የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
ከኅዳር 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 5-6
“ከእነሱ ጋር ካሉት ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ”
it-1 716 አን. 4
ኤልሳዕ
እስራኤል ከሶርያ ጥቃት ተረፈ። በእስራኤሉ ንጉሥ በኢዮራም የግዛት ዘመን ሶርያ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር አሰበች። ኤልሳዕ ሶርያውያን የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር ለንጉሥ ኢዮራም ይነግረው ስለነበር የዳግማዊ ቤንሃዳድ ሙከራዎች በተደጋጋሚ ከሸፉ። መጀመሪያ ላይ ቤንሃዳድ ከመካከላቸው ከሃዲ እንዳለ ተሰምቶት ነበር። የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ሲያውቅ ግን ወደ ዶታን ሠራዊት ልኮ ኤልሳዕን ለመያዝ ከተማዋን በፈረሶችና በጦር ሰረገሎች አስከበባት። (ሥዕል፣ ጥራዝ 1 ገጽ 950) የኤልሳዕ አገልጋይ በፍርሃት ተዋጠ፤ ሆኖም ኤልሳዕ የአገልጋዩን ዓይኖች እንዲከፍትለት ወደ አምላክ ሲጸልይ “እነሆ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራማውን አካባቢ ሞልተውት ነበር።” ሶርያውያኑ ሲቃረቡ ኤልሳዕ “እባክህ፣ ይህን ሕዝብ አሳውረው” በማለት ከቀድሞው ተቃራኒ የሆነ ተአምር እንዲፈጸም ጸለየ። ኤልሳዕ ሶርያውያኑን “እኔን ተከተሉኝ” አላቸው፤ ሆኖም እጃቸውን ይዞ መምራት ያላስፈለገው መሆኑ የታወረው ዓይናቸው ሳይሆን አእምሯቸው እንደሆነ ይጠቁማል። ሊወስዱት የመጡትን ኤልሳዕን አላወቁትም፤ ወዴት እየወሰዳቸው እንዳለም አላስተዋሉም።—2ነገ 6:8-19
ኤልሳዕ የእሳት ሠረገሎችን አይቷል—አንተስ ይታዩሃል?
ኤልሳዕ በዶታይን በጠላት ቢከበብም አልተደናገጠም። ለምን? በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ነው። እኛም ይህን የመሰለ እምነት ያስፈልገናል። እንግዲያው እምነትን ጨምሮ ሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማሳየት እንድንችል አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን እንጸልይ።—ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23
የይሖዋ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች
የሶርያ ወታደሮች ኤልሳዕን ለመያዝ ሲሞክሩ ኤልሳዕ ‘እባክህ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች አሳውራቸው’ በማለት ጸለየ። በዚህ ጊዜ ዓይናቸው ማየት ቢችልም እንኳ የት እንዳሉ ግራ ገባቸው። ኤልሳዕ ወታደሮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘የመጣችሁት ወደተሳሳተ ቦታ ነው። ተከተሉኝና ወደምትፈልጉት ሰው እወስዳችኋለሁ።’ እነሱም ኤልሳዕን ተከትለው የእስራኤል ንጉሥ እስከሚኖርባት እስከ ሰማርያ ድረስ ሄዱ።
ሶርያውያኑ የት እንዳሉ የገባቸው ሰማርያ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነበር። የእስራኤል ንጉሥም ‘ልግደላቸው?’ በማለት ኤልሳዕን ጠየቀው። ኤልሳዕ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሊጎዱት ሞክረው የነበሩትን ሰዎች ይበቀል ይሆን? በፍጹም። ኤልሳዕ እንዲህ አለ፦ ‘አትግደላቸው። የሚበሉት ምግብ ስጣቸውና አሰናብታቸው።’ ስለዚህ ንጉሡ ትልቅ ድግስ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ሄዱ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
5:15, 16—ኤልሳዕ የንዕማንን ስጦታ ያልተቀበለው ለምንድን ነው? ኤልሳዕ ስጦታውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበረው ተዓምሩን የፈጸመው በራሱ ችሎታ ሳይሆን በይሖዋ ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ ስለነበር ነው። ኤልሳዕ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ለራሱ መጠቀሚያ የማድረግ ሐሳብ አልነበረውም። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የይሖዋን አገልግሎት የግል ጥቅም ማግኛ ለማድረግ አይሞክሩም። ኢየሱስ “በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ” ሲል የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 10:8
ከኅዳር 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 7-8
“ይሖዋ ያልተጠበቀውን ፈጸመ”
it-1 716-717
ኤልሳዕ
ይሁንና ከጊዜ በኋላ ዳግማዊ ቤንሃዳድ የተወሰኑ ወራሪ ቡድኖችን ከመላክ ይልቅ ሠራዊቱን በሙሉ ሰብስቦ ሰማርያን ከበበ። ከበባው በጣም አስጨናቂ ከመሆኑ የተነሳ ቢያንስ አንዲት ሴት የገዛ ልጇን እንደበላች ለንጉሡ ተነግሮታል። “የነፍሰ ገዳይ ልጅ” ተብሎ የተጠራው የአክዓብ ልጅ ንጉሥ ኢዮራም ኤልሳዕን እንደሚገድለው ማለ። ሆኖም በችኮላ የገባውን ይህን መሐላ አልፈጸመም። ኢዮራም፣ ከሚተማመንበት የጦር መኮንን ጋር የነቢዩ ቤት ሲደርስ የይሖዋን እርዳታ እንደሚያገኝ ያለው ተስፋ እንደተሟጠጠ ገለጸ። ኤልሳዕ በማግስቱ እህል እንደሚትረፈረፍ ለንጉሡ ነገረው። ንጉሡ የሚተማመንበት የጦር መኮንን ይህን ትንቢት በመጠራጠሩ ኤልሳዕ “ይህን በገዛ ዓይኖችህ ታያለህ፤ ሆኖም ከዚያ ምንም አትቀምስም” አለው። ይሖዋ በሶርያውያን ሰፈር ድምፅ እንዲሰማ ስላደረገ ሶርያውያን የተለያዩ ብሔራትን ያቀፈ ታላቅ ሠራዊት እየመጣባቸው እንደሆነ አሰቡ፤ በመሆኑም ቀለባቸውን በሙሉ ትተው ከጦር ሰፈሩ ሸሹ። ንጉሡ ሶርያውያን እንደሸሹ ሲሰማ የሚተማመንበትን የጦር መኮንን የሰማርያን በር እንዲጠብቅ ሾመው፤ በዚህ ጊዜ የተራቡት እስራኤላውያን የጦር ሰፈሩን ለመበዝበዝ ተሯሩጠው ከከተማዋ ሲወጡ ረጋግጠው ገደሉት። ምግቡን ቢያየውም ከዚያ ምንም አልቀመሰም።—2ነገ 6:24–7:20
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 195 አን. 7
መብራት
በዳዊት የዘር ሐረግ ያሉ ነገሥታት። ይሖዋ አምላክ፣ ንጉሥ ዳዊትን በእስራኤል ዙፋን ላይ አስቀመጠው፤ ዳዊትም በአምላክ አመራር ሥር ለብሔሩ ጥበበኛ መሪና ገዢ ሆኗል። በመሆኑም ‘የእስራኤል መብራት’ ተብሎ ተጠርቷል። (2ሳሙ 21:17) ይሖዋ ከዳዊት ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን በተጋባበት ወቅት “ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል” የሚል ቃል ገብቶለታል። (2ሳሙ 7:11-16) በመሆኑም በልጁ በሰለሞን በኩል የሚሄደው የዳዊት ሥርወ መንግሥት ወይም የገዢዎች መስመር ለእስራኤል እንደ “መብራት” ነበር።—1ነገ 11:36፤ 15:4፤ 2ነገ 8:19፤ 2ዜና 21:7
ከኅዳር 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 9-10
“በድፍረት፣ በቁርጠኝነትና በቅንዓት እርምጃ ወስዷል”
ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል
የእስራኤል ብሔር በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ኢዩ አንድ ተልእኮ ተሰጠው። የሟቹ የአክዓብ ሚስት የሆነችውና በወቅቱ ንጉሥ የነበረው የኢዮራም እናት ኤልዛቤል በአገሪቱ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ታሳድር ነበር። ኤልዛቤል ሕዝቡ ከይሖዋ ይልቅ በኣልን እንዲያመልክ አድርጋ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ነቢያት ገድላለች፤ በተጨማሪም ሕዝቡን ‘በግልሙትናዋና በመተትዋ’ በክላው ነበር። (2 ነገ. 9:22 የ1954 ትርጉም፤ 1 ነገ. 18:4, 13) በመሆኑም ይሖዋ ኢዮራምንና ኤልዛቤልን ጨምሮ የአክዓብ ቤት በሙሉ እንዲጠፋ ወስኖ ነበር። ይህን እርምጃ የማስፈጸም ተልእኮ የተሰጠው ደግሞ ለኢዩ ነበር።
ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል
ኢዩ ወደ እሱ ለተላኩት ሁለት መልእክተኞች ምንም ነገር ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ንጉሥ ኢዮራምና የእሱ አጋር የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ላይ ሆነው ሊገናኙት መጡ። “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ኢዮራም ጠየቀው። ኢዩም በቁጣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና [“ግልሙትናዋና፣” የ1954 ትርጉም] መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ብሎ መለሰለት። ይህ ምላሽ ያስደነገጠው ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ መሸሽ ጀመረ። ይሁንና ኢዩ ከእሱ ይልቅ ፈጣን ስለነበር ቀስቱን አነጣጥሮ በማስፈንጠር ልቡ ላይ ወጋው፤ ንጉሡም በሠረገላው ላይ እንዳለ ሞተ። እንዲሁም አካዝያስ ለማምለጥ ቢሞክርም ኢዩ ተከታትሎ በመድረስ እሱንም ገደለው።—2 ነገ. 9:22-24, 27
ቀጥሎ መጥፋት ያለባት የአክዓብ ቤተሰብ ደግሞ ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ነበረች። ኢዩ ኤልዛቤልን ‘ይህች የተረገመች ሴት’ ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነበር። ኢዩ ኢዝራኤል ሲደርስ ኤልዛቤል ከቤተ መንግሥቱ ሆና ቁልቁል በመስኮት ስትመለከት አያት። ኢዩ ምንም ሐተታ ሳያበዛ ለቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች ኤልዛቤልን ወደ ታች እንዲወረውሯት ትእዛዝ ሰጠ። ከዚያም መላው እስራኤልን ያሳተችውን ይህችን ሴት በፈረሶቹ ረጋገጣት። በተጨማሪም ኢዩ ክፉ ከነበረው ከአክዓብ ቤት የቀሩትን በርካታ ሰዎች ለማጥፋት እርምጃ መውሰዱን ቀጠለ።—2 ነገ. 9:30-34፤ 10:1-14
ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል
ኢዩ ብዙ ደም እንዳፈሰሰ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ቅዱሳን መጻሕፍት ኢዩን የሚገልጹት፣ የእስራኤልን ብሔር ኤልዛቤልና ቤተሰቧ ከሚያሳድሩት ጭቆና ነፃ እንዳወጣ ደፋር ሰው አድርገው ነው። ማንኛውም የእስራኤል መሪ እንዲህ የመሰለውን እርምጃ ለመውሰድ ደፋር፣ ቆራጥና ቀናተኛ መሆን ነበረበት። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ይህ ኃላፊነት ከባድ ስለሆነ ቆራጥ መሆንንና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቅ ነበር። እርምጃው ለዘብ ያለ ቢሆን ኖሮ የበኣል አምልኮን ከእስራኤል ለማጥፋት የተወሰደው እርምጃ አይሳካም ነበር።”
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ኢዩ የነበሩትን አንዳንድ ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ በሚያወግዛቸው ድርጊቶች ላይ ለመካፈል ብንፈተን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከዚህ ድርጊት ለመራቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ብሎም ደፋርና ቀናተኛ መሆን አለብን። ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ለይሖዋ እንደምንቀና ማሳየት ይኖርብናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ኢዩ ንጹሑን አምልኮ ደግፏል
ኢዩ የእስራኤል መንግሥት ከይሁዳ መንግሥት እንደተገነጠለ እንዲቀጥል ከተፈለገ በሃይማኖትም መለየት እንዳለበት ሳይሰማው አልቀረም። በመሆኑም ከእሱ በፊት እንደነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ኢዩም የጥጃ አምልኮን እንዲቀጥል በማድረግ እስራኤልን ከይሁዳ ለመለየት ሞክሯል። ይሁንና ይህ ድርጊት ንጉሥ እንዲሆን በሾመው በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት እንደጠፋ የሚያሳይ ነው።
ኢዩ ‘በአምላክ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስላደረገ’ ይሖዋ አመስግኖታል። ያም ሆኖ “ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም።” (2 ነገ. 10:30, 31) ኢዩ ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ነገሮች አንጻር እንዲህ ማድረጉ ያስገርመን አልፎ ተርፎም ያሳዝነን ይሆናል። ሆኖም ለእኛ ግሩም የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በፍጹም አቅልለን መመልከት የለብንም። የአምላክን ቃል በማጥናት፣ ባነበብነው ነገር ላይ በማሰላሰልና በሰማይ ለሚገኘው አባታችን ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ሆነን መኖር እንችላለን። እንግዲያው የይሖዋን ሕግ በፍጹም ልባችን ለመጠበቅ የተቻለንን ያህል ጥንቃቄ እናድርግ።—1 ቆሮ. 10:12
ከኅዳር 28–ታኅሣሥ 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 11-12
“የሥልጣን ጥመኛ የሆነች ክፉ ሴት ከቅጣት አላመለጠችም”
ዮዳሄ ያሳየው ድፍረት
ኤልዛቤል ጎቶልያ የምትባል ልጅ ነበረቻት፤ ጎቶልያ ልክ እንደ እናቷ ክፉ ነበረች። ጎቶልያ የይሁዳን ንጉሥ አግብታ ነበር። ባሏ ሲሞት ወንድ ልጇ በአባቱ ምትክ መግዛት ጀመረ። ልጇ ሲሞት ግን ጎቶልያ ራሷ ይሁዳን መግዛት ጀመረች። ከዚያም ሌላ ሰው ሥልጣኑን እንዳይወስድባት ስትል የራሷን የልጅ ልጆች ጨምሮ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ በሙሉ ለማስገደል ሞከረች። በዚህም የተነሳ ሰው ሁሉ ይፈራት ነበር።
ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄና ሚስቱ የሆሼባ፣ ጎቶልያ የምታደርገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝበው ነበር። ስለዚህ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ከጎቶልያ የልጅ ልጆች አንዱ የሆነውን ኢዮዓስ የተባለውን ሕፃን ደብቀው ወሰዱት። ከዚያም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አሳደጉት።
ዮዳሄ ያሳየው ድፍረት
ኢዮዓስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ መቶ አለቆቹንና ሌዋውያኑን በሙሉ በመሰብሰብ ‘የቤተ መቅደሱን በሮች ጠብቁ፤ ማንንም እንዳታስገቡ’ አላቸው። ከዚያም ዮዳሄ ኢዮዓስን የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ ሾመው፤ በራሱም ላይ ዘውድ አደረገለት። የይሁዳ ሰዎችም ‘ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!’ ብለው ጮኹ።
ንግሥት ጎቶልያ የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ በፍጥነት ወደ ቤተ መቅደሱ መጣች። አዲሱን ንጉሥ ስታይ ‘ይህ ተንኮል ነው! ተንኮል ነው!’ ብላ ጮኸች። ከዚያም መቶ አለቆቹ ይህችን ክፉ ንግሥት ይዘው አወጧትና ገደሏት። በሕዝቡ ላይ ያሳደረችው መጥፎ ተጽዕኖስ ይወገድ ይሆን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1265-1266
ኢዮዓስ
ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበትና ለኢዮዓስ እንደ አባትና አማካሪ ሆኖ ባገለገለበት ወቅት ወጣቱ ንጉሥ ስኬታማ ሆነ። በ21 ዓመቱ ትዳር የመሠረተ ሲሆን ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ የአንደኛዋ ስም ዮዓዳን ነበር፤ ኢዮዓስ ከእነዚህ ሚስቶቹ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ተቃርቦ የነበረው ወደ መሲሑ የሚመራው የዳዊት የዘር ሐረግ በዚህ መልኩ በድጋሚ አንሰራራ።—2ነገ 12:1-3፤ 2ዜና 24:1-3፤ 25:1
ከታኅሣሥ 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 13-15
“በሙሉ ልብ መሥራት የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል”
ክርስቶስን ሙሉ በሙሉ እየተከተላችሁት ነው?
11 በአምላክ አገልግሎት ቀናተኛ የመሆንን አስፈላጊነት በምሳሌ ለማስረዳት የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በዮአስ ሕይወት ውስጥ የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ዮአስ፣ እስራኤላውያን በሶርያውያን እጅ ይወድቃሉ የሚል ፍርሃት ስላደረበት ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መጥቶ አለቀሰ። ኤልሳዕም በመስኮት በኩል ወደ ሶርያ አቅጣጫ አንድ ቀስት እንዲያስፈነጥር ለዮአስ ነገረው፤ ይህን ማድረጉ በይሖዋ እርዳታ በዚያ ብሔር ላይ ድል እንደሚቀዳጅ የሚያሳይ ነበር። ይህ ንጉሡን በቅንዓት እንዲነሳሳ ሊያደርገው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። ኤልሳዕ ቀጥሎም ቀስቶቹን በመውሰድ መሬቱን እንዲወጋ ለዮአስ ነገረው። ዮአስ ግን መሬቱን ሦስት ጊዜ ብቻ ወግቶ አቆመ። ኤልሳዕ ይህን ሲያይ ተቆጣ፤ ምክንያቱም መሬቱን አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መውጋት ‘ሶርያን ማሸነፍንና ፈጽሞ መደምሰስን’ ያመለክት ነበር። አሁን ግን ዮአስ የሚያሸንፈው ሦስት ጊዜ ብቻ በመሆኑ ድሉ የተሟላ አይሆንም። ዮአስ መሬቱን የወጋው ቅንዓት በጎደለው መንገድ ስለነበር ያገኘው ድል ውስን ሊሆን ችሏል። (2 ነገ. 13:14-19) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ አትረፍርፎ የሚባርከን የሰጠንን ሥራ በሙሉ ልብና በቅንዓት ስንፈጽም ብቻ ነው።
‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ’
ይሖዋ ወሮታ የሚከፍለው ለእነማን ነው? “ከልብ ለሚፈልጉት” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “ከልብ ለሚፈልጉት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ስለ አምላክ ለማወቅ ጥረት ማድረግን ብቻ ሳይሆን እሱን ለማምለክ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድንም ያመለክታል። አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ደግሞ ይህ የግሪክኛ ግስ የገባበት መንገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን እንደሚያመለክት ይገልጻል። አዎን፣ ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ለሚያሳድሩና በዚህም የተነሳ ከልብ በመነጨ ፍቅር እና ቅንዓት ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሰዎች ወሮታ ይከፍላል።—ማቴዎስ 22:37
ታዲያ ይሖዋ፣ በእምነት ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሰዎች ወሮታ የሚከፍላቸው እንዴት ነው? ወደፊት፣ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ የሆነ ሽልማት ይኸውም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው ቃል ገብቷል፤ ይህም ልግስናውና ፍቅሩ ታላቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ራእይ 21:3, 4) ይሖዋን ከልብ የሚፈልጉ ሰዎች አሁንም እንኳ የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ። ቅዱስ መንፈሱ የሚሰጣቸው እርዳታ እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።—መዝሙር 144:15፤ ማቴዎስ 5:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
13:20, 21—ይህ ተአምር እንደ ቅዱስ ተደርገው ለሚታዩ ነገሮች ክብር መስጠት እንዳለብን አያሳይም? በፍጹም አያሳይም። መጽሐፍ ቅዱስ የኤልሳዕ አጽም ክብር ተሰጥቶት እንደነበር አንድም ቦታ ላይ አያመለክትም። ኤልሳዕ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንዳከናወናቸው ሌሎች ተአምራት ሁሉ ይህንንም ያደረገው የአምላክ ኃይል ነው።
ከታኅሣሥ 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 16-17
“የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ አለው”
‘የይሖዋ መንገድ ቅን ነው’
ሰማርያ የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ ነበረች። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ሰማርያ የሚለው ስም የዚህን መንግሥት መላ ግዛት ሊያመለክት ይችላል። (1 ነገሥት 21:1) አሦራዊው ንጉሥ ሰልምናሶር አምስተኛ በ742 ከክርስቶስ ልደት በፊት የሰማርያን ከተማ ከበበ። በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰማርያ ድል ስትሆን በከተማይቱ ይኖሩ ከነበሩት ታላላቅ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ መስጴጦምያና ወደ ሜዶን በግዞት ተወሰዱ። ሰማርያን ድል አድርጎ የያዘው ሰልምናሶር አምስተኛ ይሁን ወራሹ ዳግማዊ ሳርጎን በእርግጠኝነት አይታወቅም። (2 ነገሥት 17:1-6, 22, 23፤ 18:9-12) ይሁን እንጂ የሳርጎን መዝገብ 27,290 እስራኤላውያን በላይኛው ኤፍራጥስና በሜዶን ወደሚገኙ ቦታዎች እንደተጋዙ ያመለክታል።
“እባክህ ወደ ቤትህ መልሰን”
ኤርምያስ ይህን ሐሳብ ሲጽፍ የነበረውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ኤርምያስ ከኖረበት ዘመን ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ማለትም በ740 ዓ.ዓ. ይሖዋ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት በአሦራውያን በግዞት እንዲወሰድ ፈቅዶ ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቡ በዚህ መንገድ እንዲቀጡ የፈቀደው በነቢያቱ በኩል በተደጋጋሚ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት አስጸያፊ ኃጢአቶችን ይፈጽሙ ስለነበር ነው። (2 ነገሥት 17:5-18) ሕዝቡ ከአምላካቸው ጋር መቆራረጣቸውና ከትውልድ አገራቸው ርቀው በግዞት በተወሰዱበት ቦታ የደረሰባቸው መከራ አመለካከታቸውን ቀይሮት ይሆን? ይሖዋስ ጨርሶ ረስቷቸው ይሆን? ወደ ቤቱ ይመልሳቸው ይሆን?
ይሖዋ ታጋሽ አምላክ ነው
10 ሆኖም የአምላክ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው ከታሪክ መረዳት ይቻላል። በ740 ከዘአበ አሦራውያን የአሥሩን ነገዶች የእስራኤል መንግሥት እንዲገለብጡና ሕዝቡን አግዘው እንዲወስዱ አድርጓል። (2 ነገሥት 17:5, 6) በቀጣዩ መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ደግሞ ባቢሎናውያን የሁለቱን ነገዶች የይሁዳ መንግሥት እንዲወርሩና ኢየሩሳሌምን ከነቤተ መቅደሷ እንዲያጠፏት ፈቅዷል።—2 ዜና መዋዕል 36:16-19
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 847
ሳምራዊ
“ሳምራውያን” የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው አሥሩን ነገድ ያቀፈው የሰማርያ መንግሥት በ740 ዓ.ዓ. ድል ከተደረገ በኋላ ነው፤ ቃሉ የተሠራበት የሰሜኑ መንግሥት ድል ከመደረጉ በፊት በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ከጊዜ በኋላ ከሌሎቹ የአሦር ግዛት ክፍሎች ከመጡት የባዕድ አገር ሰዎች ለመለየት ነው። (2ነገ 17:29) አሦራውያን ሁሉንም እስራኤላውያን ከዚያ ያስወጧቸው አይመስልም፤ ምክንያቱም በ2 ዜና መዋዕል 34:6-9 ላይ ያለው ዘገባ (ከ2ነገ 23:19, 20 ጋር አወዳድር) በንጉሥ ኢዮስያስ የግዛት ዘመን በምድሪቱ ላይ የቀሩ እስራኤላውያን እንደነበሩ ይጠቁማል። ከጊዜ በኋላ፣ “ሳምራውያን” የሚለው ስያሜ ሰማርያ ውስጥ የቀሩትን እስራኤላውያንና አሦራውያን ያመጧቸውን ሰዎች ዘሮች ማመልከት ጀመረ። በመሆኑም አንዳንዶቹ በእስራኤላውያንና በባዕድ አገር ሰዎች መካከል በተመሠረተ ጋብቻ የተወለዱ እንደሆኑ ጥያቄ የለውም። ውሎ አድሮ ደግሞ፣ መጠሪያው የዘር ወይም የፖለቲካ ሳይሆን ሃይማኖታዊ አንድምታ ያዘ። “ሳምራዊ” የሚለው ቃል በጥንቷ ሴኬምና ሰማርያ አካባቢ ተስፋፍቶ የነበረው ሃይማኖታዊ ቡድን አባል የሆነን ሰው ያመለክት ነበር፤ የዚህ ቡድን አባላት ከአይሁድ እምነት ፈጽሞ የተለዩ አንዳንድ መሠረተ ትምህርቶችን ይከተሉ ነበር።—ዮሐ 4:9
ከታኅሣሥ 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 18-19
“ተቃዋሚዎቻችን ሊያዳክሙን የሚሞክሩት እንዴት ነው?”
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
18:19-21, 25—ሕዝቅያስ ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ጥምረት ፈጥሮ ነበር? በጭራሽ፤ የአሦር ሠራዊት የጦር አዛዥ የመጣሁት ‘በእግዚአብሔር ፈቃድ’ ነው ብሎ እንደዋሸ ሁሉ ሕዝቅያስ በግብፅ ተመክቷል ማለቱም የሐሰት ውንጀላ ነበር። ታማኙ ንጉሥ ሕዝቅያስ የታመነው በይሖዋ ላይ ብቻ ነበር።
“አትፍራ፤ እረዳሃለሁ”
የሰናክሬም የጦር መሪ በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ ለመዝራት ሲል ተንኮል የተሞላበት ሐሳብ አቀረበ። “አንተ [ሕዝቅያስ] የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን [ደምስሰሃል።] . . . እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዝዞኛል” አለ። (2 ነገ. 18:22, 25 የ1980 ትርጉም) የጦር መሪው ይህን ሲል ይሖዋ በሕዝቡ ስላዘነ ለእነሱ እንደማይዋጋ መግለጹ ነበር። ይሁንና ነገሩ የተገላቢጦሽ ነበር። ይሖዋ በሕዝቅያስና ወደ እውነተኛው አምልኮ በተመለሱት አይሁዳውያን ተደስቶ ነበር።—2 ነገ. 18:3-7
በዛሬው ጊዜ ሰባቱ እረኞችና ስምንቱ አለቆች እነማን ናቸው?
14 የአሦር ንጉሥ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው በለኪሶ ሰፈረ። ከዚህ ቦታ ሦስት መልእክተኞች በመላክ ከተማዋ እጅ እንድትሰጥ መመሪያ አስተላለፈ። ራፋስቂስ የሚል የማዕረግ ስም ያለው የንጉሡ ቃል አቀባይ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። በዕብራይስጥ ቋንቋ በመናገር ሕዝቡ ንጉሡን እንዲከዳና ለአሦራውያን እጅ እንዲሰጥ ለመገፋፋት ሞክሯል፤ ደግሞም የተደላደለ ኑሮ ወደሚኖሩበት ምድር እንደሚያፈልሳቸው በመግለጽ የውሸት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (2 ነገሥት 18:31, 32ን አንብብ።) ከዚያም ራፋስቂስ የተለያዩ ብሔራት አማልክት አምላኪዎቻቸውን ማስጣል እንዳልቻሉ ሁሉ ይሖዋም አይሁዳውያኑን ከአሦራውያን መዳፍ መታደግ እንደማይችል አስረግጦ ተናገረ። ሕዝቡ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ በመውሰድ በሐሰት ወሬና ክስ ለተሞላው ለዚህ ፕሮፓጋንዳ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፤ ዛሬም የይሖዋ አገልጋዮች አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ።—2 ነገሥት 18:35, 36ን አንብብ።
yb74 177 አን. 1
ክፍል 2—ጀርመን
የሚገርመው፣ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን እንደካዱ በሚገልጸው ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ለማድረግ የተንኮል ዘዴዎችን አዘውትረው የሚጠቀሙት የኤስ ኤስ አባላት፣ አንድ ሰው ሰነዱ ላይ ከፈረመ በኋላ ብዙውን ጊዜ ከቀድሞው የበለጠ ሥቃይ ያደርሱበት ነበር። ካርል ኪርሽት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በማጎሪያ ካምፖቹ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎቹ ሰዎች ይበልጥ የተንኮል ሴራ ይሸረብባቸው ነበር። በዚህ መንገድ ሰነዱ ላይ እንዲፈርሙ ማግባባት እንደሚቻል ይታሰብ ነበር። እንድንፈርም በተደጋጋሚ እንጠየቅ ነበር። እርግጥ አንዳንዶች ፈርመዋል፤ ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚለቀቁት ከአንድ ዓመት በላይ ከጠበቁ በኋላ ነው። እስኪለቀቁ ድረስ ባለው ጊዜ የኤስ ኤስ አባላት ግብዞችና ፈሪዎች እያሉ በሕዝብ ፊት ይሳለቁባቸዋል፤ እንዲሁም ከካምፑ ከመለቀቃቸው በፊት በወንድሞቻቸው ፊት እንደ ድል አድራጊ እንዲንጎማለሉ ይገደዱ ነበር።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 155 አን. 4
አርኪኦሎጂ
ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአሦሩ ንጉሥ ሰናክሬም አድራሜሌክና ሳሬጸር በተባሉት ልጆቹ እንደተገደለና ኤሳርሃደን የተባለው ልጁ በእሱ ምትክ እንደነገሠ ይናገራል። (2ነገ 19:36, 37) ሆኖም አንድ የባቢሎናውያን ዜና ታሪክ በቴቤት ወር 20ኛው ቀን መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደና ሰናክሬም በልጁ እንደተገደለ ይገልጻል። በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ባቢሎናዊው ካህን በራሰስ እና በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው የባቢሎን ንጉሥ ናቦኒደስ የተናገሩት ሐሳብም ሰናክሬም በአንደኛው ልጁ ብቻ እንደተገደለ ይጠቁማል። ይሁንና በቅርቡ በተገኘ የኤሳርሃደን ፕሪዝም ስባሪ ላይ፣ ሰናክሬምን ተክቶ የነገሠው ኤሳርሃደን ወንድሞቹ (ብዙ ቁጥር) በአባቱ ላይ ዓምፀው እንደገደሉትና እንደሸሹ በግልጽ ተናግሯል። ፊሊፕ ባይበርፌልድ ዩኒቨርሳል ጁዊሽ ሂስትሪ (1948፣ ጥራዝ I ገጽ 27) በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የባቢሎናውያኑ የዜና ታሪክ፣ ናቦኒድ እንዲሁም በራሰስ ተሳስተዋል፤ ትክክል ሆኖ የተገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ብቻ ነው። የኤሳርሃደን ጽሑፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ የያዘው እያንዳንዱ ዝርዝር መረጃ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል፤ ከዚህ የባቢሎንና የአሦር ታሪክ ጋር በተያያዘ ከባቢሎናዊ ምንጮች ይበልጥ ትክክል ሆኖ ተገኝቷል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የማይስማሙ በዘመኑ የነበሩ ሌሎች ምንጮችን በምንገመግምበት ጊዜ ይህን ከግምት ማስገባታችን በጣም አስፈላጊ ነው።”
ከታኅሣሥ 26–ጥር 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 20-21
“ይሖዋ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳ ጸሎት”
ንጉሡ ያሳየው እምነት ተካሰ
23 ሰናክሬም በይሁዳ ላይ በተነሳበት በመጀመሪያው አጋጣሚ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢሳይያስ እንደሚሞት ነገረው። (ኢሳይያስ 38:1) የ39 ዓመቱ ንጉሥ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፋው። ያሳሰበው የራሱ ደህንነት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ የወደፊት ዕጣም ጭምር ነበር። ኢየሩሳሌምና ይሁዳ የአሦራውያን ወረራ አጥልቶባቸዋል። ሕዝቅያስ ከሞተ ውጊያውን ማን ይመራል? እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሕዝቅያስ ንግሥናውን የሚረከበው ወንድ ልጅ አልነበረውም። ሕዝቅያስ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋ ምሕረት እንዲያሳየው ተማጸነ።—ኢሳይያስ 38:2, 3
ይሖዋን በሙሉ ልብ አገልግሉ!
16 በአንድ ወቅት ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ ጊዜ ወደ ይሖዋ አጥብቆ በመጸለይ በእሱ ፊት እንዴት እንደተመላለሰ እንዲያስታውስ ለመነው። (2 ነገሥት 20:1-3ን አንብብ።) ይሖዋም ጸሎቱን በመስማት ከሕመሙ ፈወሰው። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚጠቁሙት በዚህ ዘመን አምላክ በተአምራዊ መንገድ ይፈውሰናል ወይም ዕድሜያችንን ያራዝምልናል ብለን መጠበቅ አንችልም። ያም ቢሆን እንደ ሕዝቅያስ “እባክህ ይሖዋ ሆይ፣ በታማኝነትና በሙሉ ልብ በፊትህ እንዴት እንደተመላለስኩ . . . እንድታስታውስ አጥብቄ እለምንሃለሁ” ብለን መጸለይ እንችላለን። አንተስ በአልጋ ላይ ተኝተህ ሳለ ይሖዋ ሊደግፍህ እንደሚችልና እንደሚንከባከብህ ትተማመናለህ?—መዝ. 41:3
ጸሎት ሊረዳኝ የሚችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንድ የእምነት ሰዎች ለጸሎታቸው ቀጥተኛ እንዲያውም ተአምራዊ የሆነ መልስ አግኝተዋል። ለምሳሌ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለሞት የሚያደርስ ሕመም እንደያዘው በተገነዘበ ጊዜ አምላክ እንዲያድነው የተማጸነ ሲሆን አምላክም “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ እፈውስሃለሁ” የሚል መልስ ሰጥቶታል። (2 ነገሥት 20:1-6) ሌሎች ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶችም እንዲሁ አምላክ በሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ተመልክተዋል።—1 ሳሙኤል 1:1-20፤ ዳንኤል 10:2-12፤ ሥራ 4:24-31፤ 10:1-7
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 240 አን. 1
ውኃ ልክ
ውኃ ልክ አንድን ሕንፃ በትክክል ለመገንባት እንዲሁም ይፍረስ ወይስ ይቆይ የሚለውን ለመገምገም ያገለግላል። ይሖዋ ‘በሰማርያ ላይ ተጠቅሞበት የነበረውን የመለኪያ ገመድ እንዲሁም በአክዓብ ቤት ላይ ተጠቅሞበት የነበረውን ውኃ ልክ’ በዓመፀኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ እንደሚጠቀም ትንቢት ተናግሯል። አምላክ ሰማርያንና የአክዓብን ቤት ሲለካ ጠማማ ወይም ምግባረ ብልሹ ሆነው አግኝቷቸዋል፤ በመሆኑም ጠፉ። በተመሳሳይም አምላክ ኢየሩሳሌምንና መሪዎቿን የፍርድ ወንበር ላይ በማስቀመጥ ክፋታቸውን ያጋልጣል፤ እንዲሁም ከተማዋን ያጠፋታል። እነዚህ ክንውኖች በ607 ዓ.ዓ. ተፈጽመዋል። (2ነገ 21:10-13፤ 10:11) በኢየሩሳሌም የነበሩት ጉረኛ ሰዎችና የሕዝቡ ገዢዎች ስለሚጠብቃቸው ጥፋትና ይሖዋ ስላስተላለፈው ውሳኔ በኢሳይያስ አማካኝነት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣ ጽድቅንም ውኃ ልክ አደርጋለሁ።” የእውነተኛ ፍትሕና ጽድቅ መሥፈርቶች ትክክለኛዎቹ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑትን ካልሆኑት ይለያሉ፤ በዚህ መሠረት ወይ ይድናሉ አሊያም ይጠፋሉ።—ኢሳ 28:14-19