የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ኅዳር 2020
ከኅዳር 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 39–40
“ሙሴ የተሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ ተከትሏል”
(ዘፀአት 39:32) የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ያዘዘውን ነገር ሁሉ ሠሩ። ልክ እንደታዘዙትም አደረጉ።
ይሖዋ ያውቃችኋል?
13 ከቆሬ በተቃራኒ ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር።” (ዘኍ. 12:3) ሙሴ የይሖዋን አመራር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ልኩን የሚያውቅና ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዘፀ. 7:6፤ 40:16) ሙሴ ይሖዋ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ጥያቄ አንስቶ አሊያም ይሖዋ የሰጠውን አሠራር በመከተሉ ተበሳጭቶ እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ለምሳሌ ያህል፣ የማደሪያው ድንኳን በተሠራበት ወቅት ይሖዋ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ክሮች ቀለምና በድንኳኑ ላይ ያሉትን ቀለበቶች ብዛት ጨምሮ ሌሎች ጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (ዘፀ. 26:1-6) በአምላክ ድርጅት ውስጥ የሚያገለግል አንድ የበላይ ተመልካች ጥቃቅን የሚመስሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ መመሪያዎች የሚሰጥህ ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ትበሳጭ ይሆናል። ይሖዋ ግን ፍጹም የሆነ የበላይ ተመልካች ነው፤ ለሌሎች ብዙ ኃላፊነቶችን የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ አገልጋዮቹ ሥራውን በብቃት እንደሚወጡ ይተማመናል። እንዲሁም በርካታ ዝርዝር መመሪያዎችን የሚሰጥበት በቂ ምክንያት አለው። ያም ሆኖ ሙሴ፣ ይሖዋ እንዲህ ያሉ ዝርዝር መመሪያዎችን ስለሰጠው አልተበሳጨም፤ እንዲሁም ዝቅ አድርጎ እንደተመለከተው አሊያም አዲስ ነገር የመፍጠር ችሎታውን ወይም ነፃነቱን እንደገደበበት ሆኖ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ሙሴ፣ ሠራተኞቹ በአምላክ መመሪያ መሠረት ‘ልክ እንደታዘዙት መሥራታቸውን’ ይከታተል ነበር። (ዘፀ. 39:32) እንዴት ያለ ትሕትና የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው! ሙሴ ሥራው የይሖዋ መሆኑንና እሱ ሥራውን ለመሥራት የሚያገለግል መሣሪያ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።
(ዘፀአት 39:43) ሙሴም ሥራቸውን በሙሉ ሲመለከት ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንደሠሩ አየ፤ ከዚያም ባረካቸው።
(ዘፀአት 40:1, 2) ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑን ትከል።
(ዘፀአት 40:16) ሙሴም ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አደረገ። ልክ እንደዚሁ አደረገ።
በሁሉም ነገር ታማኝ ናችሁ?
3 ዕብራውያን 3:5 “ሙሴ . . . ታማኝ አገልጋይ ነበር” ይላል። ይህን ነቢይ ታማኝ ያስባለው ነገር ምንድን ነው? ከመገናኛው ድንኳን ሥራ ጋር በተያያዘ “ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው [አድርጓል]።” (ዘፀአት 40:16) የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን እርሱን በታዛዥነት በማገልገል ታማኝነት እናሳያለን። ይህም አስቸጋሪ ፈተናና ከባድ መከራ ሲደርስብን ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መቀጠልን እንደሚጨምር የታወቀ ነው። ይሁንና ከባድ ፈተናዎችን መወጣት መቻላችን ታማኝነታችን የሚለካበት ብቸኛው መሥፈርት አይደለም። ኢየሱስ “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም” ብሏል። (ሉቃስ 16:10) ቀላል በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ታማኝነት ማሳየት ይኖርብናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 39:34) ለመደረቢያ የሚሆነውን ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳና ለመደረቢያ የሚሆነውን የአቆስጣ ቆዳ፣ ለመግቢያው መከለያ የሚሆነውን መጋረጃ፣
it-2 884 አን. 3
የአቆስጣ ቆዳ
እስራኤላውያን ያገኙት እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ታካሽ አንድን የአቆስጣ ዝርያ የሚያመለክት ከሆነ እስራኤላውያን የአቆስጣ ቆዳ ያገኙት እንዴት እንደሆነ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አቆስጣዎች በአብዛኛው የሚገኙት በአርክቲክ እና በአንታርክቲክ አካባቢ ቢሆንም አንዳንድ የአቆስጣ ዝርያዎች ሞቅ ያለ የአየር ጠባይ ይመርጣሉ። በዛሬው ጊዜም እንኳ በሜድትራንያን ባሕርም ሆነ በሌሎች ሞቅ ያሉ ውኃዎች ውስጥ አንዳንድ የአቆስጣ ዝርያዎች ይገኛሉ። ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት የሰው ልጅ የአቆስጣዎች ብዛት በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ግን እነዚህ እንስሳት በሜድትራንያን ባሕርና በቀይ ባሕር ውስጥ በብዛት ይገኙ የነበረ ይመስላል። እንዲያውም ከብዙ ዘመናት በኋላ በ1832 የካልሜት ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ሆሊ ባይብል የእንግሊዝኛ እትም (ገጽ 139) እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “በሲና ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ በሚገኙት በብዙዎቹ የቀይ ባሕር ትናንሽ ደሴቶች ላይ አቆስጣዎች ይገኛሉ።”—ዘ ታበርናክልስ ቲፒካል ቲቺንግ፣ በኤ. ጄ. ፖሎክ የተዘጋጀ፣ ለንደን፣ ገጽ 47
(ዘፀአት 40:34) ደመናውም የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።
ሥራህን የሚያይልህ ሰው አለመኖሩ ለውጥ ያመጣል?
የማደሪያው ድንኳን ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ደመና “የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።” (ዘፀ. 40:34) የመገናኛ ድንኳኑ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግልጽ ምልክት ነው! በዚያ ወቅት ባስልኤልና ኤልያብ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? ምንም እንኳ በሥራዎቻቸው ላይ ስማቸው ባይቀረጽም አምላክ ጥረታቸውን እንደባረከላቸው በማወቃቸው እርካታ ተሰምቷቸው መሆን አለበት። (ምሳሌ 10:22) ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታትም ሥራቸው ለይሖዋ አገልግሎት እንደዋለ ማየታቸው ልባቸው በደስታ እንዲሞላ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። ባስልኤልና ኤልያብ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ሲያገኙ ደግሞ የማደሪያው ድንኳን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ 500 ለሚያህሉ ዓመታት አገልግሎት እንደሰጠ ማወቃቸው በጣም እንደሚያስደስታቸው ጥርጥር የለውም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 39:1-21) በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል የሚለበሱትን በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑትን ልብሶች ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍና ከደማቅ ቀይ ማግ ሠሩ። ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረትም የአሮንን ቅዱስ ልብሶች ሠሩ። 2 እሱም ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። 3 እነሱም ወርቁን በመቀጥቀጥ በስሱ ጠፈጠፉት፤ እሱም ከሰማያዊው ክር፣ ከሐምራዊው ሱፍ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከጥሩው በፍታ ጋር አብሮ እንዲሠራው ወርቁን እንደ ክር በቀጫጭኑ ሰነጣጠቀው፤ ከዚያም በወርቁ ጥልፍ ጠለፈበት። 4 ለኤፉዱም ላዩ ላይ የሚጣበቁ የትከሻ ጥብጣቦች የሠሩለት ሲሆን ኤፉዱም ከትከሻ ጥብጣቦቹ ጋር የሚያያዘው በሁለቱ ጫፎቹ ላይ ነበር። 5 ኤፉዱ ወዲያ ወዲህ እንዳይንቀሳቀስ ለማሰር የሚያገለግለው ከኤፉዱ ጋር የተያያዘው በሽመና የተሠራው መቀነትም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንደ ኤፉዱ ሁሉ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ተሠራ። 6 ከዚያም የኦኒክስ ድንጋዮቹን በወርቅ አቃፊዎቹ ውስጥ አስቀመጧቸው፤ የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞችም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ቀረጹባቸው። 7 እሱም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች ሆነው እንዲያገለግሉ በኤፉዱ የትከሻ ጥብጣቦች ላይ አስቀመጣቸው። 8 ከዚያም የደረት ኪሱን የጥልፍ ባለሙያ እንደሚሠራው አድርጎ ልክ ኤፉዱ በተሠራበት መንገድ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። 9 ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜም አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ። ለሁለት በሚታጠፍበት ጊዜ ቁመቱም ሆነ ወርዱ አንድ ስንዝር የሆነውን የደረት ኪስ ሠሩ። 10 በላዩም ላይ አራት ረድፍ ድንጋዮችን አደረጉበት። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ተደረደረ። 11 በሁለተኛው ረድፍ ደግሞ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ተደረደረ። 12 በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ተደረደረ። 13 በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ተደረደረ። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ተቀመጡ። 14 ድንጋዮቹም 12ቱን የእስራኤል ወንዶች ልጆች ስሞች የሚወክሉ ነበሩ፤ ስሞቹም ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ተቀረጹ፤ እያንዳንዱ ስም ከ12ቱ ነገዶች አንዱን የሚወክል ነበር። 15 ከዚያም በደረት ኪሱ ላይ እንደ ገመድ የተጎነጎነ ሰንሰለት ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ። 16 በመቀጠልም ሁለት የወርቅ አቃፊዎችንና ሁለት ቀለበቶችን ሠሩ፤ ሁለቱን ቀለበቶችም በደረት ኪሱ ሁለት ማዕዘኖች ላይ አያያዟቸው። 17 በኋላም ሁለቱን የወርቅ ገመዶች በደረት ኪሱ ማዕዘኖች ላይ በሚገኙት ሁለት ቀለበቶች ውስጥ አስገቧቸው። 18 ከዚያም የሁለቱን ገመዶች ሁለት ጫፎች በሁለቱ አቃፊዎች ውስጥ አስገቧቸው፤ በኤፉዱ በፊት በኩል በትከሻ ጥብጣቦቹ ላይ አያያዟቸው። 19 በመቀጠልም ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ በኩል በሚውለው በደረት ኪሱ ውስጠኛ ጠርዝ ሁለት ጫፎች ላይ አደረጓቸው። 20 ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው በኤፉዱ ላይ ከፊት በኩል ከሁለቱ የትከሻ ጥብጣቦች በታች፣ መጋጠሚያው አጠገብ፣ በሽመና ከተሠራው የኤፉዱ መቀነት በላይ አደረጓቸው። 21 በመጨረሻም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ላይ ሳይንቀሳቀስ፣ ተሸምኖ ከተሠራው መቀነት በላይ እንዲውል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ገመድ አያያዟቸው።
ከኅዳር 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 1–3
“መባዎች የሚቀርቡበት ዓላማ”
(ዘሌዋውያን 1:3) “‘የሰውየው መባ ከከብቶች መካከል ተወስዶ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት እንስሳ ማቅረብ ይኖርበታል። መባውን በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል።
(ዘሌዋውያን 2:1) “‘አንድ ሰው ለይሖዋ የእህል መባ የሚያቀርብ ከሆነ መባው የላመ ዱቄት መሆን አለበት፤ በላዩም ላይ ዘይት ያፍስበት፤ ነጭ ዕጣንም ያስቀምጥበት።
(ዘሌዋውያን 2:12) “‘እነዚህንም የፍሬ በኩራት መባ አድርጋችሁ ለይሖዋ ልታቀርቧቸው ትችላላችሁ፤ ሆኖም ደስ እንደሚያሰኝ መዓዛ ሆነው ወደ መሠዊያው መምጣት የለባቸውም።
it-2 525
መባዎች
የሚቃጠል መባ። የሚቃጠል መባ የሚቀርበው እንስሳውን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በመስጠት ነበር፤ መሥዋዕት አቅራቢው የትኛውንም የእንስሳውን ክፍል ማስቀረት አይችልም። (ከመሳ 11:30, 31, 39, 40 ጋር አወዳድር።) ይህ መባ አንዳንድ ጊዜ ከኃጢአት መባ ጋር አብሮ ይቀርብ የነበረ ሲሆን ይሖዋ የኃጢአት መባውን እንዲቀበል ወይም መቀበሉን እንዲያሳይ ለመለመን ያገለግል ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እንደሚቃጠል መባ’ ራሱን ሙሉ በሙሉ ሰጥቷል።
it-2 528 አን. 4
መባዎች
የእህል መባ። የእህል መባ ከኅብረት መባ፣ ከሚቃጠል መባ እና ከኃጢአት መባ ጋር አብሮ፣ የፍሬ በኩራት ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለብቻው ይቀርብ ነበር። (ዘፀ 29:40-42፤ ዘሌ 23:10-13, 15-18፤ ዘኁ 15:8, 9, 22-24፤ 28:9, 10, 20, 26-28፤ ምዕ 29) ይህ መባ የሚቀርበው አምላክ በረከትና ብልጽግና አትረፍርፎ በመስጠቱ ለማመስገን ነበር። ብዙውን ጊዜ ከዘይትና ከዕጣን ጋር አብሮ ይቀርብ ነበር። የላመ ዱቄት፣ የተጠበሰ እሸት አሊያም ደግሞ በምጣድ የተጋገረ ወይም በድስት የተዘጋጀ የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ ወይም ስስ ቂጣ የእህል መባ ሆኖ ሊቀርብ ይችል ነበር። ከእህል መባው ላይ የተወሰነው ክፍል የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ይቀርብ ነበር፤ የተወሰነውን ክፍል ደግሞ ካህናቱ ይበሉት ነበር፤ የኅብረት መባ ከሆነ ደግሞ መሥዋዕቱን ያቀረበው ግለሰብም ከመባው ይበላል። (ዘሌ 6:14-23፤ 7:11-13፤ ዘኁ 18:8-11) በመሠዊያው ላይ የሚቀርብ የእህል መባ እርሾ ወይም ሊፈላ የሚችል “ማር” (የበለስ ወይም የፍራፍሬ ጭማቂን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም) ሊኖረው አይገባም።—ዘሌ 2:1-16
(ዘሌዋውያን 3:1) “‘አንድ ሰው የሚያቀርበው መባ የኅብረት መሥዋዕት ቢሆንና ከከብቶች መካከል ወስዶ የሚያቀርብ ከሆነ እንስሳው ተባዕትም ሆነ እንስት እንከን የሌለበትን በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል።
‘ከእውነት መሠረታዊ ገጽታዎች’ ትምህርት ማግኘት
በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተካተቱት መሥዋዕቶች መካከል አንዱ የኅብረት መሥዋዕት በመባል የሚታወቀው ነው። አንድ እስራኤላዊ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ማቅረቡ ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ዝምድና እንዳለው ያሳያል። በዚህ ወቅት ግለሰቡ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን የእንስሳ ሥጋ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ይመገባል፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው በቤተ መቅደሱ ካሉት የመመገቢያ ክፍሎች በአንዱ ውስጥ ሊሆን ይችላል። መሥዋዕቱን ያቀረበው ካህን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉት ሌሎች ካህናት እንደሚያደርጉት ከሥጋው ላይ የራሱን ድርሻ ይወስዳል። (ዘሌ. 3:1 የግርጌ ማስታወሻ፤ 7:31-33) አንድ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው እንዲህ ያለውን መሥዋዕት የሚያቀርበው ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት ካለው ልባዊ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። በዚህ ወቅት ያለው ሁኔታ ግለሰቡ፣ ቤተሰቡ፣ ካህናቱ እና ይሖዋ አንድ ማዕድ ላይ ተቀምጠው በሰላም ደስ ብሏቸው እየተመገቡ እንዳሉ ሊቆጠር ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 2:13) “‘የምታቀርበው የእህል መባ በሙሉ በጨው መቀመም አለበት፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨውም ከእህል መባህ ላይ አይጥፋ። ከማንኛውም መባህ ጋር ጨው አብረህ ታቀርባለህ።
(ሕዝቅኤል 43:24) ለይሖዋ ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ከነሰነሱባቸው በኋላ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አድርገው ያቀርቧቸዋል።
የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:13—ጨው በሁሉም “ቁርባን” ላይ መጨመር የነበረበት ለምንድን ነው? እንዲህ የሚደረገው መሥዋዕቱን ለማጣፈጥ ተብሎ አይደለም። ጨው በዓለም ዙሪያ ነገሮችን ሳይበላሹ ለማቆየት ጥቅም ላይ ይውላል። ስለሆነም ከመሥዋዕት ጋር ይቀርብ የነበረው ከብክለትና ከብልሽት ነጻ መሆንን ስለሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
(ዘሌዋውያን 3:17) “‘ስብም ሆነ ደም ፈጽሞ አትብሉ። ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለእናንተም ሆነ ለትውልዶቻችሁ ዘላቂ ደንብ ነው።’”
የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:17፦ ስብ ምርጥ የሆነው የእንስሳው ክፍል ተደርጎ ይታይ ስለነበር እስራኤላውያን ስብ እንዳይበሉ መከልከላቸው ለይሖዋ የሚገባው ምርጥ ምርጡ መሆኑን አስገንዝቧቸዋል። (ዘፍጥረት 45:18) ይህ እኛም ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እንዳለብን ያሳስበናል።—ምሳሌ 3:9, 10፤ ቆላስይስ 3:23, 24
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 1:1-17) ይሖዋም ሙሴን ጠርቶ ከመገናኛ ድንኳኑ እንዲህ ሲል አናገረው፦ 2 “እስራኤላውያንን አናግራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ከእናንተ መካከል ማንኛችሁም ከቤት እንስሳት ለይሖዋ መባ ማቅረብ ከፈለጋችሁ መባችሁን ከከብቶች ወይም ከመንጎች መካከል ማቅረብ አለባችሁ። 3 “‘የሰውየው መባ ከከብቶች መካከል ተወስዶ የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት እንስሳ ማቅረብ ይኖርበታል። መባውን በራሱ ፈቃድ ተነሳስቶ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በይሖዋ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል። 4 ለሚቃጠል መባ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ መባውም ለሰውየው ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል። 5 “‘ከዚያም ወይፈኑ በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን ያቅርቡት፤ እንዲሁም ደሙን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በሚገኘው መሠዊያ ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። 6 የሚቃጠለውም መባ መገፈፍና መቆራረጥ ይኖርበታል። 7 ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም በመሠዊያው ላይ እሳት ያንድዱ፤ በእሳቱም ላይ እንጨት ይረብርቡበት። 8 እነሱም ተቆራርጦ የተዘጋጀውን መባ ከጭንቅላቱና ከሞራው ጋር በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደርድሩት። 9 ሆድ ዕቃውና እግሮቹም በውኃ ይታጠቡ፤ ካህኑም የሚቃጠል መባ ይኸውም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ አድርጎ ሙሉውን በመሠዊያው ላይ ያጭሰው። 10 “‘ሰውየው የሚቃጠል መባ እንዲሆን የሚያቀርበው መባ ከመንጋው ማለትም ከበግ ጠቦቶቹ ወይም ከፍየሎቹ መካከል የተወሰደ ከሆነ እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ። 11 በስተ ሰሜን በኩል ባለው የመሠዊያው ጎን በይሖዋ ፊት ይታረድ፤ ካህናት የሆኑት የአሮን ወንዶች ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ጎኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። 12 እሱም ጭንቅላቱንና ሞራውን ጨምሮ እንስሳውን በየብልቱ ይቆራርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ በሚገኘው እንጨት ላይ ይደረድራቸዋል። 13 ሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ ያጥባቸዋል፤ ካህኑም ሙሉውን ያቀርበዋል፤ እንዲሁም በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው። 14 “‘ሆኖም ሰውየው አእዋፋትን ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ መባውን ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ጫጩቶች መካከል ያቀርባል። 15 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል፤ እንዲሁም አንገቱ ላይ ቦጭቆ በመሠዊያው ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ደሙ ግን በመሠዊያው ጎን ይንጠፍጠፍ። 16 ቋቱንና ላባዎቹንም ከለየ በኋላ ከመሠዊያው አጠገብ በስተ ምሥራቅ በኩል ወዳለው አመድ ወደሚደፋበት ቦታ ይወርውራቸው። 17 ሙሉ በሙሉ ለሁለት ሳይለያየው ክንፎቹን ይዞ ይሰነጥቀዋል። ከዚያም ካህኑ በመሠዊያው ላይ ይኸውም በእሳቱ ላይ ባለው እንጨት ላይ እንዲጨስ ያደርገዋል። ይህም የሚቃጠል መባ ማለትም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ያለው በእሳት የሚቀርብ መባ ነው።
ከኅዳር 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 4–5
“ለይሖዋ ምርጣችሁን ስጡት”
(ዘሌዋውያን 5:5, 6) “‘ከእነዚህ ነገሮች በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ በምን መንገድ ኃጢአት እንደሠራ መናዘዝ አለበት። 6 ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ ማለትም ከመንጋው መካከል እንስት የበግ ጠቦት ወይም እንስት የፍየል ግልገል የኃጢአት መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል። ከዚያም ካህኑ ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል።
nwt 1646 አን. 8
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ
የበደል መባ። አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአት የሚያቀርበው መሥዋዕት ነው። ከሌሎቹ የኃጢአት መባዎች የተወሰነ ልዩነት አለው፤ ይህ መባ የሚቀርበው ኃጢአት ሠርቶ ንስሐ የገባው ሰው ያጣቸውን ከቃል ኪዳኑ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መብቶች መልሶ እንዲያገኝና ቅጣት ይደርስብኛል ከሚል ስጋት እንዲገላገል ለማድረግ ነው።—ዘሌ 7:37፤ 19:22፤ ኢሳ 53:10
(ዘሌዋውያን 5:7) “‘በግ ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ግን ለሠራው ኃጢአት የበደል መባ እንዲሆኑ ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ለይሖዋ ያምጣ፤ አንዱ ለኃጢአት መባ ሌላኛው ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይሆናል።
ይሖዋ የአቅማችንን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሰጠው ሕግ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት እንደሚያሳይ ያጎላል፤ እንዲህ ይላል፦ “ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች . . . ለእግዚአብሔር ያቅርብ።” (ቁጥር 7) “ዐቅሙ ካልፈቀደ” የሚለው ሐረግ “እጅ ካጠረው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አንድ እስራኤላዊ በጣም ድሃ በመሆኑ በግ ለማቅረብ ካልቻለ አቅሙ የፈቀደለትን ይኸውም ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶችን ቢያቀርብ አምላክ መሥዋዕቱን በደስታ ይቀበለዋል።
(ዘሌዋውያን 5:11) “‘ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለማምጣት አቅሙ የማይፈቅድለት ከሆነ ደግሞ ለሠራው ኃጢአት፣ የኃጢአት መባ እንዲሆን አንድ አሥረኛ ኢፍ የላመ ዱቄት መባ አድርጎ ያምጣ። የኃጢአት መባ ስለሆነ ዘይት አይጨምርበት ወይም ነጭ ዕጣን አያድርግበት።
ይሖዋ የአቅማችንን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል
ይሁንና ግለሰቡ ሁለት ዋኖሶችን እንኳ ለማቅረብ አቅሙ የማይፈቅድለት ቢሆንስ? በዚህ ጊዜ ሕጉ “የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ [አንድ ኪሎ ግራም ገደማ] የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ” ይላል። (ቁጥር 11) ይሖዋ፣ በጣም ድሃ ለሆኑ ሰዎች ልዩ አስተያየት በማድረግ ደም ሳይፈስ የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። አንድ እስራኤላዊ የቱንም ያህል ድሃ ቢሆን፣ ይህ ሁኔታው የኃጢአት ይቅርታ እንዳያገኝ እንቅፋት አይሆንበትም፤ ወይም ከአምላክ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚያስችለውን አጋጣሚ አይነፍገውም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 5:1) “‘አንድ ሰው ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል።
ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ትምህርት ማግኘት
14 ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብህ ግራ ስትጋባ ደግነት ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራህ ከባድ ኃጢአት እንደሠራ በእርግጠኝነት ታውቃለህ እንበል። ይህ ሰው በተለይ የቅርብ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ ከሆነ ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ኃጢአቱን የምትደብቅለት ከሆነ ለአምላክ ያለህን ታማኝነት እያጓደልክ ነው። ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብህ ለይሖዋ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በመሆኑም እንደ ናታን ደግ ሆኖም ደፋር ልትሆን ይገባል። ጓደኛህ ወይም ዘመድህ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቅ አበረታታው። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይህን ካላደረገ ግን ለአምላክ ያለህ ታማኝነት፣ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች እንድታሳውቅ ሊያነሳሳህ ይገባል። እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ታማኝነት፣ ለወዳጅህ ወይም ለዘመድህ ደግሞ ደግነት ታሳያለህ፤ ምክንያቱም ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን ሰው በገርነት ለማስተካከል ይጥራሉ።—ዘሌዋውያን 5:1ን እና ገላትያ 6:1ን አንብብ።
(ዘሌዋውያን 5:15, 16) “አንድ ሰው ለይሖዋ በተቀደሱት ነገሮች ላይ ባለማወቅ ኃጢአት በመሥራት ታማኝነቱን ቢያጎድል ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መባ አድርጎ ለይሖዋ ያመጣል፤ ዋጋው በብር ሰቅል የሚተመነው እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት ነው። 16 በቅዱሱ ስፍራ ላይ ለፈጸመው ኃጢአት ካሳ ይከፍላል፤ የዋጋውንም አንድ አምስተኛ ይጨምርበታል። ካህኑ ለበደል መባ በቀረበው አውራ በግ አማካኝነት እንዲያስተሰርይለትም ለካህኑ ይሰጠዋል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
it-1 1130 አን. 2
ቅድስና
እንስሳትና ሰብሎች። በኩር የሆኑ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ለይሖዋ የተቀደሱ ተደርገው ስለሚቆጠሩ ሊዋጁ አይገባም ነበር። መሥዋዕት ሆነው ከቀረቡ በኋላ የተወሰነው ክፍል ቅዱስ ለሆኑት ካህናት ይሰጣል። (ዘኁ 18:17-19) የፍሬ በኩራት እና አሥራት እንዲሁም ሁሉም መሥዋዕቶችና ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የተለዩ ስጦታዎች ቅዱስ ነበሩ። (ዘፀ 28:38) ለይሖዋ የተቀደሱ ነገሮች በሙሉ ቅዱስ በመሆናቸው ቀላል ተደርገው ሊታዩ አሊያም ደግሞ ለተራ ወይም ቅዱስ ላልሆነ አገልግሎት ሊውሉ አይገባም አበር። ስለ አሥራት የሚገልጸው ሕግ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከስንዴ ሰብሉ አሥራት አድርጎ የሚሰጠውን ከለየ በኋላ እሱ ወይም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱ ባለማወቅ ከተለየው ስንዴ ወስዶ ምግብ ለማብሰል ወይም ለሌላ ዓላማ ቢጠቀምበት ግለሰቡ የተቀደሱ ነገሮችን በተመለከተ የወጣውን የአምላክ ሕግ በመተላለፍ በደል ይጠየቃል። ሕጉ ግለሰቡ ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን አውራ በግ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እንዲሁም የዋጋውን 20 በመቶ ጨምሮ ለቅዱሱ ስፍራ ካሳ እንዲሰጥ ያዛል። ይህም ለይሖዋ የተሰጡ ቅዱስ ነገሮች በታላቅ አክብሮት ሊያዙ እንደሚገባ ያሳያል።—ዘሌ 5:14-16
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 4:27–5:4) “‘በምድሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ማንኛውም ሰው ይሖዋ መደረግ የለባቸውም ብሎ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል አንዱን በመፈጸም ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ 28 በኋላም የሠራውን ኃጢአት ቢያውቅ ለፈጸመው ኃጢአት እንከን የሌለባትን እንስት የፍየል ጠቦት መባ አድርጎ ያምጣ። 29 እጁንም ለኃጢአት መባ በቀረበችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ እንዲሁም ለኃጢአት መባ የቀረበችውን እንስሳ የሚቃጠለው መባ በሚታረድበት ስፍራ ያርዳታል። 30 ካህኑም ከደሙ የተወሰነውን በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤ ከዚያም የተረፈውን ደሙን በሙሉ በመሠዊያው ሥር ያፈሰዋል። 31 ከኅብረት መሥዋዕቱ ላይ ስቡ እንደሚነሳ ሁሉ ከዚህ ላይም ስቡን በሙሉ ያነሳዋል፤ ካህኑም ስቡ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ እንዲሰጥ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል፤ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 32 “‘ሆኖም የኃጢአት መባ አድርጎ የሚያቀርበው የበግ ጠቦት ከሆነ እንከን የሌለባትን እንስት የበግ ጠቦት ማምጣት አለበት። 33 እጁንም ለኃጢአት መባ በቀረበችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ እንዲሁም እንስሳዋን የሚቃጠለው መባ በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአት መባ አድርጎ ያርዳታል። 34 ካህኑም ለኃጢአት መባ ከቀረበችው እንስሳ ደም ላይ የተወሰነውን በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቀባል፤ ከዚያም የተረፈውን ደሙን በሙሉ በመሠዊያው ሥር ያፈሰዋል። 35 የኅብረት መሥዋዕት ሆኖ ከሚቀርበው የበግ ጠቦት ላይ ስቡ እንደሚነሳ ሁሉ ከዚህ ላይም ስቡን በሙሉ ያነሳዋል፤ እሱም በመሠዊያው ላይ ባሉት ለይሖዋ በእሳት በሚቀርቡት መባዎች ላይ እንዲጨሱ ያደርጋል። ካህኑም ሰውየው የሠራውን ኃጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
5 “‘አንድ ሰው ሰዎች የምሥክርነት ቃል እንዲሰጡ ጥሪ እየቀረበ መሆኑን ቢሰማና እሱ መመሥከር እየቻለ ወይም ደግሞ ጉዳዩን አይቶ አሊያም አውቆ ሳለ ሳይናገር ቢቀር በሠራው ጥፋት ይጠየቅበታል። 2 “‘ወይም አንድ ሰው ርኩስ የሆነን ማንኛውንም ነገር ይኸውም ርኩስ የሆነን የዱር አውሬ ወይም ርኩስ የሆነን የቤት እንስሳ አሊያም ርኩስ የሆነን የሚርመሰመስ ፍጥረት በድን ቢነካ፣ ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆንም እንኳ ይህ ሰው ርኩስ ነው፤ በደለኛም ይሆናል። 3 ወይም አንድ ሰው ባለማወቅ የሰውን ርኩሰት ይኸውም እንዲረክስ ሊያደርገው የሚችለውን ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና በኋላም ይህን ቢያውቅ በደለኛ ይሆናል። 4 “‘አሊያም ደግሞ አንድ ሰው ነገሩ ምንም ሆነ ምን ክፉ ወይም መልካም ለማድረግ በችኮላ ቢምልና ይህን ያደረገው ባለማወቅ ቢሆን ሆኖም የማለው በችኮላ መሆኑን በኋላ ላይ ቢገነዘብ በደለኛ ይሆናል።
ከኅዳር 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 6–7
“የአመስጋኝነት መግለጫ”
(ዘሌዋውያን 7:11, 12) “‘አንድ ሰው ለይሖዋ የሚያቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት በተመለከተ ደግሞ ሕጉ ይህ ነው፦ 12 ሰውየው መሥዋዕቱን የሚያቀርበው አመስጋኝነቱን ለመግለጽ ከሆነ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋር በዘይት ተለውሶ የተጋገረ እርሾ ያልገባበት የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ፣ ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣና በዘይት በደንብ ከራሰና ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተጋገረ የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ አብሮ ያቀርባል።
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
9 ሁለተኛው ትምህርት፦ ይሖዋን የምናገለግለው አመስጋኝነታችንን መግለጽ ስለምንፈልግ ነው። በጥንት ዘመን በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው የኅብረት መባዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስተምሩን ነገር አለ። የዘሌዋውያን መጽሐፍ እንደሚያሳየው አንድ እስራኤላዊ “አመስጋኝነቱን ለመግለጽ” የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ይችል ነበር። (ዘሌ. 7:11-13, 16-18) ግለሰቡ ይህን መባ የሚያቀርበው ስለሚጠበቅበት ሳይሆን በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ስለዚህ የኅብረት መሥዋዕት፣ አንድ ሰው ለአምላኩ ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በፈቃደኝነት የሚያቀርበው መባ ነው። መባውን የሚያቀርበው ሰው፣ ቤተሰቡ እንዲሁም ካህናቱ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን እንስሳ ሥጋ ይበሉ ነበር። ሆኖም የእንስሳው የተወሰኑ ክፍሎች ለይሖዋ ብቻ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው?
(ዘሌዋውያን 7:13-15) መባውንም እርሾ ገብቶባቸው ከተጋገሩ የቀለበት ቅርጽ ያላቸው ዳቦዎችና የምስጋና መሥዋዕት አድርጎ ከሚያቀርባቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ጋር አብሮ ያቀርባል። 14 ከዚያም ላይ ከእያንዳንዱ መባ አንድ አንድ በማንሳት ለይሖዋ የተቀደሰ ድርሻ አድርጎ ያቀርባል፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቶቹን ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15 የምስጋና መሥዋዕት እንዲሆኑ ያቀረባቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ሥጋ፣ መሥዋዕቱን ባቀረበበት ቀን መበላት ይኖርበታል። ከዚያ ላይ ምንም ማስቀረትና ማሳደር የለበትም።
አምላክ የተደሰተባቸው መሥዋዕቶች
15 ሌላው በፈቃደኝነት ይቀርብ የነበረው የኅብረት መሥዋዕት ሲሆን ይህም በዘሌዋውያን ምዕራፍ 3 ላይ ተብራርቷል። ስሙ “የሰላም መባ መሥዋዕት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በዕብራይስጥ “ሰላም” የሚለው ቃል ከጦርነት ወይም ከሁከት ነፃ ከመሆን የበለጠ ነገርን ያመለክታል። “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህንንና በተጨማሪም ከአምላክ ጋር የሚመሠረተውን ሰላማዊ ሁኔታ ወይም ዝምድና፣ ብልጽግናን፣ ደስታንና ፍስሃን ያመለክታል” በማለት ስተዲስ ኢን ዘ ሞዛይክ ኢንስቲትዩሽን የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ስለሆነም የኅብረት መሥዋዕት አምላክን በመለማመን ከአምላክ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚቀርብ ሳይሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሰዎች ከአምላክ ጋር ላገኙት ሰላም ምስጋናቸውን ወይም ደስታቸውን ለመግለጽ የሚያቀርቡት ነው። ደሙና ስቡ ለይሖዋ ከቀረበ በኋላ ካህናቱና መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው ከመሥዋዕቱ ይካፈላሉ። (ዘሌዋውያን 3:17፤ 7:16-21፤ 19:5-8 የ1980 ትርጉም) መሥዋዕቱን ያቀረበው ሰው፣ ካህናቱና ይሖዋ አምላክ ውብና ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ከአንድ ማዕድ የሚካፈሉ ሲሆን ይህም በመካከላቸው ሰላማዊ ዝምድና መኖሩን የሚያመለክት ነው።
(ዘሌዋውያን 7:20) “‘ሆኖም ማንኛውም ሰው ርኩስ ሆኖ ሳለ ለይሖዋ ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።
ይሖዋን የሚያስደስቱ የምሥጋና መሥዋዕቶች
8 መሥዋዕት ከሚያቀርበው ሰውስ ምን ይጠበቅ ነበር? በይሖዋ ፊት ለመቆም የሚመጣ ማንኛውም ሰው ንጹሕና ያልረከሰ መሆን እንዳለበት ሕጉ ይናገራል። በሆነ ምክንያት የረከሰ ሰው የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የኅብረት መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይችል ዘንድ አስቀድሞ የኃጢአት ወይም የበደል መሥዋዕት በማቅረብ በይሖዋ ፊት ያለውን ንጹሕ አቋም ማደስ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 5:1-6, 15, 17) ታዲያ እኛስ በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ንጹሕ አቋም የመያዝን አስፈላጊነት እንገነዘባለን? አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን የአምላክን ሕግ በመጣስ የፈጸምነውን ስህተት ፈጥነን ማስተካከል ይገባናል። አምላክ እርዳታ ለመስጠት በሚጠቀምባቸው ‘የጉባኤ ሽማግሌዎች’ እና ‘ለኃጢአታችን ማስተሰርያ’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠቀም ፈጣኖች መሆን አለብን።—ያዕቆብ 5:14፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 6:13) በመሠዊያውም ላይ ያለማቋረጥ እሳት ይነድዳል። መጥፋትም የለበትም።
it-1 833 አን. 1
እሳት
ከማደሪያ ድንኳኑና ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ። እሳት በማደሪያ ድንኳኑና በኋላም በቤተ መቅደሱ በሚቀርበው አምልኮ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በየቀኑ ማለዳና አመሻሽ ላይ ሊቀ ካህናቱ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ማጨስ ነበረበት። (ዘፀ 30:7, 8) የአምላክ ሕግ የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ እሳቱ ዘወትር መንደድ እንዳለበት ያዝዝ ነበር። (ዘሌ 6:12, 13) እሳቱን መጀመሪያ ላይ አምላክ በተአምራዊ መንገድ እንደለኮሰው የሚገልጸው የአይሁዳውያን ወግ ሰፊ ተቀባይነት ቢኖረውም የቅዱሳን መጻሕፍት ድጋፍ የለውም። ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለሙሴ የሰጠው መመሪያ የአሮን ልጆች መሥዋዕቱን በመሠዊያው ላይ ከማቅረባቸው በፊት ‘በመሠዊያው ላይ እሳት ማንደድ’ እንዳለባቸው ይገልጽ ነበር። (ዘሌ 1:7, 8) ከይሖዋ ፊት የመጣው እሳት (ምናልባትም ከማደሪያው ድንኳን በላይ ካለው ደመና የመጣ እሳት ሊሆን ይችላል) በመሠዊያው ላይ ያለውን መባ የበላው የአሮንና የዘሮቹ ክህነት ሹመት ሥርዓት ከተካሄደ፣ ይኸውም የሹመት ሥርዓቱ መሥዋዕት ከቀረበ በኋላ ነው። ከዚህ አንጻር እሳቱ በተአምራዊ መንገድ የመጣው በመሠዊያው ላይ ያለውን እንጨት ለማቀጣጠል ሳይሆን “በመሠዊያው ላይ ያለውን የሚቃጠል መባና ስብ” ለመብላት ነው። ከዚያ ጊዜ በኋላ በመሠዊያው ላይ መንደዱን የቀጠለው እሳት ከአምላክ የመጣው እሳትና በመሠዊያው ላይ የነበረው እሳት ቅልቅል ሳይሆን አይቀርም። (ዘሌ 8:14–9:24) በተመሳሳይም ሰለሞን በቤተ መቅደሱ ውሰና ላይ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ከይሖዋ የመጣ ተአምራዊ እሳት መሥዋዕቱን በልቶታል።—2ዜና 7:1፤ ይሖዋ አገልጋዮቹ ያቀረቡትን መባ መቀበሉን ለማሳየት ተአምራዊ እሳት የተጠቀመባቸውን ሌሎች ወቅቶች ለማየት መሳ 6:21፤ 1ነገ 18:21-39፤ 1ዜና 21:26ንም ተመልከት።
(ዘሌዋውያን 6:25) “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የኃጢአት መባ ሕግ ይህ ነው፦ ለኃጢአት መባ የሚሆነውም እንስሳ፣ ለሚቃጠል መባ የሚሆነው እንስሳ በሚታረድበት ቦታ በይሖዋ ፊት ይታረዳል። ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው።
si 27 አን. 15
የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 3—ዘሌዋውያን
15 (3) የኃጢአት መባ የሚቀርበው ባለማወቅ ወይም በስህተት ለተሠራ ኃጢአት ነበር። የሚቀርበው እንስሳ ስርየት የሚጠየቀው ማን ለሠራው ኃጢአት ነው (ካህኑ፣ መላው ብሔር፣ አለቃው ወይም አንድ ተራ ሰው) በሚለው ላይ የተመካ ነው። ግለሰቦች በፈቃደኝነት ከሚያቀርቡት የሚቃጠል መባና የኅብረት መባ በተለየ መልኩ የኃጢአት መባ ማቅረብ ግዴታ ነበር።—4:1-35; 6:24-30.
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 6:1-18) ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “አንድ ሰው በአደራ እንዲይዝ ወይም እንዲያስቀምጥ ከተሰጠው ነገር ጋር በተያያዘ ባልንጀራውን በማታለል ኃጢአት ቢሠራና በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር ቢፈጽም አሊያም ባልንጀራውን ቢሰርቅ ወይም ቢያጭበረብር 3 አሊያም ደግሞ የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ብሎ ቢዋሽና ሰውየው ከእነዚህ ኃጢአቶች መካከል አንዱንም እንዳልሠራ አድርጎ በሐሰት ቢምል እንዲህ ማድረግ አለበት፦ 4 ኃጢአት ቢሠራና በደለኛ ሆኖ ቢገኝ የሰረቀውን፣ ቀምቶ ወይም አጭበርብሮ የወሰደውን አሊያም በአደራ ተሰጥቶት የነበረውን ወይም ደግሞ ጠፍቶ ያገኘውን ነገር ይመልስ፤ 5 አሊያም በሐሰት የማለበትን ማንኛውንም ነገር ይመልስ፤ ሙሉ ካሳ ይክፈል፤ የዋጋውንም አንድ አምስተኛ ይጨምርበት። በደለኛ መሆኑ በተረጋገጠበትም ዕለት ለባለቤቱ ይሰጠዋል። 6 በተተመነውም ዋጋ መሠረት እንከን የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው መካከል በመውሰድ የበደል መባው አድርጎ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያመጣዋል። 7 ካህኑም በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ እሱም በደለኛ እንዲሆን ያደረገው ማንኛውም ነገር ይቅር ይባልለታል።” 8 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 9 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ‘የሚቃጠል መባ ሕግ ይህ ነው፦ የሚቃጠለው መባ ሌሊቱን ሙሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጣል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ሲነድ ያድራል። 10 ካህኑ ከበፍታ የተሠራውን የክህነት ልብሱን ይለብሳል፤ እርቃኑንም ለመሸፈን ከበፍታ የተሠራውን ቁምጣ ያደርጋል። ከዚያም በመሠዊያው ላይ ከነበረው በእሳት ከነደደው የሚቃጠል መባ የወጣውን አመድ ያነሳል፤ በመሠዊያውም ጎን ያደርገዋል። 11 ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ከሰፈሩ ውጭ ወደሚገኝ ንጹሕ የሆነ ቦታ ይወስደዋል። 12 እሳቱ በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። መጥፋትም የለበትም። ካህኑም በየማለዳው እንጨት ይማግድበት፤ በላዩም ላይ የሚቃጠለውን መባ ይረብርብበት፤ የኅብረት መሥዋዕቶቹንም ስብ በላዩ ላይ ያጨስበታል። 13 በመሠዊያውም ላይ ያለማቋረጥ እሳት ይነድዳል። መጥፋትም የለበትም። 14 “‘የእህል መባ ሕግ ደግሞ ይህ ነው፦ እናንተ የአሮን ወንዶች ልጆች በመሠዊያው ፊት ለፊት በይሖዋ ፊት ታቀርቡታላችሁ። 15 ከመካከላቸው አንዱ ለእህል መባ ከቀረበው የላመ ዱቄት ላይ ከነዘይቱ አንድ እፍኝ ያነሳል፤ እንዲሁም በእህል መባው ላይ ያለውን ነጭ ዕጣን በሙሉ ይወስዳል። አምላክ መላውን መባ እንዲያስበውም ለይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መዓዛ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያጨሰዋል። 16 ከዚያ የተረፈውን አሮንና ወንዶች ልጆቹ ይበሉታል፤ እንደ ቂጣ ተጋግሮ በቅዱስ ስፍራ ይበላል። በመገናኛ ድንኳኑ ግቢ ውስጥ ይበሉታል። 17 ያለእርሾ መጋገር አለበት። ለእኔ በእሳት ከሚቀርቡልኝ መባዎች ውስጥ ይህን ድርሻቸው አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። እንደ ኃጢአት መባና እንደ በደል መባ ሁሉ ይህም እጅግ ቅዱስ ነገር ነው። 18 የአሮን ዘር የሆኑ ወንዶች ሁሉ ይበሉታል። ይህ ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡ መባዎች ውስጥ በትውልዶቻችሁ ሁሉ ለእነሱ የሚሰጥ ዘላለማዊ ድርሻ ነው። የሚነካቸውም ነገር ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’”
ከኅዳር 30–ታኅሣሥ 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 8–9
“የይሖዋን በረከት የሚያሳይ ማስረጃ”
(ዘሌዋውያን 8:6-9) በመሆኑም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቀረባቸው፤ በውኃም አጠባቸው። 7 ከዚያም ለአሮን ረጅሙን ቀሚስ አጠለቀለት፤ መቀነቱንም አሰረለት፤ እጅጌ የሌለውን ቀሚስም አለበሰው፤ ኤፉዱንም አደረገለት፤ ኤፉዱንም ተሸምኖ በተሠራው የኤፉዱ መቀነት ጠበቅ አድርጎ አሰረው። 8 በመቀጠልም የደረት ኪሱን አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪሙንና ቱሚሙን አስቀመጠ። 9 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥምጥሙን በራሱ ላይ አደረገለት፤ በጥምጥሙም ከፊት በኩል፣ የሚያብረቀርቀውን ጠፍጣፋ ወርቅ ይኸውም ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየውን ቅዱስ ምልክት አደረገለት።
(ዘሌዋውያን 8:12) በመጨረሻም ከቅብዓት ዘይቱ የተወሰነውን ወስዶ በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰው፤ የተቀደሰም ይሆን ዘንድ ቀባው።
it-1 1207
የሹመት ሥርዓት
ሙሴ አሮንንና ናዳብ፣ አቢሁ፣ አልዓዛርና ኢታምር የተባሉትን የአሮን ልጆች በግቢው በሚገኘው የመዳብ ገንዳ ውስጥ ካጠባቸው (ወይም እንዲታጠቡ ካዘዛቸው) በኋላ ክብራማ የሆነውን የሊቀ ክህነት ልብስ ለአሮን አለበሰው። (ዘኁ 3:2, 3) አሮን ውብ የሆነውን እንዲሁም የሥራ ምድቡ የሚጠይቀውን ባሕርይና ኃላፊነት የሚወክለውን ልብስ ለበሰ። ከዚያም ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎችና ቁሳቁሶች፣ የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ እንዲሁም የውኃ ገንዳውንና ተያያዥ ቁሳቁሶቹን ቀባቸው። ይህም ዕቃዎቹ እንዲቀደሱና ከዚያ በኋላ ለይሖዋ አገልግሎት ብቻ ለመዋል እንዲለዩ አድርጓል። በመጨረሻም ሙሴ አሮንን ራሱ ላይ ዘይት በማፍሰስ ቀባው።—ዘሌ 8:6-12፤ ዘፀ 30:22-33፤ መዝ 133:2
(ዘሌዋውያን 9:1-5) በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንን፣ ወንዶች ልጆቹንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራ። 2 አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ለኃጢአት መባ አንድ ጥጃ፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ አንድ አውራ በግ ለራስህ ውሰድ፤ እንከን የሌለባቸው ይሁኑ፤ በይሖዋም ፊት አቅርባቸው። 3 እስራኤላውያንን ግን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ለኃጢአት መባ አንድ ተባዕት ፍየል፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው አንድ ጥጃና አንድ የበግ ጠቦት ውሰዱ፤ 4 የኅብረት መሥዋዕት ሆነው በይሖዋ ፊት እንዲሠዉም አንድ በሬና አንድ አውራ በግ ውሰዱ፤ እንዲሁም በዘይት የተለወሰ የእህል መባ አቅርቡ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ዛሬ ለእናንተ ይገለጣል።’” 5 ስለዚህ ሙሴ ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት አመጡ። ከዚያም መላው ማኅበረሰብ መጥቶ በይሖዋ ፊት ቆመ።
it-1 1208 አን. 8
የሹመት ሥርዓት
በስምንተኛው ቀን፣ ካህናቱ ሙሉ በሙሉ ለሥራቸው ብቁ ከሆኑና ከተሾሙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ (ያለሙሴ እገዛ) የክህነት ሥራቸውን አከናወኑ፤ ለእስራኤል ብሔር የስርየት አገልግሎት ሰጡ፤ በወቅቱ እስራኤላውያን በዘር በወረሱት ኃጢአት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ጥቂት ቀደም ብሎ የወርቅ ጥጃ በማምለክ በይሖዋ ላይ ዓምፀው እሱን በማሳዘናቸውም መንጻት ያስፈልጋቸው ነበር። (ዘሌ 9:1-7፤ ዘፀ 32:1-10) አዲሶቹ ካህናት የመጀመሪያውን አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ይሖዋ ሞገሱን ለማሳየትና ለሹመታቸው እውቅና ለመስጠት ተአምራዊ እሳት አወረደ፤ በመሠዊያው ላይ የቀረውን መሥዋዕት የበላው ይህ እሳት ከማደሪያ ድንኳኑ በላይ ከነበረው የደመና ዓምድ የወረደ መሆን አለበት።—ዘሌ 9:23, 24
(ዘሌዋውያን 9:23, 24) በመጨረሻም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛ ድንኳኑ ገቡ፤ ከዚያም ወጥተው ሕዝቡን ባረኩ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ፤ 24 እሳትም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በመሠዊያው ላይ ያለውን የሚቃጠል መባና ስብ በላ። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያይ እልል አለ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፋ።
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
13 አራተኛው ትምህርት፦ ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል እየባረከ ነው። በ1512 ዓ.ዓ. በሲና ተራራ ግርጌ ላይ የማደሪያው ድንኳን በተተከለበት ወቅት ምን እንደተከናወነ እንመልከት። (ዘፀ. 40:17) አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲሾሙ ሥርዓቱን የመራው ሙሴ ነበር። መላው የእስራኤል ብሔር፣ ካህናቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንስሳት መሥዋዕት ሲያቀርቡ ለመመልከት ተሰብስቦ ነበር። (ዘሌ. 9:1-5) ይሖዋ አዲስ የተቋቋመውን የክህነት ሥርዓት እንደተቀበለው ያሳየው እንዴት ነው? አሮንና ሙሴ ሕዝቡን ሲባርኩ ይሖዋ በመሠዊያው ላይ የቀረውን ነገር በሙሉ እሳት እንዲበላው አደረገ።—ዘሌዋውያን 9:23, 24ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 8:6) በመሆኑም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቀረባቸው፤ በውኃም አጠባቸው።
ቅዱስ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
6 የእስራኤል ካህናት አካላዊ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ የሚያዝዘው ሕግ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም አለው። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የአምልኮ ቦታችን ንጹሕ እንደሆነ እንዲሁም እኛ ራሳችን ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበስ እንዳለን ያስተውላሉ። በተጨማሪም የካህናቱ ንጽሕና፣ ላቅ ወዳለው የይሖዋ አምልኮ ተራራ የሚወጣ ማንኛውም ሰው “ንጹሕ ልብ” ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዝበናል። (መዝሙር 24:3, 4ን በNW አንብብ፤ ኢሳ. 2:2, 3) ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ አእምሯችን፣ ልባችንና አካላችን ንጹሕ ሊሆን ይገባል። ይህ ደግሞ በየጊዜው ራሳችንን መመርመርን ይጠይቃል፤ አንዳንዶች እንዲህ ያለ ምርመራ ካደረጉ በኋላ ቅዱስ ለመሆን ሲሉ ጉልህ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል። (2 ቆሮ. 13:5) ለምሳሌ ያህል፣ ፖርኖግራፊ ሆን ብሎ የሚመለከት አንድ ክርስቲያን ‘ቅዱስ ሆኜ እየኖርኩ ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ነው። ከዚህም ሌላ ይህን ርኩስ ልማድ ለማሸነፍ እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል።—ያዕ. 5:14
(ዘሌዋውያን 8:14-17) ከዚያም ለኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ አመጣ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውን ለኃጢአት መባ በሚሆነው በሬ ራስ ላይ ጫኑ። 15 ሙሴም በሬውን አረደው፤ ደሙንም በጣቱ ወስዶ በሁሉም የመሠዊያው ጎኖች ላይ ያሉትን ቀንዶች ቀባ፤ መሠዊያውንም ከኃጢአት አነጻው፤ የቀረውንም ደም መሠዊያው ማስተሰረያ ይቀርብበት ዘንድ መሠዊያውን ለመቀደስ በሥሩ አፈሰሰው። 16 ከዚያም ሙሴ አንጀቱን የሸፈነውን ስብ ሁሉ፣ በጉበቱ ላይ ያለውን ሞራ፣ ሁለቱን ኩላሊቶችና በእነሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ በመሠዊያው ላይ እንዲጨሱ አደረገ። 17 ሙሴም ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከበሬው የቀረውን፣ ቆዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።
it-2 437 አን. 3
ሙሴ
አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ለገባው የሕጉ ቃል ኪዳን ሙሴን መካከለኛ አድርጎ ሾሞታል፤ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ማንኛውም ሰው በአምላክ ፊት እንዲህ ያለ ልዩ ቦታ አግኝቶ አያውቅም። ሙሴ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ መሥዋዕት ሆነው በቀረቡት እንስሳት ደም ረጭቶታል፤ በዚህ መንገድ የቃል ኪዳኑ አንደኛ “ወገን” ይሖዋ፣ ሌላኛው “ወገን” ደግሞ ሕዝቡ (ብሔሩን የሚወክሉት ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው) እንደሆኑ አሳይቷል። ሙሴ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ለሕዝቡ ያነበበላቸው ሲሆን ሕዝቡም “ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ ለመፈጸምና ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነን” በማለት መለሱ። (ዘፀ 24:3-8፤ ዕብ 9:19) ሙሴ የመካከለኛነት ሥራውን ሲያከናውን አምላክ በሰጠው ንድፍ መሠረት የማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች አሠራር በበላይነት የመከታተል፣ ካህናቱን የመሾም እንዲሁም የማደሪያ ድንኳኑንና ሊቀ ካህናቱን አሮንን በልዩ መንገድ በተቀመመው ዘይት የመቀባት መብት አግኝቷል። በኋላም አዲሶቹ ካህናት መጀመሪያ ላይ የሰጧቸውን አገልግሎቶች በበላይነት ተከታትሏል።—ዘፀ ምዕ 25-29፤ ዘሌ ምዕ 8, 9
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 8:31-9:7) ከዚያም ሙሴ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “ሥጋውን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀቅሉት፤ ‘አሮንና ወንዶች ልጆቹ ይበሉታል’ ተብዬ በታዘዝኩት መሠረት ሥጋውንም ሆነ በክህነት ሹመት ሥርዓቱ ቅርጫት ውስጥ ያለውን ቂጣ እዚያ ትበሉታላችሁ። 32 ከሥጋውም ሆነ ከቂጣው የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33 ለክህነት ሹመታችሁ ሥርዓት የተመደቡት ቀናት እስከሚያበቁ ድረስ ይኸውም ለሰባት ቀን ያህል በመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ ቆዩ፤ ምክንያቱም እናንተን ካህን አድርጎ መሾም ሰባት ቀን ይፈጃል። 34 ለእናንተ ለማስተሰረይ ዛሬ ያደረግነውን ነገር እንድናደርግ ይሖዋ አዟል። 35 በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቀንና ሌሊት ለሰባት ቀን ያህል ትቆያላችሁ፤ እንዳትሞቱም ለይሖዋ የገባችሁትን ግዴታ ፈጽሙ፤ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ።” 36 አሮንና ወንዶች ልጆቹም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ አደረጉ።
9 በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንን፣ ወንዶች ልጆቹንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራ። 2 አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ለኃጢአት መባ አንድ ጥጃ፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ አንድ አውራ በግ ለራስህ ውሰድ፤ እንከን የሌለባቸው ይሁኑ፤ በይሖዋም ፊት አቅርባቸው። 3 እስራኤላውያንን ግን እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ‘ለኃጢአት መባ አንድ ተባዕት ፍየል፣ ለሚቃጠል መባ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዓመት የሆናቸውና እንከን የሌለባቸው አንድ ጥጃና አንድ የበግ ጠቦት ውሰዱ፤ 4 የኅብረት መሥዋዕት ሆነው በይሖዋ ፊት እንዲሠዉም አንድ በሬና አንድ አውራ በግ ውሰዱ፤ እንዲሁም በዘይት የተለወሰ የእህል መባ አቅርቡ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ዛሬ ለእናንተ ይገለጣል።’” 5 ስለዚህ ሙሴ ያዘዛቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት አመጡ። ከዚያም መላው ማኅበረሰብ መጥቶ በይሖዋ ፊት ቆመ። 6 ሙሴም “የይሖዋ ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ ይሖዋ እንድታደርጉት ያዘዛችሁ ነገር ይህ ነው” አለ። 7 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአት መባህንና የሚቃጠል መባህን አቅርብ፤ ለራስህና ለቤትህም አስተሰርይ፤ ይሖዋ ባዘዘውም መሠረት የሕዝቡን መባ አቅርብ፤ እንዲሁም ለእነሱ አስተሰርይ።”