሳሌ 22:7) ሰይጣን፣ እሱ ለሚቆጣጠረው የንግድ ሥርዓት ባሪያ ሆነን ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን በሙሉ ስናባክን የማየትን ያህል የሚያስደስተው ነገር የለም። የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ለዓመታት ዕዳ ውስጥ እንድንዘፈቅ ሊያደርጉን ይችላሉ። አንዳንዶች ቤት ወይም መኪና ለመግዛት፣ ከፍተኛ ትምህርት ለመማር ሌላው ቀርቶ ድል ያለ ሠርግ ለመደገስ ሲሉ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ባለመግባት እንዲሁም ወጪዎቻችንን በመቀነስ አርቆ አሳቢ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን፤ ይህን ስናደርግ ለዚህ ዓለም የንግድ ሥርዓት ሳይሆን ለይሖዋ ባሪያ መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 6:10
(2 ጢሞቴዎስ 2:23) በተጨማሪም ጠብ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ ሞኝነትና አላዋቂነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር ራቅ።
የይሖዋ ሕዝብ “ከክፋት ይራቅ”
10 በዛሬው ጊዜ ባለው የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ በአብዛኛው ክህደት አያጋጥምም። ያም ቢሆን ከየትም ይምጣ ከየት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ካጋጠመን ቆራጥ በመሆን እንዲህ ካለው ትምህርት ወዲያውኑ መራቅ ይኖርብናል። ከከሃዲዎች ጋር ፊት ለፊት በመነጋገርም ሆነ ድረ ገጻቸው ላይ አስተያየት በማስፈር አሊያም በሌላ መንገድ ክርክር መግጠም የጥበብ አካሄድ አይደለም። እንዲህ ያለ ውይይት የምናደርገው ግለሰቡን ለመርዳት አስበን ቢሆንም እንኳ ይህን ማድረግ እስከ አሁን ከተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ጋር የሚጋጭ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ከከሃዲዎች ሙሉ በሙሉ እንርቃለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ጢሞቴዎስ 1:1-18) በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚገኘውን ሕይወት በተመለከተ ከተገባው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ 2 ለተወዳጁ ልጄ ለጢሞቴዎስ፦ አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን። 3 የቀድሞ አባቶቼ እንዳደረጉት ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትንና በንጹሕ ሕሊና የማገለግለውን አምላክ አመሰግናለሁ፤ ደግሞም ሌት ተቀን አንተን ዘወትር በምልጃዬ አስታውሳለሁ። 4 እንባህን ሳስታውስ፣ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። 5 በአንተ ውስጥ ያለውን ግብዝነት የሌለበት እምነት አስታውሳለሁና፤ ይህ እምነት በመጀመሪያ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበር፤ ይሁንና በአንተም ውስጥ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። 6 ስለዚህ በአንተ ላይ እጄን በጫንኩበት ጊዜ የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ በቅንዓት እንድትጠቀምበት አሳስብሃለሁ። 7 አምላክ የኃይል፣ የፍቅርና የጤናማ አእምሮ መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 8 ስለሆነም ስለ ጌታችን መመሥከር አያሳፍርህ፤ ደግሞም ለእሱ ስል እስረኛ በሆንኩት በእኔ አትፈር፤ ከዚህ ይልቅ በአምላክ ኃይል በመታመን አንተም ለምሥራቹ የበኩልህን መከራ ተቀበል። 9 እሱ በእኛ ሥራ ሳይሆን በራሱ ዓላማና ጸጋ የተነሳ አዳነን፤ እንዲሁም ቅዱስ በሆነ ጥሪ ጠራን። ይህን ጸጋ ከረጅም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰጠን፤ 10 አሁን ግን ይህ ጸጋ አዳኛችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በመገለጡ ግልጽ ሆኖ ታይቷል፤ እሱ ሞትን አስወግዶ በምሥራቹ አማካኝነት ሕይወትንና አለመበስበስን በተመለከተ ብርሃን ፈንጥቋል፤ 11 እኔም ለዚህ ምሥራች ሰባኪ፣ ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ተሹሜአለሁ። 12 አሁን መከራ እየተቀበልኩ ያለሁትም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም አላፍርበትም። ያመንኩበትን እሱን አውቀዋለሁና፤ በአደራ የሰጠሁትንም እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ጠብቆ ማቆየት እንደሚችል እተማመናለሁ። 13 ከእኔ የሰማኸውን የትክክለኛ ትምህርት መሥፈርት ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለህ አንድነት ካገኘኸው እምነትና ፍቅር ጋር አጥብቀህ ያዝ። 14 ይህን መልካም አደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጠብቅ። 15 ፊጌሎስንና ሄርሞጌኔስን ጨምሮ በእስያ አውራጃ ያሉት ሁሉ ትተውኝ እንደሄዱ ታውቃለህ። 16 ጌታ ለኦኔሲፎሮስ ቤተሰብ ምሕረትን ይስጥ፤ እሱ ብዙ ጊዜ መንፈሴን አድሶልኛልና፤ በታሰርኩበት ሰንሰለትም አላፈረም። 17 እንዲያውም ሮም በነበረ ጊዜ አፈላልጎ አገኘኝ። 18 ጌታ ይሖዋ በዚያ ቀን ምሕረቱን ይስጠው። ደግሞም በኤፌሶን ያከናወነውን አገልግሎት ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ።
ከነሐሴ 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ቲቶ 1–ፊልሞና
‘ሽማግሌዎችን ሹም’
(ቲቶ 1:5-9) አንተን በቀርጤስ የተውኩህ ያልተስተካከሉትን ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው፤ 6 ይኸውም ከክስ ነፃ የሆነ፣ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም በስድነት ወይም በዓመፀኝነት የማይከሰሱ አማኝ የሆኑ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ካለ እንድትሾም ነው። 7 ምክንያቱም የበላይ ተመልካች በአምላክ የተሾመ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን ከክስ ነፃ መሆን አለበት፤ በራሱ ሐሳብ የሚመራ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም፣ ኃይለኛና አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚስገበገብ ሊሆን አይገባም፤ 8 ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ጻድቅ፣ ታማኝ፣ ራሱን የሚገዛ፣ 9 እንዲሁም ትክክለኛ በሆነው ትምህርት ማበረታታትም ሆነ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትን መውቀስ ይችል ዘንድ የማስተማር ጥበቡን ሲጠቀም የታመነውን ቃል በጥብቅ የሚከተል ሊሆን ይገባል።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዚያ ዘመን ወንድሞች እንዴት ይሾሙ እንደነበር ቅዱሳን መጻሕፍት በዝርዝር ባይገልጹም ይህ እንዴት ይከናወን እንደነበረ አንዳንድ ፍንጮች ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስና በርናባስ ከመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞአቸው ሲመለሱ “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ ላመኑበት ለይሖዋ አደራ ሰጧቸው” የሚል ሐሳብ እናነባለን። (ሥራ 14:23) ከዓመታት በኋላ ደግሞ ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው ለነበረው ለቲቶ “አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከሉትን ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው” በማለት ጽፎለታል። (ቲቶ 1:5) ከጳውሎስ ጋር ወደ ብዙ ቦታዎች የተጓዘው ጢሞቴዎስም ተመሳሳይ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ይመስላል። (1 ጢሞ. 5:22) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወንድሞችን የሾሙት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ሳይሆኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ነበሩ።
ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር በመነሳት የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ከሽማግሌዎችና ከጉባኤ አገልጋዮች ሹመት ጋር በተያያዘ ማስተካከያ አድርጓል። ከመስከረም 1, 2014 ጀምሮ ወንድሞች የሚሾሙት በሚከተለው መንገድ ይሆናል፦ እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች በወረዳው ውስጥ የድጋፍ ሐሳብ የሚቀርብላቸውን ግለሰቦች ብቃት በጥንቃቄ ይገመግማል። ከዚያም ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ጊዜ የድጋፍ ሐሳብ ከቀረበላቸው ወንድሞች ጋር በተቻለው መጠን በአገልግሎት አብሮ በመሥራት እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እየጎበኘ ካለው ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል ጋር በድጋፍ ሐሳቡ ላይ ከተወያየ በኋላ በወረዳው ውስጥ ሽማግሌዎችንና አገልጋዮችን የመሾሙ ኃላፊነት የእሱ ይሆናል። ይህ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው አሠራር ጋር የሚመሳሰል ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎችን የሚያከናውኑት እነማን ናቸው? አሁንም ቢሆን የአምላክን አገልጋዮች የመመገብ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ነው። (ማቴ. 24:45-47) ይህም ከዓለም አቀፉ ጉባኤ አደረጃጀት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ አመራር መስጠት እንዲቻል በመንፈስ ቅዱስ እየታገዘ ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመርን ያካትታል። በተጨማሪም ሁሉንም የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የሚሾመው ታማኙ ባሪያ ነው። እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ ደግሞ ታማኙ ባሪያ ካስተላለፈው መመሪያ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ተግባራዊ መሆን የሚችል እርዳታ ይሰጣል። እያንዳንዱ የሽማግሌዎች አካል በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ሹመት እንዲቀበሉ የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርብላቸው ወንድሞች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የሚያሟሉ መሆን አለመሆናቸውን በጥንቃቄ የመገምገም ከባድ ኃላፊነት አለበት። እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች ደግሞ በሽማግሌዎች የቀረበለትን የድጋፍ ሐሳብ በጥንቃቄና በጸሎት ከመረመረ በኋላ ብቃቱን የሚያሟሉትን ወንድሞች የመሾም ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ቲቶ 1:12) ከእነሱ መካከል የሆነ የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ምንጊዜም ውሸታሞች፣ አደገኛ አውሬዎችና ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሏል።
w89 5/15 31 አን. 5
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ጳውሎስ ይህን ሲል በሁሉም የቀርጤስ ሰዎች ላይ የተሰነዘረውን ዘረኝነት የሚንጸባረቅበት ትችት መደገፉ እንዳልነበረ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ምክንያቱም ጳውሎስ፣ አምላክ ሞገሱን ያሳያቸውና በመንፈስ ቅዱስ የቀባቸው ጥሩ ክርስቲያኖች ቀርጤስ ውስጥ እንዳሉ ያውቅ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:5, 11, 33) እንዲያውም ቀርጤስ ውስጥ በርካታ ግሩም ክርስቲያኖች ስለነበሩ “በየከተማው” ጉባኤዎችን ማቋቋም ተችሏል። እነዚህ ክርስቲያኖች ፍጹማን ባይሆኑም ውሸታሞችና ሥራ ፈት ሆዳሞች እንዳልነበሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ የይሖዋን ሞገስ ያጡ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:18, 19፤ ራእይ 21:8) ደግሞም በዛሬው ጊዜ በሁሉም ብሔራት ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በቀርጤስም በዙሪያቸው ባለው የሥነ ምግባር ውድቀት የሚያዝኑና ክርስቲያኖች የሚሰብኩትን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ቅን ሰዎች ነበሩ።—ሕዝቅኤል 9:4፤ ከሐዋርያት ሥራ 13:48 ጋር አወዳድር።
(ፊልሞና 15, 16) ምናልባት ለአጭር ጊዜ ከአንተ ጠፍቶ የሄደው፣ ተመልሶ ለዘለቄታው የአንተ ሆኖ እንዲኖር ይሆናል፤ 16 ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ ይበልጥ እንደተወደደ ወንድምህ ነው፤ በተለይ ለእኔ ተወዳጅ ወንድም ነው፤ ሆኖም በሰብዓዊ ግንኙነታችሁም ሆነ ከጌታ ጋር ባላችሁ ዝምድና ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።
ለቲቶና ለፊልሞና እንዲሁም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
15, 16—ጳውሎስ፣ አናሲሞስን ነፃ እንዲለቀው ፊልሞናን ያልጠየቀው ለምን ነበር? ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመስበክና ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከማስተማር’ ተልእኮው ውጪ በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መግባት አልፈለገም። በመሆኑም ከባርነት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላለመጠላለፍ መርጧል።—ሥራ 28:31
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ቲቶ 3:1-15) ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው፤ 2 ደግሞም ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው። 3 እኛም በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በቅናት የምንኖር፣ በሰዎች ዘንድ የምንጠላና እርስ በርስ የማንዋደድ ነበርን። 4 ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ደግነትና ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በተገለጠ ጊዜ 5 (እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን በምሕረቱ) እኛን አጥቦ ሕያው በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማደስ አዳነን። 6 ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ 7 ይህን ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ከጸደቅን በኋላ ከተስፋችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ የዘላለም ሕይወትን እንድንወርስ ነው። 8 እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፤ ደግሞም በአምላክ ያመኑ ሁሉ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው። 9 ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ ናቸው። 10 ኑፋቄ የሚያስፋፋን ሰው ከአንዴም ሁለቴ አጥብቀህ ምከረው። ካልሰማህ ግን ከእሱ ራቅ፤ 11 እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከትክክለኛው መንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ላይ እንደፈረደ እወቅ። 12 አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ ስልክ፣ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። 13 ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስም ሆነ አጵሎስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። 14 ይሁን እንጂ አሳሳቢ ችግር ሲፈጠር መርዳት እንዲችሉና ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ። 15 አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለሚወዱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ። የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
ከነሐሴ 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 1-3
“ጽድቅን ውደድ፤ ዓመፅን ጥላ”
(ዕብራውያን 1:8) ስለ ልጁ ሲናገር ግን እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የቅንነት በትረ መንግሥት ነው።
ክብር የተጎናጸፈውን ንጉሥ ክርስቶስን አወድሱ!
8 ይሖዋ ልጁን በ1914 በሰማያት በመሲሐዊ መንግሥቱ ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ‘የመንግሥቱ በትር የቅንነት በትር’ ስለሆነ በእሱ አገዛዝ ጽድቅና እኩልነት እንደሚሰፍን የተረጋገጠ ነው። ሥልጣኑ ሕጋዊ መሠረት አለው፤ ምክንያቱም ‘አምላክ ዙፋኑ ነው።’ (NW) በሌላ አባባል የመንግሥቱ መሠረት ይሖዋ ነው። በተጨማሪም የኢየሱስ ዙፋን “ከዘላለም እስከ ዘላለም ይኖራል።” አምላክ በሾመው ኃያል ንጉሥ አመራር ሥር ሆነህ ይሖዋን በማገልገልህ ኩራት አይሰማህም?
(ዕብራውያን 1:9) ጽድቅን ወደድክ፤ ዓመፅን ጠላህ። ስለዚህ አምላክ ይኸውም አምላክህ ከባልንጀሮችህ ይበልጥ በደስታ ዘይት ቀባህ።”
ክብር የተጎናጸፈውን ንጉሥ ክርስቶስን አወድሱ!
7 መዝሙር 45:6, 7ን አንብብ። ኢየሱስ ለጽድቅ ጥልቅ ፍቅር ስላለውና አባቱን ሊያስነቅፍ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ስለሚጠላ ይሖዋ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ኢየሱስ ‘ከጓደኞቹ’ ይኸውም የዳዊት ዘር ከሆኑት የይሁዳ ነገሥታት ይልቅ ‘በደስታ ዘይት’ ተቀብቷል። እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስን የቀባው ይሖዋ ራሱ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ንጉሥም ሊቀ ካህናትም አድርጎ ቀብቶታል። (መዝ. 2:2፤ ዕብ. 5:5, 6) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የተቀባው በዘይት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ነው፤ የነገሠውም በምድር ሳይሆን በሰማይ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 1:3) እሱ የአምላክ ክብር ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው፤ እሱም በኃያል ቃሉ ሁሉንም ነገር ደግፎ ያኖራል። እኛን ከኃጢአታችን ካነጻ በኋላም በሰማይ በግርማዊው ቀኝ ተቀምጧል።
it-1 1185 አን. 1
አምሳል
የአምላክ አምሳያ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያትና ማንነት ሁልጊዜ በእኩል ደረጃ አንጸባርቋል?
ከጊዜ በኋላ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣው የአምላክ የበኩር ልጅ ኢየሱስ የአባቱ አምሳል ነው። (2ቆሮ 4:4) ፈጣሪ “ሰውን በመልካችን . . . እንሥራ” ያለው ይህንን ልጁን እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ከዚህ አንጻር ወልድ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የአባቱ አምሳያ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። (ዘፍ 1:26፤ ዮሐ 1:1-3፤ ቆላ 1:15, 16) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ በኖረበት ወቅት ሰብዓዊ አቅም በሚፈቅደው መጠን የአባቱን ባሕርያትና ማንነት አንጸባርቋል፤ በመሆኑም “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሎ መናገር ችሏል። (ዮሐ 14:9፤ 5:17, 19, 30, 36፤ 8:28, 38, 42) ይሁንና ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ መንፈሳዊ አካል ሲሆን እንዲሁም አባቱ ይሖዋ አምላክ ‘ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር ሲሰጠው’ ከዚህ በላቀ ደረጃ የአባቱ አምሳያ መሆን ችሏል። (1ጴጥ 3:18፤ ማቴ 28:18) በዚህ ወቅት አምላክ ለኢየሱስ “የላቀ ቦታ በመስጠት” ከፍ ከፍ ስላደረገው ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከነበረውም እጅግ በላቀ ሁኔታ የአባቱን ክብር አንጸባርቋል። (ፊልጵ 2:9፤ ዕብ 2:9) አሁን ‘የአምላክ ማንነት ትክክለኛ አምሳያ ነው።’—ዕብ 1:2-4
(ዕብራውያን 1:10-12) ደግሞም እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት ጣልክ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11 እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12 እንደ ካባ፣ እንደ ልብስም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ደግሞም እንደ ልብስ ትለውጣቸዋለህ። አንተ ግን ያው ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”
it-1 1063 አን. 7
ሰማይ
መዝሙር 102:25, 26 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሚናገረው ስለ ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር ይህን ሐሳብ ጠቅሶታል። ጳውሎስ እንዲህ ያደረገው አምላክ፣ ግዑዙን ጽንፈ ዓለም በፈጠረበት ጊዜ አንድያ ልጁን ወኪሉ አድርጎ ስለተጠቀመበት ነው። ጳውሎስ፣ የወልድን ዘላለማዊነት አምላክ ፈቃዱ ከሆነ ‘እንደ ካባ ጠቅልሎ’ ሊያስወግደው ከሚችለው ጽንፈ ዓለም ጋር እያነጻጸረ መናገሩ ነው።—ዕብ 1:1, 2, 8, 10-12
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዕብራውያን 1:1-14) በጥንት ዘመን አምላክ በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች በነቢያት አማካኝነት ለአባቶቻችን ተናግሯል። 2 አሁን ደግሞ በእነዚህ ቀናት መጨረሻ የሁሉም ነገር ወራሽ አድርጎ በሾመውና የተለያዩ ሥርዓቶችን በፈጠረበት በልጁ አማካኝነት ለእኛ ተናገረ። 3 እሱ የአምላክ ክብር ነጸብራቅና የማንነቱ ትክክለኛ አምሳያ ነው፤ እሱም በኃያል ቃሉ ሁሉንም ነገር ደግፎ ያኖራል። እኛን ከኃጢአታችን ካነጻ በኋላም በሰማይ በግርማዊው ቀኝ ተቀምጧል። 4 ስለዚህ ከመላእክት ስም እጅግ የላቀ ስም የወረሰ በመሆኑ ከእነሱ የተሻለ ሆኗል። 5 ለምሳሌ፣ አምላክ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ” ደግሞም “አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል” ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 6 ሆኖም የበኩር ልጁን እንደገና ወደ ዓለም የሚያመጣበትን ጊዜ በተመለከተ “የአምላክ መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። 7 በተጨማሪም ስለ መላእክት ሲናገር “መላእክቱን መናፍስት፣ አገልጋዮቹን ደግሞ የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። 8 ስለ ልጁ ሲናገር ግን እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ለዘላለም ዙፋንህ ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የቅንነት በትረ መንግሥት ነው። 9 ጽድቅን ወደድክ፤ ዓመፅን ጠላህ። ስለዚህ አምላክ ይኸውም አምላክህ ከባልንጀሮችህ ይበልጥ በደስታ ዘይት ቀባህ።” 10 ደግሞም እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት ጣልክ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11 እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12 እንደ ካባ፣ እንደ ልብስም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ደግሞም እንደ ልብስ ትለውጣቸዋለህ። አንተ ግን ያው ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” 13 ይሁንና “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ብሎ ከመላእክት መካከል ስለ የትኛው መልአክ ተናግሮ ያውቃል? 14 ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?
ከነሐሴ 26–መስከረም 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዕብራውያን 4-6
“ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት የተቻለህን ሁሉ አድርግ”
(ዕብራውያን 4:1) ስለዚህ ወደ እረፍቱ የመግባት ተስፋ አሁንም ስላለ ከእናንተ መካከል ማንም ለዚያ የማይበቃ ሆኖ እንዳይገኝ እንጠንቀቅ።
(ዕብራውያን 4:4) በአንድ ቦታ ላይ ሰባተኛውን ቀን አስመልክቶ “አምላክም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ” ብሏልና፤
የአምላክ እረፍት ምንድን ነው?
3 ሰባተኛው ቀን በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን አላበቃም ብለን እንድንደመድም የሚያደርጉን ሁለት ማስረጃዎች አሉ። በመጀመሪያ ኢየሱስ በሰንበት ቀን የታመሙ ሰዎችን መፈወሱ፣ ሥራ ከመሥራት ተለይቶ እንደማይታይ በማሰብ ተቃዋሚዎቹ ሲነቅፉት የሰጣቸውን መልስ እንመልከት። “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 5:16, 17) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስን በሰንበት ቀን ሠርተሃል ብለው ከሰውታል። ስለዚህ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው” ሲል ለክሱ ምላሽ መስጠቱ ነበር። በሌላ አባባል ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ነበር፦ ‘እኔና አባቴ የምንሠራው አንድ ዓይነት ሥራ ነው። አባቴ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቀው የሰንበት እረፍቱ እየሠራ ስለሆነ እኔም በሰንበት ቀንም እንኳ መሥራት እችላለሁ።’ በመሆኑም ኢየሱስ ከሰው ልጆችና ከምድር ጋር በተያያዘ፣ ታላቁ የአምላክ የሰንበት እረፍት ማለትም ሰባተኛው ቀን በእሱ ዘመንም እንዳላበቃ ጠቁሟል።
4 ሁለተኛው ማስረጃ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ነገር ነው። ጳውሎስ የአምላክን እረፍት አስመልክቶ በዘፍጥረት 2:2 ላይ ያለውን ሐሳብ በጠቀሰበት ወቅት “እኛ እምነታችንን በተግባር ያሳየነው ወደዚህ እረፍት እንገባለን” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ዕብ. 4:3, 4, 6, 9) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ሰባተኛው ቀን በጳውሎስ ዘመንም አላበቃም ነበር። ታዲያ ይህ የእረፍት ቀን ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል?
5 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሰባተኛው ቀን ዓላማ ምን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ዘፍጥረት 2:3 “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም” ይላል። ይሖዋ ይህን ቀን ‘የቀደሰው’ ወይም የለየው ዓላማውን ከዳር ለማድረስ ነው። የይሖዋ ዓላማ፣ ምድር ታዛዥ በሆኑ ወንዶችና ሴቶች እንድትሞላ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ምድርንም ሆነ በውስጧ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት እንዲንከባከቡ ነው። (ዘፍ. 1:28) ይሖዋ አምላክና “የሰንበት ጌታ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እስካሁን እየሠሩ’ ያሉት ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ ነው። (ማቴ. 12:8) የአምላክ የእረፍት ቀን፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።
(ዕብራውያን 4:6) ስለዚህ ገና ወደ እረፍቱ የሚገቡ ስላሉና መጀመሪያ ምሥራቹ የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሳይገቡ ስለቀሩ
የአምላክ እረፍት ምንድን ነው?
6 አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ዓላማውን በግልጽ የነገራቸው ቢሆንም ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ አልተመላለሱም። እርግጥ ነው፣ ያለመታዘዝን ጎዳና የተከተሉት አዳምና ሔዋን ብቻ አልነበሩም። ከዚያ በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የእነሱን አካሄድ ተከትለዋል። የአምላክ ምርጥ ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያንም ጭምር ሳይታዘዙ ቀርተዋል። ጳውሎስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ከእነሱ መካከልም እንኳ አንዳንዶቹ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በወደቁበት ወጥመድ ሊወድቁ እንደሚችሉ ያስጠነቀቃቸው መሆኑ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ በመፍራት ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።” (ዕብ. 4:11) ጳውሎስ አለመታዘዝን ወደ አምላክ እረፍት ካለመግባት ጋር እንዳያያዘው ልብ በል። ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጭ የሆነ ነገር ብንፈጽም ወደ አምላክ እረፍት አንገባም ማለት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ይህን ጉዳይ በስፋት እንመለከተዋለን። አሁን ግን እስራኤላውያን የተዉትን መጥፎ ምሳሌ በመመርመር ወደ አምላክ እረፍት መግባትን በተመለከተ ምን ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
(ዕብራውያን 4:9-11) ስለዚህ የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ገና ይቀረዋል። 10 ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏልና። 11 ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።
የአምላክ እረፍት ምንድን ነው?
16 በዛሬው ጊዜ መዳን ለማግኘት የሙሴን ሕግ መጠበቅ ያስፈልጋል ብሎ የሚያስብ ክርስቲያን የለም። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም። “በእርግጥም እናንተ የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት በዚህ ጸጋ ነው፤ ይህም እናንተ በራሳችሁ ያገኛችሁት ሳይሆን የአምላክ ስጦታ ነው። ማንም ሰው የሚመካበት ምክንያት እንዳይኖር ይህ በፍጹም በሥራ የሚገኝ አይደለም” ብሏቸዋል። (ኤፌ. 2:8, 9) ታዲያ ክርስቲያኖች ወደ አምላክ እረፍት መግባት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ሰባተኛውን ቀን የእረፍቱ ቀን አድርጎ የለየው ለምድርና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ወደ ታላቅ ፍጻሜው ለማድረስ ነው። እኛም በአምላክ ድርጅት በኩል ከሚገለጥልንና ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ እንዲሁም ታዛዦች በመሆን ወደ ይሖዋ እረፍት መግባት እንችላለን።
17 በሌላ በኩል ደግሞ በራሳችን ለመመራት የምንመርጥና ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር አቅልለን የምንመለከት ከሆነ አካሄዳችን ከይሖዋ ዓላማ ጋር የሚጋጭ ይሆናል። ይህም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ሰላማዊ ዝምድና አደጋ ላይ ይጥለዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የአምላክ ሕዝቦች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አንዳንድ የተለመዱ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፤ በእነዚህ ሁኔታዎች ረገድ አምላክን ለመታዘዝም ሆነ በራሳችን ለመመራት የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በእርግጥ ወደ አምላክ እረፍት በመግባታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዕብራውያን 4:12 ላይ “ሕያውና ኃይለኛ ነው” የተባለው “የአምላክ ቃል” ምንድን ነው?
▪ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል” ሲል ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸውን መልእክት ማመልከቱ ነው፤ ይህ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙትን ሐሳቦችም ይጨምራል።
ዕብራውያን 4:12 ብዙውን ጊዜ ጽሑፎቻችን ላይ የሚጠቀሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው ለመግለጽ ነው፤ ጥቅሱ በዚህ መንገድ መብራራቱም ተገቢ ነው። ነገር ግን ዕብራውያን 4:12 በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻር ሰፋ ያለ ትርጉም እንዳለው መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን ከአምላክ ዓላማዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለሱ ማሳሰቡ ነበር። ከአምላክ ዓላማዎች መካከል ብዙዎቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። ጳውሎስ ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡትን እስራኤላውያን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። እነዚህ እስራኤላውያን “ወተትና ማር ወደምታፈሰው” እና እውነተኛ እረፍት ወደሚያገኙባት ተስፋይቱ ምድር እንደሚገቡ ቃል ተገብቶላቸው ነበር።—ዘፀ. 3:8፤ ዘዳ. 12:9, 10
አምላክ ለሕዝቡ የገለጸው ዓላማ ይህ ነበር። እስራኤላውያን ግን ከጊዜ በኋላ ልባቸውን ያደነደኑ ከመሆኑም በላይ እምነት አላሳዩም፤ ስለሆነም ብዙዎቹ እስራኤላውያን ወደ አምላክ እረፍት አልገቡም። (ዘኁ. 14:30፤ ኢያሱ 14:6-10) ይሁንና ጳውሎስ ‘ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋ አሁንም እንዳለ’ ተናግሯል። (ዕብ. 3:16-19፤ 4:1) ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸው መልእክት ይህን “ተስፋ” እንደሚጨምር ግልጽ ነው። እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ስለ አምላክ ዓላማ መማርና ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር እንችላለን። ጳውሎስ፣ ይህ ተስፋ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማጉላት ዘፍጥረት 2:2ን እና መዝሙር 95:11ን በከፊል ጠቅሷል።
‘ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋ አሁንም’ ያለ መሆኑ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋችን እውን እንደሚሆን እናምናለን፤ እንዲሁም ወደዚያ እረፍት ለመግባት የሚያስችሉንን እርምጃዎች ወስደናል። ይህን ያደረግነው የሙሴን ሕግ በመጠበቅ ወይም የይሖዋን ሞገስ ያስገኛሉ የሚባሉ ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም አይደለም። ከዚህ ይልቅ እምነታችን፣ አምላክ ከገለጸው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር በፈቃዳችን ጥረት እንድናደርግ አነሳስቶናል፤ ወደፊትም ይህን ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘው “የአምላክ ቃል” የሚለው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስንም ሊያመለክት ይችላል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸውን መልእክት ማወቅ ችለዋል። በመሆኑም ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ አኗኗራቸውን ለመቀየር፣ እምነት ለማሳየትና ተጠምቀው ክርስቲያኖች ለመሆን ተነሳስተዋል። እነዚህ ሰዎች እየወሰዱ ያሉት እርምጃ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ” መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጽ መልእክት በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ወደፊትም በሕይወታችን ላይ ለውጥ ማምጣቱን ይቀጥላል።
(ዕብራውያን 6:17, 18) በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ። 18 ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው።
it-1 1139 አን. 2
ተስፋ
“የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” (ዕብ 3:1) የሆኑት ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት እና የማይበሰብስ ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው፤ ይህ ተስፋ ጽኑ መሠረት ያለውና እምነት የሚጣልበት ነው። ማረጋገጫ የሚሆኑት፣ አምላክ ሊዋሽ የማይችልባቸው ሁለት ነገሮች ይኸውም የገባው ቃልና መሐላው ሲሆኑ ተስፋው የማይሞት ሕይወት አግኝቶ በሰማይ በሚኖረው በክርስቶስ እጅ ነው። በመሆኑም ጳውሎስ ስለዚህ ተስፋ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤ ተስፋውም መጋረጃውን አልፈን [ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባ እንደነበረው] ወደ ውስጥ እንድንገባ ያስችለናል፤ ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል።”—ዕብ 6:17-20
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዕብራውያን 5:1-14) ከሰዎች መካከል የተመረጠ እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መባና መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ እነሱን በመወከል የአምላክን አገልግሎት ለማከናወን ይሾማል። 2 እሱ ራሱ ድክመት ስላለበት አላዋቂ የሆኑትንና የሚሳሳቱትን በርኅራኄ ሊይዛቸው ይችላል፤ 3 በዚህም የተነሳ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ እንደሚያቀርብ ሁሉ ለራሱም ለማቅረብ ይገደዳል። 4 አንድ ሰው ይህን የክብር ቦታ የሚያገኘው እንደ አሮን፣ አምላክ ሲጠራው ብቻ ነው እንጂ በራሱ ፈቃድ አይደለም። 5 ክርስቶስም ሊቀ ካህናት በመሆን ራሱን ከፍ ከፍ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ” ብሎ ስለ እሱ የተናገረው፣ ከፍ ከፍ አደረገው። 6 ደግሞም በሌላ ቦታ ላይ “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሏል። 7 ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ለቅሶና እንባ ምልጃና ልመና አቀረበ፤ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረውም ጸሎቱ ተሰማለት። 8 ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ። 9 በዚህም ፍጹም ከሆነ በኋላ የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው፤ 10 ምክንያቱም ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አምላክ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል። 11 እሱን በተመለከተ ብዙ የምንናገረው ነገር አለን፤ ይሁንና ጆሯችሁ ስለደነዘዘ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። 12 በአሁኑ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ የነበረ ቢሆንም የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች እንደገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚያስተምራችሁ ሰው ትፈልጋላችሁ፤ ደግሞም ጠንካራ ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ ጀምራችኋል። 13 ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ ከጽድቅ ቃል ጋር ትውውቅ የለውም። 14 ጠንካራ ምግብ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ላሠለጠኑ ጎልማሳ ሰዎች ነው።