የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
ከግንቦት 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 27–29
“የዳዊት የጦር ስልት”
የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
7 ዳዊት ከኖብ በስተ ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ የፍልስጥኤማውያን ክልል ሸሸ፤ በዚያም የጎልያድ የትውልድ ከተማ በሆነችው በጌት በንጉሥ አንኩስ ዘንድ ተሸሸገ። ዳዊት ወደዚች ከተማ የሄደው ሳኦል በጌት እንደማይፈልገው ተሰምቶት ይሆናል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የጌት ንጉሥ አገልጋዮች ዳዊትን አወቁት። ዳዊት እንደታወቀ በሰማ ጊዜ ‘የጌትን ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራው።’—1 ሳሙኤል 21:10-12
8 ብዙም ሳይቆይ ፍልስጥኤማውያን ዳዊትን ያዙት። ይህ የይሖዋ አገልጋይ “እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም” በማለት ይሖዋን የለመነበትን ከልብ የመነጨ መዝሙር ያቀናበረው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (መዝሙር 56:8 እና በመዝሙሩ አናት ላይ የሚገኘው መግለጫ) በዚህ መንገድ መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ሐዘኑን እንደማይረሳ ከዚህ ይልቅ በፍቅር እንደሚንከባከበውና እንደሚጠብቀው ያለውን እምነት ገልጿል። ዳዊት የፍልስጥኤማውያንን ንጉሥ ለማታለል የሚያስችለው ዘዴም ቀይሷል። በንጉሡ ፊት ሲያቀርቡት እንደ እብድ ሰው ሆነ። ንጉሥ አንኩስ ይህንን ሲመለከት ‘ያበደ ሰው’ ወደ እርሱ በማምጣታቸው አገልጋዮቹን ወቀሳቸው። ይሖዋ፣ ዳዊት የተጠቀመበትን ዘዴ እንደባረከለት በግልጽ መመልከት ይቻላል። ዳዊት ከከተማው የተባረረ ሲሆን በዚህም ጊዜ ቢሆን ከሞት ያመለጠው ለጥቂት ነበር።—1 ሳሙኤል 21:13-15
ወጣት ወንዶች—ሌሎች እምነት እንዲጥሉባችሁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
8 ዳዊት ያጋጠመውን ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታም እንመልከት። ዳዊት ንጉሥ ለመሆን ከተቀባ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ሆኖ እስኪሾም ድረስ ለበርካታ ዓመታት መጠበቅ ነበረበት። (1 ሳሙ. 16:13፤ 2 ሳሙ. 2:3, 4) በዚህ ጊዜ በትዕግሥት ለመጠበቅ የረዳው ምንድን ነው? ዳዊት ተስፋ ቆርጦ እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ አተኩሯል። ለምሳሌ በፍልስጤም ምድር በስደት ይኖር የነበረበትን ጊዜ የእስራኤልን ጠላቶች ለመዋጋት ተጠቅሞበታል። እንዲህ በማድረግ የይሁዳን ድንበር አስጠብቋል።—1 ሳሙ. 27:1-12
it-2 245 አን. 6
ውሸት
በተንኮል የሚነገር ውሸት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዘ ቢሆንም ይህ ሲባል አንድ ሰው ለማይመለከታቸው ሰዎች እውነተኛውን መረጃ የመናገር ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ። አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።” (ማቴ 7:6) ኢየሱስ በአንዳንድ ወቅቶች የተሟላ መረጃ ከመስጠት ወይም ለአንዳንድ ጥያቄዎች ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት የተቆጠበው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ አላስፈላጊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ማቴ 15:1-6፤ 21:23-27፤ ዮሐ 7:3-10) አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ረዓብ እና ኤልሳዕ ይሖዋን ለማያመልኩ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ እንደሰጡ ወይም የተሟላ መረጃ ሳይሰጡ እንደቀሩ የሚገልጹት ዘገባዎችም ከዚህ አንጻር መታየት ያለባቸው ይመስላል።—ዘፍ 12:10-19፤ ምዕ 20፤ 26:1-10፤ ኢያሱ 2:1-6፤ ያዕ 2:25፤ 2ነገ 6:11-23
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዱ ይችላሉ?
እስቲ ስለ ሁኔታው አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ‘ወደ መሬት እንደሚመለሱ’ እንዲሁም ‘ዕቅዳቸው እንዳልነበር እንደሚሆን’ ይናገራል። (መዝሙር 146:4) ሳኦልም ሆነ ሳሙኤል አምላክ ከሙታን ሳቢዎች ጋር መገናኘትን እንደሚያወግዝ ያውቃሉ። እንዲያውም ሳኦል ከዚያ ቀደም መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች ከምድሪቱ እንዲጠፉ አድርጎ ነበር።—ዘሌዋውያን 19:31
እስቲ ጉዳዩን ለማገናዘብ ሞክር። ታማኝ የሆነው ሳሙኤል መንፈስ ሆኖ የሚኖር ቢሆን ኖሮ የአምላክን ሕግ ጥሶ በሙታን ሳቢ በኩል ከሳኦል ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ ይሆን ነበር? ይሖዋ ለሳኦል መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም። ታዲያ አንዲት ሙታን ሳቢ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ በሞተው ሳሙኤል በኩል ሳኦልን እንዲያናግረው ማስገደድ ትችላለች? በፍጹም። ተነሳ የተባለው ይህ ሳሙኤል የአምላክ ታማኝ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ የሞተውን ሳሙኤል መስሎ የቀረበው አንድ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም አጋንንት ነው።
ከግንቦት 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 30–31
“በአምላካችሁ በይሖዋ ራሳችሁን አበርቱ”
ይሖዋን በመፍራት ደስተኛ ሁን!
12 ዳዊት ይሖዋን መፍራቱ የረዳው ከክፉ ድርጊት እንዲርቅ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ችግሮች ሲያጋጥሙት ቆራጥ አቋም እንዲወስድና ችግሩን በጥበብ እንዲወጣ ብርታት ሰጥቶታል። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከሳኦል ሸሽተው ጺቅላግ በተባለች የፍልስጥኤማውያን ከተማ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀምጠው ነበር። (1 ሳሙኤል 27:5-7) አንድ ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በነበረበት ወቅት አማሌቃውያን ከተማይቱን በመውረር ካቃጠሏት በኋላ ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ከብቶቻቸውን ማርከው ወሰዱ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ከተማዋ መጥተው የሆነውን ሁሉ ሲመለከቱ እጅግ አለቀሱ። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች መሪር ሐዘን ወደ ቁጣ ተለወጠና ዳዊትን ሊወግሩት ተማከሩ። ዳዊት በሁኔታው እጅግ ቢጨነቅም ተስፋ አልቆረጠም። (ምሳሌ 24:10) አምላካዊ ፍርሃት ያለው መሆኑ ወደ አምላክ እንዲመለከትና ‘በእግዚአብሔር እንዲበረታ’ አስችሎታል። በኋላም ዳዊትና ሰዎቹ በአምላክ እርዳታ አማሌቃውያን ላይ ተከታትለው በመድረስ የተወሰደባቸውን ሁሉ ማስመለስ ችለዋል።—1 ሳሙኤል 30:1-20
ይሖዋ መዳን እንድናገኝ ይጠብቀናል
14 ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ አስጨናቂ ነገሮች ደርሰውበታል። (1 ሳሙ. 30:3-6) በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ሐሳቦች ይሖዋ ስሜቱን እንደተረዳለት ይገልጻሉ። (መዝሙር 34:18ን እና 56:8ን አንብብ።) አምላክ የእኛንም ስሜት ቢሆን ይረዳልናል። ‘ልባችን’ ወይም ‘መንፈሳችን’ ሲሰበር እሱ ወደ እኛ ይቀርባል። ይህን ማወቁ በራሱ ልክ እንደ ዳዊት እኛንም ሊያጽናናን ይችላል፤ ዳዊት “በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 31:7) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጭንቀታችንን ከመረዳት ያለፈ ነገር ያደርግልናል። ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት እንድንጸና ያደርገናል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
30:23, 24፦ ዳዊት ዘኍልቍ 31:27ን መሠረት በማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ረዳት ሆነው የሚሠሩትንም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ያሳያል። እንግዲያው የምናደርገውን ሁሉ ‘ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምናደርገው ቆጥረን በሙሉ ልባችን እናድርገው።’—ቆላስይስ 3:23
ከግንቦት 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 1–3
‘ቀስት’ ከተባለው ሙሾ ምን እንማራለን?
በእናንተ ላይ ሥልጣን የተሰጣቸውን አክብሩ
9 ዳዊት እንግልት በደረሰበት ወቅት ተጨንቆ ነበርን? “ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታል” ሲል ወደ ይሖዋ ጮዃል። (መዝሙር 54:3) እንዲህ በማለት የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል:- “አምላኬ ሆይ፣ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ . . . ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ፤ አቤቱ፣ በበደሌም አይደለም፣ በኃጢአቴም አይደለም። ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፣ ተቀበለኝ፣ እይም።” (መዝሙር 59:1-4) አንተም ልክ እንደዚሁ በሥልጣን ላይ ያለ ሰው ባደረሰብህ መከራ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? ዳዊት ለሳኦል የነበረው አክብሮት አልቀነሰም። ሳኦል በሞተበት ወቅት ዳዊት በደስታ ከመፈንጠዝ ይልቅ የሚከተለውን ሙሾ አውጥቷል:- “ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ . . . ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ፣ . . . ለሳኦል አልቅሱለት።” (2 ሳሙኤል 1:23, 24) ዳዊት ምንም እንኳ ሳኦል አግባብ ያልሆነ ድርጊት የፈጸመበት ቢሆንም ይሖዋ ለቀባው ሰው ልባዊ አክብሮት በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ትቷል!
ክህደት ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ የምልክቱ ገጽታ!
8 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስለሆኑ በርካታ ሰዎችም ይናገራል። እስቲ ከእነዚህ ውስጥ ከሁለቱ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመልከት፤ የመጀመሪያው ምሳሌያችን ለዳዊት ታማኝ መሆኑን ያስመሠከረው ዮናታን ነው። የንጉሥ ሳኦል የበኩር ልጅ የሆነው ዮናታን የአባቱን ዙፋን በመውረስ የእስራኤል ገዥ የመሆን አጋጣሚ ነበረው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ዮናታንን ሳይሆን ዳዊትን ነበር። በዚህ ጊዜ ዮናታን የይሖዋን ውሳኔ አክብሯል። በመሆኑም ዳዊትን እንደተቀናቃኝ በመቁጠር በእሱ ላይ ቂም ከመያዝ ይልቅ ነፍሱ “ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች”፤ እንዲሁም ለእሱ ታማኝ ለመሆን ቃል ገባ። ሌላው ቀርቶ ልብሱን፣ ሰይፉን፣ ቀስቱንና መታጠቂያውን በመስጠት ንጉሥ መሆን የሚገባው ዳዊት መሆኑን አሳይቷል። (1 ሳሙ. 18:1-4) ዮናታን ዳዊትን ‘ለማበረታታት’ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፤ የገዛ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ በሳኦል ፊት ለዳዊት ጥብቅና እስከ መቆም ደርሷል። ዮናታን ለዳዊት ያለውን ታማኝነት ሲገልጽ “በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ” ብሏል። (1 ሳሙ. 20:30-34፤ 23:16, 17) በእርግጥም ዮናታን ሲሞት ዳዊት ሐዘኑንና ለእሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ የሐዘን እንጉርጉሮ ማሰማቱ ምንም አያስገርምም።—2 ሳሙ. 1:17, 26
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 369 አን. 2
ወንድም
“ወንድም” የሚለው ቃል በጋራ ዓላማ ወይም በተመሳሳይ ግብ የተሳሰሩ ሰዎችን ለመግለጽም ያገለግላል። ለምሳሌ ያህል፣ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ንጉሥ ሰለሞንን “ወንድሜ” ብሎ ጠርቶታል፤ ይህን ያደረገው እኩል ሥልጣንና ማዕረግ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተ መቅደሱ ሳንቃዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማቅረብ ለጋራ ዓላማ ስለተሰለፉም ጭምር ሊሆን ይችላል። (1ነገ 9:13፤ 5:1-12) ዳዊት “እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” በማለት መጻፉ በሥጋ ወንድማማቾች መካከል ሰላምና አንድነት እንዲኖር የሚያደርገው የሥጋ ዝምድናቸው ብቻ እንዳልሆነ ያመለክታል። (መዝ 133:1) ደግሞም ዳዊት ዮናታንን “ወንድሜ” ብሎ የጠራው ከአንድ ወላጅ ስለተወለዱ ሳይሆን እርስ በርስ ስለሚዋደዱና የጋራ ዓላማ ስላላቸው ነው። (2ሳሙ 1:26) ተመሳሳይ ባሕርይና ዝንባሌ ያላቸው ጓደኛሞች ባሕርያቸው መጥፎ ቢሆንም እንኳ እንደ ወንድማማች መጠራታቸው ተገቢ ነው።—ምሳሌ 18:9
ከግንቦት 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 4–6
“ይሖዋ እንዳያዝንባችሁ ጤናማ ፍርሃት ይኑራችሁ”
የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
6:1-7፦ ዳዊት ታቦቱን በሠረገላ ለማምጣት ሙከራ ያደረገው በቅን ልቦና ተነሳስቶ ቢሆንም ድርጊቱ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ችግር አስከትሏል። (ዘፀአት 25:13, 14፤ ዘኁልቁ 4:15, 19፤ 7:7-9) ዖዛም ቢሆን እጁን ዘርግቶ ታቦቱን መያዙ በቅንነት የሚደረጉ ነገሮችም እንኳ የአምላክን መመሪያዎች እንደማይለውጡት ያሳያል።
ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው
20 ዖዛ ሕጉን ከማንም በተሻለ ሁኔታ ማወቅ እንደነበረበት መዘንጋት የለብንም። ታቦቱ የይሖዋን መገኘት ይወክል ነበር። ሕጉ፣ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ታቦቱን መንካት እንደሌለባቸው ያዛል፤ መመሪያውን የጣሱ ሰዎች ደግሞ በሞት እንደሚቀጡ በግልጽ ያስጠነቅቃል። (ዘኁልቁ 4:18-20፤ 7:89) ስለዚህ ታቦቱን ወደ ሌላ ቦታ ማጓጓዝ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ሥራ አይደለም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዖዛ ካህን ባይሆንም እንኳ ሌዋዊ ስለነበረ ሕጉን እንዲያውቅ ይጠበቅበት ነበር። በተጨማሪም ከበርካታ ዓመታት በፊት ታቦቱ በአስተማማኝ ቦታ እንዲቀመጥ ተብሎ ወደ አባቱ ቤት መጥቷል። (1 ሳሙኤል 6:20 እስከ 7:1) ዳዊት ከዚያ ለመውሰድ እስከወሰነበት ጊዜ ድረስ ለ70 ዓመታት ገደማ እዚያው ቆይቷል። በመሆኑም ዖዛ ከልጅነቱ አንስቶ ታቦቱን በተመለከተ ያለውን ሕግ ሳያውቅ አይቀርም።
ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክል የሆነውን ነው
21 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይሖዋ ልብን ማንበብ ይችላል። የአምላክ ቃል የዖዛ ድርጊት ‘በድፍረት የተደረገ’ መሆኑን ስለሚገልጽ ይሖዋ በዘገባው ላይ በግልጽ ያልሰፈረ አንድ ዓይነት የራስ ወዳድነት ስሜት አይቶበት ሊሆን ይችላል። ምናልባት ዖዛ ገደቡን የማያውቅ ትዕቢተኛ ሰው ይሆን? (ምሳሌ 11:2) አባቱ ቤት ተቀምጦ የነበረውን ታቦት በሕዝብ ፊት እየመራ መውሰዱ እንዲኩራራ አድርጎት ይሆን? (ምሳሌ 8:13) ዖዛ ከነበረው እምነት ማነስ የተነሳ ይሖዋ የእርሱን መገኘት የሚወክለውን ታቦት እንዳይወድቅ ለማድረግ ክንዱ አጭር እንደሆነ ተሰምቶት ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ትክክለኛ እርምጃ እንደወሰደ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ይሖዋ ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ያደረገው በዖዛ ልብ ውስጥ አንድ ያየው ነገር ቢኖር ነው።—ምሳሌ 21:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ሸክማችሁን ምን ጊዜም በይሖዋ ላይ ጣሉ
ዳዊት፣ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ ተጠያቂ ነበር። እርሱ ያሳየው ስሜት ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ያላቸው ሰዎችም እንኳ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት አልፎ አልፎ መጥፎ ነገር ሊሠሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል። በመጀመሪያ ዳዊት በጣም ተናደደ። ከዚያም ፈራ። (2 ሳሙኤል 6:8, 9) ከይሖዋ ጋር የነበረው አስተማማኝ ግንኙነት ክፉኛ ተፈተነ። በዚህ ወቅት የይሖዋን ትእዛዛት ስላላከበረ ሸክሙን በይሖዋ ላይ አልጣለም ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ይደርስብን ይሆን? የእርሱን መመሪያዎች ሳንከተል በመቅረታችን በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ይሖዋን እንወቅሰዋለንን?—ምሳሌ 19:3
ከግንቦት 30–ሰኔ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 7–8
“ይሖዋ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ”
“መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”
ዳዊት ለአምላክ ቤት ለመሥራት ከልቡ ተነሳስቶ ያቀረበው ጥያቄ ይሖዋን አስደሰተው። አምላክ፣ ዳዊት የዚህን ያህል ለእሱ ያደረ መሆኑን በማየትና አስቀድሞ ያስነገረውን ትንቢት ግምት ውስጥ በማስገባት በዳዊት የንግሥና መስመር የሚመጣ ሰው እንደሚያስነሳና ይህ ሰው ለዘላለም እንደሚነግሥ ቃል ገባለት። ነቢዩ ናታን አምላክ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።” (ቁጥር 16) ታዲያ በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት የዳዊት ዙፋን ወራሽ የሚሆነውና ለዘላለም የሚገዛው ማን ነው?—መዝሙር 89:20, 29, 34-36
“መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”
የናዝሬቱ ኢየሱስ ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣ ነበር። አንድ መልአክ ስለ ኢየሱስ መወለድ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:32, 33) በዚህ መንገድ ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜውን አገኘ። ኢየሱስ የሚገዛው በሰዎች ተመርጦ ሳይሆን አምላክ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በመሆኑ ለዘላለም የመግዛት መብት አለው። አምላክ የሚሰጠው ተስፋ ደግሞ ምንጊዜም ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እናስታውስ።—ኢሳይያስ 55:10, 11
በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ
14 የዳዊትን ቃል ኪዳን ይኸውም ይሖዋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት የገባለትን ቃል እንመልከት። (2 ሳሙኤል 7:12, 16ን አንብብ።) ይሖዋ ከዳዊት ጋር ይህን ቃል ኪዳን ያደረገው ዳዊት በኢየሩሳሌም ንጉሥ በነበረበት ወቅት ሲሆን መሲሑ በእሱ ዘር በኩል እንደሚመጣ ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 1:30-33) በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ዘሩ የሚመጣበትን መስመር ይበልጥ ግልጽ አደረገ፤ በተጨማሪም የዳዊት ወራሽ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ለመሆን “የሚገባው ባለ መብት” ይሆናል። (ሕዝ. 21:25-27) በኢየሱስ አማካኝነት የዳዊት ንግሥና “ለዘላለም የጸና ይሆናል።” በእርግጥም የዳዊት ዘር “ለዘላለም፣ ዙፋኑም . . . እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል።” (መዝ. 89:34-37) አዎን፣ የመሲሑ አገዛዝ መቼም ቢሆን ምግባረ ብልሹ አይሆንም፤ ያከናወናቸው ነገሮችም ቢሆኑ ዘላለማዊ ይሆናሉ!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 206 አን. 2
የመጨረሻዎቹ ቀናት
የበለዓም ትንቢት። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ነቢዩ በለዓም ለሞዓብ ንጉሥ ለባላቅ እንዲህ አለው፦ “መጥተህ በቀኖቹ መጨረሻ ይህ ሕዝብ [እስራኤል] በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን ልንገርህ። . . . ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል፤ በትረ መንግሥትም ከእስራኤል ይነሳል። የሞዓብን ግንባር፣ የሁከት ልጆችንም ሁሉ ራስ ቅል ይፈረካክሳል።” (ዘኁ 24:14-17 ግርጌ) በዚህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ ላይ ‘ኮከቡ’ የሚያመለክተው ሞዓባውያንን ድል ያደረገውን ንጉሥ ዳዊትን ነው። (2ሳሙ 8:2) በመሆኑም በዚህ ትንቢት ፍጻሜ ላይ ‘የቀኖቹ መጨረሻ’ የጀመረው ዳዊት ንጉሥ ሲሆን እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ዳዊት ለመሲሐዊው ንጉሥ ለኢየሱስ ጥላ ስለሆነ ይህ ትንቢት ኢየሱስ ጠላቶቹን ድል በሚያደርግበት ጊዜም ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢሳ 9:7፤ መዝ 2:8, 9
ከሰኔ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 9–10
“ዳዊት ታማኝ ፍቅር አሳይቷል”
ደስታ ማግኘት ትችላለህ
ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለድኾች የሚያስብ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው፤ እርሱንም እግዚአብሔር በክፉ ቀን ይታደገዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል፤ በምድርም ላይ ይባርከዋል።” (መዝሙር 41:1, 2) ዳዊት፣ የወዳጁ የዮናታን ልጅ ለነበረውና ሽባ ለሆነው ለሜምፊቦስቴ ያሳየው ፍቅራዊ አሳቢነት የተለያየ ችግር ላለባቸው ሰዎች ሊኖረን በሚገባው አመለካከት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።—2 ሳሙኤል 9:1-13
የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:1, 6, 7፦ ዳዊት ቃሉን ጠብቋል። እኛም ቃላችንን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
የሥጋ መውጊያቸውን ተቋቁመው ኖረዋል
10 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ዳዊት ለዮናታን ከነበረው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ለሜምፊቦስቴ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቶታል። ዳዊት የሳኦልን ንብረት በጠቅላላ መለሰለትና ሲባ የተባለ የሳኦል አገልጋይ መሬቱን እንዲያርስለት ዝግጅት አደረገ። በተጨማሪም ዳዊት ለሜምፊቦስቴ “ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው።” (2 ሳሙኤል 9:6-10) ዳዊት ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ሜምፊቦስቴን እንዳጽናናውና የደረሰበት ጉዳት ያስከተለበትን ሥቃይ በተወሰነ ደረጃ እንዳቀለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! እኛም ከሥጋ መውጊያ ጋር እየታገሉ ላሉት ደግነት ማሳየት ይገባናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 266
ጢም
እስራኤላውያንን ጨምሮ በብዙዎቹ የጥንት ምሥራቃውያን ዘንድ ጢም የወንድነት ክብር መገለጫ ተደርጎ ይታይ ነበር። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ጆሮ ግንዳቸው አካባቢ ያለውን ፀጉር እና የጢማቸውን ዳር ዳር እንዳይላጩ ይከለክል ነበር። (ዘሌ 19:27፤ 21:5) ይህ የሆነው እንዲህ ማድረግ የአረማውያን ሃይማኖታዊ ልማድ ስለነበር እንደሆነ ጥያቄ የለውም።
ከሰኔ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 11–12
“መጥፎ ምኞት እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱ”
ከሰይጣን ወጥመዶች ማምለጥ ትችላላችሁ!
10 ይሖዋ ለንጉሥ ዳዊት ብዙ ነገሮች ሰጥቶት ነበር፤ ሀብት፣ ንግሥና እንዲሁም በጠላቶቹ ላይ ድል ሰጥቶታል። ዳዊትም የአምላክን ስጦታዎች ‘ዘርዝሮ ሊጨርሳቸው እንደማይችል’ በአመስጋኝነት ተናግሮ ነበር። (መዝ. 40:5) በአንድ ወቅት ግን ዳዊት ስግብግብነት ስላደረበት ይሖዋ ከሰጠው ተጨማሪ ነገር ፈለገ። ዳዊት ብዙ ሚስቶች የነበሩት ቢሆንም የሌላ ሰው ሚስት ተመኘ። ዳዊት የተመኘው የሂታዊው የኦርዮ ሚስት የሆነችውን ቤርሳቤህን ነው። ዳዊት በራስ ወዳድነት ስለተሸነፈ ከቤርሳቤህ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ምንዝር መፈጸሙ ሳያንስ ኦርዮ እንዲገደል አደረገ። (2 ሳሙ. 11:2-15) ዳዊት እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋል? ይሖዋ የማያየው መስሎት ነው? በአንድ ወቅት ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳዊት ለራስ ወዳድነትና ለስግብግብነት እጅ በመስጠቱ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ደስ የሚለው ግን ዳዊት ከጊዜ በኋላ ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ገብቷል። የይሖዋን ሞገስ መልሶ በማግኘቱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—2 ሳሙ. 12:7-13
ለይሖዋ በፈቃደኝነት ተገዙ
15 ይሖዋ ዳዊትን የቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የመላው እስራኤል ብሔር ራስ አድርጎ ሾሞታል። ዳዊት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ይህን ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም ከባድ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። (2 ሳሙ. 11:14, 15) ሆኖም የተሰጠውን ተግሣጽ በመቀበል ለይሖዋ እንደሚገዛ አሳይቷል። በጸሎት አማካኝነት የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ተናግሯል። እንዲሁም ይሖዋ የሰጠውን ምክር ለመታዘዝ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። (መዝ. 51:1-4) ከዚህም በተጨማሪ ትሑት በመሆን ከወንዶች ብቻ ሳይሆን ከሴቶችም ጭምር ምክር ተቀብሏል። (1 ሳሙ. 19:11,12፤ 25:32, 33) ዳዊት ከስህተቱ የተማረ ሲሆን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት መርቷል።
የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም ሕሊናችሁን አሠልጥኑ
7 ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን አካሄድ ለማወቅ፣ የአምላክን ሕጎች መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳችን ሕይወት ማየት አያስፈልገንም። በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ከሠሩት ስህተት መማር እንችላለን። ምሳሌ 1:5 “ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል” ይላል። ከሁሉ የተሻለ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከአምላክ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን እውነተኛ ታሪኮች ስናነብና ስናሰላስልባቸው ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዳዊት የይሖዋን ትእዛዝ በመጣስ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር መፈጸሙ ከፍተኛ ሥቃይ አስከትሎበታል። (2 ሳሙ. 12:7-14) ይህን ዘገባ ስናነብ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እንችላለን፦ ‘ዳዊት እንዲህ ዓይነት መዘዝ ውስጥ ላለመግባት ምን ማድረግ ይችል ነበር? እኔስ እንደ ዳዊት ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ምን አደርጋለሁ? እንደ ዳዊት ኃጢአት እፈጽማለሁ ወይስ እንደ ዮሴፍ እሸሻለሁ?’ (ዘፍ. 39:11-15) ኃጢአት በሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች ላይ ማሰላሰላችን ‘ክፉ የሆነውን ለመጥላት’ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘አባታችሁ መሐሪ ነው’
11 ዳዊትና ቤርሳቤህ ይደርስባቸው የነበረው የሞት ፍርድ ከመሻሩ በፊት ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸው ይገባ ነበር። እስራኤላውያን ፈራጆች ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን አልነበራቸውም። በመሆኑም የዳዊትን ጉዳይ እንዲያዩት ተፈቅዶላቸው ቢሆን ኖሮ የሞት ፍርድ ከማስተላለፍ በቀር ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም ነበር። ሕጉ ይህን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር። ይሁንና ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ግምት ውስጥ በማስገባት ኃጢአቱን ይቅር ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ይገኝ እንደሆነ ለማየት ወሰነ። (2 ሳሙኤል 7:12-16) በመሆኑም “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነውና ‘ልብን የሚመረምረው’ ይሖዋ አምላክ ጉዳዩን ራሱ ለማየት መርጧል። (ዘፍጥረት 18:25፤ 1 ዜና መዋዕል 29:17) አምላክ የዳዊትን ልብ በትክክል ማንበብና እውነተኛ ንስሐ መግባቱን መገምገም ችሎ ነበር። በመሆኑም ኃጢአቱን ይቅር ብሎለታል።
የይሖዋ ይቅር ባይነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
9 ይሖዋ፣ ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ካስከተለበት አስከፊ መዘዝ ነፃ እንዲሆን አላደረገም። ንጉሡ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ድርጊቱ ያስከተለው መዘዝ አልተለየውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ዳዊት ያሳየውን የንስሐ ዝንባሌ ማለትም የነበረውን ‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ በመመልከት ይቅር ብሎታል። (መዝሙር 32:5ን አንብብ፤ መዝ. 51:17) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የአንድን ሰው ትክክለኛ ዝንባሌና ኃጢአት እንዲፈጽም ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ይረዳል። ይሖዋ፣ በሙሴ ሕግ መሠረት ሰብዓዊ ዳኞች ምንዝር በፈጸሙት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት እንዲያስፈጽሙ ከማድረግ ይልቅ በምሕረት ተነሳስቶ በዳዊትና በቤርሳቤህ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ራሱ ውሳኔ ሰጥቷል። (ዘሌ. 20:10) እንዲያውም አምላክ ከእነሱ አብራክ የተገኘው ሰለሞን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን አድርጓል።—1 ዜና 22:9, 10
10 ይሖዋ ዳዊትን ይቅር እንዲለው ያነሳሳው ሌላው ምክንያት ዳዊት ለሳኦል ምሕረት ማሳየቱ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 24:4-7) ኢየሱስ፣ ይሖዋ እኛን የሚይዘን ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ እንደሆነ ተናግሯል። ደግሞም “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል” ብሏል። (ማቴ. 7:1, 2) ይሖዋ እንደ ምንዝርና ሰው መግደል የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን ብንፈጽም እንኳ ይቅር ሊለን እንደሚችል ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሁንና ይሖዋ ይህን የሚያደርገው የይቅር ባይነት መንፈስ ካለን፣ ለእሱ ኃጢአታችንን ከተናዘዝንና መጥፎ ድርጊታችንን እርግፍ አድርገን መተዋችንን ካሳየን ብቻ ነው። ኃጢአተኞች ከልባቸው ንስሐ ከገቡ ‘ከይሖዋ ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላቸዋል።’—የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።
ከሰኔ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 13–14
“የአምኖን ራስ ወዳድነት ያስከተለው መዘዝ”
it-1 32
አቢሴሎም
የአምኖን መገደል። የአቢሴሎም እህት ትዕማር ውብ በመሆኗ የአባቱ ልጅ የሆነው ታላቅ ወንድሙ አምኖን ከእሷ ፍቅር ያዘው። አምኖን የታመመ በመምሰል ትዕማር ወደ ቤቱ መጥታ ምግብ እንድታበስል ለማድረግ አሴረ፤ ከዚያም አስገድዶ ደፈራት። የአምኖን ፆታዊ ፍቅር ወደ ጥላቻ ስለተቀየረ ትዕማርን ወደ ውጭ አስወጣት። ትዕማር ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴቶች ልጆች የሚለብሱትን ያጌጠ ልብሷን ቀዳና በራሷ ላይ አመድ ነስንሳ ሳለች አቢሴሎም አገኛት። አቢሴሎም ወዲያውኑ አምኖን ያደረገባትን ተረዳ፤ ይህም ወንድሙ ለትዕማር የነበረውን ስሜት አስቀድሞ ያውቅ እንደነበር ያሳያል። ሆኖም አቢሴሎም አምኖንን እንዳትከሰው ለእህቱ ነገራት፤ እንዲሁም በቤቱ እንድትኖር ወሰዳት።—2ሳሙ 13:1-20
ራስን የመግዛት ባሕርይን አዳብሩ
11 መጽሐፍ ቅዱስ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ራሳቸውን መግዛት ስላቃታቸው ሰዎች የሚናገሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ይዟል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው የደረሰባቸውን አስከፊ መዘዝም ይናገራል። እንደ ኪም ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥመው ማንኛውም ሰው በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሰው ሞኝ ወጣት ስላጋጠመው ችግር ማሰላሰሉ ይጠቅመዋል። አምኖን የፈጸመው ድርጊት ባስከተለው አሳዛኝ ውጤትም ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (2 ሳሙ. 13:1, 2, 10-15, 28-32) ወላጆች ከላይ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ በመወያየት ልጆቻቸው ከፍቅር ግንኙነት ጋር በተያያዘ ራሳቸውን የመግዛት ባሕርይ እንዲያዳብሩና ጥበበኛ እንዲሆኑ መርዳት ይችላሉ።
it-1 33 አን. 1
አቢሴሎም
ሁለት ዓመት አለፈ። አስደሳች ወቅት የሆነው በጎች የሚሸለቱበት ጊዜ ደረሰ፤ አቢሴሎምም ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ሰሜን ምሥራቅ 22 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በበዓልሃጾር ድግስ አዘጋጅቶ ዳዊትንና የንጉሡን ልጆች ጋበዛቸው። አባቱ ለመሄድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲነግረው አቢሴሎም በእሱ ምትክ የበኩር ልጁን አምኖንን እንዲልከው ለመነው። (ምሳሌ 10:18) በድግሱ ወቅት አምኖን “የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው” አቢሴሎም አገልጋዮቹን እንዲገድሉት አዘዛቸው። ሌሎቹ የንጉሡ ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ አቢሴሎም ደግሞ ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በገሹር መንግሥት ወዳለው ወደ ሶሪያዊ አያቱ ሸሸ። (2ሳሙ 13:23-38) ነቢዩ ናታን በትንቢት የተናገረለት “ሰይፍ” በዚህ መልኩ ወደ ዳዊት “ቤት” ገባ፤ እስከ ሕይወቱ መጨረሻም ሰይፉ እዚያው ቆይቷል።—2ሳሙ 12:10
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
g 2/05 8-9
የላቀ ግምት የሚሰጠው የውበት ዓይነት
ለማነጻጸር ያህል ከዳዊት ወንድ ልጆች አንዱ የነበረውን አቤሴሎምን እንውሰድ። የሚያስቀና መልክ የነበረው ቢሆንም የማይፈለግ ሰው ሆኖ ተገኝቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር “መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም።” (2 ሳሙኤል 14:25) ይሁን እንጂ አቤሴሎም የነበረው የሥልጣን ጥም በገዛ አባቱ ላይ እስከ ማመጽና ዙፋኑን እስከ መቀማት አደረሰው። እንዲያውም የአባቱን ቁባቶች እስከ መድፈር ደርሷል። በዚህም የተነሣ አምላክ ስለተቆጣ አቤሴሎም አሰቃቂ ሞት ሊሞት ችሏል።—2 ሳሙኤል 15:10-14፤ 16:13-22፤ 17:14፤ 18:9, 15
አቤሴሎምን ትወደዋለህ? እንደማትወደው የተረጋገጠ ነው። በአጠቃላይ የሚጠላ ሰው ነው። የቁመናውና የመልኩ ማማር ከጥፋት ሊያድነውም ሆነ ዕብሪተኝነቱንና ከሃዲነቱን ሊያካክስለት አልቻለም። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አካላዊ ቁንጅናቸውም ሆነ ስለ ቁመናቸው ምንም ስላልተባለላቸው ጥበበኛ የሆኑና የሚወደዱ ሰዎች ይናገራል። ትልቅ ዋጋ የተሰጠው ለውስጣዊው ውበት እንደሆነ ግልጽ ነው።
ከሰኔ 27–ሐምሌ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ሳሙኤል 15–17
“አቢሴሎም በኩራት ተነሳስቶ ዓመፀ”
it-1 860
ፈር ቀዳጅ
በምሥራቃውያን ልማድ መሠረት ከንጉሡ ሠረገላ ፊት ፊት በመሮጥ ለንጉሡ መንገድ የሚያዘጋጁ፣ የንጉሡን መምጣት የሚያውጁና በሌሎች መንገዶች የሚያገለግሉት ሯጮች ነበሩ። (1ሳሙ 8:11) አቢሴሎም እና አዶንያስ ይህን ልማድ በመኮረጅ ዓመፃቸው ክብር እንዲኖረው ለማድረግና ተቀባይነት ያለው ለማስመሰል ከሠረገላቸው ፊት ፊት የሚሮጡ 50 ሰዎችን አዘጋጅተው ነበር።— 2ሳሙ 15:1፤ 1ነገ 1:5፤ ሯጮች የሚለውን ተመልከት።
የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ
5 መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደሩ የበርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ ልንጠቅሳቸው ከምንችላቸው ሰዎች አንዱ የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎም ነው። አቤሴሎም እጅግ ውብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን እንደ ሰይጣን የሥልጣን ጥም ስላደረበት ለእሱ የማይገባውን የአባቱን ዙፋን ለመንጠቅ ፈለገ። በመሆኑም አቤሴሎም ይህን ሥልጣን ለማግኘት ሲል ለወገኖቹ ከልብ የሚያስብ መስሎ ይቀርብ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ንጉሡ በትክክል እንደማይፈርድላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ በአሽሙር ይናገር ነበር። ዲያብሎስ በኤደን ገነት እንዳደረገው ሁሉ አቤሴሎምም በአንድ በኩል ተቆርቋሪ መስሎ ቢቀርብም በሌላ በኩል ግን በገዛ አባቱ ላይ የጭካኔ ድርጊት እየፈጸመ ነበር።—2 ሳሙ. 15:1-5
it-1 1083-1084
ኬብሮን
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ወደ ኬብሮን በመመለስ የአባቱን ንግሥና ለመቀማት ያልተሳካ ሙከራ አደረገ። (2ሳሙ 15:7-10) አቢሴሎም ዙፋኑን ለመቀማት የሚያደርገውን ሙከራ ለመጀመር ይቺን ከተማ የመረጠው ኬብሮን በአንድ ወቅት የይሁዳ መዲና የነበረች ታሪካዊ ከተማ በመሆኗ እንዲሁም የተወለደባት ከተማ በመሆኗ ሳይሆን አይቀርም። የዳዊት የልጅ ልጅ የሆነው ሮብዓም ከጊዜ በኋላ ኬብሮንን መልሶ ገንብቷታል። (2ዜና 11:5-10) ባቢሎናውያን ይሁዳን ካጠፏትና ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከግዞት ከተመለሱት አይሁዳውያን መካከል አንዳንዶቹ በኬብሮን (በቂርያትአርባ) መኖር ጀምረዋል።—ነህ 11:25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የተሟላ መረጃ አለህ?
11 አንዳንድ ጊዜ፣ ሰዎች ስለ እኛ ያልተሟላ መረጃ በማሰራጨታቸው ምክንያት ኢፍትሐዊ ድርጊት ይፈጸምብን ይሆናል። ሜፊቦስቴ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ንጉሥ ዳዊት፣ ለሜፊቦስቴ ደግነት ያሳየው ሲሆን የአያቱን የሳኦልን መሬት በሙሉ መልሶለት ነበር። (2 ሳሙ. 9:6, 7) ሆኖም ዳዊት በአንድ ወቅት ስለ ሜፊቦስቴ መጥፎ ወሬ ሰማ። ዳዊት ወሬውን ሳያጣራ የሜፊቦስቴ ንብረት በሙሉ እንዲወሰድበት ወሰነ። (2 ሳሙ. 16:1-4) ዳዊት ሜፊቦስቴን ካነጋገረው በኋላ ግን መሳሳቱን ተገነዘበ፤ በዚህ ጊዜ ለሜፊቦስቴ የንብረቱ ግማሽ እንዲመለስለት አደረገ። (2 ሳሙ. 19:24-29) ዳዊት ባልተሟላ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በችኮላ ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ረጋ ብሎ እውነታውን ለማወቅ ጥረት ቢያደርግ ኖሮ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት አይፈጽምም ነበር።